ይህ ተግባራዊ ድረገጽ በጥናቱ ግኝት መሰረት የሰንበት ትምህርት ቤታችንን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ እና በጥናቱ መጀመሪያ ላይ የቀረቡትን ስጋቶች እና ደካማ ጎኖችን ተሻግሮ የታለመለትን አላማ ሊያሳካ በሚችል አቅም የተዋቀረ ነው፡፡ ይህ ድረገጽ በቀጣይ ሂደቶች ውስጥ አቅሙን ሊያሻሽሉ የሚችሉ አስፈላጊ የሆኑ የይዘት እና የቅርጽ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት ይችላል፡፡ ይህ ተግባራዊ ድረ ገጽ በዋናነት ከሌሎች ድረገጾች በተሻለ አዳዲስ ነገረችን ያቀፈ ሲሆን በዋነነትም በማንኛውም የኤሌክትሮኒክ የግንኙነት መንገድ ማለትም በስልክ (አንድሮይድ ወይም አይ.ኦ.ኤስ) እንዲሁም በኮምፒውተር ያለምንም ችግር መጠቀም የሚያስችል አቅም ተፈጥሮለታል ይህም በስልክ (አንድሮይድ ወይም አይ.ኦ.ኤስ) ተደራሽ የሚያደርጋቸውን ምዕመናን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ የተደረጉ ገጽታዎችን በሌሎች ክፍች እንመለከታቸዋለን፡፡
የጥናቱን ግኝቶች በግብዓትነት በመጠቀም ድረገጹ በ7 ዋና ዋና ክፍሎች ተዋቅሯል፡፡ ከሰው ኃይል፣ከመረጃ ግብዓት፣ከገንዘብ እንዲሁም ከአስተዳደራዊ ቅልጥፍና አንጻር ማእከላዊ እንዲሆን በማድረግ የተዘጋጀ ድረገጽ ነው፡፡ እነዚህም 7 አቢይ ክፍላት፡- ቀዳሚ ገጽ፣ደብረ ገሊላ፣ትምህርት፣ዜማ፣ህጻናት፣ኪነጥበብ እና ወቅታዊ የሚባሉ ሲሆን በየክፍቱ ንዑስ ክፍላትን በመያዝ የሚሰራባቸው ይሆናሉ፡፡
- ቀዳሚ(ዋና ገጽ)፡-
ይህ ገጽ የመጀመሪያ ክፍል ሲሆን ወደ ድረገጹ የመጣ ማንኛውም ተመልካች በመጀመሪያ የሚያገኘው ነው፡፡ በዚህ ክፍል፡-
- ዜናዎች ፡- ወቅታዊ የደብራችን እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤታችንን እንቅስቃሴዎች ምስሎቸን ጽሁፎችን ወዘተ በመጠቀም የምናሳውቅበት
- ማስታወቂያዎች፡- በዚህ ክፍል ልዩ ልዩ የጉዞ፣የደም ልገሳ፣የጉባዔያት ማስታወቂያዎች ምስሎቸን ጽሁፎችን ወዘተ በመጠቀም የሚለቀቁበት
- አድራሻ ፡- ይህም ሰንበት ትምህርት ቤታችንን ማግኘት ለሚፈልጉ ምዕመናን የመገናኛ መንገድ ይሆናቸው ዘንድ ፖስታ ኢሜይል ስልክ እንዲሁም መንፈሳዊ ግልጋሎቶችን በገንዘብ መርዳት ለሚፈልጉ ደግሞ የሰንበት ትምህርት ቤታችንን የባንክቁጥር የሚያገኙበት
- ርዕሰ አንቀጾች፡- ወደ ክፍላት ማስፈንጠሪያ የሚሆኑ መግቢያ ጽሁፎች
- ደብረ ገሊላ፡-
