ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ሐይቅ እንደጸለየች።

በሸዋ ከፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች ሀገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ ሀገሯ ናት። በዚህም ሀገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ግንቦት 12 ቀን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና “በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች” በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።


በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን አፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነገሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማዊ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።


ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በጣም ተበሳጨችና በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት። ያም እሳት ትንታግ በአገልጋይዋ ጉረሮ ድረስ ዘለቀና ገደላት። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦችዋ መጥተው የአገልጋይቱን አስከሬን ወደሌላ ክፍል ወሰዱት። ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ “ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ” እያለች አለቀሰች።


ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለእግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች “አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ”። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በሐዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እሷ ወዳለችበት ክፍል መጥተው “እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ” አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ “ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን” ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔር አመሰገነች።


ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም “እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው” አሏት። እርሷም “ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው” አለቻቸው።

ከዚህም በኋላ ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ “በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየነሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር “ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈውን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መጽውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦

ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ፡ ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት “ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል” ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም “ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ… ” አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መጻተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደ እርስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች ከእግሩ ሥርም ወደቀች።

ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆኑ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ” አላት። እርስዋም “አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?” አለችው። “አዎን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ” አላት። “እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው” አለችው። “አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና ። የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም” በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና በአደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና “እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል” አላት።


ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ” አላት። በዚህን ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና” አለችው። “የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብዬ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋዬ እንደመሆኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና” አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ” አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ” ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዟት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ “እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ” እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህ አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።


ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው” አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ “ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል” በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም “ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ” እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ “ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን” አላት። እርሷም “ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ” አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ሁካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ “አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?” እያለች አደነቀች። ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን” አላት። እስዋም “አዎ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ” አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “እነዚህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው” አለው። በዚህ ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ የእኔ መኖሪያዬ ወዴት ነው?” አለችው። ጌታም “መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች።

በየአንዳንዳቸው አክሊል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉባቸው የእነዚህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከርስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ “እነዚህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና” አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?” አላት። እርስዋም “አዎን ጌታዬ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው” አላት። “በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ” አለችው። “ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው” አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።

ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦

ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግሉን ልጆቿን ሰበሰበችና “ከእግዲህ እርስ በራሳችሁ በመፈቃቀር ኑሩ እግዚአብሔርም በመፍራት ተቀመጡ” አለቻቸው። ይህንንም ከአለች በኋላ ለ1079 ደናግል ወይም መነኰሳት አስተዳዳሪ እመ ምኔት ሾመችላቸው። “ከወሰንኩላችሁ ሕግ ወይም ከሰራሁላችሁ ሥርዓት አትተላለፉ ከእግዲህ ከዛሬ በስተቀር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንገናኝም እና” አለቻቸው። ይህንንም ተናግራ ከእነርሱ ስትለይ አንዲት መነኵሲት ወይም መበለት ጠርታ ሹል የሆኑ ብረቶች አምጭልኝ” ብላ አዘዘቻትና አመጣችላት።


ከዚያም በእናታችን ክርስቶስ ሠምራ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፈረችና በውስጡ ዕፀ ከርካዕ ወይም የሎሚ እንጨት አስተከለችበት። ዳግመኛ “ከእግዲህ እግዚአብሔር ይቅር እስኪለኝ ድረስ ከዚህ አልወጣም” ብላ ከጉድጓዱ ውስጥ ገባች። ሦስት የተሳሉ ጦርች በፊቷ ሦስት ጦር በኋላዋ፣ ሦስት ጦር በቀኝ ጎኗ፣ ሦስት ጦር በግራዋ ጎን ተከለች። መበለቲቱም የፊጢኝ ወይም የኋሊት በገመድ አሰረቻት። ከዚህም በኋላ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕዝብ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ሰዎች አጥብቃ ትጸልይና ታዝን ጀመር።


በዚህ አይነት ተጋድሎ ሰውነቷን ወይም ሥጋዋን በልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ ስትፈትን ኖረች። ፈጥና በክንፈ ረድኤት ወደ በዓቷ የምትመለስበት ጊዜ አለ። በዚህ አይነት ግብር ለብዙ ዘመን ኖረች። በምትሰግድበት ጊዜ ወደፊት ስትል ደረቷን ወደኋላ ስትል ጀርባዋን ወደቀኝ ስትል ቀን ጎኗን ወደግራ ስተል ግራ ጎኗን ጦሩ እየወጋት ከቊስሉ የተነሣ ጦሩ የወጋት ገመዱ የከረከራት መላ ሰውነቷ ሸቶ ተልቶ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ተጋድሎ አደረገች።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን እግዚአብሔር ኃይል ጸንታለችና ከጉድጓድ ወጥታ በጣና ባሕር ውስጥ ገብታ እንድትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ አዘዛት ከዚያም በባሕሩ ውስጥ እየጸለየች ሦስት ዓመት ተቀመጠች።


ከሦስት ዓመት በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ባሕር ውስጥ ሳለች ለጌትነቱ ክብር መሰገድ የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእስዋ መጣ። እርሱም ጋር ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል እናቱ ማርያም መጡ። ዐሥራ አምስቱ ነቢያት ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰባ ሁለቱ አርድእት ጻድቃን ሰማዕታት ደናግልና መነኰሳት ሌሎች ሁሉም በየሥርዓታቸውና በየማዕረጋቸው በየነገዳቸው መጡ። ኄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት አለቃቸውን ሕፃኑ ቂርቆስን ተከትለው እደዚሁም ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በየነገዳቸውና በየወገናቸው መጡ።


ከነዚህ ሁሉ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መጥቶ “ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና” እያለ በገናውን ይደረድር ነበር። እንዲህም እያለ በሚዘምርበት ጊዜ በዚያ ያሉ ቅዱሳኖች በሙሉ “የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም ወዳጅ ይህች ክርስቶስ ሠምራ በእውነት ብፅዕት ነች” እያሉ ዘመሩ።


በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዛሬ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ላስተላልፍሽ መጥቻለሁ” አላት። “ድካምሽ ወደዕረፍት ኃዘንሽ ወደ ደስታ ችግርሽ ወደ ብልጽግና ተለውጦልሻል። እውነት በእውነት እልሻለሁ ወይም እነግርሻለሁ በፍጹም ደስታ መታሰቢያሽን ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት አስደስተዋለሁ። በችግሩ ወይም በጭንቁ ጊዜ በመታመን ስምሽን ቢጠራ እኔ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድነዋለሁ።


የገድልሽን ዜና የሚናገረውን መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፍላቸዋለሁ። ቤተ ክርስቲያንሽን የሠራ ወይም ያሠራ ያሣነፀ ወይም ያነፀ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ንጹሕ አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ። በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ በዕለተ አርብ ከተቆረሰው ሥጋዬ አበላዋለሁ። በስምሽ ለተጠማው እፍኝ ውሃ ያጠጣ እኔ በዕለተ አርብ ከጎኔ በፈሰሰው ደሜ አረካዋለሁ። በዓልሽ በሚከበርበት ዕለት ጧፍ፣ ዕጣን፣ ወይም ዘይት ንጹሕ ስንዴ የመሰለውንም ሁሉ መባ ያገባ መሥዋዕቱን እንደ አብርሃምና እንደ መልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አድርጌ እቀበልለታለሁ” አላት።


በዚህ ጊዜ “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባርያህ ባለሟልነትን በፊትህ ካገኘሁስ አንድ ጊዜ እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም “ትናገሪ ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ” አላት። ” አቤቱ ሥጋዬ የሚቀበርበትን ወይም የሚያርፍበት ቦታ ወዴት ታዝዛለህ” አለችው። መቃብርሽ በዚች ጓንጒት በምትባል ደሴት ውስጥ ነው” አላት። “ነገር ግን ሥጋሽ በመሬት ውስጥ ይቀበራል ስላልኩሽ ኀዘን አይግባሽ በኋለኛው ዕለት እኔ አስነሣዋለሁና” አላት።


“አቤቱ እንዲህ ከሆነ መታሰቢያዬን እያደረገ ስሜን እየጠራ በስሜ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚቀበረውን እስከ ስንት ትውልድ ድረስ ትምርልኛለህ” አለችው። “እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ” አላት። ይህንም ቃል ኪዳን በሰጣት ጊዜ ፈጽማ ተደሰተች።
ዳግመኛም “ይህች ደሴት እንደ ደብረ ታቦርና ደብረ ዘይት ስሟ የተጠራ ይሁን” አላት። “እንደዚሁ ይህችን ሥጋሽ የምታርፍበትን ቦታ ቀደስኳት አከበርኳት። መጽሐፍ የተናገረውን አልሰማሽምን ቦታ ሰውን የሚያከብረው አይደለም ሰው ቦታን ያስከብረዋል እንጂ። ስለዚህ ነገር ስላንቺ ይቺን መካነ መቃብርሽን ቀደስኳት አከበርኳት። ስሟም ደብረ ፍቅር ደብረ ምሕረት ተብሎ ይሰየም ወይም ይጠራል። እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርልታል። እውነት እውነት እልሻለሁ አንቺን ያከበረ ሁሉ እኔ በሰማያዊ መንግሥቴ አከብረዋለሁ። አንቺን የወደደ ወይም ያፈቀረሽን እኔ አፈቅረዋለሉ።


