
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በግእዝ “ማር ኤፍሬም ሶርያዊ” ሲባል፤ በሶርያ (ܡܪܝ ܐܦܪܝܡ ܣܘܪܝܝܐ (Mār Aprêm Sûryāyâ))፤ በግሪክ (Ἐφραίμ ὁ Σῦρος)፤ ሲባል ይህ አባት የነበረበት ዘመን ከ፫፻፮-፫፻፸፫ (306-373) ዓ.ም ነው፡፡ሀገሩ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ሲሆን አባቱ የጣዖት ካህን እንደነበር ስንክሳር ይነግረናል። ቅዱስ ኤፍሬም የንጽቢን ጳጳስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ የሔደው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሳስቶት ነበር። ከእርሱም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ የክርስትና ጥምቀትን በመጠመቅ በእርሱ ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ።
የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ያደረበት ይህ ቅዱስ አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር። ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ላይ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋር ወደ ቅዱሳን ጉባኤ ሔዷል። ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራዕይ የተነሳ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ “ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው” የሚል ቃልም ከሰማይ ወደርሱ መጣ።
ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወደደ። ወደ ቂሣርያ አገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማዕዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው። ሦስት ምልክቶችን እስኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እነዚህ ናቸው። ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምዕመናን ላይ ያድር ነበር።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ። በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመር። የየራሳቸውን ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስ ለመነው። በጸለየም ጊዜ ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራት በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎም ሁሉ ተጋደለ።
አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች እራሷንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበርና ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችው ኃጢአቷን ሁሉ ጽፋ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች። “አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢአቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱ እንዳልሽው ይሁንልሽ” አላት። እርሷ ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢአቷ በቀር ኃጢያቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበርና በአየችም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም “ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሂጂ እርሱ ይቺን የቀረች ኃጢአትሽ ያስተሠርይልሻል” ይላታል። ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሄዳ እርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። እርሱም እንዲህ አላት “ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሂጂ ግን ሞቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኚዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይቺን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመስስልሻል።”
ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሞቶ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው። ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑ ተደመሰሰላት።አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑ ዲዳን የሚባል አንድ ከሃዲ በተነሳ ጊዜም ከሃዲውን ተከራክሮ ረትቶታል።
እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሺህ ድርሳናትና ተግሣጻትን ደርሷል። ከእነርሱም ውስጥ አምላክ የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያው ውዳሴዋ አንዱ ነው። “አቤቱ የፀጋህን ማዕበል ግታልኝ” እስከሚል ደረስ ጸጋ ተትረፍርፎለት ነበር።
ቅዱስ ኤፍሬም በዓለም ባሉ ክርስቲያኖች የሚከበር ታላቅ ቅዱስ ሊቅ አባት ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት የሚያውቅና እጅግ በጣም አስደናቂ የሆኑ የሃይማኖት መጻሕፍትን የጻፈ ሊቅ ሲሆን ካለው ጥልቅ ዕውቀት የተነሣ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ በሶርያ (ܟܢܪܐ ܕܪܘܚܐ, Kenārâ d-Rûḥâ)፤ የኤዴሳ ዲያቆን (Deacon of Edessa)፤ የሶርያዎች ፀሐይ (the Sun of the Syrians)፤ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ (a Pillar of the Church) ተብሏል።
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ከጻፋቸው በርካቶች የሃይማኖት መጻሕፍት ውስጥ አራት መቶው እስካሁን ድረስ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊው ሶዘመን ባደረገው ጥናት ቅዱስ ኤፍሬም የጻፋቸው በመስመር ቢቈጠሩ ሦስት ሚሊየን እንደሚመሉ አረጋግጧል፡፡
የጻፋቸው መጻሕፍት ለአራት ክፍል የሚከፈሉ ሲሆኑ እኩሌቶቹ በስድ ንባብ እኩሌቶቹ በግጥም መልክ ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ይኸውም መጻሕፍቱ በዝርዝር ሲታዩ፡-
