ቅዱስ አትናቴዎስ

ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን)ን ቀብቶ የሾመላት የእስክድርያ ሃያኛው ሊቀ ጳጳስ ታላቁ አባት ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው ?

ቅዱስ አትናቴዎስ የተወለደው በ298ዓ.ም በእስክድርያ ነው። እርሱም ከመምህር ከሚማሩ ሕፃናት ጋራ እያለ እርስ በእርሳቸው በመጫወት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየሠሩ ከእነርሱ ውስጥ ዲያቆናትን ኤጲስቆጶሳትንም ሲያደርጉ እሊያን የክርስቲያንን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው። እርሱም “አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም” ብለው ከለከሉት እርሱ ግን “ክርስቲያን እሆናለሁ” አላቸው እነርሱም ደስ ተሰኙበት። ያን ጊዜ ወስደው በሊቀ ጳጳሳት አምሳል አደረጉት ከበታቹም ወንበር አድርገው ይሰግዱለት ጀመር። በዚያ ጊዜም ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ በዚያ አለፈ የክርስቲያን ልጆች ሲጫወቱ በአያቸውም ጊዜ አብረውት ላሉት “ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው” አላቸው።


አባቱም በሞተ ጊዜ ወደ አባ እለእስክንድሮስ መጣ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው። ከዚህም በኋላ የአባቱን ገንዘብ ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሕግ ሥርዓትንም ከአባ እለእስክንድሮስ ዘንድ እየተማረ ኖረ እርሱም ተወዳጅ ልጅ አደረገው። ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾመው የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ የተመላ ሆነ።


ስለ ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ ቤተ ክርስቲያን አጠራር በተመለከተ ሩፊኖስ የተባለው የዚያ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሚከተለውን ጽፏል።

የእስክንድርያ ክርስቲያኖች የእስክንድርያ 17ኛ ፖትርያርክ የነበረውንና በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ያረፈውን የተፍጻሜ ሰማዕት የቅዱስ ጴጥሮስን በዓል በየዓመቱ በታላቅ ሁኔታ ያከብሩ ነበር። በዚያን ጊዜ ፖትርያርክ የነበረው አባት እለእስክንድሮስ ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ በድንገት ወደ ባሕሩ ሲመለከት በዚያ የነበሩ ልጆች ጳጳስ፣ አጥማቂና ተጠማቂ እየሆኑ በባሕሩ ዳርቻ ሲጫወቱ ተመለከተ። መጀመሪያ የሕፃናት ጨዋታ ነው ብሎ አሰበ። ሁኔታቸውን እየቆየ ሲያየው ግን በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመውን መንገድ የተከተለና ከልጆች ጨዋታነት ያለፈ ነገር ሆኖ ታየው። በዚህ ጊዜ በመደነቅ አብረውት የነበሩት ካህናት ጋር በመካከር ልጆቹን ሁሉንም አስጠርቶ ምን እያደረጉ እንደሆነ ጠየቃቸው እርሱም ቅዱስ አትናቴዎስ ጳጳሳቸው ሆኖ ሌሎች ልጆች ደግሞ ተጠማቂዎች ሆነው ወደ እርሱ ሲቀርቡና እርሱ እያጠመቃቸው እንደነበረ ነገሩት።


አባ እለእስክንድሮስ በጨዋታ መልክ ሲያጠምቅ የነበረው “የጨዋታው ካህን” ምን እያለና እንዴት እንዳጠመቃቸው ሲጠይቃቸው የምሥጢራቱ አፈጻጸም መንገድ በትክክል እንደተፈጸመ በመገንዘቡ አብረውት የነበሩትን ካህናት ስለ ጉዳዩ ካማከራቸው በኋላ “እነዚህን ንጹሕ ልባቸው በመለኰታዊ ጸጋ የተጠሩትንና የተጠመቁትን ልጆች እንደገና ማጥመቅ አስፈላጊ አይደለም” ብለው በመወሰን ጥምቀታቸውን በማጽደቅ አስፈላጊ የሆኑ ቀጣይ ምሥጢራትን ፈጸመላቸው።ከዚያም ሌሎችን ሕፃናት ባርኮ አሰናበታቸው። አጥማቂውን ሕፃን አትናቴዎስን ግን ከእርሱ ጋር ይሆን ዘንድ ወደ መንበረ ፖትርያርኩ ወሰደው።


