ወርኃ ሰኔ እና የተማሪዎች ምርቃት

ወርኃ ሰኔ ሲመጣ ከሚስተዋሉ ሀገራዊ ክስተቶች መሃል አንዱ የተማሪዎች ምረቃ ነው። ከፊደል ጋር ያላቸው ትወውቅ ሰምሮ “እደጉ፣ ተመንደጉ፣ ለትልቁ ምረቃ ያብቃችሁ” ተብለው ከሚመረቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሕፃናት ጀምሮ ለዓመታት በለፉበት የትምህርት ዘርፍ “በቅታችኋል፤ ሂዱና አንፀባርቁ” እስከተባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ድረስ  በጥቁር ቀሚስና መነሳንስ ደምቀው የትምህርት ደረጃና ዓይነቱን በሚገልጡ ኅብረ ቀለማት ባላቸው ሪባን ተውበው በየተቋማቱና በየመንገዱ ይታያሉ።

የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዓምድም  የምድብ ተራውን ጠብቆ በሳምንቱ ዕለተ ዐርብ ተመልሷል። ለዚህ ሳምንት ያደረሰን አማኑኤል ይመስገን፣ እያልን በዚህ ሳምንት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታዊና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን  ማስመረቃቸውን ተከትሎ በቤተክርስቲያን የምሩቃን ሱታፌን ለማሰስ ተሰናድተናል። መልካም ቆይታ።

የአስኳላ ትምህርት ወደ ሃገራችን ብቅ ከማለቱ በፊት እንደ ትምህርት ሚንስቴር ሆና ትውልዱን የማስተማር ሸክምን የተሸከመችው ቤተክርስቲያን በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የዘመናዊ ትምህርት “ሀሁ” ሲጀመር ነበር ከምዕራብ በተቀዳ ትምህርት በሰከሩ ልጆቿ እንደ አላስፈላጊ ነገር መገፋት የጀመረችው።

ኦርቶዶክስ ክርስትና ኋላ ቀርነት በአንፃሩ ምዕራባውያኑ የካቶሊክ እና የወንጌላውያን እምነቶች ዘመናዊነት ተደርገው መሳል ጀመሩ። ከኢትዮጵያና ከቤተክርስቲያን ጋር የተገናኙ ነገሮች ሀሉ ተነወሩ። መምህር ዐሥራት የኔ ሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” በሚለው መጽሐፍ እንደገለፁት የተማረው ትውልድ የብብቱን ጥሎ የቆጡን ማሰስ ጀመረ።

በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትና ሱታፌ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮች በ”ዘመናዊ ትምህርት ያስፈልጋልና አያስፈልግም” በሚሉ ፅንፎች መሃል የሚደረግ እሰጥ አገባ ሆነ። በኋላ ላይ ሁለቱን የሚያስታርቁ እንደ ዶ/ር እጓለ ብርሃን ያሉ በቤተክርስቲያን ትምህርት የታነፁ በዓለም ትምህርት የዳበሩ ልሂቃን ወደ መድረኩ በመምጣት ሁለቱን የማስማማት ዐሳብን ማንሳታቸው ለሁለቱ ዘርፎች እፎይታን መፍጠር ችሎ ነበር፡፡

በዚህ የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮ ላይ ምንም እንኳን የተካረረ አተካሮ በቤተክህነት ልሂቃንና በ”ምሁራን” መሐል ቢደረግም ቤተክርስቲያን ለዘመናዊ ትምህርት ያበረከተችው አስተዋጽዖም አናሳ አይደለም። ትምህርት ቀርፃ ግብረ ገብን በመስጠት ተማሪው ሥነምግባር ያለው ዜጋ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የእስክንድርያና የአርመን ቤተክርስቲያን ልጆች ወደ ሃገር መጥተው ማስተማራቸው የሚጠቀስ አበርክቶ ነው። በከተማ እስከ ቅርብ ዘመን ከቅድመ አንደኛ ትምህርት በፊት የሚሰጠው የፊደልና የቁጥር ትምህርት ሥርዓትም (በተለምዶ ቄስ ትምህርት ቤት) የሚዘለል አስተዋጽዖ አይደለም።

የዘውዳዊ ሥርዓቱ ወደ መውደቅ ካዘነበለበት ወቅት ጀምሮ ደግሞ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ኅብረተሰባዊነት /ኮሚዩኒዝም ዐስተሳሰብ እየተሳበ ሃይማኖት ጠልነት እየተጫነው በመምጣቱ ትምህርት፣ የሚጠረጠር እና የሚብጠረጠር እንክርዳዱ ጎልቶ መታየት ጀመረ። “የተማሩ” የተባሉት ሰዎች ፓትርያርክ እስከ መግደል፣ ጳጳሳት እስከ ማባረር፣ ካህናትን እስከመስደብና ቤተክርስቲያንን እስከማንቋሸሽ በደረሱበት በዚያን ወቅት ዓለም ከቤተክርስቲያን የተስማማችላቸው ወጣቶች ከየአካባቢው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። በተለያዩ ከተሞች በማኅበራት እየተሰባሰቡ  ለቤተክርስቲያን ዘብ በመቆም በርካታ ሥራዎችን መሥራት ችለዋል። በኋላም ከእነዚህ ማኀበራት አብዛኛዎቹ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤትነት ተለውጠዋል።

