በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዐቶች ያውቁ ኖሯል?

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት “ወአንትሙሰ ተዐቀቡ፤ ወግበሩ ተዝከረ ሕማማቲሁ!”  (እናንተስ ተጠበቁ፤ የሕማሙን መታሰቢያ አድርጉ!” ትእዛዝ ፴፩
ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችን የምሥጢረ ሕማማቱን ነገር መንፈስ ቅዱስ ሲገልጽለት “ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ” (“እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማታችንንም ተሸከመ›!” ማቴ. ፰፥፲፯ ፣ ኢሳ ፶፫፥፬ ሲል ተናገረ። የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፈቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግስት በመሸከም መከራ መስቀሉ ስለተፈጸመበት እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ተባለ። ኢሳ. ፶፫፥፬፡

ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም. የነበረው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንኡስ፤ በማዕከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትንና በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ታዲያ ሰሙነ ሕማማትን ጌታችን ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገው ትድግና ቅዱሳት መጻሕፍት በየበኩላቸው ቢዘረዝሩትም ቸርነቱ፣ ርህራሄውና በጠቅላላው በአምላካዊ ጥበቡ የሠራቸው ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ሥራዎች ጸሐፊ፣ አንባቢና ሰሚ ሊደርስባቸውና ዝርዝራቸውን ሊከተላቸው ሲፈልግ ገና በዐሳቡ ውጥን ላይ ድካም እንዲሰማውና ፍጡርነቱ ፈጣሪን እንዳይመረምር ያስገድደዋል፡፡

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በቃሉ ብቻ ዳን በማለት ሊያድነው ሲቻለው የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ በፈቃዱ ሰው የሆነበትን፣ ሰውም ከሆነ በኋላ የተቀበላቸው ልዩ ልዩ መከራ የተቀበለበት ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማትን የምናከብረው አባቶች ሐዋርያት የጌታን ጾም ለብቻው እንድናስበው እንዳደረጉን ሁሉ የጌታ ሕማማትም እንዲሁ በተለየ ለብቻው እንድናስበው የሰሩልን ሥርዓት ነው። ታዲያ ይህንን ሳምንት ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን “ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተ ኩነኔ (፶፻፭፻ ዘመን) እና የጌታችን ሕማም፣ መከራ፣ እንግልት የሚታሰቡበት ነው” ብለው ያስቡታል፡ ፡ ስለዚህም እነዚህን ሁለት ነገሮች ምክንያት በማድረግ በሰሙነ ሕማማት የሚተገበሩ ሥርዓቶች አሉ። እነርሱም፡
ጥቁር ልብስ መልበስ፡ በሰሙነ ሕማማት ወቅት በተለይ በዕለተ ዐርብ ካህናቱ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ የኃዘንና የመከራ መገለጫ በመሆኑ በዚህ ወቅትም የጌታን ኃዘን መከራ ለማሰብና ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ባይገኝ ደግሞ የተገኘውን ልብስ ገልብጠው ይለብሱታል፡፡

በጸሎተ ኃሙስ ቃጭሉ ተለውጦ ጸናጽል ይሆናል። ምክንያቱም በዘመነ ኦሪት የነበሩ አበው ጸሎታቸው ፍጹም ሥርዓት እንዳላሰጣቸው ለማጠይቅ ነው፡፡ ከቃጭል የጸናጽሉ ድምጽ ከርቀት እንደማይሰማ ሁሉ የአበው ጩኸት አናሳ መሆኑን ለማጠየቅ፤ የይሁዳን ግብር ለመግለጥና ይሁዳ ጌታን ለማስያዝ በድብቅ ያደባ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡

እርስ በእርሳችን አንሳሳምም፤ መስቀል አንሳለምም: እርስ በእርሳችን አለመሳሳማችን ይሁዳ በመሳም አሳልፎ መስጠቱን ለማሰብና ለማስረዳት ሲሆን መስቀልን ያለመሳለማችን ምክንያቱ ደግሞ፣ መስቀል በዘመነ ኦሪት የኃጥአን መቅጫ እንጂ የሰላም ምልክት እንዳልነበረ ለማጠየቅ ነው፡፡ መጻሕፍትም “በመስቀሉ ሰላምን አደረገ” እንዲሉ መስቀል አዳኝ የሆነው ጌታ ከተሰቀለ በኋላ መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡ አብዝተን መጾም አለብን፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አብዝተን እንድንጾምና እንድንጸልይ ያዙናል። ለምሳሌ በሰሙነ ሕማማት የሚችል በሁለት ቀን ውኃና ጨው ያለበት ምግብ እየተመገበ እንዲጾም ሲያዙን ያልቻለ ግን ፲፫ ሰዓት እየጾመ እየጸለየ ውኃና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲመገብ አዘዋል።

ለሙታን ፍትሐት አይደረግም: በሰሙነ ሕማማት ወቅት ለሞቱ ሰዎች ፍትሐት አይደረግላቸውም፤ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔን የምናስብበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ የነበሩ ሰዎች ፍትሐት እንደማይደረግላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ተስፋ ላለውና ለአማኝ እንጂ ለማያምን ትንሣኤ ዘለክብር፤ ለማይነሣ ቢሆን ፍትሐት አይደረግለትም፡፡

በወይራ ቅጠል ጥብጠባ ይደረጋል:  በዕለተ ዐርብ የስግደት ሥርዓቱን ከፈጸምን በኋላ ወደ ካህናት አባቶቻችን እየሔድን በወይራ ዝንጣፊ ጥብጠባ ተደርጎልን ቀኖና እንቀበላለን፤ በዚህ ወቅት የምንቀበለው ቀኖና የሰሙነ ሕማማትን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ወይራ ጽኑ በመሆኑ የጌታ መከራ ጽኑ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ሕጽበተ እግር ይደረጋል: ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ “ጸሎተ አኰቴት” በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል። ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው። ወይራ ጸኑዕ ነው፤ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)። በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም  “ሐዋርያቲሁ ከበበ፤ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ” እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡ ቅዳሴ: የጸሎተ ኃሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉሊያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡ ፡

በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡ በዚህ ወቅት በዋነኝነት ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ይነበባል። የሰሙነ ሕማማት ሥርዓተ ጸሎትና አገልግሎት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮት ጋር የተያያዘ ቢሆንም አሁን ያለውን ሥርዓት የያዘ ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ የዋለው ከጌታ ልደት በኋላ በ፲፬ተኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፬፻፹ ዓ.ም. የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ ዐዜብ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት፣ ቀደም ሲል በግእዝ ብቻ ታትሞ በነበረው የግብረ ሕማማት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡

የመጽሐፉ ስያሜም ከጥንት ስሙ ጀምሮ ግብረ ሕማማት እንደሚባል በመጽሐፍ ውስጥ በብዙ ክፍል ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከጥንት ፍጥረት ከባሕርይ አባቱ አብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ በረቂቅ ጥበቡ ዓለማትንና ፍጥረታትን ሁሉ በየወገኑ ፈጥሮ እንደባሕርያቸው በቸርነቱ ይመግባል።

ጸሎተ አስተስርዮ፣ ፍትሐት፣ ክርስትና፣ ቅዳሴ፣ መልክአ መልኮች አይጸለዩም።

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና በጸሎተ ኃሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ኃሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡ ፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፣ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ኃሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ኃሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን በዲያብሎስ እስራት ውስጥ ስለነበርን ያንን በማሰብ ካህናት ንስሐ አይሰጡም ወይም “ይፍታህ!” አይሉም። ስንሞትም የፍትሐት ጸሎት አይደረግም ለዚህም ተብሎ በዚህ ሳምንት ሊሞት የሚችልን ሰው በማሰብ በሆሳዕና በዓል ሳምንቱን የሚወክል ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡ ቅዳሴም የሚኖረውም ኃሙስ ዕለት ብቻ ነው። ይህም ጌታችን በምሴተ ኃሙስ ሐዋርያቱን እግራቸውን አጥቦ ቆርቦ ስላቆረባቸው ነው። እኛም ይህን አብነት አድርገን ከሕጽበተ እግር ጋር ቅዳሴ ይኖራል፡፡ የመልክእ ጸሎት የሰላምታ ጸሎት በመሆኑ በዚህ ሳምንት አይጸለይም ከዚህ ልዩ የሆነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የደረሱት መልክአ ሕማማት ብቻ ይጸለያል፡፡

በአጠቃላይ በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ከሌላው ጊዜ በተለየ የሚሰገድበት፣ የቻለ ኮከብ እስኪወጣ ያልቻለ እስከ ፲፪፡00 ሰዓት የሚጾምበት፣ ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን ሙሉ ስትመራበት የነበረውን ሥርዓት ትታ አዲስ ሥርዓት የምትመራበት እጅግ ወርቃማ ጊዜ ነው።

ምንጭ፡ ማኅበረ ቅዱሳን ገጸ-ድር (Website) (በወልደ አማኑኤል) እና ስምዓ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)

