ሐዋርያው ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ፦

የቅዱስ ማርቆስ ወላጆች ስም የአባቱ ስም ቅዱስ አርሰጡጳውሎስ ሲሆን የእናቱ ስም ቅድስት ማርያም ይባላል፡፡ አባቱ ባለጸጋና ያላገባ ነበር የአባቱ ስም ስምዖን ይባል ነበር፡፡ ስምዖንም አርስጡጳውሎስን እንዲያገባ ይገፋፋው ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በቤቷ እንግዶችን የምትቀበልና የምታስተናግድ ማርያም የተባለችውን የወንጌላዊ የቅዱስ ማርቆስ እናት አገኘ ፡፡ እሱም እሷም ሳያስቡት ባዩት ሕልምና በመፈክረ ሕልም (በሕልም ፈቺዎች) በተነገራቸው መሠረት ተገናኝተው የትዳር ሕይወትን መሠረቱ፡፡


አርስጡጳውሎስ ከከበረውና በባለጸግነቱ ከታወቀው ከአባቱ ካገኘው ሀብት ለነዳያን የሚመጸውት፣ ዐሥራት በኩራት የሚያወጣና ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር የሚጸልይ ደግ አባት ነበር፡፡ እሱም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ዘመድ የአክስት ልጅ እንደሆነና ቅዱስ ጳውሎስም በመልአክቱ የጠቀሰው እሱን እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ “አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል” ቈላስይስ 4፥10 ነገር ግን አንዳንድ የግሪክ፣ የላቲን፣ የግእዝና የኮኘት ትርጉሞች “የበርናባስ የወንድሙ ልጅ” የሚለውን ሐረግ አይጠቅሱም ይህም ምንአልባት አንዳንድ የግሪክ ቃላት ከአንድ በላይ ትርጉም ስላላቸው ይሆናል፡፡


የቅዱስ ማርቆስ እናት ማርያም ተብለው ከተጠሩት ብዙ ቅዱሳት አንስት መካከል አንዷ ናት፡፡ ቤቷ በኢየሩሳሌም እንደነበረና ምዕመናንም በቤቷ በጸሎት ይሰበሰቡ እንደነበር በሐዋ 12-12-17 በሰፊው ተገልጾአል፡፡ ይህም በጥንት ወይም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ካሉት መንፈሳውያኑ ሴቶች (ቅዱሳት አንስት) ከፈተኛ ቦታ ያላት እንደነበር ያመለክታል። በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን በአንድነት በክርስቶስ ስም ይሰባሰቡ ስለነበር ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኙትም በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ “በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ”፡፡ ሐዋ 11-26


የቅዱስ ማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ነበር፡፡ በማርቆስ እናት በማርያም ቤት በጽርሐ ጽዮን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጸላቸውና መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ እንዲህ ተጽፏል “አመ ሣልስት ዕለት ተንሥአ እሙታን ወቦአ ኀበ ሀለው አርዳኢሁ ጉቡአን ወአስተርእዮሙ በጽርሐ ጽዮን … ወበ ፶ ዕለት ፈነወሎሙ መንፈሰ ቅዱስ ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኩሉ በሐውርት … በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የተሰበሰቡ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ገባ በጽርሐ ጽዮንም ታያቸው …በ50ኛው ቀንም
በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው በአገሩ ቋንቋ ሁሉ ተናገሩ”


በኢየሩሳሌም ውስጥ የማርያም ቤት የሐዋርያት መገናኛና መሰባሰቢያ ነበር፡፡ ስለዚህም የማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኀብረት መለያ ሆኖ ይታወቃል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ የተወለደው በአባቱ ወገን ከነገደ ይሁዳ ሲሆን የተወለደበት ቦታ ከአምስቱ የምዕራብ ከተሞች አንዷ በሆነችው በሊቢያ በሲርኔ ይኸውም አብራይሮሎስ በተባለች ትንሽ መንደር ተወለደ፡፡ ትውልዱ ዕብራዊ ቤተሰቦቹም ይኖሩበት የነበረው በሰሜን አፍሪካ በጥንታዊቱ ፔንዲፓሊስ ሲሪኒካ (ቀሪና) በተባለችው በዛሬው ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ደማቅ ከተማ ስለነበር ቅዱስ ማርቆስ አፍሪካዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው የሚሉ አሉ፡፡( ሉሌ መላኩ ቤተክርስቲያንን እወቅ)


