
የቅድሳት ስዕላት መቀደድ የማይረብሸው ምእመን አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቃጠለ ተብሎ ልቡ በደስታ የሚሞላ አንድም ሰው ማግኘት ይከብደናል። ነገር ግን ይህ ጥቃት በሰው ልጆች ላይ ተሰነዘረ ሲባልስ?
ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዕድምተኞቻችን!
ሰሞኑን በማኅበራዊ መግባቢያ(Media) ሲዘዋወሩ ከነበሩ ዐሳቦች በመነሳት ጾታዊ ጥቃትን በዚህ ሳምንት ርእሰ ጉዳያችን በማድረግ እውን የክርስትና አስተምህሮና ቤተ ክርስቲያን ጾታዊ ጥቃትን ትገፋፋለች ወይ? የሚለውን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ጾዊ ጥቃት ከስሙ በመነሳት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ለመገንዘብ አድካሚ አይደለም፡፡ በዚህ ጥቃት ሰለባ ለመሆን የተጠቂው ጾታ ለጥቃት ተፈላጊ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትን ያለ አድሎ የምታወግዝ በመሆኑ በዕድሜና በጾታ ባትከፋፍለውም በጉዳዩ ዙሪያ ያላት አስተምህሮ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሠረቱን ያደረገና በቅዱሳን አበው ትምህርት የተደገፈ ነው፡፡
የሰው ልጅ ስለመፈጠሩ የሚነግረን ሊቀ ነብያት ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፉ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩን ማንሳቱ ለቤተ ክርስቲያን የነገረ ሰብእና የክብረ ሰብእ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህም ሰው የቅድስት ሥላሴ ክብር የሚገለጽበት ሕያው ስዕለ ሥሉስ ቅዱስ በመሆኑ ሰው ላይ የሚደርስ ጥቃት በፈጣሪው፣ በአስገኚውና በሥዕሉ ባለቤት በሆነው በእግዚአብሔር ላይ እንደተቃጣ ይቆጠራል፡፡
ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ጳውሎስ በቀዳሚው የቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ እንደተወልን የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆኑ በሰዎች ላይ (በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ) የሚፈጸም ጥቃት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እግዚአብሔር የመሠረተውን የሰው ልጆችን የእርስ በእርስ በፍቅርና በአንድነት የመኖር ዕቅድ የሚያዛባና በወንድሞች/እኅቶች መካከል መፈራራትንና መጠራጠርን የሚያነግስ ተግባር መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስታውቁናል፡፡ ጥቃት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጠውን አንድን ነገር የማድረግ ወይም ያለማድረግ ነጻ ፈቃድን የሚነጥቅና በግዳጅ ባርነት ውስጥ የሚከት ተግባር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ትጸየፈዋለች፡፡
ጾታዊ ጥቃት በራሱ ኃጢአት ከመሆኑም ባሻገር ተደራራቢ መተላለፎችን የሚይዝ መሆኑን የዳዊት ልጅ ትዕማርን ባስነወረው የአምኖን ታሪክ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ዝሙት፣ አመንዝራነት፣ መግደልን ጨምሮ በርካታ በሁለቱ ኪዳናት የተሰጡ ትዕዛዞችን የሚተላለፍ ተግባር ነው፡፡
