📖አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

የአባታቸው ስም ስምዖን ፣የእናታቸው ደግሞ አቅሌስያ ይባላሉ። በደቡባዊ ግብፅ ይኖሩ ነበር።በትዳር ሲኖሩ ልጅ ባለመውለዳቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር ።

ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” ይላል (ማቴ ፯÷፯-፰) አቅሌስያ እግዚአብሔን የሚፈራ ልጅ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚሆን ልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን የማያውቅ ከሆነ ግን ማኅፀኗን እንዲዘጋው ትለምን ነበር።ልጅ እንደምትወልድ ተነግሯትም ወደ ቤቷ ተመለሰች።

በእግዚአብሔር ኃይል የተዘራው ፍሬም አፍርቶ ለክርስቲያን ተስፋ የሚሆን ልጅ ተወለደ።ወዲያው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስሙን ገብረ መንፈስ ቅዱስ አለው።እንደ ተወለዱ ስብሐት ለአብ ፣ ስብሐት ለወልድ ፣ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣቸውን ፈጣሪ አመስግነዋል። የእናታቸውንም ጡት ሳይቀምሱ በእግዚአብሔር ተአምር. እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይኖሩ ጀመሩ። ስምዖን እና አቅሌስያም ባዩት ነገር ተደነቁ።በዚህም ሁኔታ ፫ ዓመታት ተቆጠሩ።ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ታዞ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀብለህ ገዳማውያን ወዳሉበት ውሰደውና ከአበምኔቱ በር አስቀምጠው ስለምግቡ እንዳይጨነቁ ፣ምግቡም ቃለ እግዚአብሔር ነው ብለህ ንገር አለው።

ቅዱስ ገብርኤልም ሕፃኑን አቅፎ ወደ ፯ኛው ሰማያት ወስዶ ከእግዚአብሔር ጋር አገናኘው።

እግዚአብሔርም ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳኑ ጋር እንዲገናኙ መልአኩን አዘዘው።መልአኩም መልሶ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወሰደው ።ሕፃኑን አባ ዘመደ ብርሃን በር ላይ አገኙት፣ደስ ብሏቸውም ተቀበሉት።አስተምረው መዓርገ ዲቁና አቡነ አብርሃም ከተባሉ ጳጳስ እንዲቀበሉ አደረጓቸው። 60 አንበሶችና 60 ነብሮችም አብረዋቸው ይኖሩ ነበር። እነዚህን ምን አበላቸዋለሁ? አሉጻድቁ “የረገጥከውን እየላሱ ይጠግባሉ፣ወደ እኔም እስክትመጣ አብረውህ ይኖራሉ” አላቸው።

ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸውም ፩ ክንድ ከስንዝር የሚሆን ፀጉር በቀለላቸው።ከሰው ተለይተው ጻድቁ በጫካ ከአናብርትና ከአናብስት ጋር ይኖሩ ጀመር።

በግብፅ ለ፫ መቶ ዓመታት ሲጋደሉ ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ለመሔድ ተነሡ። ምድረ ከብድ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ እግራቸውን የኢትዮጵያን አፈር ነካ።ከዚያም መልእክ ወደ ደብር ቅዱስ ዝቋላ ወሰዳቸው። ከባሕር ዳር ቁመው የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአት ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፣ ወደ ባሕር ተወርውረው በመዘቅዘቅ ይጸልዩ ነበር።መልአከ እግዚአብሔር ውጣ ሲላቸው መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ካልማርክልኝ አልወጣም ብለው ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ። መቶ ዓመታት ያህል በባሕር ወድቀው ከጸለዩ በኋላ ጌታችን ወደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሄዶ መላውን ሕዝብ ምሬልሃለሁ ውጣ አላቸው።

ሰይጣን ሲፀልዩ በቊራ ተመስሎ ፪ቱንም ዐይኖቻቸውን አጠፋቸው።ሳያቋርጡ ፀለዩ ። ቅዱስ ጳውሎስ ” ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” እንዲል (፩ ተሰ ፭÷፲፰) በሱባኤም ቆዩ ። ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ወርደው ዐይናቸውን እፍፍ ቢሉባቸው ከቀድሞው የላቀ ብርሃን አገኙ።ወደ ዝቋላ ሔደው መቶ ዓመት ሲዋጓቸው የነበሩትን አጋንንትን አጠፏቸው።

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ100 ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው። ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ብዙ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት።

ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት 5 ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል። ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። “ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ: ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ: ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ: ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ: ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።” እንዲል::

ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍቱ መጋቢት 5 ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 15 ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ የመጋቢት 27 ስቅለት ጥቅምት 27 ቀን እንደሚከበረው ሁሉ ወደ ጥቅምት 5 ቀን ተዛውሮ እንዲከበር ተደረገ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፣ ገድለ መንፈስ ቅዱስና ስንክሳር

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
https://youtu.be/qprpfEqVSG4
የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