የቅዱስ ማርቆስ የስሙ ትርጓሜ ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው ንብ ከሁሉ እንዲቀስም አስቀድሞ ከክርስቶስ በኋላም ከሐዋርያት ተምሮአልና፡፡ አንድም አንበሳ ማለት ነው አንበሳ ለላሕም ጌታው እንደሆነ እንዲሰብረው እርሱም አምልኮተ ላሕምን ከግብጽ አጥፍቷልና፡፡ አንድም ካህን ልዑክ ማለት ነው፡፡ ብሥራተ ማሪ ማርቆስ ይላል የተደራረበ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ካህን ማለት ነው፡፡


የቅዱስ ማርቆስ ሁለተኛ ስሙ ዮሐንስ ይባላል። “ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለ ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ” ሐዋ12፥12


የቅዱስ ማርቆስ ተክለ ቁመናና መልክ
እንዲሁም አለባበሱን እንዲህ በማለት ተጠቅሷል፡፡ “የግብጽና የኢትዮጵያ ኮከብ ብፁዕና ቅዱስ ማርቆስ መልኩ ቀይ ቅንድቦቹም ከበድ ያሉ ዓይኖቹም እንደሰማያዊ ኀብር የጠሩ ቁመቱ ረጅም ከአንገቱም ስር ስርጉድ የሆነ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ራሰ በራህ የሆነ ቀሚስ (ልባልባውም) በወገቡ የሆነ የግብጽና የኢትዮጵያ አባት የቅዱስ ማርቆስ ምልክቱ ይኸ ነበር፡፡


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዊ በሚሰብክበት ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ ወጣት ነበር፡፡ ልቦናው የቀና እንደሆነም አውቆ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የመጀመሪያ አድርጐ መረጠው ከዚህ በኋላ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኖ ጌታ ወንጌልን ሲያስተምር፤ ተአምራት ሲያደርግ ያስተውል ነበር ፡፡ በምሴተ ሐሙስ በአይሁድ ሲያዝና መከራን ሲቀበል ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም መንገድ ላይ ሆኖ በርቀት ድርጊቱን ይከታተል ነበር፡፡ በወንጌሉም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ስለ አርሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ “ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጐበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ”፡፡ ማር14-51-52
ቅዱስ ማርቆስ በቤቱ መጻፊያ ይዞ የጌታን ተአምራት ይጽፍ ነበር፡፡ የግሞ ሊናሮስ የሚባል አገልጋዩን ጌታን እንዲከተልና የሚያደርገውንም ተአምራት እንዲጽፍ ያደርግ ነበር ፡፡

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዓለ ፋሲካን ሲያከብር ተከተሉት” የተባለውም ቅዱስ ማርቆስን እንደሆነ እንዲህ ተጽፍል፤ “ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እነዲህም አላቸው ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውሃ የተሸከመ ሰውም ያገኛችኋል ተከተሉት የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ፣ ከደቀመዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት፡፡ እርሱም በደርብ ላይ ያለውና የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፣ በዚህም አሰናዱልን፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ ፋሲካም አሰናዱ” ማር 14፥13-15፤ ሉቃ 22፥10-12።


ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም የእናቱ የማርያም ቤት የደቀ መዛሙርቱ መገናኛና መሰባሰቢያ ስለነበር ደቀመዛሙርቱን የበለጠ እንዲያውቃቸውና እንዲቀርባቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ በተለይም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ባለው የጠበቀ ዝምድናና ቀረቤታ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት ልጅ በመሆንና ለአገለግሎቱም ፍጹም መንፈሳዊና እውነተኛ የክርስቶስ ምስክር ለመሆን በቅቷል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በልጅነቱ በኢየሩሳሌም ለመኖር በመታደሉ በዚያም ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት የማግኘት ዕድል ገጥሞት ነበርና የዕብራይስጥ፣ የላቲንና የግሪክ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌልን መስበክ የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ያስተምር ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት አንደተገለጸው ቅዱስ ማርቆስ ከቅድስ ጳውሎስና ከቅድስ በርናባስ ጋር ይሰበክ ነበር፡፡ ከዚያም በፊት ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አስተምሮአል፡፡