በቤተክርስቲያንና በዓለሙ ትምህርት በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከለወጡ ቀዳምያን መካከል የወሊሶው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዲዮስቆርስና የዝዋዩ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ብፁዓን አባቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ኮሌጆችና ዩንቨርስቲዎች የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በማሰባሰብ ያስተምሩ ነበር በኋላም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረቱን ያደረገው ማኅበረ ቅዱሳን እንዲወለድ ሆነ፡፡ የማኅበሩ መከሰት በርካቶች በዓለማዊው ትምህርት ሰበብ ከቤተ ክርስቲያን እንዳይርቁ እንደውም ይበልጥ እንዲቀርቧት፣ እንዲያይዋትና እንዲወዷት መንገድ የከፈተ ነበር፡፡ ማኅበሩ ወደ አርባ በተጠጋው ዕድሜው በርካታ ቁጥር ያላቸውን ካሕናት፣ መምህራንና ዘማርያንን ከማፍራት ባሻገር ቤተ ክርስቲያን ግድ የምትላቸው ከሚንስትር ጀምሮ በተለያየ የኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ለቤተ ክርስቲያን የማደክሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ መስነፍን የማያውቁ በልዩ ልዩ ዘርፍ የሚሳተፉ ተመራማሪዎች፣ ባለሞያዎችን እንዲወጡ በማድረግ ሀገራችን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬዎች ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ይህ የማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ከተመረቁ በኋላ ኦርቶዶክሳውያን ምሩቃንን የመጠበቅና ወደ አገልግሎት የማሰማራት ልማድ ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት አንጻር ዝቅተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የህንድና የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሚያደራጇቸው የሞያ ማኅበራት አማካኝነት የምሩቃንን ዓለማዊ ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም በሚጠቅም መልኩ ያደራጁታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማድ በኢትዮጵያ ስንመጣ ግን አነስተኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድና በማኅበረ ቅዱሳን ከተደራጁ የሞያ አገልግሎቶችና የሠራተኛ ጉባዔያት ባሻገር በራስ ተነሳሽነት ከተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህክምና ማኅበርና በ፳፻፲፭ ዓ.ም. ከነበረው ሕገ ወጥ ሹመት ማግስት ብቅ ብሎ ከነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሕግ ባለሞያዎች ኅብረት ውጪ ያሉ ጎልተው የወጡ ሞያዊ ማኅበራት ውስን ናቸው፡፡

በዓለማዊ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁና በሥራ ላይ የተሰማሩ የቤተክርስቲያን ልጆች በሞያቸው አይተኬ ሚና እንደሚኖራቸው የማይካድ ነው፤ በተለይም:
•  በሕግና ዲፕሎማሲ፣
•  በምጣኔ ሀብትና የሀብት አጠቃቀም፣
•  በቴክኖሎጂና በዲጂታል ተልእኮ፣
•  በትምህርትና ሥልጠና፣
•  በጥበበ-ዕድ እና ምርታማነት፣
•  በጤናና ማኅበራዊ አገልግሎት፣
•  በጥናትና ምርምር እንዲሁም በመሳሰሉት ቤተ ክርስቲያንን መራዳት እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ በይበልጥ ደግሞ አሁን ላይ ቤተ ክርስቲያን እየተቸገረችባቸው የሚገኙትን፣
•   ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው ባላቸው ውስን አቅም የተወሰኑ ምርቶችን እያመረቱ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት ከእርዳታ ተላቀው ራሳቸውን ማስቻል፣
•  በሀገር ውስጥና ከሃገር ውጪ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎችና ሕጋዊ መብቶቿን ማስጠበቅ፣
•  ከቴክኖሎጂው ጋር አብሮ የሚሄድ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት፣
•  ያላትን ሰብአዊና ምጣኔ ሃብታዊ አቅም በአግባቡ እንድትጠቀምና አስተዳደሯን ለማዘመን፣
•  በማኅበራዊ አገልግሎት ብዙዎች ጋር በመድረስ የበጎ ፈቃድን ወንጌል ለተገፉትና ለተጎዱት ሁሉ ለማዳረስ የምሩቃኑ ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡

በመሆኑም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ምሩቃንን ወደ ቤተ ክርስቲያን በማቅረብ፣ በማስተማር በማነጽና ከምስጥራት ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ለቤተክርስቲያን የልጅነት ግዴታቸውን እንዲወጡ እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረብንና ተመራቂዎች ከጥቁሩ ልብስ ደስታ ወደ ሰማያዊው ነጭ ልብስ ምረቃ የሚያሸጋግር ሕይወትን እየተመኘን  እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የዛሬውን ዓምድ በዚህ ቋጨን።

የምስጋና ሕይወት

የምስጋና ሕይወት የሚኖር ሰው የተደረገለትን ሥራ እና የተፈጸመለትን መልካም ነገር ሁሉ የማይረሳ ለዚህም ምስጋናውን በደስታ የሚገልጽ አዋቂ ሰው ነው፡፡ ለእግዚአብሔር እና ለሰዎች የሚያቀርበው ምስጋና በልቡ ጽላት ላይ ተጽፎ የተቀመጠ በመሆኑ ምስጋና ከአንደበቱ ፈጽሞ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ካነጻቸው ከዐሥሩ ለምጻሞች መካከል አንዱን ባርኮታል፡፡ ከእነርሱ አንዱ እንደተፈወሰ ባየ ጊዜ “በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ” ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት ሄዱ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም” አለ፡፡ ሉቃ ፲፯÷፲፭-፲፰ ስለዚህ ለተደረገልህ ነገር ምስጋና ስታቀርብ እግዚአብሔርን እያከበርህ ለአንተ የሰጠህን ፍቅሩን እና ትሕትናውንም እየገለጽህ መሆንህን ተረዳ፡፡

