ደብረ ሥልጣን፡ እኅታማማቾችን ባላንጣ ያደረገው ገዳም

ኢየሩሳሌም በተለይም ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት የሚጓዝ ማንኛውም ጥቁር ክርስቲያን በአውሮፓውያንና በአረቦች በተያዙ ቅዱሳት መካናት መካከል የትንሣኤው ቤተክርስቲያን ኩታ ገጠም በሆነ ቦታ ላይ ኢትዮጵያዊውን የጥቁሮች ገዳም ሲያይ ልቡ በሐሴት መሞላቱ አይቀርም፡፡

በእርግጥ ለክርስቲያን ፡ ሁሉ ሀገሩ፣ ሁሉ ወንድሙ ቢሆንም በመልኩ እንደ እንግዳ የማይታይበት እርሱም እንደ ሌሎች ሁሉ በክርስትና ቅድሚያ ጥሪ ከደረሳቸው ወገን መሆኑን ማወቅ ለደካማው ሥጋ የሚሰጠው ልዩ ዕረፍት አለ፡፡ ያ ቦታ ደግሞ ጥንታዊው በኢየሩሳሌም ካሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘጠኝ ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው ደብረ ሱልጣን ወይም በሃገሬው ቋንቋ ዴር ሱልጣን የተሰኘው ገዳም ነው፡፡ ገዳሙ በኢትዮጵያ ሥር የሚተዳደር ቢሆንም “የይገባኛል” ጥያቄ በሚያነሱት የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳትና ምእመናን ጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም በቦታው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በእምነትና ምሥጢራት አንድ በሆኗቸው ግብጻውያን አቻዎቻቸው ይደበደባሉ፣ ይዛትባቸዋል፣ ባዕታቸው ይወረራል፡፡

ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ወዳጆች በሰሙነ ትንሤኤው ውስጥ ሆነን በትንሳኤው መካን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያን ይዞታ ለመጎብኘት የምናብ ጢያራችን ላይ ልናሳፍራችሁ ከዛሬው የእለተ አርብ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ማረፊያ ላይ ተገኝተናል መልካም ጉዞ፡፡

የዴር ሡልጣን ገዳም ከ፱፻፶ (1950) ዓመተ ዓለም ገደማ ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት ዘመን ድረስ ያለ አንዳች ባላንጣ ለኢትዮጵያውያን ማረፊያና መኖሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ኢየሩሳሌምና አካባቢው በሮማውያንና ባይዛንታውያን እየተገዛ ሲተዳደር በቆየባቸው ዘመናት ጭምር የኢትዮጵያ ሕጋዊ ንበረትነቱና ይዞታነቱ በይበልጥ ተረጋግጦ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በቦታው ላይ መኖሪያና ቤተ ጸሎት ሠርተው ለ፫፻ (300) ዓመታት ያህል ይዞታቸውን በሰላም አስጠብቀው ኖረዋል።

የመጀመሪያው እስላማዊ ንጉሥ ዑማር ኢብን አል ካታብ ኢየሩሳሌምን እንደተቆጣጠረ የዑማር ቃል ኪዳን በተሰኘው ዐዋጁ አማኝነት ኢትዮጵያውያን በዴር ሡልጣን ላይ ያላቸውን የባለቤትነትና የይዞታ ባለመብትነት በማረጋገጥ የሰጠው ይፋዊ መግለጫም የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ዴር ኤል ሡልጣንንና ሌሎችንም አያሌ ንብረቶች ከጥንት ጀምሮ በይዞታዋ ሥር አድርጋ ስትገለገልባቸው እንደነበረ ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች በየዘመኑ መዝግበውታል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ ስለ ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ጽሑፍ በ፲፫፻፸፫ (1373) ዓ.ም. እና በ፲፱፻፸፩ (1971) ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ስለ ንብረቶች ባለቤትነት የወጡ ማስታወቂያዎች ጭምር ኢትዮጵያ በከተማዋ የንብረቶች ባለቤት እንደነበረች ይጠቁማሉ፡፡

በብሪቲሽ ቤተመዘክር የሚገኝ አንድ ስለ ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ጽሑፍ ከ፲፬፻፸፫ (1473) ዓ.ም. በፊት ኢትዮጵያ በጎልጎታ መቅደስ እንደ ነበራት መዝግቦታል፡፡ በተጨማሪም ዐፄ ዘርዓያዕቆብ በ፲፬፻፴ (1430) ዓ.ም. ለዴር ሡልጣን ገዳም የላኩት ስጦታና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅድሳት መካናት ንብረቶች በኢየሩሳሌም ማስታወቂያ ተገልጾአል። ከእነዚህ መረጃዎች ኢትዮጵያ እስከ ፲፭ (15) ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የንብረቶቹ ባለቤት እንደነበረች ማስተዋል ይቻላል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ እነዚህ ሕጋዊ የታሪክ ማስረጃ ሰነዶች እያላት ግብጻውያኑ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያውያንን ያህል ቀርቶ አንዳች ቦታ ሳይኖራቸው ዴር ሡልጣን “የእኛ ነው” ለማለት እንዴት በቁ?

ታሪክ እንደሚነግረን በ፲፯፻፸፭ (1775) ዓ.ም. ኢብራሃም ጃወሀሩ የሚባል ግብጻዊ ኢየሩሳሌም ሔዶ የሚጠጋበትና የሚያስጠጋው አጣ፡፡ ግራ ሲገባው ወደ ኢትዮጵያውያኑ በመሔድ “የሃይማኖት ወገናችሁ ነኝ” ብሎ ማረፊያ ሲለምናቸው እነርሱም በደግነት አስጠጉት፡፡ ከዚያ በኋላ በገዳሙ በነበረው ቆይታ ከኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጋር በመላመዱ ቀስ በቀስ ይዞታውን እያስፋፋ ሔደና “ቀሲስ ጆርጅ” የተባለ። የሚያግዘው ግብጻዊም ከሀገሩ አስመጣ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ አስቀመጠው። ጥቂት ቆይቶ ይህ በ”አስጠጉኝ” ልመና የመጣ ግብጻዊ ተስፋፊ ያልተጠበቀ ችግር በኢትዮጵያ መነኮሳት ላይ አደረሰ፡፡

አምባሳደር ተፈራ ኃይሌ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅድሳት መካናት ንብረቶች በኢየሩሳሌም በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹትም በንብረቶቹ ላይ ተቀናቃኝ የተነሣው በ፲፱ (19)ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ መሆኑን ጠቁመው በወቅቱ በኢየሩሳሌም ገብቶ የነበረው ወረርሽኝ በሽታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያስረዳሉ። ወረርሽኙ ኢትዮጵያውያን ምእመናንን ፈጃቸው፡፡ በዚህ አሳዛኝ አደጋ ተጠቅመው የአርመንና የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በገዳሙ የነበሩትን መጻሕፍት፣ መዛግብትና ሰነዶች ወዘተ “ወረርሽኝ ያሰራጫሉ’ ” በሚል ሰበብ እንዲቃጠሉ የኢየሩሳሌም ገዢ ለነበረው ለቱርክ መንግሥት እንደራሴ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ እንደራሴውም በቀረበለት አቤቱታ መሠረት ሰነዶቹ እንዲቃጠሉ አደረገ፡፡ በዚህም እርምጃ የኢትዮጵያውያን የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ረጃዎች በእሳት ቃጠሎ ወደሙ፡፡ ግብጾቹም ያለአንዳች ስጋት የመቅደሱንና የገዳሙን ቁልፎች በእጃቸው አደረጉ፡፡ ወረርሽኙ ካለፈም በኋላ ግብጾቹ ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱትን ኢትዮጵያውያን ምእመናን መጸለያና መጠለያ ነፈጓቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ምእመናንና መነኮሳቱም ንብረታቸውን መነጠቃቸውንና የደረሰባቸውን ግፍ በመዘርዘር ንብረቶቹ እንዲመለሱላቸው ለቱርክ መንግሥት እንደራሴ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡

እ.ኤ.አ በ፲፱፻፸ (1970) ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል አከባባር ወቅት ግብጻውያኑ ለጸሎት በሔዱበት በእስራኤላውያን የፀጥታ ኃይሎች ተከላካይነት ኢትዮጵያውያኑ የሁሉቱን አብያተ መቅደስ ቁልፎች በመለወጥ በእጃቸው አስቡ፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያውያኑ ፍላጎት ወረራን በኃይል ማስመለስ ሳይሆን ሁለቱ ወገኖች ያላቸው ማስረጃ ከሥር ጀምሮ ታይቶ በገዳሙ የባለቤትነትና የይዞታ ጭብጥ ላይ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበት ነበረ። በእስራኤል መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔና “ገዳሙን አጥተን ከምንቆይ ቁልፉን በእጃችን አስገበተን እንዲከበር እንከራከር” በሚለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፈቃድ ቁልፎቹ ተቀየሩ፡፡ ኮፕቶቹም ከ፲፱፻፶፩ (1951) ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፹፩ (1981)ዓ.ም. እኤአ ሊታዩልን የሚገቡ ቀሪ ሰነዶች በሚልና አስተዳደሩን ያወኩትን ይዞታን የማስፋፋት ግድያዎችን ለመግታት የኦቶማን ቱርክ አዝ እኤአ በ፲፰፻፴፭ (1835)ዓ.ም. ያወጣውን የ “ባለህበት ዕርጋ” ሥርዐተ እግድ (irman of Zlcede) ወይም ‘Status Quo Are’ በመጥቀስ የአብያተ መቅደሱን ቁልፎች በኃይል መቀየር ተቃውመው ለኢየሩሳሌም ጠቅላይ ፍ/ቤት ከሰሱ፡፡ ጠቅላይ ፍ/ቤቱም መንግሥት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የመሸጋገሪያ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል ብሎ ስለነበር የእስራኤል መንግሥት በ፲፱፻፹፩ (1981)ዓ.ም. እኤአ የሚኒስትሮች ኮሚቴን አቋቋመ፡፡ ሁለቱም ወገኖች ኮሚቴው ድረስ መረጃቸውን አቅርበው የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ኢትዮጵያውያኑ ቁልፎቹን ይዘው እንዲቆዩ የሚል ውሳኔ ቀረበ፡፡

አሁን ላይ የባለቤትነት ጥያቄው በፍርድ ቤት እየተካሄደ ቢሆንም የግብጽ ቤተክርስቲያን ሀገሪቱ ያላትን የመካከለኛው ምሥራቅ ተቀባይነት እንዲሁም ተጽዕኖ በመጠቀም ባገኘችው አጋጣሚ የባለቤትነት ጥያቄዋን እያጎላች ትገኛለች፡፡ የዛሬ ሳምንት ባነሳነው ርእስ ላይ እንደተመለከትነው ሁለቱን የመካከለኛው ምሥራቅ ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናትን በማሳመን ፍትህ የራቀው መግለጫ እስከ ማውጣት ደርሳለች፡፡ ምንም እንኳን የባለቤትነት ክርክሩን የመርታት አቅም እንዳላት የምትታመን ብትሆንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩ ላይ ያላት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑ ገዳሙን የመነጠቅ ዕድሏን እንደሚያሰፋው ይታመናል፡፡

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በሰላምና በፍቅር ይጠብቅ! ለዘገባው በዋነኝነት የሚያዚያ ፳፻፭ (2005) ዓ.ም. አዲስ ጉዳይ መጽሔትን እና የተዋሕዶ ሚደያ ማዕከል ዘገባዎችን ተጠቅመናል፡፡

የጻድቃኔ ማርያም ገዳምን ያውቁት ኖሯል?