ይህ ገጽ ቋሚ (ሰታቲክ) የሚባለው አይነት ክፍል ነው ይህም ማለት መደበኛ የሆነ የመረጃ እድሳት የማያስፈልገው ነው፡፡ የደብራችንን እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤታችንን ታሪክ የሚቀመጥበት ክፍል ነው፡፡ ከታሪክ በተጨማሪም የጉባዔ እንዲሁም የጸሎት መርሐግብራትን የሚያሳይ መረጃ ሰጪ ጽሁፎች ይኖሩታል፡፡ በዚህ ክፍል አዲስ ገጽታ የታከለበት ሲሆን ይህም ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ለመግባት የሚፈልግ ማንኛውም ምዕመን በቀላሉ መረጃ የሚያገኝበት ሥርዓት ተበጅቶለታል፡፡ ይህም ሲባል ድረገጹን የሚጎበኝ እና ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ገብቶ አባል ለመሆን የሚፈልግ ሰው ሙሉ ስሙን እድሜውን እንዲሁም የሚገኝበትን ኢሜይል እንዲያስገባ እና በአካል መጥቶ የሚማር ከሆነ መምጣት የሚገባውን ሰዓት እንዲሁም በጊዜው ለምዕመኑ በሚመጥነው ክፍል ላይ የሚገኘውን ተጠሪ ስልክ በመጠቀም በኣካል እንዲመዘገብ የማድረጊያ መንገድ ነው፡፡
- ትምህርት፡-
ይህ ክፍል ማንኛውም መንፈሳዊ ትምህርቶች የሚቀርቡበት ክፍል ሲሆን ለአስተዳደር እንዲመች በሦስት ክፍሎች ተከፍሏል፡፡
- ስብከት፡- የተለያዩ ህይወት ነክ ስብከቶች የሚቀርቡበት ንዑስ ክፍል ነው፡፡
- ተከታታይ ትምህርት፡- ይህ ንዑስ ክፍል ደግሞ ተከታታይ የሆኑ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡
- መጻህፍት፡- የተለያዩ መንፈሳዊ መጻህፍትን በነጻ የሚቀርብበት ክፍል ነው፡፡
- ዜማ፡-
ይህ አቢይ ክፍል ደግሞ መንፈሳዊ ዜማዎችን በተመለከተ የሚዘጋጁ ትምህርቶች መዝሙራት ወረቦች ወዘተ የሚቀርቡበት ነው በውስጡም ሁለት ንዑስ ክፍላት አሉት
- ልዩ ልዩ፡- የተለያዩ ዜማን የተመለከቱ ትምህርታዊ ጽሁፎች ማለትም የዜማ ንዋያት የዜማ ምልክቶች ታሪካዊ አመጣጦች በዜማ ላይ የሚታወቁ አባቶች ታሪክ ወዘተ የሚቀርብበት ክፍል ነው፡፡
- መዝሙራት፡- የድምጽ መዝሙራት ከነስንኞቻቸው ወረቦች ወቅታዊ ቀለሞች በድምጽ እንዲሁም በጽሁፍ ተደግፎ የሚቀርብበት ነው በዚህ ክፍል የሚለቀቁ መዘሙራትን እንዲሁም ወረቦችን ምእመናን እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ወደራሳቸው ከድረገጹ የሚያወርዱበት (ዳውንሎድ) የሚያደርጉበት ገጽታ ያለው ነው፡፡
- ህጻናት፡-
በዚህ ክፍል ህጻናትን የሚመለከቱ ማንኛውም የመንፈሳዊ ማስተማሪያዎች የሚቀርቡበት ክፍል ነው፡፡የሚቀርቡት ማስተማሪያዎች እድሜያቸው ከ6 አስከ 13 ዓመት የሆናቸውን ታዳጊ ህጻናትን ያማከለ ነው፡፡ ይህም የህጻናት ጨዋታ መዝሙራት ታሪኮች ስነጽሁፎች ሰንበት ትምህርት ቤት ህጻናት የሰሯቸው ልዩልዩ የኪነጥበብ ውጤቶች ወዘተ ያጠቃልላል፡፡
- ኪነጥበብ፡-
ይህ አቢይ ክፍል በሰንበት ትምህርት ቤታችን የተዘጋጁ የተለያዩ መንፈሳዊ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ማለትም ግጥሞች ወጎች ትረካዎች ወዘተ የሚቀርቡበት ክፍል ነው፡፡
- ወቅታዊ፡-
በዚህ ክፍል ደግሞ ወቅታ የሆኑ የቅዱሳን መታሰቢያዎች፤ በታሪክ ውስጥ በዚህ ወቅት የተደረጉ አቢይ ነገሮች የአጽዋማት እንዲሁም የበዓላት ምስባኮች ወዘተ ይቀርብበታል፡፡

