ቅዱስ ድሜጥሮስ

ይህም አባት አስቀድሞ መጻሕፍትን ያልተማረ ሕዝባዊ ገበሬ ነው። በወላጆቹ የወይን አታክልት ቦታዎች ውስጥ የሚሠራ ሆነ። ከታናሽነቱም ሚስት አጋብተውት ከእርሷ ጋር ዐርባ ስምንት ዓመት ኖረ። ድንግልናቸውን በንጽሕና የጠበቁ ናቸው። የተሠወረውን ከሚያውቅ እግዚአብሔር በቀር ይህን የሚያውቅ የለም ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ዮልያኖስ ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት።ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆነውን በምልክት ገለጠለት እንዲህም አለው ። “ነገ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ አንተ የሚገባ ሰው አለ ከአንተ በኋላ ሊቀጳጳሳት የሚሆን እርሱ ነውና ያዘው አትተወው።” በዚያችም ቀን ድሜጥሮስ ወደ አታክልቱ ቦታ ገባ። ያለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ አገኘ ያንንም የወይን ዘለላ በረከት ሊቀበልበት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮልያኖስ ይዞት ሔደ።በዚያንም ጊዜ አባ ዮልያኖስ ድሜጥሮስን በእጁ ይዞ ለሕዝቡ ሁሉና ለኤጲስ ቆጶሳት አሳልፎ ሰጠው ። “ከእኔ በኋላ ሊቀጳጳሳት የሚሆናችሁ ይህ ነው ስለ’ርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ነግሮኛልና ይዛችሁ ሹሙት” አላቸው ።ከዚህም በኋላ አባ ዮልያኖስ በአረፈ ጊዜ የጸሎቱን ሥርዓት ፈጽመዉለት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መላበት። የቤተክርስቲያን የሆኑ የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍትን አንብቦ ተረጐማቸው። ብዙዎች ምሥጢራትም ተገለጡለት። ከዚህም በኋላ ባሕረ ሐሳብ የተባለውን የዘመን መቊጠሪያ ሠራ። ከእርሱ በፊት የነበሩ የክርስቲያን ወገኖች የመድኃኒታችን የጥምቀቱን በዓል ጥር ዐሥራ አንድ ቀን አክብረው በማግስቱ የከበረች ዐርባ ጾምን ጀምረው እስከ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ድረስ ይጾማሉ።ከዚያም በኋላ መጋቢት ሃያ ሁለት ቀን የሆሣዕናን በዓል አክብረው በማግስቱ የሕማማትን ሰሞን ጾም ጀምረው ይጾማሉ።ከሐዋርያትም ዘመን ጀምሮ እስከ ‘ርሱ ዘመን እንዲህ እያደረጉ ኖሩ።እርሱም እንዲህ ሠራ። የከበረች የጌታችን ጾም መግቢያዋ ከሰኞ ቀን እንዳይፋለስ ፍጻሜውም በዐርብ ቀን። ከዚህም የሆሣዕናን በዓል አያይዞ ሠራ ። በሚቀጥለው ሰኞ ቀን የሕማማት ጾም ተጀምሮ እንዲጾም የስቅለቱም በዓል ከዐርብ ቀን እንዳይፋለስ የከበረች የትንሣኤውና የጰራቅሊጦስም በዓል ከእሑድ ቀን የዕርገቱም በዓል ከሐሙስ እንዳይፋለስ። እንዲሁም አዘጋጅቶ ለኢየሩሳሌም ሀገር፣ ለሮሜ ፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሀገር ሊቃነጳጳሳት ለየአንዳንዳቸው ላከላቸው።እነርሱም በደስታ ተቀብለው ሠሩበት እስከዚችም ቀን ጸንቶ ኖረ።በቊርባን ቅዳሴ ጊዜም ዘወትር ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያየው ሆነ።የሕዝቡ ኃጢአታቸው በፊቱ ግልጥ ሆነ ። ስለዚህም የማይገባቸውን ሥጋውንና ደሙን ከመቀበል ይመልሳቸዋል ።እንዲህም ይላቸዋል ፣ “ሒዱ ንስሐ ግቡ ከዚያም በኋላ መጥታችሁ ሥጋውና ደሙን ተቀበሉ።” ስለዚህም ነገር ብዙ ሕዝቦች ኃጢአት ከመሥራት የሚጠበቁ ሆኑ። ልባቸው የደነደነ ሌሎች ግን ጠሉት። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ።”