እግዚአብሔር በማንም በኩል አንድ መልካም ነገር ካደረገልህ ከእግዚአብሔር በተጨማሪ ያንን መልካም ነገር እንድትቀበል ምክንያት ለሆነህ ሰውም ምስጋና ስጥ፡፡

ብዙ ሰዎች በየዕለቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ በታላላቅ ክብረ በዓላት ላይ እና በሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ጊዜያት ላይ ብቻ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን “ሁል ጊዜ ስለ ሁሉ አመስግኑ” ኤፌ ፭-፳ ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ስናቀርብ ጊዜና ወቅት ጠብቀን በተለየ ጊዜ ሳይሆን “ሁል ጊዜ” መሆን አለበት፡፡ ምስጋናውም ደግሞ የማይቋረጥ እስከሆነ ድረስ መላ የሕይወት ዘመንን ያጠቃልላል፡፡ “ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” ፩ተሰ ፭÷፲፮-፲፰ ተብሎ ተገልጧል፡፡

ይህ ትምህርት የምስጋና ጸሎት ጸሎቶችን እንደሚመራ ያስረዳል፡፡ የሰርክ እና የነግህ ጸሎቶችን ጨምሮ ሁሉም የቤተክርስትያን ሥርዓቶችና አገልግሎቶች የሚጀምሩት በምስጋና ጸሎት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በማለዳ፣ በቀትር እና በማታ እናመሰግነዋለን፡፡ በማንኛውም ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ስለ ሁሉም ነገር ጭምር ማመስገን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው “እግዚአብሔር ለሚወዱት እንደ ዐሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡” ሮሜ ፰-፳፰ አንዳለ እግዚአብሔር ያለ ማቋረጥ በጎ ነገር ያደርግልናል፡፡ 

✍አቡነ ሺኖዳ የምስጋና ሕይወት

ሰቆቃ ገዳማውን፡ ዓለም የምትከታተላቸው ገዳማትና ገዳማውያን

ሰላም ውድ የቤተክርስቲያን ሳምንታዊ ተከታታዮች! ጣዕመ ዓለም አንገሽግሷቸው ፍቅረ እግዚአብሔር ናፍቋቸው ከእርሱ ጋር ለመኖር ድምጸ አራዊትን ፀብዐ አጋንንትን ታግሰው ለመኖር የቆረጡ መነኮሳት፣ እንደ አባ እንጦስ በገዳም በምንኩስና፤ እንደ አባ ጳውሊ በብሕትውና ለመወሰን ከዓለም ይኮበልላሉ፡፡ የብዙኃኑ መነኮሳት መሪ ጥቅሳቸው “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያገኝ ነፍሱን ግን ባያተርፍ ምን ይረባዋል?” የምትለው አምላካዊ ቃል በመሆኗ ከዓለም ሲለዩ ከዓለም አንድም ነገርን መያዝ አይፈልጉም፡፡

ይህ ሥርዓተ ምንኩስና አስቀድሞ በአዳም ሰባተኛ ትውልድ ሄኖክ በኋላም የአብርሐምን መስዋዕት በተቀበለው በአምሳለ ክርስቶስ ካሕኑ መልከ ጼዴቅ፣ ከነቢያት ወገን ከሆነው ከነቢዩ ኤልያስ እንዲሁም በተኻራሚው ሰባኪ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወት ውስጥ ተገልጧል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው ዐርባ ቀንና ሌሊት ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ባርኮታል፡፡ ይህ ሕይወት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በክርስቲያኖች ዘንድም የሚታወቅ ሲሆን ይበልጡኑ ሥርዓት ሠርቶለት መልክ አበጃጅቶለት ያጸናው ግን የገዳመ አስቄጥሱ እንጦንስ እንደሆነ ቅዱስ አትናቴዎስ በመጽሐፈ ገነት ላይ ያሰፈረው የቅዱሱ ዜና መዋዕል ያሳያል፡፡፡

ይህ በላዕላይ ግብጽ የተጀመረውና በኋላም በመላው ዓለም የተስፋፋው የገዳም ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያም የገባው ከእንጦንስ ፭(5)ኛ የቆብ ልጅ በሆኑትና ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ ነው፡፡ ይህ የገዳም ሥርዓት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በሃገራችን የሰሜኑ ክፍል የተስፋፋ ሲሆን በኋላም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ወደ ምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ ሊስፋፋ እንደቻለ ታሪክ ያስረዳናል፡፡

በዚህ ሳምንት በገዳመ ዝቋላ በጽንፈኛ ታጣቂዎች የደረሰውን ጥቃት መሠረት በማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወደዚህ እየተደጋገመ የመጣውን ገዳም ተኮር ጥቃቶች ለመመልከት እና መፍትሄዎችን ለማመላከት እንሞክራለን፡፡

ቀኑ ሰኔ  ፲፫/፳፻፲፯ (ሰኔ 3-2017) ዓ.ም. አመሻሹ ላይ  ነበር፣ የታጠቁና መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም  መነኮሳት በኅብረት ከሚኖሩበት በዓት ራቅ ብለው ዘግተው ወደሚኖሩ አባቶች በዓት የሄዱት፡፡ በዚህ ገዳም ባለፈው ዓመት አራት መነኮሳትን በሰማዕትነት  እንዳሳረፏቸው ዛሬም አስቀድመው ለዓለም የሞቱትን በሥጋ በመግደል መነኮሳቱን ለማመናመንና ያሉትን በፍርሃት ለመበተን ነበር ወደ መናንያኑ የተጠጉት፡፡ በዚህ መሳሪያ የለም፣ በዚህ ተዉ የሚላቸው አካል የለም፡፡ በቅርብ በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት መውጣትን ተከትሎ ነበር ወደ ሥፍራው ያቀኑት፡፡

