የደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰ/ት/ቤት ታሪክ

በቅድስት ቤ/ክ ታሪክ ውስጥ የሕጻናት እና የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ቤ/ክ ወጣቶችን በማስተማር ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ካላት ፅኑ ፍላጎትና እምነት ነው፡፡

ከ 1940 ዓ.ም ጀምሮ የወጣቶች እና የጎልማሶች መንፈሳዊ ማኅበራት ብቅ ብቅ አሉ፤ በጊዜው ከነበሩት አንጋፋዎቹ ማኅበራት ውስጥ ሃይማኖተ አበው እና ተምሮ ማስተማር ይገኙበታል፡፡

አሁን ያለበትን መልክ ይዞ እንዲጓዝ መሰረት የጣሉ ባወጡትም ቃለ አዋዲ መብት የሰጡት ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡

በ1971 ዓ.ም በመንበረ ፓትያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የወጣቶች ጉዳይ መምሪያ እንዲቋቋም እና ማኅበራቱ ሁሉ በመምሪያው ስር እንዲተዳደሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡

በ1973 ዓ.ም ኅዳር 29 የወጣቶች መንፈሳውያን ማኅበር በሚል ስያሜ ህጋዊ መብት አግኝቷል፡፡

በ1973 ዓ.ም አዲስ መመሪያ እና ህግ የፀደቀ ሲሆን የወጣቶች እና የጎልማሶች ማኅበራት የሚለውም ስያሜ የሰንበት ትምህርት ቤቶች በሚል እንዲተካ ተደርጓል፡፡ የስያሜው ለውጥ ያስፈለገበትም ምክንያት በጊዜው በነበረው የደርግ መንግስት ከፖለቲካዊ አቋም እና አላማ ውጪ በማኅበራት ስም መደራጀት እንዳይኖር በመከልከሉ እንደሆነ በጊዜው የነበሩ ሰዎች ይስማማሉ፡፡ ይህ መተዳደሪያ ደንብ እስከ ግንቦት 2 1986 ዓ.ም ድረስ ለ 13 አመታት አገልግሏል፡፡

1986 ዓ.ም ግንቦት 3 ቀን ተሸሽሎ  የፀደቀው ህግ እና ደንብ አሁንም ድረስ በማገልገል ላይ ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ምስሌነ

ከ1958-68 ዓ.ም

ስለቤተክርስቲያን ዶግማ እና ቀኖና ለመማር በየቦታው የሚደረገው መሰባሰብ ምክንያት በማድረግ በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካኝነት ወጣቶች በቤ/ክ እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት ሚያዚያ 16 1958 ዓ.ም የደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰ/ት/ቤት የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር ተብሎ ተመሠረተ፡፡

ይህን መንፈሳዊ ማኅበር የመሰረቱት አባቶችና ወንድሞች

በቀድሞው አጠራር አባ ተፈራ መልሴ(በአሁን ንቡረ ዕድ ገ/ህይወት መልሴ)        የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

መምህር ሙሉጌታ አሽኔ (መ/ህይወት ሙሉጌታ አሽኔ )                                የማኅበሩ ፕሬዝዳንት

መሪጌታ ወልደ ዳዊት ቸኮል                                                                የማኅበሩ መምህር

አቶ ጌታቸው ንጉሴ                                                                          የማኅበሩ ም/ፕሬዝዳንት

ዲያቆን በቀለ ኪዳኔ                                                                         ዋና ጸሐፊ

አቶ አበበ ማስረሻ                                                                           ም/ ጸሐፊ

መዘምር አሰፋ ግዛው                                                                        ድርሰት ክፍል

አቶ ተስፋዬ ዘለቀ                                                                            ግምጃ ቤት

አቶ ነጋሽ ገብርዬ                                                                            አባል

መምሬ ማሞ ገ/ጻድቅ                                                                        አባል

አቶ ሠይፈ ገላግሌ                                                                           አባል

በወቅቱ ሴቶች ወደ ቤ/ክ እንዲሁም የማኅበሩ አባል መሆን የተለየ ትርጉምና ስም ያሰጥ ነበር፤ ሆኖም ችግሩን አባ ተፈራ መልሴ ለካህናት እና ለምዕመናን በቤተክርስቲያን በየደጀ ሰላሙ በማስረዳት እና በማሰባሰብ ብዙዎች ልጆቻቸውን ወደ ቤ/ክ እንዲልኩ ካህናት እና ዲያቆናትን እንዲሳተፉ አድርገዋል፡፡