ይህ ሰው ሚስት አግብቶ ሚስቱም ከእርሱ ጋር ትኖራለች። ሳይገባውም በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ተቀምጠ። ከንጹሕ ድንግል በቀር አይሾምበትም ነበርና እኛንም ኃጢአተኞች ናችሁ ብሎ ይገሥጸናል።” በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ “ድሜጥሮስ ሆይ ራስህን ብቻ ማዳንን አትሻ ወገኖችህም ይጠፉ ዘንድ አትተው። ነፍሱን ስለመንጋዎቹ አሳልፎ ለሞት የሚሰጥ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደ ሆነ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል የተናገረውን አስብ” አለው። ድሜጥሮስም መልአኩን “ጌታዬ የምትለኝ ምንድን ነው?” አለው መልአኩም “በአንተና በሚስትህ መካከል ተሰውሮ ያለውን ምሥጢር ለወገኖችህ ግለጽ!” ብሎ መለሰለት። ከዚህም በኋላ ሕዝቡን አሰባሰባቸው። ሊቀ ዲያቆኑንም “ወጥተው ወደቤታቸው እንዳይገቡ ሕዝቡን ንገራቸው !” አለው። ራሱም ቅዳሴውን ቀደሰ ሁለተኛም ዕንጨቶችን ሰብስበው እሳትን እንዲያነዱ አዘዛቸው ። እንዳዘዛቸውም አደረጉ። ያን ጊዜ ይህ አባት ተነሥቶ ከሚነደው እሳት መካከል ገብቶ ለረጅም ጊዜቁሞ ጸለየ ከእሳቱም ፍህም አንሥቶ በሚከናነብበት ቀጸላ አደረገ ፤ ሚስቱንም ጠርቶ “መጎናጸፊያሽን ዘርጊ!” አላት። በዚያም የእሳቱን ፍህም ጨመረ፤ በእሳቱም መካከል በአንድነት እየጸለዩ ቆሙ ፤ሕዝቡም እጅግ ያደንቁ ነበር።ከዚህም በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ እንዲህ ብለው ለመኑት። “አባታችን ሆይ ይህን የሠራኸውን ሥራ ታስረዳን ዘንድ ከቅድስናህ እንሻለን ።” እርሱም “ይህን ሥራ የሠራሁት ከንቱ ውዳሴን ሽቼ አይደለም። እናንተ እኔን አምታችሁ ስለ እኔ እንዳትጐዱ እንድትድኑ ከዚች ሴት ጋር በመካከላችን ተሠውሮ ያለውን ምሥጢር እገልጽላችሁ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ አዘዘኝ ነው እንጂ!” አላቸው ።እርሷ የአባቴ የወንድሙ ልጅ ናት፤ በሕፃንነቷም አባቷ ሞተ፤ በአባቴም ቤት ከእኔ ጋር አደገች፤ አካለ መጠንም በአደረሰን ጊዜ አባቴ እርሷን አጋባኝ። ወደጫጉላ ቤትም በገባን ጊዜ “እኔ እኅትህ ስሆን ለአንተ እንዴት አጋቡኝ?” አለችኝ።እኔም “የምትፈቅጂ ከሆነ ድንግልናችንን ጠብቀን በአንድነት እንኑር። ይህንንም በመካከላችን ያለውን ምሥጢር የሚያውቅ አይኑር !”አልኋት በዚህም ተስማምተን በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ዐልጋ እየተኛን አንድ መጐናጸፊያንም እየተጐናጸፍን ዐርባ ስምንት ዓመት ያህል ኖርን። ይህን ሥራችንንም ያለ እግዚአብሔር የሚያውቅ የለም። እኔም እርሷ ሴት እንደሆነች አላወቅኋትም፤ እርሷም እኔን ወንድ እንደሆንኩ አታውቅም፤ በየሌሊቱም ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ በንስር አምሳል ወደ መኝታችን እየገባ ክንፎቹን አልብሶን ያድራል ሲነጋም ከእኛ ይሠወራል አላቸው ። በዚያንም ጊዜ በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቀው ለመኑት፤ እርሱም ይቅር አላቸው፤ አጽናናቸውም ።ይህንንም ድንቅ ሥራ ያዩ ሁሉ ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
በዚህ አባት ዘመንም ስማቸው ቀሌምንጦስ፣ አርጌንስ የሚባሉ ሌሎችም መናፍቃን ሰዎች ተነሥተው ታዩ። ሌሎችም በአንድነት ሁነው ስለሃይማኖት የፈጠራ መጽሐፍን ጻፉ፤ እርሱም አውግዞ ከምእመናን ለያቸው እርሱም ሁል ጊዜ ያለ ዕረፍት ከጠዋት እስከ ማታ ምእመናንን የሚያስተምራቸው ሆነ።ሸምግሎ በደከመም ጊዜ በአልጋ ላይ አስቀምጠው፣ ተሸክመው ወደ ቤተክርስቲያን ያደርሱታል፤ እስከ ማታድረስም ያስተምራቸዋል። ሰዎችም ሁሉ ትምህርቱን ይሰሙ ዘንድ ይጨናነቃሉ መላ የሕይወቱ ዘመንም መቶ ሰባት ነው። በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ። ከቅዱስ ድሜጥሮስ ረድኤት በረከት ያሳትፈን። (ዋቢ፡ ስንክሳር ዘወርኃ ጥቅምት)