📖ከንግግር የሚበልጥ ዝምታ

‹‹ከመቀየም ይልቅ የዋህነት የምትወድ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የትግስትህ መጠኑን አውቅ ዘንድ የአፍ መዝጊያ ቁልፍ የሆነች ዝምታን ስጠኝ››ይላሉ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ። ጌታችን አይሁድ በሐሰት ክሶች ደጋግመው ሲከሱት፤ ሲሰድቡት፤ሲዘብቱበት የታገሰውን የትዕግስቱን መጠን እንዴት ልንረዳው እንችላለን?

ባላጠፋኸው ስትከሰስ፤ያላደረከውን አድርገሃል እየተባለ ለሞት በሚያደርስ ክስ ስትወቀስ በዝምታ መሸከም እጅግ ከባድ ነው፡፡እናም በብስጭት እና በምሬት ራስህን ለመከላከል መሞከርህ አይቀርም፡፡ምናልባትም ከመናገር አልፈህ ከሳሾችህን፤ የሚሰድቡህን፤ የሚተፉብህን ሁሉ መሬት ተሰንጥቃ እንድትውጣቸው ማድረግ ብትችል ከማድረግ አትመለስም፡፡

ጌታችን ግን ሁሉን ማድረግ ሲቻለው በዝምታ ተቀበለ፡፡‹‹ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው?ይህ ያህል ትዕግስት እንደምን ያለ ትዕግስት ነው?›› እያልን በቅዳሴያችን ከማድነቅ በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡

የጌታችን ዝምታ ከአይሁድ ንግግር ይልቅ የጲላጦስን ልብ ገዛው የጌታችን ትዕግስት ጲላጦስን አስጨነቀው፡፡እንደ ሎሎች ተከሳሾች ሕይወቱን ለማዳን በገዢው ፊት ዕንባ የማይማጸን ክሶቹን ለማስተባበል የማይሞክር ከሳሾቹን መልሶ እየከሰሰ ራሱን ነጻ ለማውጣት የማይፍጨረጨርበሰንሰለት ታስሮ እየተጎተተ እንኳን ከሚጎትቱት ጋር የማይታገል ሞት ሊያስፈርድበት በሚችል ወንበር ፊት ቀርቦ በፍጹም እርጋታና ሰላም የሚቆም ተከሳሽ ከጌታ በቀር አይቶ የማያውቀው ጲላጦስ ከሊቃነ ካህናቱ ጩኸት በላይ በናዝራዊ ዝምታ ተማረከ፡፡ማር 15 4-5

ጲላጦስ ከግቢው ውጪ ቆመው የሚጮኹት አይሁድ ወደ ጎን ትቶ ጌታችንን ለብቻው መረመረው፡፡‹‹ጰላጦስም እንደገና ወደ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው፡፡ኢየሱስም መልሶ፡-አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነው ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው››(ዮሐ 18 32-35) ለመናገርም ጊዜ አለውና ጌታችን መልስ ሰጠ፡፡ምላሹ ግን ጥያቄ ነበር፡፡

የጌታችን መልስ ከላይ ሲታይ‹እንዴት እንዲህ ይላል?››የሚያሰኝ ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ጌታችን ይህንን ያለው የጲላጦስ ጥያቄ ሁለት መልስ ያለው ስለሆነ ነው፡፡‹‹ንጉሥ ነህ ወይ? ለሚለው ጥያቄ መንፈሳዊ ትርጉሙ ከሆነ እርሱ ከክርስቶስ እንደመሆኑ ‹አዎን አንተም አልከው›የሚያሰኝ ነው፡፡ ቄሳርን የሚጋፋ ንጉሥ እንዳይነሳ በሚፈሩት በሮማውያን እይታ ከሆነ ደግሞ ጌታችን‹ንጉሥ አይደለሁም› ሊል ይችላል፡፡

ጲላጦስ በጠየቀው ጊዜ ‹ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ንገሩህን? ማለቱ ጥያቄው ከራስህ የመጣ ከሆነ ንጉሥ አይደለሁም እንድልህ አይሁድ የነገሩህን ብቻ ይዘህ ከሆነ ደግሞ ‹‹መሲሑ ንጉሥ እኔ ነኝ›› ብዬ ለይቼ እመልስልህ ዘንድ የጥያቄህን መነሻ ንገረኝ እንደማለት ነው፡፡

ጰላጦስ የጌታችንን አጠያየቅ ስለተረዳ በአይሁድ ዘንድ ያለው ነገር ለእርሱ እንደማይገደው በማሳየት‹‹እኔ አይሁዳዊ ነኝን?ወገኖችህ የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ ምን አድርገሃል?›› አለው፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹‹መንግስቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም መንግስቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎች ይዋጉልኝ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግስቴ ከዚህ አይደለችም›› አለው፡፡

ጌታችን በዚህ መልሱ ሰማያዊ ንግሥናውንም ምድራዊ ሥልጣንን የሚፈልግ ንጉሥ አለመሆኑን በአንድ ላይ አስረዳ፡፤ ‹‹መንግስቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም››ብሎ አይሁድ እንደሚከሱት ለቄሳር በተቀናቃኝነት የሚያሰጋ መንግስት እንደሌለው አስረዳ፡፡ ይህም መልስ የጰላጦስን ልብ የሚያሳርፍ ነው፡፡ምክንያቱም የሀገረ ገዢው ዋነኛ ጭንቀት ኃላፊ የቄሳር ሥልጣን እንዳይነካ ማድረግ ላይ ብቻ ነው፡፡

‹‹መንግሥቴ›› የሚለው ቃል ደግሞ የክርስቶስ ንጉሥነትን ያሳያል፡፡የቤተክርስትያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘቄሳሪያ እንዳለው‹‹የክርስቶስ መንግሥቱ በምድራዊ ሕግጋት የማይወሰን በአምላካዊና ሰማያዊ ትምህርቱ ነፍሳትን ብሩሕ ስላደረገ ብቻ ዓለም ሁሉ የተስፋፋ መንግሥት ነው››በዙህም መሰረት መንግሥቱ ተብለን የተጠራነው በስሙ አምነው የተከተሉት ሐዋርያት በእነርሱ መሠረትነት የተመሠረተችው ቤተክርስትያን በስሙ ያመንን እኛ ክርስትያኖች ነን፡፡

መንግሥቱ የተባልነው በእርሱ ያመንን እኛ ክርስትያኖች ከሆንን ‹‹መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም››የሚለው ቃልስ እንዴት ይታያል? እኛ ያለነው በዚህ ዓለም አይደለምን?የሚልጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ጌታችን መንግሥቴ ‹‹ከዚህ ዓለም አይደለችም›› አለ እንጂ ‹‹በዚህ ዓለም አይደለችም››አላለም፡፡በስሙ የምታምን ቤተ ክርስትያንና ክርስትያኖች ሁሉ‹በዓለም›ናቸው እንጂ‹ከዓለም› አይደሉም።

✍ሕማማት
ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ገጽ 177

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.comS/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org