ታላቁ አባ አቡፋና

በየካቲት ፳፭ ስንክሳር ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው የቅዱሱ አባታችን አቡፋና ታሪክ እንዲህ ነው ፡፡ በግብጽ ሀገር  ናይን አውራጃ በመዓልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊት አምስት መቶ ጊዜ አቡነዘበሰማያት የሚጸልዩ አባት ነበሩ። እህል ደግሞ በ፵ ቀን አንድ ጊዜ እየቀመሱ መላ ዘመናቸው በጽሞና ያሳለፉ ናቸው።
አንድ ቀን “እኔ ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ነው?” ሲሉ ዐሰቡ፤ ዓሳቡ ብዙዎቻችንጋ ያለ ግን ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው። እንዴት ቢሉ ጠቃሚ ሲባል ሰው ሞቱን ሲያስብ ንስሐ ይገባል፣ ክፋትን ይተዋል። ያልተፈቀደ ነው የተባለው ደግሞ ሰው አጭር ዕድሜ እንዳለው ቢያውቅ ሽብርና ጭንቀት ይበላዋል። ረጅም ዕድሜ እንዳለው ካወቀ ደግሞ ኃጢያት እየሠራ ልክ እንደ ኖህ ዘመን ሰዎች ለንስሐ ይዘናጋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ስለዚህ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሚለውን አስበን ልንኖር ይገባል። ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና አባ አቡፋ የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ “ዐስራ ስምንት አላቸው” እሳቸውም “ዐስራ ስምንት ምን?” ሲሉ ሳይመልስላቸው ተሰወረ። እሳቸውም “ዐስራ ስምንት ቀን ነው” ብለው ስዕለት ተሳሉ፤ ስዕለታቸውም እስክሞት አልቀመጥም የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ፲፰ ቀናት ቆመው ጸለዩ፣ ግን ሞት አልመጣም። “ዐስራ ስምንት ሱባዔ ይሆን እንዴ?” ብለው ፲፰ ሱባዔ ያዙ፤ አሁንም ሞት አልመጣም። “አይ ዐስራ ስምንት ወር ይሆናል” ብለው ቆመው ተጉ ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ይህን ጊዜ ወደ ፈጣሪ ጸለዩ፡ “ጌታዬ ያልኸኝ ዐስራ ስምንት ምንድን ነው?” አሉ። ቅዱስ መልአክ መጣና “አቡፋና ሆይ የቀረህ ዐስራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና” አለው። ቅዱሱም የገቡትን ስዕለት ሳያጥፉ ዐስራ ስምንት ዓመት እንደ ምሰሶ ተተክለው፣ ቆመው ጸለዩ። ስዕለቱን ሲፈጽሙ ዕረፍታቸውን አውቀው ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ወደ መኖሪያቸው ሔደው ራሳቸውን ዘንበል አድርገው ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። የቅዱሱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን! ምንጭ፡ የየካቲት ፳፭ ስንክሳር

አድዋ

የዓድዋ ድል፣ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የሥነ ልቡና ልዕልና የተገኘ ነው። ጦርነቱ በሁለት አውሮፓውያን ወይም በሁለት አፍሪካውያን ሀገራት መካከል የተደረገ ቢሆን ኖሮ ጥቂትም ቢሆን የኃይል መመጣጠን ስለሚኖር ይህን ያህል አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን በጉልበተኞች ጽንፍ ባለች በአንዲት ሀገርና በምስኪኖች ጽንፍ ባለች በሌላ ሀገር ምክንያት የተደረገ በመሆኑና ውጤቱም ሥጋ ለባሽ ከሚጠብቀው አመክንዮአዊ ውጤት እጅግ የተለየ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። ከጦርነቱ መጀመሩ አስቀድሞ ጳውሎስ ኞኞና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ገለጹት ሁሉም፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምታሸንፋት ያስቡ የነበረው ይህን አለመመጣጠን በሰውኛ መነጽር በማየት ነበር። ታዲያ ድሉ እንዴት ተገኘ? የድሉ ዋና መሠረት የሥነ ልቡናና ዐስተሳሰብ ሚዛን ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውና በውጊያ አቅማቸው ክፉኛ ተማምነውና መተማመናቸውም ወደ ትዕቢት ከፍ ብሎ ነበር።
“…በቅርብ ቀን ምኒልክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…” ይል የነበረው የኢጣሊያ የጦር መሪ፣ የጄኔራል ባራቲዬሪ ንግግርም ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ሕዝቡም ገና ጦርነቱ ሳይጀመር “ድል አድራጊው” እያሉ እርሱን መጥራታቸው የዚህ ሌላው ማሳያ ነበር። በኢትዮጵያውያን በኩል ምንም እንኳን የኢጣሊያ ዐቅም እጅግ እንደሚልቅ ቢረዱትም ከንጉሡ አዋጅ ጀምሮ ካላቸው የጦር ቁስ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መተማመናቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቶአል። እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የሀገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ጣልያናዊ ተዋጊም በጦርነቱም ወቅት   “በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተመላለሰ ወደ ጦርነቱ ግቡ ኢጣሊያኖችን ማርኩ እያለ ትእዛዝ ሲሰጥና ሲዋጋን የዋለ ማነው?” ብሎ መጠየቁ እየተገለጸ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጋዥነት መገለጹም እዚህ ላይ መነሣት የሚገባው ነው። የዓድዋ ድል ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱም መነገር የሚገባው ነው።
በእውነት የእግዚአብሔር ፍርድ በዕለቱ ተፈጸመ፤ ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።መልካም ዕለተ ሰንበትምንጭ፡ ሐመር መጽሔት  የካቲት ፳፻፲፫ዓ.ም.