📖 የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የከበረች ራሱ መገኘት

ይህም እንዲህ ነው ከሐዲ ኄሮድስ የከበረ ዮሐንስን ራሱን ይቆርጡት ዘንድ ባዘዘ ጊዜ በእሥር ቤት ራሱን ቆርጠው ወደ ኄሮድስ አቀረቧት እርሱም ለወገኖቹ በማሳየት በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ስለ አደረገው ሥራ እንደሚያዝን ገለጠላቸው የክብር ዮሐንስንም ራስ በቤቱ ውስጥ አስቀራት። የፊተኛዪቱ ሚስቱ የንጉሥ አርጣ ልጅ ግን በአባረራት ጊዜ ወደ አባቷ መጥታ በፊቱ አለቀሰች ኄሮድስ በእርሷ ላይ ያደረገውን ሁሉ እርሷን አሳዶ የወንድሙን ሚስት ኄሮድያዳን እንዳገባ ነገረችው። በዚያንም ጊዜ ንጉሥ አርጣ ተቆጥቶ ተነሣ ሠራዊቱንም ሰብስቦ ወደ ገሊላ ዘመተ የገሊላንም አገሮች ሁሉ አጠፋ በእሳትም አቃጠለ። ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ኄሮድስ በአባረራት በልጁ ምክንያት ንጉሥ አርጣ ይህን እንዳደረገም በአስረዱት ጊዜ ስለዚህ ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ተቆጣ ኄሮድስንም ወደ ሮሜ ከተማ ወደርሱ አስቀረበው በእርሱም ምክንያት የአገሮች ጥፋት በመደረጉና ታላቁን ነቢይም ስለ መግደሉ ከሹመቱ ሻረውና ወደሌላ አገር አስጓዘው በዚያም በክፉ አሟሟት ሞተ። የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ግን በኄሮድስ ቤት ተቀብራ ትኖር ነበር ከዚህም በኋላ ንጉሥ ጢባርዮስ ጭፍሮቹን ልኮ የኄሮድስን ቤት አስፈረሰ ጥሪቱን ሁሉ ወሰዶ ለሚያየውም ሁሉ አርአያና ተረት ሆነ ያለ ጣሪያና ያለ ደጃፍ ቀርቷልና ነጋዴዎችም መናኸሪያ አድርገው ያድሩበት ነበር።

በዚያንም ወራት በገንዘብ ድኆች በሃይማኖት ባለጸጎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ እነርሱም ሊሰግዱ የከበረች የአርባ ቀን ጾምንም ሊጾሙ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ ነው። ምሽትም በሆነ ጊዜ ምድረ በዳ በሆነ በኄሮድስ ቤት ውስጥ አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሳቸው ለአንዱ በሕልም ተገለጠለትና የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ አስረዳው ወደቤቱም ተሸክሞ ይወስዳት ዘንድ አዘዘው በነቃም ጊዜ ራእይን እንዳየ ለባልንጀራው ነገረው። ቅዱስ ዮሐንስም ወደአመለከተው ወደዚያ ቦታ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ በቆፈሩም ጊዜ የሸክላ ዕቃ አግኝተው ከፈቷት ያን ጊዜ እጅግ የሚመስጥ በጎ መዓዛ ወጣ የቅዱስ ዮሐንስንም ራስ አገኙዋት ከእርሷም ተባረኩ ወደ ሸክላው ዕቃ መለሱዋትና በፊቱ እንደ ነበረ አፉን ዘጉ ያም ሰው ከእርሱ ጋር ወደ ቤቱ ወሰዳት ታላቅ ክብርንም አከበራት ሁል ጊዜም የሚያበሩ መብራቶችን በፊቷ አኖረ።

የዚያም ሰው ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ ለእኅቱ ነገራት እርሷ ቅድስና ስለአላት እርሱ ሲሠራው እንደነበረ ትሠራ ዘንድ አዘዛት እርሷም የምታከብራትና ሁል ጊዜ መብራትንም የምታበራ ሆነች። የቅዱስ ዮሐንስም ራስ ወደ አርዮሳዊ ሰው እስከ ደረሰች ድረስ ከአንዱ ሰው ወደ አንዱ ሰው የምትፋለስ ሆነች ይህም ሰው በከሀዲው አርዮስ እምነት ውስጥ እያለ የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ድንቆች ተአምራቶችን እንደምታደርግ ያስብ ነበር።

የከበረ ዮሐንስም ከእርሱ የሚበልጥ ሰው በላዩ አስነሣበትና በዚያ ቦታ አሳደደው ያም ቦታ አባ ቄርሎስ በኢየሩሳሌም አገር አባ አንያኖስ በአገረ ኀምዳ ኤጲስ ቆጶስነት እስከ ተሾሙ ድረስ ፈጽሞ ሰው የማይኖርበት ምድረ በዳ ሆነ። ቅዱስ ዮሐንስም ለአባ አንያኖስ በሕልም ተገልጦ የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ ነግሮ አመለከተው አባ አንያኖስም ሒዶ እንደ ዛሬው ግንቦት ሠላሳ ከዚያ አወጣት ይህም የካቲት ሠላሳ ቀን ከአገኙዋት በኋላ ዳግመኛ ያገኙበት ነው።

