እንኳን አምላክን ለወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ለጸናች ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ለልደቷ መታሰቢያ ዓመታዊ የንግሥ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
የዕለቱ አንገርጋሪ፦ “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም እም ሐና ወኢያቄም ከመ ትቤዙ ነቢያት ወጻድቃነ አማን ተወልደት እመ ብርሃን”። ትርጉም፦ በእመቤታችን ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ ይኸውም ከሐና ከኢያቄም መወለዷ ነው ነቢያትና ጻድቃንን በልጇ ታድናቸው ዘንድ በእውነት የብርሃን እናት ተወለደች። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።
አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት፦ እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ቅዱስ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ቅድስት ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና። እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኀዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።
ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው። በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለቅድስት ሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት፡፡ ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርም አመሰገኑት።ኢያቄም ለሚስቱ ሐና እንዲህ አላት “ሰማያት ሲከፈቱ አየሁ፤ ነጭ ወፍ መጣ በራሴ ላይም አረፈ” እንደዚህም ሁሉ ሐናም “ርግብ በራሴ ላይ ስትቀመጥብኝ በማሕፀኔም ስታድር አየሁ ገባች” አለችው።
ከዕለታት በአንድ ቀን ሐና እና ኢያቄም ወጥተው ወደ ተክል ቦታ ገቡ፡፡ ቁመውም ሲጸልዩ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ልጅ ስለሌላቸው ፈጽመው አዘኑ፡፡ከሐዘናቸውም ብዛት የተነሳ አንቀላፍቷቸው ተኙ፡፡ ሐናም ተኝታ ሳለች በባሏ በኢያቄም እጅ በትር እንደተያዘች ያችም በትር አብባ አፍርታ አየች፡፡ሁለተኛም ኢያቄም በሐና እጅ ከፍሬ ሁሉ የሚመስለው የሌለ የሚጣፍጥ መልካም ፍሬ ተይዞ አየ፡፡ከእንቅልፋቸው በነቁ ጊዜ ደስ አላቸው በመኝታቸው ስላዩት ነገር እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡
ከዚህም በኋላ ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን ብለው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ከዚህም በኋላ የከበረች ሕፃን ነሐሴ ሰባት ቀን ተፀነሰች፡፡የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ በቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ተሳለች።ከስድስት ወር በኋላም የብፅዕት ሐና መፅነስ ታወቀ። ዘመዶቿም ሰሙ ወደ እርሷ መጥተውም “የምንሰማው ይህ ነገር አውነት ነውን? ዘመንሽ ካለፈ በኋላ በአንቺ ላይ የተደረገው ነገር ምንድን ነው?” አሏት። ከሐና ዘመዶች ወገን የአርሳባን ልጅ የምትሆን አንዲት ዐይኗ ማየት የተሳናት አንዲት ሴት ነበረች። “የሰማሁት እውነት ነውን?” ብላ የሐናን ማኅፀን ዳሰሰች። “እህቴ ሆይ ሽማግሌ ስትሆኚ እንዴት ፀነስሽ” አለቻት። ዳግመኛም ማየት የተሳነው ዐይኗን ዳሰሰችው ያን ጊዜም ዐይኗ ተከፈተላት ብርሃንንም አየች። “ብፅዕት ሐና ሆይ ለአንቺ ብፅዓን ይገባሻል ፅንስሽ በማኅፀንሽ እያለ ገና ሳይወለድ በሽተኞችን የፈወሰ በግልጽ ከታየ ከማሕፀንሽ ከወጣማ ምን ያህል ይፈውስ ይሆን?”አሉ፡፡እንደዚሁም ሁሉ ብዙ በሽተኞች መጥተው እየዳሰሱ ከበሽታቸው ይፈወሱ ይድኑም ነበር። ይህ ነገርም በእስራኤል ሽማግሎዎች ሁሉ ዘንድ ዕፁብ ድንቅ ሆነ።
ቅድስት ሐናም የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ በግንቦት አንድ ቀን ከፀሓይ ይልቅ ፈጽማ የምታበራ ሴት ልጅ በሊባኖስ ተራራ ላይ ወለደች፤ የመልኳም ደም ግባት ከመዓር ከሦከር ይልቅ ደስ ያሰኛል፤ የመዓዛዋም ሽታ ከሽቱ ሁሉ ይበልጣል። ዘመዶቿና ጐረቤቶቿም በሰሙ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አላቸውና ተሰብስበው ወደስዋ መጡ ወደሷም መጥተው ልጅዋን ባዩ ጊዜ ፈጽመው አደነቁ እርስ በርሳቸውም “እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም” ተባባሉ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ ላይ አድሯልና የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና። ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ ያችንም ብላቴና ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው። በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናትና ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን። በዘአዝፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት”። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት ወንጌል ማቴ 1፥1-18።
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን። ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ”። መዝ 86፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 4፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 8፥13፣ የሐዋ ሥራ 7፥44-51 ወይም የሐዋ ሥራ 1፥12-15 የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የልደታ ለማርያም በዓል፡፡ ለሁላችንም ይሁንልን።
ምንጭ፦ ተአምረ ማርያም፣ ድርሳነ ቅድስት ሐና ወኢያቄምና የግንቦት 1 ስንክሳር ።

