ወጥመድ

“ዘወትር በወጥመዶች መካከል እንደምትኼድ በገደልም መካከል እንደምትመላለስ ዕወቅ”(ሲራ9:13)
ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ድረስ ወርኅ ጽጌ ብለን በምንጠራው ይህ ወቅት ቅድስት በቤተክርስቲያናችን የአምላክ እናት የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያምንና የልጇ ክርስቶስን ስደት እያሰበች በአበባ ታጅባ ሌሊቱን በሙሉ በማኅሌት ታመሰግናለች።
ታድያ እናንተስ እንዴት አደራችሁ? ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ነጠላችሁን አጣፍታችሁ አጥቢያችሁ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ለማኅሌት ተፋጠናችሁ? አበባ ይዛችሁ “ልጅሽን ታቅፈሽ እመቤቴ ሆይ ነይ ማርያም”እያላችሁ ከሊቃውንቱ ጋር ወረባችሁ? ሌሊቱን ሙሉ ነጫጭ ለብሰው “አክሊለ ጽጌማርያም”ከሚሉምዕመናን መካከልበእጣኑ ልዩመዓዛታውዳችሁ፡የከበሮድምጽእየሰማችሁየቅዱሳን መላእክትን ምግብተመገባችሁ? ኪዳንአደረሳችሁ? ታላቁን የቤተክርስቲያን ጸሎት ቅዳሴን አስቀደሳችሁ? ለምን? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው በወጥመድ እንዳይያዙ ነው። ሰዎችም የማሰቡ ኃይልን የተሰጣቸው ኃጢአትን እንዲያስወግዱ ነው በማለት ይነግረናል። ሊቁ ይህንን የሚነግረን እንሰሳት በወጥመድ መያዝ እንደማይፈልጉ ሊያስረዳን አይደለም።ይልቁኑ የማሰብ ኃይል ተሰጥቶን ሳለ ይባስ ብለን ከምድር አራዊት በታች የማናስተውልከኾንን ሊደረግልን የሚችል ምሕረት ወይም ይቅርታ እንደምን ያለ ምሕረት እንደምንስ ያለ ይቅርታ ነው? ብሎ በተግሳጽ ከተያዝንበት ሊመልሰን ነው። የሚደንቀው ነገር ደግሞ እንሰሳት ሲሆኑ፡ የያዛቸው ወጥመድ ተመልሶ የማይ’ዛቸው መኾኑነው።
እንደምታውቁት ወጥመድ እንሰሳትን ለመግደል፡ ወይንም ደግሞ ለመያዝ የምንጠቀመው መሳሪያ ነው። ወጥመድ ስናጠምድ ፡ የሚወዱትንና አይተውት ሊያጓጓቸው የሚችሉ ነገሮችን ከፊት በማስገባት ነው። በወጥመድ የተያዘ እንሰሳ መጨረሻው የሚሆነው ወይ መሞት ወይንም ደግሞ የተጠመደበትን አላማ ሲፈጽሙ መኖር ነው። ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስየሰውን ልጅ ዓለም እንደፈለገ ለማድረግ የሚጠበቅበት አንዱንና ዋነኛውን የሰውነት ክፍል ብቻ መያዝ፡ ማዘናጋትና መቆጣጠር ነው። አእምሮን። ለሰው ልጅ “እንደ ባለአእምሮ ተመላለሱ”የሚል ትእዛዝ እስኪሰጠው ድረስ አእምሮው ኃያልና ለሚሰራቸው ነገሮች ሁሉ ዋና ክፍል ነው።ታድያ ይህ ክፍል በወጥመድ በተያዘ ጊዜ መላ ሰውነት አይንቀሳቀስም።ውጤታማ አይሆንም።
አብዛኞቻችን ከስልኮቻችን ጋር ያለን ቁርኝት የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ከተቀመጥን እንዳንነሳ፡ ከምንም በላይ ደግሞ አምሽተን ተኝተን ጠዋት ላለማስቀደሳችን፡ ማጠናቀቅ የሚገቡንን ስራዎች ጨርሰን ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንሄድ ምክንያቶቻችን ናቸው።አንድ ደቂቃ ብቻ ውሰዱና አስቡት በአንድቀን ምን ያህል መንፈሳዊ መጻሕፍትን ታነባላችሁ? ምን ያህል ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ትማራላችሁ? በቀን ለምን ያህል ደቂቃ ጸሎት ታደርሳላችሁ? ምን ያህል የእግዚአብሔርን ፍቅር ታስባላችሁ? በሌላ በኩልስ በእጃችሁ የምትይዙት ስልክ ይህንን አእምሮዋችሁ ምን ያህል ተቆጣጠረው? ምን ያህል ሰዓታትን በስልክ ታጠፋላችሁ? በስልክ ላይስ ለተመለከታችሁት አሉታዊ፡የማይጠቅም ከእናንተ ጋር የማይገናኝና
የማይመለከታችሁ ነገር ምን ያህል ታወራላችሁ? ምን ያህል ስልካችሁ አእምሮዋችሁን ፡ ሰዓታችሁን ጉልበታችሁን ይመጠዋል? ያደርቀዋል? ይቆጣጠረዋል? መልሱን ለእናንተ ትተነዋል!!!