👉 እንዲህም የሚል አለ የከበረ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ተናገረ ይህም ኄሮድስ በአዘዘ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በእሥር ቤት ሳለ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው በጻሕል አድርገው ወደ ኄሮድስ አመጡለት እርሱም ለኄሮድያዳ ልጅ ሰጣት እርሷም ለእናቷ ወስዳ ሰጠቻት። ይቺም የረከሰች አመንዝራ ልትዳስሣት በወደደች ጊዜ በወጭቱ ውስጥ ጠጒሩዋ ተዘርግቶ ወደ አየር በረረች በአየርም ሆና “የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም” እያለች የምትጮኸ ሆነች እንዲህም እያለች ዐሥራ አምስት ዓመተት ኑራ በዓረቢያ ምድር ዐርፋ በዚያ ተቀበረች።

ነጋድያንም በዚያ ቦታ የሚያድሩ ሆነ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሁለት አማንያን ነጋዴዎች ወደዚያ ቦታ ደርሰው አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም በሕልም ተገለጠላቸውና የከበረች ራሱን ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም አወጡዋት ከእርሳቸውም ጋር ቤታቸው ወስደው ታላቅ ክብር አከበሩዋት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም መለኮትን በአጠመቀ በከበረ ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን ልዩ የሆነች በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 30 ስንክሳር።

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

📖 አስታውስ

👉ደካማነትህን አስታውስ፦ ያን ጊዜ በጣም ጠንቃቃ ትሆናለህ፣ ሊጎዱህ በሚችሉ በትምክህትና በውዳሴ ከንቱም አትሸነፍም።

👉የተሰጠህን በፍቅር የተሞላ የእግዚአብሔርን ቸርነት አስታውስ፦ ይህም በምስጋና የተሞላ ሕይወት እንድትመራ ያደርግሃል።

👉በእግዚአብሔር ፍቅርና ሥራ ላይ ስትታመን ፍጹም የሆነ እምነት በልብህ እያደገ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያሳለፍከው ጊዜ ደግሞ በእምነት እንድትኖር ያበረታታሃል።

👉የሰዎችን ፍቅርና ካንተ ጋር ያሳለፉትን መልካም ጊዜ አስታውስ፦ የሰዎችን ቀናነት ትጠራጠር ዘንድ ወይም ያደረጉብህን ክፉ ነገር ታስብ ዘንድ ይገባሃልን? የቀደመ ፍቅራቸው ስለ እነርሱ ይማልዳል ያንተንም ቁጣ ያበርዳል።

👉ሞት እንዳለ አስታውስ፦ እንዲሁ በዓለም ያለ ፈተናም እንደሚያልፍ። “ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” መክብብ 1፡14 ማለትን ትረዳለህ።

👉በእግዚአብሔር ፊት መቆምህንና እርሱም እንደሚመለከትህ አስታውስ፦ ያኔ ኃጢአት አትሰራም እግዚአብሔርን ታየዋለህና።

👉ስለ አንተ የፈሰሰውን የክርስቶስን ክቡር ደም አስታውስ፦ በዚህም ሕይወትህ ያለውን ዋጋ በእርግጥ ታውቃለህ፤ በዓይኖችህ ፊት የከበረ ይሆናል፣ ስለዚህም በከንቱ በመኖር አታጠፋውም “በዋጋ ተገዝታችኋልና” 1ኛ ቆሮ. 6፥20 እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ።

👉በወላጆችህ እምነት በተጠመቅህባት ቦታ ለእግዚአብሔር የገባኸውን ቃል አስታውስ፦ ዲያብሎስን፣ ሥራዎቹን ሁሉ፣ ሐሳቦቹንና ጥበቡን፣ ኃይሉንም ትክድ ዘንድ ኃይል ታገኛለሕና።

👉በዚህ ዓለም እንግዳ መሆንህንና ወደ ሰማያዊው ቤትህ እንደምትመለስ ዘወትር አስታውስ፦ ያን ጊዜ በዚህ ዓለምና በደስታው ተስፋ ማድረግን ትተዋለህ።

👉በጠባቡ በር መጓዝ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚያደርስህ አስታውስ፦ ሰፊው ደጅ ፊት ለፊትህ ተከፍቶ ብታየው፣ አልፈኸው ሂድ ከእሱም ራቅ፣ በእርሱ የሄዱ እንዳሉ አልቀዋልና።

👉ዘላለማዊውን ሕይወትህን አስታውስ፦ ሁልጊዜም ስለዚህ ትጋ።

👉የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህንና እርሱን መምሰል እንዳለብህ አስታውስ፦ እውነተኞች ከሆኑት ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር አካሄድህን አስተካክል።

👉የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆንህን አስታውስ፦ በውስጥህ ያለውንም ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝን። ዘወትርም ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሁን።

