የሰንበት ት/ቤት ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እንቅስቃሴዎች

ባሳለፍነው ሳምንት እሑድ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ቀን ለ፲፬(14)ኛ ጊዜ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተከብሯል፡፡ ይህን ተከትሎ ቅዳሜ ግንቦት ፴(30)ና እሑድ ሰኔ ፩(1) በአዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ጽዮን አዳራሽ  ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የመንበረ ፓትሪያርክ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባዔ የተደረገ ሲሆን በጉባዔው ላይ ከተለያዩ አሕጉረ ስብከቶች የተወጣጡ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱም በትግበራ ላይ የሚገኘው የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀው የሰ/ት/ቤቶች መዋቅርና ስልታዊ ዕቅድ ዋነኛ አጀንዳ የነበሩ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከነበረው ሁነት ባሻገር በደሴ፣ ወልዲያ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋና በሌሎች የክልል እንዲሁም የውጭ ሃገራት ሀገረ ስብከቶች በዓሉ ምእመናንን በሚያሳትፍ መልኩ በዝማሬ፣ በስብከተ ወንጌልና በልዩ ልዩ መንገዶች አክብረውታል፡፡ ይህን ተከትሎ በዛሬው የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን ስለ ሰንበት ት/ቤት ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እንቅስቃሴዎች በማንሳት አሁናዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እንሞክራለን ሰላም ቆዩን፡፡

የሰንበት ት/ቤት እንቅስቃሴ የቀደሙ አብነቶች ያሉት እንቅስቃሴ ቢሆንም ሰንበት ት/ቤት በሚል ስያሜ የመጣው ግን ከድህረ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በኋላ በ፳(20)ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ መሆኑን ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ምንም እንኳን ሰንበት ት/ቤት በቤተ ክርስቲያን ያለው ታሪክ ከአንድ ምዕት የበለጠ ባይሆን አብነቶቻቸው ግን ጥንታውያን ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን ወጣቶች በረበናት ይማሩባቸው የነበሩ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ናትናኤልን የመሰሉ ሐዋርያት የተገኙባቸው የአይሁድ ትምህርት ቤቶች፣ በሐዲስ ኪዳን በዘመነ ክርስቶስ የሐዋርያት፣ ፴፮(36)ቱ ቅዱሳት አንስት እና ፸፪ (72)አርድዕት አገልግሎት፣ በእስክንድርያና በአንጾኪያ የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስንል ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተስፋፋውን የአብነት ትምህርት እንደ መንፈስ አባቶቻቸው መቁጠር የምንችል ይመስለናል፡፡

ሰንበት ት/ቤቶች በሰንበት ት/ቤት (በእሑድ ት/ቤት) ሥያሜ የተመሠረቱት በድሕረ ተሃድሶ ዘመን በተነሳው ምዕራባዊ የተሃድሶና የመድፍነ ተሃድሶ (የጸረ ተሐድሶ) እንቅስቃሴ አማካኝነት ቢሆንም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርሥቲያን የሰንበት ት/ቤት ቅርጽ በሥርዓተ ዓምልኳዊ ይዘቱ ደረቅ የሳይንስ ትምህርት ይዘት ካለው የምዕራባውያን ሰ/ት/ቤት በእጅጉ የሚለይ አገልግሎት ነው፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ የቀደመ የሰ/ት/ቤት እንቅስቃሴ የምናገኘው በ፲፱፻(ዐሥራ ዘጠኝ መቶ)ዎቹ አካባቢ በተነሳው በሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ ሀቢበ ጊዮርጊስ አማካኝነት መሆኑን የቅዱሱ ዜና መዋዕል ያሳያል፡፡ ቅዱሱ በወቅቱ ከነበሩት ፓትሪያርክ አቡነ ቄርሎስ አምስተኛ ጋር በመተባበር እንደ ናዚር ጋይድ (የኋላው አቡነ ሺኖዳ) ያሉ ወጣቶችን በማሰባሰብ ሥርዓተ ትምሕርት ቀርጾ ሕጻናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች በዘመኑ እየጀመረ ለነበረው ምዕራባዊ ጠባይና የእስልምና ጭቆና የማይበገሩ በሃይማኖት፣ በሥነ ምግባርና በዓለማዊ ዕውቀት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስጠሩ ወጣቶችን ማፍራት ችሏል፡፡

ከዚህ ዘመን ዘግየት ብሎም ቢሆን በፓራሙላው ሊቀጳጳስ ቅዱስ አቡነ ጊዮርጊስ አነሳሽነት የተጀመረው የሕንድ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎትም ሌላው የሚጠቀስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ የማላንካራው ሜትሮፖሊታን የቅዱስ አቡነ ዲዮናስዮስ  ቫታሳሪ ሚና ላቅ ያለ እንደነበር እናገኛለን፡፡