የማኅበሩ የመጀመሪያ  አባል ወ.ት ከበደች ተ/አብ ፣ አልማዝ ተ/አብ፣ መንበረ ጥላዬ በወቅቱ ከነበሩት ሴቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ማኅበሩ ሲቋቋም መተዳደሪያ ደንብ እንደነበረው እንዲሁም በዛፍ ጥላ ስር እንደሚሰበሰቡ እና ከዚያም በመቃብር ቤት ከጥቂት ጊዜ በኃላ ግን በክርስትና ቤት ይሰባሰቡ ነበር፡፡አባላቱ እየበዙ በሄዱ ጊዜ አዳራሽ ተዘጋጅቶ በዚያ መርሐ ግብር ያካሂዱ ነበር፡፡

በወቅቱ በሰ/ት/ቤት ያገለግሉ ከነበሩት መምህራን መካከል

ዲ/ን ኢያሱ (1960 ዓ.ም የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ የነበሩት የአሁኑ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል )

አባ ኤልያስ(ብጹዕ አቡነ ኒቆዲሞስ /አሁን በሕይወት የሌሉ)

መሪጌታ ወልደ ዳዊት ቸኮል

መሪጌታ አብርሃም መኮንን

መሪጌታ ብርሃኑ ወደስ

መሪጌታ ፀሃይ ብርሃኑ በማኅበሩ እየተገኙ ለት/ት ከፍተኛ እገዛ ያደርጉ ነበር፡፡

በተጨማሪም በየሳምንቱ አምሳ ሳንቲም መዋጮ ያደርጉ ነበር፡፡

በወቅቱ የነበሩ ማኅበሩ አገልግሎቶች

በደብረ ታቦር በዓል ላይ ጸበል ጻድቅ በማዘጋጀት ለምዕመናን ያድል ነበር

በትንሳኤ ሌሊት እና በማዕዶት ዕለት ነድያንን መመገብ

ከ1968-72 ዓ.ም

የሰ/ት/ቤቱ እንቅስቃሴ በ1968 ዓ.ም መገባደጃ አገልግሎቱን ያደበዘዘ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ይኸውም በሰ/ት/ቤት ያገለግሉ ከነበሩ ሴቶች የተወሰኑት ካህን ሊያደርገው የሚገባውን የቤተክርስቲያን ቀኖና በመፈጸማቸው በሊቀ ጳጳሱ ተወግዘው ሰ/ት/ቤቱ ለ2 አመታት እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡

ከሁለት አመት በኃላ በወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ በነበሩት በአባ ጴጥሮስ በአዲስ መልክ እንደገና ተከፍቷል፡፡

አገልግሎቱ በአዲስ መንፈስ በመቀጠልም በሊቀ ሊቃውንት አባ ተፈራ መልሴ አማካኝነት አሁን የሰ/ት/ቤቱ አባላት የሚገለገሉበት አዳራሽ በማኅበሩ አባላት ጉልህ ተሳትፎ ሊሰራ ችሏል፡፡

ለግንባታው የፈጀው 35000 ብር ሲሆን

ከአለም አብያተ ክርስቲያናት ተራድኦ 24000

ከማዘጋጃ ቤት 5000

ከእድሮችና ግለሰቦች 5000 ተሰብስቧል፡፡

የአዳራሹ ግንባታ እንደተጠናቀቀ በዚያን ወቅት የነበረው ቤተ መቅደስ ፈርሶ ታቦተ ህጉ አደራሽ እንዲገባ ስለተደረገ የሰ/ት/ቤቱ መርሐ ግብር በፋፋ ቤት ይካሄድ ነበር፡፡

የካቴድራሉ ግንባታ ሲጀመርም የሁሉም ትኩረት ወደዚያ ሆነና የማኅበሩ አገልግሎት ተዳከመ፡፡ በተጨማሪም በነበረው ርዕዮተ አለም አማካኝነት ከ1970-72 ዓ.ም የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች የእድገት በህብረት ዘመቻ በመሔዳቸው እንቅስቃሴውን ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ሊያዳክሙት ችሏል፡፡

ከ1972-82

በርካታ መንፈሳዊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

መሪጌታ ይባቤ ዘመልአክ የሰ./ት/ቤቱ መምህር ሆነው ተመድበዋል፡፡

የመጠቀ ፣ ትክክለኛ የነገረ መለኮት የትርጓሜ ት/ትን ወጣቱ በሚገባው መልክ ይሰጡ ነበረ፡፡በዚህም በርካታ የሰ/ት/ቤቱ አባላት ለመምህርነት እንዲበቁ አድርገዋል፡፡