ዳግመኛም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ይህ የዛሬው በዓልሽ የደስታና የተድላ ቀን ነው” አላት። ይህንንም ብሎ በብዙ ወገን ወይም ሠራዊት ላይ ሾማት። “ክብርሽ ከአሮንና ከሙሴ፣ ከጴጥሮስና ከጳውሎስ፣ ሰይጣንን ድል ከአደረገው ከሕፃኑ ቂርቆስ፣ ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከፀሐየ ልዳ እየተባለ ከሚጠራ ከጊዮርጊስ ጋር ክብር ጋር ትክክል ነው” አላት።


በደብረ ጽዮን ከሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ጋር ትዘምሪ ዘንድ በክብር ተካከልሽ። በእውነት አንቺን የሚያፈቅሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ እግዚአብሔርን ከሚያከብሩ ወይም ከሚፈሩ በስተቀር በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውስ ተራራ ላይ ማን ይኖራል” ብሎ ተናግሯልና። ስለዚህም አንቺን የሚያከብሩ ሁሉ አንቺን ከአለሽበት ቦታ ገብተው ከአንቺ ጋር ይደሰታሉ”።
ከዚህም አምላካዊ ቃል ጋራ በነሐሴ 24 ቀን የአባታችን ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ዕለት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች። በዚህ ጊዜ የነጎድጓድ ብልጭልጭታ ሆነ ነቢዩ ዳዊት “በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ” ብሎ እንደተናገረ የመላእክት ሠራዊትና ጻድቃን ሰማዕታትም ሁሉ እልል እያሉ አመሰገኑ። እርሷም ከነርሱ ጋር እየተደሰተች አመሰገነች። ከዚያም መላእክት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አድርሰዋት ወይም አሳርገዋት በአሸናፊው በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሰገደች።


ከዚህ በኋላ ጌታ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን እናቴ ማርያምን ወደ ምትኖርበት ውሰዳት” አለው። ቅዱስ ሚካኤልም “ጌታ ወደ አዘዘልሽ ቦታ እንሒድ” አላት። ቅዱስ ሚካኤልም ይዟት ሲሔድ እጅግ የሚያስደነግጥና ከፀሐይ ከጨረቃ ከዋክብት ብርሃን ይልቅ ብርሃኑ የሚያበራ መንበር አየች። ይህን መንበር በአየችውም ጊዜ በጣም አድርጋ ወደደችው።


የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ክርስቶስ ሠምራ ምን ትመለከቻለሽ” አላት። “ያን ቡሩህ የሆነ መንበር እመለከታለሁ” አለችው። “ይህ መንበር ለአንቺ ቢሆን ትወጃለሽን” አላት። “አዎን ጌታዬ ለእኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያውስ ለአንቺ የተዘጋጀ ነው” አላት። በዚያ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ጌታዬ መኖርያሽ እናቴ ከማርያም ጋር ነው ብሎኝ አልነበረምን”። ታዲያ እንዴት ይህ መንበር ለአንቺ የተዘጋጀ ነው ትለኛለህ” አለችው። መላአኩም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ለምን ቸኮልሽ” አላት። ይህን ካለ በኋላ ወደ እመቤታችን ወደ ድንግል ማርያም መኖርያ ወስዶ አደረሳትና። “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እግዲህ ተመልከች” አላት። በተመለከተቻት ወይም ባየቻት ጊዜም ማርያም ወይም ሰው አልነበረችም ነገር ግን ከፍታዋ ወይም ቁመቷ የላቀ ተራራ ነበረች እንጂ።


ቅዱስ ሚካኤልም “ማርያም ነች ብኸኝ አልበረምን ታዲያ እንዴት ተራራ ልትሆን ቻለች” አለችው። ያን ጊዜ ምሥጢሯ እስኪገለጽልሽ ድረስ ትንሽ ታገሽ” አላት። ከዚያም ቀና ብላ ብትመለከት እመቤታችን ድንግል ማርያምን አየቻትና እንደአሞራ በራ አንገቷን አቅፋ ሳመቻት። እመቤታችንም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ አንቺንም የሚያፈቅር የገድልሽን ዜና የሚሰሙ ሁሉ የተባርኩ የተመሰገኑ ናቸው” በማለት ሳመቻት። ይህንም ከአለቻት በኋላ በቀኟ አስቀመጠቻት…።


ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ አባ ይስሐቅ የሚባል መነኵሴ ከእናታችን ከክርስቶስ ሠምራ ዘንድ ቢሄድ ሥጋዋ ብቻ ወይም አስከሬኗ በጉድጓድ ውስጥ እንደተተከለ ምሰሶ ወይም ዓምድ ቆሞ አገኘው። ነፍስዋ ከሥጋዋ ያልተለየች ወይም በሕይወት ያለች መስሎት ነበርና “እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ባርኪኝ” አላት። የሚመልስለት ቢያጣ ወደ እርስዋ ቀረበና ሥጋዋን ዳሰሰው። እንዳረፈችም ባወቀ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ ከመሬት ላይ እየወደቀ እየተነሣ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።


መነኰሳቱን ሁሉ ያለቅሱላት ዘንድ ጠራቸው። መነኰሳቱም እየተሽቀዳደሙና እየተሯሯጡ መጥተው አርፋ አገኟት። በዚህ ጊዜ “አንቺን የተሸከመች ማኅፀን የተባረከች ነች አንቺንም ያጠቡ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው” እያሉ ጽዕኑና መራራ ልቅሶን አለቀሱ።
ከዚህ በኋላ አባ ይስሐቅ ሥጋዋን ወይም አስከሬኗን በንጹሕ በፍታ ገንዞ በሳጥን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቀበራት። መነኰስ ይስሐቅም ወደ በዓቱ መመለሱ ቀርቶ በዚያው ቤተ ክርስቲያን በስተ ምሥራቅ በኩል በቁመቱ ልክ ጎድጓድ አስቆፍሮ በውስጧ ገባ።
ከዚያም ከጎድጓዱ ውስጥ ገብቶ “ከእንግዲህ እስክሞት ድረስ እንደ እናቴ ክርስቶስ ሠምራ ከዚህ ጎድጓድ አልወጣም” በማለት ወሰነ። ይህንንም ካለ በኋላ መሪር እንባ እያለቀሰ እህል ሳይቀምስ እስከ 40 ቀን ተቀመጠ። ከ 40 ቀን በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየችና በእናታችን በክርስቶስ ሠምራ አማላጅነትና ልመና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ።


እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ የኖረችው ሦስት መቶ ሰባ አምስት (375) ዓመታትን ነው። ከእናታችን ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ።

እጨጌ (እጨ) አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ

በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 ዓመት ለኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩት ጻድቅ ።

እጨጌ (እጨ) አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ፦ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ “በምን አውቀኸኝ ነው?” ብላ አቅፋ ሳመችውና “ከእንግዲህ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ዓመት ትኖራለህ…” ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኋላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጣ። ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኵስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖረዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ተዘጋጀላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡


ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡


አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚህም በኋላ “ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?” ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም “አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?” አሏት እርሷም “አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?” አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው “በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ” ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ “የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ” ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለሃይማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዮሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምህረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡


አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበስ በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዮሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኋላ ዕረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋርያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ “ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኵሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…” የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡


ቅዱስ አባታችንም በ 500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው “በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም” አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ 134 ዓመት በኋላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡


ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምህረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምህረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡


ከአባታችን ከእጨጌ አቡነ ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።

ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ

በሰማዕትነት እንደሚያርፉ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡ “አለቃ ተጠምቀ” የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው “ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ” ብለዋቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት ናቸው። አቡነ ጴጥሮስ ። የተወለዱት በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ነው፡፡

ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ኃይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ሁሉንም በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አወቁ፡፡ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሐ አባት ሆኑ፡፡
ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡

ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለሀገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡

በወቅቱ በነበረው ጦርነት የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም “ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ” በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያንቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን “የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል” ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኃይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡ እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡

ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።

“ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው “ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም” ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡ወደ ምሥራቅ አፍሪካው ዜና መዋዕል አዘጋጁ ወደ ፖጃሌ ዘገባ እንመለስና የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- “ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞች ሦሰት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው፤ መካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡

የቀረበባቸውም ወንጀል “ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል” የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም “ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፡- “አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡ ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ፡- “አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፤ እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን” ብለው አወገዙ፡፡

ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍጥነት ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ፡፡ ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡ የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኚያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ “ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ “ይህ ያንተ ሥራ ነው” ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡ ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ “ተኩስ!” በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡

ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው” በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?” ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውን ተናረዋል፡- “አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡
ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት “በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል” አለኝ፡፡ “እንዴት?” ብለው “አላየህም ሲያጨበጭብ?” አለኝ፡፡ “ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባህል ሲናደድም ያጨበጭባል” አልኩት፡፡ “እንዴት?” ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡ “ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ” ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል” ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል ሙስሊም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ። በዚያው እርሷም “የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ” ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ ቀብራቸው በምሥጢር መፈጸሙን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምሥጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም “ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምሥጢር ቀበሯቸው” ከሚል ከመላምት ያለፈ ነገር ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ “ፉሪ ለቡ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው “ሙኒሳ ጉብታ” ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡

እንዲሁም የአቡነ ጴጥሮስን ሥጋ በተመለከተ ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአ.አ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር መደረጉ በትንሣኤ መጽሔት ቁ.58 1978 ዓ.ም ላይ የተገለጠ ቢሆንም ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ቅዱሳን መላእክት የጻድቃንን በድን እያመጡ ወደሚያስቀምጡበትና በውስጡ የሚቀመጥ አስክሬን ወደማይፈርስበት አቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ገዳም መላእክት ወስደው እንዳስቀመጡትና በዚያም እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ውስጥ የቅዳሱኑ አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ የአንገት ክራቸው ራሱ ሳይበጠስ እንደዛው እንደነበሩ ስለሚገኝ ቦታውም እጅግ ትልቅ የቃልኪዳን ቦታ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በዚህ በጨረሻው ሀሳብ ይስማማል፡፡

ሰማያዊ ክብርን የሚያስገኝ አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተክርስቲያን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) አቡነ ዼጥሮስን “የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት” ወይም በፈረንጅኛው አፍ (MARTYR OF THE MILLENIUM) በሚል መጠሪያ ሰይሟቸዋል።
ላልተነገረላቸውና ላልተዘመረላቸው ለእኚህ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያናችን ድንቅ አባት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 12 ቀን 1998 ዓ.ም እኚህን ሰማዕት “አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ” ተብለው እንዲጠሩ ወስኗል፡፡ በስማቸውም መቅደስ እንዲታነጽ ፈቅዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት (ኢሳ 56፡4) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቁ በተወለዱበት ሥፍራ መታሰቢያ አቁማላቸዋለች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው የተሰየመው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና መታሰቢያ ሐውልታቸው ሲሠራ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ለግንባታ የሚሆን አሸዋ ከመርዳት አንስቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ድንኳን እስከመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረዋል፡፡ ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የአባታችንን እጅግ አኩሪ ታሪክ ሲያዘክራቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአ.አ መሐል ከተማ ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።

ሶርያዊው ሊቅ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በግእዝ “ማር ኤፍሬም ሶርያዊ” ሲባል፤ በሶርያ (ܡܪܝ ܐܦܪܝܡ ܣܘܪܝܝܐ (Mār Aprêm Sûryāyâ))፤ በግሪክ (Ἐφραίμ ὁ Σῦρος)፤ ሲባል ይህ አባት የነበረበት ዘመን ከ፫፻፮-፫፻፸፫ (306-373) ዓ.ም ነው፡፡ሀገሩ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ሲሆን አባቱ የጣዖት ካህን እንደነበር ስንክሳር ይነግረናል። ቅዱስ ኤፍሬም የንጽቢን ጳጳስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ የሔደው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሳስቶት ነበር። ከእርሱም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ የክርስትና ጥምቀትን በመጠመቅ በእርሱ ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ።


የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ያደረበት ይህ ቅዱስ አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር። ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ላይ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋር ወደ ቅዱሳን ጉባኤ ሔዷል። ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራዕይ የተነሳ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ “ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው” የሚል ቃልም ከሰማይ ወደርሱ መጣ።


ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወደደ። ወደ ቂሣርያ አገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማዕዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው። ሦስት ምልክቶችን እስኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እነዚህ ናቸው። ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምዕመናን ላይ ያድር ነበር።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ። በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመር። የየራሳቸውን ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስ ለመነው። በጸለየም ጊዜ ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራት በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎም ሁሉ ተጋደለ።


አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች እራሷንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበርና ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችው ኃጢአቷን ሁሉ ጽፋ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች። “አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢአቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱ እንዳልሽው ይሁንልሽ” አላት። እርሷ ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢአቷ በቀር ኃጢያቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበርና በአየችም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም “ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሂጂ እርሱ ይቺን የቀረች ኃጢአትሽ ያስተሠርይልሻል” ይላታል። ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሄዳ እርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። እርሱም እንዲህ አላት “ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሂጂ ግን ሞቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኚዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይቺን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመስስልሻል።”


ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሞቶ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው። ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑ ተደመሰሰላት።አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑ ዲዳን የሚባል አንድ ከሃዲ በተነሳ ጊዜም ከሃዲውን ተከራክሮ ረትቶታል።
እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሺህ ድርሳናትና ተግሣጻትን ደርሷል። ከእነርሱም ውስጥ አምላክ የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያው ውዳሴዋ አንዱ ነው። “አቤቱ የፀጋህን ማዕበል ግታልኝ” እስከሚል ደረስ ጸጋ ተትረፍርፎለት ነበር።

ቅዱስ ኤፍሬም በዓለም ባሉ ክርስቲያኖች የሚከበር ታላቅ ቅዱስ ሊቅ አባት ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት የሚያውቅና እጅግ በጣም አስደናቂ የሆኑ የሃይማኖት መጻሕፍትን የጻፈ ሊቅ ሲሆን ካለው ጥልቅ ዕውቀት የተነሣ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ በሶርያ (ܟܢܪܐ ܕܪܘܚܐ, Kenārâ d-Rûḥâ)፤ የኤዴሳ ዲያቆን (Deacon of Edessa)፤ የሶርያዎች ፀሐይ (the Sun of the Syrians)፤ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ (a Pillar of the Church) ተብሏል።

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ከጻፋቸው በርካቶች የሃይማኖት መጻሕፍት ውስጥ አራት መቶው እስካሁን ድረስ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊው ሶዘመን ባደረገው ጥናት ቅዱስ ኤፍሬም የጻፋቸው በመስመር ቢቈጠሩ ሦስት ሚሊየን እንደሚመሉ አረጋግጧል፡፡
የጻፋቸው መጻሕፍት ለአራት ክፍል የሚከፈሉ ሲሆኑ እኩሌቶቹ በስድ ንባብ እኩሌቶቹ በግጥም መልክ ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ይኸውም መጻሕፍቱ በዝርዝር ሲታዩ፡-
ሀ) በመዝሙራት መልክ የተዘጋጁ
☞ስለ እምነት (ባለ ፹፯ (87) ክፍል መዝሙራት)፤
☞መናፍቃንን በመቃወም (ባለ ፶፮ (56) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ገነት (፲፭ (15) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ጁሊያንን በመቃወም (፭ ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ክርስቶስ ልደት (፶፱ (59) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ቤተ ክርስቲያን (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ንጽቢን (፸፯ (77) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ድንግልና (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ጾም (፷፯ (67) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ኅብስት፤ ስለ ጥምቀት፤ ስለ ስቅለት፤
☞ስለ ትንሣኤ (፴፭ (35) ክፍል ያላቸው መዝሙራት) ወዘተርፈ ጽፏል፡፡

ለ) በድርሳናት መልክ የተዘጋጁ
☞ስድስት የሃይማኖት ድርሳናት፤
☞በ፫፻፶፰ (358) ዓ.ም በመሬት ንውጽውጽውታ ስለ ኒኮሜድያ ጥፋት ድርሳን፤
☞ስለ ሰሙነ ሕማማት፤ ሌሎች በርካቶች ድርሳናት ወዘተርፈ. ጽፏል፡፡