ቅዱስ ማርቆስ ንጹሕና ድንግል መሆኑን መልካምነቱንና ትምህርቱን ተመልክቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ለግብጽና ለአካባቢዋ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ ሾመው፡፡ በግብጽ አገሮች በሎኒያ፣ በመርቅያ፣ በጣውንቄ፣ በበርቃ ለመጀመሪያ አስተማረ እርሱ ነው፡፡ ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ አዳኝ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንንም አስተማራቸው፡፡ ሁሉም የዚያች አገር ሰዎች ልቡናቸው የደነደነ ነበሩ በርኵሰት ሁሉ የተሞሉ አማልክትንም ያመልኩ ነበር፡፡ ሰይጣንን በማምለክም ይኖሩ ነበር፡፡ በየቦታው በየመንገዱም ሁሉ ምኩራቦችን የአማልክትን ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ መድኃኒትን፣ ዝሙትንም ያደርጉ ሕጻናትን ይገድሉ በደማቸው መድኃኒትን ያደርጉ ነበር፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሐዋርያት በሄደ ጊዜ አስቀድሞ ብርቃ ደረሰ፡፡ ዘመዶቹ ከእነርሱ ወገን ናቸውና፡፡ እግዚአብሔርን ቃልም አስተማራቸው በመካከላቸው ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ በሽተኞችን ፈወሳቸው ለምጻሞችንም አነጻቸው፤ በእርሱ ላይ በአደረው ጸጋም አጋንንትን አስወጣ፤ ብዙዎችም በትምህርቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ አምላኮቻቸውንም (ጣዖቶቻቸውንም) ሰባበሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጠመቃቸው፡፡


በዚያ ቦታም ወደ እስክንድርያ ይሄድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተገለጠለት፡፡ በዚያም መልካም ተዘራባት ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ወንጌላዊው ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ለጦርነት እንደተዘጋጀ ጎልማሳ ሆነ ወንድሞቹንም ሰላም አላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ቦታ ቅዱስ ወንጌልን አስተምር ዘንድ ወደ እስክንድርያ እንድሄድ አዝዞኛል” አላቸው፡፡ እነርሱም ሸኙት በመርከብም ተሳፍሮ ወደ እስክንድርያ ሄደ በደረሰ ጊዜም ወደ ከተማው በር ገባ የጫማው ማሠሪያም ተቆረጠ “በቅንነትም መንገድ ፈጠነች” አለ በዚያም ከከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበር፡፡ ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዩናኒም ቋንቋ “ኢታስታያስ” አለ ትርጓሜው አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን” አለው “እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም” አለ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በጣቶቹ ላይ መራቅ ጨመረና አፈር ወሰደ ያን ጫማ ሰፊ ቀባው “በሕያው አግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ስም አጅህ ትፈወስ” አለው፡፡ ስለዚህም ተፈወሰች ጫማ ሰፊውም በሥልጣኑ በቃሉ ያደረገውን ድንቅ ተአምር በተመለከተ ጊዜ “የቸሩ አምላክ አገልጋይ ሆይ እለምንሃለሁ ዛሬ ውጣና በቤቴ ዕረፍ በአንድነትም እንመገብ መልካም ነገርን አድርገህልኛልና” አለው፡፡ ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ተደሰተ፡፡

“እግዚአብሔር ሰማያዊት የምትሆን ሕይወት ኀብስትን ይስጥህም” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ አስገባው፡፡ ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ ገባለት። “የእግዚአብሔር በረከት በዚህ ቤት ይኑር” አለ፡፡ ወንድሞች በአንድነት ጸለዩ ከጸሎት በኋላም ተቀመጡና ደስ እያላቸው ተመገቡ፡፡ ጫማ ሰፊውም ቅዱስ ማርቆስን “አባት ሆይ እለምንሃለሁ ይህንን የምትለው እንዴት ነው፤ ይህ ስምስ ምንድን ነው ይህ እንደዚህ የሚቻለው ነው” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ ላየው እሻለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ አሳይሃለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ ነው እያለ የወንጌሉን መጀመሪያ አስተማረው፡፡ በትንቢት ስለ እርሱ የተናገሩትንም ከመጻሕፍት ተናገረ፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ የምትለውን ይህን መጽሐፍ እለምንሃለሁ ከረጅም ዘመን ጀምሮ የግብጻውያን ልጆች እንደማይማሩበት አልሰማህምን” አለው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔርን ነገር ይነግረው ዘንድ አስቀደመ “የዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ናት” አለው ጫማ ሰፊውም የቅዱስን ነገር በሰማ ጊዜ በእግዚአብሔር አመነ ለእርሱም አመለከተው ከእርሱም ኃይላትን ተአምራትን አየ እርሱ ቤተሰቡ፣ ከአገሩ ሰዎችም ብዙዎቹ ተጠመቁ፡፡ የጫማ ሰፊው ስምም አንያኖስ ይባላል፡፡ ያን ጊዜም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምዕመናን በዙ፡፡ የአገሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜም “ይህ የገሊላ ሰው ከዚህ አገር ደርሷል፤ የአማልክትን እጅ መንሻ ለውጧል፤ እንዳይመለኩ ከልክሏል” አሉ ሊገሉትም ፈለጉት ይጥሉት ዘንድም በእርሱ ላይ ፍለጋን አበዙ ብፁዕ ማርቆስ ይህን በተረዳ ጊዜ አስተማራቸውና አንኖስንም ኤጲስ ቆጾስነት ሾመላቸው ሦስት ካህናትንም ሾመላቸው ስማቸውም ወልዮስ፣ መሪደስና በሪሞስ ይባላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ሰባት ዲያቆናትን አንድ ላይ አሥራ አንድ ሰዎችን ሾመላቸው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ብርቃ ወጣ ለዓመታትም በእርሷ ተቀመጠ፡፡ በሁሉም አገራት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትን ሾሞላቸው ወደ እስክንድርያም ተመለሰ፡፡ በእግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ጸጋና ማመን በዛባት የላም ቦታ በሚባለው በባሕሩ ዳር ካለው ቦታም ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከዚያ ቦታ ከዓለቱ ሥርም ታላቅ ድንጋይ ቁራጭ ነበር፡፡ ጻድቁም ስለ ምዕመናን መልካም ሃይማኖት እግዚአብሔርን አመሰገነ ብዙ ዘመን በቆየ ጊዜም ክርስቲያኖች በዙ አማልክትንም ተዘባበቱባቸው፤ አረማውያንንም ናቋቸው፡፡