ጉባኤ ኬልቄዶን

የንስጥሮስ ክህደት በኤፌሶን ጉባኤ በ፬፻፴፩ ዓ.ም. ከተወገዘ በኋላ የክህደቱ ተከታዮች ፈጽመው ባይጠፉም፣ ንስጥሮሳውያን በብዛት ተሰራጭተው የሚገኙት በፋርስና በባቢሎን ቢሆንም በኤፊሶንና በቁስጥንጥንያም በመጠኑም ይገኙ ስለነበር እነርሱን የሚቃወሙ ደግሞ በብዛት ከእስክንድርያ ሌላ በቁስጥንጥንያም ይገኙ ነበር፡፡ የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ የሚቃወም አውጣኪ (Eutyches) የሚባል በቁስጥንጥንያ የአንድ ትልቅ ገዳም አበምኔት የነበረና “ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል” የሚለውን የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ በመቃወም እርሱ በተቃራኒው ወደባሰ ክህደት አመራ፡፡ በቁስጥንጥንያ አውጣኪ “ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባህርይ” አለው ብቻ ያስተምር ነበር፡፡ አባባሉ የቄርሎስን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ቢመስልም አውጣኪ ግን አንድ ባህርይ ሲል የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ብቻ ማለቱ ነበር፡፡ በአውጣኪ አባባል “ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ውጦታል አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት በተዋሐዱ ጊዜ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፡፡” ግን ልክ አይደለም። የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ የአውጣኪን ኑፋቄ ትምህርት እንደሰማ ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፎ ስሕተቱን በማስረዳት ከዚህ ስህተት በአስቸኳይ እንዲታረምና ይህንን ትምህርት እንዳያሰራጭ አስጠነቀቀው፡፡ አውጣኪም ትምህርቱን ማሰራጨት ባለማቆሙ የተነሳ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በስሩ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳት ሰብስቦ በ፬፻፵፰ ዓ.ም. አወገዘው፡፡ አውጣኪ “የቄርሎስን ሃይማኖት ስለ መሰከርኩ እንጂ አንዳች ስሕተት ሳይኖርብኝ ያለ አግባብ ተወገዝኩ” ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ቴዎድስዮስ አመለከተ፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱ ዓለም አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት እንዲሰባሰቡ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤው በኤፌሶን በ፬፻፵፱ ዓ/ም እዲደረግ በጉባኤው ላይ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ተመረጠ። አውጣኪም ለጉባኤው ተጠርቶ እንዲያስረዳ ተጠየ። እሱም “እምነቴ ልክ እንደቄርሎስ ነው” በማለት የኤፌሶኑ ጉባኤ የወሰነውን የቄርሎስን ዐሳብ በውሸት አቀረበ። ጉባኤው ይህን ሰምቶ ከውግዘቱ ፈታው። የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በቴዎዶስዮስ ዳግማዊ ጸደቀ፡፡ ይህም ጸድቆ የቆየው ይህ ንጉሠ ነገሥት እስከ ሞተ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ፪ኛው የኤፊሶን ጉባኤ ከአለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ ወር ፬፻፶ ዓ.ም. ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ በድንገት ከፈረስ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ቴዎዶስዮስ ወራሽ ስላልነበረው ለአልጋው ቅርብ የነበረች ታላቅ እኅቱ ብርክልያ (Pulcheria) ነበረች፡፡ ብርክልያ ግን በድንግልና መንኵሳ ነበር፡፡ ሆኖም ብርክልያ ለሥልጣን ስለጓጓች ምንኵስናዋን አፍርሳ የሮም መንግስት የጦር አዛዥ ጄኔራል የነበረውን መርቅያን (Marcianus) አግብታ በነሐሴ ፬፻፶ ዓ.ም. እሱ ንጉሰ ነገስት እሷ ንግስት ሆነው የሮምን መንግስት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ይህ የብርክልያ ምንኵስናን ማፍረስ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በተለይም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የሮሙ ፖፕ ግን ከአዲሶቹ የሮም መንግስት ነገስተ-ነገስታት ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት ጋብቻቸውን በማወደስ አጽድቆላቸዋል። በዚህም የተነሳ ከንጉሳዊው ቤተሰብ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፡፡ብዙም ሳይቆይ ፖፕ ልዮን በአሳሰበው መሠረት ንጉስ መርቂያን ጥቅምት ፰ ቀን በ፬፻፶፩ ዓ.ም. ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፤ ጉባኤውም ኬልቄዶን እንዲደረግ ተወሰነ። በጉባኤውም ላይ ከ፮፻ በላይ የሚሆኑ ጳጳሳት ተገኙበት። በጉባኤውም ላይ የፖፕ ሊዮን ጦማር እንዲነበብ ተደረገ። በውስጡ አንድ አካል ሁለት ባህሪይ የሚል ክህደት ስለተገኘበት ዲዮስቆሮስ “አልቀበለውም” አለ።በጉባኤው የነበሩ ጳጳሳት ነገስታቱን ስለፈሩ ዝም አሉ፡፡  ዲዮስቆሮስና እርሱን ተከትለው የወጡት ጳጳሳት ጉባኤውን አውግዘው ሄዱ፤ ጉባኤውም እነርሱን አወገዛቸው። ንግስት ብርክልያም  “ጉባኤውን የማትቀበለው እኛን በመናቅህ አይደል?” ብላ አስደበደበቺው፣ ጽህሙንም አስነጨችው፣ እርሱንም በግዞት አስላከችው። እርሱም የወለቀውን ጥርሱን የተነጨውን ጽህሙን ለእስክንድርያ “እንኩ የሃይማኖት ፍሬ” በማለት ላከላቸው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ከሮሙ ቤተክርስቲያን ጋር ተለያይታ ቀረች። ጉናኤውንም “ጉባኤ ከለባት” አሉት፤ የውሾች ጉባኤ ማለት ነው፤ ጳጳሳቱ የነገስታቱን ፈቃድ ለመፈጸም ታድመዋልና፡፡ እንደ እኅቶቿ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔና ቀኖና አልተቀበለችውም፤ አትቀበለውም፡፡ ምንጭ፡- የቤተክርሰትያን ታሪክ በዓለም መድረክ

