
ቅድስት ቅፍሮንያ በደናግል ገዳም ቁጥራቸው ኃምሳ ለሆኑ ለደናግሉ እመ ምኔት እኅት ነበረች። የእመ ምኔትዋም ስሟ ኦርያና ነው። ይህችንም ቅድስት በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደገቻት። በትሩፋት ሥራ ተጋዳሊት እስከሆነችም ድረስ አምላካውያት የሆኑ መጻሕፍትን አስተማረቻት። ከዚህም በኋላ ፍጹም ገድልን ጀመረች፤ በየሁለት ቀኑ ትጾም ነበር። ብዙ ጸሎታትንም ትጸልይ ነበር። ያቺም እመ ምኔት ሥራዋ ያማረ በሃይማኖቷም የጸናች ነበረች። በበጎ ሥራ ሁሉ እንዲጸኑ ወገኖቿን ታስተምራቸው ነበር።
ከዚህም በኋላ ሰዎች ሁሉ ጣዖታትን እንዲያመልኩ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ በአዘዘ ጊዜ ብዙዎች ክርስቲያኖችን ይዘው አሠቃዩአቸው፤ ሰማዕታትም ሆኑ። እሊያ ደናግልም ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ከገዳም ወጥተው ሸሽተው ተሠወሩ። እመ ምኔቷ ግን ከዚች ቅድስት ቅፍሮንያ ጋራ ብቻዋን ቀረች።
በማግሥቱም የንጉሡ መልክተኞች ወደ ዚያ ገዳም በመጡ ጊዜ እመ ምኔቷን አግኝተው ያዟት፤ ሌሎችንም ደናግል ፈለጓቸው ግን አላገኟቸውም። ቅድስት ቅፍሮንያም በእርሷ ፈንታ እኔን ውሰዱኝ ይቺንም አሮጊት ተውዋት አለቻቸው። እነርሱም ያዟት፤ በብረት ሰንሰለትም አሠሯት፤ መኰንኑ ወደአለበትም ከተማ ወሰዷት፤ እመ ምኔቷም እያለቀሰች ተከተለቻቸው።
ወደ መኰንኑም በአደረሷት ጊዜ ለአማልክት ሠዊ አላት፤ ብዙ ቃል ኪዳንም ገባላት። እርስዋ ግን ቃል ኪዳኖቹን አቃለለች፤ ትእዛዙንም አልተቀበለችም። እንዲደበድቧትም አዘዘና በበትሮች ደበደቧት።
ዳግመኛም ልብሷን ገፍፈው ሥጋዋን ግልጥ እንዲያደርጉ አዘዘ። እመ ምኔቷ ኦሪያናም “አንተ ከሀዲ፣ ይቺን ታናሽ ብላቴና እንዳጐሳቈልሃት እግዚአብሔር ያጐሳቍልህ ዘንድ አለው” ብላ ጮኸች። መኰንኑም እጅግ ተቈጥቶ ይህቺን ቅድስት ቅፍሮንያን አሥረው በመንኰራኵር ውስጥ እንዲያሠቃዩዋት፣ በብረት መጋዝም እንዲሠነጥቋት አዘዘ። ሁሉንም አደረጉ ይህንም ሁሉ ፈጸሙባት። እርሷም ርዳታን ሽታ ወደ እግዚአብሔር ጮኸች። ወዲያውኑ ከሕመሟ ሁሉ ድና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ሆነች።
ከዚህም በኋላ ደግሞ ምላሷንና ሕዋሳቷን ሁሉ ቆረጡ ጥርሶቿንም ሰበሩ። ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ሕማም አስነሣት። መኰንኑም እሷን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧት። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች።
አንድ ባለ ጸጋ ምእመን ሰውም መጥቶ የቅድስት ቅፍሮንያን ሥጋ ወሰደ፤ በአማሩ የሐር ልብሶችም ገንዞ በወርቅ ሣጥን አኖራት። ከሥጋዋም ብዙ ድንቅ ታአምር ተገለጠ።
ምንጭ፡ ስንክሳር ከሚያዝያ እስከ ጳጉሜን

