አዳምና ማርያም

አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነው ፈቅዶ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› ብሎ ቃል የገባለትን በማሰብ ከትንሳኤ በኋላ ያለው  ዕለተ ሐሙስ ‹የአዳም ሐሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ታድያ ይህ የአዳም ሐሙስ ዘንድሮ በ2016 ዓ.ም ለአዳም ተስፋው፡ ለሔዋንም መድኃኒቷ ከሆነችዋ ኢሳይያስ ከእሴይ በትር ውስጥ እንደምትገኝ ከነገረላት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ጋር በአንድ ቀን ውሏል።

ይሕ ሐሙስ አዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ዕለቱ ይከበራል፡፡ (ሉቃ. ፳፬ ፥፳፭-፵፱)

    አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት በዕለተ ዓርብ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት  የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በማሰብ ዝክረ አዳም ሐሙስ እንዲከበር በወሰኑት መሠረት የሚከበረው የአዳም ሐሙስ አባታችን አዳም በተሰጠው የተስፋ ቃል የሁላችን ድኅነት ስለመፈጸሙ፣ አዳም ከነልጆቹ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለ መውጣቱ ይዘመራል።

      ከገነት በኃጢአቱ ምክንያት የወጣው አዳም የተገባለትን የቃልኪዳን መፈጸም በጉጉት ይጠብቅና በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሲዖል ነጻ እስኪወጣ ተጨንቆ ለነበረው አዳም እመቤታችን ምልክት ነበረች። አዳምም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በተባለው መሰረት አምላኩ የሚወለድባትን የልጁን ልጅ መወለድ ዛሬ አገኘ።

አዳምና ሔዋን በንስሐ ተመላልሰው የተቀበሏትም ይኅችም ተስፋ፡ በሲኦል ውስጥ ለደረቀው አዳም መረስረስ እንዲሆንለት ለሰው ልጆች ዝናምን የምታሰጥ ደመና ናት።

አዳም እመቤታችን እስኪያገኝ ምን ያህል ናፈቀ? ምን ያህልስ ጓጓ? ነቢያት አምላካቸው እንደሚወለድ ይተነብዪት የነበረ ትንቢት የሚፈጸምባትን እናቱን እስከሚያገኟት ጓጉ። ለዓለሙ ሁሉ ደስታ እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ የጻፈለት አምላክ በማህጸኗ እንደሚያድር በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ሰማች።  አዳም በሔዋን ምክንያት ያጣውን ገነት በእመቤታችን በኩል አገኛት። ተረግማና ደርቃ የነበረችው ምድር በልጇ በረከትን ለበሰች።

  የእመቤታችን ለአዳም ተስፋ መሆን በጌታችን መወለድ ብቻ አላበቃምና ዛሬም፡ አዳም ተስፋ ሲያጣ ከእመቤታችን ይጠጋጋል። በእንተ ማርያም መሀረነ እያለ አምላኩን በእርሷ በኩል ይለምናል። የተሰጣትን ቃልኪዳን እያሰበ ምንም እንኳም ኃጥእ ብሆን ለእናትህ ስለገባህላት ቃልኪዳን ብለህ እያለ ይማጸናል። ከገነት ተራቁቶ በተሰደደ ጊዜ ልብስ ሆና እርቃኑን የሸፈነችለት እናቱን እያሰበም ዛሬም ድረስ በተስፋዋ ይኖራል።

የአልዓዛር ትንሳኤ

የትንሳኤውን ሳምንት ቀናት እንደ በዓል የምታከብረዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን በእለተ ረቡዕ የአልዓዛርን መታሰቢያ ታደርጋለች። የአልዓዛርን መታሰቢያ ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት በታሪክ ቅደም ተከተል መሰረት ከሆሳዕና በፊት ባለው ቅዳሜ የሚያከብሩ ሲሆን ቤተክርስቲያናችን ግን የምስጢር ቅደም ተከተልን መሰረት አድርጋ ከትንሳኤው በኩር ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ቀጥሎ ባለው ረቡዕ ታስበዋለች።


በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የክርስቶስን ትንሳኤ ሳይጨምር 9 ከሞት የመነሳት ታሪኮች የተመዘገቡ ሲሆን ከ9ኙ ውስጥ 3ቱ በነብያት (የሰራፕታዋ ልጅ፣ የሱነማዊቷ ልጅ፣ በኤልሳዕ መቃብር ላይ የወደቀው ሬሳ ) የተፈፀሙ ሲሆን 4ቱ ደግሞ የተፈፀሙት በኢየሱስ ክርስቶስ ነበር (የኢያኢሮስ ልጅ፣የናይኗ እናት ልጅ፣ የቢታኒያው አልዓዛርና በተሰቀለ ወቅት መቃብሮች ተከፍተው የወጡ ሙታን ናቸው)። የተቀሩት ሁለት ተአምራት የተሰሩት ደግሞ በሐዋርያት ነው (ጣቢታና አውጤኬስ)።
ከነዚህ ሁሉ የተዘገቡ ከሞት የመነሳት ታሪኮች ውስጥ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 የተመዘገበው የአልዓዛር ከሞት መነሳት ከትንሳኤው ጋር የተገናዘበ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ለምን ተከበረ? ብለን እንጠይቅ።


አልዓዛር ክርስቶስን ከሚያገለግሉ ብርቱ ቤተሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን በአገልግሎት የሚራዱና ጌታን አጥብቀው የሚወዱት የማርታና የማርያም ወንድም ነው። ክርስቶስም ቤተሰቡን አብዝቶ ይወድ የነበረ ሲሆን አልዓዛር ሲታመምም እኅቶቹ በነብሱ ይደርስ ዘንድ መታመሙን ፈጥነው የነገሩት ለጌታችን ነበር። ጌታችን መልዕክቱ በደረሰው ጊዜ አልዓዛር አርፎ ነበርና ይሄን ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው በማግስቱ ወደ አልዓዛር ቤት ለመሄድ ተነሱ።

ወደ አልዓዛር ቤት ሲደርሱ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር ። እኅቶቹን ማርታንና ማርያምን አናግሮ ወደ የት እንደቀበሩት ጠየቃቸው። ወደ መቃብሩም ወርዶ መቃብሩን አንሱት ብሎ አላዓዛርን ተጣራ አልዓዛርም ከተቀበረበት መቃብር በሕይወት ወጣ (ዩሐ 11:1-44)።


የአልዓዛር ትንሳኤ ከብዙ ትንሳኤዎች የተለየበት ብዙ ምክንያት አለው። የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፡-


የአልዓዛር ከሞት መነሳት ለጌታችን ሞት ምክንያት ነበር


ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የአልዓዛርን ታሪክ ባሰፈረበት ምዕራፍ ከታሪኩ ግርጌ ብዙዎች በእርሱ እንዳመኑ ጠቅሶ ከፊሎች ግን ለፈሪሳውያን በመናገራቸው አይሁድ ክርስቶስን ለመግደል እንዲሰባሰቡ አደረጋቸው። ዮሐ 11:45-47 በመሆኑም የአልዓዛር ሞት በተቀራራቢ ጊዜ ከተከናወኑት የሆሳዕና ክብር፣ ቤተመቅደሱን ከማፅዳት ጋር እንደ ክርስቶስ ስቅለት መንደርደሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።


የአልዓዛር ሞት የክርስቶስ አምላክነቱ ማረጋገጫ ነው


ከአልዓዛር በስተቀር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ የመነሳት ታሪኮች የተፈፀሙት በትኩስ ሬሳ ማለትም ሟቹ በሞተበት ወይም በሚቀበርበት ቀናት ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ከሞት ማስነሳት በአይሁድ ዘንድ የክርስቶስን አምላክ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያስችል አልነበረም። የመጀመሪያው ተመሳሳዩን ተግባር ነብያትም ፈጽመውት የነበረ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአይሁዳውያን ልማዳዊ አስተሳሰብ ነው። አይሁዳውያን ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ለሦስት ቀናት በአየር ላይ ሆና ሳትርቀው ትቆያለች ከዛ በኋላ ነው ጥላው የምትሄደው የሚል እምነት ነበራቸው በመሆኑም ክርስቶስ በኢያኢሮስና በናይኗ መበለት ልጅ የሰራው ተአምር በአይሁድ ዘንድ አምላክ የሚያስብል አይደለም። በአልዓዛር ትንሳኤ ግን አስቀድመው ነብያት በኋላም ሐዋርያቱ ያልሰሩትን ድንቅ ሰርቶ ኃይሉን ገለጠ።


