የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት

የ፳፻፲፯ (2017) ቱ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዕለተ ረቡዕ ግንቦት ፳ / ፳፻፲፯ (ግንቦት 20- 2017) ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ በዚህ ሳምንት በቅዱስ ሲናዶስ የምደባ ውሳኔ መሠረት ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተመደቡባቸው ሐገረ ስብከቶችና የአገልግሎት ክፍሎች እየሄዱ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ፣ የባህርዳር ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በዚህ ሳምንት የእንኳን ደህና መጡ መርሐግብራት ተካሂደዋል፡፡

እኛም ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ሳምንት የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አደረጃጀት በሥርዓተ ሐዋርያት ፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቃለ አዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መነሻነት የምንቃኝ ይሆናል፡፡ አብራችሁን ሁኑ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ጥንታዊና የዳበረ የነገረ ሃይማኖትና የሥርዓተ አምልኮ ታሪክ ቢኖራትም ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ተላቃ ራሷን የቻለችውና አስተዳደራዊ ነጻነትን የተጎናጸፈችው  የዛሬ ፷፮ (ስልሳ ስድስት) ዓመት በ፲፱፻፶፩ (1951) ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ሆነው በተሾሙበት ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ልማድና ሓዋርያዊ ትውፊት በቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራ ሲሆን ይህም ቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚሰበሰቡበት ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያስተላልፍ አካል ሲሆን በዋንኝነትም

፩.  በነገረ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ማለትም በእምነት፣ በቀኖና በትውፊትና በመንፈሳዊ ባህሎች ዙሪያ መልስ የመስጠት፣
፪.  የአጽዋማትና የበዓላትን ጨምሮ በሚነሱ የቀኖና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት፣
፫.  የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር የመምራት፣ ሕጎችን የማውጣት፣ ሐገረ ስብከት የማደራጀት፣ መምሪያዎችና ድርጅቶችን የመክፈትና ሹመቶችን የመስጠትና በቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ  ውሳኔ የመስጠት መብቶች አሉት፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም ጥቅምት ፲፪ (12) ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ባስተማረው በሐዋርያውና ወንጌላዊው ማቴዎስ በዓል ቀንና መንጋውን የመጠበቅ ክህነታዊ አደራ ለሐዋርያት በተሰጠበት በበዓለ ርክበ ካህናት (በትንሳኤ ፳፭/25ኛ ቀን) የሚካሄድ ሲሆን ጉባዔው ሁል ጊዜ የፓትሪያሪኩ መንበር ባለበት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በዋዜማው በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚደረግ ሥርዓተ ጸሎት መክፈቻውን ያደርጋል፡፡

ቅዱስ ፓትሪያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር ማለትም ሰብሳቢ ሲሆኑ በእርግና፣ በጤና ችግር አልያም ለረጅም ጊዜ በመንበራቸው መገኘት በማይችሉበት ጊዜ ወይም አጀንዳው እርሳቸውን የሚመለከት ካልሆነ በስተቀር ያለ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሰብሳቢነት ጉባዔውን ማካሄድ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም በሹመት ቅድምና ካላቸው ሦስት አባቶች መሐል በሚደረግ ምርጫ የሚመረጡት አባት ጉባዔውን የሚሰበስቡ ይሆናሉ፡፡

በጉባዔው ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በተመለከተ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ከምልዓተ ጉባኤው ከግማሽ በላይ ድምጽ አስፈላጊ ሲሆን ለሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የተመለከተ እንደሆነ ሙሉ ድምጽ  ያገኘ ሲሆን ብቻ ውሳኔ ይተላለፍበታል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በነገረ ሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ማድረግ የማይችሉ ሲሆን  ድምጸ ተዓቅቦ አድርጎ የተገኘ አባት ከሲኖዶስ አባልነቱ ይሰረዛል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከመደበኛ ዓመታዊው ጉባዔያቱ ባሻገር እንደ አስፈላጊነቱ አስቸኳይ ጉባዔያትን በቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ በብፁዕ ዋና ጸሐፊ ወይም በቋሚ ሲኖዶስ ጥያቄ እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከግማሽ በላዩ ስብሰባ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜ ሊጠራ ይችላል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሥልጣን ዘመን ዕድሜ ልክ ሲሆን በዕርግናና በጤና ምክንያት ጉባዔያትን መካፈል ካልቻለ ሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ተከብሮለት በማረፊያው የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሃይማኖታዊ ጉዳይ ቢከሰስ በጉባዔው ቀርቦ ራሱን የመከላከል መብት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባልነቱ ይሰረዛል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ሥራውን ለማከናወን ይረዳው ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሚመራ ጽ/ቤት የሚኖረው ሲሆን የዋና ጸሐፊውና የምክትላቸው የሥራ ዘመን ለሦስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን ለተጨማሪ አንድ ዙር በድጋሚ መመረጥ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባሸገር ቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ ብጹዕ ዋና ጸሐፊና ብጹዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በቋሚነት እንዲሁም ሌሎች በየሦስት ወሩ የሚመረጡ ፬ የሲኖዶስ አባላትን የያዘ ቋሚ ሲኖዶስ ሲኖር በሳምንት ሁለት ጊዜ በመሰብሰብ በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪነታቸው ለእርሱ የሆነ ስድስት አካላት ሲኖሩ እነርሱም የሊቃውንት ጉባዔ፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ የሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር ኮሚሽን፣ የቁጥጥርና ምርመራ አገልግሎት፣ የልማትና ክርሥቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንዲሁም የሕጻናትና የቤተሰብ ጉዳዮች መምሪያ ናቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስና የቋሚ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር የሆኑት ቅዱስ ፓትሪያርኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት፣ መሪና ወካይ ሲሆኑ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥማቸው በጸሎት ይታሰባል፡፡ ሙሉ ስማቸው “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዕገሌ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት” ይሆናል ይኸውም
፩.  ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ :-  በኢትዮጵያ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ራስ/ሰብሳቢ መሆናቸውን፣
፪.  ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም :-በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ አንብሮተ ዕድ በቅዱስ ፍሬሚናጦስ የተመሠረተው የአክሱም መንበር ሐዋርያዊ ወራሽ መሆናቸው፣
፫.  ዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት:- በኢትዮጵያዊው ሐዋርያ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር ከ፲፫ (13)ኛው መ.ክ.ዘ. ጀምሮ ከግብጽ ለሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት እንደ ኤጲስ ቆጶስ ያገለገሉት የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌዎች መንፈሳዊ ወራሽ መሆናቸውን ያሳያል።
በብዙዎች ዘንድ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምትለዋ ሃረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበር “የተክለሃይማኖት መንበር ነው” የሚል የተሳሳተ መረዳት ቢኖርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግብጽና ኤርትራ አቻዎቿ ከእስክንድሪያው መነበረ ማርቆስ የተገኘች የመንበሩ ወራሽ ስትሆን  ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚወርሱት የዕጨጌነት ሥልጣኑን ነው፡፡