መጋቤ ምስጢር ጌድዮን ዘላለም የግእዝ ት/ት መሰጠት ተጀመረ፡፡

መምህር ሐረገወይን ጸጋዬ የቁምና የቸብቸቦ መዝሙራትን በብዛት በማስጠናት ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አሁን ሰ/ት/ቤቱ ያሬዳዊ መዝሙርን በተመለከተ ላለው ጹኑ አቋም መሠረቱ ያን ጊዜ የነበረው የመዝሙር ሀብት ነው፡፡

መምህር አምደ ብርሃን የሰ/ት/ቤቱ መምህር በነበሩበት ወቅት በርካታ ወጣቶችን በትምህተ ሃያማኖት ሊያንጹ  ችለዋል፡፡

መንፈሳዊ ድራማዎች መነባንቦች በማዘጋጀት ለምዕመናን ይቀርቡ ነበር፡፡

ለሕጻናትና ማዕከላዊያን ክፍል ይሰጥ የነበረው ት/ት ጠንካራ ነበር፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄና መልስም በተደጋጋሚ ሰ/ት/ቤቱ በአ.አ ከሚገኙ አድባራት ጋር ተወዳድሮ ብዙውን ጊዜ በማሻነፉ በወቅቱ ከነበሩት ፓትርያርክ እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡

ከተለያዩ አድባራት እና ሰ/ት/ቤቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ተጀመረ፡፡

ሁለተኛው

ይህ ሁሉ መልካምና በጎ ነገሮች እየተደረጉበት የነበረው ሰ/ት/ቤት ጥቂት አባላት በነበራቸው የመንፈሳዊ ሕይወት ጉድለት የቡድን ጸብ ክርክር ተከስቶ የነበረ በመሆኑ ሰ/ት/ቤቱ ቀደም ሲል የነበረው ስምና ዝና ላይ ጥላውን እንዲያጠላ በማድረጉ አባላት ከሰ/ት/ቤት እንዲርቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህን ጉዳይ ለመፍታት በወቅቱ ከነበሩ ታላላቅ ወንድሞች መካከል

መጋቤ ሥርዓት በጋሻው ወ/ሰንበት፣ አቶ ካሳሁን ውርጂ፣አቶ ሚሊዮን ከድር፣ አቶ ታደለ ይፍሩ እና አቶ አውላቸው አሻግሬ በሰከነ መንፈስ ሰ/ት/ቤቱን ሊለውጥ የሚችል ሀሳብ በማምጣት ‹‹ የሰ/ት/ቤት ትንሳኤ›› በሚል ቁጥራቸው ከሰባት መቶ በላይ የሆኑ ታዳሚዎች እንዲሁም የቤተ ክህነት ታላላቅ አባቶች በተገኙበት ሚያዚያ 28 1982 ዓ.ም ታላቅ ጉባዔ ተደረገ፡፡በመጨረሻም የሰ/ት/ቤቱን መዋቅርና ደንብ የሚቀርፅ አጥኚ ቡድን ተዋቅሮ ጉባዔው ተጠናቋል፡፡

ከአንድነት ጉባዔው በኃላ የሰ/ት/ቤቱ መዋቅርና መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ ሰባት አባላት ያሉት የሥራ አመራር ኮሚቴና ሶስት አባላት ያሉት የሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር  ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገባ፡፡

በወቅቱ በሰ/ት/ቤቱ መርሐ ግብር ላይ ቅዳሜና እሁድ ይገኝ የነበረው ከፍተኛው አባላት ቁጥር አምሳ ያህል ነበር፡፡

የሰ/ት/ቤቱ ጽ/ቤት ሦስት በአራት የሚያህል ዙሪያው ቆርቆሮ የሆነ ለስራ ማስኬጃ ፈጽሞ የማያመች ነበር፡፡

በወቅቱ የነበሩ ንብረቶች

  • መጸሐፍ ቅዱስ ብዛት ስድስት
  • ዩኒፎርም በሁለት አይነት ቀለም ብዛቱ ከሠላሳ ሁለት ያልበለጠ

ሰ/ት/ቤቱ የነበረው ከፍተኛ የገንዘብ፣ የጽ/ቤት ፣ የጽሕፈት መሳሪያ ችግር በመ/ር ሚሊዮን አሳሳቢነት ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር የጽሕፈት መሳሪያ ተሟልቶበታል፡፡