አባ እለእስክንድሮስም አትናቴዎስን በመንበረ ፖትርያርኩ የቤተ ክርሰቲያንን ትምህርትና ሥርዓት እያስተማረ አሳደገው፤ እርሱም ተወዳጅ ልጅ ሆነው። ከዚህም ጋር ሰዋስው፣ ፍልስፍና፣ ክሂሎተ ነቢብና ሌሎች በዘመኑ የነበሩ ትምህርቶችንም በሚገባ ተማረ። ቆይቶም ለመዓርገ ምንኵስና በቃ። በቅድስናው፣ በሞያውና በግብረ ገብነቱ እንከን የሌለው ወጣት አትናቴዎስ በ23 ዓመቱ ሊቀ ዲያቆን ሆነ። በዚያ ዘመኑ መዓርግ “ሊቀ ዲያቆን” ማለት የሊቀ ጳጳሱ አፈ ጉባኤ፣ እንደራሴ እንደ ማለት ነበር። ብዙውን ጊዜ የሊቀ ጳጳሳት ሲያርፉ በመንበራቸው የሚተካው ሊቀ ዲያቆናቸው ነበር።


የከበረ አባት እለእስክንድሮስ በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት አትናቴዎስ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ከዚህ አስቀድሞ ግን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ በተደረገ ጊዜ አባ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም ሳይለይ ይህም አትናቴዎስ ከእነርሱ ጋራ ተሰብስቧል። የጉባኤውም ጸሐፊ አድርገውት በኒቅያ ከተማ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከእነርሱው ጋራ ሠራ።


ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ አርዮሳዊ ልጁ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ አርዮሳውያንም በዙ ።ይህንንም አባት አርዮሳዊው ንጉሥ ከመንበረ ሢመቱ አሳደደውና በእርሱም ፈንታ ጊዮርጊስ የተባለ ከሀዲ ሰው ሾመ። ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ሲያሳድዱትና ሲመልሱት ኖረ። በስደትም በአንዲት ምዕራባዊት አገር በነበረ ጊዜ በዚያ የጣዖት ቤት ነበረች። በዚያቺም የጣዖት ቤት ብዙ ሕዝቦች በውስጧ የሚሠሩ ብዙ የሰይጣን ሥራዎች አሏት። እርሱም የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ለመነው ያቺም የጣዖት ቤት አፍርሶ የአገር ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ወደማወቅ መለሳቸው።


ይህንንም አባት አምስት ጊዜ አሳደዱት የሹመቱም ዘመን አርባ ሰባት ሲሆን ዐሥራ አምስቱን ዓመት በስደትና በእሥራት ነው ያሳለፈው። ይህም አባት ብዙ መከራና ድካም መሰደደም ስደረሰበት ሐዋርያዊ ተብሎ ተጠራ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አትናቴዎስ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የግንቦት7 ስንክሳርና ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሕይወቱና ትምህርቱ።

“ሰላም ለአትናቴዎስ ከመ ላዕሌሁ ተነበዩ። ደቂቀ ክርስቲያን ኵሎሙ እንዘ ይትዋነዩ። ሊቀ ጳጳሳት ዘኮነ ወምእመነ ክርስቶስ ዲበ ንዋዩ። ወበእንተ ዘበጽሖ ስደት እመንበረ ክብሩ ወዕበዩ። ተሰምየ ሐዋርያዌ በኵሉ አያዩ”። ትርጉም፦ የክርስቲያን ልጆች ኹሉ ሲጫዋወቱ በርሱ ላይ ትንቢትን እንደተናሩ የጳጳሳት አለቃ ኾኖ ለተሾመና በክርስቶስ ገንዘብ (ምእመን) ላይ ታማኝ ኾኖ ለተገኘ ለቅዱስ አትናቴዎስ ሰላምታ ይገባል፤ ከፍፁም ክብሩ ዙፋን ላይ ስደት ስለደረሰበትም በግብሩ ኹሉ ሐዋርያ ተብሎ ተሰየመ።(አርኬ) የግንቦት 7።