
ሰላም ውድ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ ተከታታዮች! ጣዕመ ዓለም አንገሽግሷቸው ፍቅረ እግዚአብሔር ናፍቋቸው ከእርሱ ጋር ለመኖር ድምጸ አራዊትን ፀብዐ አጋንንትን ታግሰው ለመኖር የቆረጡ መነኮሳት፣ እንደ አባ እንጦስ በገዳም በምንኩስና፤ እንደ አባ ጳውሊ በብሕትውና ለመወሰን ከዓለም ይኮበልላሉ፡፡ የብዙኃኑ መነኮሳት መሪ ጥቅሳቸው “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያገኝ ነፍሱን ግን ባያተርፍ ምን ይረባዋል?” የምትለው አምላካዊ ቃል በመሆኗ ከዓለም ሲለዩ ከዓለም አንድም ነገርን መያዝ አይፈልጉም፡፡
ይህ ሥርዓተ ምንኩስና አስቀድሞ በአዳም ሰባተኛ ትውልድ ሄኖክ በኋላም የአብርሐምን መስዋዕት በተቀበለው በአምሳለ ክርስቶስ ካሕኑ መልከ ጼዴቅ፣ ከነቢያት ወገን ከሆነው ከነቢዩ ኤልያስ እንዲሁም በተኻራሚው ሰባኪ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወት ውስጥ ተገልጧል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው ዐርባ ቀንና ሌሊት ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ባርኮታል፡፡ ይህ ሕይወት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በክርስቲያኖች ዘንድም የሚታወቅ ሲሆን ይበልጡኑ ሥርዓት ሠርቶለት መልክ አበጃጅቶለት ያጸናው ግን የገዳመ አስቄጥሱ እንጦንስ እንደሆነ ቅዱስ አትናቴዎስ በመጽሐፈ ገነት ላይ ያሰፈረው የቅዱሱ ዜና መዋዕል ያሳያል፡፡፡
ይህ በላዕላይ ግብጽ የተጀመረውና በኋላም በመላው ዓለም የተስፋፋው የገዳም ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያም የገባው ከእንጦንስ ፭(5)ኛ የቆብ ልጅ በሆኑትና ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ ነው፡፡ ይህ የገዳም ሥርዓት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በሃገራችን የሰሜኑ ክፍል የተስፋፋ ሲሆን በኋላም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ወደ ምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ ሊስፋፋ እንደቻለ ታሪክ ያስረዳናል፡፡
በዚህ ሳምንት በገዳመ ዝቋላ በጽንፈኛ ታጣቂዎች የደረሰውን ጥቃት መሠረት በማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወደዚህ እየተደጋገመ የመጣውን ገዳም ተኮር ጥቃቶች ለመመልከት እና መፍትሄዎችን ለማመላከት እንሞክራለን፡፡
ቀኑ ሰኔ ፲፫/፳፻፲፯ (ሰኔ 3-2017) ዓ.ም. አመሻሹ ላይ ነበር፣ የታጠቁና መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት በኅብረት ከሚኖሩበት በዓት ራቅ ብለው ዘግተው ወደሚኖሩ አባቶች በዓት የሄዱት፡፡ በዚህ ገዳም ባለፈው ዓመት አራት መነኮሳትን በሰማዕትነት እንዳሳረፏቸው ዛሬም አስቀድመው ለዓለም የሞቱትን በሥጋ በመግደል መነኮሳቱን ለማመናመንና ያሉትን በፍርሃት ለመበተን ነበር ወደ መናንያኑ የተጠጉት፡፡ በዚህ መሳሪያ የለም፣ በዚህ ተዉ የሚላቸው አካል የለም፡፡ በቅርብ በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት መውጣትን ተከትሎ ነበር ወደ ሥፍራው ያቀኑት፡፡
ምስኪኖቹንና ደካማዎቹን መነኮሳት ለማጥቃት ሰይፍና ሥለት ታጥቀው ወደ ገዳሙ የመናንያን ዋሻ ደረሱ፡፡ ቀታልያኑ ከአንድ አባት በስተቀር እንዳሰቡት ብዙ አባቶችን ማግኘት አልቻሉም፡፡ የተገኙት አባት አባ ኃይለ ሚካኤል ነበሩ፡፡ አባ ኃይለ ሚካኤል በማኅበረ ሥላሴ፣ በዲሙ በረሃና በደብረ ሊባኖስ የነበራቸውን ተጋድሎ ፈጽመው ነበር ማረፊያቸው እንድትሆን ወደ መረጧት ዝቋላ የመጡት፡፡ በገዳሙ በበርካታ ልዩ ልዩ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው የዛሬ ፲፪ (12) ዓመት ነበር በገዳሙ ፈቃድ ወደ ዋሻው በመሄድ በብህትውና ያሳለፉት፡፡ ታጣቂዎች ባህታዊውን ዐይተው ማለፍ አልፈለጉም ነበርና ገደሏቸው፡፡ ክብርት ሥጋቸው አምና በግፍ በነዚሁ እጅ ከተገደሉት መነኮሳት ጋር ሲያርፍ ነፍሳቸው ወደ መነኑለትና ዓለምን ወደረሱለት አምላካቸው ዘንድ ተጓዘች፡፡
የገዳሙ መነኮሳት “የታጣቂዎች ፍላጎት አንድ ነው፤ እሱም ገዳሙን ማጥፋት ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እንደሚደረጉበት ገልጸዋል፡፡ ለቅርብ ጊዜ ዜናዎች ሩቅ ላልሆነ ሰው ይህ ዓይነቱ መከራ ለዝቋላ ብቻ የተሰጠ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ ዋልድባ፣ አሰቦት፣ ማኅበረ ሥላሴ፣ ደብረ ሊባኖስ ያሉ ታላላቅ ገዳማትን ጨምሮ በርካታ ገዳማት ከወቅታዊ ሃገራዊ የእርስ በዕርስ ጦርነቶች ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቃቱ ዓላማ ተደርገዋል፡፡ የተፋላሚ ወገኖች በገዳማቱ ከመጠለል አልፎ፣ ዘረፋ፣ መነኮሳቱን ማንጓጠጥ፣ መግደል፣ ማስፈራራትን መፈጸም የተለመደ ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ገዳማት የቀደመ መፈራታቸውና መሰማታቸው ቀርቷል፡፡ ይልቁንም በዓለም ትተውት የመጡት ጎጠኝነትና ቡድንተኝነት፣ ሃብት እና ሥልጣን ለማግኘት የሚደረጉ ሹኩቻዎች መካሄጃ ሥፍራ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
ለገዳማት መደፈር የመጀመሪያ ምክንያት በሀገሪቱ የሚገኘው የፌደራሉ መንግስትና የክልል መንግስታት ለነዚህ ለዜጎች የሥነ መግባር ትምህርት፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር በውስጣቸው በያዙት ቅርስ ምክንያት ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ አስተዋጽዖ ላላቸው ገዳማት ተገቢውን የጥበቃና የደኅንነት ሽፋን መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ገዳማት የግል ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
በዓለውያን መካከል ያለደኅንነት ሽፋን የሚኖሩት የግብጽ፣ የሶሪያና የኢየሩሳሌም ገዳማት ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ገዳማቱ እንደ ኢትዮጵያ ገዳማት ክፍት ሳይሆኑ ጥብቅና ዙሪያቸውን የታጠሩ ናቸው፡፡ ምንም ያሕል ሰፊ ቢሆኑም ገዳማታቸው በመታጠራቸው ከአላስፈላጊ የሰውና የሀራዊት ትንኮሳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሕጋዊ መታወቂያ የሌለው የትኛውም መነኮስ ይሁን ቱሪስት ወደ ገዳማቸው ዝር እንዲል አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህም ቢሆን የመጣበትን ምክንያት የማስረዳትና ጎጂ ቁሶችን አለመያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ገዳማውያኑ ሳይረበሹ ልባቸውን ጥለው በፍጹም ጸጥታ ወደ እግዚአብሔር እንዲያተኩሩና ተጋድሏቸውን እንዲያጠነክሩ ይረዳቸዋል፡፡ በእነዚህ ከላይ ባነሳናቸው ሃገራት ያሉ ገዳማት ከአድባራት አንጻር ዝቅ ያለ የጥቃት ተጋላጭነት ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ሌላው ገዳማት በምጣኔ ሀብት ራሳቸውን የሚችሉና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ድጋፎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ የላዕላይ ግብጽ እንዲሁም የኢትዮጵያው ምዕራፈ ቅዱሳን ተከዜ ገዳም ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ገዳማት በያዟቸው መሬቶች የተለያዩ የግብርና፣ የዕደ ጥበብ ምርቶችን እያቀረቡ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በዚህም ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ላቅ ያለ በመሆኑ ከመንግስት ተገቢውን ትኩረት ከማግኘታቸውም ባለፈ ለአካባቢው ምእመናን የሥራ ዕድልን ስለሚያመጣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በእኔነት እንዲጠብቃቸው ያስችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር እንደ ትምህርትና ጤና ባሉ መስኮች ላይ መሳተፍም ከኅበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው በማስቻል ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጪ ባሉ ነዋሪዎች ሳይቀር እንዲከበሩ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
እግዚአብሔር መነኮሳትንና መነኮሳይያትን፤ ገዳማቸውንና ባዕታቸውን ይጠብቅልን፡፡ ቸር እንሰንብት