ምስኪኖቹንና ደካማዎቹን መነኮሳት ለማጥቃት ሰይፍና ሥለት ታጥቀው ወደ ገዳሙ የመናንያን ዋሻ ደረሱ፡፡ ቀታልያኑ ከአንድ አባት በስተቀር እንዳሰቡት ብዙ አባቶችን ማግኘት አልቻሉም፡፡ የተገኙት አባት አባ ኃይለ ሚካኤል ነበሩ፡፡ አባ ኃይለ ሚካኤል በማኅበረ ሥላሴ፣ በዲሙ በረሃና በደብረ ሊባኖስ የነበራቸውን ተጋድሎ ፈጽመው ነበር ማረፊያቸው እንድትሆን ወደ መረጧት ዝቋላ የመጡት፡፡ በገዳሙ በበርካታ ልዩ ልዩ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው የዛሬ ፲፪ (12) ዓመት ነበር በገዳሙ ፈቃድ ወደ ዋሻው በመሄድ በብህትውና ያሳለፉት፡፡ ታጣቂዎች ባህታዊውን ዐይተው ማለፍ አልፈለጉም ነበርና ገደሏቸው፡፡ ክብርት ሥጋቸው አምና በግፍ በነዚሁ እጅ ከተገደሉት መነኮሳት ጋር ሲያርፍ ነፍሳቸው ወደ መነኑለትና ዓለምን ወደረሱለት አምላካቸው ዘንድ ተጓዘች፡፡

የገዳሙ መነኮሳት “የታጣቂዎች ፍላጎት አንድ ነው፤ እሱም ገዳሙን ማጥፋት ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እንደሚደረጉበት ገልጸዋል፡፡ ለቅርብ ጊዜ ዜናዎች ሩቅ ላልሆነ ሰው ይህ ዓይነቱ መከራ ለዝቋላ ብቻ የተሰጠ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ ዋልድባ፣ አሰቦት፣ ማኅበረ ሥላሴ፣ ደብረ ሊባኖስ ያሉ ታላላቅ ገዳማትን ጨምሮ በርካታ ገዳማት ከወቅታዊ ሃገራዊ የእርስ በዕርስ ጦርነቶች ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቃቱ ዓላማ ተደርገዋል፡፡ የተፋላሚ ወገኖች በገዳማቱ ከመጠለል አልፎ፣ ዘረፋ፣ መነኮሳቱን ማንጓጠጥ፣ መግደል፣ ማስፈራራትን መፈጸም የተለመደ ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ገዳማት  የቀደመ መፈራታቸውና መሰማታቸው ቀርቷል፡፡ ይልቁንም በዓለም ትተውት የመጡት ጎጠኝነትና ቡድንተኝነት፣ ሃብት እና ሥልጣን ለማግኘት የሚደረጉ ሹኩቻዎች መካሄጃ ሥፍራ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ለገዳማት መደፈር የመጀመሪያ ምክንያት በሀገሪቱ የሚገኘው የፌደራሉ መንግስትና የክልል መንግስታት ለነዚህ ለዜጎች የሥነ መግባር ትምህርት፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር በውስጣቸው በያዙት ቅርስ ምክንያት ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ አስተዋጽዖ  ላላቸው ገዳማት ተገቢውን የጥበቃና የደኅንነት ሽፋን መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ገዳማት የግል ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በዓለውያን መካከል ያለደኅንነት ሽፋን የሚኖሩት የግብጽ፣ የሶሪያና የኢየሩሳሌም ገዳማት ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ገዳማቱ እንደ ኢትዮጵያ ገዳማት ክፍት ሳይሆኑ ጥብቅና ዙሪያቸውን የታጠሩ ናቸው፡፡ ምንም ያሕል ሰፊ ቢሆኑም ገዳማታቸው በመታጠራቸው ከአላስፈላጊ የሰውና የሀራዊት ትንኮሳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሕጋዊ መታወቂያ የሌለው የትኛውም መነኮስ ይሁን ቱሪስት ወደ ገዳማቸው ዝር እንዲል አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህም ቢሆን የመጣበትን ምክንያት የማስረዳትና ጎጂ ቁሶችን አለመያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ገዳማውያኑ ሳይረበሹ ልባቸውን ጥለው በፍጹም ጸጥታ ወደ እግዚአብሔር እንዲያተኩሩና ተጋድሏቸውን እንዲያጠነክሩ ይረዳቸዋል፡፡ በእነዚህ ከላይ ባነሳናቸው ሃገራት ያሉ ገዳማት ከአድባራት አንጻር ዝቅ ያለ የጥቃት ተጋላጭነት ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ሌላው ገዳማት በምጣኔ ሀብት ራሳቸውን የሚችሉና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ድጋፎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ የላዕላይ ግብጽ እንዲሁም የኢትዮጵያው ምዕራፈ ቅዱሳን ተከዜ ገዳም ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ገዳማት በያዟቸው መሬቶች የተለያዩ የግብርና፣ የዕደ ጥበብ ምርቶችን እያቀረቡ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በዚህም ያላቸው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ላቅ ያለ በመሆኑ ከመንግስት ተገቢውን ትኩረት ከማግኘታቸውም ባለፈ ለአካባቢው ምእመናን የሥራ ዕድልን ስለሚያመጣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በእኔነት እንዲጠብቃቸው ያስችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር እንደ ትምህርትና ጤና ባሉ መስኮች ላይ መሳተፍም ከኅበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው በማስቻል ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጪ ባሉ ነዋሪዎች ሳይቀር እንዲከበሩ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