ገዳሟ ከወረዳው ከተማ ሠላድንጋይ በስተምሥራቅ አቅጣጫ በእግር ጉዞ የዐሥር ደቂቃ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት የተመሠረተች ገዳም ናት፡፡ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስሥት ቱርኮች ግብፅን ወረው ክርስቲያኑን ፈጅተው በዚያው የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናትን ባቃጠሉና በፈጁት ጊዜ በወቅቱ ከተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የደብረ ምጥማቅ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡

ከወረራውና ከቃጠሎው በፊት አስቀድመው ቀሳውስቱ ጽላቷን አውጥተውና ሸሽገው አስቀምጠዋት ስለነበር በጊዜው አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የሚባሉ መነኩሳት ከብዙ ተከታዮቻቸው ጋር በሱዳን በኩል አድረገው ወደ ሀገራችን አምጥተው ጽላቷን ለአጼ ዘርዓያዕቆብ እንዳስረከቡ ከገዳሟ የተገኙት ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ንጉሡም ጽላቷን ተቀብለው ጅባት፣ ከዚያም አንጦጦ፣ በበረህ ተራራ ላይ፣ ደብረ-ብርሃንና በሌላም ስፍራ በማዘዋወር አስቀምጠዋታል፡፡ ከዚያ በኋላ አፄ ዘርዓያዕቆብ በተገለፀላቸው ራእይ መሠረት አሁን ደብረ ምጥማቅ እየተባለ በሚጠረው ስፍራ ቤተ ክርስቲያን አሳንጸው የቤተክርስቲያኒቱም ስም ግብጽ ባለው መጠሪያዋ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ደብረ ምጥማቅ ተብላለች፡፡

ከብዙ ዘመን በኋላ ግራኝ አህመድ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ሲያቃጥል ከተቃጠሉት መካከል አንዷ ይህች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ሆኖም ከወረራው በፊት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ በራይዕ በተገለፀላቸው መሠረት የቤተ ክርስቲያኑን ቅርስና ንብረት አሁን ፃድቃኔ ማርያም መካነ ቅዱሳን ገዳም በሚባለው ዋሻ ውስጥ ሰውረውታል፡፡

በኋላም በተቃጠለችው ቤተክርስቲያን ሌላ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በእርጅና ምክንያት ፈርሶ ስለነበር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንድ ኢጣሊያዊ መሃንዲስ ልከው በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም. ቤተከርስቲያኑን አሠርተዉት ነበር፡፡ በአሁኑም ሰዓት ከቆይታዋ የተነሳ በማርጀቷ ሌላ ቤተክርስቲያን ለማሠራት የግንባታ ፕላን ተዘጋጅቶ ቤተክርስቲያኗን ለመሥራት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ይህች ቤተክርስቲያን / ገዳም ብዙ ዕድሜ ያስቆጠረች ብትሆንም ታላቅ ዕውቅና ያገኘችው ከ፲፱፻፺ዎቹ ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ከ፴ ሰዎች በማይበልጡ የተጀመርው የጉብኝት ጉዞ በአሁኑ ጊዜ በዓመት ከ፻፶ ሺህ- ፮፻ ሺህ ሕዝብ በላይ ወደ ገዳሟ እንደሚመጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የፃድቃኔ ማርያም መካነ ቅዱሳን ገዳም ዓመታዊ በዓላት መስከረም ፳፩፣ ኅዳር ፳፩፣ ጥር ፳፩፣ ግንቦት ፳፩ እና ነሐሴ ፲፮ ናቸው፡፡ በተለይም በግንቦትና በነሐሴ በሚከበረው በዓሏ ላይ የሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በዚህ ቅዱስ ስፍራ በተለያዩ ደዌ የተያዙ ሰዎች ሲፈወሱ ማየትና መስማት ቦታውን እጅግ ታላቅ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያንና የሕንድን አብያተ ክርስቲያናት ያስቆጣው የመካከለኛው ምሥራቅ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ምንድነው?

በዚህ ሳምንት በግብጽ የተካሄደውን  ፲፭ኛው (15) ዙር የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መግለጫ ተከትሎ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጉባኤውን ውሳኔ አንድ ነጥብ በመቃወም መግለጫ አውጥታለች፡፡ ይህ ዓይነቱ መግለጫን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. ከተካሄደው ፲፫ (13)ኛው ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ መውጣቷ የሚታወስ ነው፡፡

ለመሆኑ ይህ በአብያተ ክርስቲያናቱ ቅሬታ ያመነጨው የመካከለኛው ምሥራቅ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ክፍተት ምንድነው? ለምንስ ነው ቅሬታ የሚነሳበት? የሚለውን በዚህ ሳምንት የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን ለመቃኘት እንሞክራለን አብራችሁን ሁኑ፡፡

የሠሜን አፍሪካንና የእስያን ምዕራባዊ ክፍልን የሚያካልለው የመካከለኛው ምስራቅ በአብዛኛው ዐረብኛ ተናጋሪ የሆኑ ኢስላማዊ ሀገራትን የሚይዝ ሲሆን ይህ ዐረብኛ ተናጋሪ ኢስላማዊው ሕዝብ የከባቢውን ማኅበራዊ፣ ምጣኔሀብታዊና ፖለቲካዊ አቅም ይቆጣጠራል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ሆኑ ዐረባዊ ያልሆኑ ሕዝቦች ለልዩ ልዩ ጫናዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡

የሚገርመው ይሄው አካባቢ ዐረባዊ መልኩ እንዲህ ከመስፋፋቱ በፊት ቀደምት የክርስትና መነሻና መስፋፊያ መሆኑ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋለ ሥጋዌውን የፈጸመው በዚሁ አካባቢ ባሉ የእስራኤልና የፍልስጤም ግዛቶች ነው፡፡ ሐዋርያትም በርካታ አገለግሎቶች ያከናወኑት በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ፣ በግብጽና በመሳሰሉት ሀገራት ነው፡፡ ከ፭ (5)ቱ ታላላቅ መናብርት ውስጥ በዚህ ክልል  ውስጥ የማይገኘው የሮም መንበር ብቻ ነበር፡፡ ትልልቆቹ የክርስትና ትምህርት ቤቶች አንጾኪያና እስክንድርያም የተገኙት ከዚሁ ግዛት ነው፡፡

ይህ አካባቢ የቤዛንታይን ክርስቲያናዊ መንግስት በሙስሊሞች መሸነፉን ተከትሎ በተስፋፉት እስላማዊ ስልጣኔዎች ምክንያት ክርስቲያኖች በግዳጅ ለመስለም፣ ለመፈናቀልና ለሞት በመዳረጋቸው በአካባቢው የሚኖሩ የክርስቲያኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በ፲፱፻፺ (1990)ዎቹ አካባቢ በአካባቢው ካሉ ሕዝቦች ፲፫ (13)በመቶው ክርስቲያኖች የነበሩ ሲሆኑ ነገር ግን ባለፉት መቶ ዓመታት በአርመናውያን፣ ግሪኮችና አሶሪያውያን ክርስቲኖች ላይ የተካሄዱ ጭፍጨፋዎች፣ የኢስላማዊ የሽብር ቡድኖችና አክራሪ ኢስላማዊ መንግስታት መስፋፋትን ተከትሎ  የዛሬ ፭(5) ዓመት በ፳፻፲፪ (2012) ዓ.ም. በተደረገ ጥናት የክርስቲያኖች ቁጥር ወደ ፭ (5)በመቶ መውረዱ ተመላክቷል፡፡

ይህንን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ኅብረቶችና አንድነቶችን በማስፈን በችግሮቻቸው ዙሪያ ለመነጋገርና መፍትሔ ለማስቀመጥ እየሞከሩ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል የዛሬ የውይይታችን ማዕከል የሆነው የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ዓመታዊ ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤው በብጹአን ወቅዱሳን ፓትሪያሪኮች ከሚደረገው ውይይት በተጨማሪው በተዋረድ የጳጳሳት፣ የካህናትና የነገረ መለኮት ምሁራን የሚገኙበት ቋሚ ኮሚቴዎች እንዳሉበት መግለጫዎቹ ያመላክታሉ፡፡

መጋቢት ፪ / ፲፱፻፺ (2/1990)ዓ.ም. በግብጽ ዋዲ አል ናጥሩን የአባ ቢሾይ ገዳም የመጀመሪያውን ጉባኤ ያካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መንበራቸው በመካከለኛው ምስራቅ  የሚገኙ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኪልቂያ ካቶሊኮስ የሚያጠቃልል ሲሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ካልተከሰቱ በስተቀር በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡ ጉባኤው አብያተ ክርስቲያናቱ በመካከለኛው ምርራቅ እንደመገኘታቸው በአካባቢውና በኦርየንታል ኦርቶዶክስ ዙሪያ ባሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ በተለይም በኢኮሚዩኒካል አንድነቶች (በአብያተ ክርስቲያናት ኅበረት)፣ በነገረ መለኮት ውይይት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳዮችና በአብያተ ክርስቲያናቱ ግላዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል፡፡

በ፲፱፻፺፩ (1991) ዓ.ም. በሶሪያ የተካሄደው ሁለተኛው ጉባኤ መግለጫ እንደሚያመላክተው ጉባኤው ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ ሌሎች የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናትን በማካተት የዛሬ ፷ (60) ዓመት በ፲፱፻፶፰ (1958)ዓ.ም. የተካሄደው የአዲስ አበባ ጉባኤ ተከታይ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ቢያሳውቅም ባለፉት 27 ዓመታት ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳየም፡፡ ስለ ጉባኤው ቀደም ሲል አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዘመነ ፕትርክናቸው በወቅቱ የነበሩትን የሦስቱንም አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች የጠየቁ ሲሆን በወቅቱ የመለሱላቸው መልሶች አንደኛው ጉዳዩ የሚመለከተው መንበረ ፓትርያኮቻቸው እና ዋና ማዕከላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የግብጽ እስክንድርያ፣ የሶርያ አንፆኪያ እና የአርመን ቂልቅያ መንበሮችን መሆኑን እንዲሁም የምክክሩ ዓላማም በወቅቱ በመካከለኛው መሥራቅ የነበረውን የአክራሪዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ፣ በተጨማሪም ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ሌሎቹን ለማግለል ሳይሆን የመካከለኛው ምሥራቅ ችግር ከሌሎቹ ስለሚለይ ያንን የተመለከተ ጉባኤ መሆኑን ገልጸው እንደነበረ የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ዘገባ ያመላክታል፡፡

ጉባኤው ዘንድሮ እና በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በተካሄዱ ውይይቶች ላይ ከሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ባሻገር የኢትዮጵያንና የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በአብያተ ክርስቲያናቱ ዘንድ ጥያቄ አምጥቷል፡፡ በዴር ሱልጣን ገዳምና በህንድ የያዕቆባዊት የሦሪያ ቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረገው ጉባኤው ጉዳዩ ከግብጽና ሦሪያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስለሚነካካ መነሳቱ የሚያስከፋ ባይሆንም በአንድ ወገን በቀረበ መረጃ መሠረት አቋም መያዙ ነበር ተቃውሞ እንዲገጥመው ያደረገው፡፡ እስቲ ሁለቱን ጉዳዮች እንመልከታቸው፡፡

በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቀረበውን በዴር ሱልጣን የይገባኛል አቤቱታ ምክንያት በማድረግ ፫ቱ ቅዱሳን ፓትሪያሪኮች በ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም. በዕለተ ትንሣኤ ዋዜማ ኢትዮጵያን መነኮሳት የሃገራቸውን ሰንደቅ አዓማ በርስት ምድር ዴር ሱልጣን መትከላቸውን “ትንኮሳ” ብለው የገለጹት ሲሆን ዴር ሱልጣን የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ይዞታ እንደመሆኑ መሰል ትንኮሳዎችን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡ የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን በኩል ያለውን ብቻ በመስማት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ሳያማክሩና በርካታ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ትውፊታዊ ማስረጃ ያለውን የኢትዮጵያ ቤ/ክ የባለቤትነት መብት ወደ ጎን በመተው ያስተላለፉት ውሳኔ ኢፍትሐዊ መሆኑን በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ግንኙነት መምሪያዋ በኩል መግለጫ ሰጥታበት ነበር፡፡

ሰሞኑ ደግሞ የኒቂያ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በተደረገበት ፲፭ኛው (15)ጉባኤ ደግሞ የሶሪያ ቤተ ክርስቲያን ዘንድሮ በመጋቢት ፳፻፲፯ (2017) ዓ.ም. ያዋቀረቺው  ዓለምአቀፋዊ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብጹዕ ማር ባስሊዮስ ዮሴፍን በህንድ የሶሪያ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ አድርጎ በመሾም በአንድ ሀገር ውስጥ ከማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲን ጋር ትይዩ ቤተ ክርስቲያናዊ መዋቅር መመሥረቷን በማድነቅ ከሶሪያ ቤተክርስቲያን መዋቅር ውጪ ካሉ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር የምሥጢርና የነገረ ሃይማኖት አንድነት እንዳይፈጸም የተወሰነውን ውሳኔ ጉባኤው መቀበሉ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስቆጥቷል። መግለጫው የማላንካራ ቤተ ክርስቲያንን “ተገንጣይ” ማለቱ የህንድ ቤተ ክርስቲያን ያላትን መንፈሳዊ ስልጣንና አንድነት “የናደ ነው” ብላዋለች፡፡

በ፲፭ኛው (15) ጉባኤ መግለጫ የአርመኑ የኪልቂያ ፓትርያርክ አቡነ አራም ቀዳማዊና የግብጹ ፓትሪያርክ አቡነ ታዎድሮስ ከሶሪያው ፓትሪያርክ አቡነ ኢግናጥዮስ ኤፍሬም ሁለተኛ ጋር በመሆን ሁለቱን የህንድ ካቶሊኮሶች ወደ እስክንድርያ አምጥቶ ለማደራደርና ለማስማማት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢጠቅሱም የህንድ ማላንካራ ቤተ ክርስቲያን “የአርመን ኦርቶዶክስ የቅድስቲቱ ኢታችማንዴዝ እናት መንበር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባልተገኙበት የተካሄደ ጉባኤ ይህንን የመወሰን መብት የለውም” ስትል ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች፡፡

በህንድ ከፈረንጆቹ ፲፱፻፸፬ (1974)ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት (በብጹዕ ወቅዱስ ባስሊዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ የሚመራ የማላንካራ  ሶሪያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በሶሪያ የአንጾኪያና የመላው ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበር ሥር ያለው የህንድ የሶሪያ ቤተክርስቲያን) ሲኖሩ በመካከላቸው ከፍተኛ የሕጋዊነትና የባለቤትነት ክርክሮችና ግጭቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ጉዳያቸውን የተመለከተው የህንድ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱን ቆጥሮ እስከማካፈል ድረስ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። በቅርቡም የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሳውን ጥያቄ ተመልክቶ ሕጋዊ መብቷን ማረጋገጡ በመግለጫው ላይ ተመላክቷል፡፡ በቅርቡ የሶሪያ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ካቶሊኮስ ለሕንድ መሾሟ ውጥረቱን እንዳያሰፋው ሲሰጋ ነበር፡፡

እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን አባቶች መልካሙን መንገድና ዐሳብ እንዲያሳያቸው እየጸለይን ቤተ ክርሰቲያን አንድነቷ የተጠበቀ ሰላማዊት የክርስቶስ ማኅደር እንድትሆን በመመኘት የዛሬውን በዚህ አበቃን፡፡

ሚሊዮን ሰማዕታት፡ የአርመን ኦርቶዶክሳውያን ሰማዕታት የ፻፲ (110)ኛ ዓመት ማስታወሻ

ከመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ፍቅር ቲያትር በኩል ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ የሚያልፍ ሰው ዓይኑ ከአንድ ጠባብ ነገር፣ ግን ውብ ኪነ ሕንጻን ከሚያሳይ ቤተ ክርስቲያን ጋር መላተሙ አይቀርም፡፡ ሕንጻው የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን አርመናዊያኑ ቤተ ክርስቲያኑን በቋንቋቸው “ሶርፕ ኬቩርክ ኤኬጌስቲ” (Սուրբ Քեւորք եկեղեցի) ይሉታል።  የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ውስጥ በጉልህ ከሚታየው ቤተ መቅደስ ባሻገር ከቤተ መቅደሱ በስተግራ የሚገኝና በቅርብ ካልሆነ ሳያስተውሉት የሚታለፍ ከነጭ ዕብነ በረድ የተሠራ የመታሰቢያ ሐውልት አለ፤ የአርመናውያን ሰማዕታት መታሰቢያ።

ሰላም ውድ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዕድምተኞች በዚህኛው የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዓምዳችን በበዓለ ትንሣኤው ሰሙን ምክንያት በወቅቱ መታሠሥ ያልቻልነውን አርመናውያን ኦርቶዶክሳውያን በኢስላማዊው የኦቶማን ቱርክ መንግስት የደረሰባቸው ጭፍጨፋ የዚህ ሳምንት የኃሠሣችን አካል አድርገነዋል፤ ሰናይ ንባብ!

የአርመን አካባቢ በሁለቱ ሐዋርያት ማለትም በበርተለሜዎስና ታዴዎስ ክርስትና የተሰበከባት ሲሆን ከበርካታ የክርስትና የመከራ ዘመናት በኋላም  በ፫፻፩ (301)ዓ.ም. ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርጋ የተቀበለች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡ የአርመን ቤተ ክርስቲያን አሁንም ድረስ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ ፰ (8)መሠረት የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማት ስትሆን ከሀገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት የዚችሁ የአርመን  ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም አርመንና ኦርቶዶክሳዊነት በአንድ ሳንቲም ላይ ያሉ ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ስለ አርመን ቤተ ክርስቲያን ያለውን ትውውቅ ከዚህ ጋር ገትተን ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንግባ።

በምሥራቅ አናቶሊያ ከፍ ያሉት ሜዳዎችና የኖህ መርከብ ያረፈበት አራራት ተራራ ሺህ ዓመታትን ስላስቆጠረው የአርመናውያን ህላዌ ምስክር ነው፡፡ አርሜንያውያን እስከ ፲፱፻፳፫ (1923) ዓ.ም. ድረስ ከ፫ (3)ሺህ ዓመታት በላይ በዚህ አፈር ላይ ተነስተው ኖረዋል። ምንም እንኳን አሁንም ጥቂት የተረፉ ቢኖሩም ታሪካቸው በሚገርም ሁኔታ ተሰርዟል።
አርመናውያን ከእናት ምድራቸው ተሻግረው በአሁኗ የቱርክ መሬት ማለትም በቁስጥንጥንያ (ኢስታቡል)፣ በአንቶሊያና በዙሪያው ባለው ምድር መስፈር የጀመሩት ቱርኮች በግዛቱ ከመስፈራቸውም ሆነ የእስልምና እምነት ከመፈጠሩ በፊት በ፮(6)ኛው ክፍለ ዘመን እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች ማዕከል እንደመሆኗና ከአምስቱ ንዑዳን መናብርት አንዱ የሆነው የቁስጥንጥንያው መንበር በዚያ በመገኘቱ በመንበሩ ሥር የነበሩት አርመናውያን ከሌሎች የመንበሩ ሕዝቦች ጋር መልክዓ ምድርና እምነት ተጋርተው ይኖሩ ነበር፡፡ እንደ ቁስጥንጥኒያ መንበርነታቸው በ፬፻፶፩ (451) ዓ.ም. የተካሄደውን የኬልቄዶን ጉባዔ ተቀብለው የነበረ ቢሆንም በ፫ (3) ኛው የዲቪን ጉባኤ የኬልቄዶን ጉባኤን በመቃወም ከቁስጥንጥኒያ መንበር ወጥተው ከእስክንድሪያ መንበር ጋር የእምነት አንድነት ካደረጉ በኋላም የምድሯ አካል መሆናቸው አላበቃም ነበር፡፡

በኦቶማን ግዛት ወቅት፣ የኦቶማን ኢምፓየር በባህል እና ሃይማኖት የተለያዩ ሕዝቦች የተሞሉ ነበር። አርሜንያውያን፣ ምንም እንኳን በእስልምና አገዛዝ ላይ እንደ ሁለተኛ ዜጎች ቢቆጠሩም፣ በንግድና በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ተሳትፈው ነበር። ነገር ግን በ፲፱ (19)ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ ኦቶማን የደረሰበት የጦርነት ሽንፈት፣ የኢኮኖሚ ውድቀትና ሃይማኖታዊ ቀውስ ፊቱን በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ በአናሳ ክርስቲያኖች ላይ በተለይም በአርመናውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እንዲያዞር አስገድዶታል፡፡ ይህ የአርሜንያ የሕዝብ ጭፍጨፋ ታሪክ ነው። ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ እና በጭፍጨፋ ሞተዋል። ከአንድ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ድረስ የሚጠጉ ኦርቶዶክሳውያን በግዳጅ ሰልመዋል፡፡

የኦቶማኑ ገዢ ሱልጣን አብዱል ሃሚድ ፪ (2) ኛ  የአርሜንያውያን የእኩልነት ጥያቄ ስለፈራ ከ፲፰፹፯– ፲፰፹፱ (1887 – 1889)ዓ.ም. የሃሚድ ጭፍጨፋዎችን አስከተለ። ከ፫፻ (300) ሺህ በላይ አርሜንያውያን ተገደሉ። የተረፉ አርመናውያን መንደሮች እንደተቃጠሉ፣ አብያተክርስቲያናት እንደጠፉ እና ወንዞች በደም እንደተሞሉ ተናግረዋል።

በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ “ነፃነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት” በሚል ቃል የሱልጣኑን ዙፋን የገረሰሱት የቱርክ የወጣቶች ዐብዮት የሱልጣኑን ተግባር የተቃወሙ ቢመስሉም እውነተኛ ግባቸው ከዚህ የከፋውን የኢስላማዊ የቱርክ ብሔርተኝነትን ማፋፋም ነበር። በ፲፱፻፮ (1906) ዓ.ም. ኤንቨር፣ ታላትና ጀማል የተመራው የማኅበረሰብ እና እድገት ኮሚቴ (CUP)  ስልጣን ሲይዝ በፓን ቱርኪ ጽንሰ-ዐሳብ ከአናቶሊያ እስከ ማዕከላዊ እስያ ያሉ ቱርኮችን በማንቀሳቀስ “ቱርክ የቱርኮች ብቻ ናት” ሲል ቀደምት የመሬቱን ነዋሪ ክርስቲያኖች ያገለለ ሥርዓት ተከለ፡፡

“በ፲፱፻፯ (1907) ዓ.ም. የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲጀመር፣ የወጣቶቹ ፓርቲ በሳሪካሚሽ ጦርነት ላይ በሩስያ ስለተሸነፉ በዚህ አሳብበው አርሜናውያኑን ለመበቀል ዐቀዱ፡፡ በመሆኑም ሚያዚያ ፲፯ ፲፱፻፯ (ሚያዝያ 17, 1907) ዓ.ም.፥ ሌሊት ታላቁን የአርመናውያን ጭፍጨፋ አስጀመሩት፡፡ ዓለም በስፋት ከሚያቃቸው የናዚና የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በፊት የ፳ (20) ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የዘር ጭፍጨፋ ማስጀመሪያ ፊሽካ ፪፻፶ (250) የሚሆኑ ካህናትና ታዋቂ አርመናውያንን በመግደል ተጀመረ፡፡