ክርስቶስ ያስነሳው አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን የሞላውና መቆየቱም የተነሳ ሽታ ያመጣ ሬሳ ነበር። ሌላው ደግሞ እንደው ተጠራጣሪዎች እንደሚሉት የውሸት ሞት እንኳን ቢሆን (ሞቶ መስሏቸው የቀበሩት እንኳን ቢሆን) /Staged death/ ለአራት ቀን ያለምግብ፣ ያለውሀና ያለ አየር መቆየቱ በራሱ የሚገድለው በመሆኑ መሞቱ በህዝብም በአህዛብም የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም የአልዓዛር መነሳት የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት ያረጋገጠ ነበር።


የአልዓዛር መነሳት የክርስቶስን ፍቅር የሚያሳይ ነው።


የክርስቶስ ተአምራት ሁሉ የመነጩት ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር ቢሆንም ለኢያኢሮስ ልጅ ዘመዶች  “አታልቅሱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” ያለው ክርስቶስ ስለ አልዓዛር ሞት ከማርታ፣ ማርያምና አብረው ካሉ ዘመዶቿ ጋር አለቀሰ። በዚህም ፍቅሩንና የሰው ልጅ መሆኑን አረጋገጠ።


የአልዓዛር ትንሳኤ የእውነተኛው ትንሳኤ ውብ ምስል መሆኑ


የእስክንድርያው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ የአልዓዛርን ትንሳኤ ባብራራበት ትምህርቱ የአልዓዛር ትንሳኤን የሚመጣው የዕለተ ምጽዐት የሰው ልጅ ትንሳኤ ቆንጆ ማሳያ አድርጎ ያነሳዋል። ቅዱስ ቄርሎስ አልዓዛር የተነሳበት የአይሁድ 7ኛ ወር የመለከት በዓል (የዳስ በዓል መቃረቢያ) የመሆኑን መነሻ ከእለተ ምጽዓት የመለከት መነፋት ጋር ያያይዘዋል። ሙሴ ለዳስ በዓል መቃረቢያ መለከት እንደሚያስነፋ ለዘላለማዊቷ ድንኳን (መንግስት) መቃረቢያ መላእክትን መለከት እንደሚያስነፋ ያለ ነው ይላል። ቅዱሱ ከአልዓዛር መነሳት በፊት የነበረውንም ለቅሶ ከክርስቶስ በክብር መገለጥ በፊት ከሚኖረው ለቅሶ ጋር በማስተባበር የአልዓዛርን ትንሳኤ የኋለኛው ትንሳኤ ምልክት ነው ይለዋል።


የአልዓዛር ትንሳኤ የክርስቶስ ትንሳኤና ሕይወት መሆኑንና በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ሕያው መሆናቸው የተመሰከረበት ነው።


ክርስቶስ ከማርታ ጋር የነበረው ንግግር  ወንጌላዊው እንዲህ ይተርክልናል።
ማርታም ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።
ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት።
ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።
ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤
ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።


እዚህ ላይ ክርስቶስ ለማርታ የተናገረው ወሳኝ ነገር እንይ ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ነው በማለት ትንሳኤ ከሌሎች በፀጋ የሚያገኘው ሳይሆን የባህርይ ገንዘቡ መሆኑን በመናገር በርሱ ለሚያምኑ ሁሉ በእርሱ ሕያው በመሆን የዘላለም ሕይወት የፀጋ ተካፋዮች መሆናቸውን አውጆበታል።
በመሆኑም የአልዓዛር ትንሳኤ ከፍጥረታት የሞት መነሳት ታሪኮች ሁሉ የተለየና ጌታችን አምላክነቱን ያወጀበት ልዩ ትንሳኤ በመሆኑ ከክርስቶስ ትንሳኤ ጋር ተያይዞ ይከበራል።


ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ።

የልደታ ለማርያም ክብረ በዓል የት የት ይከበራል?

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በእነዚህ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ የልደታ ለማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል ይከበራል።

1) ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ልደታ /ክ/ከ ልደታ             
 

2)ደብረ መድኃኒት አቡነ ሃብተማርያም ወቅድስት ልደታ ወቅድስት አርሴማ ገዳም 
          
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አስኮ ካኦጄጄ ዱቄት ፋብሪካ ከፍ ብሎ ቃሌ ተራራ ላይ             
              
3) ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል             
   
ልዩ ስም፡- አዲስ ከተማ ክ/ከ መርካቶ             
                 
4)    ደብረ ስብሐት ቅድስት ልደታ እና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቀራንዮ            
                 
5)     ቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን                     

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቦሌ እግዚአብሔር አብ                   
                 
6)   ኤረር በር ምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ዑራኤል  ቤተክርስቲያን        

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ኤረር በር             
                 
7)     አያት መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም እና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ    
       
ልዩ ስም፦ቦሌ /ክ/ከ አያት ጠበል             
                 
8)    ኮተቤ  ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤልና ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ መሳለሚያ             
                 
9) መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ            
                 
10) ሲኤምሲ መካነ ጻድቃን አቡነ ተክለሃይማኖትና ቅድስት ልደታ  ቤተክርስቲያን
          
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ መሪ ሎቄ              
                 
11)  ቦሌ ሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ             

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ሰሚት             
                 
12)     መሪ አያት ምስራቀ ፀሐይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ             

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ መሪ             
                 
13) ካራ አሎ ደብር ቅዱስ ደብረ ቀርሜሎስ መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ገሪማ            
   
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ ካራ             
                 
14)    ርእሰ አድባራት እንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወ ኤልያስ             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ  እንጦጦ             
                 
15)   መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ ሽሮ ሜዳ            
                 
16)     ደብረ ዕንቁ ልደታ ለማርያም             
   
ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ 01 ራሽያ ኤምባሲ ጀርባ             
   
17)    እንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም             
   
ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ ሽሮሜዳ             
   
18)   ፈረንሳይ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ             
  
 ልዩ ስም፦የካ /ክ/ከ ፈረንሳይ ብረት ድልድይ
             
   
19)   ብሔረ ፅጌ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያምና መድኃኔዓለም ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ብሔረ ፅጌ             
  
20)     ጽርሐ ንግስት ቅድስት ሐና ቤ/ክ             
   
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ፉሪ ሐና ማርያም              
   
21)  ድልበር መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቤ/ክ      
ልዩ ስም፦ጉለሌ ድልበር       


22)    ደብረ ቢታንያ አቡነ ተክለሃይማኖት እና ቅድስት ልደታ ለማርያም              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ቆሬ 5 ቁጥርና 2 ቁጥር ማዞርያ              
 
23)   አዲስ አምባ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና ደብረ ፍስሐ  ቅዱስ ገብርኤል              
 
 ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ሳሪስ አዲስ ሰፈር              
  
24) ፉሪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል             
 
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጋራ ኦዳ              
 
25)    መካኒሳ ደብረ ገነት  ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ              
 
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መካኒሳ               
 
26)   ለቡ ደብረ ታቦር በዓለወልድና አበ ብዙሃን አብርሃም ገዳም              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ /ክ/ከ ለቡ              
 
27)     ጎፋ መብራት ኃይል ደብረ መዊዕ ቅዱስ መርቆሬዎስ እና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ              
  
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጎፋ መብራት ኃይል              
 
  28)  ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ              
  
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቤተል              
  
29)     ቦሌ ቡልቡላ ምስካበ ቅዱሳን አባ ሳሙኤልና ቅዱስ አማኑኤል              
  
ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቡልቡላ              
  
30) አለም ባንክ ጀሞ ደብረ ራማ ቅዱስ ገብርኤል             
  
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አለም ባንክ              
  
31)  አቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤ/ክ              
  
ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ጋራው መድኃኔዓለም

መልካም በዓል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ

በሚያዚያ ወር ዜና እረፍታቸው ከሚከበርላቸው ቅዱሳን አንዱ የግብፅ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት የመንበር አባት የሆነው የመጀመሪያው የእስክንድርያ ፓትሪያርክ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ነው።