እግዚአብሔር መነኮሳትንና መነኮሳይያትን፤ ገዳማቸውንና ባዕታቸውን ይጠብቅልን፡፡ ቸር እንሰንብት

ጾታዊ ጥቃትና ቤተ ክርስቲያን

የቅድሳት ስዕላት መቀደድ የማይረብሸው ምእመን አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቃጠለ ተብሎ ልቡ በደስታ የሚሞላ አንድም ሰው ማግኘት ይከብደናል። ነገር ግን ይህ ጥቃት በሰው ልጆች ላይ ተሰነዘረ ሲባልስ?

ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዕድምተኞቻችን!
ሰሞኑን በማኅበራዊ መግባቢያ(Media) ሲዘዋወሩ ከነበሩ ዐሳቦች በመነሳት ጾታዊ ጥቃትን በዚህ ሳምንት ርእሰ ጉዳያችን በማድረግ እውን የክርስትና አስተምህሮና ቤተ ክርስቲያን ጾታዊ ጥቃትን ትገፋፋለች ወይ? የሚለውን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

ጾዊ ጥቃት ከስሙ በመነሳት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሆኑን ለመገንዘብ አድካሚ አይደለም፡፡ በዚህ ጥቃት ሰለባ ለመሆን የተጠቂው ጾታ ለጥቃት ተፈላጊ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትን ያለ አድሎ የምታወግዝ በመሆኑ በዕድሜና በጾታ ባትከፋፍለውም በጉዳዩ ዙሪያ ያላት አስተምህሮ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሠረቱን ያደረገና በቅዱሳን አበው ትምህርት የተደገፈ ነው፡፡

የሰው ልጅ ስለመፈጠሩ የሚነግረን ሊቀ ነብያት ሙሴ  በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፉ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩን ማንሳቱ ለቤተ ክርስቲያን የነገረ ሰብእና የክብረ ሰብእ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህም ሰው የቅድስት ሥላሴ ክብር የሚገለጽበት ሕያው ስዕለ ሥሉስ ቅዱስ በመሆኑ ሰው ላይ የሚደርስ ጥቃት በፈጣሪው፣ በአስገኚውና በሥዕሉ ባለቤት በሆነው በእግዚአብሔር ላይ እንደተቃጣ ይቆጠራል፡፡
ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ጳውሎስ በቀዳሚው የቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ እንደተወልን የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆኑ በሰዎች ላይ (በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ) የሚፈጸም ጥቃት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰዎች ላይ  የሚፈጸሙ ጥቃቶች እግዚአብሔር የመሠረተውን የሰው ልጆችን የእርስ በእርስ በፍቅርና በአንድነት የመኖር ዕቅድ የሚያዛባና በወንድሞች/እኅቶች መካከል መፈራራትንና መጠራጠርን የሚያነግስ ተግባር መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስታውቁናል፡፡ ጥቃት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጠውን አንድን ነገር የማድረግ ወይም ያለማድረግ ነጻ ፈቃድን የሚነጥቅና በግዳጅ ባርነት ውስጥ የሚከት ተግባር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ትጸየፈዋለች፡፡

ጾታዊ ጥቃት በራሱ ኃጢአት ከመሆኑም ባሻገር ተደራራቢ መተላለፎችን የሚይዝ መሆኑን የዳዊት ልጅ ትዕማርን ባስነወረው የአምኖን ታሪክ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ዝሙት፣ አመንዝራነት፣ መግደልን ጨምሮ በርካታ በሁለቱ ኪዳናት የተሰጡ ትዕዛዞችን የሚተላለፍ ተግባር ነው፡፡

ጥቃት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለተሰጠው ቅዱሱ የትዳር ሕይወትም ጸር ነው፡፡ መምህረ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትዳር ሲናገር በቤተ ክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል ባለ ግንኙነት ይመስለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ወዳና ፈቅዳ እንደምትገዛለት ሚስቶች ለባሎች በፍቅር ሊገዙ እንደሚገባ ሁሉ ባሎች ደግሞ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳትና ለለ እርሷም መከራ መስቀልን እንደታገሰ ሁሉ እነሱም ሚስቶቻቸውን በፍጽም ፍቅር ሊወዱ እንጂ እጃቸውን ሊያነሱ አይገባም፡፡

በዚህ ዙሪያ አስፍተው ካሰተማሩ አባቶች አንዱ የሆነው ታላቁ ቅዱስ ባስሊዮስ ስለ ጠላፊዎች ባስተማረው ትምህርት “ጠለፋ ሕጋዊ ያልሆነ እና አንባገነንነት ነው፡፡” ሲል ይነግረናል። ዳግመኛም “በዚህ ጉዳይ አንድ ዐሳብ ቢኖራችሁ ኖሮ ከሃገራችሁ ይጠፋ ነበር፤ አሁንም ስለ ክርስትና ቅንዓት ስትሉ ተነሱ፤ ልጅቷን ባገኛችኋት ጊዜ ወደ ቤተሰቦቿ መልሷት፤ እርሱን ግን ከጸሎት ለዩት/አግዱት” ሲል ከጾታዊ ጥቃት አንዱ ስለሆነው ስለጠለፋ ሕገ ወጥነት ያስተምራል። ይኸው ቅዱስ በሐዋርያት ቀኖና ላይ “ድንግሊቱን ከክብር ያወረዳት ቢኖር እርሱ ከጉባዔያችሁ ይለይ ሲል አስገድዶ መድፈር ኃጢያት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ አፈ በረከት የተሰኘው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በ፩ኛ ቆሮንቶስ ላይ በጻፈው ፳፮ኛ ማብራሪያ ላይ ደግሞ “በሚስቱ ላይ እጁን የሚያነሳ፣ እንዲህ ያለው ወንድ ሰው ሳይሆን አውሬ ነው።” ሲል ያስተምራል፡፡

