
አንዳንድ ሰዎች መስቀሉን የሚሸከሙት በትዕግስት እና በድፍረት ነው፡፡ ሌሎቹ የሚሸከሙት ደግሞ በማማረርና በመቃወም ነው፡፡ ለልዩ ምክንያት ሲሉ መስቀሉን መሸከም የማይችሉ ሰዎችም አሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ መስቀሉን መሸከም ስለማይፈልጉ ከእነርሱ ዘንድ ይወሰዳል፡፡ ከላይ ከተመለከትናቸው መካከል የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ክፍሎች ክርስትያናዊ እምነታቸውን ለመግለጽ የማይፈልጉ ስለሆኑ መጥፎ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ ውስጥ ምእመናን ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ገልጧል፡፡ ይህን የገለጠው ከክርስቶስ ፍቅር ማንም እንደማይለያቸው፣ ስለ እርሱ ሲሉ በየቀኑ መታረዳቸውንና ለመታረድ እንደቀረበ በግ መቆጠራቸውን በመዘርዘር ነው፡፡ በዚያው ላይ በመቀጠል የተናገረው ግን እንዲህ ብሎ ነው፡፡ “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡” ሮሜ ፰÷፴፭-፴፯ ስለሆነ እውነተኛ ድል የሚገልጠው የመከራን፣ የጭንቀትን፣ የስደትን፣ የረሀብን፣ የራቁትነትን፣ የፍርሃትን፣ የሰይፍን፣ወዘተ. ሕማምን በጽናት በመታገስ ነው፡፡ ይህን ልናደርግ የምንችለውም በጌታችን በመድኃኒታችንና በኢየሱስ ክርስቶስ እርዳታ ነው፡፡
በአገልግሎት ውስጥ መከራን በጽናት በመቀበል ቀዳሚ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው፡፡ በጽናቱ በተቀበላቸው ፈተናዎችና በተልእኮዎቹ መስክ ውስጥ እጅግ በመድከሙ ቅዱስ ጳውሎስ በእውነት የሚቆጠረው ከሐዋርያት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ሆኖ ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ ሲናገር “…ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፤ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ “፩ኛ ቆሮ ፲፭÷፲
ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያን ሆኖ ከተለወጠ በኋላ ተልእኮውን ደማስቆ ወስጥ የጀመረው ኢየሱስ ክርስቶስን ከታላቅ መነሳሳት ጋር በየምኩራብ ውስጥ በመስበክ ነበር፡፡ ብዙ ቀናት ካለፉ በኋላ ግን አይሁድ ሊገድሉት አሤሩበት፡- “…ሳውል (የቅዱስ ጳውሎስ የቀድሞ ስሙ) ግን ዐሳባቸውን አወቀ፡፡ ይገድሉት ዘንድ በሌሊት እና በቀን ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት፡፡”
ቅዱስ ጳውሎስ የመሞቻው ጊዜ በደረሰ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “በመሥዕዋት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና የምሄድበት ጊዜ ደርሷል፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል…” በማለት ተናግሯል፡፡፪ኛ ጢሞ ፬÷፮-፰
ይህ ታላቅ ሐዋርያ በዚህ መልእክቱ ውስጥ የተናገረው እንዲህ በማለትነው፡- “የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? …..በድካም አብዝቼ በመገረፍ፣ አብዝቼ በመታሰር፣ አትርፌ በመሞት፣ ብዙ ጊዜ ሆንሁ፡፡ አይሁድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ፤ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ፤ ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድኩ ፤ በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት ፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፣ በአህዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረበዳ ፍርሃት ፣ በባሕር ፍርሃት ፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት፣ ነበረብኝ፤ ድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ ማጣት ፣ በርሃብና በጥም፣ ብዙ ጊዜም በመጦም፤ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ፡፡ የቀረውንም ነገር ሳልቆርጥ ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስትቲናት ዐሳብነው፡፡”
ምንጭ ፡ መከራ እና ክርስትና
በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን
የቀድሞው የጋርቢያ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ እንደ ጻፉት አያሌው ዘኢየሱስ እንደ ተረጎመው

