ይህንን ጥሪ ሰምታችሁ ኖሯል ? የንስሐ ጥሪ

የሰው ልጆችን አብዝቶ የሚወደውና መጥፋታቸውን የማይሻ ፈጣሪ ከጥልቅ ፍቅሩ የተነሳ ልጆቹን ዘወትር ወደ ንስሐ ይጠራቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የሰው ልጆች ድኅነት በመሆኑ ወደ ንስሐ ከመጣራት አይሰለችም ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ እግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው” በማለት ፈጣሪያችን ለሰው ያለውን ፍቅር ገልጦታል፡፡ ፩ጢሞ ፪÷፬፡፡ የሰዎች መዳን መሻት ብቻም ሳይሆን ወደ ንስሐ እንዲመለሱ ከቸርነቱ የተነሳ ስለኀጢአታቸው ከመቅጣት ይታገሳል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እነጂ ማንም እናዳይጠፋ ወድዶ ስለእናንተ ይታገሳል” በማለት አረጋግጦታል፡፡፪ጴጥ ፫÷፱  ይህ የእግዚአብሔር ትዕግስት ሰፊ ነውና የጥሪውን ድምጽ  የሚሰሙት ሁሉ ሊጠቀሙበት እንዲችሉ የፈጣሪ ፈቃዱ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና ከተማ በአርዮስፋጎስ መካከል የግሪክ ሰዎችን ሲሰያስተምር “እንግዲህ እግዚብሔር  ያለማወቅን ወራት (በኃጢአት የመኖር ዘመን) አሳልፎ  አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፡፡” የሐዋ ፲፯÷፴

  “ንስሐ ግቡ ኃጢአትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ፡፡ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፡፡ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፡፡  ስለምን ትሞታላችሁ የሟቹን ሞት አልፈቅድምና ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ”  ሕዝ ፲፰÷፴-፴፪

  አምላካችን እግዚአብሔር ይወደናል፡፡ ከፍቅሩ የተነሳ በንስሐ አማካኝነት ከበደላችን ታጥበን የቸርነቱን እና የማታልፍ መንግስቱ ተካፋይ እንድንሆን ይፈልጋልና ሰዎችን ወደ ንስሐና ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ከመጠራት አላቋረጠም፡፡

የምንኖረው በኃጢአት ዓለም በመሆኑ ከኃጢአትም ተለይተን በንጽህና መኖር ባለመቻላችን ፈጣሪአችን እግዚአብሔር  በሕይወት እንድንኖር  እንድንነጻ እና እንድንቀደስ አስፈላጊያችን ወደሆነው ንስሐ ይጠራናል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ስለእኛ ድኅነት ወደ ተቀደሰው ሕይወት እንድንገባ የተሰጠን እንጂ በላያችን በግድ የተጫነ ሸክም አለመሆኑን በመረዳት ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ንስሐ ብንገባ የእግዚአብሔርንም ጥሪ ብንቀበል ምክሩንም ብንሰማ በሕይወት እንኖራለን ፡፡ ከሞተ ነፍስም እንድናለን፡፡ እምቢ ብንልም ንስሐ ባንገባ የኀጢአታችን ዋጋ በጊዜው ማግኘታችንን የማይቀር ነው፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት “እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹ ሠይፍ ይበላችኋል፡፡” እግዚአብሔር  ተናግሯል፡፡ ኢሳ ፩÷፲፱-፳፡፡ እኛ ግን መልካሙን ብንሠራ የእግዚአብሔር  የንስሐ ጥሪ  ብንቀበል እና ከኃጢአታችን ሥርየት  አግኝተን በተቀደሰ ሕይወት በእግዚአብሔር  መንግሥት ብንኖር መልካም ነው፡፡

ምንጭ: አቡነ ሺኖዳ  የንስሐ ሕይወት