አባ ሚካኤል

ይህም አባት በአስቄጥስ በአባ መቃርስ ገዳም መንኲሶ በገደል ተጸምዶ ኖረ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎድሮስ በአረፈ ጊዜ በላዩ የትንቢት መንፈስ ያደረበት አንድ ጻድቅ ሰው እስከሚያስረዳቸው ድረስ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ አድርገው ለዚች ሹመት ስለሚሻል ሲመክሩና ሲመረምሩ ብዙ ቀኖች ኖሩ። ከዚህም በኋላ ያ ሰው ‘እኔ በአባ መቃርስ ገዳም በነበርኩ ጊዜ ስጸልይ “የሊቀ ጵጵስና ሹመት ለሚካኤል ይገባዋል፤ ለዚች ሹመት የሚሻል እሱ ነውና” የሚል ቃልን ከሰማይ ሰማሁ’ አላቸው፡፡ ሁሉም ስለ ትሩፋቱ ተናገሩ፤ ስለ እርሱም ተስማምተው ከገዳሙ ወደ እስክንድርያ ሊያመጡት ከመስር ገዥ ዘንድ ደብዳቤ አጽፈው ያዙ። ሊያመጡትም ሲሔዱ ስለ ገዳሙ አገልግሎት ከሽማግሎች መነኰሳት ጋር ወደ ጋዛ ከተማ ሲመጣ በመንገድ አገኙት፤ ይዘውም አሰሩት። ወስደውም በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፤ ያቺም ዕለት በጌታ ደም የከበረ መስቀል በዓሉ የሚከበርባት ናት። ይህም የሆነው ከዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በኋላ የሐሚድ ልጅ እልሲድ በሚገዛበት ዘመን ነው። በሹመቱ ወራትም መርዋን አልጋዲን ነገሠ። የእስክንድርያም አገር ሰዎች ከጥቂት ካፊያ በቀር ብዙ ዝናብ ሳይዘንብላቸው ብዙ ዓመታት ኖሩ። በዚያች እርሱ በተሾመባት ቀን በሁለተኛውም በሦስተኛውም ብዙ ዝናብ ዘንቦላቸው እጅግ ደስ አላቸው።በዚህም አባት ዘመን በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ደረሰ፤ ከምእመናንም ብዙዎች ሸሹ። የክብር ባለቤት ክርስቶስንም የካዱት ሰዎች ቁጥራቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነ። ለዚህ ነገር ምክንያት የሆነውን ከእርሱ እግዚአብሔር እስከአጠፋው ድረስ ይህ አባት ስለዚህ በታላቅ ኀዘን ውስጥ ነበር። ዳግመኛም በዚህ አባት ዘመን ለመለካውያን፣ ቆዝሞስ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ ሳለ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ክርስቶስ ተዋሕዶ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ጋራ ተከራክሮ ይህ አባት አባ ሚካኤል እንዳስረዳው አመነ። እንዲህም ብሎ በእጁ ጻፈ፡ “የክብር ባለቤት ክርስቶስ ከተዋህዶ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ እንደተናገረ የመለኮቱና የትስብእቱ አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንቶ ይኖራል” ሲል ኤጲስቆጶሳቱም እንዲሁ ‘ “ከተዋሕዶ በኋላ ስለ ክርስቶስ የተለያዩ ሁለት ባሕርያት፣ ሁለት ገጻት አሉት” ይሉ ዘንድ የሚገባ አይደለም’ ሲሉ ጻፉ።
ሐዋርያትም በሰበሰቧት በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድነት ጸንተው ሊኖሩ ተስማሙ።ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ሰዎች መለካዊ የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የሚባል ሰው በላያችው ጥፋትን አመጣ። እርሱ ኤጲስቆጶስነት እንዲሾሙት ሽቶ አልሾሙትምና ስለዚህ ወደ እስላሞች ንጉሥ ሒዶ በአባ ሚካኤል ነገር ሠራበት። ከዐመፀኞች ነገሥታትም ብዙ መከራ ደረሰበት። ጽኑዕ የሆነ ሥቃይም አሠቃዩት፤ ብዙ ግርፋትም ገረፈው፣ ለረጅም ጊዜ በእግር ብረት አሠሩት፣ አንገቱንም በሰይፍ ሊቆርጡ ወደ መኰንኑ አቅርበውት ነበር። ስለ መንጋዎቹም ጥበቃ እግዚአብሔር አዳነው።ዳግመኛም በመርዋን አልጋዲ ዘመነ መንግስት የሙሴ ልጅ በሆነ በንጉሥ አገልጋይ አደባባይ በታላቅ ሥቃይ አሠቃዩት። መኰንኑም ገንዘብ እንዲሰጠው ሽቶ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ሚካኤልን አስረው ሰዎችም መጥተው ዋስ ሁነው አወጡት። ምጽዋትም ጠይቆ ለመኰንኑ ብዙ ገንዘብ አምጥቶ እንዲሰጠው ወደ ላይኛው ግብጽ ወሰዱት።
ይህ አባትም ወደ ላይኛው ግብጽ በሔደ ጊዜ በዚያ ብዙ ተአምራትን አድርጎ የክብር ባለቤት ክርስቶስን የካዱትን ምእመናን ብዙዎቹን ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አስገባቸው። የኢትዮጵያ ንጉሥም ይህን አባት የእስላሞች መኳንንት እንዳሠቃዩት በሰማ ጊዜ ፍጹም ኀዘንንም አዘነ። መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ወደ ግብጽ ሀገር ዘምቶ ከላይኛው ግብጽ ደረሰ፡፡ ከርሱ ጋርም መቶ ሺህ ፈረሰኞች፣ አርበኞች፣ መቶ ሺህ በበቅሎ የተቀመጡ፣ አሁንም በግመል የተቀመጡ፣ መቶ ሺህ አርበኞች ወታደሮች ነበሩ። ብዙ ሀገሮችንም አጠፉ፤ ብዙዎችንም ማረካቸው። የግብጽ ንጉሥም ይህ ሁሉ የሆነው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱ ስለ አባ ሚካኤል እንደሆነ ዐውቆ ከእስራቱ ፈጥኖ ፈታው፤ ታላቅ ክብርንም አከበረው። እንዲሁም የክርስቲያንን ወገኖች ሁሉ እጅግ አከበራቸው።
ከዚህም በኋላ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ ይልክ ዘንድ ወደ አገሩም እንዲመለስ ያዝዘው ዘንድ የግብጽ ንጉሥ ይህን አባት አባ ሚካኤልን ለመነው። ይህም አባት ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ እርሱንና መኳንንቱን መሳፍንቱንና ሠራዊቱን እየባረከና እየመረቀ ደብዳቤ ጽፎ ላከ። እንዲህም አለው “እነሆ በአንተ ምክንያት ከእስራትና ከስቃይ ሁሉ እግዚአብሔር አድኖናልና አሁን ወደ ሀገርህ በሰላም በፍቅር ተመለስ። ስለ እኔና ስለ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ስለ ደከምህ መልካም ዋጋህን እግዚአብሔር በመንግሥተ ሰማያት ይስጥህ።” የኢትዮጵያ ንጉሥም የዚህን አባት የሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልን ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ ወደ ሀገሩ በሰላም በፍቅር አንድነት ተመለሰ።
አባ ቆዝሞስና ወገኖቹም ከሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋራ በተስማሙ ጊዜ አባ ቆዝሞስ በውዴታው ለምስር ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሹሞ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ስልጣን በታች ሆነ። ይህም አባት መልካም ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሔደ።
ጸሎቱ በረከቱም  ለዘለዓም ከእኛ ጋራ ይኑርደ አሜን!

ምንጭ፡-ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት

ማራናታ: ዳግመ ይመፅዕ በስብሐት

ጥንታዊቷና ብቸኛዋ የክርስቶስ አካሉ የሆነችው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅዳሴዋ ላይ ከምታውጀውና ከምትመሠክረው ምስክርነት አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ነው። “…ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት። ዘተንሥአ እም ሙታን አመ ሣልሥት ዕለት፤ ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፤ ዳግም ይመፅዕ በስብሐት፤ ተሰአለነ እግዚኦ…።” / “ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፣፤ ቅዱስ የማይሞት። በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፤ በምሥጋና ወደ ሰማያት ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በምሥጋና ይመጣል…።” ሠላም ውድ የእግዚአብሔር ምስሌነ ቤተሰቦች! በቤተክርስቲያን ሣምንታዊ ዐምዳችን ከፊታችን የምንቀበለውን የደብረ ዘይት ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ጋር የተያያዙ ዐሳቦችንና ክስተቶችን እንዳስሳለን አብራችሁን ሁኑ። መጽሐፏን አንብቦና መርምሮ በሕይወት፣ በእውነትና በእውቀት ቤተክርስቲያንን የወደዳት ቅዱስ ያሬድ ትምህርቷን ለየወቅቶቹ በደለደለበት ድጓው የጌታችንን ዳግም መምጣት በእኩለ ፆመ እግዚእ እና በወርሐ ጳጉሜ እንዲታሰብ ሥርዓት ሠርቶልናል። በእነዚህ ወቅቶች አብዝተን እንድናስበው አድርጎናል እንጂ ቤተክርስቲያን የጌታ መምጣት ለቅፅበት እንኳን ዘንግታው አታውቅም።  ራሱ ባስተማራት ጸሎት “መንግሥትህ ትምጣ” እያለች የወርቅ ልብስን ተጎናፅፋ በቀኙ የምትቆምበትን ቀን ትናፍቃለች። ዳግመኛም በአዋጇ “ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ፣
ወትንሣኤከ ቅድስት፣
ነአምን ዕርገተከ፣
ወዳግመ ምፅአትከ….።” (“ጌታችን ሆይ ሞትህንና ቅድስት የምትሆን ትንሳሣህን እንናገራለን፤ ዕርገትህንና ዳግም መምጣትህንም እናምናለን” በጸሎተ ሃይማኖቷ ላይም  “…. ዳግመኛም በምሥጋና ይመለሳል፣ በህያዋንና በሙታን ለመፍረድ…… የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን….” በማለት ነገረ ምፅዐቱ በፍቅር የምትጠብቀው እምነቷና ተስፋዋ መሆኑን ታነሳለች። በእርግጥ የክርስቶስ ዳግም መምጣት ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ተጠባቂ ነገር ነው። ምንም እንኳን ይመጣል የሚሉበት ሁኔታና ምክንያት ቢለያይም በዓለም ላይ ያሉ ከሦስት ቢሊዮን በላይ የሆኑ የክርስትና፣ የእስልምና፣ የይኾዋ ምስክሮችና ልዩ ልዩ እምነቶች የክርስቶስን ዳግም መምጣት ይጠባበቃሉ። ይህንን መሠረት በማድረግ በርካቶች በተቀነባበሩ ሤራዎችና ሀሰተኛ ትንቢቶች ክርስቶስ በዚህ ቀን ይመጣል ሲሉ ተደምጠዋል። የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ግምቶችና ሃሳዊ ትንቢቶች መነገር የጀመሩት ክርስቶስ ካረገ ፵ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ነበር። በ፸ ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም መጥፋት ጋር ተያይዞ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት መድረሱን ያወጁ ብዙዎች ነበሩ። በ፭፻ ዓ.ም. በተመሳሳይ ክርስቶስ እንደሚመጣ ያስተማሩ ነበሩ። የፍሎሪው (የጣልያን) እያቄም የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በ፲፪፻፷፰ ዓ.ም. እንደሚከናወን ሲተነብይ ጆን ዴ ሪኩታሊድ እስከ ፲፫፻፸ ዓ.ም. ጌታ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። ኢማኑኤል ስዊዲንበርግ የተሰኘው ሀሰተኛ ነብይ ኢየሱስ በ፲፯፻፶፯ እንደሚመጣ የተነበየ ሲሆን ይህ ትንቢቱ ሲከሽፍበት ጊዜውን አሻሽሎ በ፲፯፻፸ ዓ.ም. የክርስቶስን መምጣት “በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ይመጣል” ሲል አሻሽሎታል ምንም እንኳን ይሄም ቅዥት ቢሆንበትም። የክርስቶስ መምጣት ዙሪያ የተደረጉ ትንቢቶች ብዙ ቢሆኑም የይሖዋ ምስክሮች አስገራሚ ትንቢት ነው። የቤተ እምነቱ መሥራች ቻርለስ ራስል የክርስቶስ መምጣት በ፲፱፻፲፬ ዓ.ም. እንደሚሆን የተናገረ ሲሆን እርሱም እንደቢጤዎቹ ትንቢቱ ሳይሰምርለት ሲቀር ዝም ከመሰኘት ወይም ሌላ ቀን ከመተንበይ ይልቅ የመጨረሻው ቀን ቅዱሳን ወደ ላይ መነጠቃቸውንና የጌታ ምፅዓት መከናወኑን በ “ካፈርሁ አይመልሰኝ” ትምህርቱ ቀጥሎበት ነበር። የአድቬንቲስት፣ የመጨረሻው ቀን ቅዱሳን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሥራቾችም የጌታን መምጫ ቀን ቢተነብዩም ከመንፈስ ቅዱስ ያልሆነው ትንቢታቸው አሳፍሮ መልሷቸዋል። በ፳፻፲፪ በማያ ቀመር መሠረት ክርስቶስ እንደሚመጣና ዓለም እንደምትጠፋ የተሰበከው ስብከት ለበርካቶች እውነት የመሰለ ቢሆንም ለሆሊውድ ፊልም መሥሪያ ከመሆን አልተረፈም ነበር። በዘመናችንም በርካቶች በተለይ በፈረንጆቹ ፳፻፳፭ እና ከእዛ በኋላ “ዓለም ትጠፋለች” ብለው በመስበክ የአማኞቻቸውን ንብረት በማሸጥና በመዝረፍ የከበሩ በርካታ ሃሳውያን መሲሆች ተገኝተዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት “ክርስቶስ ሊመጣ ነው፤ ወደ ተራራ ወጥተን በፆም እንቀበለው” በሚል ስብከት የምእመናኑን ነብስ የቀጠፈውን አፍሪካዊ ፓስተር ጨምሮ። ቤተክርስቲያን ግን “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፣ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” ማቴ ፳፬÷፵፪-፵፬ በማለት የጌታዋን ቃል በማስተማር “በዚህ ቀን ይመጣል፤ በዚህ አይመጣም” በሚል ትምህርት በመደናበር እንዳይስቱና ሁሌም ተዘጋጅተው እንዲኖሩ ታስተምራለች። እኛ ክርስቲያኖች የዳግም ምፅዓት በነቢይ አስቀድሞ  “እግዚአብሔር ገሃደ ይመፅዕ” (“እግዚአብሔር ግልፅ ሆኖ ይመጣል”) ተብሎ እንደተነገረ በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት ለፃድቃን ሊፈርድላቸው ለኃጥአን ሊፈርድባቸው እንዲሁም ይህን ዓለም አሳልፎ የማያልፈውን ዓለም ሊሰጥ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም ይህችን ወደፊት ያለች ቀን በየዓመቱ ሰንበተ እግዚኡ – የጌታ ሰንበት እያልን በዓልን እናከብራለን። ስለዚህ ቀን በዓል በኢትዮጵያ በትግራይና በሰሜን ሸዋ ንግሥ የሚካሄድ ሲሆን በጉራጌ አካባቢዎች የሚገኘው ማኀበረሰብም በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ ፲፱ ላይ ያለውን እራት በማሰብ በደብረ ዘይት ዕለት ድግስ፣  በዚህም ስለክርስቶስ መምጣት ፍስሀ ያደርጋሉ።እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመጣ ጊዜ እንዳያሳፍረን የሕይወት ቃሉን ያሰማን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱን እየተማፀንን ስለነገረ ምፅዓቱ አምልቶ በፃፈው ባለራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ቃል ጽሑፋችንን እንዘጋለን። ማራናታ! አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!