የቅዱስ ፓትሪያርኩ መቀመጫ በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሲሆን ፓትሪያርኩ ዕምነትና በቀኖና ጥሰት ካልተወገዙ፣ ጥፋታቸው ከታመነበት ወይም የገቡትን ቃል ሲያከብሩ ካልተገኙ በስተቀር በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡ በህመም፣ በዕርግና ሥራቸውን ለመሥራት የማይቻላቸው ሆኖ ሲገኝ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሚሾምላቸው ሲሆን ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራቸውን በማካሔድ ላይ እያሉ እሥራትና ግዞት ቢደርስባቸው ቤተክርስቲኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡

ቅዱስ ፓትሪያርኩ ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፉ አዲስ አባት እስኪመረጥ ድረስ በሹመት ቅድምና ካላቸው ጤነኛ አባቶች መሐል አንዱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ ይሾማሉ የሥራ ዘመናቸው ከዐርባ እስከ ሰማንያ ቀናት ብቻ ይሆናል፡፡ በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀመንበር ሆነው ምርጫውን ያስፈጽማሉ፤ ነገር ግን ዕጩ መሆን አይችሉም፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስና ከቅዱስ ፓትሪያርኩ በመቀጠል የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛው የአስተዳደር አካል በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ የሚመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ፲፯ (17) መምሪያዎች (የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ፣ ውጭጉዳይ መምሪያ፣ የገዳማት መምሪያ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያ እና ሌሎችም) ፣ ፮ (6) ድርጅቶች (ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ፣ ትንሣኤ አሳታሚ፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና ሌሎችም) የሚኖሩ ሲሆን ለተወሰኑ መምሪያዎችና ድርጅቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ይመደብላቸዋል፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተዋረድ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካል ሀገረ ስብከት ነው። ይህም በአንድ ሊቀጳጳስ ወይም ጳጳስ ሥር የሚተዳደር መንፈሳዊ የአስተዳደር ክልል ሲሆን በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከሰባ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐገረ ስብከቶች ሲኖሩ ቁጥራቸው እንደየዘመናቱና ለአስተዳደር እንዳለው ምቹነት ሊጨምርና ሊቀንስ ይችላል፡፡ ሐገረ ሰብከቱ ከሊቀ ጳጳስ/ጳጳስ በተጨማሪ የክህነት ማዕረግ ያለው ሥራ አስኪያጅ የሚመደብለት ሲሆን በውስጡ ልዩ ልዩ ጽ/ቤቶችና የአስተዳደር ጉባዔን ያካትታል፡፡

አንድ ሐገረ ስብከት የሚያስተዳድረው መንፈሳዊ የአስተዳደር ክልል በወረዳ ቤተ ክህነቶች የሚከፋፈል ሲሆን በመጨረሻም አስተዳደራዊው መዋቅር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት / ገዳማት ጋር ይደርሳል፡፡ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያዎች ለሦስት የሚከፈሉ ሲሆን
፩.  ገዳማት፡- የወንዶች፣ የሴቶችንና የአንድነት ገዳማትን የሚያጠቃልል በአበምኔት/እመምኔት የሚመራ ፣
፪.  አድባራት፡ በከተሞችና በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥባቸው በፓትርያርክ ወይም በሊቀጳጳስ የደብርነት ማዕረግ የተሰጣቸው፣ በደብር አለቃ ሰብሳቢነት በሚመራ ሰበካ ጉባዔ የሚተዳደሩ፣
፫.  ገጠር ቤተ ክርስቲያን
፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸምባቸው የደብርነት ማዕረግ ያላገኙ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

በ፳፻፲፯ (2017)ዓ.ም. የተካሄደው የርክበ ካህናት ጉባዔን መነሻ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ቅርጽ በወፍ በረር ለመዳሰስ የሞከርንበት መሰናዶን እዚጋ በመግታት ለሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መልካም የአገልግሎተ ዘመንን እንመኛለን፡፡ ሰናይ ሳምንት።