በሮም አደባባይ ባዶ እጃቸውን ዓለምን ያሸነፉ ጀግኖች

ውድ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ እድምተኞቻችን በዚህኛው ሳምንት በእግረ ልቡናችን ሐዋርያት የተመላለሱባትን ሮምን ለመጎብኘት የዐሳብ ፈረሳችንን ኮርኩረን ካለንባት ምድር ወደ ጣልያኗ ርእሰ ከተማ ሮም እንጋልበዋለን፡፡

ከዘመናት በፊት ምድራችን በአንድ ታላቅ ክስተት ተጎብኝታ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ሰው ሆነ፡፡ ይህንን መገለጥ ዓለሙ ባላወቀው ሰዓት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ኬፋ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ለሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ ሰጠ፡፡ “አንተ ግን የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፡፡” ይህ ምስክርነት ስምዖንን ወደ ጴጥሮስነት/ኬፋነት አሻገረው፡፡ ስምዖን አለት ሆነ፡፡ ከዚህ ትዕይንት ከዓመታት በኋላ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ሰማያት ካረገ፣ ደቀ መዛሙርቱም በ፲ (10)ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ለአገልግሎት ከወጡ ከዓመት በኋላ ወደ ደማስቆ የሚጓዝ አንድ ጎልማሳ በታላቅ ብርሃን ከመንገዱ ተሰናከለ፡፡ ብርሃኑ ሊያስቆመው አልቻለምና ወደቀ፡፡ ያ ብርሃን ስሙን ጠርቶ “ለምን ታሳድደኛለህ?” አለው፡፡ አሳዳጁን ያላወቀው ጎልማሳም “አንተ ማነህ?” ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ፡፡ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ” ብሎ መለሰለት፡፡ ያ “አንተ ግን የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ተብሎ የተመሰከረለት አምላክ በሰብዓዊ ነገዱ በናዝሬት ራሱን ጠርቶ ተገለጠ፡፡ ይህ ገጠመኝ ሳዖልን ወደ ጳውሎስነት ለወጠው፡፡ ጳውሎስ ምርጥ ዕቃ ሆነ፡፡

እያንዳንዱን ትምህርቷን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችው ቤተክርስቲያን “የዓለም ብርሃን ናችሁ” የሚለውን ቃሉን መነሻ አድርጋ እነዚህን ሁለት ሐዋርያት “ብርሃናተ ዓለም” ብላ ትጠራቸዋለች፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ሐዋርያት ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ አገልግሎት ከተላኩ በኋላ ወንጌል በዓለም መስፋፋት ጀመረ፡፡ ክርስትና እንደ አይሁድ በዘርና በጎሳ ሳይገደብ ዓለምን ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ሮም፣ አንጾኪያና ወደ ተለያዩ ሕዝቦች ተሰማራ፡፡ በቃልና በጽሑፍ በማስተማር ብዙኀኑን ውደ እግዚአብሔር መንግሥት ማረከ፡፡ የአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስም በግሪክ፣ በሮምና በተለያዩ የአሕዛብ መንደሮች ወንጌልን አዳረሰ፡፡

ይህ የመንግሥተ ወንጌል መስፋፋት ሰላም የነሳው ጠላት በአላውያን መንግሥታት በኩል ጠላትነትን አወጀ፡፡ እጅግ የበዛ መከራን አጸናባቸው፡፡ በሮማ አደባባይ ባዶ እጃቸውን ዓለምን ተፋለሟት፡፡ በቁልቁል በመሰቀል፣ በሰይፍ በመቀላት በኩል ዓለምንና ፍላጎቱን ድል ነሱት፡፡ ይህ ሞቶ የማሸነፍ ድል ለሰይጣን ክፉ ትዝታውን ቀሰቀሰበት፡፡ ያጠፋው ዘንድ ቆርጦ፣ ባሰቀለው ጊዜ ድል ያደረገውን ክርስቶስን አስታወሰው፡፡ በድጋሚ ያውም በሜዳው በግዛቱ በሮም አደባባይ ተሸነፈ፡፡ ሐዋርያቱ በቃለ ጳውሎስ በኩል “ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማቴን ጠብቄያለሁ፤ ከእንግዲህ የጽድቅ አክሊል ይጠብቀናል” አሉ፡፡