በ1984 ለ ሰ/ት/ቤት አንድ መቶ ሃያ የሚደርስ ዩኒፎርም በወቅቱ የነበሩት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ፀባቴ ተ/ሚካኤል ፋንታሁን ከምዕመናን(ቤት ለቤት በመሄድ) ወደ አስር ሺህ የሚደርስ ብር በመሰብሰብ እና አባላት ራሳቸው በመስፋት ለጥምቀት በዓል አገልግሎት ተሰጥቶበታል፡፡

የተምሮ ማስተማር ኮርስ በወቅቱ በነበሩ የሰ/ት/ቤቱ መምህር አባ ገ/ማርያም አስተባባሪነት ለአንድ ወር ያህል ከሰዋሰወ ብርሃን በመጡ መምህራን ተሰጥቷል፡፡ ይህም ለሦስት ወራት ለሚቆይ መደበኛ ኮርስ መጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡

የጽዋ ማኅበራትና የወንጌል ጉባኤያት በሰ/ት/ቤቱ ም/ሊቀመንበር ሥር አንድ ክፍል ሆኖ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ይህም ከተሃድሶ እንቅስቃሴ ጠብቋል፡፡

የሰ/ት/ቤቱ መደበኛ የጸሎት መርሐ ግብር የተጀመረው በዚህ ዘመን ነው፡፡

በ 1988 ዓ.ም የሰ/ት/ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ከካቴድራሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጋር በመጣመር መንፈሳዊ መጻሕፍትን ከሰ/ት/ቤታችን ዓለማዊ መጻሕፍትን ደግሞ ከት/ቤቱ በማምጣት ተቋቋመ፡፡

ከ1990-2000 ዓ.ም   

የሰ/ት/ቤቱ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚሰጠው ትምህርት ቋሚ ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶለት ወደ ተግባር ገባ፡፡

የሰ/ት/ቤቱ የመጀመሪያ ካሴት ታተመ፡፡

የሰ/ት/ቤቱ ሕጻናት እና ማዕከላዊ ክፍል በዕድሜ በመከፋፈል ቀዳማይ፣ ካልዐይ፣ ሣልሳይ፣ አድርጎ በማዋቀርና ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት ለሕጻናት ት/ት መስጠት ቀጥሏል፡፡

አባ ፍቃዱ የተባሉ አባት የነበራቸውን በርካታ መጻሕፍት እንዲደራጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ፡፡

በ1992ዓ.ም ለወረብ አገልግሎት የሚሆን 27 ጥንድ ድርብ ተዘጋጀ፡፡

የውጭ ግንኙነት በአዲስ አበባ፣በኢትዮጵያ እንዲሁም ውጭ ሀገር ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስኬታማ ግንኙነቶች ይደረጉ ነበር፡፡

የሰ/ት/ቤቱ ደንብ ማሻሻይ ተደረገበት፡፡

ከ2000ዓ.ም

ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገለውን ወንበር በሰ/ት/ቤቱ አባላት፣ደጋፊ ምዕመናን አስተዋጽኦ ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በላይ የፈጀ አራት መቶ የሚደርስ ወንበር ተሰራ፡፡

አንድ መቶ ዩኒፎርምና ሰባ ሦስት ጥንድ ድርብ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደረገ፡፡

መስማት የተሳናቸው አባላትን በቋንቋቸው እንዲማሩ መርሐ ግብር ዘርግቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት(2008) ሁለት መቶ አምሳ የሚደርስ ዩኒፎርም ተዘጋጀ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት የሚገኙ አባላት ቁጥር ሁለት ሺህ አምስት መቶ ደርሷል፡፡

የሰ/ት/ቤት ፍሬዎች

የአባላት መንፈሳዊነት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ጊዜ ነው፡፡

ክፍለ ማርያም ደምሴ፡ ከአባልነት እስከ ሊቀ መንበርነት ደረጃ ሲያገለግል ነበር፤ ይህ ለመናፍቃን ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ብዙ ምዕመናንን ከመነጠቅ የታደገ ነው፡፡ በመጨረሻም ቤት ንብረቱን ትቶ እንደመነነ ይነገራል፡፡

እማሆይ ፍቅርተ ማርያም በቀለ፡ የሰበታ ቤተ ደናግል እመ ምኔት

እማሆይ እህተማርያም ይፍሩ፡ የደብረ ወገግ አባ ሳሙኤል ገዳም እመ ምኔት

እማሆይ ጽጌ ማርያም (አይናለም አስፋው)፡ በጊሸን ማርያም በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፡፡