✍አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

የመድኃኔዓለም ጥሪ

“ልጆቼ! በድህነቴ ላይ ቸርነትን አድርጉልኝ፡፡ በዚህስ አልችልም ካላችሁ እሺ በቁስሌ ላይ ዘይትን አፍሱልኝ፡፡ አሁንም ይህን ማድረግ ካልቻላችሁ ወደ እኔ ጠጋ በሉና አናግሩኝ፡፡ እናንተን ማየት፣ ከእናንተ ጋር መጨዋወት ይናፍቀኛልና፡፡ በገዛ ደሜ የገዛኋችሁ ልጆቼ! ከባድ ነገር እኮ አልለመንኳችሁም፡፡ እኔ የምፈልገው ትንሽ ዳቦ፣ ጊዜአዊ ማደርያ፣ እንዲሁም የሚያጽናኑ ቃላትን ብቻ ነው፡፡ “ይህ ሁሉ ማድረጌ ምን ይጠቅመኛል?” ካላችሁ ስለ ምሰጣችሁን ርስት መንግሥተ ሰማያት ብላችሁ አድርጉት፡፡ አሁንም ልባችሁ አልተነካምን? ስለ መንግሥተ ሰማያት አታድርጉት፤ ግን ደግሞ ስለ ሰብአዊ ርኅራኄ ይህን አድርጉልኝ፡፡ የእኔን መራቆት የሚያሳዝናችሁ በቀራንዮ አደባባይ ስለ እናንተ ብዬ የተራቆትኩት ብቻ ነውን? ታድያ አሁንም ‘ኮ በደጃችሁ ላይ ተጥዬ ዕራቁቴን ነኝ፡፡ ለምን አላዘናችሁልኝም? የታሰርኩት በቀራንዮ ብቻ ነውን? አይደለም፡፡

ታድያ እንደምን አታዝኑልኝም? የማፈቅራችሁ ልጆቼ? † በመስቀል ላይ ተሰቅዬ ሳለሁ “ተጠማሁ” እንዳለኩ ዛሬስ ስለ እናንተ ብዬ ደጋግሜ ይህን ቃል አልተናገርኩምን? ጕሮሮዬ ደርቆ ስለምን ትንሽ እንኳ አላሳዝናችሁም? ስለምንስ ይህ ሁሉ ፍቅር ስለ እናንተ መሆኑን ትዘነጉብኛላችሁ? የምለምናችሁ እናንተን ባለጸጋ ለማድረግ አይደለምን? ይህችን ትንሽ ቸርነት ስላደረጋችሁልኝ በዐይን ያልታየች፣ በጀሮ ያልተሰማች፣ በሰውም አእምሮ ያልታሰበች ርስት መንግሥተ ሰማያት እንድታገኙ ብዬ አይደለምን? ስለ እናንተ ብዬ ደሀ የሆንኩት ያኔ በመዋዕለ ሥጋዌዬ ብቻ እንደሆነ አታስቡ ልጆቼ! ዛሬም ቢሆን በደጃችሁ የተጣልኩት ስለ እናንተ ጥቅም እንደሆነ ተረዱልኝ፡፡

ከባድ ነገር ‘ኮ አልለመንኳችሁም፡፡ † እስር ቤት መጥታችሁ ጠይቁኝ እንጂ አስፈቱኝ አላልኳችሁም፡፡ ታምሜ ጠይቁኝ እንጂ ፈውሱኝ አላልኳችሁም፡፡ ከጠየቃችሁኝ ብቻ በቂዬ ነው፡፡ እስኪ ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ! በዚያ በአስፈሪው ቀን ስመጣ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” የሚለውን ቃሌ መስማት አትፈልጉምን? ዛሬ የሰጣችሁኝ ሁሉ የምረሳ ይመስላችኋልን? ያኔ በክብር ስመጣ ከእልፍ ወለዱ ጋር እንድሰጣችሁ አትሹምን? የማፈቅራችሁ ልጆቼ! ከደጃችሁ ተጥዬ የምለምናችሁ፣ ከበራችሁ ላይ ቆሜ ማደርያን የምጠይቃችሁ፣ እጄን ዘርግቼ እናንተን እናንተን የማየው ያኔ ትሉ ወደማይጠፋው እሳቱ ወደማያንቀላፋው እሳት እንዳትሄዱብኝ ብዬ ነው፡፡

ታድያ ይህን ለምን አትረዱልኝ ልጆቼ? ስለምን እንዳስቸገርኳችሁ ታስባላችሁ? ለእናንተ ጥቅም እንደሆነ እንዳትረዱ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ከእናንተ ጋር ቁጭ ብዬ ልብላ ስላችሁ ስለምን ትገፈትሩኛለችሁ? ይህን ያህል ቸርነት አድርጌላችሁ ሳለሁስ ስለምን በግልምጫ አያችሁኝ? ይህን ያህል መውደድ ወድጃችሁ ሳለሁ ስለምን በቅጡ ልታነጋገግሩኝ አልወደዳችሁም? ከአዳም ጀምሮ ዓለም እስኪያልፍ ድረስ ያለው ሕዝብ ሁሉ በአንድ አደባባይ ላይ ቆሞ፣ እልፍ አእላፍ መላእክት በዙርያዬ ረበው “ይህ/ ይህቺ ልጅ ወዳጄ ነው/ ናት፤ በመሆኑም በታላቅ ክብርና ዕልልታ አጅባችሁ ወደ ዘለዓለም ደስታዋ አግቡት/ አግቧት” የሚለውን ፍርዴ አትናፍቁምን? † ልጆቼ! እኔን ላለማየት ስለምን ፊታችሁን ትሸፍናላችሁ? ስለምን ታፍራላችሁ? እኔ ሳላፍርባችሁ ስለምን እናንተ አፈራችሁ? ልጆቼ! ልባችሁ እንደተነካ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ስሜት ብቻ አይሁን፡፡