ቅዱስ ማርቆስ አባቱ አርስጦቡሎስ እናቱ ደግሞ ማርያም ይባላሉ፤ በልጅነቱም በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን የላቲን፣ ግሪክ፣ የዕብራይጥን ቋንቋዎችን ተምሯል፤ጌታችን በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቅዱስ ማርቆስ ገና ታዳጊ ወጣት ነበር፤ ወላጆቹን እየታዘዘና እያገለገለም አድጓል፡፡ ጌታችን በምሴተ (ጸሎተ) ሐሙስ የአይሁድን ፋሲካ ለማክበር ቤት እንዲያሰናዱለት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሲልክ ቤቱን የሚያሳያቸው ልጅ እንደሚያገኙ ነግሯቸዋል። ይህም ልጅ ቅዱስ ማርቆስ ነበር ፤ ‹‹…ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ያገናኛችኋል፤ ተከተሉት፤ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት…›› (ማር.፲፬፥፲፫ ) ሊቃውንት አባቶች በትርጓሜ ይህ ልጅ ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ተርጉመውልናል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ጌታችን በተያዘበት ምሴተ ሐሙስ ተከትሎትም ነበር ‹‹… ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር…..›› (ማር. ፲፬፥፶፩ ) ይህ ጎበዝ የተባለውም ቅዱስ ማርቆስ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስ የቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር፤ጌታችን የሐዲስ ኪዳን ቁርባን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠበት ቤት እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ለአንድ መቶው ሃያ ቤተሰብ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሲልክ፤ ( ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት) በማርቆስ እናት በማርያም ባውፍልያ ቤት በነበሩ ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ቤታቸው የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ተብላለች፡፡


ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹…ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው፤ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› በማለት አዘዛቸው፤(ማቴ.፳፰፥፳) ቅዱሳን ሐዋርያትም ዓለምን ዞረው እንዲያስተምሩ ባዘዛቸው መሠረት ለማስተማር ሲሄዱ ቅዱስ ማርቆስ መጀመሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ከዚያም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር አብሮ ተጉዟል፤ ከእነርሱም የማስተማር ልምድን ከወሰደ በኋላ ወንጌልን ለመስበክ ለብቻው ወደ እስክንድርያ ተጓዘ፤ በዚያን ወቅት የእስክንድርያ ከተማ ነዋሪዎች የጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፤ ወደ ከተማው ከገባ በኋላ እንዴት አድርጎ ሕዝቡን እንደሚያስተምር ሲዘዋወር ያደረገው የጠፍር ጫማው ተበጠሰ፤ ወደ ሰፊም ሄደ፤ ጫማ ሠሪውም እየሰፋ ሳለ እጁን ወስፌ ወጋው፤ ከዚያም ‹‹ኤስታኦስ›› አለ ! በዮናናውያን ቋንቋ ‹‹ኤስታኦስ›› አንድ አምላክ ማለት ነው፤ ቅዱስ ማርቆስም ከጫማ ሰፊው ይህንን በመስማቱ ጠጋ አለና‹‹ አንድ አምላክን ታውቀዋለህ?›› አለው ሰውየውም ሲሉ እንደሚሰማ እንጂ ምን እንደሆነ እንደማያውቅ ገለጸለት፤ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ የታመመ እጁን በተአምራት ፈወሰለት፡፡
ከዚያም ወንጌልን አስተማረው፤ እውነትን አሳውቆ ከጣዖት አምልኮ መለሰው፤ ሰውየውም ደስ ብሎት ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ቤተሰቦቹንም አስተምሮ አጠመቃቸው፤ብዙዎችም ከተሳሳተ መንገድና ከጣዖት አምልኮ ተመለሱ፤ የዚህ ሰው ቤትም በእስክንድርያ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ሆነች፤ ብዙ ሰዎችም በክርስትና እምነት አመኑ፡፡ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሌላ ሀገርም ለማስተማር ተጓዘ፡፡


ከብዙ ጊዜ በኋላ ያመኑት ምእመናን (ክርስቲያኖች) የትንሣኤን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በደረሰ ጊዜ አብሯቸው እንዲያከብር ቅዱስ ማርቆስን ጠሩት እርሱም በመጣ ጊዜ ጣዖት አምላኪዎች ያዙት፤ ከዚያም ጣዖት አምላኪዎቹ ቅዱስ ማርቆስን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሠረገላ ጋር አሥረውት መሬት ለመሬት ይጎትቱት ጀመር፤ ብዙ ካንገላቱት በኋላ ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) በ፷፰ (ስድሳ ስምንት) ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ አላውያኑም የቅዱስ ማርቆስን ክብርት ሥጋ ሊያቃጥሉ ሲሉ ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ በተናቸው፤ክርስቲያኖቹም በክብር አንሥተው በቤተ ክርስቲያን ቀበሩት፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል …›› ባለን መሠረት ምእመናን በረከቱን እናገኝ ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ማርቆስን የዕረፍት መታሰቢያ በዓል ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ) ቀን ታከብረዋለች፡፡ (ማቴ.፲፥፵፪) በረከቱ ይደርብን፤

አምላከ ቅዱስ ማርቆስ በረከቱን ያድለን አሜን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

ጌታዬ ፡ አምላኬም

  በሙታን መነሳት ከማያምኑ ሰዱቃውያን ወገን የነበረው ዲዲሞስ የተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የሚታወቀው የጌታችንን ከሞት መነሳት ከአሥሩ ሐዋርያት በሰማ ጊዜ ችንካሩን ካላየና ካልነካ እንደማያምን በተናገረው በኋላ ግን ዳግመኛ እርሱ በተገኘበት በዝግ ቤት ተገልጦ ጌታችን መሻቱን ሲፈፅምለት እጁ ተኮማትሮ ፣ ማመንን አምኖ ” ጌታዬ ፡ አምላኬም ” ብሎ በመመስከሩ ነው።

    በሮማና በፐርሺያ መካከል ይኖር የነበረ የዑር (ኤዴሳ) አብጋር ዑካማ (አብጋር-ጃንሆይ እንደማለት ነው) የተባለ ገዢ  በጠና ታሞ ነበርና የጌታችንን የማዳን ዝና ከግሪክ ነጋድያን በመስማቱ እርሱም ፈውስን ከእጆቹ ያገኝ ዘንድ ለጌታችን በሐዋርያው እንድርያስ አገናኝነት ጌታችንን ባገኙት ግሪኮች ለላከለት መልእክት ምላሽ ከትንሣኤው በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱን ይልክለት ዘንድ ቃል ገብቶለት ነበርና ከዕርገቱ በኋላ ቅዱስ ቶማስን ወደ ዑር ልኮታል።  ቅዱስ ቶማስ ወደ ሕንድ ተጉዞ ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነውን ታዴዎስ በላከው መሰረት ይህን ንጉሥ ፈውሶ ሀገሩን ባርኮ ፣ ብዙ ሰዎች ተጠምቀው ክርስቲያኖች ለመሆን በቅተዋል፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ተተክለውም በምሥራቅ እስያ የመጀመሪያይቱ የክርስቲያኖች ከተማ መሆንዋ በታሪክ ተጽፏል።

በሀገረ ሕንድ በታክሻሲላ ከተማ የነበረ ንጉሥ ጎንዶፓረስ በኢየሩሳሌም ስለነበረው የሰሎሞን ቤተ መንግሥት ዝና ይሰማ ነበረና የታወቁ ግንበኞችን እንዲያመጡለት ነጋድያንን ባዘዘው መሰረት ቅዱስ ቶማስን ወደ ሕንድ ሲጓዝ በመንገድ ያገኘው አንድ ነጋዴ በኢየሩሳሌም በግንበኝነት ሙያ ይተዳደር እንደነበር ነግሮት ነበርና ከንጉሡ ጋር ለቤተ መንግሥቱ ስራ እንዲዋዋል ያደርጋል። ንጉሡም ባሳየው ሰፊ ሜዳና ጫካ ምኞቱ ይፈጸምለት ዘንድ በየጊዜው የሚሆኑ ብርና ወርቅ ፣ ለሰራተኛ መቅጠሪያ እና እብነበረድ እንዲሁም ብረትና እንጨት መግዣ የሚሆን ገንዘብም ይልክለት ነበር። ቅዱስ ቶማስ ግን ወደ ድኾች መንደር በመዝለቅ ይመጸውተው የመንግሥተ ሰማያትንም ወንጌል ማስተማሩን ቀጠለበት።