የአርዮስ አሟሟት እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተክርስቲያን ላይ ያደረጉት ዘመቻ

የኒቂያ ጉባኤ ከተፈጸመ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አርዮስን በቦታ ወስኖ ባጋዘው በሁለት ዓመቱ የቆስጠንጢኖስ እኅት በአርዮስ እና በአውሳብዮስ ደጋፊዎች ተለምና አርዮስ ከውግዘቱ እንዲፈታ ቆስጠንጢኖስን ለመነችው፡፡ ቆስጠንጢኖስም ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመለስለት አዘዘ፡፡

የአርዮስ መመለስ በቤተክርስቲያን ላይ ችግር አላመጣም፡፡ ዋናው ችግር በቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የተወሰነው ውሳኔ በንጉሡ አለመከበሩ ነው፡፡ ይህም ድፍረት ቤተክርስቲያንን እና የቁስንጥንያ ቤተመንግሥትን አጋጭቷል፡፡ አርዮስና ደጋፊዎቹ የኒቂያ ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ በግልጥ ሊቃወሙ ባይችሉም ወደ ቤተመንግሥቱ ጠጋ ብለው በጉባኤው ተስማሚነት የነበራቸውን ሰዎች ስም በማጥፋት ከንጉሡ ማጣላትና ማሳደድ ጀመሩ፡፡

ለምሳሌ ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመራው ኤዎስጣቴዎስ በ፫፻፴ ዓ.ም. የአንጾኪያው መንበር በንጉሡ በቆስጠንጢኖስ ትዕዛዝ እንዲለቅ ተደረገ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የቆስጠንጢኖስ እናት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ስትሔድ በአንጾኪያ አልፋ ነበርና “መንግሥታዊ  አቀባበል አላደረገላትም”፡፡ በማለት አርዮሳውያን ነገር ሰርተው ነው ፡፡ ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን በውስጥ ለውስጥ አድማ ይህን የመሠለ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ብዙ ግፍ ከተፈጸመባቸው ኦርቶዶክሳውያን አባቶች አንዱ አንጋፋው ቅዱስ አትናቴዎስ ነው፡፡ አትናቴዎስና ቆስጠንጢኖስ ሆድና ጀርባ ሲሆኑ አትናቴዎስን ለመክሰስ ለወንጀለኞች ቀላል ነበር፡፡

አርዮሳውያን  አትናቴዎስን በኃጢአት ከሰሱት።
  ፩. በነፍሰ ገዳይነት፣
  ፪. በድብድብ ወንጀል፣
  ፫. በንጉሡ ላይ ለመጡ ሽፍቶች ስንቅና ትጥቅ አቀብሏል፣
  ፬. በዝሙት አግኝተነዋል፡፡


በማለት ከሰሱት፤ ጉዳዩ በጉባኤ እንዲታይ  ተደረገ፡፡ጉባኤው ተጀምሮ የአትናቴዎስ ክሶች እየተነበቡ የእምነት ክህደት ቃል ይስጥ ተባለ፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ የተከሰሰባቸውን ክሶች እንዳላደረገ በማስረጃ  አስደግፎ ተናገረ፡፡ ሁሉም ውሸት እንደሆነ ተናገረ፡፡ ከሳሾቹም አፈሩ፤ ንጉሡ ግን በግል ቂም ተነሳስቶ ወደ ትሬቬሬ አስጋዘው፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ አትናቴዎስ ለ፵፯ ዓመታት በፓትርያሪክነት፣ ለ፲፬ ዓመታት በስደት አሳልፎ በ፸፭ ዓመቱ ግንቦት ፯ ቀን በ፫፸፬ ዓ.ም. ዐረፈ።

ምንጭ፦ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ.

ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

ቅዱስ ያዕቆብ ቅዱሳን ከሆኑ ወላጆቹ ከቅዱስ አረጋዊ ዮሴፍ(የእመቤታችን ጠባቂ) እና የእመቤታችን አክስት ልጅ ከሆነችው ማርያም የተወለደ እድለኛ ቅዱስ ነው። ምክንያቱም በእመቤታችን እጅ ያደገ የጌታ ወንድም እየተባለ ይጠራ ነበር። አባቶች የጌታ  ወንድም መባሉ ለዚህም ምክንያት ሲያስቀምጡ ለ፴ ዓመታት ከጌታችን ጋር ማደጉ፣ የጌታ የሥጋ አያቱ (ቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣ የዮሴፍም የአንድ ቅድመ አያት ልጅ  በመሆኑ በማለት ያስቀምጡታል። የሥጋ  ወንድሞቹ ደግሞ ይሁዳ ፣ ዮሳ እና ሰሎሜ የተባለች እኅት ነበረችው። እናታቸው ማርያም ከሞተች በኋላም ተጎሳቁለው ነበር፤ በተለይ ቅዱስ ያዕቆብ ትንሽ ልጅ ስለነበር ያሳዝን ነበር። እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ ተሰጥታ ከቤተ መቅደስ ወጥታ ወደ አረጋዊ ዮሴፍ ቤት ስትሄድ የአክስቷን ልጆች ሁኔታ አይታ አለቀሰች። በተለይ ያዕቆብን ስታይ ወዲያውኑ ማድጋ ይዛ ወደ ምንጭ ወረደች፤ ውኃውን አምጥታ ሕፃኑን አጠበች። የሰላም፣ የበረከት፣ የምሕረት እናት፤ የአምላክ እናት ገብታለችና የሀዘን ቤት ወደ ደስታ ተቀየረ። ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ፱ወር ከ5ቀን እና ከተወለደ በኋላ ለ፪ ዓመታት ያዕቆብን ተንከባከበችው። ከዛ ጌታን ይዛ ተሰዳ ነበር። ከስደት መልስ ደግሞ ለ፳፭ ዓመታት አንድም ቀን እናቱ ትዝ ሳትለው በእንክብካቤ አድጓል። ቅዱስ  ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው፤ ከሰባ ሁለቱ አርድዕትም ተቆጠረ። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ። ከዛም መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ፤ የኢየሩሳሌምም ጳጳስ ሆኖ አገለገለ።
ቅዱስ ያዕቆብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከዮሐንስ ጋር ሆኖ  “የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም” በማለት ማክፈልን አስጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀመንበርነት መራ። ከዚህ በኋላ ብዙ ተአምራትን ማድረግ ጀመረ። ብዙ አይሁዳውያንን ወደ ክርስትና መለስ። በመጨረሻው ዘመኑም የአይሁድ አለቆች ወደ  ቤቱ ተሰብስበው “የናዝሪቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው ?የማንስ ልጅ ነዉ?” ሲሉ ጠየቁት። እነሱ የሚፈልጉትን ምላሽ ስላላገኙ በብስጭት ወደ መሬት ወረወሩት፤ እየተፈራረቁ በገድል የተቀጠቀጠን አካሉን ደበደቡት። አንዱ ግን በጭካኔ ከእንጨት በተሠራ ገንዳ የቅዱሱን ራስ ቀጠቀጠው። ሰማዕቱ ቅዱስ ያዕቆብም ወደ ወደደው ክርስቶስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ሔደ። ቅዱሱ ሐዋርያ ቤቱን እንደ ቤተመቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙበት ነበር። ቅዱሱ ሐዋርያ የሚያጎድፍ (ጥሉላት ምግብ ) ቀምሶ ፣ ፀጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦ አያውቅም። የያዕቆብ መልእክት የሚለውንም ባለ አምስት ምዕራፍ መጽሐፍ ጽፏል። ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ለመባል ካበቃው ቅዱሱ በረከትን ያድለን በምልጃው በረከቱ አይለየን ። ምንጭ፡ ስንክሳር ከመስከረም እስከ መጋቢት