ከንፈራችሁን ብቻ አትምጠጡብኝ፡፡ ከእናንተ የምፈልገው አንዲት ነገር ብቻ ነው፡፡ ከላይ የጠየቅኳችሁን ነገሮች ወደ ተግባር ቀይሯቸው፡፡ ለማይጠቅማችሁ ነገር አብዝታችሁ እየሮጣችሁ ለሚጠቅማችሁ ነገር አትስነፉ፡፡ “እኔኮ ሥጋ ለባሽ ነኝ፤ ይህን እንደምን እችላለሁ?” አትበሉኝ፡፡ አውቃለሁ! ነገር ግን ፈቃዳችሁን ብቻ ስጡኝ እንጂ እኔ ራሴ አደርግላችኋለሁ፡፡

“ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብዬ ያስተማርኳችሁን ቃል ረሳችሁትን? /ዮሐ.15፡5/፡፡ እንግዲያውስ ከእናንተ የምፈልገው ፈቃዳችሁን ነው፡፡ አሁን ካላችሁበት ቦታ ተንቀሳቅሳችሁ ወጣ ስትሉ ታገኙኛላችሁ፡፡ አናግሩኝ! አፍቃሪያችሁ መድኃኔዓለም ነኝ፡፡”

✍ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ መልእክተ ጳውሎስ /ሮሜ.8፡31-39/ ትርጕም

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

📖ከንግግር የሚበልጥ ዝምታ

‹‹ከመቀየም ይልቅ የዋህነት የምትወድ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የትግስትህ መጠኑን አውቅ ዘንድ የአፍ መዝጊያ ቁልፍ የሆነች ዝምታን ስጠኝ››ይላሉ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ። ጌታችን አይሁድ በሐሰት ክሶች ደጋግመው ሲከሱት፤ ሲሰድቡት፤ሲዘብቱበት የታገሰውን የትዕግስቱን መጠን እንዴት ልንረዳው እንችላለን?

ባላጠፋኸው ስትከሰስ፤ያላደረከውን አድርገሃል እየተባለ ለሞት በሚያደርስ ክስ ስትወቀስ በዝምታ መሸከም እጅግ ከባድ ነው፡፡እናም በብስጭት እና በምሬት ራስህን ለመከላከል መሞከርህ አይቀርም፡፡ምናልባትም ከመናገር አልፈህ ከሳሾችህን፤ የሚሰድቡህን፤ የሚተፉብህን ሁሉ መሬት ተሰንጥቃ እንድትውጣቸው ማድረግ ብትችል ከማድረግ አትመለስም፡፡

ጌታችን ግን ሁሉን ማድረግ ሲቻለው በዝምታ ተቀበለ፡፡‹‹ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው?ይህ ያህል ትዕግስት እንደምን ያለ ትዕግስት ነው?›› እያልን በቅዳሴያችን ከማድነቅ በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡

የጌታችን ዝምታ ከአይሁድ ንግግር ይልቅ የጲላጦስን ልብ ገዛው የጌታችን ትዕግስት ጲላጦስን አስጨነቀው፡፡እንደ ሎሎች ተከሳሾች ሕይወቱን ለማዳን በገዢው ፊት ዕንባ የማይማጸን ክሶቹን ለማስተባበል የማይሞክር ከሳሾቹን መልሶ እየከሰሰ ራሱን ነጻ ለማውጣት የማይፍጨረጨርበሰንሰለት ታስሮ እየተጎተተ እንኳን ከሚጎትቱት ጋር የማይታገል ሞት ሊያስፈርድበት በሚችል ወንበር ፊት ቀርቦ በፍጹም እርጋታና ሰላም የሚቆም ተከሳሽ ከጌታ በቀር አይቶ የማያውቀው ጲላጦስ ከሊቃነ ካህናቱ ጩኸት በላይ በናዝራዊ ዝምታ ተማረከ፡፡ማር 15 4-5

ጲላጦስ ከግቢው ውጪ ቆመው የሚጮኹት አይሁድ ወደ ጎን ትቶ ጌታችንን ለብቻው መረመረው፡፡‹‹ጰላጦስም እንደገና ወደ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው፡፡ኢየሱስም መልሶ፡-አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነው ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው››(ዮሐ 18 32-35) ለመናገርም ጊዜ አለውና ጌታችን መልስ ሰጠ፡፡ምላሹ ግን ጥያቄ ነበር፡፡

የጌታችን መልስ ከላይ ሲታይ‹እንዴት እንዲህ ይላል?››የሚያሰኝ ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ጌታችን ይህንን ያለው የጲላጦስ ጥያቄ ሁለት መልስ ያለው ስለሆነ ነው፡፡‹‹ንጉሥ ነህ ወይ? ለሚለው ጥያቄ መንፈሳዊ ትርጉሙ ከሆነ እርሱ ከክርስቶስ እንደመሆኑ ‹አዎን አንተም አልከው›የሚያሰኝ ነው፡፡ ቄሳርን የሚጋፋ ንጉሥ እንዳይነሳ በሚፈሩት በሮማውያን እይታ ከሆነ ደግሞ ጌታችን‹ንጉሥ አይደለሁም› ሊል ይችላል፡፡

