
እጅግ ታላቁ የመከራ በረከት እኛ ከዚህ ጎስቋላ ዓለም ወደ ዘላለማዊ ክብር የምንሸጋገርበት ጠንካራና ኃያል ድልድይ ነው፡፡ መከራ ልባችንን ለዓለም ፍቅር ጎትቶ በማውጣት እኛን ለሌሎች ሰዎች አድርጎ ይቀይረናል፡፡ በሌላ ቃላት መከራ እኛን ከዓለም ፍቅር ያስጥለናል፡፡ በዘለዓለማዊነት ውስጥ ያለችውን አንድ ቀን በመከራዎች የተሞሉ ብዙ ዓመታትን ታካክስልናለች፡፡
ቅዱስ አውግስጢን እንዲህአለ፡- “ነፍስ ከዓለም ፍቅር ውስጥ ተጎትታ ካልወጣች በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መመለስ አትችልም፡፡ እርሷን ጎትቶ ለማውጣት ደግሞ ከመከራና ከፈተና የተሻለ ምንም ነገር የለም፡፡” ከዚህ በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፡፡ “የወይን ዘለላዎች ካልተረገጡ በስተቀር የወይን ጠጅ ሊሆኑ አይችሉም፤ ወይራም በድንጋይ ካልተጨመቀ በስተቀር የወይራ ዘይት ሊወጣው አይችልም፡፡” ከዚህ ሌላ ደግሞ አውግስጢን እንዲህ በማለት ተናግሯል፡- “ፈተናና መከራ ሲበረቱ ፍጹምነትን ያስገኛሉ እንጂ በጥፋት አይጠቃለሉም፡፡”
ሰው በመከራና መስቀሉን በመሸከም ካልሆነ በስተቀር ክብርን ሊቀበል አይችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር በይፋ ካሳወቁ በኋላ እርሱን ያለምንም መከራ ነው የሚወዱት፡፡ ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ጊዜ ከዓለም ክብርና ውዳሴ ከሚቀበሉ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ” ሉቃ ፲፪÷፳፬ ፣ ማቴ ፯÷፲፫ የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ይረሱታል፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን “በክርስትና ውስጥ ወዳለ ክብር መግባት የሚቻለው በመከራ ነው፡፡” የሚለውን ጠቃሚ መመሪያ ልንማርና ልንገነዘብ ይገባናል፡፡
መከራን ተከትሎ ስለሚመጣው ክብር ስናስብ መንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛው መልእክቱ ውስጥ የተናገረውን ቃል እናስታውሳለን፡- “ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም፡፡ ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እና የዋለን እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፡፡” ፩ኛ ዮሐ ፫-፪
ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል፤ መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ረሀብ …ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን?” እና “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፡፡” በማለት ከተናገረ በኋላ ነው “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡” ያለው ሮሜ ፰÷፴፭-፴፭
መከራ እና ክርስትና
በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን
የቀድሞው የጋርቢያ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ እንደጻፉት አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው

