
በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ ባየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ የወጣ፡ ጌታቸንም መርቶ ወደ ምዕራባዊቷ በረሀ ያደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ለብቻውን የኖረ ሰውም ሆነ የዱር አራዊት ቢሆኑ ያላዩት ይህ ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር። ቅዱስ አባታችን ኪሮስ። በሐምሌ 8 በዓለ ዕረፍቱን ስለምናከብረው አባታችን በአስቄጥስ ገዳም የነበረው ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ እንዲህ አለ ።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለሁ “አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ”። ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” ብዬ ጠየቅሁት “አዎን” አለኝ። ሁለተኛም “ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት” “ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው” አለኝ።
ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” አልሁት “አዎን አለ” አለኝ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ “ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ” እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ “አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው” ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ። “እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ” አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር።ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ “እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ” ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ “እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው” አልሁት።
እርሱም “ልጄ ሆይ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም” አለኝ። “በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም “ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል አለኝ። በሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ “በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው” አለ።
ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ። አባ ኪሮስም መድኃኒታችንን “ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው ባርከው” አለው መድኃኒታችንም “የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ” አለኝ።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው “እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ሥጋዬንና ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም። አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ” መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። “ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር የሠራት ናት” እያለ አመሰገነባት።
መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን “እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር” አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን “በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው” አለው። ቅዱስ አባ “ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ” አለ። ያን ጊዜ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ “የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” አለ ዳግመኛም “ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም” አለ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤልም ሰጣት።
እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ መስቀሉን አኑሮ ዘጋት። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከመድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች።
እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስሁ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው። መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ኪሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