የኋላ የኋላ ይህን የጓጓለትን ቤተ መንግሥት መጠናቀቅ ለማየት በሄደ ጊዜ ምንም ባለማግኘቱ የተበሳጨው ንጉሡ አስጠርቶ በጠየቀው ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ” በምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥትን ላያዩ ይችላሉ ፡ በሰማይ ላይ ግን ሰርቼልዎታለሁ” በማለት መልሷል። በዚህም መልሱ ንጉሡ ተበሳጭቶ ወደ ወኅኒ እንዲወርድና እንዲሰቃይ አዘዘ። ያን ዕለት ሌሊት ልዑል ጋድ የተባለ የንጉሡ ወንድም ታሞ ያርፋል ፡ ነፍሱንም መላእክት ማረፊያዋን ባስመረጧት ጊዜ የሚያምረውን ቤተ መንግሥት መረጠች ፡ ከመላእክቱም አንዱ “ይህ ያንቺ አይደለም ፡ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሰራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው” አላት። በዚህ ቅስፈትም የልዑሉ ነፍስ ከሥጋው ተዋሐደች ። ያየውንም ሁሉ ሊቀብሩት ለተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉና ለንጉሡ መሰከረ። ንጉሡም በቅዱስ ቶማስ ላይ ስላደረሰው ግፍ አዝኖና ተጸጽቶ ከወኅኒ አወጣው ፣ ከነቤተሰቡም ተጠመቀ ። በሀገሩ የነበሩ ባለጸጋጎችም ይህንን ለድኾች በመመጽወት የሰማይ ቤተ መንግሥት የመስራት ምሳሌውን ተከተሉ።
  
   ቅዱስ ቶማስ ከሕንድ ማላባር እስከ ቻይና ሰብኳል ፡ በኋላም በሚላፒር አምላክያነ ጣዖት ቆዳውን ገፍፈው ስልቻ በመስራት በሰውነቱ ጨው ነስንሰው ባደረሱበት ግፍና መከራ ሰማዕትነትን ተቀብሏል ፡ አጽሙም በኤዴሳ በክብር አርፏል። መታሰቢያው በቤተክርስቲያናችን ግንቦት 26  ይደረጋል።

ምንጭ:- ኦርቶዶክሳዊ ወጣት

ማዕዶት- መሻገር

ማዕዶት “ዐደወ” ተሻገረ ከሚል የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም መሻገር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ከትንሳኤ ቀጥሎ ለሚገኘው ሰኞ ስያሜ የሆነው ማዕዶት የበዙ ምስጢራትን የያዘ ነው።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና መከራ እኛ የሰው ልጆች ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻግረናልና ማዕዶትን እናከብራለን።

በዚህ ቀን በዋነኝነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከስጋው በሥልጣኑ ለይቶ ክብርት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ በሲኦል የምስራቹን ቃል እርሱም የተስፋ አበው ፍፃሜን መስበኩና ሙታንን ከሲኦል ማውጣቱ የሚታሰብበት እለት ነው።

በእርግጥ ይህ ሁነት የተከናወነው እጅግ የበዛ ምስጢራትና ተአምራት በተከናወነበት በእለተ አርብ ቢሆንም መሻገር ትፍስሕት ነውና ቤተክርስቲያን ከትንሳኤው በኋላ ባለው የመጀመሪያ ቀን በሲኦል የነበረው የእዳ ደብዳቤ መቀደዱን ታከብራለች።

ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ በሲኦል ቅድስት ነፍሱ ያደረገችውን ስብከት እንዲህ ይነግረናል:- ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው። 1ኛ ጴጥ 3:18-19

የቤተክርስቲያን መምህር የሆነው አፈ በረከት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የክርስቶስን በሲኦል መውረድና ነፍሳትን ማሻገር ከጨጓራ አለመስማማት ጋር (gastronomic analogy) አመሳስሎ እንዲህ ይለዋል:-

‹‹የክርስቶስን ሰውነት በመቀበሉ ሞት ታላቅ ስኅተት ሠራ፡፡ ይህ ሰውነት በእርሱ የገዥነት ሥልጣን ሥር ያለ ተራ ሰውነት ፣ ኃጢአተኛ የሆነና የሚሞት ሰውነት መስሎት ነበር፡፡ ከሰውነታቸው ጋር የማይስማማ ምግብን የበሉ ሰዎች ሲያስመልሳቸው የሚያወጡት አልስማማ ያላቸውን ምግብ ብቻ ሳይሆን የበሉትን ነገር ሁሉ ነው፡፡ በሞትም ላይ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሞት ፍጹም ንጹሕና የማይሞት የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ዋጠ ፤ የማይሞተው ሕያዉ ክርስቶስ ለአልጠግብ ባዩ ሞትና ሲኦል የሚመር እና የማይስማማ ምግብ ሆነበት፡፡ ሊስማማው ስላልቻለም ተፋው ፤ ከክርስቶስ ሥጋ ጋርም ሲኦል ሆድ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ውጦ የያዘውን ሙት ሁሉ አብሮ ተፋ፡፡ ለሞት የሚስማማው ብቸኛ ምግብ ኃጢአት ብቻ ነው፡፡ ኃጢአት የሌለበት የጌታ ሰውነት ለሲኦል የማይስማማ ምግብ ነው፡፡


ሞት ሊላመጥ የማይችልን ትልቅ ድንጋይ ዋጠ ፤ ይህ ድንጋይ የማይላመጥ ብቻ ሳይሆን በሆድ ውስጥ ቆይቶ የሚያፈራርስና የሚሰባብር ነው፡፡ ስለዚህ ሞት ‹የማዕዘን ድንጋይ› የሆነውን የክርስቶስን ፍጹም ቅዱስ የሆነ ሥጋ በዋጠ ጊዜ በታላቅ ሥቃይና ድካም ውስጥ ሆኖ ጥንካሬዎቹን ሁሉ አጣ፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም› ያለው፡፡ (ሐዋ.፪፥፳፬) የትኛዋም ሴት ልጅ ለመውለድ ምጥን ባማጠች ጊዜ ሞት የክርስቶስን ሥጋ ይዞ የተጨነቀው ያህል ተጨንቃ አታውቅም” በእርግጥም መብላት የሌለበትን መብል የበላው አዳምን ካጋጠመው ደዌ ይፈውስ ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ በሞት ተበላ። ዕፀ በለስ ለአዳም ባህርይ ባለመስማማት ሁሉንም እንዳሳጣችው ክርስቶስን የዋጠ ሲኦልም ለባህርዩ የሚስማማ አልነበረምና ሁሉንም አስተፋው።

ሌላኛው የቤተክርስቲያን ኮከብና ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ይሄንን በክርስቶስ ከተደረገ ታላቅ ምሥጢር በኋላ ሞት ያጣውን ክብርና ነፃነት በሰውኛ ዘይቤ እንዲህ ያናግረዋል:-

‹‹ሞት እንዲህ አለ ፡- ‹‹ይህ ማን ነው? የማንስ ልጅ ነው? እኔን ድል የነሣኝ ይህ [ኢየሱስ የተባለ] ሰው ከየትኛው ቤተሰብ የተገኘ ይሆን? የትውልዶች ሁሉ የዘር ሐረጋቸው የተዘረዘረበት መጽሐፍ በእጄ ላይ አለ፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩት ሰዎች ስም አንድ በአንድ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ከእኔ ያመለጠ [ያልሞተ] አንድም ሰው የለም፡፡ ነገድ በነገድ ሁሉም በክንዶቼ ላይ ተጽፈዋል…