እግዚአብሔር የሚወደው ጸሎት

ከ፭ መቶ ዓመታት በፊት አንድ አይሁዳዊ ወጣት ከስፔን ምርኮ ሸሽቶ ወደ ትውልድ ሀገሩ እስራኤል ይመለሳል ። ወደ መንደሩም በደረሰ ጊዜ አይሁድ ከገጠማቸው መከራ ይድኑ ዘንድ የሚድራሽ ረቢ(መምህር) የሆነው ይስሐቅ ሉርያ የአይሁድ ጉባኤን ሰብስቦ እየጸለየ ነበር ያገኘው ። ይህ ከምርኮ ያመለጠው ወጣትም በመካከለቸው ገብቶ እያለቀሰ ፈጣሪውን
       ” ጌታዬ ሆይ! ምንም የማውቀው ጸሎት የለኝም። የዕብራይስጥ ፊደላትን ብቻ እንጂ፤ ቋንቋውንም ቢሆን አላውቀውም፤ እባክህ ጌታ ሆይ እነዚህን ፊደላት ወስደህ ፥ አንተ የምትወደውን ፣ ለአንተ የሚገባውን ፣ ላንተ የሚሆነውን እጅግ ውብ ጸሎት አድርገህ አዘጋጀው” እያለ ከልቡ ያዝን ጀመር። ቀኑን ሙሉም የዕብራይስጥ አሌፋትን እየደጋገመ ሲጠራ ዋለ ። በዚያን ምሽት አይሁድ ከገጠማቸው ፈተና የዳኑት በዚህ ምስኪን ፣ ት።ሑትና የተሰበረ ልብ የነበረው ወጣት ጸሎት እንጂ ፥ በይስሐቅ ሉርያ፣ በደቀ መዛሙርቱና በአይሁድ ጉባኤ ጸሎት እንዳልነበር መምህሩ ይስሐቅ ሉርያ በራዕይ ተገለጠለት ።  ረቢውም የትሑት ሰው ጸሎት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ተረዳ ። ሥጦታን ለወዳጁ ሊሰጥ ያሰበ ሰው ወዳጁ ምን እንደሚያስደስተው አስቀድሞ እንዲመረምር ፣ እንዲጠይቅ ፥ በፈጣሪው ዘንድ የተወደደ ሥጦታ  የሚያቀርብም ሰው አምላኩን ምን ሊያስደስተው እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል። ስጦታን የሚቀበል ሰው የሚወደውን ስጦታ ገዝተው ሲሰጡትም እንዲወድ ፥ እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ሲያቀርቡለት ይወዳል ።
       “እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ሥጦታ ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ አምላኩን “መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” በማለት እግዚአብሔር ከጸሎታችን በላይ ጸሎታችንን ያቀረብንበት በንስሐ የተሰበረ ልባችንን ፣ በትሕትና የተገነባ ሕይወታችንን እንደሚወድ ይነግረናል። ከቃየን ይልቅ የአቤልን መሥዋዕት፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ የቀራጩን ጸሎት እግዚአብሔር የተቀበለው ሥጦታቸውን ሳይሆን ስጦታቸውን ያቀረቡበትን ልበ ትሕትናቸውን ስለተመለከተ ነው ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ኦሪት ዘፍጥረትን በተረጎመበት ድርሳን “እግዚአብሔር የአቤልን የበግ መሥዋዕቱን የተመለከተው ከተቀባዩ ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታይ መሥዋዕቱ በምንም መልኩ ከነውርና ነቀፋ ንጹሕ ስለነበር ሳይሆን ከመስዋዕቱ አቅራቢ በንጹሕ ልብ የቀረበ ስለ ነበር ነው።” በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት ላይ የሚገኘውን የቀራጩንና ፈሪሳዊ ታሪክ አንስቶ ባስተማረበት ድርሳንም የፈሪሳዊው ልመና ለምን ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲገልጽ “ፈሪሳዊው ስለ ቀራጩ የተናገረው እውነት ቢሆንም ነገር ግን በጸሎቱ የራሱን ኃጢአት ከማሰብና ከማሳሰብ ይልቅ ወንድሙን እያማ ስለነበረ ወደ ቤቱ የተመለሰው የጾምን ዋጋ ሳያገኝ ባዶውን ነበር ” በማለት የትዕቢተኛ ሰው ጸሎት እንደሆነ ይነግረናል።  የእኛስ ጸሎት?? በዲ/ን ዘአማኑኤል ገዛኸኝ

ጾም

ስለ ጾም:- “ጾምን ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ” ት.ኢዩ ፩፥፲፬። ጾም የሚለው ቃል “ጾመ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ተከለከለ፣ ተወ፣ ታቀበ ማለት ነው:: ጾም ማለት ራስን ከእህልና ከውኃ ብሎም እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ነገሮች ወይም ከክፉ ምግባራት ሁሉ ራስን በመከልከል የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት መቆየት ማለት ነው::

የጾም መንፈሳዊ  ጥቅሞች ምንድናቸው?
፩. የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ የምናስገዛበት መንፈሳዊ ተግባር ነው። ጾም ከመንፈሳዊ ምግባራትና ተጋድሎ አንዱ ነው:: ለሥጋ መንፈሳዊ ልጓም ነው:: አንድ ክርስቲያን ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት መንፈሳዊ ስንቅ ነው።

፪. ጾም የኃጢአት ሥርየት የምናገኝበትና ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንገድ ነው::  “በፍፁም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ት.ኢዩ. ፪፥፲፪

፫. ጾም የዲያብሎስን ፈተናና ውጊያ  ድል የምናደርግበት መንፈሳዊ  የጦር መሳርያ ነው::
   – ይህንን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር አስተምሮናል። ማቴ ፬÷፩-፲፩  እንደተጠቀሰው ዲያብሎስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሦስት ዋና ዋና የኃጢአት ሥሮች በተባሉት አርእስተ ኃጣውእ እንደፈተነው ጌታችንም ድል እንዳደረገው ተገልጿል::