ሌላው በዕድሜ ላቅ ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ነው። በእርግጥ እስከ ሰባዎቹ ድረስ የሰንበት ት/ቤት ስያሜን የያዘ ባይሆንም በተለያዩ አድባራት የተጀመሩ የወጣት ማኅበራት ምሥረታዎች ዕድሜ ወደ ሰባ የሚሻገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከንጉሣዊ ሥርዓት ወደ ኅብረተሰባዊ ሥርዓት ለመሻገር እያጣጣረች ባለችበት ወቅት የውጭ መጻሕፍትን ማንበብና እነሱን መከተል እንደ ስልጣኔ በታየበት ወጣቱ ሃይማኖቱን እንዲሁም ባሕሉን ማጥላላት በጀመረበት የ፲፱፻፶ (1950)ዎቹ ወቅቶች ፍቅር ያገበራቸው መንፈስ ቅዱስ ያነቃቸው ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራትን መመሥረት ጀመሩ፡፡ በደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል የተመሠረተውን የእግዚአብሔር ምስሌነ የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበርን ጨምሮ ቀዳምያኑ የተምሮ ማስተማር (ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም)፣ ማኅበረ ሥላሴና ማኅበረ ክርስቶስ (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል)፣ ምክኻ ለደናግል (ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም) እንዲሁም እንደ ሃይማኖተ አበው (በተሃድሶ ትምህርቶቹ ምክንያት ተወግዘዞ የተለየ) ያሉ ማኅበራት እስከ ሰባዎቹ ድረስ በማኅበርነት ቅርጽ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴን ያከናውኑ ነበር። በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክሕነት ሥር የወጣቶች መምሪያ ተቋቁሞለት ይመራ የነበረ ሲሆን የአገልግሎት  አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርትም በወቅቱ ተዘጋጅቶ እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል፡፡

ዐብዮታዊው መንግስት ከዐብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበርና ሴቶች ማኅበር ውጪ የወጣት ማኅበራትን በመከልከሉ መንፈሳዊ ማኅበራቱ በሌላ ስም መጠራት ግድ ስላላቸው ከአኀት አብያተ ክርስቲያናት ልምድና ከመሰባሰቢያ ቀናቸው በመነሳት ሰንበት ት/ቤት በሚል ሥያሜ ተዋቅረዋል፡፡ በሰንበት ት/ቤት ዕድገት ውስጥ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ደማቅ አስተዋጽዖ ነበራቸው፡፡

ይሕን ታሪክ በምትጋራው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት በራሷ መንበር መመራት ከጀመረች በኋላ ወዲያውኑ ነበር የሰንበት ት/ቤት እንቅስቃሴን የጀመረችው። በተለይም የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ አቡነ ፊሊጶስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በአርመንና በሶርያ የሰንበት ት/ቤት ጅማሮ ከሌሎቹ በተለየ በዲያስጶራው ማኅበረሰብ አማካኝነት የተጀመረ ነው፡፡ በውጭ ያሉ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን የማስተማር ቅርጽ ተከትለው በአሜሪካና በአውሮፓ ትምህርቱን ካስጀመሩ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሃገር ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት ማስገባት ችለዋል፡፡

እንደ ጥቅል በስድስቱም አብያተ ክርስቲያናት የሰንበት ት/ቤቶች በሊቃነ ጳጳሳት በሚመሩ የሰ/ት/ቤት ወይም የወጣቶች መምሪያ ሥር የሚተዳደሩ ሲሆን ከኢትዮጵያና ኤርትራ ውጪ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ያለ በዕድሜና በትምህርት ደረጃ የተከፋፈለ (ከኬጂ እስከ 12) የሰንበት ት/ቤት የሥርዓተ ትምህርት ልምድ ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች በአንጻሩ ለማኅበር ቅርጽ ያደላ የዘመን አከፋፈል (ሕፃናት፣ ታዳጊ ወጣት፣ ጎልማሳ) የሚከተል ሲሆን ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት ሳይኖረው ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፳፻፲፬ ዓ.ም. (2014)ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርቱን በሙከራ እንዲሁም ፳፻፲፮ (2016)ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ሃገሪቱ እንዲተገበር እያደረገች ሲሆን ይሔም ከቅድመ መደበኛ እስከ ፲፪(12)ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በዕድሜያቸውና በግንዛቤያቸው ልክ በየትም ሆነ በየትም ሆነው እንዲማሩ የሚያስችላቸው ነው፡፡ ሥርዓተ ትምሕርቱ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን የመማሪያ መጻሕፍት ኅትመትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለ ወጥ የሰ/ት/ቤት መዋቅር  ሰንበት ት/ቤቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ያደረጋቸው ሲሆን በተለይ የግብጽና የሕንድ ሰንበት ት/ቤቶች አሁን ላይ ለደረሱበት ትልቅ ስምና አቅም እንዲሁም ላፈሯቸው ልጆች በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቦታዎች ትልቅ ቦታ መድረስ ተችሏል፡፡ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያሉ ሰንበት ፣ት/ቤቶቸ ወጥና ተናባቢ ሥርዓትን ስላልገነቡ ከአጥቢያቸው አለፍ ያለ ተሸጋሪ ተጽዕኖ መፍጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህንን አስመልከቶ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤመዋቅርና ሥልታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ በለቱ የቅዱበስ ሲኖዶስ ጉባዔ ያጸደቀ ሲሆን በቀጣ ዓመት ይተገበራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 
ለወደፊት የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሰ/ት/ቤት ልምድ በመጠኑ ለመዳሰስ ቀጠሮ በመያዝ እዚህ ላይ እናብቃ፡፡ በክርስቶስ ሰላም