…. በእርግጥ አልዋሽም ፤ የሁለት ሰዎች ስም ብቻ ከእኔ ዘንድ የለም ፤ ሄኖክና ኤልያስ ወደ እኔ አልመጡም … በመላው ምድር ሁሉ ዞሬ ፈለግኋቸው ፣ ዮናስ እስከ ወረደበት የዓሣ አንበሪው ሆድ ድረስ ወርጄ ፈለግኋቸው፡፡ በገነት ውስጥ ተሸሽገው ከሆነ እንዳልፈልጋቸው የሚያስፈራ ኪሩብ ጠባቂ ሆኖ ቆሟል፡፡ ያዕቆብ መሰላልን ተመልክቶ ነበር ፤ ምልባት ወደ ሰማይ የወጡት በዚያ መሰላል ይሆንን?››

በቅዱሱ ብዕር ሞት ስለሆነው ነገር እንዲህ እያለ መናገሩን ይቀጥላል።

“ሞት እንዲህ አለ ፡- ወደ ሙሴ ዘመን ብመለስ ሳይሻለኝ ይሆን? ሙሴ እኮ በዓልን ደግሶልኝ ነበር፡፡ በግብፅ ፋሲካ የታረደው በግም ከእያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት የበኩር ልጅን ሠጥቶኝ ነበር፡፡ በሙት ላይ ሙት በሲኦል ደጃፍ ተከምረውልኝ ነበር፡፡ ይኼኛው የፋሲካ በግ [ክርስቶስ] ግን ሲኦልን በዘበዘው ፣ ሙታንንም ከእጄ ነጥቆአቸው ወጣ፡፡ ሙሴ ያሳረደው የቀደመው በግ መቃብሮችን ሞላልኝ ፤ ይኼኛው በግ ክርስቶስ ግን ሞልተው የነበሩትን መቃብሮች ባዶ አደረገብኝ››
​‹‹የኢየሱስ ሞት ለእኔ ሥቃይ ነው ፤ ከሞቱ ይልቅ ለእኔ በሕይወት እንዲቆይ በተውኩትና ወደ እርሱ ባልቀረብኩ ይሻለኝ ነበር፡፡ በሌሎች ሰዎች ሞት ደስ ይለኝ ነበር ፤ የእርሱን ሞት ግን ጠላሁት፡፡ በሕይወት ሳለ የሞቱ ሰዎችን አስነሥቶ ነበርና እርሱም ከሞት እንደሚነሣና ወደ ሕይወት እንደሚመጣ ገምቼ ነበር፡፡ እርሱ ግን በሞቱ ሙታንን ወደ ሕይወት ወሰዳቸው ፤ ይዤ ላስቀራቸው ስሞክርም በሲኦል ደጃፍ አሽቀንጥረው ጥለውኝ ሔዱ … ገና አሁን እኔም ስለ ወዳጆቻቸው ሞት የሚያለቅሱ ሰዎችን የኀዘናቸውን ጣዕም ቀመስሁት … ከሰዎች ላይ የሚወዷቸውን በመቀማት የማመጣባቸው ሥቃይ በተራው በእኔም ላይ ወደቀ”። ሶሪያዊው ኤፍሬም እንደተናገረው የክርስቶስ ሞት ምትን ያስደነገጠና ያሸበረ ነበር። አባቱ ቅዱስ ዳዊት ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም እንዳለው ዳግመኛም ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠ እንዳለው (መዝ 16:10፣ መዝ 68:18) በሲኦል ነብሳችን እንዳይቀር የቀኝ ገዢያችንን ሞት ምርኮ ማረከ፣ ለኛም ክቡር የሆነውን ነፃነት ስጦታ አድርጎ ሰጠን። እንደ ሙሴ ከባህረ ኤርትራ ሳይሆን ከባህረ እሳት ያሻገረን እግዚአብሔር ይመስገን።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ።

ቅዱሱ እሳት – የሚያስደንቀው የትንሳኤው ሕያው ምስክር

ክሪስቶስ አንስቲ (Χριστός Ανέστη)ክርስቶስ ተነስቷል ለሚለው ቃል የግሪክ አቻ ነው። ቃሉን በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ በልዩ ልዩ ቋንቋ ደውላቸውን እየመቱ ለከተማዋ ያውጁታል። ከዚህ አዋጅ በፊት ግን የጌታችን የመድኃኒታችንና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ሥጋ ያረፈበት መቃብሩ ከሚገኝበት የትንሳኤው ቤተክርስቲያን በመላው ኦርቶዶክሳውያን የሚጠበቅ አንድ ነገር አለ። – የትንሳኤው ቅዱስ እሳት

እንደ ቤተክርስቲያን ታሪክና በ2016ዓ.ም የእድሜ መመርመሪያ መሳሪያ (OSL) በመጠቀም በአቴንስ ዩንቨርስቲ የተሰራው ጥናትም እንደሚያመላክው የትንሳኤው ቤተክርስቲያን በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን የተሰራ ሲሆን በውስጡም የጌታችንን መቃብር ይገኝበታል። ቤተመቅደሱ የተሰራው ከካልሲየም አለት፣ ከእምነ በረድና ከእንጨት ሲሆን በዓመት ሁለት የትንሳኤ በዓላት (የጎርጎርዮሳዊያንና የኦርቶዶክሳዊያን) በዓላት ይከበሩበታል።

በዚህ ቤተክርስቲያን የቅዱሱ እሳት ተአምር የሚጀምረው  በኛ ከቀኑ አራት ሰአት ላይ ነው። በኢየሩሳሌም ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤትና ና በፓሊስ መምሪያው ትዕዛዝ የእስራኤል ፓሊስ እስከ ቀትር 6 ሰዓት ድረስ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሱን በመፈተሽ ምንም አይነት ተቀጣጣይ ነገር ክርስቶስ በተቀበረበት ዋሻም ሆነ በቤተመቅደሱ እንደሌለ ያረጋግጣሉ። ፍተሻቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሁለት ሙስሊም አባወራዎች ቤተመቅደሱን ቆልፈው በማህተማቸው አትመው ያሽጉታል። በማስከተልም የትንሳኤ ዋዜማ የጸሎት ሥርዓት የሚከናወንበት ሰዓት ሲደርስ በኢየሩሳሌም የግሪክ ሊቀ ጳጳሳት መሪነት የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትሪያርክ፣ የግብፅና የሶሪያ አብያተክርስቲያናት ልዑካንና ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የተሰባሰቡ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን በተገኙበት ሥርዓተ ፀሎቱ ይጀመራል።

የጸሎቱ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ የግሪኩ ፓትሪያርክ ልብሰ ፕትርክናቸውን (ካባቸውንና አክሊላቸውን) አውልቀው ምንም ተቀጣጣይ ነገር አለመያዛቸውን በእስራኤል የፀጥታ ሃይሎች ከተፈተሹ በኋላ 20 በ25 ጫማ (1ጫማ = 0.305 ሜትር)  ስፋት ወዳለው የክርስቶስ የመቃብር ቦታ (ኤዲኪዩር) ሻማ ይዘው ይገባሉ። በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስና በዙሪያው ያሉ መብራቶች ይጠፋሉ። ሁሉም ነገር ፀጥ ብሎ ምዕመናን ቅዱሱን እሳት መጠበቅ ይጀምራሉ። ሊቀ ጳጳሱ በዋሻው ውስጥ ከቆዩ በኋላ ቅዱሱን እሳት ይዘው በመውጣት በመጀመሪያ የአርመኑን ፓትርያርክ ሻማ በመለኮስ እንደየ ክህነታዊ ደረጃቸው ለግብፅና ሦርያ ልዑካን ይሰጣሉ። በመቀጠል እሳቱ ለምዕመናን ሁሉ ይዳረሳል።

የኢየሩሳሌም ከተማም የኢየሱስን ትንሳኤ በሚያውጅ ደውል ይናጣሉ።  እሳቱ በአካባቢው ወደሚገኙ አብያተክርስቲያናት ይሰራጫል። ከዛም አልፎ በፈጣን አውሮፕላኖች ወደ ግብፅ፣ አረመን፣ ሩሲያ፣ ሰርቢያና መሰል ሃገራት ይሰራጫል።