ከዚያች ሌሊት አንስቶ ለድፍን አንድ ዓመት በቱርክ መንግስት ስር የሚገኙ አርመናውያን ለሞት፣ ለስደትና መፈናቀል፣ ለግዳጅ የሃይማኖት መለወጥ ተዳረጉ፡፡ እልፎች በረሃብ በስደት ምድር ወደቁ፡፡ በሶሪያ በነበሩ የማጎሪያ ካምፖች የጅምላ ግድያ ተፈጸመባቸው፡፡  

አሁን ላይ የሰማዕታቱ መታሰቢያ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በታነጸበት በዘመኑ የበረሃዋ ሲዖል ዳር ዛር የተፈጸመው ድርጊት እጅግ የሚያሰቅቅ እንደነበር በወቅቱ የዓይን እማኝ የነበሩ የኩርድ ነጋዴዎች ያስታውሳሉ። ጉድጓዶች በአስክሬን የተሞሉ ነበሩ ኤፍራጠስም በሞቱ ሕፃናት ተሞልታ ነበር፡፡

የአንድ ዓመቱ ጭፍጨፋ አሰቃቂ ቢሆንም ግድያው፣ አፈናው፣ ማፈናቀሉና የግዳጅ እምነት ማስለወጡ አስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያና የቱርክ ሪፐብሊክ ምሥረታ ድረስ ለ፰ (60)ዓመታት የቀጠለ ነበር፡፡ ከጭፍጨፋው በፊት በቱርክ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ አርመናውያን ኦርቶዶክሳውያን የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን ከቀየሩ እስከ ሁለት መቶ ሺህ እስከሚደርሱ አርመናውያን በቀር ክርስቲያኖቹ በጣት የሚቆጠሩ ሆነው ነበር፡፡

በዚህ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አርመናውያን በተገደሉበት ጭፍጨፋ ከአርመናውያን ባሻገር የግሪክ ኦርቶዶሳውያንና አሶሪያውያን ሲገደሉ በቱርክ ይኖሩ የነበሩ አዘርባኖችና ኩርዶች አለመነካታቸው ጭፍጨፋው ሃይማኖታዊ መልኩ ትልቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

የአርመን ሃዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዛሬ ዐሥር ዓመት የአርመን ሰማዕታት መታሰቢያ መቶኛ ዓመት በተከበረበት ዕለት ለነዚህ ኦርቶዶክስ አርመናውያን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያን ጨምሮ የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን ፓትሪያርኮችና ልዑካን በተገኙበት “ሰማዕታተ እምነት – አቃቢያነ ሃይማኖት በደም” ስትል የጅምላ ቅድስናን ሰጥታቸዋለች፡፡ ቱርኮችና አዘርባጃኖች “የዘር ጭፍጨፋ አይደለም፤ ጦርነት እንጂ” ብለው በሚከራከሩትና የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓና ሩሲያን ጨምሮ ወደ ፴ (30) ሃገራት የዘር ጭፍጨፋ መሆኑን በተቀበሉት በዚህ እልቂት ምክንያት አርመናውያን በየቦታው እንዲበተኑ ምክንያት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያም፣ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የወቅቱ ንጉሥ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ አርመናውያን በምድሯ አስጠልላ ከመከራ ሰውራቸዋለች፡፡ ዛሬ ላይ “በአርመን ከሚገኘው አርመናዊ በሰው ሃገር ያሉት ይበልጣሉ” አስኪባል በየሀገሩ የተበታተኑት አርመናውያን በየሀገራቸው ያንን አሰቃቂ ጭፍጨፋና የቅዱሳን ሰማዕታቱን አይበገሬነት በማሰብ ይዘክሩታል፡፡

ጠፍተዋል የተባሉት አርመናውያን ሰማዕታት በየአንዳንዱ አርመናዊ ልብና በቤተክርስተያን ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ አጥፍተናቸዋል ያሉት ነገስታት ግን እንደ ፈርዖንና እንደ ናቡከደነጾር እንደ ዲዮቅሊጢያኖስና መክስሚያኖስ በታሪክ ፊት ተነስተው በክፉ ብቻ እየታሰቡ ይኖራሉ፡፡ ሊያጠፏት ያሰቧት ቤተ ክርስቲያን ግን ከትናንት ሳትጎድል ዛሬን ትኖራለች፤ ነገም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ይቻለው ዘንድ ማንም የለምና በክርሰቶስ ደም እንደታተመች በሰማዕታቷ ደም እንደ ተዋበች ትቀጥላለች፡፡

የሰማዕታቱ ድል የማትነሳ የእምነት በረከት ለኛም ትድረሰን፡፡ እግዚአብሔር አካሉን ቤተክርስቲያንና ልጆቿን ይጠብቅ፡፡
ይቆየን!

ነቢዩ ኤርምያስ

በገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ኅዳር ፳፱፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)

“ኤርምያስ” ማለት “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል” ማለት ነው፡፡ ከአራቱ ዓበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አባቱ “ኬልቅያስ” ይባላል፡፡ እናቱ ደግሞ “ማርታ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ያስረዳል፡፡ አገሩ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ካለው ከተማ ከ“ዓናቶት” ነው፤ ትውልዱም ከካህናት ወገን እንደነበረ ተጽፏል።  ኤር.፩፥፩

ነቢዩ ኤርምያስ ለነቢይነት የተለየው ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ነው። ኤር.፩፥፮   ይኸውም እንደ ነቢዩ ሳሙኤል፤ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ማለት ነው፡፡ አንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በእናቴ ማኅፀን ሳለኹ የለየኝ …” እንዳለው ነው። ገላ. ፩፥፲፭ ነቢዩ ኤርምያስ ለእስራኤል ብቻ ሳይኾን ለአሕዛብም ጭምር ነቢይ እንዲኾን በተጠራ ጊዜ ደንግጧል፤ “ሕፃን፣ አንድም ሕፃነ አዕምሮ ነኝና ወዮልኝ” በማለትም አመንትቷል፡፡ በኋላ ግን እግዚአብሔር፡- ‘እስራኤልና አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ትመልሳቸዋለኽና “ሕፃን ነኝ አንድም ሕፃነ አዕምሮ ነኝ አትበል” ‘  ተብሎ በተሰጠው ተስፋ መሠረት በረታ፡፡

በነቢዩ ዘመን በይሁዳ ነግሠው የነበሩት ነገሥታት አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
፩.     ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ብዙ የደከመው፣ በመሞቱም ነቢዩ ያለቀሰለት ፪ኛ ዜና ፴፬÷፴፭/ ኢዮስያስ፤
፪.    በነገሠ በ፫ኛው ወር የግብጽ ንጉሥ አስሮ የወሰደው የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአክስ (ሰሎም) /፪ኛ ዜና ፴፮፡፩-፬፣ ኤር.፳፪÷፲-፲፪/፤
፫.    ፈርዖን ኒካዑ በወንድሙ በኢዮአክስ ምትክ በይሁዳ ያነገሠው፣ አስቀድሞ ለግብጽ በኋላም ለባቢሎን የተገዛው ፪ኛ ዜና ፴፮÷፬-፰/፣ በ፲፩ የንግሥና ዘመኑ እጅግ ክፉ የነበረው ኤር.፳፪÷፲፫-፲፱/፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናቅ ኤርምያስን የተቃወመው መጽሐፉንም ያቃጠለበት ኤር.፴፮ ኢዮአቄም፤
፬.    ከአባቱ ከኢዮአቄም በኋላ በኢየሩሳሌም ለሦስት ወራት የነገሠ፣ በ፭፻፺፯ ከክ.ል.በ. ላይ ከቤተሰቦቹና ከአለቆቹ በጠቅላላ ከዐሥር ሺሕ ሰዎች ጋር ወደ ባቢሎን ተማርኮ የሔደው ፪ኛ ነገ.፳፬÷፰-፲፯፣ ኤር.፳፪÷፳፬-፴ ዮአኪን (ኢኮንያን)፤
፭.    ከኢዮስያስ ልጆች ሦስተኛ የኾነው፣ የወንድሙ ልጅ ዮአኪን በተማረከ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከ፭፻፺፯-፭፻፹፯ ከክ.ል.በ. በይሁዳ ያነገሠው፣ ከነቢዩ ኤርምያስ ምክር ላይጠቀምበት ምክርን ይጠይቅ የነበረው፣ በክፋቱ የጸና፣ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ባቢሎን ተወስዶ የተመለሰው ኤር.፶፩፥፶፱፣ በኋላ ላይ በግብጽ ተማምኖ ባቢሎን ንጉሥ ላይ ያመፀው፣ ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ ተይዞ የተማረከና ዕውር ኾኖ በግዞት ቤት ሳለ የሞተው ሴዴቅያስ ናቸው፡፡

ነቢዩ ኤርምያስ የነበረበት ነባራዊ ኹኔታ
ነቢዩ ኤርምያስ አገልግሎቱን የጀመረው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ (ከ፮፻፵-፮፻፱ ከክ.ል.በ.) በነገሠ በ፲፫ኛው ዓመት ላይ ነበር፡፡ ይኸውም በ፮፻፳፮ ከክ.ል.በ. መኾኑ ነው፡፡ ይኽ ዓመት ደግሞ እጅግ በጣም ወሳኝ የኾነ ወቅት ነበር፡፡ በአንድ በኵል ንጉሥ ኢዮስያስ ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ከጀመረ አንድ ዓመት ኾኖታል፡፡ በሌላ በኵል ደግሞ ባቢሎናውያን ከእኤሦር አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አንድ ዓመት ይቀራቸው ነበር፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ኤርምያስ አገልግሎቱን የጀመረው በቤተ ክህነቱም በፖለቲካውም ወሳኝ ኩነቶች የሚፈጸሙበት ሰዓት ላይ ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚኹ ጋር በተያያዘ የሰሜኑ ክፍል ሕዝብ ወደ ሶርያ ተማርኮ ከፈለሰ ገና ፻ ዓመቱ ነው (የተማረኩት በ፯፻፳፪ ከክ.ል.በ. መኾኑ ከዚኽ በፊት መነጋገራችን ያስታውሱ)፡፡

የሕዝቡን ግብረ ገብነት ስንመለከት ደግሞ፥ በቤተ መቅደስ ሔደው መሥዋዕት ስላቀረቡ ብቻ እግዚአብሔርን ከልባቸው ያመለኩት ይመስላቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ከመሥዋዕት ይልቅ ልብን ነው የሚፈልገው፡፡ ይኸውም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “እግዚአብሔር ከወርቃማ ምሥዋዕ ይልቅ ወርቃማ ነፍሳትን ይሻል” እንዳለው ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምስያስ ይኽን የግብዝነት ምልልሳቸውን እንዲያስተካክሉ ነገራቸው፡፡ መፃተኛውን፣ ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱን እየበደሉ እልፍ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረባቸው ቤተ መቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረግ እንደኾነ አሳሰባቸው። ኤር.፯፥፰-፲

ካልተመለሱ ግን እነርሱ በባዕድ ንጉሥ እንደሚማረኩ፥ ቤተ መቅደሱም እንደሚፈርስ በቤተ መቅደሱ በር ኾኖ በመጮኽ በግልጽ ነገራቸው። ኤር.፯፡፬ ሕዝቡና ካህናቱ ግን አላመኑትም፡፡ ይባስ ብለውም መቱት ኤር.፳፥፪፣ በእግር ግንድ ያዙት፤ በጭቃ ጕድጓድ ጣሉት፣ ኹለት ጊዜ አሰሩት። ኤር.፴፯፥፲፫-፳፩፤ ” አብዷል” አሉት። ኤር.፳፱፥፳፮