ጉባኤ ኤፌሶን  የጉባኤው ውሳኔ

፩. ተዋሕዶ የሚለው ቃል የተገኘው በዚህ ጉባኤ ነው።

፪. በአማን ድንግል ወላዲተ አምላክ (የእውነት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ እግዚአብሔር መሆንኗን)

የጉባኤ ኤፌሶን ቀኖናዎች
፩.  “በቤተ ክርስቲያናዊም ሆነ በሥጋዊ ምክንያት ከቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነት ያላቸው ሰዎች የጉባኤውን ድንጋጌ ችላ ማለት የለባቸውም (ውሳኔውን ማክበር ይኖርባቸዋል)፡፡ በዚህም ለቅዱስነትዎና ለተወዳጅነትዎ የምናሳውቀው የአንድ ሀገረ ስብከት ርእሰ ኤጲስ ቆጶሳት ለዓለም ዐቀፋዊው ሲኖዶስ ውሳኔ የማይታዘዝ ሆኖ የእምቢተኛነት ጉባኤ ቢሰበስብና ተቃራኒ ውሳኔ ቢያሳልፍ ወይም ከሌሎች ተቃራኒዎች ከሆኑ ውሳኔዎች ጋር ቢስማማ ከአሁን ጀምሮ በጉባኤው ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተባሮ የተለየ በመሆኑ በሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ ምንም ውሳኔ ሊያስተላልፍ አይችልም። ቀጥተኛ አስተያየት ያላቸው የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ከክህነት ደረጃው ያባርሩት ዘንድ ጉባኤው ወክሎአቸዋል፡፡”

፪. የአንዳንድ ሀገረ ስብከቶች ኤጲስ ቆጶሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዘግይተው ወደ እምቢተኛነት ካዘነበሉ ወይም ንስጥሮስ ተወግዞ ከተለየ በኋላ ከመናፍቃን ጋር አንድ ግንባር ለመፍጠር የተስማሙ ከሆነ እንደዚህ ያሉት ሰዎች ከክህነት መዓርጋቸው መሻር አለባቸው ብሎ ጉባኤው ወስኖአል።
፫. ከአስተሳሰባቸው ቀናነት የተነሣ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በንስጥሮስ ወይም በተከታዮቹ አማካኝነት ከክህነታቸው የተሻሩ ከሆኑ ጉባኤው በክህነት ደረጃቸው እንዲቀጥሉ ፈርዶላቸዋል። ዓለም ዐቀፋዊና ኦርቶዶክሳዊ በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ የእምነት ቀኖና ጸንተው ለሚገኙ ካህናት ሁሉ የምናስተላልፈው ትእዛዝ በውግዘት ለተለዩት ኤጲስ ቆጶሳት እንዳይታዘዙ ነው።

፬. ከካህናት መካከል እምቢተኞች ሆነው የንስጥሮስንና የካላስትዮስን የክሕደት ትምህርት በመቀበል ሕዝብም ያንን የክሕደት ትምህርት እንዲቀበል የሚያደርጉ ቢኖሩ ትክክለኛ በሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ፍርድ እንደተለዩ ይቆጠራሉ።
፭. የክህነት ተግባሮችን እንዳያከናውኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ወይም በኤጲስቆጶሳት ለተከለከሉ ሰዎች ንስጥሮስና ተከታዮቹ በግዴለሽነት በክህነት ደረጃ ኅብረት እንዲኖሩ ቢያደርጉአቸው እነዚህን ሰዎች በውግዘት እንዲኖሩ ፈርደንባቸዋል።
፮. በኤፌሶን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ ከመዘገበው ውሳኔ ተቃራኒ የሆነ ድርጊትን ለማድረግ የሚፈልጉ ቢኖሩ ኤጲስ ቆጶሳት ወይም ቀሳውስት ከሆነ ከክህነት መዓርጋቸው ይሻሩ፤ ተራ ምዕመን ቢሆን ግን ይለይ፡፡
፯. የሃይማኖትን ቀኖና በሚመለከት፣ ማንም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በኒቅያ የተሰበሰቡት ቅዱሳን አባቶች ከወሰኑት እምነት የተለየ ትምህርት መከታተል፣ መጻፍና መድረስ አይገባውም። ወደ አረማዊነት፣ ወደ አይሁዳዊነት፤ ወይም ወደ ሌላ የመናፍቃን ትምህርት ለመመለስ ለሚፈልጉ ሰዎች የእነዚያን እምነት ለማሳወቅ በድፍረት ድርሰት የሚያዘጋጁ ካሉ ኤጲስ ቆጶሳት ቢሆኑ ከኤጲስ ቆጶስነት መዓርጋቸው ካህናት ቢሆኑ ከክህነታቸው ይሻሩ። ምእመናን ቢሆኑ ከኅብረቱ ይለዩ፡፡ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ካህናት ወይም ሌሎች ምእመናን ስለ እግዚእብሔር ወልድ ሥጋ መልበስ የንስጥሮስን ትምህርት በመመርኰዝ ቄስ ካሪሲዩስ ያዘጋጀውን የክሕደት ትምህርት የተቀበሉ ወይም ያስተማሩ በዚህ ዓለም-ዐቀፋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍርድ ኤጲስ ቆጶስ ቢሆን ከሹመቱ ተሽሮ በውግዘት ይለይ፤ ካህን ሲሆን ከክህነት ደረጃው ይሻር ተራ ምእመን ቢሆን ከኅብረቱ ይለይ።
፱. በኤጲስ ቆጶስነት ተባባሪአችንና የእግዚአብሔር ወዳጅ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ አርጌኖስ፣ እንዲሁም አብረውት የመጡት የእግዚአብሔር ወዳጆች ዘይኑንና ኢዩዋግሩስ ከቤተ ክርስቲያን ደንብና ከቅዱሳን ሐዋርያት ቀኖና የተለየ ድርጊት መፈጸሙን ነግረውናል። የአጠቃላዩ ችግር የበለጠ ጉዳት እንዳያመጣ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሲሆን ከቆጵሮስ የመጡት ሁላቸውም በቃልና በጽሑፍ እንደገለጹት የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ ከአሁን በፊት በቆጵሮስ ጉዳይ ገብቶ የማያውቅ ከሆነ በንጹሓን አባቶች ቀኖና እና ቀድሞ በነበረው ልማድ መሠረት በቅድስት የቆጵሮስ ቤተክርስቲያንና በኃላፊዎችዋ ላይ ምንም ግራ መጋባትና ቅሚያ እንዳይደረግ፣ እነርሱም ኤጲስ ቆጶሳትንና መሪዎቻቸውን ሁሉ በራሳቸው ይሠይሙ ። ይህም ጉዳይ በሌሎች ሀገረ ስብከቶች ሁሉ ይጠበቅ፡፡ ማንኛውም የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ኤጲስ ቆጶስ የእርሱ ተከታይ ባልነበረ ወይም እርሱ በተካው ኤጲስ ቆጶስ ሥር ያልነበረውን ሀገረ ስብከት በሥሩ ለማድረግ መሞከር የለበትም፡፡ የሌላውን ሀገረ ስብከት በድፍረት በቅሚያ መልክ በሥልጣኑ ሥር ያደረገ ካለ ያባቶችን ቀኖና ላለመቃወም ይመልስ፡፡ ማንኛውም ሀገረ ስብከት የተቀማውና ከቀድሞ ጀምሮ የነበረው መብቱ ይመለስለት ዘንድ ዓለም-ዐቀፋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