ለ20 ዓመታት የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዱዶሮስ በፈረንጆቹ 1988 ዓ.ም በነበራቸው ቃለ መጠይቅ በጌታችን መቃብር ዋሻ ለብቻቸው ከገቡ በኋላ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ሲናገሩ በጨለማ ውስጥ መንገድ እየፈለኩ ወደ ውስጥ እገባና ከጌታችን መቃብር ላይ ጸሎት አደርጋለሁ። ብዙ ጊዜ ጸሎቱን እንደጨረስኩ አንዳንዴ ደግሞ ደቂቃዎችን ዘግየት ብሎ ልዩ መልክ ያለው እሳት ይመጣል። እኔም ሻማዬን እለኩስና ወጥቼ በመጀመሪያ ለአርመኑ ፓትርያርክ በመቀጠልም ለምዕመናን ሁሉ አሰራጫለሁ። ብለው ነበር።

ስለዚህ ቅዱስ እሳት የተዘገበ ጥንታዊ ዘገባ የዛሬ 1700 ዓመት በ4ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊታዊ መረጃ የእሳቱ መታየትን ወደ 1ኛው ክፍለ ዘመን ይወስደዋል። የኒሳኑ ቅዱስ  ጎርጎርዮስና ቅዱስ ዮሐንስ ደማስዮስ  በትንሳኤው 1 ዓመት ማለትም በ 34ዓ.ም  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን መቃብር እሳቱን ማየቱን ፅፈዋል።

ታሪካዊው ማስረጃ ግን በክርስቲያኖች የተዘገበ ብቻ አይደለም በ964 ዓ.ም የሞተው ሙስሊሙ የአረብ የታሪክ ተመራማሪ ኢብን አል ቃስና በ1000ዓ.ም አካባቢ ኢየሩሳሌምን የጎበኘው አል ባይሩኒም በታሪክ ማስታወሻቸው ላይ እውነትነቱን የዘገቡ ሲሆን በቱርክ ኢስላማዊ መንግስት ትመራ የነበረችው ኢየሩሳሌም በከተማዋ ሱልጣን/አሚርና በከተማዋ ኢማም (ዋና የእስልምና የሃይማኖት አባት) ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚከወንና የከተማዋ መስጊዶች መብራት ጭምር ከትንሳኤው ቤተክርስቲያን ቅዱስ እሳት እንደሚለኮስ ፅፈዋል።

የትንሳኤው ቅዱስ እሳት ለየት የሚያረገው ያለ ለኳሽ መብራቱ ብቻ ሳይሆን የእሳቱም ለየት ያለ ተፈጥሮ ነው። አቡነ ዲዶርዮስም ሆነ ብዙዎች እንደሚናገሩት እሳቱ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ያህል አያቃጥልም። በቅዱሱ እሳት ዙሪያ የተቀረፁ ቪዲዮች እንደሚያሳዩት ምዕመናኑ ያለምንም ጉዳት እሳቱን ሲደባበሱ ያሳያል። ነገር ግን ይሄ ለደቂቃዎች ብቻ የሚቆይ ነው ይላሉ የኦርቶዶክስ ሳይንቲስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ተመራማሪው አባ ገናዲ ዛይድዜ። ራሳቸው በ2016 ዓ.ም የሙቀት መለኪያ (Pyrometer) በመጠቀም ባደረጉት ምርመራ ሊቀ ጳጳሱ እሳቱን ይዘውት ከወጡ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ሲለኩት 42° ሴንቲ ግሬድ (መደበኛ ሙቀት) የነበረ ሲሆን ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ግን የእሳቱ የሙቀት መጠን ወደ 350° ሴንቲግሬድ ከፍ ማለቱን ይገልፃሉ።


በሩሲያ ብሔራዊ የኒዩክለር ጥናት ዩንቨርስቲ የማቴሪያል መካኒክስ ረዳት ፕሮፌሰርና የሂሳብና ፊዚክስ ሊቁ ዶ/ር አንድሪው ፎልኮም በ2008 ከመቃብሩ 15 ሜትር ርቀት ላይ የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ፍሪኩዌንሲ መለኪያ ማሽን (oscilloscope) በመግጠም ባካሄዱት ጥናት ተዓምሩ በሚከናወንበት ወቅት ላይ ብቻ የተለየ የሙቀት ባህርይ (low temperature plasma) እንደሚታይ ጠቅሰው ምርምሩን ባካሄዱበት ወቅት ኢየሩሳሌም በመደበኛ አየር ንብረቷ ላይ እንደ ነበረችና ልኬቱን የሚያዛባ ምንም አይነት ከባድ ነፋስ እንዳልነበር አረጋግጠዋል።

የቤተክርስቲያኑ ዜና መዋዕሎች ደግሞ አንዳች የተለየ ታሪክን ዘግበዋል በፈረንጆቹ 1579 የነበሩት የቱርክ መሪዎች ሊቀ ጳጳሱን ሶፎንያስ 4ኛና ምዕመናኑን ቤተመቅደስ እንዳይገቡና በዓሉን እንዳያከብሩ አገዷቸው። የታገዱት ካህናትና ምዕመናንም ከመቅደሱ በር በስተግራ በቆሙት ሊቀ ጳጳሳቸው ከውጭ ሆነው ሥርዓተ ጸሎቱን አድርሰው እንደጨረሱ ቅዱሱ እሳቱ የቤተክርስቲያኑን ግድግዳ ሰንጥቆ በመውጣቱ ሊቀ ጳጳሱም እሳቱን መለኮስና ለሁሉም ማጋራታቸው ተዘግቧል። እሳቱ የሰነጠቀውም ቦታ አሁንም ድረስ ይታያል።

በስንጥቃቱ ዙሪያ ያጠናው ሩሲያዊው ሳይንቲስት ኢቭጋኒ ሚካኤሎቪችም ይህ ስንጥቃት በአንዳች ሃይል የተፈጠረ እንጂ ሰው ሰራሽ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስ እውቀት እንዲህ አይነት ስንጥቃት  መፍጠር የማይታሰብ መሆኑን ያትታል።

በተአምር በማያምኑ ወይም በሚጠራጠሩ ወገኖች ተአምሩን እንደ አንድ ማጭበርበር ወይም ማታለል (fraud/trick) የሚወስዱት ሲሆን ማጭበርበሩ ተፈጽሟል ሲሉ ሁለት መላምቶችን ያስቀምጣሉ አንደኛው ቤተመቅደሱ ውስጥ የተቀመጠ ወይም ሊቀ ጳጳሱ ይዘውት የሚገቡት ተቀጣጣይ ነገር ይኖራል የሚል ሲሆን ይህ መላምት ውድቅ የሚያደርገው ከሥርዓቱ በፊት በሊቀጳጳሱም ላይ ሆነ በቤተመቅደሱ ላይ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር መደረጉ ነው። ቁጥጥሩ የሚደረገው በቤተክርስቲያኗ ሳይሆን በመንግስት አካላት መሆኑና ፍተሻውን የሚያካሂዱት የክርስቶስን ትንሳኤ የሚክዱት የአይሁድና የእስልምና እምነት ተከታዮች መሆኑ ደግሞ ፍተሻው ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን አመላካች ነው።

ሌሎች ተጠራጣሪዎች ደግሞ በራሱ የሚነደው ነጭ ድኝ (White phosphorus) ይጠቀማሉ ባይ ናቸው የነዚህ ክርክርም ቢሆን ሚዛን የማይደፋ ሆኖ ይገኛል። በመጀመሪያ በፍተሻ ወቅት መያዙ አይቀርም ግን አለፈ እንኳን ቢባል እንደዚህ አይነት እሳት መፍጠር አይችልም።