ተወዳጆች ሆይ! እኛስ? እኛስ መፃተኛውን አልበደልንምን? ድኻ አደጉን አላንከራተትንምን? መበለቲቱን አላስከፋናንትምን? ይኽን እንድናስተካክልስ እግዚአብሔር ስንት ጊዜ ተናገረን? ታድያ ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን እስኪፈርስ ድረስ እየጠበቅን ነው? ወይስ እንደ ነቢዩ ቃል ተመልሰናል? እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን ከኀጢአታችን ጋር ተስማምቶ ሳይኾን የንስሐ ጊዜ ሲሰጠን ነው፡፡

የነቢዩ ኤርምያስ ልዩ ባሕርያት
፩.     በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ደረሰበት መከራ እንደ ኤርምያስ ያለቀሰ ሰው የለም፡፡ በስነ መለኮት ምሁራን ዘንድ፡- “አልቃሻው ነቢይ” እየተባለ መጠራቱም ይኽን ባሕርዩን የሚያመለክት ነው፡፡ ሰቆቃወ ኤርምያስ ማንበብም ይኽን ዐሳብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡

፪.    የጸሎት ነቢይ ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከሌሎች ነቢያት ለየት የሚያደርገው ሌላኛው ነጥብ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገረው በጸሎት መኾኑ ነው፡፡ ትንቢቱን፣ ራእዩን የሚገለጽለት ሲጸልይ ነው፡፡ ሲከፋው የሚያወያየው ወዳጅ ሚስት የለውም፤ አላገባምና፡፡ ልጅም የለውም፡፡ ስለዚኽ ሲከፋው፣ የወንድሞቹን ስቃይ ሲያይ፣ ቤተ መቅዱስን መፍረስ ሲመለከት ያለቅሳል፡፡ እግዚአብሔርም ያናግረዋል፡፡

፫.    ነቢዩ ምንም እንኳን ኢየሩሳሌምንና ሕዝቡን ቢወድም ኤር.፰÷፲፰-፱፡፩ ፣ ፲፫÷፲፯ መማረካቸው እንደማይቀር ሊነግራቸው ተገድዷል፡፡ ከዚኽም በላይ፡- “ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ስጡ፤ ተገዙም፤ ምርኮኞችም እስከ ፸ ዓመት ድረስ አይመለሱም” ብሎ የተገለጠለትን የእግዚአብሔርን ቃል ስለተናገረ ተጠላ፡፡ ብዙዎችም ሊገድሉት ዐሰቡ ኤር.፲፩፥፳፩፣ ፳፮፥፲፩፣ ፴፮፥፲፮፣ ፴፰፥፮-፲ ተመታ ኤር.፳፥፪፣ በእግር ግንድ ተያዘ ፣ በጭቃ ጕድጓድ ተጣለ፣ ኹለት ጊዜ ታሰረ ኤር.፴፯፥፲፫-፳፩፣ አብዷል ተባለ። ኤር.፳፱፡፳፮ ስለዚኽ ነቢዩ በራሱ መጽሐፍ ላይ ስለ ራሱና ስለደረሰበት መከራ ብዙ ስለ ጻፈ ከሌሎች ነቢያት ይልቅ ጠባዩና ኹኔታው ተገልጿል፡፡

፬.    ከዚኹ ኹሉ ጋር ለሕዝቡ ምልክት እንዲኾን ሚስት እንዳያገባ፣ ወደ ግብዣ ወይም ወደ ልቅሶ እንዳይሔድ ተከልክሏል። ኤር.፲፮

፭.    ወእለ ዘተርፈ…

ትንቢተ ኤርምያስ

ነቢዩ ኤርምያስ ትንቢቱን የተናገረው ከላይ በገለጽናቸው አምስት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ነው፡፡ እግዚአብሔር ኤርምያስን በጠራው ጊዜ፡- “የይሁዳ ሕዝብ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን ስላመለኩ ከሰሜን ጠላት አስነሣባቸዋለኹ” ብሎ ነገረው። ኤር.፩፥፲፫-፲፮  ኤርምያስም ሕይወታቸው ወደ ኾነው እግዚአብሔር እንዲመለሱ ያለማቋረጥ ለ፳፫ ዓመታት ይጠራቸው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙትም። ኤር.፳፭፥፫-፯ በዚያም፥ በተጠራ በ፳፫ኛው ዓመት ከሰሜን የሚመጣባቸው ንጉሥ ናቡከደነፆር በባቢሎን ነገሠ። ኤር.፳፭፥፩  እርሱም በይሁዳ ላይ ብቻ ሳይኾን በብዙ ሕዝቦች ላይ እንደሚመጣ፣ እስከ ፸ ዓመትም ድረስ እነዚኽ ሕዝቦች ለባቢሎን እንደሚገዙ ተነበየ። ኤር.፳፭፥፰-፲፩

ከዚኽም በኋላ ባቢሎን እንደሚወድቅ ገለጠ።  ኤር.፳፭፥፲፪-፲፬ ይኽን ከባድ የፍርድ  መልእክት ለመናገር የበቃው በአምላኩ ኃይል እንጂ በራሱ ችሎታ አልነበረም።  ኤር.፩፥፮-፲ በእነዚኽም ፳፫ ዓመታት የተናገረው ትንቢት ኹሉ ተጽፎ ሲነበብለት ንጉሥ ኢዮአቄም ጽሑፉን ቆራርጦ አቃጠለው፤ ኤርምያስ ግን እንደገና በባሮክ እጅ አስጻፈው። ኤር.፴፮

ተወዳጆች ሆይ! እኛስ ስንት ጊዜ ተመለሱ ተብለን ይኾን? ስንት ጊዜስ የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ብለን ተኝተን ይኾን? እስኪ ኹላችንም የየራሳችንን እንመልከት!!!

ሴዴቅያስ ከነገሠ ጊዜ ጀምሮ ኤርምያስ፥ ሴዴቅያስን፡- “ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ኢየሩሳሌምም አትጠፋም” ይለው ነበር። ኤር.፳፯፥፲፪-፲፯ ሴዴቅያስ ግን በግብጽ ስለተማመነ  ኤር.፴፯፡፫-፲ ፣ ደግሞም ስላመካኘ ኤር.፴፰፥፲፱ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አልሰጠም፡፡ ከዚኽም የተነሣ በእርሱና በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ፍርድ የባሰ ኾነ። ኤር.፴፱፥፩-፲ ፣ ፪ኛ ዜና ፴፮፥፲፩-፳፩

ነቢዩ ኤርምያስ የፍርድን መልእክት ብቻ የተናገረ አይደለም፤ ጨምሮም የተስፋ ቃልን ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ እንደሚመልስ፣ ኢየሩሳሌም ታድሳ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደምትባል ኤር.፴፫፥፲፮ ፣ እግዚአብሔርም ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳንን እንደሚያደርግ፣ ከዳዊት ዘር የኾነው ንጉሥ ነግሦ፣ ስሙ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደሚባል ተንብዮአል። ኤር.፳፫፡፩-፮፣ ፴-፴፫

የትንቢተ ኤርምስያስ ዋና መልእክት፡- እግዚአብሔር ታላቅና ቅዱስ ስለኾነ ሕዝቡ ከክፋት ተመልሰው በፍጹም ልብ እንጂ በሐሰት እንዳያመልኩት ማስገንዘብ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ወምስለ ኵሉ ኢተመይጠት ኀቤየ ኅሥርተ ይሁዳ እኅታ በኵሉ ልባ” / “አታላዪቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልቧ ወደ እኔ አልተመለሰችም” ኤር.፫፥፲ ፤ ካህናቱና ነቢያቱ እግዚአብሔርን ስለመፍራት፣ በቅንነትም ስለመኖር ሳይኾን ሕዝቡን፡- “የእግዚአብሔር ቤት እዚኽ ነው፤ እናንተም ሕዝቡ ናችሁ፤ አይዞአችሁ፤ ምንም አይደርስባችሁም” እያሉ ማታለላቸው። ኤር.፯፥፫-፲፩፣ ፲፬፥፲፫-፲፰፣ ፳፫፥፱-፵ ለዚኹ ምስክር ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚያየው ደጋግመን እንደተናገርነው ልብን ነው፤ በፍጹም ልባቸው እግዚአብሔርን የሚፈልጉትም ያገኙታል፡፡

መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
፩.     የነቢዩ መጠራት (፩)፤
፪.    ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ የሚል ጥሪና የማስጠንቀቂያ መልእክቶች (፪-፳)፤
፫.    ዮአኪን ከተማረከ በኋላ ለነገሥታት፣ ለሕዝቡና ለምርኮኞች የተሰጡ መልእክቶች (፳፩-፳፱፣ ፴፭-፴፮፣ ፵፭)፤
፬.    የኢየሩሳሌም ልማትና የአዲስ ኪዳን ተስፋ (፴-፴፫)፤
፭.    የኢየሩሳሌም መከበብና ውድቀት (፴፬፣ ፴፯-፴፱)፤
፮.    ኤርምያስ በይሁዳ ከቀሩት አይሁድ ጋር መኖሩ (፵-፵፪)፤
፯.    የኤርምያስ በግብጽ መኖር (፵፫-፵፬)፤
፰.    በአሕዛብ ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (፵፮-፶፩)
፱.    ተጨማሪ የታሪክ ክፍል ፣ የኢየሩሳሌም መውደቅ (፶፪)፡፡

ሰቆቃወ ኤርምያስ

ሰቆቃ ማለት ሙሾ፣ ለቅሶ ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ በዚኽ ስያሜ እንዲጠራ የኾነበት ዋና ምክንያትም ኢየሩሳሌም በጠላት እጅ ወድቃ፣ ቤተ መቅደሷና አጥሮቿ በጠላት ፈራርሳ፣ እናቶች ልጆቻቸው በረሃብ አልቀው በማየት ዝም እስከማለት የደረሱበት ረሃብና ጥም ጸንቶባቸው፣ ካህናትና ነቢያት መገደላቸውን አይቶ የጻፈው ስለኾነ ነው፡፡ መጽሐፉ አምስት ምዕራፎችን የያዘ ሲኾን በውስጡ ከለቅሶው በተጨማሪ የእግዚአብሔር ቊጣና ቅጣት እንዲኹም ስለ ተስፋ ድኅነት በስፋት ተገልጾበታል፡፡

ተረፈ ኤርምያስ

የሰቆቃወ ኤርምያስ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ መጽሐፉ ስለ ጣዖት አምልኮ ከንቱነት በስፋት ስለሚያትት “አርአያ መጽሐፍ ዘኤርምያስ – ኤርምያስ ፊት የጻፈውን መጽሐፍ የሚመስል መጽሐፍ፤ አንድም የጣዖትን መልክ ለይቶ የሚያሳይ መጽሐፍ” ተብሎ ይጠራል፡፡

መጽሐፈ ባሮክ

የዚኽ መጽሐፍ ጸሐፊ የነቢዩ ኤርምያስ ታማኝ ወዳጅ፣ ደቀ መዝሙርና ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ነው። ኤር.፴፮፥፩-፴፪  ምንም እንኳን ጸሐፊው ባሮክ ቢኾንም በይዘቱና እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለት በመኾኑ ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በመደመር አንድ ኾኖ ይቈጠራል፡፡ መጽሐፉ፥ ባሮክ በተማረከበት አገር በባቢሎን ሳለ ለኢየሩሳሌም ኗሪዎች ጽፎ የላከላቸው ነው፡፡ በውስጡም በምርኮ ስላሉት የአይሁድ ኑሮ፣ ስለ ኃጢአት ኑዛዜ ንስሐና ጸሎት እንዲኹም ለአይሁድ የቀረቡ ልዩ ልዩ ምክሮችን ይዟል፡፡