እነዚህም:-
፩. ስስት
‘ “የሚፈታተነውም ቀርቦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች  እንጀራ እንዲሆኑ በል” አለው’ ማቴ ፬፥፫ በማለት ለጌታችን የመጀመሪያውን ፈተና እንዳቀረበለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል:: ጌታችን ይህንን ፈተና “ሰው  ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል” ብሎ ዲያብሎስን  በትእግስት ድል አድርጎታል።

፪. ትእቢት
‘  “መላእክቱን ስላንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ ተጽፏልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ወደ ታች ራስህን ወርውር’ አለው።
በዚህ ዲያብሎስ ለክፋትና ለተንኮል በጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የምንረዳው ጥቅስ መጥቀስ መጻሕፍትን ማወቅ ብቻ የእውነተኛ ሰዎች ምልክት አለመሆኑን እንረዳለን::
ለዚህም ፈተና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመልስ “ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፏል” በማለት በትእቢት የመጣበትን የዲያብሎስን ፈተና በትህትና ድል አድርጓል::

፫. ፍቅረ ነዋይ
  ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምንም መንግስታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህንን ሁሉ እሰጥሃለሁ” በማለት ብዙዎችን ድል ባደረገበት በፍቅረ ነዋይ የመጨረሻውን ፈተና አቀረበ:: በእውነቱ ከሆነ ዛሬ በዚህ ፈተና ያልተሸነፈ ሰው የለም:: እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ጦርነቶች ብዙ ምክንያት ቢሰጣቸውም ዋናው ምክንያት ግን ፍቅረ ነዋይ ነው:: ዝሙት፣ ስርቆት፣ ዘፈን ምንጫቸው ፍቅረ ነዋይ ነው::
“እናምናለን” የምንል ሰዎችም በዚህ ኃጢአት በመያዛችን ቤተክርስቲያናችን በብዙ ችግር ውስጥ ገብታለች::  ለሁላችንም  ከዚህ ሕይወት መውጫ መንገዱን አምላካችን ያሳየን::
ጌታችንም ‘ ሂድ አንተ ሰይጣን “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ” ተብሎ ተጽፏልና::’ በማለት በፍቅረ ነዋይ የመጣበትን ፈተና ድል አድርጎታል:: እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ “ዲያብሎስ ተወው። እነሆም መላእክትም ቀርበው ያገለግሉት ነበር” ይላል።

መላእክት ባይረዱት መች ድል ያደርገኝ ነበር እንዳይል አንድም ደግሞ እነዚህን ሦስቱን የኃጢአት አለቆች ድል ስታደርጉ መላእክት ይገለጹላችኋል ብሎ ሲያስተምረን ነው:: እኛም በእነዚህ የጾም ወራት በጾም በጸሎት እንዲሁም በበጎ ምግባራት ሁሉ በርትተንና ጠንክረን የዲያብሎስን ውጊያና ፈተና ሁሉ ድል እንድናደርግ ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን::

ጾሙን የበረከት ያድርግልን አሜን።

    ምንጭ፡   ዲያቆን አቤል (ፍቅረ አብ)

አባ አውሎግ አንበሳዊ

የጻድቁ አባታችን በጎ ሥራው ከወላጆቹ የሚጀምር ነው። በበጎ  ሥራ ፍጹማን የሆኑ ባለጸጋዎች ናቸው። ልጃቸውን የቤተክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ አስተምረውታል። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ንብረታቸውን ለልጆቻቸው ሰጥተው አረፉ። በአንዲት ዕለትም “አውሎግ ያለህን ገንዘብህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ሰጥተህ መከራ መስቀሉን ተሸክመህ ና ተከተለኝ።” የሚለውን የከበረ የወንጌል ቃል አሰበና ወዲያውኑ ጻድቁ  አውሎግም ንብረቱን ለድሆች ሰጥቶ ወደ አባ አውሎጊን ሔደ። እርሱንም በደስታ ተቀበሉት፤ አስቀድሞ ስለ እሱ እንዲህ የሚለውን ራእይ አይተው ነበርና፡ “እነሆ ጎልማሳ ይመጣል።” ተቀበለውና ከዛም ከመነኮሳቱ ጋር ቀላቀለውና ለ፫ ዓመታት እየፈተነው ፍጹም የሆነውን ቅድስናውን ባየ ጊዜ የምንኩስና ልብስ የመላእክት አስኬማ አለበሰው። በእዚያም ከሰንበት እስከ ሰንበት እየጾመ እየተጋደለ ኖረ። ምግቡም እንጀራና ጨው ነበር። ለ፵ ዓመታት ኖረና መምህሩ አባ አውሎጊንን እንዲያሰናብቱት ለመነና ወደ በረሀ ገብቶ ለ፶ ዓመታት በተጋድሎ ኖረ። እግዚአብሔርም ለፍላጎቱ የሚያገለግሉት ሁለት አንበሶችን እንዲያገለግሉት ሰጠው። በዚህም አባ አውሎግ አንበሳዊ ስትል ቅድስት ቤተክርስቲያን ትጠራዋለች። በአንዲት ዕለትም ለአንበሶቹም የሞቀ ውኃ አምጡልኝ አለ። አንደኛው አንበሳም ወደ ተራራው ሔዶ አንድ እረኛ ይዞለት መጣ እረኛውም ለአባ አውሎግ የሚፈልገውን አድርጎለት አንበሳው እረኛውን ወደ ቦታው መለሰው። ያም እረኛ በሔደበት ሁሉ  “ጻድቅ ሰው አገኘሁ” እያለ ተናገረ። የሰሙ መምህሩ ሰዎችም ወደ ቅዱሱ ሔ፤ በሽተኞችንም እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር። በዚያ  ወራትም መምህሩ አባ አውሎጊን በፋርስ ጣዖት የሚያመልኩትን ለመመለስ ፈለገና ልጁ አውሎግን ፈለገ። አናብስቱም የጌታ ፈቃዱ ሆኖ የቅዱሳኑን ፈቃድ ያውቁ ስለነበር አባ አውሎግን ከበዓቱ ይዘውት መ። ሁለቱም ተገናኝተው ወደ ተለያዩ ሀገሮች አየዞሩ በማስተር ብዙዎችን አጠመቁ። አናብስቱ ለቅዱሳኑና ለሕዝቡ ሲርባቸውም ተግተው ይመግቧቸው ነበር፤ በግብጽና በሶርያ በረሃዎች ለ፺ ዓመታት የተጋደሉ ጻድቅና ሐዋርያ ናቸው። ብዙ ተአምራትን ሰርተው ፈጣሪያቸውን አክብረዋል። በጥር ፲፩ የቅዱሱ አባ አውሎግ በዓለ ዕረፍታቸው ነው። ምንጭ፦ ስንክሳር