የካምብሪጅ ዩንቨርስቲው ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ዶ/ር ራሚ ሞርጋን እንደሚናገረው የነጭ ድኝ እሳት የተቀመጠበትን ነገር እያቃጠለ የሚነድ ሲሆን ቅዱሱ እሳት ግን ነገሮችን የማቃጠል አቅሙ ደካማ ነው ይላል። ሌላው ነገር ደግሞ ነጭ ድኝ ከባቢ አየር ላይ ካለው ኦክስጅን ጋር ሲዋሃድ ፎስፈረስ ኦክሳይድ (phosphorus oxide) የተባለ መርዛማ ጋዝ ስለሚፈጥር እሳቱ መርዛማ ይሆን ነበር። ነገር ግን እስካሁን ድረስ አንድም ታሪካዊ ሰነድ፣ አንድም ተጓዥም ሆነ የከተማዋ አስተዳደር በእሳቱ የተመረዙ (የተቃጠሉ) ሰዎች መኖራቸውን ሪፖርተር አድርገው አያውቁም ይላል።

የአቴንስ ዩንቨርስቲ የፍራክቸራል መካኒክ ምሁሩ ጆርጅ ፓፓዶብሎስ “በሳይንሳዊ አነጋገር እሳቱ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም” ይላል።

ፅሁፋችንን ለዚህ ዝግጅት በዋቢነት በተጠቀምነበት የሲዋይሲ የግብፅ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ዶክመንተሪ አዘጋጅ ዶ/ር ሃኒ አሽማላ ሃሳብ እናጠናቅ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ላይ እንደተጠቀሰው ቶማስ የክርስቶስን ትንሳኤ በተጠራጠረ ወቅት ክርስቶስ ናና ሰውነቴን አረጋግጥ ብሎት ነበር ዛሬም በትንሳኤው ህያው ምስክር በቅዱሱ እሳት ዙሪያ የሚጠራጠር ቢኖር መጥቶ እንዲያይ እንጋብዘዋለን።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል።

✨ቀዳም ሥዑር(የተሻረች ቅዳሜ)

ቀዳም ስዑር ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ ትባላለች፡፡

    ቀዳም ሥዑር መባሉ ከወትሮው ዕለታት በተለየ ይህችኛዋ ዕለት በጾም ስለምትታሰብ የተሻረች ቅዳሜ እንላታለን፡፡

ለምለም ቅዳሜ መባሏም ካህናቱ የምሥራች አብሳሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ ምእመናን ቤት ስለሚሔዱ ለምለም ቅዳሜ ትባላለች፡፡

  ቅዱስ ቅዳሜ መባሉም ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን በጥንተ ተፈጥሮ ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው በዕለተ ዐርብ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ከሥራው ያረፈበት ዕለት ናት፡፡

   በዘመነ ሐዲስም የማዳን ሥራውን አከናውኖ በከርሰ መቃብር አድሮ በአካለ ነፍስም ሲዖልን በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበት ዕለት በመሆኑ ቅዱስ /ልዩ/ ቅዳሜ ተብላ ተሰይማለች፡፡ ዕለቱ ዝርዘር አድርገን ስንመለከተውም ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፤ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ስላረፈባት ሰንበት ዐባይ (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች (ዘፍ. 1፡3)

   ይህችን ታላቋን ሰንበትም እንዲያከብሯት ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን ታዘው ነበር፡፡
ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የድኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፍጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደተደረገባት ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በሐዲስ መቃብር አርፎባታል (ማቴ. 27፡61)፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ በምሥጢር ከሰንበት ዐባይ ጋር ትገናኛለች፡፡
ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ) የተሰኘችውም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡

   እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ መምህራቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ነገረ ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

   ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በሐዘን፣ በጾምና በጸሎት ዕለቷን እንዳከበሯት ክርስቲኖችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል፣ አሊያም ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም የጌታን ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡

   የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም ”ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፣ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት ምእመናንም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡

    የዚህ የቄጠማው ታሪክ መነሻው የኖኅ ዘመን ታሪክ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች በማየ አይህ ከጠፉ በኋላ የውኃውን መጉደል እንድትመለከት የተላከች ርግብ የምሥራች ምልክት የሆነ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ ተመልሳለች፡፡ በዚህም የውኃው መጉደል፣ የቅጣቱ ዘመን ማለፍ ተረጋግጧል (ዘፍ. 9፡ 1-29)፡፡

    ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነው ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፣ በጣታቸው ቀለበት ያደርጉታል፡፡

የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲዖል (የሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

   ምንጭ :- አትሮንስ ዘተዋህዶ

🏡ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/

ተፈፀመ

ጊዜ ተስዓቱ ሰዓት
አጽንኖ ርእሱ ኢየሱስ
ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ

ለሦስት ሰዓታት በመስቀል ላይ የቆየው ጌታችን የተናገራቸው ሰባት ንግግሮችን ብቻ ነበር። በዙሪያው ሳያቋርጡ የሚጮኹ ሰዎች በተሰበሰቡበት እርሱ ግን እርሱ ሰዊ፣ እርሱ ተሰዊ (መስዋዕት)፣ እርሱ መስዋዕት ተቀባይ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክነቱን በሰባት ወሳኝ ቃላት ብቻ ተናገረ።

ቃላቱ ለብቻቸው በብዙ የሚተነተኑና የሰፉ ቢሆንም የተወሰነ አይተናቸው ወደ ርዕሳችን ተፈጸመ እንመለሳለን።

ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ ማቴ.27፤46

ዳግማዊው አዳም የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ፈንታ መስዋዕት አቅራቢ ሆኖ የአዳምን ጩኸት ጮኸለት።

አባት ሆይ የሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው፤ ሉቃ.23:34

መስዋዕትን የሚያቀርብ ሊቀ ካህን ስለህዝቡ ይቅርታ እንዲለምን  እንደ መልከጸዲቅ የዘለዓለም ሊቀ ካህን የሆነ ክርስቶስ ስለ ህዝቡ ሁሉ ሃጢአት ልመናን ያቀርብ ዘንድ ይቅር በላቸው አለ።

አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፡፡ ሉቃ.23፤46

የአለምን ሃጢአት የሚያስተሰርይ አማናዊ በግዕ እንደሆነ የተመሰከረለት ክርስቶስ መስዋዕትነቱን ሲገልፅ ይህን ተናገረ። አባ ህርያቆስ እንደተናገረው ወየው የሚናገር በግ እንደምን ያለ ነው??

እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ ሉቃ.23፤43

በድካሙ ተሳልቀው በሕማሙ በሚቀልዱ መሐል የክርስቶስን አምላክነት የተረዳው በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ባለው ጊዜ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሆኖ ፈረደለት።

ተጠማሁ፤  ዮሐ.19፤30

ለፊያታዊው በገባለት ቃል አምላክነቱን መግለፅ የወደደ ክርስቶስ ሰውነቱን ይገልፅ ዘንድ ተጠማሁ አለ። በመዝሙረኛው ዳዊት የተነገረ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ተጠማው አለ ሀሞትና ከርቤም ቀላቅለው ሰጡት።

እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ፤ ዮሐ.19፤26-27

በእለተ ሐሙስ ሁሉንም በስምህ ጠብቃቸው ብሎ ለአባቱ አደራ የሰጠው ጌታ በዕለተ አርብም ከመስቀሉ ሥር የተገኘውን ሐዋርያ ዮሐንስን ለእናቱ በአደራ ሰጣት። በበዛ ሃዘን ውስጥ ያለችውን እናቱን ያፅናና ዘንድ በተሰጠው በአንፃረ ዮሐንስ ለምዕመናን ሁሉ ለቤተክርስቲያንም እናት ትሆን ዘንድ ሰጣት።

ተፈጸመ፤ ዮሐ.19፤30

ወደ ጠቅላዩ ቃል እንመለስ። የሕማሙ ምስክር የሆነ ዮሐንስ ተፈፀመ ብሎ ከተናገረ በኋላ ራሱን አዘንብሎ ነፍሱን እንደሰጠ ይነግረናልና ይህቺ በመስቀል የተናገራት የመጨረሻ ቃል ናት።

ለመሆኑ የተፈፀመው ምንድነው?

