ዘወረደ / ጾመ ሕርቃል

የመጀመሪያ የዐቢይ ጾም መግቢያ እሑድ ዘወረደ ይባላል ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡

«ዘወረደ» ማለት «የወረደ» ማለት ነው፡፡  አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህም  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር፤  ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ የሚታወስበት፣ የሚነገርበት  የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት   ነው፡፡

ዮሐ.3፥13፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሰረት “ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ”ገላ 4፥4 እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጠፋውን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መውረዱን የምናዘክርበት ነው።

ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ጾመ ሕርቃል ተብሎም ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም  ፤ ተስፋ አበው ፤ ትንቢተ ነቢያት ፤ ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ፤ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው።

ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡

ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪም በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡

በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡

ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል።

እኛም በዚህ በዐቢይ ጾም የለመነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀር እንዲከናወንልን ጾምን ገንዘባችን እናድርግ።

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org