እንግዳ መቀበል

ሰው በብዙ በሚፈልገውም ሆነ በማይፈልገው ምክንያት ከቤቱ ይወጣል። የሚቀበለው ሊፈልግ ይፈልጋል፤ የሚያስተናግደው ይሻል። “የእግዚአብሔር እንግዳ” ብሎ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ እንዲያሳድሩት ሰዎችን ይለምናል። በዚህ ጊዜ ራሱን እግዚአብሔርን በአካል እንደተቀበሉት ቆጥረው በደስታ የሚያስተናግዱ አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ቤቱን ለመሥራት የራሳቸው ብቻ አስተዋጽዖ እንጂ ቤቱ የእግዚአብሔር ስጦታ እንዳልሆነ በመቍጠርና የእግዚአብሔርንም ቸርነት ባለመረዳት “ማንም እንዳይመጣብኝ” የሚሉም አሉ። ሐዋርያው እንግዳ መቀበልን ዕለት ዕለት የሚያዘወትሩትን እያመሰገነ የማይቀበሉትን ደግሞ በረከት እንዳይቀርባቸው እያሳሰበ ያስተምረናል። እንግዳ መቀበል እንደሚገባ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የፋሲካን ሕግ በአስረዳበት ትእዛዝ “እንግዳ ሰውም በመካከላችኹ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድ፟ አስቀድሞ ወንድ ዅሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ፣ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይኾናል፤ ያልተገረዘ ዅሉ ግን ከርሱ አይብላ።” (ዘፀ.፲፪፥፵፰) በማለት ስለ ፋሲካ ክብር “መገረዝ አለበት” ቢባልም ሊቀበሉት እንደሚገባ ግን ያስረዳናል።
ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር አምላካችን “በሀገራችሁ ውስጥ እንግዳ ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና፤ ወደ እናንተ የመጣ እንግዳ እንደ ሀገር ልጅ ይሁንላችሁ፤ እርሱን እንደ ራሳችሁ ውደዱት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና” (ዘሌ.፲፱፥፴፫-፴፬) ሲል ለሕዝቡ ያስተላለፈውን አምላካዊ ትእዛዝ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ከጥንት ጀምሮ እንግዳ መቀበል አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑን ነው። እንግዳ ይቀበሉ የነበሩ ሰዎች መላእክትን እንዲሁ እግዚአብሔርን በአንድነት በሦስትነቱ ለመቀበልና ከቤታቸው ለማስተናገድ በቅተዋል። እንግዳ የመቀበል መልካም ልማድ የነበረው ሎጥ መላእክቱን ከቤቱ አስተናግዷል። በቅዱስ መጽሐፍ ‘ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደላቸው፤ አላቸውም “ጌቶች ሆይ ወደ ባሪያችሁ ቤት ገብታችሁ እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገም ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።”
እነርሱም “በዐደባባዩ እናድራለን እንጂ አይሆም” አሉት። እርሱም ግድ አላቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፤ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ቂጣንም አስጋገረላቸው፤ እነርሱም በሉ።’ (ዘፍ.፲፱፥፩- ፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል የታደሉ አሉና።” (ዕብ.፲፫፥፩) በማለት የነገረን እንደ ሎጥ ያሉትን እንግዳ ወዳዶች ሊያመስግን ለእኛም ያላቸውን አርአያነት ሊያሳየን ነው። ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት መልካም ዕለተ ሰንበት

ለመስቀሉ ሕዝቦች

የተፈጥሮን ዑደት ጠብቆ የሚጓዘው የሜዲትራኒያን ባሕር ውኃ በነፋስ እየተገፋ ከሲርጥ የባሕር ዳርቻ አሸዋ ጋር  ይላተማል። ከዚህ ትዕይንት የቅፅበታት ማለፍ በኋላ ፳ ጥቁር የለበሱና ፊታቸውን የሸፈኑ ታጣቂዎች ሬንጀር ከለበሰ መሪያቸው ጋር በመሆን በአንድ እጃቸው ቢላ በሌላ እጃቸው  በባዶ እግር እንደ በግ በዝምታ የሚነዱ ብርቱካናማ የእስር ቱታ የለበሱ ንጹሐንን አንገት ጨምድደው ሲጓዙ ይታያል።

ለዛሬ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብር የመረጥነው የዛሬ ዐሥር ዓመት በዚሁ ሳምንት የካቲት ፰/፳፻፯ ዓ.ም. በዕለተ ሰንበት ፅንፈኛው አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. /ዳዕሽ(ISIS) አል ሃያት በተሰኘ ገፁ  “የመስቀሉ ሕዝቦች፣ የጠበኛዋ የግብፅ ቤተክርስቲያን ተከታዮች” በሚል ርእስ ያዘጋጀው የ፭ ደቂቃ ቪዲዮው ወግቢያ ነው።

በሚያቃጥለው የሊቢያ በረሃ በባዶ እግራቸው እንደ በግ የሚነዱት ፳፩ ንጹሐን የቅብጥ ክርስቲያኖች የመታረጃ ቦታቸው ላይ ሲደርሱ በአጋቾቻቸው ተገፍትረው ሲንበረከኩ ይታያል። ሬንጀር ለባሹ መሪያቸው ፈጣሪውን በማመስገን በሚጀምረው ንግግር “ወገኖች ሆይ በአልሻም ተራራ (ሶሪያ) ላይ በዳቢቅ ሜዳ የመስቀሉን ተረት የተሸከሙትን በእስልምናና በሙስሊሞች ጥላቻ የተሞላውን ጭንቅላታቸውን ስንቆርጥ አሳይተናችኋል። ዛሬም በደቡብ ሮም በኢስላም ምድር ሊቢያ ሌላኛውን መልእክት እናስተላልፋለን። ባለ መስቀሎች ሆይ ከእንግዲህ ደኅንነት ለእናንተ ምኞት ብቻ ይሆናል፤ በተለይ ልትፋለሙን ከሞከራችሁ። ጦርነቱ ሸክሙን እስኪያወርድ፣ ኢሳ (ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የሚመጣ ነብይ አድርገው እንደሚያስቡት ልብ ይሏል) መጥቶ መስቀሉን እየሰበረ፣ እሪያውን እየገደለ፣ ጂዚያን(ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የሚከፍሉት ታክስ) እስኪሰርዝ ድረስ የሼህ ኦሳማ ቢላደንን አስክሬን የደበቃችሁበት ባሕር ደማችሁን እንቀላቅላለን።” ሲል ይደመጣል።

