ታላቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ

“ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ፤ ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኵሎሙ መጻሕፍት ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ”። ትርጉም፦ የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ አገርን በጥዑም ማሕሌትና በማያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ለቅዱስ ያሬድ ሰላምታ ይገባል።”ሊቁ አባ ጊዮጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።


ያሬድ ማለት ርደት፣ ወሪድ፣ ማለትም መውረድ ማለት ነው። ከአዳም ስድስተኛ በሆነው በመላልኤል ልጅ በያሬድ ጊዜ ደቂቅ ሴት ከደብር ቅዱስ ወደ ደቂቀ ቃየን ወደ ምድረ ፍዳ ስለወረዱ ያንን ለማስታወስ አባቱ መላልኤል ያሬድ ብሎታል። ኩፍ5፥21-22 በኢትዮጵያም ዳግማዊ ያሬድ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተነስቶ ሰማያዊውን ልዩ ጣዕመ ዜማ ወደ ኢትዮጵያ የሚያወርድ ነውና ይህንን ለመግለጽ እግዚአብሔር አምላክ በእናቱ እና በአባቱ ላይ አድሮ ያሬድ እንዲባል አድርጓል። ምስጢሩ ልዩ ጣዕመ ዜማን ከሰማይ የሚወርድ መሆኑን ያሳያል።


አንድም ያሬድ፦ ማለት ንብ ማለት ነው። ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ከቅዱሳት መጻሕፍት የማይጠቅሰው የለምና።


አንድም ያሬድ፦ ማለት ረአዬ ምስጢር ነጻሬ ኅቡአት “ምስጢር ተመልካች ምስጢር ገላጭ ማለት ነው። ምስጢር ገላጭ መባሉ የመላእክት ምስጢራት የነበሩትን ጸዋትወ ዜማ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯልና፤ ” ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን፤ ከቅዱሳን መላእክት በሰማይ የሰማኹት ዜማ ምን ይረቅ! ምን ይጠልቅ!” እንዲል። ምስጢር ተመልካች መባሉ ደግሞ ኅቡእ (ስውር) የኾነ የነቢያት፣ የሐዋርያትን፣የሰማዕታትና የጻድቃን ገድል አምልቶ አስፍቶ ስለሚናገር ነው።


አንድም ያሬድ፦ ማለት እንዚራ፣ በገና፣ መሰንቆ ማለት ነው። እነዚህ በስልት በስልት ሲመቱ ለሚሰማቸው ደስ እንዲያሰኙ፤ የቅዱስ ያሬድም ዜማ በንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ አደባባይ በቤተ ክርስቲያን ሲሰማ መላእክት ፣ሰውንና እንስሳትን ደስ ያሰኛልና።


ታላቁ ማኅሌታይ ካህኑ ቅዱስ ያሬድ፦ ከእናቱም ቅድስት ክርስቲና (ታውክልያ) ከአባቱ ከቅዱስ አብዩድ (ይስሐቅ) በአኵስም (አክሱም) በ505ዓ.ም ሚያዝያ5 ቀን ተወለደ። አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር። በዚያን ጊዜ የብሉያትና የሐዲሳት መምህራንና ተማሪዎች የሚገኙት አክሱም ጽዮን ነውና የአኵሱም ቤተ ቀጢን (ቤተ ጉባኤ) መምህር የነበረው የእናቱ ወንድም አጎቱ መምህር ጌዴዎን ይባል ነበር።

ቅዱስ ያሬድ የሰባት ዓመት ሕጻን በኾነ ጊዜ አባቱ ስለ ሞተ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በዚያ ዘመን አጠራር ለጌታው ዐደረ። ጌታውም የዐፄ ገብረ መስቀል ቢትወድድ አዛዥ ዜና ገብርኤል ይባላል። ያሬድን ዐቅሙ ለጉልበት ሥራ እንዳነሰ አይቶት ወደ አጎቱ ላከው።

መምህር ጌድዎንም ዐቅሙንና ዕውቀቱን በመገመት ለተማሪዎች “በሉ ፊደል አስቆጥሩት” አላቸውና ትምህርቱን ጀመረ። ኾኖም ቃለ እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለነበር አብረው የሚማሩትም ሕፃናት “ሰነፍ ያሬድ ዕንጨት ስበር ውሃ ቅዳ” እያሉ አፌዙበት፤ ቀለዱበት። አጎቱ ጌዴዎንም ከትምህርቱ ድክመት የተነሣ በጨንገር (በአለንጋ) ቢገርፈው ሕፃኑ ያሬድም በዚህ ተበሳጭቶና ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ወደ መደባይ ወለል ደረሰ። ለጥሙ ከምንጭ ውሃ ጠጥቶ ለድካሙ ከዛፋ ጥላ አረፈ። በምን ምክንያት ከጓደኞቹ በታች እንደኾነ ሲያስብና ሲያሰላስ ሳያዝንና ሲተክዝከቆየ በኋላ እግዚአብሔር አንድ የሚያጽናና ምልክት አሳየው። ይኸውም አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፋ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ ተማሪ ያሬድም ከዚህ ትል ትዕግሥትን፣ ጽናትን፣ ጥረትን፣ ስኬትን ትምህርት ወስዶ እኔም እኮ ተስፋ ሳይቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረግኹ እግዚአብሔር ያሳካልኛል ብሎ በተስፋ ተጽናንቶ እንደገና ወደ መምህሩ በመመለስ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ። ወደ መደባይ ያደረገው የነበረውን ጉዞ ሠርዞ ወደ አክሱም ከተማ ወደ መምህሩ ጌድዬን ጉባኤ ቤት ተመለሰ። በመጸጸት አጎቱን “አባቴ ስለተቆጣኸኝና ስለገረፍከኝ ተበሳጭቼ ሔጄ ነበር ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ እግዚአብሔር ስላስተማረኝ ተጸጽቼ መጥቻለኹ። ከእንግዲህስ ወዲህ እየተቆጣኽና እየገሠጽህ አስተምረኝ” ሲል አሳቡን ሳይደብቅ ገለጸለት።


አጎቱም ያሬድ ተጸጽቶ በመመለሱ በጣም ተደስቶ ዐይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ ፈጣሪውን እያለቀሰ በለመነለት ጊዜ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለያሬድ ዕውቀትን ገለጸለት። የያሬድ ኅሊናው ተከፍቶለት መዝሙረ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መሓልየ ነቢያት፣ መሐልየ ሰሎሞንን፣ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ንባባቸውን እስከ አገባባቸው አወቀ።
ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቃሉ ይዞ ሲያስተምር ሳለ የትምህርቱን ጥራት፣ የሃይማኖት ጽናት፣ ደግነቱንና ትዕግስቱን፣ ትሕትናውና ተልኮውን በመምህሩና በካህናቱ ተመስክሮለት የአክሱም ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ሢመተ ዲቁና ሾመው። ቅዱስ ያሬድ የታላቋ የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አጋልጋይ ዲያቆን ኾነ።


ትምህርቱን በስፋት ስለቀጠለበት የመጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳት፣ የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ ሊቅ ኾነ። ቅዱስ ያሬድም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋራ በቤተ ቀንጢን ጉባኤ ቤት ይውል ስለነበር ገዳማዊ ሕይወት ከእነርሱ በመማር እንደ እነ አቡነ አረጋዊ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጰንጠሌዎን በድንግልና ተወስኖ በንጽሕና ሲያገለግል ቆይቷል።

ኅዳር 5 ቀን 527 ዓ.ም እግዚአብሔር ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን (መላእክት በአዕዋፍ ተመስለው) እርሱ ወዳለበት ላከለት። እነርሱም ያሬድ ባለበት ቦታ አንጻር በአየር ላይ ረብበው በግእዝ ቋንቋ “ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ (የተመሰገንክና የተባረክ ያሬድ ሆይ፤ አንተን የተሸከመች ማሕፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው”) ብለው አወደሱት። ቅዱስ ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን አዕዋፍ አየና “እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችኹ” አላቸው። ከሦስቱ አዕዋፍ አንዷም “ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌትን ሰምተኽ እንድታዜም የተመረጥኽ መኾኑን እነግርህና እናበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልከን መጥተናል” አለችው። ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ።


በዚያም ቅዱሳን መላእክት የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ እግዚአብሔር በቅኔና በከፍተኛ ደምፅ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ኾነው ሲያመሰግኑ እንዲሁም የእንዚራ፣ የበገና የመሰንቆ ድምፅ በሰማ ጊዜ ካለበት ሥፍራ እነርሱ ወዳሉበት ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም።

በመጨረሻም እነዚያ አዕዋፍ ወደ እርሱ ተመልሰው መጡ። “ያሬድ ሆይ፤ የሰማኸውን አስተውለኸዋል?” ብለው ጠየቁት እርሱም “አላስተዋልኹም” ብሎ መለሰላቸው። እንግዲያውስ አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ጥራ፤ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ከእግዚአብሔር መዘምራን ከቅዱሳን መላእክት በየዐይነቱ ዜማ ያለውን ማሕሌት ትማራለኽ፤ ታጠናለኽ” አሉት። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ማሕሌቱን በየዓይነቱ አውጥቶ “መልካምን ነገር ልቤ ተናገረ” እያለ ከቅዱሳን መላእክት ተማረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ሌሎችን አገልጋዮች ሰዎች ይሾሟቸዋል፤ አንተን ግን እኔ ሢመተ ክህነት (ቅስና) ሾሜኻለሁ” አለው።


ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዓታቸው ዐይቶ፤ ማሕሌታቸውን አጥንቶ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል። ከዚያም ኾኖ ፊቱን ታቦተ ጽዮን ወዳለችበት ወደ ምሥራቅ አዙሮ እጆቹን ዘርግቶ እንዲህ ብሎ ሰማያዊ ዜማን ለመጀመርያ ጊዜ በአክሱም አደባባይ (ዐውደ ምሕረት) ዘመረ።


“ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብር ግብራ ለደብተራ”። ብሎ በዓራራይ ዜማ አዜመ። ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር አሁንም ላለ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው። ስለምን በዓራራይ ዜማ ጀመረ ቢሉ ቋንቋን የሚያናግር ምስጢር የሚያስተረጉም መንፈስ ቅዱስ የገለጠልኝ ዜማ ነው ሲል ነው። ምክንያቱም ዓራራይ ዜማ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነውና።


ከሰማይ እንደተመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣዕመ ዜማውን ያሰማበት ቦታ “ሙራደ ቃል” (የቃል መውረጃ) እየተባለ ይጠራል። ይኸውም ዜማው ከሰማይ የወረደ ለመኾኑ እውነተኛ ማስረጃ ነው። ይህችንም ዜማ “አርያም” አላት። ይህም ማለት ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው።


ከዚህም በኋላ ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነ አትናቴዎስ፣ ቄርሎስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ። የመጽሐፉ የድርሰቱ ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በትግርኛ ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው፤ ሙሾ የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግእዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግእዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው ፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግእዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ ፣ታዝሎ የሚነገር ማለት ነው። ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ፣ አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው። ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ.ም ሲሆን በአፄ ገብረ መስቀል መንግሥት ነው።


አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ ይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።


ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾች አስደነቀ። ለዚህም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ የብርና የወርቅ የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽላት አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ ጠገቡ።


ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተክርስቲያኑን እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ “ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ ፤ ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተ ክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ።

“ይሔውጽዋ መላእክት እንተ በሰማያት ይሔውጽዋ መላእክት እስመ ማኅደረ መለኮት ይእቲ ዖድክዋ ዖድክዋ ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምስአል ወምስጋድ ወምስተስርዬ ኃጢአት ይእቲ ቅድስት ደብተራ፤ በሰማያት ያሉ መላእክት ይጎበኟታል፤ የመለኮት ማደሪያ ናትና መላእክት ይጎበኟታል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዞርኋት፣ ዞርኋት፣ ዞርኋት የሕንፃዋን ማማር ዐየኹ፤ እርሷ መጸለያ፣ መስገጃና የኃጢያት ማስተሰረያ ቅድስት ማደርያ ናትና”። እያለ ስለዘመረ ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሎ ተጠራ። ደብረ ዳሞ የሚለው ስያሜ በኋላ የወጣ ስም እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ። ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ገዳም ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ወደ አክሱም ተመለሰ።


ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድ ጋር አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በጣና በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።


ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ አቡነ አረጋዊን “ዑድ አባ መንገለ ምሥራቅ ወዑዳ ለዛቲ ደብር፤ ዙር አባ ወደ እርስዋም ትወጣ ዘንድ በምሥራቅ በኩል ዙር” አላቸው ወደ ምስራቅ ሲዞሩ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነጭ ሐረግ ዘረጋላቸው እርሱን ይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ገዳም ምሥራቃዊ አቅጣጫ ቅዱስ ያሬድን የምትዘክር “ከርሞ አይደርቅ” የምትባል ዛፍ አለች። ቅዱስ ያሬድ በዚች ዛፍ ሥር ተቀምጦ ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መጽሐፍ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ስላስተማረበት ይህም ቦታ ገዳም እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ከአኵሱም ወደ ማይኪራህ አምርቶ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን በአካለ ነፍስ ከሶርያ አባ ሕርያቆስ ከብሕንሳ አምጥታ ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን ንባቡን እየነገሩት በዜማ እንዲደርስላት አድርጋለች። ከዚህም አያይዞ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን ንባቡ የሌሎች ሊቃውንት ድርሰት የሆኑትን ዐሥራ አራቱን ቅዳሴዎች በዜማ አዘጋጀ።


ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ጸለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን ድርሰቱን ደረሰ። ከዚህ በኋላ አገው፣ ፎገራ እና ወደ ሌሎችም ቦታዎች እየዞረ አስተማረ።


ቅዱስ ያሬድ በአኵሱም ወንበር ዘርግቶ፣ ጉባኤ አስፍቶ ደቀ መዛሙርቱን እያስተማረ ሲኖር በጾመ ፵ ሱባኤ ላይ ሳለ አንድ ቀን በምኵራብ ሰሞን ስለምናኔው እያስታወሰ በተመስጦ ሲዘምር የዜማው ጣዕም እንኳን ሌላውን ራሱን እጅግ ይመሥጠው ነበር። በጣዕመ ዝማሬው ተመሥጦ ሲያዳምጥ የነበረው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ የዐፄ ገብረ መስቀል ዐይን ዐይኑን እየተመለከተ ሳይታወቀው በመስቀል ስላጢኑ (በበትረ መንግሥቱ ዘንግ) ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው። ቅዱስ ያሬድ ግን ከሰማያት የተገኘች ቃለ ማሕሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ ሕመሙ ሳይታወቀው ቀጠለ፤ ደሙም ያለማቋረጥ ፈሰሰ።
ቅዱስ ያሬድ የጀመረውን በፈጸመ ጊዜ ንጉሡ ደንግጦ በትሩን ከቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ቢነቅለው ደሙ በኃይል ይፈስ ጀመር። ያን ጊዜ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል የቅዱስ ያሬድን ትዕግሥት ባለ ጊዜ በመደነቅ፣ በመገረምና በመደንገጥ ዝም በማለት አፉን ይዞ ቆመና ምድራዊ ዋጋ የሚፈልግ መስሎት “ካህን ያሬድ ሆይ የምትፈልገውን ዋጋ ጠይቀኝ” አለው። ቅዱስ ያሬድ መልሶ “የፈለግኹትን እንዳትከለክለኝ ቃል ኪዳን ግባልኝ” አለው። ንጉሡም የጸና ቃል ኪዳን ለቅዱስ ያሬድ ገባለት። ቅዱስ ያሬድም “ከዚህ ሐላፊ ዓለም ክብር ተለይቼ መናኝ ሆኜ እንድኖር ተወኝ አሰናብተኝ” ብሎ አሳብን ገለጸለት።


ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ያሬድ ካህን የጠየቀውን እንዳይከለክለው ከአፉ የወጣውን መሐላ አስቦ በምናኔ አሰናበተው እንጂ ሊከለክለው አልቻለም።


ቅዱስ ያሬድ ካህንም የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ወዳለችበት ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሁለት እጆቹን በታቦተ ጽዮን ላይ አኑሮ “ቅድስት ወብፅዕት፣ ስብሕት ወቡርክት፣ክብር ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዓርገ ሕይወት” ብሎ በደረሰው አንቀጸ ብርሃን ጸሎት እመቤታችንን አመሰገ። በዚህ ጊዜ እጁ በታቦተ ጽዮን ላይ ረቦ በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ ስለነበር ከመሬት አንድ ክንድ ከፍ ከፍ ብሎ ይታይ ነበር። እስከመጨረሻው በከፍተኛ ቃል በዕዝል ዜማ እየዘመረ እግዚአብሔር እና እመቤታችንን ከአመሰገነ በኋላ እመቤታችን የቀና መንገድ እንድትመራውና እስከ ፍጻሜ ገድሉ ትረዳው ዘንድ በጸሎት ለመናት። እመቤታችንም መልሳ “ሰማያዊት ጽዮን ያደረግኻት መቅደሴን፣ በመዝሙር በማሕሌት ምስጋና የኪሩቤልና የሱራፌል ወገን ሰማያውያን ያደረግኻቸው ልጆቼ ካህናትን እንዴት ትተህ ትሔዳለህ” ብላ ቃል በቃል አነጋገረችው። የመንገዱን ስንብት እስክትፈቅድለት ድረስ በለቅሶና በእንባ ዳግመኛ ለመናት እርሷም እንዲሔድ ፈቀደችለት።


የቅዱስ ያሬድ ምናኔ፦ ወደ ገዳም ሊሄድ ተዘጋጀ በዚህ ጊዜ የሚወዱት ካህናት፣ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ተከትለውት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት። ከእርሱ በሚለዩበትም ጊዜ “ሰላመ ነሳእነ ወሰላም ኃደግነ ለክሙ ወሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስለ ኩልክሙ፤ ሰላምን ከእናንተ ተቀበልን ለእናንተም ሰላምን ተውንላችሁ የእግዚአብሔር ሰላምም ከሁላችሁ ጋራ ይኹን” ብሎ በዜማ ተሰናበታቸው። ዳግመኛ “ወሰላም እግዚአብሔር እንተ ኵሉ ባቲ ተሀሉ ወትረ ምስለ ኵልክሙ፤ ፍቅርና ስምምነት ሁሉ ያለበት የእግዚአብሔር ሰላምታ ሁል ጊዜ ከሁላችሁ ጋራ ትኑር” ብሎ በጣዕ ዜማው መረቃቸው። ካህናቱም ይህን ሰምተው አለቀሱ። እርሱም ከእርሱ ጋራ አለቀሰ። በዚሁ ጣዕመ ዜማው የመጨረሻ ቡራኬውን ሰጣቸውና እርስ በእርሳቸው ተሳስመው ተነሰነባብተው ከእርሱ በመለየታቸው እያዘኑና እየተከዙ ወደ አገራቸው አኵሱም ተመለሱ። እርሱ ግን የተከዜን ወንዝ ተሻገረ። የወንዙ ፏፏቴና ጎርፍ እንሚጮህ አንበሳ ሲጮህ በሰማ ጊዜ “አኅለፍኮሙ በእግር እንተ የብስ ማእከለ ባሕር ተከዜ…፤ በተከዜ ባሕር መካከል በእግር እንደሚሻገር በደረቅ አሻገርካቸው…” እያለ በረቀቀ ምስጢር እግዚአብሔርን በማመስገን እየዘመረ ሲሒድ አንዲት ሴት ውሃ ቀድታ ወደ ቤቶ ስትመለስ ድምፁን ሰምታ ወይ ቃል! ወይ ቃል! እንዴት አንጀት ይበላል! ምንኛስ ያሳዝናል! ብላ ደጋግማ ስለተናገረች ቅዱስ ያሬድ ቆሞ የዘመረባት ቦታ “ወይ ቃል” ተብላ ተጠራች። ዛሬ ይህች ቦታ ጎንደር ክፍለ አገር ደባርቅ አካባቢ “ወይ ቃል” ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች።


ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ሔዶ ጸለምት ወጥቶ ብርድ በጸናበት በረዶ በተከማቸበት ሳኔር ተብሎ በሚጠራ በሐዊ ዐምባ ጽሞና ይዞ ተቀመጠ። በዚያም በብዙ ትጋት በጾምና በጸሎት ይልቁንም በስብሐት እግዚአብሔር ብቻ ተወስኖ ጉባኤ ዘርግቶ፣ ትምህርት አስፍቶ ከሱራፌል መላእክት እንደተማረው አድርጎ ከጸለምት፣ ከስሜን፣ ከአገውና ከሌላ አገር ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ሁሉ ማሕሌተ እግዚአብሔር እያስተማረ ኖረ።
ቅዱስ ያሬድ ከትውልድ አገሩ አኵሱም መንኖ ከወጣ በኋላ ትዕግሥቱን እያዘወተረ ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ በማስተማር በገዳመ ስሜን ኖረ። ቅዱስ ቍርባን ለመቀበልና ቅዱሳት ገዳማትን ለመሳለም በፈለገ ጊዜ በሠረገላ ብርሃን ተጭኖ አኵሱም ደርሶ ቅዱስ ቍርባን ተቀብሎ ሌሎች ገዳማትንም ይሳለም ነበር።


በመጨረሻ ቅዱስ ያሬድ ካህን ዘመኑን ሁሉ በመላእክት ማኅሌት እግዚአብሔርን በማገልገልና ይህን ማኅሌት ለሚከተሉት ደቀ መዛሙርት በማስተማር ዘመኑን ፈጽሞ ለሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በምናኔ ታግሦ በገድሉና በጣዕመ ዜማው ፀላኤ ሠናያትን ድል አድርጎ ከዚህ ዓለም ድካምና መከራ የሚያርፍበት፣ የሚሰወርበት ቀንና ሰዓት መድረሱን በጸጋ በዐወቀ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ “ይቤ ጳውሎስ ኃላፊ ንብረቱ ለዝንቱ ዓለም አኃውየ አስተፋጥኑ ገቢረ ሠናየ አነሰ በድረየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሠለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየዓሥየኒ መኰንነ ጽድቅ” 2ጢሞ4፥7-8 እያለ በሚያራራ ቃል ምክሩን ሰጥቶ ተሰናበታቸው። እነርሱም ምክሩን ተቀብለው “አባ አቡነ፣ አባ መምህርነ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተኀድገነ፤ አባታችን መምህራችን ወደ የት ትሔዳለኽ? ለማንስ ትተወናለኽ? እያሉ ሲያዝኑ ሲያለቅሱ በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ግንቦት11 ቀን በ571ዓ.ም ተሰወረ።


ቅዱስ ያሬድ ከመሰወሩ በፊት በእግዚአብሔር አምነው በእርሱ ቃል ኪዳን ለተማፀኑ፣ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ላሳነጹና ላነጹ፣ መጽሐፈ ገድሉን ለጻፈና ላጻፈ፣ ዕጣን ቋጥረው ጧፋና ጥላ ገዝተው መገብሪያ ሰፍረው፣ መጋረጃና ሌሎችንም ንዋያተ ቅዱሳት ገዝተው አምጥተው በስሙ ለታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ላበረከቱት ሁሉ የማየሠልፈውን ርስት መንግሥተ ሰማያት እንደሚያወርስለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ገብቶለታል።


ንዑድ ክብር ቅዱስ ያሬድም ስውር ዋሻ ውስጥ ገብቶ ፈጣሪውን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት ለመነው “መታሰቢያዬን የመምህሬን የጌድዮንን መታሰቢያ የሁላችንንም አባት የአዳምን መታሰቢያ ያደረገው እንግዲህ ዋጋው ምንድን ነው?” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው “የክብር መቀውጫ አስቀምጠው ዘንድ በመንግሥቴ ማልኩልኽ በፍርድ ቀን ማለትም በዕለተ ምጽዋት ያለ ሐፍረት በግልጥ ከአንተ ጋራ ይለፍ” አለው። መታሰቢያህን ያደረገ የገድልኽንም መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ ንዑድ ምስጉን ክብር ነው፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጠዋለኹ፤ የክብር ዙፋንም አወርሰዋለኹ” አለው። ይህንንም ቃል ኪዳን ጌታችን ከሰጠው በኋላ በስሜን ከሚገኝ አንድ ገዳም በኅቡእ (በስውር) እስከ ዕለተ ምጽአት ይኖል ዕረፍቱ ይህ ነው። ከቅዱስ ያሬድ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱም ይማረን!።

ምንጭ፦ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ቅዱስ ያሬድና የቅዱስ ያሬድ ታሪክ ከሚሉት መጻሕፍት።


“ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ። እንተ አዕረገ ልቡ ሕሊና መንፈስ ረዋጼ። ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ። በብዙኅ ፃማ ዘአልቦ ሑፃፄ። መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕፄ”። ትርጉም፦ የመላእክት ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለኾነ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከኼደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለኾነ ለቅዱስ ያሬድ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የግንቦት 11።