ምንጭ፡- የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ (አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ)

ቅዱስ ኩትን ሐዋርያ

በሶርያ አገር ስሟ በንጣንዮስ ከምትባል ቦታ የሚኖር ነበር፤ አባቶቹም ከዋክብትን ያመልኩ ነበር። የአባቱ ስም ንስጣር የእናቱም ስም ቴዎድራ ይባላል። በአደገ ጊዜም ወላጆቹ ሊአጋቡት ፈለጉደ፤ እርሱ ግን አልወደደም። ግድ ብለው ያለውዴታው ሚስትን አጋቡት። ሊገናኛትም አልፈለገም ስለ ሥጋ ድካም ወይም ስለ ጽድቅ ሳይሆን የሥጋ ፍትወትን ስለሚጠላት ነው እንጂ። ደናግልም እንደሆኑ ሁለቱ ሁሉ ከሚስቱ ጋራ በአንድነት ኖረ። “አምላክ ሆይ ወደ ዕውቀትህ” ምራኝ በማለት ጸሎትና ምልጃን ያዘወትር ነበር። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ለቆርኔሌዎስ እንደተገለጠ ተገልጦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን አስተማረው ከሐዋርያትም ወደ አንዱ ሔዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቅ አዘዘው።
የሐዋርያት የስብከታቸው ወራት ነበረና ሒዶ ተጠመቀ። የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሁሉ ሕጉን ሥርዓቱንም ሁሉ ተማረ፤ መለኮታዊ ምሥጢርንም ተቀበለ። በየቀኑ ሁሉ የሐዋርያ ጳውሎስን ትምህርት ይሰማ ነበር። የጽድቅን ሥራ መሥራትና ንጽሕና ለበጎ ሥራ መጠመድ፣ ትጋት፣ ቅንነት፣ የዋህነት፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ሰጊድ በላዩ ተጨመረ። በእነዚህ ሁሉ የሚተጋ ሆነ። እግዚአብሔርም አስደናቂ ተአምራትን እንዲያደርግ በርኲሳን አጋንንት ላይ ሥልጣንን ሰጠው። በሚያደርጋቸው ተአምራትም ወላጆቹን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደማመን ስቦ አስገባቸው፤ ደግሞ ሚስቱንና ወላጆቿን አስገባቸው። ከከሀድያን አንዱ ለሰይጣን ሊሠዋ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ቅዱስ ኩትን አውቆ በሰይጣን ላይ ጮኸ። እርሱ ሰይጣን እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሰው ፊት ያምን ዘንድ አዘዘው። ሰይጣንም እንዳዘዘው ራሱን ገለጠ በዚያ የነበሩ ሁሉም “የቅዱስ ኩትን አምላክ አንድ እርሱ ብቻ ነው” እያሉ ጮኹ፤ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ። ከዚህ በኋላ ከቀላውዴዎስ ቄሣር የተላከ መኰንን የቅዱስ ኩትንን ዜናውን በሰማ ጊዜ ወታደር ልኮ አስቀረበው። ስለ ሥራውም ጠየቀው፤ እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። መኰንኑም ጽኑ ግርፋት ገርፈው፤ እንዲአሥሩት አዘዘ፤ ይህንንም አደረጉበት። የሀገሩ ሰዎችም ቅዱስ ኩትንን አሠቃይተው እንዳሠሩት በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደርሱ ተራወጡ። መኰንኑንም ሊገሉት ወደዱ፤ መኰንኑም ሸሸ። ቅዱስ ኩትንንም ከማሠሪያው ፈትተው ከደሙም አጥበው ተሸክመው ወደቤቱ ወሰዱት። ከዚያም በኋላ ብዙ ዘመናት ኑሮ የወደደውን እግዚአብሔርን አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት አረፈ። ከዕረፍቱም በኋላ ቤቱን ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሥጋውን በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከሥጋው ብዙዎች ታላላቅ ተአምራትን አሳየ።
ጸሎቱ በረከቱም  ለዘላለም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን ምንጭ፡-ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት

የበረከት ዳናዎች – መንፈሳዊ ጉዞዎች እንዴትና ለምን

ታላቁ የበረከት ጾም፣ ጾመ እግዚእ ሦስተኛ ሳምንቱን ጨርሶ ወደ አራተኛው ሳምንት እየተንደረደረ ይገኛል፡፡ በዚህ በዓቢይ ጾም በምእመናን ዘንድ ከሚስተዋሉ መንፈሳዊ ተግባራት አንዱ ደግሞ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ዓቢይ ጾም ደረስኩ ከማለቱ የአድባራትና ገዳማት ግድግዳዎች በመንፈሳዊ ጉዞ ማስታወቂያዎች ይመላሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዙሪያ አድባራና ገዳማት እስከ ግብጽና ኢየሩሳሌም ድረስ መዳረሻቸውን ያደረጉ ማኅበራትና ሰንበት ት/ቤቶች ምእመናንን በልዩ ልዩ መንገድ ይጣራሉ፡፡ በተለይ በጾሙ ወቅት ላይ የሚያርፈው የመጋቢት ፭ቱ የቅዱስ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ በዓልና በጾሙ እኩሌታ የሚከበረው የእግዚአ ለሰንበት በዓላት በርካታ ምእመንን ወደ ምድረ ከብድ፣ ዝቋላና ሳማ ሰንበት ያነጉዳል፡፡ እኛም ይህንን አስታከን በዛሬው ቤተክርስቲን ሳምንታዊ መሰናዶ ስለ መንፈሳዊ ጉዞዎች ማንሳት ወደናል፡፡

መንፈሳዊ ጉዞዎች ስማቸው እንደሚያመለክተው ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲባል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የሚደረግ ጉዞን ይወክላል፡፡ ጉዞው በተጓዦቹ ፈቃድ የሚደረግ በመሆኑ ከስደትና ግዞት የሚለይ ሲሆን ዓላማው መንፈሳዊ በረከትና ትምህርት መሆኑ ደግሞ ለተዝናኖትና ለዘገባ ከሚደረጉ ጉብኝቶች ይነጠላል፡፡ ይህ ትርጓሜ ቅዱሳን ገዳማትን ለመሳለም ምእመናን የሚያካሂዱትን ጉዞ እንዲሁም አገልጋዮች የሚጓዙትን ሐዋርያዊ ጉዞዎች ያካትታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ መንፈሳዊ የጉዞ ታሪኮች ሲገኙ በተለይም እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ እንዲሁም ወደ ተለያዩ ሀገራት የተበተኑ እስራኤላውያን ለአይሁድ ፋሲካ፣ ለዳስ በዓልና ለበዓለ ኃምሳ የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያውያኑ የንግሥተ ሳባና የህንደኬ ጃንደረባ የቅዱስ ባኮስ ጉዞም ከመንፈሳዊ ጉዞዎች መካከል የሚካተት ነው፡፡
በዘመነ ሐዲስ ኪዳን የሐዋርያቱ አገልግሎት በውስን አካባቢ በመሆኑ እንዲሁም ቀጥሎ የነበረው ዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች በግድ የሚሰደዱበት እንጂ እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት፣ በአካል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ባለመሆኑ በጉልህ ጉዞዎች ባይገኝም ወደ መንፈሳዊ ቦታዎች የሚካሄድ ጉዞ የክርስቲያን ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ ይጠቀስ ነበር፡፡

መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዲሁም ሐዋርያነ አበው በትምህርቶቻቸው ላይ ክርስትና ወደ ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ አድርገው ማስተማራቸው መንፈሳዊ ጉዞን ከብሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ በአካላዊ ቦታዎች ብቻ ያልተገደበ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በዕለት ተዕለት ሥርዓተ አምልኮዋ ምእመናንን ከቤተልሔም ወደ ማዕከለ ቀራንዮ በመውሰድ ዳግመኛም “አልዕሉ አልባቢክሙ /ልቦናችሁን ከፍ ክፍ አድረጉ” እያለች በሰማያዊው ምሥጢር በኩል ወደ ሠማያዊው ሥርዓት እንዲገቡ ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡

በቀደመቺው ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጉዞዎች የሚካሄዱት ጌታችን በነበረባቸው የቤተልሔም፣ ኢየሩሳሌም፣ ቀራንዮና መሰል አካባቢዎች ላይ ነበር፡፡ በ፪ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ያሉ እንደ ኦሪገን ያሉ ሊቃውንት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዙ ታሪክ ይዘግባል፡፡ በ፬ኛው ክፍለዘመን ክርስትና በተጎናጸፈው ነጻነትና ከፍታ ምክንያት በተለይም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስና በእናቱ ቅድስት እሌኒ አማካኝነት እየሩሳሌም በመታደሷና አብያተ ክርስቲያናት በመታነጻቸው መንፈሳዊ ገዞ ከቀድሞ በተሻለ መጠን ተበራክቷል፡፡

እንደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀጳጳስ ቄርሎስ፣ እንደ ቅዱስ ጀሮም እንደእነ ቅድስት ሜላኒያ ያሉ ታላላቅ ቅዱሳንም በዚህ ወቅት ወደ ኢየሩሳሌም ማቅናት ችለዋል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ያለውን መንገድ የሚያሳየው ለዘመናችን ከደረሱ ጥንታዊና ወደ ኢየሩሳሌም የሚያቀና ፍኖትን የሚያሳይ ካርታ ቦርዲክስ በወቅቱ ዜና ሰማዕታት በብዛት ይነገር ስለነበር የሰማዕታቱን በረከት ለመካፈል በሮም ወደሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች ማለትም ወደ እስክንድሪያ፣ የአሁኗ ጣልያን፣ ቅርጥግና (ቱኒዚያ)፣ ሶሪያና የመሳሰሉት ይጓዙ ነበር፡፡ በዚሁ በ፬ኛው ክፍለ ዘመን በበረሃው ከዋክብት ቅዱስ እንጦስና ቅዱስ ጳውሎስ (አባ ጳውሊ) አማካኝነት የተስፋፋው ምንኩስናም ቢሆን ለመንፈሳዊ ጉዞ የራሱን አሻራ አሳልፏል፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩ በርካታ ቅዱሳን አባቶችና ክርስቲያኖች በግብጽ ምድር አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌምና ግብጽ ይጓዙ የነበረ ሲሆን በፖለቲካ ችግር ወደ ግብጽ መሄድ በማይቻልባቸው ወቅቶች በሃገር ውስጥ በረከቱ ሳይቀርባቸው እንዲሳተፉ ለማድረግ ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ አምሳለ ኢየሩሳሌምን በሮሃ መገንባቱ ይታወቃል፡፡ በአሁን ወቅት ርእሰ አድባራት አክሱም ጽዮን ማርያምን፣ ቅዱስ ላሊበላን፣ ግሸን ማርያምን፣ ደብረ ሊባኖስንና የመሳሰሉትን በመጎብኘት በረከትን ለመካፈል ከቅዱሳኑ ረድኤት ለማግኘት፣ ያሳለፉትን መንገድ አብሮ ለመጓዝ በርካታ ምእመናን ወደ ቦታው ይጓዛሉ፡፡

ምንም እንኳን መንፈሳዊ ጉዞዎች ለብዙዎች በረከትና ሕይወት ቢሆኑም ከጉዞ አዘጋጆች የዕውቀት እጥረት፣ ግዴለሽነትና ከተጓዦች የመንፈሳዊ ጉዞ ዓላማን መዘንጋት አንፃር በርካታ ስህተቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላሉ። ወደ ገዳማት በሚደረጉ ጉዞዎች መናንያኑን ከማወክ፣ ያልተፈቀደ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጀምሮ በመንፈሳዊ ጉዞ ስም ስካር፣ የአልኮል መጠጦች ሸመታ፣ ልዩ ልዩ ግብይቶችን መፈፀምና መንፈሳዊ ባልሆነ ሁኔታና ቦታ ማደርና የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈፀሙ ይስተዋላል።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለመንፈሳዊ ጉዞዎች ባነሳበት ድርሳኑ “ልብህ ሳይዘጋጅ ወደ ጎልጎታም ሆነ ወደ ደብረ ዘይት ብትወጣ ክርስቶስን አታገኘውም። ነገር ግን ልብህን ብታዘጋጅ ግን በቀጰዶቅያም ሆነህ ክርስቶስን ልታገኘው ትችላለህ” ብሎ እንደሚነገር በቅዱሳን ገዳማትና ቦታዎች የሚካሄዱ ጉዞዎች አስቀድሞ በጎ ፈቃድና መንፈሳዊ ዝግጅት ከሌለባቸው ከቱሪስት ጉብኝት የሚለዩና በረከት የሚያስገኙ አይሆኑም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውጪ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ግላዊ ትርፍ ለማካበትና ምእመናንን ለመቀሰጥ መንፈሳዊ ጉዞዎችን እያዘጋጁ መሆኑ የጉዞዎቹ ሌላ ችግር እየሆነ ይገኛል። በመሆኑም ምእመናን ወደ መንፈሳዊ ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት ስለጉዞ አዘጋጁ ማንነትና ምንነት፣ ጉዞው ስለሚያካትታቸው ተግባራትና በሚሄዱበት ገዳማትና መካናት ያሉ መመሪያዎችን ማወቅ ይገባል። ከምንም በላይ ግን ጉዞውን የሚሄዱት ከቅዱሱ መካን ለመባረክ በመሆኑ በዙሪያቸው ባሉ ሌሎች ተጓዦች በጎ ያልሆኑ ልማዶች እንዳይሰናከሉ ሊጠበቁ ይገባል።

በጾሙ ውስጥ ወደ ቅዱሳን መካናት ለምትጓዙ ሁሉ ሰናይ ጉዞን እየተመኘን ጽሑፋችንን ከመቋጨታችን በፊት በጾሙ ወራት ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከሀገር ውስጥ ወደ ሳማ እግዚኡ ለሰንበት (ሳማ ሰንበት)ና ከሀገር ውጭ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ጉዞዎች እንዲሁም በ፱ኛው ዙር ፍኖተ ሕይወት ወደ መቄዶንያ ለመጓዝ መጋቢት 28 ማቀዱንም ለመጠቆም ወደድን።

ጾሙን በመንፈሳዊ ተግባራት በርትተን ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ለጀመርነው ጉዞ የመንገድ ስንቅ የምንሰንቅበት ያድርግልን። መልካም ጾም! መልካም ጉዞ!

ጉባኤ ኤፌሶን (፬፻፴፩ ዓ.ም.)

ከተቆረቆረች ጀምሮ የሃይማኖት ጭቅጭቅ ተለይቷት የማታውቀው ቁስጥንጥንያ በሊቀ ጳጳሷ በንስጥሮስ ክህደት የተነሣ ሌላ ችግር ውስጥ ገባች፡፡ ንስጥሮስ ኤፍኘሬፕዮስ በሚባል የግሪክ ገዳም ይኖር የነበረ:: ትምህርቱን በአንጾኪ.ያ ትምህርት ቤት ከጠርሴስ ሊቀ ጳጳስ ከዲያድርስ የተማረ ነበር። የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርቱም እንደ መምህሩ የነበረ ሲሆን ጌታን ወልደ ዳዊት፣ ወልደ እግዚአብሔር ብሉ ያምን ነበር። “ወልደ እግዚአብሔር በወልደ ዳዊት አደረ እንጂ አልተዋሀደም” ብሎ የኑፋቄ ትምህርቱን ማስተማር ጀመረ። እመቤታችንንም “የወለደችው ሰው እንጂ አምላክ አይደለም” ብሎ በአደባባይ ያስተምር ነበር፡፡ንስጥሮስ የዲያድርስን እምነትና የክህደት ትምህርት ማለትም፤ በምስጢረ ሥጋዌ ክርስቶስን በሁለት ከፍሎ አንዱን ወልደ ዳዊት ሁለተኛውን ወልደ እግዚአብሔር ነው ብሎ ያምንና ያስተምር ነበር፡፡ በእርሱ አባባል ከማርያም የተወለደው የዳዊት ልጅ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ነው ብሏል ፡፡
ንስጥሮስ በአንጾኪያ የተማረውን የሁለት ባሕሪይ ትምህርት የገለጠው በቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ የቤተክርስትያን ታሪክ እንደሚያስረዳው ፬፻፳፭ – ፬፻፳፯ ዓ.ም የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ሱስንዮስ ቀዳማዊ ሲሞት በ፬፻፳፰ ዓ.ም ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ኤጲስ ቆጶስ ተባለ፡፡ ንስጥሮስ የኅድረት ትምህርትን ለማስፋፋት አማኝ መስሎ የታየው ይህ ሥልጣን ጊዜው ነበር፡፡ማርያም የወለደችው ዕሩቅ ብእሲ ነው፡፡ወላዲተ አምላክ ሰብእ ናት እንጂ ወላዲተ አምላክ አትባልም ብሎ ማስተማረ ጀመረ፡፡
ይህንን ክህደት በመጀመሪያ የተቃወመችው የእስክንድርያ ቤተክርስትያን ነበረች በዛን ጊዜ የነበረው የእስክንድርያ ፓትሪያሪክ ቅዱስ ቄርሎስ ነበር:: ቅዱስ ቄርሎስም ቃል በማይመረመር መግቦቱ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ ከኃጢዓት በቀር ሰው የሚሰራውን ሁሉ ሠራ ፡፡ ሰው ስለኾነ ሥጋ ስለለበሰ የሰራውን ሁሉ ለይቶ ከፍሎ ግማሹን ለመለኮት ግማሹን ለትስብእት ሰጥቶ መናገር ጠቅላላው የምስጢረ ሥጋዌን ጠባይ ይለውጠዋል፡፡ሰው ሆነ ሥጋ ለበሰ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ ኾነ ፍጹም ሰው መሆኑን የምናውቀው ሰብአዊውን ሁሉ የራሱ በማድረጉ ነው፡፡ ተዋሐደን ካልተቀበልን ሁለት ልጆች ከማለት አዘቅት ውስጥ እንገባለን:: ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ የምትባልበትን ምክንያት ሲያስረዳ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ የምንላት ቃል ከዊነ ቃልነቱን ከእሷ ያገኘው ነው ወይም የወልድ አካል የተገኘው ከእሷነው፡፡ በመግቦት ምስጢሩ ሰውን ለማዳን ከእሷ በሥጋ ተወለደ፡፡ ይህንኑ ትምህርት በመደጋገም ሲያስረዳ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ናት ብሎ የማይቀበል ማርያም የወለደችው ዕሩቅ ብእሲ የሚል ሥጋዌ ያልገባው ነው ብሎ አስተምሯል፡፡
የኤፌሶን ጉባኤ የተካሄደው በ፬፻፴፩ ዓ.ም. ሰኔ ፯ ሲሆን የተሰባሰቡት አበው ብዛት ፪፻ ነው፡፡ የስብሰባው ዋና ዓላማም ንስጥሮስን ከክህደት ለመመለስ ሲሆን የጉባኤው አፈ ጉባኤ ቅዱስ ቄርሎስ ነበር።
በዚህ ጉባኤ የተነሱት ዋናዋና ጉዳቶች:
፩. ጉባኤው እንዲደረግ ምክንያት የሆነው የንስጥሮስ የክህደት ትምህርት፣
፪. የቅዱስ ቄርሎስ የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርትና በንስጥሮስ ክህደት ላይ ያደረገው ዘመቻ፣
፫. የኤፌሶን ጉባኤ መሰብሰብና ያስተላለፈው ውሳኔ ናቸው፡፡
የኤፌሶን ጉባኤ ሦስተኛው የዓለም አብያተ ክርስትያን ሲኖዶስ ነው፡፡ እነዚህም ‹‹ኅድረት›› የሚለውን ከላይ የድያድርስን ከታች የንስጥሮስን ትምህርት አውግዘው‹‹ተዋሐደ›› የሚለውን ትምህርት ተስማምተው ተመልሰዋል፡፡ ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም የነበረው በሥጋ ስለወለደችው በአማን ወላዲተ አምላክ ናት ብለው የሐዋርያትን ትምህርት በውሳኔያቸው አጽድቀዋል፡፡
ምንጭ፡- የቤተክርሰትያን ታሪክ በዓለም መድረክ