ጲላጦስ በጠየቀው ጊዜ ‹ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ንገሩህን? ማለቱ ጥያቄው ከራስህ የመጣ ከሆነ ንጉሥ አይደለሁም እንድልህ አይሁድ የነገሩህን ብቻ ይዘህ ከሆነ ደግሞ ‹‹መሲሑ ንጉሥ እኔ ነኝ›› ብዬ ለይቼ እመልስልህ ዘንድ የጥያቄህን መነሻ ንገረኝ እንደማለት ነው፡፡

ጰላጦስ የጌታችንን አጠያየቅ ስለተረዳ በአይሁድ ዘንድ ያለው ነገር ለእርሱ እንደማይገደው በማሳየት‹‹እኔ አይሁዳዊ ነኝን?ወገኖችህ የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ ምን አድርገሃል?›› አለው፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹‹መንግስቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም መንግስቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎች ይዋጉልኝ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግስቴ ከዚህ አይደለችም›› አለው፡፡

ጌታችን በዚህ መልሱ ሰማያዊ ንግሥናውንም ምድራዊ ሥልጣንን የሚፈልግ ንጉሥ አለመሆኑን በአንድ ላይ አስረዳ፡፤ ‹‹መንግስቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም››ብሎ አይሁድ እንደሚከሱት ለቄሳር በተቀናቃኝነት የሚያሰጋ መንግስት እንደሌለው አስረዳ፡፡ ይህም መልስ የጰላጦስን ልብ የሚያሳርፍ ነው፡፡ምክንያቱም የሀገረ ገዢው ዋነኛ ጭንቀት ኃላፊ የቄሳር ሥልጣን እንዳይነካ ማድረግ ላይ ብቻ ነው፡፡

‹‹መንግሥቴ›› የሚለው ቃል ደግሞ የክርስቶስ ንጉሥነትን ያሳያል፡፡የቤተክርስትያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘቄሳሪያ እንዳለው‹‹የክርስቶስ መንግሥቱ በምድራዊ ሕግጋት የማይወሰን በአምላካዊና ሰማያዊ ትምህርቱ ነፍሳትን ብሩሕ ስላደረገ ብቻ ዓለም ሁሉ የተስፋፋ መንግሥት ነው››በዙህም መሰረት መንግሥቱ ተብለን የተጠራነው በስሙ አምነው የተከተሉት ሐዋርያት በእነርሱ መሠረትነት የተመሠረተችው ቤተክርስትያን በስሙ ያመንን እኛ ክርስትያኖች ነን፡፡

መንግሥቱ የተባልነው በእርሱ ያመንን እኛ ክርስትያኖች ከሆንን ‹‹መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም››የሚለው ቃልስ እንዴት ይታያል? እኛ ያለነው በዚህ ዓለም አይደለምን?የሚልጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ጌታችን መንግሥቴ ‹‹ከዚህ ዓለም አይደለችም›› አለ እንጂ ‹‹በዚህ ዓለም አይደለችም››አላለም፡፡በስሙ የምታምን ቤተ ክርስትያንና ክርስትያኖች ሁሉ‹በዓለም›ናቸው እንጂ‹ከዓለም› አይደሉም።

✍ሕማማት
ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ገጽ 177

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.comS/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

ዘወረደ / ጾመ ሕርቃል

የመጀመሪያ የዐቢይ ጾም መግቢያ እሑድ ዘወረደ ይባላል ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡

«ዘወረደ» ማለት «የወረደ» ማለት ነው፡፡  አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህም  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር፤  ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ የሚታወስበት፣ የሚነገርበት  የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት   ነው፡፡

ዮሐ.3፥13፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሰረት “ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ”ገላ 4፥4 እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጠፋውን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መውረዱን የምናዘክርበት ነው።

ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ጾመ ሕርቃል ተብሎም ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም  ፤ ተስፋ አበው ፤ ትንቢተ ነቢያት ፤ ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ፤ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው።

ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡

ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪም በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡

በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡

ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል።

እኛም በዚህ በዐቢይ ጾም የለመነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀር እንዲከናወንልን ጾምን ገንዘባችን እናድርግ።

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org
              

ዐቢይ ጾም

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ (ፍትሃ ነገስት አንቀፅ.15) “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍጥረት 2፥17 ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው።

መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳግም 32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ 14፥16፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴዎስ 5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝሙር 68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርዓያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴዎስ 6፥16 ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን።

✨የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች፦

👉ዐቢይ ጾም
ባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል።

👉ጾመ ሁዳዴ
በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል።

👉የካሳ ጾም
አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ።

👉የድል ጾም
አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴዎስ 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል.