ከንግግሩ በኋላ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ “ያ ረብ የሱሃ አል መሲህ” (አቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ) የሚለው የሰማዕታቱ ድምፅ ይሰማል። “ለጣዖታቸው ከነ ሽርክናቸው ይሙቱ” የሚል የዐረብኛ ጽሑፍ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ይነበባል።

“ከአላህ ጋር ሮምን እንቆጣጠራለን” የሚለው የመሪያቸው መፈክር ከተሰማ በኋላ አይ.ኤስ.የአይ.ኤስ. ታጣቂዎች ሰማዕታቱን አጋድመው እንደ በግ ሲያርዳቸውና ደማቸው ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ሲቀላቀል በማሳየት ቪዲዮው ይጠናቀቃል።

፳ው ግብፃውያን እና ፩ የጋና ተወላጅ ከእናት ሀገራቸው ወደ ሊብያ የተሰደዱት ኑሮን ለማሸነፍና የተሻለ ቀንን ለማየት ነበር። በሊቢያ በረሃ በግብርናና በልዩ ልዩ ሥራዎች የተሰማሩ ከፊሉም ድንበር  የሚያቋርጡ ነበሩ። ይህ ታዲያ እስከ ተያዙባት የታኅሣሥ ፳፻፯  ዓ.ም.  ምሽት ድረስ ነው። ከዛች ምሽት በኋላ ሁሉም አንድ ናቸው። ሰማዕታት። ከተንቀሳቃሽ ምስሉ በኋላ ከሌሎች ስደተኞችና በቁጥጥር ስር ከዋሉ የአይ.ኤስ.አይ.ኤስ. አባላት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መጀመሪያ ላይ የተያዙት ፯ ብቻ ሲሆኑ ቀጥለው ፲፫ቱ ተቀላቅለዋቸዋል። የመሞታቸው ምክንያት በተንቀሳቃሽ ምስሉ በግልፅ እንደሚታየው አምላካቸውን ላለመካድ በመምረጣቸው ነበር። ይህ የ፳ው የዕምነት ፅናት የሳበውና ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና  ሰማዕት ሚቲው አያርጋ “እኔም ክርስቲያን ነኝ፤ እንደ እነሱ ነኝ” በማለት ተቀላቀላቸው። አጋቾቻቸው ኢየሱስን እንዲክድ በጠየቁት ሰዓትም “አምላካቸው አምላኬ ነው” የሚል ምስክርነትን ሰጠ።

የሰማዕታቱን የመጨረሻ የምድር ቆይታ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስሉ የብዙኃንን ልብ የሰበረ ቢሆንም ልባቸውን በክርስቶስ ፍቅር ለሞሉ ኦርቶዶክሳውያን የሚያነቧቸውን ዜና ሰማዕታት እውነትነት ያረጋገጡበትና አንገታቸውን ቀና ያደረጉበት ነበር። “The 21” (21ዱ) የተሰኘውን የሰማዕታቱን ዜና መዋል የሚያትት መጽሐፍ የፃፈው ጀርመናዊው ማርቲን ሞስባህ “ብዙዎች የጥቃት ሰለባዎች ብለው ይገልጿቸዋል፤ እነርሱ ግን እንዲህ አይደሉም። ሰለባ ያለፈቃዱ ጥቃት የደረሰበት ነው፤ እነርሱ ግን በፈቃዳቸው ሰማዕትነት የመረጡ ናቸው” ሲል በኩራት ያነሳቸዋል።

የግብፅ ቤተክርስቲያንም ይህንን ለዓለም የተነገረ ዜናቸውን በመመልከት ሰማዕትነታቸውን አውጃዋለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ከግብፅ አቢያተክርስቲያናት ጋር ባለ ነባር አንድነት በተመሳሳይ መልኩ በሚያዚያ ከተሰው ፴ ልጆቿ ጋር  ታስባቸዋለች። የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ከባለፈው ዓመት ጀምራ ስማቸውን በመዝገበ ሰማዕታት ውስጥ አካታዋለች።

መካነ ሰማዕታት ሲርጥ በጥቅምት ፳፻፱ ዓ.ም. ከአክራሪዎች ነፃ በሆነች ሰዓት ነበር የሰማዕታቱ ክብርት ሥጋ መገኘቱን የአካባቢው ባለሥልጣናት ያሳወቁት። ይህን ተከትሎ ከሰማዕታቱ ቤተሰቦች በተሰበሰበ ዘረመል (DNA) አማካኝነት የ፳ው ሰማዕታት ክቡር ሥጋ በግብፅ ሚኒያ ግዛት አል አውር በስማቸው በታነፀው የሰማዕታተ አሚን ቤተክርስቲያን (The church of Martyrs of Faith) በክብር አርፏል። በሐምሌ ፳፻፲፩ ዓ.ም. የግብፅ ቤተክርስቲያን ባቀረበችው ይፋዊ ጥያቄ መሠረት በ፳፻፲፫ ዓ.ም. የ፳፩ኛው ጋናዊ ሰማዕት ክቡር ሥጋ ፳ውን ወንድሞቹን ተቀላቀለ። በዕለቱ የተገኙ የ፳ው ሰማዕታት ቤተሰቦች የጋናዊውን ሰማዕት አፅም መምጣት ተመልክቶ “ደስታችን ሙሉ ሆነ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ብዙዎችን እንዲያስቆጣና ተስፋ እንዲያስቆርጥ የተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ምስል በተቃራኒው አማንያኑን በፅናት የሚያጀግንና ከበቀል ይልቅ ፍቅርና ይቅርታን ያሳየ ነበር። የግብፅ ቤተክርስቲያን የእንግሊዝኛ የምሕዋጸ-ርሑቅ(Television) ጣቢያ የሆነው ሲ.ዋይ.ሲ. ምሕዋጽ ከሰማዕታቱ ቤተሰብ ጋር ባደረገው ቆይታ የሳሚህ ሳላህ ባለቤት መርየም እንዲህ ትላለች “እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በፍፁም አላዝንም። ክርስትናዬን አውቀዋለሁ። ባሌ በሰማዕትነት እንጂ በአደጋ አልሞተም። ከተጋባን ጀምሮ ስለ እግዚአብሔርና ስለሁሉም ነገር ይነግረኝ ነበር። ስለሱም እግዚአብሔርን እወደዋለሁ። በክርስትናችን እንኮራለን እንደ ክርስቲያን የሆነው ነገር አኩርቶናል። ጌታችን ክርስቶስ ስለኛ ተሰቅሏል፣ ደሙን አፍሷል ተገርፏል። እኛ ይህን ማድረግ ይከብደናል? ትንሽ የደም ጠብታ ስለሱ ያቅተናል? በፍፁም! ይህንን ማድረግም መቋቋምም እንችላለን። . . . እንደነሱ መሞትን እንመኛለን። ይህ ሞት አይደለም ሰማዕትነት ነው። ሳይገባኝ(“ባ” ጠብቆ ይነበብ) የሰማዕት ሚስት ሆኛለሁ። እግዚአብሔር ማንንም አይተውም። ጥቁር ለብሰን በቤታችን ብንቀመጥም ይህ የመጨረሻው አይደለም። በእነሱ እንኮራለን።”