ሐ) ጥበባዊ፤ ግጥማዊም፤ ስድ ንባባዊም ይዘት ከሆኑት፡-
☞ስለ ጌታችን ንግግር፤ ☞ስለ ዕለተ ምጽአት የሚናገር ወዘተርፈ
መ) ሙሉ በሙሉ ስድ ንባብ የሆኑ
☞የኦሪት ዘፍጥረትና ዘጸአት ትርጓሜ፤
☞የአራቱ ወንጌላት ትርጓሜ፤
☞የግብረ ሐዋርያት ትርጓሜ፤
☞የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜ፤
☞ለባርዳይሰን፤ ለማኒ፤ ለመርቅያን ክሕደቶች መልስ ወዘተርፈ ጽፏል፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ዕረፍቱም በ373 ዓ.ም ሐምሌ15 ሲሆን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህነን ሊቅ ሲያወድሰው፡-
“ሰላም ለኤፍሬም ደራሲ ዘጽሩይ ልሳኑ፤
አብያተ ክርስቲያናት ይሠረጉ በድርሳኑ”፡፡
(በድርሳኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚሸለሙ (የሚያጌጡ) አንደበቱ የጠራ ለደራሲው ለኤፍሬም ሰላምታ ይገባል) ብሎታል፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም እነዚህን ድርሰቶቹን በሶርያ ቋንቋ የጻፋቸው ሲሆኑ ወደ በርካቶች ቋንቋዎች የተወሰኑ ሥራዎቹ ሲተረጐሙ ከነዚህ ውስጥ በአርማንያ፤ በኮፕቲክ፤ በግእዝ፤ በሕንድ፤ በአረብኛ፤ በጆርጂያ፤ በግሪክና በሌሎች ተተርጒመዋል፡፡

በእጅጉ የሚገርመው በእኛ ቋንቋ በግእዝ ከተተረጎሙት ውዳሴ ማርያምን ጨምሮ በጥንታዊ ብራና መጻሕፍታችን ውስጥ ዐሥራ ሰባት የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍት ሲገኙ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ በሃይማኖተ አበው ላይና በግብረ ሕማማት ላይ ብቻ ለሕትመት ሲበቁ ሌሎቹ ግን በዘረፋ ብራናዎቹ ከሀገር በመውጣታቸው ምክንያት ሊገኙልን አልቻሉም፡፡

በግእዝ ተተርጉመው የነበሩ የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍትን ዝርዝር “Mariological themes in the writings of St. Ephrem the Syrian” በሚል ርእስ በጻፍሁት የመመረቂያ ጽሑፌ ላይ ከገጽ ፯-፰ ድረስ ስላሰፈርሁት በዚያ ላይ ተመልከቱ (Rodas Tadese, Mariological Themes in the writings of St. Ephrem the Syrian, Un published essay pp 7-8)፡፡

ይህ ታላቅ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን በእጅጉ ይወዳት የነበረ ሊቅ ሲሆን፤ ርሷንም ከመውደዱ የተነሣ ከሉቃስ ወንጌል ወበሳድስን ጸሎተ ማርያምን አውጥቶ በዕድሜዋ ልክ 64 ጊዜያት ድረስ እየጸለየ የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እንደ ልብስ ለብሼው ተጎናጽፌው እያለ ይመኝ ነበር ።

የአምላክ እናትም ለርሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አይታ ከልጇ አማልዳው “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ) እስኪል ድረስ እጅግ በርካቶች መጻሕፍትን እንዲጽፍ ሆኗል፡፡ ለዚህ ፍጹም አባትም ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰባት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ክብር ሆና እየተገለጸችለት ውዳሴዋን ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፤ በዚህም የአምላክ እናት “የቅዱስ ኤፍሬም እመቤት” ተብላ ትወደሳለች፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በመዋሥዕት መጽሐፉ ላይ ስለ ቅዱስ ኤፍሬም ክብር ሲመሰክር፦“ሖረት ማርያም ኀበ ኤፍሬም ወትቤሎ ትወድሰኒ ሊተ ኀቤከ መጻእኩ ወይቤላ ኤፍሬም ለማርያም አንሰ ኢይክል ወድሶተኪ እስመ ላዕላዕ ወልቱት አነ፤ ካዕበ ትቤሎ ማርያም እሞሙ ለሰማዕት ወድሰኒ ሊተ በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ፤ ቆመ ኤፍሬም ወጸለየ ኀበ እግዚአብሔር ወይቤ ፈኑ ሊተ መንፈስ ቅዱስ ውዳሴ ማርያም ዘእነብብ” (እመቤታችን ማርያም ወደ ኤፍሬም ሄደች፤ እንዲህ አለችው ታመሰግነኝ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ፤ ኤፍሬም እመቤታችን ማርያምን አንቺን ማመስገን አልችልም አላት፤ እኔ ፍጹም አንደበተ ኮልታፋ ምላሰ ጎልዳፋ ነኝና፤ ዳግመኛ የሰማዕታት እናታቸው ማርያም ተናገረችው፤ መንፈስ ቅዱስ ባስገዘበህ መጠን አመስግነኝ፤ ኤፍሬም ቆመና ወደ እግዚአብሔር አመልክቶ የማርያምን ምስጋና በምናገር ገንዘብ መንፈስ ቅዱስን ላክልኝ አለ) በማለት ገልጿል፡፡

ይህ ሊቅም በተቀበለው ሰፊ በረከት እጅግ ጥልቅና ብዙ የነገረ ማርያም አስተምህሮ ይኸውም የንጽሕናዋን፣ የቅድስናዋን፣ የዘላለማዊ ድንግልናዋን፣ የአምላክ እናትነቷን፣ የክብሯን ነገር አምልቶ አስፍቶ የጻፈላት ቅዱስ አባት ነው፡፡
መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር በሐምሌ 15 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በብፁዕ ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 15 ስንክሳርና መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ያጋጀው ጽሑፍ

አባ ባውማ ስለ አቡነ ኪሮስ

በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ ባየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ የወጣ፡ ጌታቸንም መርቶ ወደ ምዕራባዊቷ በረሀ ያደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ለብቻውን የኖረ ሰውም ሆነ የዱር አራዊት ቢሆኑ ያላዩት ይህ ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር። ቅዱስ አባታችን ኪሮስ። በሐምሌ 8 በዓለ ዕረፍቱን ስለምናከብረው አባታችን በአስቄጥስ ገዳም የነበረው ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ እንዲህ አለ ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለሁ “አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ”። ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” ብዬ ጠየቅሁት “አዎን” አለኝ። ሁለተኛም “ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት” “ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው” አለኝ።
ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” አልሁት “አዎን አለ” አለኝ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ “ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ” እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ “አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው” ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ። “እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ” አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር።ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ “እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ” ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ “እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው” አልሁት።


እርሱም “ልጄ ሆይ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም” አለኝ። “በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም “ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል አለኝ። በሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ “በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው” አለ።


ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ። አባ ኪሮስም መድኃኒታችንን “ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው ባርከው” አለው መድኃኒታችንም “የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ” አለኝ።


ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው “እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ሥጋዬንና ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም። አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ” መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። “ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር የሠራት ናት” እያለ አመሰገነባት።


መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን “እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር” አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን “በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው” አለው። ቅዱስ አባ “ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ” አለ። ያን ጊዜ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ “የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” አለ ዳግመኛም “ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም” አለ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤልም ሰጣት።


እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ መስቀሉን አኑሮ ዘጋት። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከመድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች።


እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስሁ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው። መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ኪሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አስተርእዮተ ሥሉስ ቅዱስ በቤተ አብርሃም

ቅድስት ሥላሴ

ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው። ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው።


አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ
ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም
አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ
እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን
ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል
(ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፬፥፴፪)፡፡


በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር
በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው
ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን
አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች
ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ
መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡


የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን ‹‹ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ›› ሲላቸው
‹‹ደክሞናልና አዝለህ አስገባን›› አሉት፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ (በአምላካዊ
ጥበብ) ከቤቱ ገቡ፡፡ አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ሔደና ‹‹ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ አብርሃምም ወይፈን አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡ ወይፈኑም ተነሥቶ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፤›› ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ
እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም
ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች
ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና
አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡


በዚህ ትምህርት ብዙ ምሥጢራት ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹን በመጠኑ ለማስታወስ ያህል፦ ‹‹… ሦስት ሰዎች … ሊቀበላቸው … ወደ እነርሱ …›› የሚሉትና ሌሎችም በብዙ ቍጥር የተገለጹ ተመሳሳይ ሐረጋት የእግዚአብሔርን ሦስትነት፤ ‹‹… በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ? …›› የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡ ሣራ ዳቦ ያዘጋጀችበት ሦስቱ መሥፈሪያ የሦስትነቱ፤ ዳቦው አንድ መኾኑ ደግሞ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡

ሥላሴ አብርሃም ያዘጋጀውን እንስሳ ተመገቡ ተብሎ መነገሩም በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ነው እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ አይስማማቸውም (አይነገርላቸውም)፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ (እግዚአብሔር ምግብ በላ) ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣትን የመሰሉ የሥጋ ተግባራት የመለኮት ባሕርያት አይደሉምና፡፡ ከዚህ በተለየ ምሥጢር ሥላሴ ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› ብለው ከጠየቁበት ኃይለ ቃል መካከል ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› የሚለውን እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› (ሉቃ. ፩፥፴፯) ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ መናገሩ የእግዚአብሔር ቃል በዘመን ብዛት የማይለወጥ ሕያውና እውነተኛ መኾኑን ያጠይቃል።
እግዚአብሔር አብርሃምን ‹‹ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል መጠየቁም ያለችበት ጠፍቶበት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ
የምሥራች እንዳለ ለማጠየቅ ነው፡፡ ሰውን ያለበትን ጠይቆ፣ ጠርቶ፣ አቅርቦ አስደሳች ዜና መንገር የተለመደ ነውና፡፡
ይኸውም ‹‹አዳም ወዴት ነህ?›› ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው (ዘፍ. ፫፥፱)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አዳምን ‹‹ወዴት ነህ?›› ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረው፣ ‹‹ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚለውን የድኅነት ቃል ኪዳን ሊሰጠው ፈቅዶ ነበር፡፡ እንደ አዳም ዅሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከምትኾን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለሙን እንደሚያድነው ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ጠይቆታል፡፡ ከዚያም የይስሐቅን መወለድ አብሥሯቸዋል፡፡ ይኸውም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሔር
ከአብርሃም የልጅ ልጅ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደ (በአካለ ሥጋ ወደ ምድር እንደ መጣ)፤ በዚህ ጊዜም በሣራ የተመሰለች ወንጌል በይስሐቅ የሚመሰሉ ምእመናንን እንዳስገኘች ማለትም ሐዲስ ኪዳን
ተመሥርታ ብዙ ክርስቲያኖችን እንዳፈራች የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡


የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደ ተረጐሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ‹‹ተናግዶቱ (ተአንግዶቱ)
ለአብርሃም፤ ለአብርሃም የሃይማኖቱን (የእንግዳ ተቀባይነቱን) ዋጋ የምታሰጪው አንቺ ነሽ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ፡፡
በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚው ይመግብበት፣ ያርፍበት እንደ ነበረ ዅሉ በእመቤታችንም አማላጅነትም
መንገደኞች ማረፍያ፤ እንግዶች መጠለያ፤ ስደተኞች ተስፋ ያገኛሉና፡፡ ከዅሉም በላይ የነፈስ የሥጋ መድኀኒት፤
የዘለዓለም ማረፍያ፤ እውነተኛ መብልና መጠጥ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን
ትመሰላለች፡፡ ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ
ዅሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል
ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፡፡ በዚህ ቃለ ወንጌል ‹‹ስድስተኛው
ወር›› የሚለው ሐረግ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ
እመቤታችን ለብሥራት መላኩን ያመለክታል፡፡
በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ
እንዳመሰገነ ዅሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች ‹‹ስብሐት
ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም
በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ›› እያሉ እግዚአብሔርን በአንድነት አመስግነዋል (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡


እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድ እና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡
፡ ‹‹ሄዷል›› ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት በሰው አምሳል ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ዅሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ
ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና
የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ዅሉ
በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን
ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም
እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የተማጸነው በዚሁ ዕለት ነው፡፡


ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ ድኅነት እንደሚጸልዩ እና እንደሚያማልዱ፤ እንደ አብርሃም
ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ተግባራቸው አድርገው በሚኖሩ
ሰዎች ቤት እግዚአብሔር እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤት ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡


በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የመገለጥ ትምህርት በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና ‹‹ነበር›› እየተባለ
የሚነገር ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህንም እግዚአብሔር
ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡

ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመለየት በተጨማሪ ለተቸገሩ በመራራት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፤ ይቀደሳልና፡፡ ደግሞም ልጅ ለሌለን ልጅ፤ ዘመድ ላጣን ዘመድ በመስጠት ዘራችንንም ይባርክልናል፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ዅሉ ይፈጽምልናል፡፡ ይህ ዅሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ እኛም በርትዕት የተዋሕዶ ሃይማኖት እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባርም እንትጋ፡፡

አዘጋጅ- የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ትምህርት ቤት።

ጻድቅ ወሰማዕት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ)

እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ በአጤ (ዐፄ) ሱሱንዮስ አንገቷን ተሰይፋ ሰማዕት ለሆነችና ታላቁን ገዳም ራማ ኪዳነ ምሕረትን ላቀናች ለታላቋ ለጻድቅ ወሰማዕት ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ለዕረፍቷ በዓል በሰላም አደረሰን (የካቲት 29) ።

በጎንደር ክፍለ አገር ደራ ፎገራ አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አጠገብ ኮክታ ማርያም ተብሎ በሚጠራው ቦታ ውስጥ ተወለደች፡፡ዛሬም ይህ አካባቢ እመ ምዑዝ መንደር ይባላል፡፡የአባቷ ስም ቅዱስ ላባ የእናትዋ ስም ቅድስት ወንጌላዊት ይባላል፡፡ እነዚህም ወላጆቿ እጅግ ደጋግ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለተራበ፣ ለተጠማ የሚያዝኑና የሚራሩ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ በጎ ምግባር ያላቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በረከት ሁሉ በሥራ ላይ የሚያውሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ ስላልወለዱ ወደፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ ቸር አምላክ ስለሆነ እንደ ቅድስት ሐና እመ ሳሙኤል ጸሎታቸውን ሰምቶ የተመረጠች ደግ ሴት ልጅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በሚያዚያ 4 ቀን ተፀንሳ ታኀሣሥ29 ቀን ከእነሱ ተወለደች፡፡ ስመ ጥምቀቷ ማርያም ጸዳላ የዓለም ስሟ ሙዑዚት ሲሆን ሙዑዚት ማለት ጣፋጭ ማለት ነው፡፡ (ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ደግሞ የቆብ ስሟ ነው።)

በተወለደችም ጊዜ በእግርዋ ቆማ “በማኀየዊ ቸርነትህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኸኝ ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል” ብላ አመሰገነች ከእግዚአብሔር የተላከ መነኵሴም ወደ እርሷ በመሄድ የዳዊትን መዝሙር፣ መጻሕፍትንና የቤተክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ አስተምሯታል፡፡

ቅድስት እናታችን አምላኳን አስከ መጨረሻው በድንግልና ማገልገል ብትፈልግም ዕድሜዋ ከፍ ሲል ቤተሰቦቿ ዘርዐ ክርስቶስ ከሚባል አገረ ገዥ ጋር በቤተክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል አጋቧት ፡፡ እርሷ ግን በጫጉላ ቤት ሳሉ በእኩለ ሌሊት ባሏን “ወንድሜ ሆይ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ድንግልናችንን እንጠብቅ” አለችው፡፡ እርሱም “እሺ” ብሏት ይህንን ተመካክረው በጸሎት ሲተጉ አደሩ፡፡ ለእግዚአብሔር እየተገዙ በጾም በጸሎት በንጽሕናና በድንግልና ኖሩ በሌሊትም ወደ፡ባሕር ውስጥ እየገቡ ጸሎት ያደርጉ ጀመር፡፡ በመጨረሻም እርሷ በጳጳሱ በአባ ማርቆስ እጅ ስትመለኵስ ባሏም ድንግልናውን እንደጠበቀ በሰማዕትነት አንገቱን ተሰይፎ አርፏል፡፡ እርሷ በነበረችበት ዘመን ንጉሥ ሱስንዮስ “ሁለት ባሕርይ” የሚለውን የረከሰ የሮማውያንን ሃይማኖት ሕዝቡ ሁሉ እንዲያምን በማወጁ ምክንያት በአገራችን ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት ግጭት ስለተነሣና ከ8ሺህ በላይ ክርስቲያኖች በግፍ ተጨፍጭፈው ሲያልቁ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከእነ አቡነ ስምዖንና ከሌሎችም ቅዱሳንና ቅዱሳት ጋር ተሰልፋ ሰማዕትነትን ተቀብላ ለሃይማኖትዋ ምስክር ሆናለች፡፡ ባለቤቷ ዘርዐ ክርስቶስም በሰማዕትነት ዐርፎ ሰባት አክሊላት ወርደውለታል፡፡

እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሱስንዮስ በአደባባይ ሲያስገርፋቸው ሥጋቸው እየተቆራረጠ መሬት ላይ የወደቀውን የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ሰብስባ “ይህን ለንጉሡ እጅ መንሻ ስጡልኝ” ብላ ላከችለት፡፡ “ይህ የየሃይማኖት ፍሬ ነው፡፡ እኛስ አስከአሁን በሃይማኖታችን አለን፣ አንተ ብትገለን መከራም ብታደርስብን ሃይማኖታችንን አልካድንም፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ከሞት አስነሣን ይህን የሥጋዬን ቁራጭና የእህቶቼን የደናግላንን ሥጋ ብላው ፣ ደማችንን ጠጣ ሃይማኖትህ የከፋ፣ ሰነፍ፣ የረከስህ ነህ” ብላ ልካለታለች፡፡ መልእክተኞቹም ለንጉሡ ወስደው ሰጥተውታል፡፡

ሱስንዮስ አዋጁን እንዳወጀ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖንም ካህናትንና ክርስቲያን ልጆቻቸውን አነሳስተው እያስተማሩና እያጠነከሩ እያለ በጦር ተወግተው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡


ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት ግን እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስን፣ ቅድስት አካለ ክርስቶስን፣ ቅድስት እመ፡ወተትን … ወዘተ አነሳስተው ንጉሡን መክረውታል፣ ገሥጸውታል፣ ንጉሡ ግን ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የሃይማኖቷን ጽናት ስላየ ሥጋዋ እየተቆረሰ መሬት ላይ እስኪወድቅ ድረስ በብረት በትር አጥብቆ ያስገርፋት ጀመር፡፡
በመጨረሻም ምድር እየሰወረቻት ለመግረፍ የማይመቻቸው ቢሆን ከሌሉቹ ሰማዕታት ጋር አንገቷን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡ በዚህም ጊዜ ፍጹም ጨለማ ሆኖ ምድርም ተነዋወጠች፡፡ ስምንት ሺህ ዐሥር ቅዱሳንም በሰማዕትነት ዐረፉ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን አንገቷን በሰይፍ ቢቆርጧትም ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ገነትንና ሲኦልን አሳይቶ 14ቀን በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተቀመጠች በኋላ እንደገና እንደተኛ ወይም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ከሞት አስነሥቶ ወደ ቦታዋ መለሳት፡፡

እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤልም ከሞት ካስነሣት በኋላ መናኝ ሆና በየገዳሙና በየአድባራቱ እየሄደች ዓለምን ስትዞር ያቀናቻቸው ብዙ ገዳማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአባ ጉባ ተመሥርታ በግራኝ ወረራ ጠፍታ የነበረችውን ራማ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምን አቅንታ የወንድና ሴቶች መነኰሳት በጋራ አብረው ይኖሩ የነበረ ቢሆንም የበጎ ሥራ ጠላት የሆነው ሰይጣን በማኀበረ መነኰሳቱ መካከል ሊፈጥር ያለውን ክፉ ፈተና ለእናታችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጾላት በገዳሟ ውስጥ የወንዶችና የሴቶች መነኰሳት መኖሪያ የተለያየ እንዲሆን አድርጋለች፡፡

ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምም በመሄድ ላይ ሳለች በመንገድ ሰውን የሚበሉ ፍጡሮች ወደሚኖሩበት አካባቢ ስትደርስ 60 የሚሆኑ አገልጋዮቿን ለመብላት ይዘው ሳር ቅጠል እንዲበሉ በማድረግ ዓይናቸውን በጉጠት በማውጣት ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ዘጉባቸው ሰይጣንንም ያመልኩ ነበርና ከ4 ወራት በኋላም በዓል አድርገው ለመብላት ከእሳት ውስጥ ጨመሩአቸው፡፡ እነርሱ ግን ምንም አልሆኑም፡፡ ያን ጊዜም “እናንተ ሰዎች ምንድን ናችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡ ቅድስት እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስም ክርስቲያን መሆናቸውንና እነርሱ የሥላሴ ሕንጻ የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው ብትመክራቸው “ምን እንበላለን?” አሏት፡፡ እርሷም ከራማ ኪዳነ ምሕረት ስትነሳ የእህል ዘርን ለአገልጋዮቿ አስይዛ ስለነበር ከዚያ ስንዴ ወስዳ ዘራችው፡፡ስንዴውም በአንድ ቀን ተዘርቶ በቅሎ፣ ታጭዶ፣ ደርቆ፣ ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡


ቅድስት እናታችንም ቀምሳ ስታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም እንደዚህ እያደረጉ እየሠሩ እንዲበሉ አስተምራ አስጠምቃቸው ስድስት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታላቸዋለች፡፡ወንጌልን፣ ስንክሳርን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ግንዘትን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ አርጋኖንን ሁሉ በእጅዋ ጽፋ አስቀመጠችላቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጣላት በልጅዋ ምክንያት ስለ ደረሰባት ሀዘኖች አውርታላታለች፡፡ የፈለገችውንም እንድታደርግበት በእጅዋ ያለውን መስቀል ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሰጥታታለች፡፡ በዚህም መስቀል ባሕር ከፍላ ደቀ መዛሙርቶቿን አሻግራለች፡፡

እናታችን የአባታችን የአባ ኤዎስጣቴዎስን ገድል በማንበብና በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እርዳታ ባሕሩን በአጽፏ ተሻግራ ወደ አገረ ናግራን ሄዳለች፡፡ እንዲሁም በበትረ መስቀል እንደ ዘርዐ ቡሩክ ከባሕር ውስጥ የሰጠሙ የደቀ መዛሙርቶቿን መጻሕፍት ምንም ሳይሆኑ ማውጣት ችላለች፡፡ በሁሉም አገር እየዞረች ቅዱሳት መካናትን ትሳለም ነበር፡፡ ደብረ ደሞ ሄዳ “ሴቶች መውጣት አይችሉም” ቢሏት በሀዘን ስታለቅስ ቅዱስ ሚካኤል በሥውር ወስዶ አድርሷታል፣ አቡነ አረጋዊም ተገልጸውላት ባርከዋታል በዚያም ሥጋ ወደሙን ተቀብላለች፡፡


እናታችን ወደ ኢየሩሳሌምም ሄዳ ቅዱሳት መካናትን እየተሳለመች ለ7 ዓመታት ቆይታለች ቅዱስ ሚካኤልም በዓምደ ብርሃን እየመራት ተመልሳ ወደ አገራችን መጥታ በድጋሚ ከሱስንዮስ ጋር ተሟግታለች፡፡ ሙታንንም እያስነሳች እንዲመሰክሩላት ብታደርግም እርሱ ግን ከጥፋቱና ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም ነበር፡፡ የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ መልእክቷንም በንስር አሞራ አድርጋ እየላከች ትመክረው ነበር ፡፡

በአንድ ወቅትም በአገራችን እህል መታጣት ሆነና ቅድስት እናታችን ዝክር የምታደርግበት እህል አጣች፡፡ደናግል ልጆቿንም ጠርታ ትንሽ ዱቄት እንዲያመጡላት ነግራቸው በእርሱ ጸሎት አድርጋበት “ወደ ቦታው መልሱት” አለቻቸው፡፡ በማግስቱም እንሥራው ጋኑ ሁሉ በዱቄት ተሞልቶ አግኝተውታል፡፡ የካቲት ኪዳነ ምሕረትንም በዓል በደስታ አክብረዋል፡፡ መልአኩም ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ካመጣት በኋላ ዛሬ ገዳሟ ካለበት ቦታ ስትደርስ ከቦታዋ ላይ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ በቀስተ ደመና ተከቦ አይታ “ይህች ቦታ ምንታምር” ብላ ጠራቻት፡፡

በቦታውም ላይ በመድኃኔዓለም ትእዛዝ የቅድስት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀን ታህሣሥ14 ቀን በዕለተ ዓርብ ጧት በሰንሰል (በስሚዛ) እንጨት ጀምራ ማታ እንደተፈጸመ በ3ኛው ቀን እሁድ ታህሣሥ16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር በድርገት (በቁርባን) ጊዜ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አእላፋት መላእክት ጋር ወርዶ መቅደሱን ሲባርክ መቅደሱ በ4ቱ ማዕዘን ለጌታ ሰገደ። ለጌታ እንደ ሰገደ ዛሬም ድረስ ይታያል ጌታችንም “ይህ መቅደስሽ ሳይፈርስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ይቆይልሻል፡፡ በዚህ ቦታ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡ በምድርም ስምሽን የጠራ፣ መታሰቢያሽን ያደረገ፣ የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ የተረጐመ ሁሉ ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና ያልታሰበውን ለነዚህ ሁሉ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፡፡ ከሩቅም ከቅርብም ከቀኝም ከግራም መጥቶ መቅደስሽን ለተሳለመ ሁሉ እስከ 12ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ፡፡ላልምረው ቦታችን አላስረግጠውም፡፡ በረከቴም በእሱ ላይ በልጆቹም በንብረቱ ላይ ለዘለዓለሙ ይኖራል፡፡ ስለጾምሽ፣ ስለጸሎትሽ፣ ስለተጋድሎሽ፣ ስለ ስግደትሽ ሰባት አክሊል ሰጠሁሽ” አላት፡፡