ተረፈ ባሮክ

ይኽ መጽሐፍ የመጽሐፈ ባሮክ ቀጣይ ጽሑፍ ሲኾን እግዚአብሔር ለባሮክ፣ ለአቤሜሌክና ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ሲኾን እስራኤላውያንን በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት ዘመን እንዴት ጠብቆ እንዳሳለፋቸውና በኤርምያስ መሪነት ምርኮኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደተመለሱ የሚተርክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለትና በባሮክ እጅ የተጻፈ ነው፡፡ ለዚኽም ምስክራችን፥ ወንጌላዊው ማቴዎስ፡- “በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት የሚል ተፈጸመ” ብሎ የተናገረው ቃል በዚኹ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ መኾኑ ነው። ማቴ.፳፯፥፱-፲   ቃሉም ቃል በቃል እንዲኽ ይላል፡- ‘ኤርምያስም ጳስኮርን እንዲኽ አለው፡- “እናንተስ በዘመናችሁ ኹሉ ከአባቶቻችሁና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡ ልጆቻችሁ ጋር ጽድቅን ትቃረኗታላችሁ፡፡ እነርሱስ ከአባቶቻችሁ ይልቅ እጅግ የተናቀች ኃጢአትን ሠሩ፡፡ እነርሱም ዋጋ የማይገኝለትን ይሸጡታል፤ ሕማማትን የሚያስወግደውን እንዲታመም ያደርጉታል፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርየውንም ይፈርዱበታል፡፡ የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክብሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ይቀበላሉ፤ ያንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ አድርገው ይሰጡታል፡፡ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ እንዲኹ እናገራለኹ፡፡ ስለዚኽ ንጹሕ ደምን ፈርደው አፍስሰዋልና ፍርድና ጥፋት በእነርሱ ላይ፥ ከእነርሱም በኋላ በልጆቻቸው ላይ ይወርድባቸዋል” ‘  ተረ.ባሮ.፩፥፩-፭

የነቢዩ የመጨረሻ ዕረፍት

  በራሱ የትንቢት መጽሐፍ እንደሚነግረን፥ ነቢዩ ኤርምያስ ኢየሩሳሌም እስከተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር፥ ማለትም እስከ ፭፻፹፯ ከ ክ.ል.በ. በዚኹ አገልግሎቱ ቆይቷል። ኤር.፩፥፫  ግንቦት ፭ ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንደሚነግረን ነቢዩ ኤርምያስ ያረፈው አይሁድ በድንጋይ ወግረዉት እንደሞተ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በድንጋይ ተወግረው ሞቱ” ብሎ በዕብራውያን ፲፩፥፴፯ ከጠቀሳቸው ቅዱሳን አንዱ ነቢዩ ኤርምያስ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡

ዋቢ ድርሳናት፡-
©     የትንቢተ ኤርምያስ አንድምታ መቅድም፤
©     የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤
©     ስንክሳር
©     መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ፣ በመምህር ቸርነት አበበ የተዘጋጀ፡፡

የልደታ ለማርያም ቅዱስ ትውፊት

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓላት ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ትችቶችን መሰማት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። የዓለማቀፋዊቷ ቤተክርስቲያንን ትውፊት ያጠና ግን በዓላቱ በዘመን የረዘመ፣ በቦታም የሰፋ፣ ነገር ግን እንደ ቦታው ታሪካዊ ሂደት ለውጥን የሚያስተናግድ ተመሳሳይነትን ማግኘቱ የማይቀር ነው። የዚህ ምንጩም ዜና ቅዱሳን ነው።;የቅዱሳንን ዜና ሕይወት መጻፍ በብሉይ ኪዳን የተጀመረ ሲሆን ሊቀ ነብያት ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፉ የቀደሙ ርእሳነ አበውን የነአዳም፣ ኖህ፣ ሄኖክ፣ አብርሃምን ታሪክ ሰንዶልናል።

የቅዱሳን ፣ መሳፍንትና ነገስታትም ዜና ሕይወት በመጽሐፈ መሳፍንት፣ ነገሥትና ዜና መዋዕል በሌሎቹም ክፍላት የተፃፉ ናቸው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉም ሉቃስ የሐዋርያትን አገልግሎት ከትቧል። እኒህ ሁሉ ዜና ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ሳይገኙ በመዘግየት ያልተካተቱ የሀዋርያት ጽሑፎችና የድህረ ሐዋርያት ዜና ቅዱሳን በተናጥል (ገድላትና ተአምራት) እንዲሁም በስብስብ (ስንክሳር) መልኩ እየተዘገበ ከዚህ ዘመን ተደርሷል። የአንዳንድ ቅዱሳን ዜና በዓለም ሁሉ የሚታወቅ ሲሆን የሌሎች ዜና ገድል ግን በተወሰነ ቦታ ብቻ የሚታወቅ ሆኖ እናገኘዋለን።

እንደ ዓለም ገዝፎ በመታወቅ ደረጃ የቅድስት ድንግል ማርያምን መታወቅና መከበርን የሚያህል የለም። የድንግል ማርያም ነገረ ልደት በሁሉም ጥንታውያን አብያተክርስቲያናት የሚታወቅና የሚከበር በዓል ነው። በነገረ ድኅነታዊ ዋጋቸው በዓለም ሁሉ ከሚከበሩት የሁለት ፍጡራን በዓላትም ዋነኛው የእመቤታችን ልደት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ተብሎ በጌታችን የተነገረለት የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት ነው።

የእመቤታችን ነገረ ልደት የተመዘገበበት ጥንታዊው መጽሐፍ የጌታ ወንድም ተብሎ የተጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ያዘጋጀው መጽሐፈ ልደት (The book of nativity) ወይም መጽሐፈ ያዕቆብ (Book of James) በግሪኩ ደግሞ ፕሮቶቫንጌልዮን ነው።

መጽሐፉ በኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተክርስቲያናት በቀኖናቸው ተቀባይነት የሰጡት መጽሐፍ ሲሆን ፲፮ ምዕራፎች ያሉት መጽሐፍ ነው። እንደ ስያሜው አምላክን ስለወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያወራ ሲሆን እመቤታችን ዘመዱ እንደመሆኗ ከእርሷና ከቅርብ ዘመዶቿ እየሰማ እንደጻፈው ይታመናል።

በ፪ኛው ክ/ዘ እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት ይህ መጽሐፍ እንደ ኦሪገን ያሉ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት በትምህርታቸው ላይ የጠቀሱት ሲሆን በ፲፭፻፶፪ ወደ ላቲን ተተርጉሟል።
መጽሐፉ ሲጀምር “የኢየሱስ ክርስቶስና የዘለዓለማዊት ድንግል ማርያም የልደት ታሪክ፤ የክርስቶስ ዘመድና ወንድም በሚሆን ዋና ሐዋርያ እንዲሁም የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ሊቀጳጳስ በሆነ ታናሹ ያዕቆብ” ብሎ ይዘቱንና ጸሐፊውን ይናገራል።

የመጽሐፉ ታሪክ በሁሉም አቢያተክርስቲያናት የሚታመን ሲሆን ታሪኩ ከመጽሐፉ መታተም ከ፮፻ ዓመት በፊት በተጻፉ ሌሎች ጥራዞች ላይ ሳይቀር መጠቀሱ በዕድሜ ቅድምናና መነሻ ታሪክ እንዳለው ማሳያ ይሆናል።

የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ስፍራን በተመለከተ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን ናዝሬትና የኢየሩሳሌም መግቢያ ከተሞች “በኔ ነው! በኔ ነው የተወለደችው!” እያሉ ሚፎካሩ ሲሆን ኦርቶዶክሳዊት የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን “ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።” መኃልየ. ፬፥፰ የሚለውን የሰለሞንን ቃል መነሻ አድርጋ መወለዷ ከሊባኖስ መሆኑን ታስተምራለች። በሊባኖስም እጅግ ጥንታዊ የሆነ በስሟ የሚጠራ ቤተመቅደስም ይገኛል።

በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ ክርስቲያኖች (ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንጋሊካን፣ ሉተራውያን) የእመቤታችን ልደት በተለያዩ ቀናት የሚያከብሩ ሲሆን የምዕራብ አብያተክርስቲያናት ጷግሜ ፫ (September 8), የምሥራቅ አብያተክርስቲያናት (ኦርየንታልና ምስራቅ ኦርቶዶክስ መስከረም ፲ (September 21) እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በግንቦት ፩ ያከብሯታል። የእመቤታችንን ፴፫ በዓላቷን በሚዘረዝረው የተአምረ ማርያም መቅድም ላይም መስከረም ፲ የሚያከብሩ እንዳሉ ይጠቅስና “እኛ ግን..” ብሎ ‘…በተረዳ ነገር አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ልደቷ “ግንቦት ፩ ነው” እንላለን’ ሲል ይመልሳል።

የእመቤታችን የልደት በዓል እስከ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መግባት ድረስ በብሔራዊ በዓልነት ሲከበር የነበረ ሲሆን እንደ ፊሊፒንስ ባሉ ሀገራት ሥራ የሚያዘጋ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል።

ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሣ!

የመስቀሉ ተከታዮች

የዛሬ ዐሥር ዓመት ነበር ናኤል ጎይቶም ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች ኤርትራውያን ጓደኞቹ ጋር የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ለመሻገር በሱዳን በኩል  ወደ ሊቢያ ድንበር የገባው፡፡

በወቅቱ የዐሥራ ስድስት ዓመት ታዳጊ የነበረው ናኤልና ባልንጀሮቹ  ብዙዎቹ የእነርሱ ታላላቆች እንዳደረጉት ሁሉ የእነርሱም ሕልማቸው  ለመለወጥና ለዘመዶቻቸው ለመትረፍ ቢሆንም በቀላሉ ነበር በሊቢያ ምድር በሚንቀሳቀሰው በአይ.ኤስ.አይ. ኤስ. እጅ የወደቁት፡፡

ናኤል ስለዚያች ቀን ሲናገር  “ቀኑ የካቲት ሃያ አራት ነበር፡፡  ከኛ ጋር ሶማሊያውያንና ወደ ሰባዘጠኝ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ቁጥራቸው ከ፳ እስከ ፴ የሚጠጋ የአይ.ኤስ. ወታደሮች በደቡባዊው የሊቢያ በረሃ ይዘው ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ጠየቁን፡፡ ከኛ መሃል ሙስሊም የሆኑትን ለመለየት ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹ መስቀልና ቅድሳት ስዕላትን ይዘን ስለነበር ክርስትናችንን መደበቅ አልተቻለንም ነበር፡፡” ይላል።

ሰላም ውድ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መሰናዶ ተከታታዮች በወርኃ ታኅሣሥ በሊቢያ ስለተሰዉ ግብጻውያን ሰማዕታት ስናነሳ በወርኃ ሚያዚያ ኢትዮጵውያንና ኤርትራውያንን ለማዘከር ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ ምንም እንኳን በሰሙነ ሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤ ዝክሮች ምክንያት የሰማዕታቱ ዜና ምስክርነት የተገለጠበት ሚያዝያ ፲፩ ብናልፈውም ስለሰማዕታቱ እንዘክር ዘንድ ፍቅር ያስገድደናልና ዝክራቸውን በዛሬው ዕለት ማንሳት ጀምረናል፡፡