👉የመሸጋገሪያ ጾም
ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል።

👉ጾመ አስተምህሮ
ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ። ማቴዎስ 4፥2

👉የቀድሶተ ገዳም ጾም
ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል።

👉የመዘጋጃ ጾም
ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል።

👉የሥራ መጀመሪያ ጾም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በምድር ሳለ ስብከት፣ ተዓምራት ከመጀመሩ በፊት የጾመው ጾም ነውና የሥራ መጀመሪያ ጾም ይባላል። ጾሙን የኃጢአት መደምሰሻ የድያብሎስ ድል መንሻ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ የልቦና ማደሻ የእድሜ መለመኛ የፍቅር ያድርግልን ።

እንኳን ለታላቁ ለዐቢይ ጾም በሰላም አደረሰን። በሰላም አስፈጽሞ በቸርነቱ ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን አሜን።

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org
              

📖መጻሕፍትን ስለ ማንበብ – በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

📖መጻሕፍትን ስለ ማንበብ – በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን መጻሕፍት ለሰው ልጆች የተሰጡት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ እንዲርቅ ስላደረግነውና እግዚአብሔርን መስማት የምንችልበት መንፈሳዊ ጆሮ (እዝነ ልቡና) በማጣታችን ምክንያት ነው (ማቴ.፣ ድር. 1፡1)፡፡

ቃሉን በልቡናችን መጻፍ ስላቃተን በጽላትና በወረቀት ተጽፎ የተሰጠን ነው (ዝኒ ከማሁ)፡፡

አንድ ሰው በአጠገቡ ለሌለ ወዳጁ ደብዳቤ እንደሚጽፍለት ኹሉ፥ እግዚአብሔርም ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ከእርሱ ለራቀው ለሰው ልጅ የላካቸው ደብዳቤዎች ናቸው – ቅዱሳት መጻሕፍት (ዘፍ.፣ ድር.2፡4)፡፡

ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር ወደ አዳም መጥቶ ካነጋገረው፣ ቃኤልን ከገሠጸው፣ ከኖኅ ጋር ከተነጋገረው፣ የአብርሃምን ደግነት ከተቀበለበት አንጻር ኹለተኛ አማራጭ ናቸው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ምድር ሲመጣ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ እንደ መጀመሪያው አፍ ለአፍ እንዲያናግራቸው ነበር (ማቴ.፣ ድር.1)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ የነገራቸውን እንደሚያስታውሳቸው እንጂ የተጻፈ ነገር አለመስጠቱም ይህን የሚያስረዳ ነው (ዮሐ.14፡26)፡፡

ዳግመኛም ነቢያቱ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እኾናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይኾኑኛል” ብለው ትንቢት የተናገሩትም ለዚህ ነው (ኤር.31፡33)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም “ሥጋ በኾነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ” ያለውም ይህን እንደሚያስረዳ ሊቁ ያብራራል (2ኛ ቆሮ.3፡3)፡፡

ስለዚህ መጻሕፍት የተሰጡት በኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንደ ኾኑ ሊቁ ያብራራል፡-

☞ የመጀመሪያው በጊዜ ሒደት አንዳንዶች ከመሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ፈቀቅ እያሉ ስለ ኼዱ ነው፡፡

☞ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ማለትም በምግባራቸው ንጽህናቸውነን እያቆሸሹ ስለ ኼዱ ነው፡፡

በመኾኑም መጻሕፍት ሲሰጡ እነዚህ በሃይማኖትም በምግባርም ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከጣባቢቱ ወደ ሰፊይቱ መንገድ ፈቀቅ ያሉትን ለመመለስና ሌሎችም ወደዚያ እንዳይሔዱ ለማስታወስ የተሰጡ ናቸው (ሉቃ.1፡1-4)፡፡

ከላይ ከተመለከትነው መረዳት እንደሚቻለው መጻሕፍትን ማንበብ የሕይወት (የድኅነት) ጉዳይ እንጂ የአማራጭ ጉዳይ እንዳልኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ መጻሕፍትን ስለ ማንበብ፡- “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ፤ በማንበብ ተወስነህ ኑር” ካለው በኋላ ምክንያቱን ሲነግረውም፡- “ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” ያለውም ለዚህ ነው (1ኛ ጢሞ.4፡16)፡፡ ጳጳስ ቢኾንም፣ ሕመምተኛ ቢኾንም ከእናቱና ከሴት አያቱ እንደ ለመደው ማንበብ ነበረበትና !

ሊቁም፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥንቃቄና በብልሐት የምናነብ ከኾነ እውነተኛውን ሃይማኖትን እንደምንማር መንፈሳዊ ሕይወትንም መምራት እንደሚቻለን አሰተምሯል (ዮሐ.፣ ድር.30)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በተቀመጠበት ላይ ዲያብሎስ ወደዚያ መቅረብ ካልተቻለው፥ ቃሉ በእኛ ዘንድ ሲኖርም አጋንንት ወደ እኛ አይቀርቡም፡፡

ክፉ ሰሚዕ ብሎም ርእይ አጋንንትን ወደ እኛ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ኹሉ፥ ደግ ሰሚዕ ብሎም ርእይም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንድናገኝ ያደርጋል (ዮሐ.፣ ድር. 32)፡፡

ስለዚህ ከዚህ ከለመለመ የአበባ መስክ እንደ ንብ መቅሰም ፍሬውንም በየጊዜው መብላት እጅግ ያስፈልጋል (ሐውል.፣ ድር. 1)፡፡ ከምግበ ሥጋ ረሃብ ይልቅ ቃለ እግዚአብሔርን መራብ ይከፋልና፤

