ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ

ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ


ኤርምያስ የስሙ ትርጉም ከእግዚአብሔር የተላከ ብርሃን ማለት ሲኾን፤ ትውልዱ ከነገደ ሌዊ በመኾኑ ክህነትን ከነቢይነት አስተባብሮ የተገኘ ነው። ይህም እውነተኛ ነቢይ የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ማስተማር ጀመረ። ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዐሥራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመን መንግሥቱ እስከሚፈጸም በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት ጊዜ ያስተምር ነበር።


ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ እንደ ቅዱስ ኢሳይያስ በበትር የምትመሰል የቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ በለውዝ በትር አምሳል ተመልክቷታል (ኤር1፥11)። ይኽ ብቻ ሳይኾን ከኹለት (ሁለት) ደቀ መዛሙርቱ ከባሮክና ከአቤሜሌክ የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነች ዐጽቀ በለስ በንስር አንገት የተላከለት ታላቅ ነቢይ ነው።


ስለ ራሱ እንዲህ ሲል ራሱ ተናገረ “የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ በእናትህ ማሕፀን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ ከእናትህም ማሕፀን ሳትወጣ መረጥኩህ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ” አለኝ። ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አስረዳቸው “ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ ያለዚያ የከላውዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያሥነሣዋል ይማርካችኋልም” እንደቃሉም ሆነ። ሁለተኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ። ደግሞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና ሠላሳ ብር እንደሚወስድ ተናገረ። ስለ ብዙ ሥራዎችም ተናገረ አይሁድ ግን ሊገድሉት ወደው ገርፈው አሥረው በጒድጓድ ውስጥ ጣሉት እግዚአብሔርም አዳነው። እርሱ ግን ስለእነርሱ ይለምንና ይማልድ ነበር እግዚአብሔርም “ስለ እርሳቸው ወደእኔ አትማልድ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና” አለው።


ናቡከደነጾርም ኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልማረከውም። ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት የግብጽን ሰዎች ሲያጠፋቸው የነበሩ በግብጽ ወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በእርሱ ጸሎት እግዚአብሔር አጠፋቸው።


ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲያስተምር ኖረ። የትንቢት ወራትም በተፈጸመ ጊዜ አይሁድ በደንጊያዎች ወገሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ግንቦት 5 ቀን ሰጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የግንቦት5 ስንክሳር እና መጽሐፈ ተአምኆ ቅዱሳን (የቅዱሳን ሰላምታ) ንባቡና ትርጓሜው መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ከሚለው መጽሐፍ።


“ሰላም ለኤርምያስ እምነቢያት ዐቢያን። ወልደ ኬልቅዩ ካህን። አረፍተ ብርት ተሰምየ ወዓምደ ኀፂን። እስመ በእንተ ክርሰቶስ መድኅን። እስከ ወገርዎ እስራኤል በዕብን”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የግንቦት5።


የዕለቱ ምስባክ፦ “ላዕሌከ ተገደፍኩ እማኅፀን። እምከርሠ እምየ አንተ አምላኪየ። ኢትርኀቅ እምኔየ እስመ አልጸቁ እትመንደብ”። መዝ 21፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 2፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 7፥51-55። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 21፥33-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።