የሰማዕቱ ናሲፍ ኢዛት ሚስት ደግሞ እንዲህ ትላለች “ለሱ (ለባሏ) መንገር የምፈልገው ‘ምን ያህል ዕድለኛ ነህ?…ልጃችን ስታድግ ትኮራብሃለች። አባቷ ሰማዕት እንደሆነ ትናገራለች። ኢዛት እኔም እኮራብሃለው የትም ስሄድ የሰማዕቱ ሚስት እንደሆንኩ እናገራለሁ”  ስለ ገዳዮቹ ስትጠየቅ “በኢየሱስ እንደሚያምኑ አምናለሁ ስለሰሩት ኃጢያት እንደሚፀፀቱ አምናለሁ። ይቅር ብያቸዋለሁ አልጠላቸውም።”

የሰማዕቱ ታድሮስ ሚስትም “እሱ የእኔ ትልቁ ሰማዕት ነው፤ በሰማይ ስለእኛ እንዲጸልይ እጠይቀዋለሁ። እነሱንም እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመልሳቸው እጠይቃለሁ” ኢብስታም ኖሺይምም እንደሌሎቹ ሴቶች ባሏ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት ወደ ተሻለው ቦታ እንደሄደና በዚህም እግዚአብሔርን እንደምታመሰግንና በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ባሏን እንዲያስባት እንደምትጠይቀው ከተናገረች በኋላ “እነሱ (ገዳዮቹ) ልባችንን በጥልቅ ጎድተውታል ግን እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው።…ባሌ በሰማዕትነቱ ወቅት ደስተኛ ነበ፤ እርሱ ክርስቶስንና ድንግል ማርያምን ሲያያቸው ነበር። በፊቱ ገነት ተከፍታ ነበር። ለምንም ግድ አልነበረውም ሁሌም ፈገግ ብሎ ነበር። መስቀሉን ስላልበጠሰና ስላልተሸነፈ እንኮራበታለን። እግዚአብሔርንም እናመሰግናለን እርሱ እኔንና የሰማዕቱን ልጆች ይጠብቃል።” ትላለች።

እንደ ቅብጣውያኑ ሁሉ በወርሃ ሚያዝያ በክርስቶስ ስላለች እምነታቸው ምስክር የሆኑትን ኢትዮጵያዊያንን ዜና ገድል በወቅታቸው ለመዘከር እንዲያበቃን እየተመኘን የዚህ ሳምንቱን ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ በዚህ ቋጨን። የማርቲን ሞስባህ  ሃያ አንዱ (the 21)፣ CYC tv ከሰማዕታቱ ቤተሰብ ጋር ያደረገው ቆይታ፣ አል አረቢያ ስለ ሰማዕታቱ ግድያ የዐይን ምስክር ምስክርነት ጥንቅርና የቮይስ ኦፍ ማርቲር፣ቫቲካን ኒውስና የሪዎተርስ ዘገባዎችን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

ጉባኤ ኒቂያ

ኒቂያ በጥቁር ባሕር ወደብ አካባቢ የምትገኝ ስትሆን የተመሠረተችውም በዲዮናሲስ ነው፡፡አርዮስ የተባለው መናፍቅ በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ  ተወግዞ የተለየ ሲሆን ለአርዮስ ስልጣነ ክህነት የሰጠው እና ከውግዘቱ የፈታው አክላስ ለመንበረ ማርቆስ ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ሞተ፤ እለ እስክድሮስም ተተካ፡፡ ለቤተክርስትያን የተጋደለ ታማኝ አባት ነው፡፡

የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን የአርዮስን ዐሳብ ብትታገሰውም እርሱ ግን በድፍረት ዐሳቡን በመግለጽ  የግጥም ጽሑፎችን እያሰራጨ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ይህ የአርዮስ የግጥም መጽሐፍ “ታሪያ” ይባላል፡፡ ብዙ የዋሃንን ማወናበድ ስለጀመረ መቶ የሚያህሉ የሊቢያ እና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳት ተሰብስበው  አርዮስን አወገዙት፡፡ አርዮስ እለ እስክንድሮስን “የሰባልዮስ የክህደት ትምህርት ያስተምራል” ብሎ ይለፍፍ ጀመር። ዐሳቡን ያልተቀበሉትን ሁሉ “ሰባልዮሳውያን ናቸው” ይል ነበር፡፡ ይህ ውንጀላ በእስክንድርያ ተቀባይነት ስላጣ ወደ ፍልስጤም ምድር ሄደ። ሶርያና ቂሳርያ እየዞረ  በአንጾኪያ ትምህርት ቤት አርዮስ ጓደኞች ስለነበሩት  ለሁሉም “እለ እስክንድሮስ በግፍ አወገዘኝ፤ የሰባልዮስንም ትምህርት እያስተማረ ነው” ብሎ ነገራቸው ፡፡