ዛሬ ላይ ለመንግስታቸው መጽናት በሮም ዐደባባይ ሐዋርያቱን ያሰዉት ነገስታት መንግስታቸው አልፎ፣ ክብራቸው ተገፎ፤ ስም አጠራራቸው ተረስቶ የሐዋርያቱ ታሪክ ሲነገር ብቻ የሚነገሩ የታሪክ ተቀጽላ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ዛሬ ያ አደባባይ ስሙ የሮማ አደባባይ አይደለም፤ ይልቁንም ተዘቅዝቆ የተሰቀለበትን የቅዱስ ጴጥሮስን ስም ወስዷል፡፡ ከሮማ ግንቡ ባሻገር ያለው የሮማ መሬትም አንገቱን በተቀላው በቅዱስ ጳውሎስ ስም ተሰይሟል፡፡ ዛሬ ሮም የጴጥሮስና ጳውሎስን ታሪክ የምትዘክር መሬት ሆናለች፡፡

እስቲ ፈረሳችንን በሮም እምብርት ወዳለችው ትንሽዬዋ ሃገር ቫቲካን እንውሰደው፡፡ በዚህ ባለው ትልቁ ካቴድራል የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ክቡር ሥጋው አርፏል፡፡ በ፷፬ (64) ዓ.ም. ሰማዕትነት የተቀበለው ቅዱስ ጼጥሮስ ካረፈ በኋላ ከቀዩ ግንብ አቅራቢያ በኔክሮፖሊስ ባለ ዋሻ ክቡር ሥጋው አርፎ የነበረ ሲሆን በፈረንጆቹ ፲፱፻፵ (1940) ዓ.ም. በተደረገ አሰሳ Πέτρος ἐνὶ /ጴጥሮስ እዚህ ነው የሚል ጥንታዊ የግሪክ ጽሑፍ በመቃብሩ ላይ ተጽፎበት ተገኝቷል፡፡ ከ፲፱፻፷ (1960) ዓ.ም. ጀምሮ አጽሙ ለዐሥርት ዓመታት በካቶሊኩ ፖፕ ቤተ ጸሎት ተቀምጦ የነበረ ሲሆን ከ፳፻፮ (2006)ዓ.ም. ጀምሮ ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት ሆኗል፡፡ የተወሰኑ የዓጽሙ ቅሪት ክፍሎችም ለኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ቦታ ጎብኝተንና የቅዱሱን አጽም ተሳልመን ከአደባባዩ ቅጥር ጀርባ እንጓዝ፡፡

የቤተክርስቲያናችን ቅዱስ ትውፊት እንደሚነግረን ቅዱስ ጳውሎስ ከከተማው ውጪ በዚህ ቦታ እንዳረፈ ነው፡፡ በዚህም በካቶሊካውያን በሚተዳደር ቤተክርስቲያን መንበር ሥር የአሕዛብ ሃዋርያ የንዋየ ህሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ክቡር ሥጋ አርፏል፡፡ በዚህ መቃብሩ ላይም በጥንታዊ የላቲን ቃል PAULO APOSTOLO MART /ጳውሎስ ሐዋርያ ሰማዕት ከሚል ጽሑፍ ጋር ያለበት ሲሆን በ፲፱፻፺፱ (1999)ዓ.ም. በተካሄደ ቁፋሮ ተገኝቶ በ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. ከመቃብሩ በተወሰደ ቅሪተ አካል ላይ በተደረገ የካርቦን ምርመራ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

አሁን ፈረሳችንን ወዳለንበት እንመልሰው፡፡ ሥጋቸውን እንጂ ነፍሳቸውን መግደል የማይችሉትን ነገስታት ያልፈሩት የቅዱሳኑ ሥጋ በምድር እንዳረፈው ሁሉ ዓይነ ህሊናችንን ወደ ክርስቶስ ስናቀና ሕያው ነፍሳቸውን በሰማይ በአባታቸው ዘንድ እናየዋለን፡፡ በኛም ልብ ደግሞ ጸጋቸው እንዲያርፍ እየተመኘን የዛሬን “ቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ” በዚሁ አተምን፡፡
መልካም በዓል፡፡