ወርኃ ሰኔ እና የተማሪዎች ምርቃት

ወርኃ ሰኔ ሲመጣ ከሚስተዋሉ ሀገራዊ ክስተቶች መሃል አንዱ የተማሪዎች ምረቃ ነው። ከፊደል ጋር ያላቸው ትወውቅ ሰምሮ “እደጉ፣ ተመንደጉ፣ ለትልቁ ምረቃ ያብቃችሁ” ተብለው ከሚመረቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሕፃናት ጀምሮ ለዓመታት በለፉበት የትምህርት ዘርፍ “በቅታችኋል፤ ሂዱና አንፀባርቁ” እስከተባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ድረስ  በጥቁር ቀሚስና መነሳንስ ደምቀው የትምህርት ደረጃና ዓይነቱን በሚገልጡ ኅብረ ቀለማት ባላቸው ሪባን ተውበው በየተቋማቱና በየመንገዱ ይታያሉ።

የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዓምድም  የምድብ ተራውን ጠብቆ በሳምንቱ ዕለተ ዐርብ ተመልሷል። ለዚህ ሳምንት ያደረሰን አማኑኤል ይመስገን፣ እያልን በዚህ ሳምንት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታዊና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን  ማስመረቃቸውን ተከትሎ በቤተክርስቲያን የምሩቃን ሱታፌን ለማሰስ ተሰናድተናል። መልካም ቆይታ።

የአስኳላ ትምህርት ወደ ሃገራችን ብቅ ከማለቱ በፊት እንደ ትምህርት ሚንስቴር ሆና ትውልዱን የማስተማር ሸክምን የተሸከመችው ቤተክርስቲያን በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የዘመናዊ ትምህርት “ሀሁ” ሲጀመር ነበር ከምዕራብ በተቀዳ ትምህርት በሰከሩ ልጆቿ እንደ አላስፈላጊ ነገር መገፋት የጀመረችው።

ኦርቶዶክስ ክርስትና ኋላ ቀርነት በአንፃሩ ምዕራባውያኑ የካቶሊክ እና የወንጌላውያን እምነቶች ዘመናዊነት ተደርገው መሳል ጀመሩ። ከኢትዮጵያና ከቤተክርስቲያን ጋር የተገናኙ ነገሮች ሀሉ ተነወሩ። መምህር ዐሥራት የኔ ሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” በሚለው መጽሐፍ እንደገለፁት የተማረው ትውልድ የብብቱን ጥሎ የቆጡን ማሰስ ጀመረ።

በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትና ሱታፌ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮች በ”ዘመናዊ ትምህርት ያስፈልጋልና አያስፈልግም” በሚሉ ፅንፎች መሃል የሚደረግ እሰጥ አገባ ሆነ። በኋላ ላይ ሁለቱን የሚያስታርቁ እንደ ዶ/ር እጓለ ብርሃን ያሉ በቤተክርስቲያን ትምህርት የታነፁ በዓለም ትምህርት የዳበሩ ልሂቃን ወደ መድረኩ በመምጣት ሁለቱን የማስማማት ዐሳብን ማንሳታቸው ለሁለቱ ዘርፎች እፎይታን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡

በዚህ የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮ ላይ ምንም እንኳን የተካረረ አተካሮ በቤተክህነት ልሂቃንና በ”ምሁራን” መሐል ቢደረግም ቤተክርስቲያን ለዘመናዊ ትምህርት ያበረከተችው አስተዋጽዖም አናሳ አይደለም። ትምህርት ቀርፃ ግብረ ገብን በመስጠት ተማሪው ሥነምግባር ያለው ዜጋ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የእስክንድርያና የአርመን ቤተክርስቲያን ልጆች ወደ ሃገር መጥተው ማስተማራቸው የሚጠቀስ አበርክቶ ነው። በከተማ እስከ ቅርብ ዘመን ከቅድመ አንደኛ ትምህርት በፊት የሚሰጠው የፊደልና የቁጥር ትምህርት ሥርዓትም (በተለምዶ ቄስ ትምህርት ቤት) የሚዘለል አስተዋጽዖ አይደለም።

የዘውዳዊ ሥርዓቱ ወደ መውደቅ ካዘነበለበት ወቅት ጀምሮ ደግሞ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ኅብረተሰባዊነት /ኮሚዩኒዝም ዐስተሳሰብ እየተሳበ ሃይማኖት ጠልነት እየተጫነው በመምጣቱ ትምህርት፣ የሚጠረጠር እና የሚብጠረጠር እንክርዳዱ ጎልቶ መታየት ጀመረ። “የተማሩ” የተባሉት ሰዎች ፓትርያርክ እስከ መግደል፣ ጳጳሳት እስከ ማባረር፣ ካህናትን እስከመስደብና ቤተክርስቲያንን እስከማንቋሸሽ በደረሱበት በዚያን ወቅት ዓለም ከቤተክርስቲያን የተስማማችላቸው ወጣቶች ከየአካባቢው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። በተለያዩ ከተሞች በማኅበራት እየተሰባሰቡ  ለቤተክርስቲያን ዘብ በመቆም በርካታ ሥራዎችን መሥራት ችለዋል። በኋላም ከእነዚህ ማኀበራት አብዛኛዎቹ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤትነት ተለውጠዋል።