ቅዱሳት መጻሕፍት ማለት የመድኀኒት ሳጥኖች ናቸው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ለሚያጋጥመው ማንኛውም ዓይነት መከራና ኀዘን ወደ እነርሱ ኼዶ መድኀኒትን ለራሱ ሊወስድ ይገባል (ቆላ.፣ ድር.9)፡፡

ጠላታችን ዲያብሎስ ረቂቅ ነው፡፡ እርሱን ድል የምናደርግበት መሣሪያም ረቂቅ ሊኾን ይገባል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ረቂቃን መንፈሳዊ ትጥቆች ናቸው፡፡ እነዚህን አለመታጠቅ ማለት ወደ ጦር ሜዳ ያለ ትጥቅ እንደ መኼድ ነው (ቆላ.፣ ድር.9)፡፡ ማደግ የምንችለው እነዚህን በአግባቡ ስንታጠቅ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት መብራቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መብራቶች የማይጠቀም ሰው በምንፍቅናና በምግባር ጨለማ ይጓዛል፡፡ ቢደክምም እንኳን ድካሙ ረብ የለሽ ድካም ይኾንበታል (ሮሜ.፣ መቅድም)፡፡

ለክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማንበብ እጅግ ውርድት ነው፡፡ አሕዛብ ስለ ፈረስ ግልቢያ ቢጠይቁአቸው የተጨዋቾቹን ስም፣ ጨዋታው የሚካኼድበት ከተማ፣ የተጨዋቾቹ ብቃት፣ ከተጫዋቾቹም አልፈው ስለ ፈረሶቻቸው ሳይቀር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በቤ.ክ. የሚካኼደውን ነገር የማያውቁ ክርስቲያኖች ግን አሉ (ዮሐ.፣ ድር. 32)፡፡

እንደ ሊቁ አነጋገር ለስሕተት ትምህርት መግነን፣ ለአሕዛባዊ ሕይወትም መበራከት ተጠያቂዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እውነትን ይዘው እውነት እንድታበራ ማድረግ ሲገባቸው ተውጠውና በቸልታ ስለሚኖሩ ከላይ የጠቀስናቸው እንዲበዙ አድርጓቸዋል፡፡

አሕዛብ አንድ የሚወዱት ተጫዋች ሲዘለፍ ዝም አይሉም፡፡ ስለ ተነቀፈው ዘፋኝ ወይም ተጫዋች ይከራከራሉ፡፡ ነቃፊውን ያሳምኑ ዘንድም ረዘም ያለ ክርክርን ያደርጋሉ፡፡ ክርስቲያኖች ግን በክርስትና ላይ እንደዚህ ያለ ነቀፋ ሲደርስ ወይ አብረው ይስቃሉ፤ ወይም አንገታቸውን ደፍተው ዝም ይላሉ፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀሰቅስ ነው (ዮሐ.፣ ድር. 17)፡፡

መጻሕፍትን አለማንበብ ክሕደት የተባለ ልጅ እንዲወለድ፣ የተበላሸ ሕይወት እንዲኖር፣ እንደዚሁም ነገሮች ኹሉ ምስቅልቅላቸው እንዲወጡ ያደርጋል (ሀብታምና ድኻ፣ ድር. 3)፡፡

ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ የድኅነት – የዘለዓለም ሕይወት ጉዳይ መኾኑን በመገንዘብ ዕለት ዕለት ማንበብና መዳናችንንም መፈጸም ይገባናል !

✞ ይህን እንድናደርግ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፥ አሜን !
(ጥንቅር ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.comS/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

በበገና እና መሰንቆ ትምህርት አባላትን አስመረቀ

የእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት መዝሙር ክፍል
በበገና እና መሰንቆ ትምህርት ሲያስተምራቸው የነበሩ አባላትን አስመረቀ

*,,,🌼💥🌼 ***
የደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰ/ት/ቤት ከሚያከናውናቸው ዓበይት አገልግሎት መካከል አንዱ የሆነው የዜማ መሣሪያዎች ትምህርት ነው። ዘንድሮም እንደ አምላክ ፈቃድ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት በተገኙበት እሑድ ታህሳስ 16, 2015 ዓ.ም በበገና በመሰንቆ ያሠለጠናቸውን 45 ሠልጣኞች በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
ሠልጣኞች በየተመረቁበት የዜማ መሣሪያ ዝማሬን ያቀረቡ ሲሆን ለመምህራንና ለሰንበት ት/ቤቱ ስጦታ አበሮክተዋል። ለተመራቂዎችም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
Egziabher Meslene
እግዚአብሔር ምስሌነ
በእነዚህ ገጾች ቤተሰብ ይሁኑን
የዩቲዩብ ቻናል፡
https://youtu.be/qprpfEqVSG4
የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

እንኳን ለጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረችሁ፡፡

ቅዱስ አባታችን በምልጃቸው ሀገራችንን ሰላም ያድርጉልን፡፡

በእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት
የዩቲዩብ ቻናላችን ያልተቀላቀላችሁ እየው ልንኩ፡
https://www.youtube.com/channel/UCNjEKBSeBmsSGrHdlN3aSpQ

Subscribe_and_share