ከአርዮስ ጓደኞች አንዱ በጣም የሚረቆርለት የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ የሆነው አውሳብዮስ ከቁስጥንጥንያ ቤተመንግስት ባለ ሙሉ ሥልጣን ነበር፡፡ ወደ ኒቆሜድሮ ገስግሶ እንዲመጣ ጥሪ አደረገለት፤ በአካባቢው የሚገኙ  ኤጲስ ቆጶሳት ሁሉ አርዮስን እንዲደግፉ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ቁስጥንጥንያ እስክትመሠረት ድረስ የምስራቁ ሮም ክፍል ዋና ከተማ ኒቆሜድሮ ነበረች፡፡ አርዮስም ወደዚህች ከተማ በሔደ ጊዜ አውሳቢዮስ ተቀብሎ ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ ስለ አርዮስ ጉዳይ ጉባኤ አረደገ፡፡ ሲኖዶሱንም የመራው እራሱ አውሳቢዮስ  ነበር፡፡ ሲኖዶሱም አርዮስ መወገዝ እንደሌለበት ከውግዘቱ በመፍታት ወደ አንጾኪያ እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የእስክንድርያ ቤተክርስትያን አልሰማችም ነበር፡፡ አርዮስ “እለ እስክንድሮስ ሲያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ” በማት የክህደት ትምህርቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ በእስክንድርያ ብቻ ሳይሆን በቁስጠንጢኖስ ቤተመንግሥት ስጋት ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም  ተጨባጭ መፍትሔ እንዲገኝ በማሰብ የእስጳኝ ኤጲስ ቆጶስ ኦስዮስ ወደ እስክንድርያ ላከው። መረጃዎችንም  ሰብስቦ ወደ ቆስጠንጢኖስ ተመለሰ፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ እንዲደረግ አዋጅ ነገሩ፡፡ ለመጀመሪያው ጉባኤ እንዲደረግ የታሰበው በእንቆራ ነበር፡፡ ባልታወቀ ምክንያት በኒቂያ እንዲሆን ተወስኗል፡፡በዚህ አዋጅ መሠረት  የቤተክርሰቲያን አባቶች ኤጲስ ቆጶሳት እና ሊቃውንት  በኒቂያ ተሰበሰቡ ፡፡ በሲኖዶሱ የተሰበሰቡት  አባቶች በሕይወታቸው ንጽሕና ቅድስና ያላቸው፣ በሃይማኖታቸው  የሐዋርያትን ፈለግ የተከተሉ፣ ስለ ሃይማኖታቸው  በሚመሰክሩበት ጊዜ ተቃዋሚዎች በሚፈጽሙባቸው የግፍ ድርጊት  ዐይናቸው የፈረጠ እጅ እግራቸው የተቆረጡ ነበሩ፡፡ ቁጥራቸውም አትናትዮስ  እንደመሰከረው 318 ናቸው፡፡ 

ሌሎችም የቤተክርሰትያን  ጸሐፊዎች ከፍ እና ዝቅ አድርገው ጽፈዋል፡፡ ሶዞሜን የተባለው የቤተክርሰትያን ታሪክ ጸሐፊ የአርዮስ ደጋፊዎች የግሪክ ፈላስፎች እና አርዮሳውያን በጉባኤው በብዛት ተጠርተው ነበር ኦርቶዶክሳውያን ግን ጥቂት ነበሩ፡፡ ጉባኤውን  በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት 3 ሲሆኑ እነርሱም ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት የእስክንድርያው እለ እስክንድሮስ  እና የአንጾኪያው  ኤዎስጣቴዎስ  ናቸው። ሦስተኛው  የእስጳኝ ኤጲስ ቆጶስ ኦስዮስ ነው፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጉባኤው ላይ ንግግር አድርጎ “ለቤተክርስትያን እና ለምእመናን አንድነት የመሰላችሁን ታደርጉ ዘንድ ሙሉ ሥልጣን  ሰጥቻችኋለሁ” ብሎ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ የነገሠበትን ዘውዱን ቀለበቱን  አውልቆ ለጉባኤው አስረከበ፡፡ የጉባኤው የመግቢያ ውይይት  ከግንቦት ፳ እስከ ሰኔ ፲፫ ከተደረገ በኋላ ከሰኔ ፲፬ እስከ ነሐሴ ፳፭ ክርክሩ ቀጥሏል ፡፡

ጉባኤው መጀመሪያ የተነጋገረባቸው አንቀጾች

ሀ. አርዮስ ያቀረባቸው ሁሉንም ጥቅሶች መመርምር፣
ለ. ጥበብ የሚለውን ቃል እንዴት እንደተረጎመው ማየት፣
ሐ. ወልድ በባሕርይው ፍጡር ከሆነ በመዳን ምሥጢር ላይ ስለሚደርሰው አደጋ መወያየት፣
መ. የእግዚአብሔር ቃል ለሰው ልጆች ሲል ወዶ ያደረገውን ተዋሕዶ “አርዮስ የባሕርይ ተወራጅነት ቢኖርበት ነው” ስለማለቱ፣
ሠ. ወልድ በባሕርይ ፍጡር ሳለ እንደሌሎች ፍጡራን በገድል በትሩፋት የአምላክነት ክብር አገኘ ስለማለቱ፣ በጉባኤው አርዮስ አቋሙን እንዲያብራራ ተጠይቆ ሲናገር፡ ‹‹ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበር፤ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው፤ ይህም ማለት አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጡር ፈጥሮታል ማለት ነው፡፡ አብም ወልድን ከፈጠረ በኋላ ስልጣን ሰጥቶት ሁሉን ነገር እንዲፈጥር አደረገው . . .›› በማለት አብራራ፡፡

በዚህ ወቅት እለስንድሮስ ፡ “አምልኮትና ስግደት የሚገባው ለፈጣሪያችን ነው ወይስ ላልፈጠረን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አርዮስም “ለፈጠረን›› ሲል መለሰ፡፡ እለእስክንድሮስም፡ ‘ “ፍጡር ነው” ያልኸው ወልድ የፈጠረን ከሆነ፣ ለአብ አምልኮትና ስግደት እንዳቀረብን፣ ለወልድስ ማቅረባችን ምን ያስጠይቃል?’ ሲለው አርዮስ ምላሽ አልነበረውም፡፡ አትናትዮስም፡ “ኢየሱስ የደኅንነቴ ዋስትና ነው፤ ለማዳን የበቃው አምላክ ስለሆነ ነው።” ማለቱ ይታወሳል፡፡

ጉባኤው የወሰነው ውሳኔ
1. አንቀጸ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት)
2. ሕንፃ መነኮሳት (ለመነኮሳት)
3. ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የተወሰነው የተገኘው በዚህ ጉባኤ ውሳኔ ነው። በአጠቃላይ ይህ የኒቅያ ጉባኤ የተካሄደው በ፫፻፳፭ ዓ.ም. ፫፻፲፰ ተሰብሳቢዎች በተገኙበት “ወልድ ፍጡር”ሲል የሳተውን ቀንደኛ መናፍቅ አርዮስን አውግዘው ለይተዋል፡፡ምንጭ፦  የቤተክርስትያን ታሪክ በዓለም መድረክ