የቤተ ክርስቲያን የጾታዊ ጥቃት ምልከታም ከላይ ያሉ አስተምህሮቶችን መሠረት ያደረገና እንኳን ምንም ያልበደለንን ሰው፣ እንበድል ዘንድ ይቅርና የበደሉንን ሳይቀር ይቅር እንል ዘንድ በታዘዝነው “የክፉውን በክፉ አትመልሱ!” አስተምህሮ የተቃኘ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህን ባለማወቅ እንዲሁም በእኛ በምእመናን ግዴለሽነትና ወንድማችንን/እኅታችንን የመጠበቅ ሰብዓዊ ግዴታችን በተግባር አለማሳየታችንን በመመልከት ቤተ ክርስቲያን ጾታዊ ጥቃትን እንደምታስፋፋ እንዲሁም አድሎአዊት እንደሆነች አድርገው ሲከሱ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ከአስተምህሮ ባሻገር በተቋም ደረጃ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን ሥር ክፍል አደራጅታ ከካሕናት ጀምሮ አስከ ምእመናን ድረስ በማስተማር የግንዛቤ ለውጥ እንዲስፋፋ እየሠራች ትገኛለች፡፡  ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን እንደ ፌሚኒዝም ያሉ አንድ ጾታ ላይ መሠረት ያደረጉ የመፍትሔ እንቅስቃሴዎችን ባትደግፍም በኃጢአት ምክንያት በምድር ላይ የሰፈነው መጠፋፋትና መጨካከን ክርስቶስን ማዕከል በማድረግና የክርስቶስን ልብ ገንዘብ በማድረግ እንደሚፈታ ታምናለች፡፡ በዚህም አምላክን የመምሰል /ሱታፌ አምላክ መንገድ የሰው ልጅ እንኳን ለሌላው አምሳያው ይቅርና ለፍጥረት ሁሉ የሚራራ፣ ራሱን የሚገዛ፣ የተረጋጋ ሰብዕ ስለሚሆን በዚህ መንገድ በምድር ያሉ ችግሮችና ኢፍትሐዊነቶች እንደሚፈቱ ታስተምራለች፡፡ ለዚህም ነው የሱታፌ አምላክ በር የሆነውን የንሥሐ ጥሪ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ዕለት ዕለት ስታዘክር የምትኖረው፡፡

ፍቅር

ሰው የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንደሆነ እና የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጡ እንደሚያድር ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ወደ እኛ የላከው በእኛ ውስጥ ለዘለዓለም እንዲያድር በእኛ ውስጥ በእኛ በኩል እንዲሠራ ሥራውም ፍሬ እንዲያፈራ ላከው። ይኸውም የመንፈስ ፍሬ ነው ፩ ቆሮ ፫÷፲፮ ፣ ዮሐ ፲፬÷፲፮-፲፯ እጅግ ጠቃሚዎቹ የፍቅር ዓይነቶች የእግዚአብሔር ፍቅር እና ለመልካም ነገር ያለን ፍቅር ናቸው። እያንዳንዳቸውም ወደ ሌላው ይመራሉ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ለመልካም ነገር እና ምግባር ወደ ሚደረግ ፍቅር ይመራል፤ ይህም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ይመራል፡፡ አንዱም ሌላውን ያጠነክራል፡፡

መልካም ነገርን ለመውደድ ፍላጎት ያለው መልካም ነገርን ለመመለስ አይታገልም:: ነገር ግን የእርሱ ትግል የሚሆነው  በእግዚአብሔር ፍቅር መልካም ነገርን በመውደድ ማደግ ነው፡፡ የእንደዚህ ዓይነት ሰው ትግል የተቃውሞ ይልቅ አወንታዊ ነው፡፡ ከፍላጎት አባልነት ይልቅ አዎንታዊነቱ የላቀነው፡፡ ይህ ከአንድ የቅድስና ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገር ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ትግል ፈጽሞ አድካሚ ሳይሆን ጣፋጭ ነው፡፡ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን የሚወድና መልካም ምግባርን የሚጠላ ሰው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ይዝላል፡፡ ዮሐ ፫÷፲፱ ነገር ግን መልካምን የሚወድ ወደ ሌላ ከፍተኛ መልካም ነገር ሊሸጋገር ወደ ሚችልበት ፍጻሜ ወደ ሌለው ዕረፍት ይገባል፡፡

ግዴታ እንደ አንድ ምግባር ነገር ማድረግ ለሚወዱ ለተቀደሱ ሰዎች መልካም ለመሥራት ራሳቸውን ማስገደድ የተገባ አይደለም፡፡ እነርሱ ማንም ድካምና ጫና ሳያሳድርባቸው ፈጥነው መልካም ነገርን ያደርጋሉ፡፡