አባ መከራዊ

ይህ አባት በግብጽ ደቡብ ከምትገኝ ከእስሙናይን ከታላላቆቿ ወገን ነው። ለኒቅዮስ ከተማም ኤጲስቆጶስነት ተሾመ።
የስደትና የመከራ ወራት በሆነ ጊዜም ስሙ ዮፋንስ የሚባል መኰንን ወደዚያች አገር ከንጉሥ ተልኮ መጣ። የክርስቲያን ወገኖችንም ያሠቃይ ዘንድ ጀመረ። የዚህንም የቅዱስ ኤጲስቆጶስ አባ መከራዊን ዜና ሰምቶ ወደርሱ ያመጡት ዘንድ ወታደሮቹን ላከ። እርሱም ወደ መኰንኑ ከመሔዱ በፊት ወደ ቅዱስ መሠዊያው ገባ፤ እጆቹንም ዘርግቶ ጸለየ። ንዋየ ቅዱሳቱንና የመቀደሻውን ልብሶች በመቅደሱ ውስጥ አኖረ።
ከዚያም በኋላ ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ ማለደ። በላያችሁ የፀሐይ ብርሃን ይወጣ ዘንድ ያልተዋችሁ የጽዮን ልጅ ደጆች ሆይ “ለእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆነ ነዋየ ቅድሳቱን ጠብቁ” እያለ ታላቅ ልቅሶ በማልቀስ ጮኸ። ከዚህም በኋላ ከንጉሥ መልክተኞች ጋራ ወጥቶ ሔደ፤ ወደ መኰንኑም ቀረበ። ስለ ስሙና ስለ አገሩ ስም፣ ስለ ሥራውም ጠየቀው። የኒቅዮስ ከተማ ኤጲስቆጶስ እንደሆነም ባወቀ ጊዜ እንዲገርፉትና እንዲያጐሳቁሉት ብርና እርሳስም አቅልጠው በአፉ እንዲጨምሩ አዘዘ።
እግዚአብሔርም የሚያጸናውና የሚያስታግሠው ሆነ። ያለ ጉዳትም በጤንነት መልሶ ያነሣው ነበር። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ገዥ ወደ ኄርሜኔዎስ ሰደደው። እርሱም ቅዱስ አባ መከራዊን እንዲአሥሩት አዘዘ። እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራትን አደረገ። ከተአምራቱም አንዱ ለአቅፋስ ከተማ ሹም ለሆነ ለዮልዮስ ስሙ አውካሪስጦስ የሚባል እጆቹና እግሮቹ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። አባ መከራዊም በላዩ ጸለየ፤ ከደዌውም አዳነው። ከዚህ በኋላ በዮልዮስ ቤት ቀድሶ ለአማንያን ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ስለ ሥጋውም እንዲዐስብና ገድሉንም እንዲጽፍለት ከዮልዮስ ጋራ ስምምነት አደረገ። መኰንኑ ኄርሜኔዎስም አባ መከራዊ ስለ አደረጋቸው አስደናቂ ተአምራት በሰማ ጊዜ በተለያየ ሥቃይ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ።
ሕዋሳቱ እስኪቆራረጡ በመንኰራኵሮች ውስጥ አስገብተው አሠቃዩት። ለነጣቂዎች አንበሶችም ጣሉት፣ በባሕርም አሠጠሙት፣ በእሳት ምድጃ ውሰጥም ጨመሩት። ቅዱስ አባ መከራዊ በሥቃዩ ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የሚታገሥና የሚጸና ሆነ። ጌታም ያለ ጉዳት መልሶ በጤንነት ያስነሣው ነበር። የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ቤተ ክርስቲያን የምታገለግል አንዲት ድንግል እኅትም ነበረችው። ሁለት ወንድሞችም ነበሩት፤ የአንደኛው ስም ዮሐንስ የሁለተኛውም ይስሐቅ ይባላል። በእሥር ቤትም ሳለ ወደርሱ መጡ። “አንተ ስለ አባታችን ፈንታ አባት ሆነኽን ነበር፤ እነሆ የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ ትተኸን ትሔዳለህ” እያሉ በፊቱ አለቀሱ። እርሱም አጽናንቶ ወደ ቤቶቻቸው አሰናበታቸው። ዮልዮስም “የዚህን ሽማግሌ ሞት በጽሑፍ እዘዝ ከእርሱም ታርፋለህ” ብሎ መኰንኑን መከረው። ቃሉንም ተቀብሎ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ። ዮልዮስም የቅዱስ አባ መከራዊን ሥጋ ወስዶ በከበሩ በወርቅ ልብሶች ገነዘው፣ በደረቱም ላይ የወርቅ መስቀል አደረገ፣ ወደ ሀገሩ ወደ ኒቅዮስም ከአገልጋዮቹ ጋራ ሰደደው። መልካም ነፋስም ሆኖላቸው፤ መርከቢቱ ፈጥና ሔደች። በከተማውም በር አንጻር ደርሳ ቆመች። ቀዛፊዎችም ሊያንቀሳቅሱዋት ፈልገው ነበር ግን አልተቻላቸውም። አብዝተው በደከሙም ጊዜ ሥጋዬ በውስጡ እንዲኖር እግዚአብሔር የፈቀደው ቦታ ይህ ነው የሚል ቃል ከበድኑ ወጣ። ይህንንም ለሀገር ሰዎች ነገሩአቸው፤ የሰሌን ዝንጣፊም እየያዙ ወደርሱ መጡ። በሀገራቸውም ውስጥ እርሱ በመረጣት ቦታ እስከ አኖሩት ድረስ በታላቅ ክብር ተሸክመው ወሰዱት። መላው የሕይወቱ ዘመን አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ሆነ። መጻሕፍትን እስከተማረ ድረስ ስምንት ዓመት፣ በዲቁና ሹመት ሃያ አራት ዓመት፣ ከዚያም ቅስና ተሹሞ በቅስና አገልገሎት ሠላሳ ዓመት ኖረ። ከዚያም በኋላ ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሾመ። በዚህም ስልሳ ዘጠኝ ዓመት ኖሮ መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ። የሕይወት አክሊልንም ከክብር ባለቤት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተቀበለ። 
ጸሎቱ፣ በረከቱም  ለዘለዓለም ከእኛ ጋራ ይኑር። አሜን!ምንጭ፡- ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት

መከራ የፈተነው ሐዋርያዊ ተልዕኮ

ወርኀ የካቲት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱሳን ፓትርያሪኮች አገልግሎት ላይ ልዩ ትዝታን ከሰነዱ ወሮች መካከል አንዱ ነው። በያዝነው ወር በ፳፬ኛው ቀን ከተከበረው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመትና በማግስቱ ታስቦ ከዋለው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቀርዮስ ዜና-ዕረፍተ ተጨማሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ደርግ በግፍ ከመንበራቸው የተነሱትም በዚህ የየካቲት ወር ፱ኛው ቀን ላይ ነበር። ይህ ዕለት አቡነ ቴዎፍሎስን ከመንበረ ፕትርክና ከማውረዱ በተጨማሪ የያኔው ጳጳስና በኋላም ፭ኛው ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከሌሎች ጳጳሳት ጋር ለእስር የተዳረጉበት ነው። በዛሬው ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ ከእነዚህ ሁሉ የየካቲት መዋዕሎች መካከል በዕለተ ሰኞ የተከበረውን ፲፪ኛ ዓመት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን የ፲፪ ዓመታት ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዳስሳለን። በዓለ ሲመት ክህነታዊት በሆነችው ቤተክርስቲያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቀን ነው። ለልጆቿ መንፈሳዊ አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የተጠበቀውን የእረኝነት አገልግሎት የሚያስቀጥሉ አበውን የምታገኝበት ስለሆነ ቤተክርስቲያን በዓሉን በልዩ ሁኔታ ታከብረዋለች። የሚሾሙበት ዕለትም በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን እንዲሆን በፍትህ መንፈሳዊ መደንገጓ በዓለ ሲመት ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ያሳያል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚያመላክተው ረጅሙን ዘመኗን በግብፅ ቤተክርስቲያን ሥር እንደሚገኝ አኅጉረ ስብከት ከእስክንድርያ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት ስትተደዳር ቆይታለች። ኢትዮጵያዊያን አባቶችና ነገሥታት ቋንቋና ባህላቸው የሚገባቸው ኢትዮጵያዊ ሊቃነ ጳጳሳትን ለማሾም ብዙ ደክመዋል። ከዘመነ ዛጉዌ ጀምሮ ከግብፅ መንግሥትና እስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር የተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ፍሬ አፍርቶ በ፲፱፻፵ ዓ.ም. የራሷ ተወላጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በ፲፱፻፶፩ዓ.ም. ደግሞ የራሷን መንበረ ፓትርያርክ ለመመሥረት ችላለች። እንግዲህ ዛሬ ዜና መዋዕላቸውን የምናነሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከቅዱሳን ፓትርያርኮች አቡነ ባስልዮስ፣ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ መርቆርዮስና አቡነ ጳውሎስ ቀጥሎ ፮ኛው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የመንበረ ማርቆስ ወራሴ፣ የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃኗ የአክሱም ሊቀጳጳስና በተክለሃይማኖት መንበር ዕጨጌ ናቸው። በ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. በትግራይ አጋመ አውራጃ የተወለዱት የቀድሞው ተክለ ማርያም አሥራት ከወቅቱ የአስመራው ሊቀጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ድቁናን ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ደግሞ የቁምስና ማዕረግ ተቀብለዋል።
ቅዱስነታቸው ለአገልግሎትና ትምህርት ወደ የተለያዩ አድባራትና ገዳማት የተዘዋወሩ ሲሆን በአዲስ አበባ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አቡነ ቀሲስና ምክትል ፀሐፊ በመሆን አገልግለዋል። ተኻራሚውና መናኒው ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት በጥር ፱፫ በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም. ባካሄዱት ሲመተ ጵጵስና መምህር ተክለ ማርያም አሥራትን ብፁዕ አቡነ ማትያስ ብለው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ አድርገው ሾመዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በኢየሩሳሌም፣ በሰሜን አሜሪካ በተለይም በዩናይትድ ስቴት ከፍተኛ አባታዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በተለይም በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. የተከሰተው የሲኖዶስ መከፈል በምዕመናንና በአገልጋዮች ዘንድ ሥር እንዳይሰድ የማቀራረብ ሚናን ይጫወቱ ስለነበር ከሁለቱም ሲኖዶስ ውጪ እንዳሉ ገለልተኛ ሊቀጳጳስ ተብለው እስከመቆጠር ደርሰው ነበር። በ፳፱፬ ዓ.ም. ነሐሴ የተሰማውን የ፭ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ዜና ዕረፍት ተከትሎ በተካሄደ ምርጫ ፮ኛ ሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መንበረ ፕትርክና የተረከቡት አቡነ ማትያስ ላለፉት ፲፪ ዓመታት የመንጋው እረኛ በመሆን አገልግለዋል። የቅዱስ ፓትርያርኩ ዘመነ ፕትርክና በመከራ የተፈተነ ነበር። ገና በተሾሙ ቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያዊያንን ስደተኞች መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለይም በአይ.ኤስ.አይ.ኤስ. የታረዱ ፴ ኦርቶዶክሳዊያን ዘመነ ፕትርክናቸውን የሚፈትን ነበር። ከዚህ ባሻገር ከ፳፻፰ ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ሃገሪቱ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መበራከትና ትኩረቱን ኦርቶዶክሳውያንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ማድረጉ ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ ነበር።ሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ኢትዮጵያ በሰላም ሰባኪዋ ቤተክርስቲያንና በልጆቿ ደም ታጥባለች። ማንነትን መሠረት ካደረጉ ጥቃቶች መለስ ስንል በሃገሪቱ የሰሜኑ ክፍል የተጀመረውና ቀስ በቀስ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተዛመተው በመንግስትና ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነትም ለዘመናቸው መራር መልክን የሰጠ ክስተት ነው።
ቅዱስነታቸው በመልእክቶቻቸው ደጋግመው የሚያነሷቸው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የሰብዓዊ መብቶች መሸራረፍ፣ ኢሰብአዊ ጨካኝ ድርጊቶችና ረሃብም ሌሎች ዘርፎች ናቸው። የኮሮና ወረርሺኝ ያመጣው ችግር ሳይረሳ። በውስጣዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥም እየጠፋ የመጣው ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ጎጠኝነት ዘመናቸውን የፈተነ ተግባር ነበር። ራሳቸውን የጎጃም ሃይማኖት ብለው የሚጠሩት የቅባት ሰዎች በጎቃ ኪዳነምሕረት ከመሠረቱት መንበር ጀምሮ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የማያቃቸውና ራሳቸውን መንበረ ጴጥሮስ፣ መንበረ ሰላማ፣ መንበረ ሃርቤ እያሉ የሚጠሩ የጎጥ ሲኖዶሶች የተፈለፈሉትም በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና ነው። በእኒህ ሁሉ ችግሮች ቢታጀብም ዘመናቸው ዛሬም እግዚአብሔር ከቤተክርስቲያን ጋር እንዳለ በሚያሳዩ በርካታ ጠብቆቶች የተከበቡ መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም። ከምንም በላይ በልዩነት ለዘመናት ተከፋፍለው የነበሩ ብፁዓን አበው ወደ አንድነት መጥተው ቅዱስነታቸው ከአራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጋር በአንድነት ቤተክርስቲያንን ለመምራት መታደላቸው እጅጉን የሚከበር ታላቅ ስኬት ነው። ከዚህ ባሻገር ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲኖራት ማስቻል፣ በደርግ ዘመን የተወረሱ በርካታ ንብረቶቿን ማስመለስ፣ የቤተክርስቲያንን በዓለም ደረጃ ያላትን ተደራሽነት መጨመር፣ በዐረብ ሀገራት የቤተክርስቲያን ይዞታ ማግኘት፣ የሃገረስብከቶችን ቁጥር ከነበረበት ከፍ እንዲል ማድረግ፣ ቃለ-ዓዋዲን ማሻሻል፣ ከአኀት አብያተክርስቲያናት ጋር የነበረን ግንኙነት በተለይም ከኤርትራ ቤተክርስቲያን ጋር የነበረንን ግንኙነት ማደስ፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስና ከካቶሊክ አብያተክርስቲያናት ጋር የሚደረጉ የነገረ መለኮት ውይይቶችን እንደገና ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት መደገፍና የመሳሰሉ ስኬቶችን ዘመነ ፕትርክናቸው አስገኝቶልናል። ሰላም ከቅዱስነታቸው አንደበት የማትጠፋ ቃል መሆኗን ከሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆች፣ የበዓላትና የቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቶቻቸው መረዳት ይቻላል። ምንም እንኳን ሰሚ ለማግኘት መታደላቸውን ማረጋገጥ ቢከብድም ከዓለም መንግስታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያሉ የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ ታጣቂ ኃይሎች፣ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ምእመናንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ሳያነሱ አያልፉም። በዘንድሮው በዓለ ሲመታቸውም ላይ አፅንዖት የሰጡት ስለሰላም አስፈላጊነት ነበር። የቅዱስነታቸው የሰላም ጥሪ ፍሬ ያፈራ ይሆን? ይሄ ሁላችንም ራሳችንን የምንጠይቅበትና በቀጣይ ዘመናቶቻቸው የሚመለስ ጥያቄ ነው። የዛሬውን ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ አምዳችንን የምንቋጨው ለቅዱስነታቸው ረጅምና ያማረ የአገልግሎት ዘመን በመመኘት ነው። የቅዱሳን አባቶቻችን ድል የማትነሳ ሃይማኖታቸው ከእኛ ጋር ትሁን። አሜን!