ሀ) በመዝሙራት መልክ የተዘጋጁ
☞ስለ እምነት (ባለ ፹፯ (87) ክፍል መዝሙራት)፤
☞መናፍቃንን በመቃወም (ባለ ፶፮ (56) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ገነት (፲፭ (15) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ጁሊያንን በመቃወም (፭ ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ክርስቶስ ልደት (፶፱ (59) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ቤተ ክርስቲያን (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ንጽቢን (፸፯ (77) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ድንግልና (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ጾም (፷፯ (67) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ኅብስት፤ ስለ ጥምቀት፤ ስለ ስቅለት፤
☞ስለ ትንሣኤ (፴፭ (35) ክፍል ያላቸው መዝሙራት) ወዘተርፈ ጽፏል፡፡
ለ) በድርሳናት መልክ የተዘጋጁ
☞ስድስት የሃይማኖት ድርሳናት፤
☞በ፫፻፶፰ (358) ዓ.ም በመሬት ንውጽውጽውታ ስለ ኒኮሜድያ ጥፋት ድርሳን፤
☞ስለ ሰሙነ ሕማማት፤ ሌሎች በርካቶች ድርሳናት ወዘተርፈ. ጽፏል፡፡
ሐ) ጥበባዊ፤ ግጥማዊም፤ ስድ ንባባዊም ይዘት ከሆኑት፡-
☞ስለ ጌታችን ንግግር፤ ☞ስለ ዕለተ ምጽአት የሚናገር ወዘተርፈ
መ) ሙሉ በሙሉ ስድ ንባብ የሆኑ
☞የኦሪት ዘፍጥረትና ዘጸአት ትርጓሜ፤
☞የአራቱ ወንጌላት ትርጓሜ፤
☞የግብረ ሐዋርያት ትርጓሜ፤
☞የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜ፤
☞ለባርዳይሰን፤ ለማኒ፤ ለመርቅያን ክሕደቶች መልስ ወዘተርፈ ጽፏል፡፡
የቅዱስ ኤፍሬም ዕረፍቱም በ373 ዓ.ም ሐምሌ15 ሲሆን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህነን ሊቅ ሲያወድሰው፡-
“ሰላም ለኤፍሬም ደራሲ ዘጽሩይ ልሳኑ፤
አብያተ ክርስቲያናት ይሠረጉ በድርሳኑ”፡፡
(በድርሳኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚሸለሙ (የሚያጌጡ) አንደበቱ የጠራ ለደራሲው ለኤፍሬም ሰላምታ ይገባል) ብሎታል፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም እነዚህን ድርሰቶቹን በሶርያ ቋንቋ የጻፋቸው ሲሆኑ ወደ በርካቶች ቋንቋዎች የተወሰኑ ሥራዎቹ ሲተረጐሙ ከነዚህ ውስጥ በአርማንያ፤ በኮፕቲክ፤ በግእዝ፤ በሕንድ፤ በአረብኛ፤ በጆርጂያ፤ በግሪክና በሌሎች ተተርጒመዋል፡፡
በእጅጉ የሚገርመው በእኛ ቋንቋ በግእዝ ከተተረጎሙት ውዳሴ ማርያምን ጨምሮ በጥንታዊ ብራና መጻሕፍታችን ውስጥ ዐሥራ ሰባት የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍት ሲገኙ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ በሃይማኖተ አበው ላይና በግብረ ሕማማት ላይ ብቻ ለሕትመት ሲበቁ ሌሎቹ ግን በዘረፋ ብራናዎቹ ከሀገር በመውጣታቸው ምክንያት ሊገኙልን አልቻሉም፡፡
በግእዝ ተተርጉመው የነበሩ የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍትን ዝርዝር “Mariological themes in the writings of St. Ephrem the Syrian” በሚል ርእስ በጻፍሁት የመመረቂያ ጽሑፌ ላይ ከገጽ ፯-፰ ድረስ ስላሰፈርሁት በዚያ ላይ ተመልከቱ (Rodas Tadese, Mariological Themes in the writings of St. Ephrem the Syrian, Un published essay pp 7-8)፡፡
ይህ ታላቅ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን በእጅጉ ይወዳት የነበረ ሊቅ ሲሆን፤ ርሷንም ከመውደዱ የተነሣ ከሉቃስ ወንጌል ወበሳድስን ጸሎተ ማርያምን አውጥቶ በዕድሜዋ ልክ 64 ጊዜያት ድረስ እየጸለየ የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እንደ ልብስ ለብሼው ተጎናጽፌው እያለ ይመኝ ነበር ።
የአምላክ እናትም ለርሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አይታ ከልጇ አማልዳው “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ) እስኪል ድረስ እጅግ በርካቶች መጻሕፍትን እንዲጽፍ ሆኗል፡፡ ለዚህ ፍጹም አባትም ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰባት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ክብር ሆና እየተገለጸችለት ውዳሴዋን ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፤ በዚህም የአምላክ እናት “የቅዱስ ኤፍሬም እመቤት” ተብላ ትወደሳለች፡፡
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በመዋሥዕት መጽሐፉ ላይ ስለ ቅዱስ ኤፍሬም ክብር ሲመሰክር፦“ሖረት ማርያም ኀበ ኤፍሬም ወትቤሎ ትወድሰኒ ሊተ ኀቤከ መጻእኩ ወይቤላ ኤፍሬም ለማርያም አንሰ ኢይክል ወድሶተኪ እስመ ላዕላዕ ወልቱት አነ፤ ካዕበ ትቤሎ ማርያም እሞሙ ለሰማዕት ወድሰኒ ሊተ በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ፤ ቆመ ኤፍሬም ወጸለየ ኀበ እግዚአብሔር ወይቤ ፈኑ ሊተ መንፈስ ቅዱስ ውዳሴ ማርያም ዘእነብብ” (እመቤታችን ማርያም ወደ ኤፍሬም ሄደች፤ እንዲህ አለችው ታመሰግነኝ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ፤ ኤፍሬም እመቤታችን ማርያምን አንቺን ማመስገን አልችልም አላት፤ እኔ ፍጹም አንደበተ ኮልታፋ ምላሰ ጎልዳፋ ነኝና፤ ዳግመኛ የሰማዕታት እናታቸው ማርያም ተናገረችው፤ መንፈስ ቅዱስ ባስገዘበህ መጠን አመስግነኝ፤ ኤፍሬም ቆመና ወደ እግዚአብሔር አመልክቶ የማርያምን ምስጋና በምናገር ገንዘብ መንፈስ ቅዱስን ላክልኝ አለ) በማለት ገልጿል፡፡
ይህ ሊቅም በተቀበለው ሰፊ በረከት እጅግ ጥልቅና ብዙ የነገረ ማርያም አስተምህሮ ይኸውም የንጽሕናዋን፣ የቅድስናዋን፣ የዘላለማዊ ድንግልናዋን፣ የአምላክ እናትነቷን፣ የክብሯን ነገር አምልቶ አስፍቶ የጻፈላት ቅዱስ አባት ነው፡፡
መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር በሐምሌ 15 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በብፁዕ ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 15 ስንክሳርና መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ያጋጀው ጽሑፍ