ጥቃት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለተሰጠው ቅዱሱ የትዳር ሕይወትም ጸር ነው፡፡ መምህረ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትዳር ሲናገር በቤተ ክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል ባለ ግንኙነት ይመስለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ወዳና ፈቅዳ እንደምትገዛለት ሚስቶች ለባሎች በፍቅር ሊገዙ እንደሚገባ ሁሉ ባሎች ደግሞ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳትና ለለ እርሷም መከራ መስቀልን እንደታገሰ ሁሉ እነሱም ሚስቶቻቸውን በፍጽም ፍቅር ሊወዱ እንጂ እጃቸውን ሊያነሱ አይገባም፡፡
በዚህ ዙሪያ አስፍተው ካሰተማሩ አባቶች አንዱ የሆነው ታላቁ ቅዱስ ባስሊዮስ ስለ ጠላፊዎች ባስተማረው ትምህርት “ጠለፋ ሕጋዊ ያልሆነ እና አንባገነንነት ነው፡፡” ሲል ይነግረናል። ዳግመኛም “በዚህ ጉዳይ አንድ ዐሳብ ቢኖራችሁ ኖሮ ከሃገራችሁ ይጠፋ ነበር፤ አሁንም ስለ ክርስትና ቅንዓት ስትሉ ተነሱ፤ ልጅቷን ባገኛችኋት ጊዜ ወደ ቤተሰቦቿ መልሷት፤ እርሱን ግን ከጸሎት ለዩት/አግዱት” ሲል ከጾታዊ ጥቃት አንዱ ስለሆነው ስለጠለፋ ሕገ ወጥነት ያስተምራል። ይኸው ቅዱስ በሐዋርያት ቀኖና ላይ “ድንግሊቱን ከክብር ያወረዳት ቢኖር እርሱ ከጉባዔያችሁ ይለይ ሲል አስገድዶ መድፈር ኃጢያት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ አፈ በረከት የተሰኘው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በ፩ኛ ቆሮንቶስ ላይ በጻፈው ፳፮ኛ ማብራሪያ ላይ ደግሞ “በሚስቱ ላይ እጁን የሚያነሳ፣ እንዲህ ያለው ወንድ ሰው ሳይሆን አውሬ ነው።” ሲል ያስተምራል፡፡
የቤተ ክርስቲያን የጾታዊ ጥቃት ምልከታም ከላይ ያሉ አስተምህሮቶችን መሠረት ያደረገና እንኳን ምንም ያልበደለንን ሰው፣ እንበድል ዘንድ ይቅርና የበደሉንን ሳይቀር ይቅር እንል ዘንድ በታዘዝነው “የክፉውን በክፉ አትመልሱ!” አስተምህሮ የተቃኘ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህን ባለማወቅ እንዲሁም በእኛ በምእመናን ግዴለሽነትና ወንድማችንን/እኅታችንን የመጠበቅ ሰብዓዊ ግዴታችን በተግባር አለማሳየታችንን በመመልከት ቤተ ክርስቲያን ጾታዊ ጥቃትን እንደምታስፋፋ እንዲሁም አድሎአዊት እንደሆነች አድርገው ሲከሱ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ከአስተምህሮ ባሻገር በተቋም ደረጃ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ሥር ክፍል አደራጅታ ከካሕናት ጀምሮ አስከ ምእመናን ድረስ በማስተማር የግንዛቤ ለውጥ እንዲስፋፋ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን እንደ ፌሚኒዝም ያሉ አንድ ጾታ ላይ መሠረት ያደረጉ የመፍትሔ እንቅስቃሴዎችን ባትደግፍም በኃጢአት ምክንያት በምድር ላይ የሰፈነው መጠፋፋትና መጨካከን ክርስቶስን ማዕከል በማድረግና የክርስቶስን ልብ ገንዘብ በማድረግ እንደሚፈታ ታምናለች፡፡ በዚህም አምላክን የመምሰል /ሱታፌ አምላክ መንገድ የሰው ልጅ እንኳን ለሌላው አምሳያው ይቅርና ለፍጥረት ሁሉ የሚራራ፣ ራሱን የሚገዛ፣ የተረጋጋ ሰብዕ ስለሚሆን በዚህ መንገድ በምድር ያሉ ችግሮችና ኢፍትሐዊነቶች እንደሚፈቱ ታስተምራለች፡፡ ለዚህም ነው የሱታፌ አምላክ በር የሆነውን የንሥሐ ጥሪ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ዕለት ዕለት ስታዘክር የምትኖረው፡፡