መልካም ነገርን የሚወድ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አክብዶ አይመለከትም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀን ና በሌሊት ያስባል። መዝ ፩÷፲፪ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “ትዕዛዛትን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና ትዕዛዛቱም ከባዶች አይደሉም፡፡” ፩ኛ ዮሐ ፭÷፫ ብሏል፡፡ እኛም ትዕዛዛቱን የምንወዳቸው ከሆነ ይህ ስሜት ይሰማን እና “የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል” መዝ ፲፰÷፰ ማለት እንጀምራለን፡፡
ጌታን እና መልካም ምግባርን የሚወድ ማንኛውም ሰው ሕግ ከሚጠይቀው የላቀ እና ወደ ፍቅር መንገድ ውስጥ የገባ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰው ትዕዛዝን ሳይጠብቅ መልካም ነገርን ይሠራል፡፡ መልካም ባሕርይ መልካም ነገርን ለመሥራት ጥሪን እንዲጠባበቅ አያደርገውም፡፡

እንዲህ ያለው ሰው መልካምነት ባሕርይው ውስጥ ስላለና የእግዚአብሔር አምሳል ስለሆነ መልካም ነገርን ያደርጋል፡፡ እንደ አንድ የተለመደ ነገር ወደ ውጪ እንደሚወጣ እስትንፋስ ያልተለመደ አዲስ ነገር ወይም ከችሎታው በላይ እንደሚሠራ ዓይነት ስሜት ሳይሰማው መልካም ነገር ይሠራል። በሥራው ከመኩራት ይልቅ የሚፈጽመው ተግባር እንደተለመደ ሥራ ይመለከተዋል፡፡ በተቃራኒው መልካምን የማይወድ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከባድ ሆኖ ያገኘዋል፤ እርሱም የእግዚአብሔር ጠላት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአት የሚገኘው ደስታ እንደከለከለው የእርሱም ትዕዛዝ እንዳስጨነቀው ወደ ማይፈለገው መንገድ እየመራው እንደሆነ ያስባል። ስለዚህ ለእርሱ የእግዚአብሔር መንገድ አስቸጋሪ ይሆንበታል። በመንገዱም የሚጓዝ ከሆነ በኃይልና በግዴታ ይጓዛል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው በእግዚአብሔር ሕልውና የማያምንነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በእግዚአብሔር የማያምን ሰው በርሱ ሕልውና የእግዚአብሔር መኖር እንቅፋት እንደሆነበት እራሱን አሳምኗል፡፡ በእግዚአብሔር የማያምን ከሆነ የመኖር ስሜት ሊሰማው አይችልም፤ “እኔ የምኖር ከሆነ እግዚአብሔር ባይኖር የተሻለ ነው” ብሎ ሊናገር የቻለው ለዚህ ዋናው ምክንያቱ እግዚአብሔርን አለመውደዱ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የጠፋው ልጅ ከቤተሰቦቹ ርቆ ተጓዘ፤ በነፃነቱ መደሰት በፈለገ ጊዜ የአባቱን ቤት ጥሎ ሄደ፡፡ ሉቃ ፲፭÷፲፫

በሌላ በኩል መልካም ነገርን የሚወድ ፍቃዱ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይስማማል እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር አ ይጣላም፡፡ እግዚአብሔርን ይወዳል፤ የሚያስበውንም ነገር ከእርሱ ያገኛል፡፡ ሊያደርገው የተነሳሳበትን መልካም ነገር ሁሉ ስለእግዚአብሔር ብሎ ይወዳል፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ ብቸኛ ምኞቱ እና ብቸኛ ደስታው ይሆናል፡፡

አቡነሺኖዳ፡ የመንፈስ ፍሬዎች

ቅድስት ሶፍያ እና ደናግል ልጆቿ

ስሙ ዋርስኖፍ የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በወደዱ ጊዜ ሸሽቶ ወደ ናባ አውራጃ እሊህ ደናግል ወዳሉበት ወደ ግሕሙን ደርሶ በዚያ አደረ።

በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጦለት ከዚህ ለምን ትተኛለህ ተነሥተህ ተጋደል ለአንተና ሰማዕት መሆን ለሚሹ ሁሉ አክሊል ተዘጋጅቷልና አሁንም ተነሥተህ ወደ መኰንኑ ሒድ በፊቱም ቆመህ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመን አለው።

ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ራእይን እንዳየ ለቅዱሳት ደናግል ነገራቸው። ሲነጋም ተነሥተው ከእርሱ ጋራ ወደ መኰንኑ ሔዱ። በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ታመኑ። መኰንኑም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸውና ወደ ወህኒ ቤት ጨመራቸው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከቅዱስ ዋርስኖፍ ጋራ ወደ ስንሑር ላካቸው፤ እናታቸውም ትከትላቸው ነበር።

መኰንኑም ለአማልክቱ ዕጣን ዕጠኑ አላቸው። ባልታዘዙለትም ጊዜ ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው፤ እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ አጸናቸው፤ ቊስላቸውንም ፈወሰ። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ከእርሱ ጋር ወደ ሀገረ ጻ ይዞአቸው ሔደ። የጣዖታቱ ካህናትም ጣዖታቱን እንደምትረግም ስለ ቅድስት ደባሞን ነገሩት። እንዲሁም ባልጀራዋ ዮና የምትባል ሴት አንዳለች ነገሩት፤ እነርሱም ኀብራቸው በየራሱ የሆኑ መልካም ልብሶችን እየሠሩ ለምግባቸው ይሸጡ ነበር፤ የተረፋቸውንም ይመጸውቱ ነበር። መኰንኑም የዮናን ዜና ሰምቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጥ ባለሰይፉን ላከው፤ የሰያፊውም ስም አውሎጊስ ነው።