ፃድቋ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ብዙ ገድል በሠራችበት ብዙ መነኰሳይያትን በአቋቋመችበት ገዳሟ በእመ ምዑዝ ኪዳነ ምሕረት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም የካቲት29 ቀን ዐረፈች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር መጥቶ ነፍሷን ተቀብሎ ወደ ገነት ወስዶ አኖራት፡፡ ባረፈች ጊዜ በሥጋዋ ላይ ታላቅ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ የታየ ሲሆን እንደ ፀሓይም ከጠዋት እስከ ማታ ያበራ ነበር፡፡ በመካነ መቃብሩዋም ላይ እስከ አርባ ቀን ድረስ ብርሃን ተተክሉ ታይቷል፡፡

ምንጭ፦ገድለ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ። ከእናታችን ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። በጸሎቷም ይማረን!።

ማርያም እንተ ዕፍረት

ይችም ቅድስት አስቀድማ ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ኃጢኣተኛ ነበረች። እርሷም ጐልማሶችን ወደርሷ ትማርካቸው ዘንድ በየራሱ በሆነ ሽልማትና ጌጥ ትሸለም ነበር። በአንዲትም ዕለት እንደ ልማድዋ ተሸልማ አጊጣ ሽቱም ተቀብታ ፊቷን በመስታዋት ተመለከተች የጉንጯ ቅላትና ደም ግባቷ፡የዓይኗም ወገግታና ጥራት ማማሩን አይታ እያደነቀች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች ከዚህም በኋላ በጎ ኀሳብ በላይዋ መጣ ሞትንና የዚህን ዓለም ማለፍ አሰበች። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስም ኃጢኣተኞችን እንደ ሚቀበልና ኃጢአትንም እንደሚያስተሰርይ ሰምታ በዝሙት የሰበሰበችውን ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ አላት ። ያላትን ይዛ ኼዳለች።

ዲያብሎስም ታመልጠኛለች ይኽነን ጊዜ ላስትታት ብሎ ቀድሞ ከምታውቀው አንዱን መስሎ፡በመልከ፡መልካም ወጣት አምሳል ከመንገድ ላይ ቆይቷት “ወዴት ትኼጃለሽ” አላት፤ ዝም አለችው፤ “አንቺ ባትነግሪኝ እኔ እነግርሽ የለም፤ እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቶ ልትገዢ ትኼጃለሽ” አላት፤ “አዎን” አለችው፤ ይኽም አይደለም “ፍቅሩ ያላለቀበት ወንድ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትኼጃለሽ” አላት፤ “አዎን” አለችው። ይኽም አይደለም “በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትኼጃለሽ” አላት፤ “አዎን” አለችው። ኹሉንም “አዎን አዎን ትያለሽ ማናቸው ነው ትክክል” አላት፤ ርሷም ተገልጾላት “እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ አልከኝ፤ ከዚኽ ዓለም ልዩ የሚኾን ጌታ መጥቷል፤ ፍቅሩ ያላለቀበት ወንድ መጥቶብሽ ላልከኝ የሰው ፍቅር አገብሮት ሊሞት መጥቷል፤ በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ላልከኝ “አዎን በጥቂት ትሩፋት ብዙ ክብር የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷልና ለርሱ የምቀባው ሽቱ ልገዛ እኼዳለኊ”ብላ ስሙን ብትጠራበት እንደ ትቢያ በኖ እንደ ጢስ ተንኖ ጠፍቶላታል፤ ከዚኽ በኋላ ሃድኖክ የሚባል ባለጸጋ ነጋዴ አለ፤ ኼዳ “ለነገሥታት የሚገባ ሽቱ አምጣ” ብላ ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ ሰጠችው፤ በአገራቸው “ሐሰት የለምና ይኽን ያኽልስ የሚያወጣ የለኝም” አላት፤ እርሱ የማያውቀው እናቱ የምታውቀው ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውለት የተረፈ ነበርና ከእንዲኽ ያለ ቦታ አለና ሽጥላት ብላው ሽጦላት አምጥታ ቀብታዋለች፤ ይኽም ብቻም አይደለም ጌታ ከእናቱ ጋር ግብጽ በተሰደደበት ጊዜ ሰሎሜም ፈያታዊ ዘየማንም ይዘውት ሳለ ከልብሱ ላይ ወዛ ቢያጥቡት ሰፈፈ ይኽም በዕቃ አኑረውት ነበርና ያም ተጨምሮበታል፤ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ ዋጋው እጅግ የበዛውን ይኽነን ሽቱ የመላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ ርሱ ቀርባ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፍስሳዋለች፤ ጌታችንም ለደቀ መዛሙርቱ “ይኽነን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች፤ እውነት እላችኋለኊ ይኽ ወንጌል በዓለም ኹሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበትእ ርሷ ያደረገችው ደግሞ ለርሷ መታሰቢያ እንዲኾን ይነገራል” ብሏታልና። (የካቲት6 ስንክሳርና መጽሐፈ ተአምኆ ቅዱሳን ንባብና ትርጓሜው መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ከጻፈው።)

ቀድሞ በዝሙት የኖረችበትን አስከፊ ሕይወት በመተው በቆራጥ ኅሊና ፍጹም ንስሓ ገብታ ገንዘቧን ሁሉ አውጥታ እጅግ ውድ የሆነውን ሽቱ ገዝታ ጌታችንን ስትቀባው ጌታችንም በፍጹም ንስሓዋ ተደስቶ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› በማለት አስደናቂ ትእዛዙን የሰጠላት ቅድስት ናት፡፡ ማቴ 26፡6፡፡ ይህንን የጌታችንን ትእዛዝ ልብ ብለን ካየነው በውስጡ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ስለ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው ራሱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ መሆኑን በዚሁ ልብ ይሉታል፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረት የቀድሞውን ሕይወቷን ስናየው ሁልጊዜ ከነጭ ሐር የተሠራ ልብስ የምትለብስ፣ ከሽቱ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ውድ ሽቱን ትቀባ ነበር፡፡ በወርቅም ታጌጥና በክፉ ሥራ ሁሉ ጸንታ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የዚህን ዓለም ጣዕም አጣፈጠላት፡፡ ነገር ግን ስለዚህች ሴትና ስለ ኃጥአን ሁሉ ጌታችን ከጌትነቱ ከፍታ ሳይለወጥ ከልዑል ዙፋኑ ወረደ፡፡ በሰዎች መካከልም ከእነርሱ እንደ አንዱ እየተመላለሰ አስተማረ፡፡

አንድ ቀን እንደልማዷ ማርያም እንተ ዕፍረት ነጭ ሐር ለብሳ፣ አጊጣና ተኳኩላ ፊቷን በመስታወት አይታ ውድ ሽቱ ተቀባች፡፡ ጉንጮቿ ቀያዮች፣ ዐይኖቿ የተዋቡ ሆነው ደም ግባቷ በጣም አማራት፡፡ እንደዚህ እየተመለከተች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች፡፡ ከዚህ በኋላ መልካም አሳብ በእርሷ ላይ አድሮ እንዲህ አለች፡- ‹‹ይህን ሁሉ ታስወግድ ዘንድ መልኬንም ትለውጥ ዘንድ ሞት ትመጣ የለምን? ይህ መልካም ሽታ ወደ ትልነትና ወደ መሽተት ይለወጣል፡፡ ይህስ ብርታት ፍጻሜው ጉስቁልናና ድካም አይለምን? ሊቀርቡኝ የሚወዱትስ የሚርቁኝ አይደሉምን? እንደዚህስ ከሆነ ዘለዓለም ከጥፋትና ከኩነኔ በቀር እንግዲህ ምን አገኛለሁ? የዚህን ዓለም ገንዘብ ብገዛ፣ ብነዳ ከድካም በዐይኖቼም ዕንባን ከማፍሰስ የሚያድነኝ ይኖራልን? ወይስ ይህ ሁሉ ከሞት ያድነኝ ዘንድ ይችላልን? ነፍሴ ሆይ! እንግዲህ ሁሉን ለሚገዛ ጌታ ምን ትመልሻለሽ? ከእውነተኛው ፈራጅ ዘንድ በአንቺ ላይ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! ንስሐ በሌለበት፣ ነፍስ የተናቀች በምትሆንበት ጩኸት፣ ልቅሶና ጩኸት ባለበት ቦታ የሚረዳሽ ማነው? ነጭ ሐርና ኅብሩ ልዩ ልዩ የሆነ ልብስ በመልበስ ደስ የምትሰኝ ሥጋዬ ሆይ በክብር ባለቤት በእግዚአብሔርና በመላእክቱ ፊት ራቁትሽን በቆምሽ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! በዚህ ዓለም የተደሰችው ምን ይጠቅምሻል?…›› እያለች ራሷን መመርመር ጀመረች፡፡
ከዚህ በኋላ በማመን ጸንታ እንዲህ ብላ አሰበች፡- ‹‹ስለ ኃጥአን ወደዚህ ዓለም የመጣ ስለ እነርሱ በመካከላቸው እንደሰው የተመላለሰ ይህ አይደለምን? የኃጢአተኛን መመለሱን ነው እንጂ ሞቱን አልሻም ያለስ እርሱ አይደለምን? ነፍሴ ሆይ ምሕረትስ ቅርብ ናት፣ ባለመድኃኒትም የራቀ አይደለም፣ ሌላ መድኃኒትሽን ተስፋ የምታደርጊበትስ አለን? መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዲቱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልጋት የሚሄድ አይደለምን? ባገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከማታል፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሷ ደስ የሚሰኝ አይደለምን? እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ የሚል እርሱ መድኃኒት ክርስቶስ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ለምን እሰንፋለሁ? ለምንስ ንስሓ አልሻም? እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ወደ እርሱ ሄጄ ራሴን በፊቱ እክዳለሁ›› ብላ ካሰበች በኋላ ተጽናናችና በፍጥነት ተነስታ ገንዘቧን፣ የገዛችውን ወርቋንና ብሯን ሁሉ ሰበሰበች፡፡