ከላይ ምስክርነቱን ያነሳነው የያኔው ታዳጊ ናኤል ጎይቶም በ፴ዎቹ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ላይ ስለተፈጸመው ሰማዕትነት የዓይን ምስክር ከሆኑ ጥቂት ግለሰቦች አንዱ ነው፡፡ ይህ ታዳጊ አንገታቸው የታረዱትንም ሆነ በመሳሪያ አፈ-ሙዝ ምስክርነታቸውን የፈጸሙትን ሰማዕታት ከተያዙበት የየካቲት ወር መጨረሻ እስከ ጊዜ እረፍታቸው ድረስ የሆነውን ተመልክቷል፡፡ ያየውንና የሰማውንም በዩናይትድ ኪንግደም ለሚታተመው የኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይም በ፳፻፲፩ ዓ.ም. አካፍሏል፡፡

ናኤል እንደሚለው በቦታው የነበሩ ሶማሊያውያንን ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራውያንን ሲለቋቸው ክርስቲያኖቹ ግን ወደ አይ.ኤስ. ካምፕ ተወሰዱ፤ ለቀናት ታስረውም ጭምር ነበር፡፡ ወደ ካምፕ የተወሰዱ ክርስቲያኖች ሦስት ምርጫዎች ነበር የተሰጣቸው እምነትን መቀየር ወይም ጀዛ መክፈል ወይም መሞት፡፡ ናኤል ጎይቶምና ሌሎች ጓደኞቻቸው ሃይማኖታቸውን ለመቀየር ሲስማሙ ሰማዕታቱ ግን በሃይማኖታቸው መጽናትን መረጡ፡፡

ስለሞታቸው ቀን ናኤል ጎይቶም ሲናገር ሁለቱም በተለያየ ቦታና ቀን እንደተገደሉ ያነሳና ‘ከዕለታት አንድ ቀን ጥቁር ቱታዎች አመጡና ሃይማኖታችንን አንቀይርም ካሉት ውስጥ ለተወሰኑት እንዲለብሱ ሰጧቸው። ከዛም ይዘዋቸው ሲወጡ ዐስር የምንሆነውን “እኛን ተከተሉን!” አሉን’ ። “ከጀርባቸው ሲተኮስባቸው በዓይናችን ተመለከትን” ብሏል፡፡ “ዐሥራ ዐራት የሚሆኑትንም ብርቱካናማ ቱታ አስለብሰው እንዲከተሏቸው አዘዟቸው። እነሱን ደሞ በፊታችን አረዷቸው” ይለናል፡፡ ይህ የናኤል ምስክርነት ከሌሎች ፫ በተመሳሳይ መንገድ ተርፈው በስደተኛ ማቆያ ከነበሩ ኤርትራውያን ምስክርነት ጋር ይመሳሰላል፡፡

እስቲ አሁን ደግሞ ምስክረነቱን ገታ አድርገን ሚያዚያ ፲፩/፳፻፯ ዓ.ም.  የተለቀቀውንና ፴ ደቂቃዎችን የሚፈጀውን ቪዲዮ በዓይነ ልቡናችን እንመልከት፡፡  ግልጽ ማስረጃ እስከመጣላቸው ድረስ /”Until There Came to Them Clear Evidence” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ሲሆን በኢራቅና በሶሪያ ያለውን የረጅም ጊዜ የሙስሊምና ክርስቲያን ግንኙነት ያሳይና አምላካችን ኢየሱስን ከቁርአን አንጻር በመመዘን የክርስቲያን ክፍል እንዴት እንደመጣ ያነሳል፡፡

በወቅቱ የቡድኑ መሪ የነበረው አቡበከር አልባግዳዲ የአል ኑሪ መስጂድ ሚንበር ላይ በመውጣት ክርስቲያኖአች “ከሃዲ” መሆናቸውን በማወጅ ወይ ጃዛ መክፈል ወይ መገደል እንዳለባቸው ያውጃል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በሶሪያ በተለይም ቡድኑ በወቅቱ በተቆጣጠራቸው የአሌፖና የራቃ ከተማ የሚኖሩ ጃዛያ የሚከፍሉ ክርስቲያኖች ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸው ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ተራኪውም ይህ የሆነው ጀዛያ ስለከፈሉና ቡድኑ መሐሪ ስለሆነ እንደሆነ ያነሳል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን ምንም እንኳን ደህና ነን ቢሉም ፍርሐታቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አይ.ኤስ. ክርስቲያኖችን ሲያሰቃይ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትን፣  ሃውልቶችንና የክርስቲያኖችን መካነ መቃብር ሲያፈራርስ ያሳያል፡፡

ለደቂቃዎች እንዲህ ካሳየ በኋላ በጥቁርና ብርቱካናማ ልብስ የተያዙ የሁለት የክርስቲያን ቡድኖችን ያሳያል፡፡ የመጀመሪያው በምሥራቅ ሊቢያ ባርቃ ግዛት የተያዙ በደርዘን የሚቆጠሩ በብርቱካናማ ቱታ የሚታዩ ሲሆን ሁለተኞቹ በደቡብ ሊቢያዋ ፋዛን ግዛት የተያዙ ፲፮ በጥቁር ቱታ ያሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡  ምርኮዎቻቸውን እየታዩ ከሥር “የጠላት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመስቀሉ ተከታዮች” የሚል ጽሑፍ ይታያል፡፡

አንዱ ጥቁር የለበሰ ወታደር መሳሪያውን ወደ ካሜራው በመደቀን “ምስጋና ለአዓማቱ ጌታ ለአላህ ይሁን እንዲሁም ሰላምና በረከት በነብዩ መሐመድ ላይ ይሁን! ለመስቀሉ ሕዝቦች፣ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ረገጡት አሸዋ ተመልሰን እንነግራችኋለን፤ በእናንተ ሃይማኖት እጅ የፈሰሰው የሙስሊም ደም ርካሽ አይደለም፣ እንደውም ደማቸው ንጹህ ደም ነው፤ ምክንያቱም በቀላቸውን የሚወርስ ሕዝብ ከኋላቸው አላቸው፡፡ በእጃችን እንዲያዋርዳችሁ ለአላህ ቃል ገብተናል፡፡ እስልምናን እስክትቀበሉ በህልማችሁ እንኳን ደኅንነት አይኖራችሁም! “

ተናጋሪው ይህ ጦርነት በእምነትና በክህደት መሐል የተደረገ መሆኑን ያነሳና ጣዖት አምልኮና ለአላህ መገዛት እስካልተፈጸመ ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ያነሳል፡፡ በመቀጠል በምስሉ ብርቱካናማ የለበሱት ክርስቲያኖች ሲታረዱ ጥቁር የለበሱትም በመደዳ በመሳሪያ ሲገደሉ ያሳያል፡፡ ቪዲዮው በአል ናሽያን ንግግር ይጠናቀቃል፡፡ አል ናሽያን በንግግሩ ክርስቲያኖች እስልምናን ወይም ጀዛያን ካልከፈሉ ከአይ.ኤስ. ሰይፍ እንደማያመልጡ ይናገራል፡፡

ከምስሉ መለቀቅ በኋላ መላው ዓለም በድንጋጤ ተዋጠ። አትዮጵያና ኤርትራ በሀዘን ተሞሉ። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከሰማዕታት መሀል በማየቷ ስትኮራ ስለ ደረሰባቸው መሪር ስቃይ አዘነች፡፡ በየሚዲያው የውግዘትና የሀዘን መግለጫ ተሰጠ፡፡  ስለወቅቱ የሚዲያ ሽፋን ጥናቱን ያካሄደው ስለሺ ሰማኸኝ በወቅቱ “በየሚዲያው የነበሩ ዘገባዎች ሃይማኖታዊ ምስክርነቱን ያቃለሉና በይበልጥ ፖለቲካዊ መልክ የነበራቸው ናቸው።” ይለናል በጥናቱ፡፡ በእርግጥም የጥቃቱ ግብረ መልስ ፖለቲካዊ በመሆኑ ሽብርተኝነትን በሚያወግዙ ሰልፎች እና የስደተኝነትን አስከፊነት በሚያሳዩ መርሐግብራት የተሞላ ነበር፡፡

በ፳፻፯ የተሰበሰበው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እነዚህን ምስክሮች ሰማዕትነት ያወጀ ቢሆንም ለዚህ ጥንቅር በተመለከትናቸው ዘገባዎችና መረጃዎች መሠረት የሰማዕታቱ ስም በአግባቡ አለመታወቁንና የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን ለመመልከት ተችሏል፡፡ በሊቢያ የነበረው የአይ.ኤስ. ይዞታ ከተነጠቀ በኋላ በታኅሣሥ ፲፭/፳፻፲፩ ዓ.ም. የሊቢያ የወንጀል ምርመራ መምሪያ የሰማዕታቱ አጽም መገኘቱን ያረጋገጠ ሲሆን በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የሰማዕቱ አጽም ማሳረፊያ የተዘጋጀና ክቡር ስጋቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚመጣ በመንግስትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን በኩል የተነገረ ቢሆንም ዜና ገድላቸው በወጉ ሳይያዝና አጽማቸው ወደ ሀገር ሳይገባ እነሆ ዐሥር ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ሰማዕታቱ በእምነታቸው ጸንተው ዓለምን ድል ያደረጉ ቢሆንም በፍርሐት ለጊዜው ክደው የነበሩት ወንድሞቻቸው ስለተቀረው ጊዜያቸው በናኤል አንደበት እንዲህ ይናገራል፡፡ “ስለጉዳዩ ማስተሳሰብ የጀመርሁት አሁን ነው፡፡ ከቀናት በፊት ነገሮች ሁሉ በሕይወት መትረፍ ነበሩ። አሁን ግን ከባባድ ቅዠት አለብኝ፡፡ ሰዎች አንድ በአንድ  ሲታረዱና ሲገደሉ አያለሁ።” ሲል ይደመጣል።

በዚያው ዓመት ሚያዚያ ፲፮ በሰጠው ቃል በየወንድሞቻችንን ዜና ሰማዕትነት የዘከርንበት ዓምድ በዚህ ፈጸምን። ድል የማትነሳ የዕምነት ጽናታቸው ከእኛ ጋር ትሁን፡፡ ዝክራቸውና ክብርት ሥጋቸው እንደ ግብጻውያን ወንድሞቻቸው ሲከብር ለማየት አምላከ ቅዱሳን ይርዳን። አሜን!