1. ከእግዚአብሔር አብ የተላከበት ተግባር ተፈፀመ

ምንም እንኳን የክርስቶስ መምጣት የማይነጣጠል የሥላሴ ፈቃድ ቢሆንም ቃል ከልብ እንደሚወጣ እርሱም ከእግዚአብሔር አብ የወጣ ነውና ከእግዚአብሔር አብ ወደ ምድር የመጣበትን ተግባር ስለ መፈፀሙ ተፈጸመ ብሎ ተናገረ። አስቀድሞ በዕለተ ሐሙስም ይህን የመሰለ ቃል ተናግሮ ነበር።  “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤” ዮሐ 17፥4

2. ይሰራው ያለው ፅድቅ ሁሉ ተፈጸመ

በባሕረ ዮርዳኖስ ከመንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ጋር ሲነጋገር “ አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና (ማቴዎስ 3፥15) እንዳለው በሥጋው ወራት ይፈጽም ዘንድ ያለውን ሁሉንም የፅድቅ ስራ ፈጽሟልና ተፈጸመ አለ።

3. ዘመነ መርገምና ፍዳ ተፈፀመ

የቀደመው የሰው ልጅ በድሏልና በበደሉ የመጣበት እርግማንን አስወግዷልና የአዳም ዘመነ ፍዳ ተፈፀመ

“በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤” ቆላ 2፥14

4. የሐጢአትና የሞት ገዢነት ተፈፀመ

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” 1ኛ ቆሮ 15፥55 እያለ ይጠይቃል። ትናንት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎችን ይወጋበት የነበረው ዘመን ተፈጽሟልና ተፈፀመ አለ።

5. የነቢያት ትንቢትና ልዩ ልዩ ምሳሌያት ተፈፀመ

የወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን አስቀድሞውንም በብዙ ምሳሌያትና ህብረ አምሳላት የተነበረ ነበር። ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ በኦሪትና በነብያት የተነገሩት ሁሉ ተፈጽመዋልና ተፈፀመ አለ።

6. በመስቀሉ የሰራው የአስታራቂነት ስራ ተፈጽሟልና ተፈፀመ አለ

ዝንጉዖች ዛሬም ይማልድልናል እንደሚሉት የዘወትር አማላጅነት የሚፈጽም አይደለምና አንድ ጊዜ የማስታረቅ ስራውን ፈጽሟልና ተፈፀመ አለ። ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያጠይቅ ” ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ” ዕብ 9:10-11 ብሎ ተናገረ።

“ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።” ዮሐ 19፥30

ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ

ተሰቀለ

ጊዜ ስድስቱ ሰዓት
ሰቀልዎ ለኢየሱስ
ማዕከለ ክልዔ ፊያት

ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ ያንገላቱትን የክብር ንጉስ በመስቀሉ ላይ ሰቀሉት። ቅዱስ ጳውሎስ ቢያውቁስ ኖሮ የክብር ንጉስን ባልሰቀሉት ነበር እንዳለ (1ቆሮ 2:8) ዝንጉዎች በመስቀል ላይ ሰቀሉት።

መጽሐፋቸው በእንጨት የሚሰቀል የተረገመ ነው እንዲል (ዘዳ 21:23) ያዋርዱት ዘንድ በእንጨት ሰቀሉት ነገር ግን በእንጨት መሰቀሉ የእነርሱ ሳይሆን ከዘመናት በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ አስቀድሞ በሙሴ ዘመን የተሰራውን የነሐሱ እባብ ሕብረ አምሳል ምሳሌነቱ ስለራሱ እንደ ሆነ እንዲህ ብሎ ሲናገር እናገኘዋለን።

“ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።”
   ዮሐ 3፥14-15

በእርግጥም ያ የነሐስ እባብ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ ነበር። ፍጡሩ እባብ እንጂ የእባብን መልክ ገንዘብ ያደረገ ነሐስ በባህሪው መርዝ እንደሌለበት የሀጢአተኛን ሰው መልክ ገንዘቡ ያደረገ ክርስቶስም ሃጢአትና በደል የሌለበት ንፁሀ ባህሪ ነው።


ከሆሳዕና መልስ እስከ ሊጦስጥራ ይጠይቁትና ይፈትኑት የነበሩ አይሁዳውያን ሊቃውንትም ሆነ ሮማውያን ባለስልጣናት አንዳች ሀሰት ከአንደበቱ፣ ጥቂት ስህተትም ከስርዓቱ ያላገኙበት አማናዊው የነሐሱ እባብ ክርስቶስ ተሰቀለ።

እግዚአብሔር ሙሴ ስለሰራት የነሐስ እባብ እንዲህ ብሎ ነበር

“ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው።”
  ዘኍ 21፥8

እስራኤል በበደለ ወቅት ወደ ህዝቡ ከተሰደዱ የሚናደፉ እባቦች ህዝቡ ይጠበቅ ዘንድ የነሐሱን እባብ ለሙሴ እንዲሰራ ያዘዘው እግዚአብሔር ወደ እርሱ የሚመለከት ሁሉ በሕይወት እንደሚኖር ተናግሮ እንደነበር ሁሉ በቀራንዮ በሁለት ወንበዴዎች መሀል ወደ ተሰቀለው ንጉስ ክርስቶስ በአይነ ልቦናው የሚያይ ሁሉ ይድን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቀለ።

በዕፀ በለስ የጠፋውን የሰው ልጅ በዕፀ መስቀል ይመልሰው ዘንድ ለሚፈሩትም ሁሉ ከጠላት ፊት የሚያመልጡበትን ምልክታቸውን በደሙ ባርኮ ይሰጣቸው ዘንድ መድኀኒታችን ተሰቀለ።

በነቢይ ኢሳያስ (ኢሳ 53) እንደ ተተነበየው ትንቢት በደላችንንና መርገማችንን ያስወግድ ዘንድ የዋሁ ክርስቶስ ተሰቀለ። ሊቀካህናቱ ክርስቶስ ስለሁሉ ሃጢአት መስዋዕት ይከፍል ዘንድ መሰዊያው ወደ ምትሆን መስቀል ወጣ፣ ንጉስ ክርስቶስ የሞትን መንግስት ገልብጦ ነግሷልና ዙፋኑ ወደ ምትሆን መስቀል ከፍ አለ። ፈራጅ ክርስቶስ የአዳምን ነፃነት ይበይን ዘንድ በመስቀል የችሎት መንበሩ ተሰየመ።

የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያሳይ ዘንድ አይሁድ ከመስቀል ውረድ አሉት እሱ ግን መስቀልን የርሱ መውረጃ ሳይሆን የኛ መወጣጫ እንዲሆን ፈቀደ

እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።
³³ በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ።

ዮሐ 12: 22-23

ንዑድ ጳውሎስ እንደተናገረው አይሁድ ባይረዱትም ፀሐይ በመጨለም፣ ጨረቃ በመድማት፣ ከዋክብት በመርጠፍ አለት በመሰነጣጠቅ፣ መቃብር በመከፈት፣ ሙታን በመነሳት የእግዚአብሔርነቱን ክብር ተናገሩለት።

በመስቀሉ በሰራው ሀዲሱ ኪዳን  የህዝብና የአህዛብ ቤት ስለምትሆን ቤተክርስቲያን የኦሪቱ ቤተመቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለች።

ነገር ግን ይህንን ከተውልዱ ማን አስተዋለ? ቢያስተውሉስ የክብርን ንጉስ ባልሰቀሉት ነበር። እነርሱ ግን በሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራትናሮዳስ በተሰኙ ቅንዋት (ችንካር) ቸነከሩት። አለማወቃቸውን ግን አስቀድሞ ያውቅ ነበርና የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ተናገረ።

ጌታ ሆይ ባለማወቅ በሃጢአት ችንካር የምንቸነክርህ እኛን ስለተቀበልካቸው ሕማማተ መስቀል ብለህ ይቅር በለን።

13ቱ ሕማማተ መስቀል

1ኛ. ተአስሮ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)
2ኛ. ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)
3ኛ. ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ)
4ኛ. ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድ መረገጥ)
5ኛ. ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋር መላተም)
6ኛ. ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
7ኛ. ተቀሰፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)
8ኛ. ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)
9ኛ. አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)
10ኛ. ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)
11ኛ.  ተቀንዎ በቅንዎት (በችንካር መቸንከር)
12ኛ.  ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይ መሰቀል)
13ኛ. ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞትን መጠጣት)