በቤተክርስቲያንና በዓለሙ ትምህርት በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከለወጡ ቀዳምያን መካከል የወሊሶው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዲዮስቆርስና የዝዋዩ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ብፁዓን አባቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ኮሌጆችና ዩንቨርስቲዎች የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በማሰባሰብ ያስተምሩ ነበር በኋላም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረቱን ያደረገው ማኅበረ ቅዱሳን እንዲወለድ ሆነ፡፡ የማኅበሩ መከሰት በርካቶች በዓለማዊው ትምህርት ሰበብ ከቤተ ክርስቲያን እንዳይርቁ እንደውም ይበልጥ እንዲቀርቧት፣ እንዲያይዋትና እንዲወዷት መንገድ የከፈተ ነበር፡፡ ማኅበሩ ወደ አርባ በተጠጋው ዕድሜው በርካታ ቁጥር ያላቸውን ካሕናት፣ መምህራንና ዘማርያንን ከማፍራት ባሻገር ቤተ ክርስቲያን ግድ የምትላቸው ከሚንስትር ጀምሮ በተለያየ የኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ለቤተ ክርስቲያን የማደክሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ መስነፍን የማያውቁ በልዩ ልዩ ዘርፍ የሚሳተፉ ተመራማሪዎች፣ ባለሞያዎችን እንዲወጡ በማድረግ ሀገራችን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬዎች ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ይህ የማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ከተመረቁ በኋላ ኦርቶዶክሳውያን ምሩቃንን የመጠበቅና ወደ አገልግሎት የማሰማራት ልማድ ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት አንጻር ዝቅተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የህንድና የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሚያደራጇቸው የሞያ ማኅበራት አማካኝነት የምሩቃንን ዓለማዊ ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም በሚጠቅም መልኩ ያደራጁታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማድ በኢትዮጵያ ስንመጣ ግን አነስተኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድና በማኅበረ ቅዱሳን ከተደራጁ የሞያ አገልግሎቶችና የሠራተኛ ጉባዔያት ባሻገር በራስ ተነሳሽነት ከተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህክምና ማኅበርና በ፳፻፲፭ ዓ.ም. ከነበረው ሕገ ወጥ ሹመት ማግስት ብቅ ብሎ ከነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሕግ ባለሞያዎች ኅብረት ውጪ ያሉ ጎልተው የወጡ ሞያዊ ማኅበራት ውስን ናቸው፡፡

በዓለማዊ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁና በሥራ ላይ የተሰማሩ የቤተክርስቲያን ልጆች በሞያቸው አይተኬ ሚና እንደሚኖራቸው የማይካድ ነው፤ በተለይም:
•  በሕግና ዲፕሎማሲ፣
•  በምጣኔ ሀብትና የሀብት አጠቃቀም፣
•  በቴክኖሎጂና በዲጂታል ተልእኮ፣
•  በትምህርትና ሥልጠና፣
•  በጥበበ-ዕድ እና ምርታማነት፣
•  በጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት፣
•  በጥናትና ምርምር እንዲሁም በመሳሰሉት ቤተ ክርስቲያንን መራዳት እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ በይበልጥ ደግሞ አሁን ላይ ቤተ ክርስቲያን እየተቸገረችባቸው የሚገኙትን፣
•   ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው ባላቸው ውስን አቅም የተወሰኑ ምርቶችን እያመረቱ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት ከእርዳታ ተላቀው ራሳቸውን ማስቻል፣
•  በሀገር ውስጥና ከሃገር ውጪ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎችና ሕጋዊ መብቶቿን ማስጠበቅ፣
•  ከቴክኖሎጂው ጋር አብሮ የሚሄድ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት፣
•  ያላትን ሰብአዊና ምጣኔ ሃብታዊ አቅም በአግባቡ እንድትጠቀምና አስተዳደሯን ለማዘመን፣
•  በማኅበራዊ አገልግሎት ብዙዎች ጋር በመድረስ የበጎ ፈቃድን ወንጌል ለተገፉትና ለተጎዱት ሁሉ ለማዳረስ የምሩቃኑ ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡

በመሆኑም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ምሩቃንን ወደ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብ፣ በማስተማር በማነጽና ከምስጥራት ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ለቤተክርስቲያን የልጅነት ግዴታቸውን እንዲወጡ እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረብንና ተመራቂዎች ከጥቁሩ ልብስ ደስታ ወደ ሰማያዊው ነጭ ልብስ ምረቃ የሚያሸጋግር ሕይወትን እየተመኘን  እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የዛሬውን ዓምድ በዚህ ቋጨን።