አረማውያንም ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ወደ አገራቸው እንደ ደረሰ ተረዱ፡፡ ከሰሙት ተአምራት ብዛት የተነሳ ልቡናቸው በቁጣ ተሞላ እርሱ ሕመምተኞችን ይፈውስ፣ ለምጻሞችንም ያነጻ፣ ደንቆሮዎችንም እንዲሰሙ፣ እውራንንም እንዲያዩ ያደርጋል መልካም ተስፋንም ያስተምራቸው ነበር ይይዙት ዘንድም ፈለጉት፤ በየቤታቸውም ጥርሳቸውን ያፋጩ ነበር፤ በአማልክቱ ምኵራብም “እኛ ለዚህ ጠንቋይ ተሸነፍን” እያሉ ጮኹ፡፡ ምዕመናን የሚያከብሩት ዕለት ሰንበት የተባረከው የፋሲካ በዓልም በሰንበት ቀን ሆነ፤ ይህም ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን ነው፡፡


በዚያች ዕለትም በእነርሱ ዘንድ የሰራቢስ የልደቱ ቀን ነበር፡፡ ያማረች ዕለትን አገኙ ሰላዮችን ላኩና ያዙት፡፡ እርሱን የቅዳሴ ጸሎት ሳይፈጽምም በሰንሰለት አሠሩት በላሞች ቦታ እንጐትተው እያሉም እንደ አውራ ፍየል በየመንገዱ ጐተቱት፡፡ ቅዱስ ማርቆስም በጐተቱት ጊዜ አግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በተቀደሰው ስምህ መከራን እንድቀበለ አዘጋጅተኸኛልና አመሰግንሃለሁ” አለ፡፡ ሥጋውም በየመሬቱ ተቆራረጠ ደሙም በየዐለቱ ፈሰሰ፡፡


ሌሊት ሲሆንም ይገድሉት ዘንድ እስከሚሰበሰቡ ድረስ ወደ እስር ቤት አስገቡት፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲሆንም በሮች ተዘግተው ጠባቂዎችም ተኝተው ሳሉ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክም “የግብጽን አገራት ሁሉ የምታረጋጋ የእግዚአብሔር አገልጋይ ማርቆስ ሆይ ስምህ በሰማይ ባለ የሕይወት መጽሐፍ ተጽፏል ከሐዋርያት ቁጥርም ተቆጥሮአል፤ መታሰቢያህም አይረሳም፤ በምድርም ስፍር ቁጥር የሌላትን ሥልጣን፣ ጸጋ ኃይል እነሆ ሰጥቶሃልና፤ ነፍስህ በሰማይ ይሆናል ሥጋህም በመሬት አይጠፋም” አለው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ይህን ምሳሌ በተመለከተ ጊዜ እጆቹን ወደ ሰማይ አነሣ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከፊትህ አልጣልኸኝም፣ ከቅዱሳን ማኀበርም ደምረኸኛልና አመሰግንሃለሁ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ ነፍሴን በሰማይ ተቀበላት፤ ከፊትህም አትተወኝ” አለ፡፡ ይህን በተናገረ ጊዜ ጌታችን አዳኝ ከሆነው ከሕማሙ በፊት በመቃብርም ከመጨመሩ አስቀድሞ በሐዋርያት መካከል እንደነበረ ሆኖ ታየው፡፡ “የመረጥሁህ ማርቆስ ሆየ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሁን፤ በወንጌል አስተማርሁህ፤ እነሆ መከራን ከመቀበሌ አስቀድሞ ከጓደኞችህ ከሐዋርያት ጋር አንደሆንሁት በአርአያ ተገለጥኩልህ፤ ከእነርሱ ምንም ጉድለት እንዳይኖርብህ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከጸጋህ ታላቅነት የተነሣ አመሰግንሃለሁ፤ በሥጋህ አንደነበርህ ሆነህ አንዳይህ የተገባኝ አድርገኸኛልና” አለው “ስለተቀደሰው ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ ትዕግሥትን አድለኸኛልና” ጌታችንም ሰላምን ሰጠውና በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማይ አረገ ፡፡ ሲነጋም የአገሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከእስር ቤትም አወጡት በሰንሰለትም አሰሩት፤ ዳግመኛም በላሞች ቦታ እንደፍየል እንጐትተው እያሉ በከተማው ጐተቱት፡፡