ፍርሃትን የሚጥል ፍፁም ፍቅር

በሌሊት ማለፍና በፀሐይ መውጣት መካከል ገና ጨለማ ሳለ ሁለቱ ማርያሞች፡ ማርያም መግደላዊትና የያዕቆብ እናት ማርያም ከሰሎሜ ጋር ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ ሄዱ። በዚህ ግርማ ሌሊቱ ባልተለየው ድምፀ አራዊቱ በሚሰማበት ሌሊት የአይሁዳውያን ዛቻና የኃያላኑን የሮማ ወታደሮች ቁጣ ተጋፍጠው የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ሽቶ ይቀቡ ዘንድ ወደ መቃብሩ ገሰገሱ። እነኚህ ሴቶች የክርስቶስን ሞት ሰምተው መቃብሩን ሊያዩ ከሩቅ የመጡ እንግዶች አልነበሩም፤ ይልቁንም በዕለተ ዐርብ እየተላጋ ሲወሰድ፣ በየመንገዱ ሲጎተትና መስቀል ተሸክሞ ሲሄድ እያለቀሱ በደም የተዋበ የመስቀሉን መንገድ በእንባ ያጠቡ ሴቶች ናቸው።

ሴቶቹ ሐዋርያቱ ሸሽተው በሄዱበት፣ “አሁን አድን” ያሉት የኢየሩሳሌም ሰዎች “አሁን አጥፋው” ብለው ጲላጦስን በሚማፀኑበት ወቅት ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበሩ ሴቶች ናቸው። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ሲቀብሩት ከሩቅ ሆነው ያዩት ሴቶች ናቸው። ጌታቸውን በመቃብር ትተው እንቅልፍ አልወስድ ቢላቸው በሌሊት ተነስተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ሁለቱ ሴቶችን በስም ሲጠራ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በትንሳኤው ዘርዘር ያለ መገለጥን ያየችው ቅድስት ማርያም መግደላዊት ላይ ዋናውን ትኩረቱን ያደርጋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ግን የሦስቱንም ስም ዘግቦ እናገኘዋለን። ይሄ አዘጋገብ የታሪክ ልዩነት ሳይሆን የወንጌላውያኑን የትኩረት ነጥብ የሚያሳይ ነው።

እነዚህ ሴቶች ማልደው ወደ መቃብሩ ሲደርሱ ድንጋዩን ማን እንደሚያንከባልልላቸው ተጨንቀው ነበር። ራሔልና ሴቶቹ የውኃውን ምንጭ መዝጊያ ድንጋይ የሚያንከባልልላቸው አጥተው “እስከ ቀትር እንጠብቃለን?” ብለው እንደተጨነቁት ማየ ሕይወት ክርስቶስ ያለበትን በጲላጦስ ማኅተም ታትሞ በሮማ ወታደሮች የሚጠበቀው የመቃብር ድንጋይን ሚያንከባልላቸው ሰው እያሳሰባቸው ነበር። ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ፍፁም ተቃራኒ ነበር። እንደ ያዕቆብ ሆኖ የመቃብሩን ድንጋይ የሚያንከባልል መልአክን እግዚአብሔር ልኮላቸው ነበር። ዘፍ ፳፱÷፰-፲

የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ፡ በልደቱ ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች  ‘ “አትፍሩ!” ያሉ መላእክት (ሉቃ ፪÷፲) ዛሬም እጅግ ጨለማ በነበረው ፀሐይ አልባ የማለዳ ጠዋት የመጡትን ሴቶችን “አትፍሩ” አሏቸው’ እያለ በልደቱ የተሰበከውን የምስራች በትንሳሣው ሌሊት ስለመደገሙ ይደነቃል። መላእክቱ የተናገሩት ቃል እጅግ የሚያረጋጋ ነበር። የሚፈልጉትን አስቀድመው ያውቁ ነበርና ከሕማማቱ በፊት የነገራቸውን አስታውሰው “እንደተናገረው ተነሥቷል” ብለው አወጁላቸው። ይሄንን ዜና የሰሙት አንስት ለሐዋርያት ለመናገር ተፋጠኑ። ቅዱስ ቄርሎስ የቅዱስ ጳውሎስንና የኢሳይያስን ቃል ተውሶ “ትንሣኤውን ሊያውጁ የተነሱት እግሮችን መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?!” ሲል ያወድሳል። ሮሜ ፲÷፲፭፣ ኢሳ ፶፪÷፯
መነሣቱን ግን በመላእክት ብቻ ሰምተው እንዳይቀሩ እርሱ ራሱም በፊታቸው ታየላቸው። አስቀድመው በመላእክት “አትፍሩ!” የተባሉ ቅዱሳት አንስት ከክርስቶስም አንደበት የሚያረጋጋውን ቃል ሰሙ “እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ ደስ ይበላችሁ!” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ “አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው።” ማቴ ፳፰÷፱-፲

ወንጌላዊው ዮሐንስ ደግሞ ሌላም ቃል ይነግረናል። ሴቶቹ ለደቀመዛሙርቱ ከተናገሩ በኋላ ሐዋርያት ወደ ቦታው መጥተው መቃብሩ ባዶ መሆኑን አይተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ማርያም መግደላዊት ግን ከመቃብሩ አጠገብ ቀረች። ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ነገር ይደመማል። ቅዱስ ጴጥሮስ መቃብሩን አይቶ ተመለሰ ማርያም መግደላዊት ግን እዛው መቅረቷን ከሴትነት ልባዊ ፍቅርና ርህራሄ ጋር ያገናኘዋል። በእውነትም ሴት ያላትን የፍቅር ጥግ አስቀድሞ በመስቀል ኋላም በትንሣኤው ተገለጠልን።

የዮሐንስ አፈወርቅን እይታን ገታ አድርገን የወንጌላዊውን ትረካ እንከተል። በጌታ መቃብር ቀኝና ግራ የተቀመጡ መላእክት “ምን ትፈልጊያለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም “ጌታን ወስደውታል፤ የትም እንዳረጉት አላውቅም።” ብላቸው ወደ ኋላ ዘወር ስትል ክርስቶስን አየቺው። ታሪኩን ከወንጌላዊው አፍ እናዳምጥ:-
‘ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ “አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሏት፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ማርያም!” አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።’ ዩሐ ፳÷፲፬-፲፰

ቅዱስ ቄርሎስ ይሄንን ተመልክቶ እንዲህ ይላል “ሞት በሷ በኩል የመጣባት ሔዋን በገነት የአትክልት ስፍራ የሞትን ቃል እንደሰማች ሁሉ (ዘፍ ፫÷፩) ማርያም መግደላዊትም በአትክልቱ ስፍራ ለሞት ሞት የሆነውን ትንሣኤውን ሰማች።” ይለናል። ምናልባት በዚህ ንግግር ውስጥ ክርስቶስ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አላረግኹም” የሚለው ቃል ጥያቄ ያስነሳ ይሆናል ። ሊቁ ጠርጡለስ “ክርስቶስ ሌላ አምላክ እየጠራ አይምሰላችሁ” ይለናል። “ይልቁንም ፈጣሪ ያለውን የፍጡር ሥጋን ይዞ እንደተነሳ ሊያመላክት እንጂ እርሱ ፍጡር ሆኖ ሌላ ፈጣሪ ኖሮት አይደለም” ይላል። በዚህ ዐሳብ ቅዱስ ቄርሎስና አፈወርቅ ዮሐንስም ይስማማሉ፤ ፍጡር ሥጋን ገንዘብ ስላደረገ ተናገረ እንጂ። እግዚአብሔር አብ የእርሱ አባትና አምላክ የሚሆንበት አገባብ ከኛ ይለያልና “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ” አለ እንጂ ወደ አባታችንና አምላካችን አለማለቱን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

ወደ ቅዱሳት እናቶቻችን እንመለስ። ጌታን እስከመስቀል ላልተለየው ሐዋርያ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሰጠው ሁሉ እስከመስቀል ለታመኑለት ቅዱሳት የከበረች ትንሣኤውን አስቀድሞ ገለጠላቸው። ባገለገሉት ልክ በወደዱትም መጠን አከበራቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ በረከት እንዳለው የትንሣኤውን ወንጌል ለሐዋርያት ይሰብኩ ዘንድ የተገቡ አደረጋቸው። ቤተክርስቲያንም ለዚህ መታሰቢያ የትንሣኤን ስድስተኛ ቀን ቅዱሳት አንስት ብላ ታከብረዋለች።ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ!

አባ መክሲሞስ ሊቀ ጳጳሳት

ይህ አባት መንፈሳዊና በሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው። እርሱም ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው። ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነበረ። የዮናናውያንንም ጽሕፈትና መጽሐፋቸው፣ ጥበባቸውንም ሁሉ ተምሮ ፍጹም አዋቂና አስተዋይ ሆነ፤ በዮናኒ ቋንቋ። ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ልዑል እግዚአብሔር የሠራውን ሕግና ሥርዓት ተማረ። አባት ያሮክላም ዲቁና በእስክንድርያ ሾመው፤ ከዚያም በኋላ ዲዮናስዮስ ቅስና ሾመው።

በተሾመባት ሁሉ ላይ ተጠምዶ የሚአገለግልና የሚጋደል ሆነ። አባ ዲዮናስዮስም በአረፈ ጊዜ አዋቂዎች፣ ኤጲስቆጶሳትና ካህናት፣ ማኅበሩም ሁሉ መረጡት በእግዚአብሔርም ፈቃድ በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ዲዮናስዮስም ስለ ጳውሎስ ሳምሳጢ በአንጾኪያ ከተማ የተጀመረው የኤጲስቆጶሳት ማኅበር ጉባኤ ተጀምሮ ሳይፈጸም አረፈ። ይህም አባት መክሲሞስ በተሾመበት ወንበር በተቀመጠ ጊዜ በማኅበሩ ጉባኤ ስለ ተወሰነውና ከሀዲው ጳውሎስ ሳምሳጢን እንደአወገዙት ከጉባኤው ሹማምንት መልእክቶች ወደርሱ ደረሱ። በትምርቱ ያመኑትንም መልእክቶቹንም ካህናቱ በአንድነት በተሰበሰቡበት አነበበው።

ከዚያም በኋላ ዳግመኛ ከራሱ መልእክቶችን ጽፎ የጳውሎስ ሳምሳጢን ስሕተት ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልዩና እንዲማልዱ እያዘዘ ወደ ግብጽ አገሮች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኖባ አገር ላካቸው ። የክብር ባለቤት ጌታችን ልመናቸውን ተቀበለ። ይህም ከሀዲ ከጥቂት ቀኖች በቀር አልኖረም፤ በፍጥነት አጠፋው እንጂ። የረከሰች ሃይማኖትንም ከዓለም አስወገደ፤ አራቀ። በዚህም አባት ዘመን ከምሥራቅ አገር ማኒ የሚባል ራሱን የዕውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስን ያደረገና ክፉ ስሕተትን የሳተ ሰው ተገለጠ። ወደ ሶርያ ምድርም ደረሰ፤ አርኬላዎስ የሚባል ኤጲስቆጶስም ከእርሱ ጋራ ተከራከረ። ስሕተቱንም ገላልጦበት አሳፍሮ ከአገሩ አሳደደው ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ፋርስ ሔደ፣ ራሱንም ነቢይ አደረገ፣ የፋርስ ንጉሥ ብህራምም ይዞ ከሁለት ሠነጠቀው።

ተከታዮቹ የሆኑ ሁለት መቶ ሰዎችን ዘቅዝቆ እስከ ወገባቸው በምድር ውስጥ ተከላቸው እነሆ ከሰው አትክልትን ተከልሁ አለ። ይህም አባት መንጋውን በመጠበቅ ሲጋደልና በቀናች ሃይማኖትም ሲያጸናቸው ኖረ። ከመናፍቃንና ከከሀድያን ችግር እስከ አረፈባት ቀን ድረስ በድርሳናትና በተግሣጻት ጠብቆ አዳናቸው። በማርቆስም ወንበር ዐሥራ ስድስት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ። በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር። አሜን። ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ

የሰሙነ-ሕማማት ፤ ኃሙስ

ጸሎተ-ሐሙስ :- በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡  የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ (ማቴ. ፳፮÷፴፮-፵፮፣  ዮሐ.፲፯)

          ሕፅበት ሐሙስ ፡- ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች “በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም፤ የሌላውን እግር እናጥባለን” ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

       የምስጢር ቀን :-ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም “ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው ፤ እንካችሁ ብሉ” ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ “ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ” በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

       የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ፡- ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡  “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፤ ከእርሱ ጠጡ” በማለቱ ይታወቃል። (ሉቃ. ፳፪÷፳) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊዉን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳስ ሐሙስ ተባለ፡፡

        የነጻነት ሐሙስ ፡-ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ” በማለት (ዮሐ. ፲፭÷፲፭)፤ ከባርነት የወጣንበት፣ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ኃሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል። “ባሮች አልላችሁም” ተብለናልና፡፡