‹‹ምን አደርጋለሁ ይህን ገንዘብ ወስጄ ብሰጠው አይቀበልም እርሱ ፈጣሪ፣ ጌታና የዓለም መድኃኒት ነውና›› ብላ አሰበች፡፡

ከዚህ በኋላ ሽቱ ወደሚሸጥ ሰው ፍለጋ ሄደች፣ ያን ሰው ከጥንት ጀምሮ ታውቀው ነበርና ከእርሱ ዘንድ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቱን ገዛችና በደስታ ስትሄድ እነሆ ሰይጣን በወርቅ ያጌጠች ሴት መስሎ ወደ እርሷ መጣ፡፡ የዚህን ዓለም ምኞት እያጣፈጠ ይነግራት ጀመር፡፡ መብላትን፣ መጠጣትን፣ ያማረ ልብስ መልበስን፣ ሽቱ መቀባትን… ይህን ሁሉ ያሳስባት ጀመር፡፡ ጌታችንም በይቅርታው ብዛት የጠላት ዲያብሎስን ክፋት ገለጠላትና ‹‹ለበደልና ለኃጢአት ሥራ የተዘጋጀሁ አድርገኸኛልና ኃፍረትና ጉስቁልናንም በእኔ ላይ አምጥተሃልና አንተ ሰይጣን ከእኔ ወግድ›› ብላ በቁርጥ ነገር መለሰችለት፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የሃይማኖቷን ጽናት ባየ ጊዜ ከእርሷ ሽሽቶ ፈሪሳዊ ወደሚሆን ስምን ወደሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ ልቡናውን ያውከው ጀመር፡፡ እርሱም ጌታን በቤቱ ማዕድ ይመገብ ዘንድ ጋብዞት ነበርና፡፡ በልቡናው ያደረው ክፉ ሰይጣንም እንዲህ ብሎ እንዲናገር አደረገው፡- ‹‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ኃጢአተኛ እንደነበረች አያውቅም ነበር? ብሎ እንዲያስብ አድረገው፡፡››

“ከንቱ ነገርን ስትመለከቱ የኖራችሁ ዐይኖቼ ሆይ! ጌታን ታዩ ዘንድ ተሰጣችሁ፤ ርኩስን የምትዳስሱ እጆቼ ሆይ! የሰማያዊ ጌታን እግር ትዳስሱ ዘንድ ሰጣችሁ፤ ኃጢአተኛ ነፍሴ ሆይ! እነሆ ፈጽሞ ከፍ ያለ ባለሟልነትን አገኘሽ፤ ስላደረገልኝ ምን እከፍለዋለሁ› እያለች ታላቅ ልቅሶን አለቀሰች፡፡ የጌታንም እግር ይዛ በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ ታብስ ጀመር፡፡ አስቀድማ በልቧ እንዲህ ብላ አስባለችና ‹በጌታ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ወደ እርሱ ዘንድ እንድቀርብ ያደርገኛል፡፡ በሥራዬም ክፋት ካበረረኝ ግን ዳግመኛ አልድንም› ብላ አስባ ነበር፡፡ ከጌታም ባለሟልነትን ባገኘች ጊዜ ጨክና በራሱ ላይ ሽቱውን ጨመረች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋርም ልቅሶንና ልመናን አላቋረጠችም፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በእርሷ ላይ እንደበዛ ባየ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ በእርሷ ላይ ታላቅ መቅናትን ቀናባት፡፡ ተቆጥቶም ወደ ስምዖን ተመልሶ ልቡን አወከው፡፡ ‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነች ያውቅ ነበር› እንዲል አደረገው፡፡

ጌታችንም ስምዖንን ሁሉ ከእርሱ እንዳልተደበቀና ሀሳቡንም እንዳወቀበት እንዲረዳና እግዚአብሔርም በደለኞችን ማዳንና ከኃጢአታቸው ማንጻት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ እንዲያስተውል አደረገው፡፡›› ሉቃ 7፡36-50፡፡

ይህ እጅግ ውድ ዋጋ ያለው የማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መነሻ መገኛው ራሱ ጌታችን ነው፡፡ ይኸውም ነገሩ እንዲህ ነው፡- ‹‹ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን አረጋዊ ዮሴፍ ሕፃኑንና እመቤታችንን ይዞ ወደ ምድረ ግብፅ ሲሄዱ በመንገድ ላይ አንድ ፈረሰኛ ሰው አገኛቸውና ከእነርሱም ጋር ይሄድ ጀመር፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንገድ እንደደከመች ባየ ጊዜ ሕፃኑን አንሥቶ ፈረሱ ላይ አውጥቶ በጭኑ ታቀፈው፡፡ ያንጊዜም በፈረሱ ላይ የመልካም ሽቱ መዓዛ ይሸት ነበር፡፡ ወዙም ሲንጠፈጠፍ ባየው ጊዜ መልካም ሽታም እንዳለው ባየ ጊዜ ሻሹን ከራሱ ላይ አውልቆ የሕፃኑን ወዝ ጠረገለትና ቆይቶ ሕፃኑን ለእናቱ ሰጥቷት በጐዳናው ሄደ፡፡ እቤቱም በደረሰ ጊዜ ልብሱን ታጥበው ዘንድ ለእናቱ ሰጣት፣ እርሷም በሻሹ ላይ ያለውን መልካም ሽታ ካየች በኋላ በማጠቢያ ባስቀመጠችው ጊዜ ከሻሹ ውስጥ ሽታው እጅግ የሚያስደስት መልካም ዘይት ወጣ፡፡

እርሷም ደስ ተሰኝታ ከቅባቷ ጋር በማሰሮ አድርጋ አስቀመጠችው፡፡ ያም ዘይት ባለበት በዚያች መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የሽቶውን መዓዛ ያደንቁ ነበርና ስለዚህ ያች ሴት ከአገረ ገዥው ጋር እንዳያካስሷት ፈርታ በብዙ ገንዘብ ሽቱ ከሚገዙ ነጋዴዎች ለአንዱ ሸጠችለት፣ እርሱ ግን ምን እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡ ያም ዘይት ብፅዕት ማርያም እንተ ዕፍረት እስክትምጣ ድረስ ለብዙ ዘመን በእርሱ ዘንድ በዚያ ኖረ፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረትም ከእርሱ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ገዝታ በጌታችን ሥጋ ላይ አፈሰሰችው፡፡ እነሆም ይህ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነው ሽቱ ከጌታችን ዘንድ እንደተገኘ የታወቀ ሆነ፡፡ ያም በፈረስ ላይ ተቀምጦ ጌታችንን በሕፃንንቱ በጭኑ አቅፎ የያዘው ፈረሰኛ ሰው ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ያመነበት ፊያታዊ ዘየማን (ጥጦስ) ነው፡፡››

ማርያም እንተ ዕፍረት ጌታችን ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ ዐርፋለች፡፡ የንግሥ በዓላቶቿ መጋቢት 21 ቀን የጌታችንን እግር ሽቱ የቀባችበት ሲሆን የካቲት 6 ቀን ደግሞ ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ጥቅምት 1 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሏ እንዲሆን አባቶቻችን ሕግ ሠሩልን፡፡ የማርያም እንተ እፍረትን ገድሏንና ድርሳኗን የጻፈላት ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡
የቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረትን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡( ገድለ ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት፣ የጥቅምትና የካቲት ስንክሳር)

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.comS/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org