ብፁዕ ማርቆስም ምስጋናን አቀረበ በሰማይ ተገለጠ፡፡ በየአገሩ ከጎተቱት በኋላም ደሙ በየመንገዱና በየአደባባይዋ ሞላ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን በእጅህ ሰጠሁ” አለ፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላም ሚያዝያ 30 ቀን ዐረፈ፡፡ ሁሉም አረማውያን ቅዱስ ማርቆስ አንዳረፈ በተመለከቱ ጊዜም ሥጋውን በእሳት ያቃጥሉት ዘንድ አውበካልዮን በምትባል ቦታ ጽኑ እሳትን አነደዱ፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድም ጨለማና ቀዝቃዛ ነፋስ ሆነ፤ ፀሐይም ብርሃኑን ሰወረ፡፡ በዚች ዕለትም እስከ ምሽት ድረስ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ዝናምና ብርድም ሆነ፤ ከአገሩ ሰዎች ከሽማግሌዎች ብዙዎች ወደቁ ከእነርሱም ብዙዎቹ ሞቱ ያን ጊዜ ፈሩ ሂደወም ከአገሩ ሰዎች የቅዱሱን ሥጋ አኖሩት፤ የተዘባበቱበትም አሉ “ ታላቁ አምላክ ሆይ የዚህን ሰው ነፍስ ተቀበላት በዚች ዕለት የልደቱ ዕለት ናትና” አሉ፡፡ ምዕመናን ወንዶች ደረሱና የቅዱሱን ሥጋ ከእሳቱ ወሰዱት ጸሎት ወደሚጸለይበት ቦተም አደረሱት በእርሱ ላይም ተሳሉ፣ ምስጋናንም አቀረቡ እንደ ሥርዓታቸውም እንደ አገሩ ሰዎች ገነዙት በቆፈሩለት መቃብርም ቀበሩት፡፡ መታሰቢያውንም በደስታ፣ በምሥጋና አብዝተው አደረጉ፣ አበዙ በአገሩ መሠረታዊ ቦታም አስቀመጡት፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ በግብጽ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰ የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ ዕረፍቱ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በ30 ሠላሳኛው ቀን በታላቋ አገር በእስክንድርያ ሆነ ፡፡ ከሐዋርያውና ከወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡ በጸሎቱ ይማረን!፡


፡ ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያት ፤ ስንክሳር ፤ ክብረ ቅዱስ ማርቆስ ከሚለው መጽሐፍ።


“ሰላም ለማርቆስ ለማርያም ዕጓላ። ዘሰሐብዎ በአህባል ውስተ ዐፀደ ላሕም ከመ ዳቤላ። አመ አውዕዮቶ ፈቃዱ ለእሳት በነበልባላ። ዝናም ወአስሐትያ አጥፍኡ ማዕበላ። መብረቅኒ ለሥጋሁ ከለላ”። ትርጉም፦ በላም በረት ውስጥ እንደ ወይፈን በገመድ የሳቡት ለኾነ ለማርያም ልጅ ለቅዱስ ማርቆስ ሰላምታ ይገባል፤ ርሱን በእሳቲቱ ላንቃ (ወላፈን) ለማቃጠል በወደዱ ጊዜ ውርጭ እና ዝናብ ማዕበሏን አጠፋ፤ መብረቅም ሥጋውን ጋረዳት። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 30።