ወደርሷም በቀረበ ጊዜ ፊትዋ እንደ መላእክት ፊት ብርሃንን ተመልቶ አየና ፈራ፤ እርሷንም ወደ መኰንኑ እንዲወስዳት እንጂ እንዳይገድላት የእግዚአብሔር ጸጋ አስገነዘበችው። ቤተ ሰቦቿም ተሰነባብተዋት ጸንፋ ከሚባል አገር ወጣች። ወደ ሀገረ ፃ ደርሳም መኰንኑን ተገናኘችው፤ ከቅዱስ ወርስኖፍና ከባልንጀሮቹ ጋራ እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ።

ሰያፊው አውሎጊስም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነና ራሱን ቆረጡት። የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ፤ እንዲሁም እሊያን ቅዱሳት ደናግልንም ራሳቸውን ቈረጧቸው፤ ገድላቸውንም ፈጽመው የድል አክሊልን ተቀበሉ።
ቅድስት ደባሞንን ግን ጽኑዕ ሥቃይ ያሠቃዩአት ዘንድ በመንኰራኵር ላይ ሰቀሉአት። በዚህ ሥቃይም ውስጥ ለብዙ ቀኖች ኖረች፤ የእግዚአብሔር መልአክም ያጸናት ያስችላትና ቊስሎቿን ይፈውሳት ነበር። መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገባት፤ በዚያም ጥቂት ቀን ኖረች፤ ወደ ፍርድ ሸንጎም አስቀርቦ “ለአማልክት ሠዊ” አላት። ባልሰማችውም ጊዜ ራሷን እንዲቆርጡ አዘዘ።

ራስዋንም ሊቆርጡ ከከተማ ወደ ውጭ በአወጧት ጊዜ ሴቶች ሁሉ እያለቀሱ ከብበዋት ነበ፤ እርሷ ግን ፈጽማ ደስ ይላት ነበር። ራስዋንም በሰይፍ ቆረጥዋት እንዲሁም እናቷንና እኅቷን በሰይፍ ቆረጧቸው፤ በመንግሥተ ሰማያትም የድል አክሊልን ተቀበሉ።

ምንጭ፦ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ

የሰንበት ት/ቤት ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እንቅስቃሴዎች

ባሳለፍነው ሳምንት እሑድ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ቀን ለ፲፬(14)ኛ ጊዜ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተከብሯል፡፡ ይህን ተከትሎ ቅዳሜ ግንቦት ፴(30)ና እሑድ ሰኔ ፩(1) በአዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ጽዮን አዳራሽ  ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የመንበረ ፓትሪያርክ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባዔ የተደረገ ሲሆን በጉባዔው ላይ ከተለያዩ አሕጉረ ስብከቶች የተወጣጡ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱም በትግበራ ላይ የሚገኘው የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀው የሰ/ት/ቤቶች መዋቅርና ስልታዊ ዕቅድ ዋነኛ አጀንዳ የነበሩ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከነበረው ሁነት ባሻገር በደሴ፣ ወልዲያ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋና በሌሎች የክልል እንዲሁም የውጭ ሃገራት ሀገረ ስብከቶች በዓሉ ምእመናንን በሚያሳትፍ መልኩ በዝማሬ፣ በስብከተ ወንጌልና በልዩ ልዩ መንገዶች አክብረውታል፡፡ ይህን ተከትሎ በዛሬው የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን ስለ ሰንበት ት/ቤት ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እንቅስቃሴዎች በማንሳት አሁናዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እንሞክራለን ሰላም ቆዩን፡፡

የሰንበት ት/ቤት እንቅስቃሴ የቀደሙ አብነቶች ያሉት እንቅስቃሴ ቢሆንም ሰንበት ት/ቤት በሚል ስያሜ የመጣው ግን ከድህረ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በኋላ በ፳(20)ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ መሆኑን ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ምንም እንኳን ሰንበት ት/ቤት በቤተ ክርስቲያን ያለው ታሪክ ከአንድ ምዕት የበለጠ ባይሆን አብነቶቻቸው ግን ጥንታውያን ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን ወጣቶች በረበናት ይማሩባቸው የነበሩ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ናትናኤልን የመሰሉ ሐዋርያት የተገኙባቸው የአይሁድ ትምህርት ቤቶች፣ በሐዲስ ኪዳን በዘመነ ክርስቶስ የሐዋርያት፣ ፴፮(36)ቱ ቅዱሳት አንስት እና ፸፪ (72)አርድዕት አገልግሎት፣ በእስክንድርያና በአንጾኪያ የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስንል ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተስፋፋውን የአብነት ትምህርት እንደ መንፈስ አባቶቻቸው መቁጠር የምንችል ይመስለናል፡፡

ሰንበት ት/ቤቶች በሰንበት ት/ቤት (በእሑድ ት/ቤት) ሥያሜ የተመሠረቱት በድሕረ ተሃድሶ ዘመን በተነሳው ምዕራባዊ የተሃድሶና የመድፍነ ተሃድሶ (የጸረ ተሐድሶ) እንቅስቃሴ አማካኝነት ቢሆንም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርሥቲያን የሰንበት ት/ቤት ቅርጽ በሥርዓተ ዓምልኳዊ ይዘቱ ደረቅ የሳይንስ ትምህርት ይዘት ካለው የምዕራባውያን ሰ/ት/ቤት በእጅጉ የሚለይ አገልግሎት ነው፡፡

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ የቀደመ የሰ/ት/ቤት እንቅስቃሴ የምናገኘው በ፲፱፻(ዐሥራ ዘጠኝ መቶ)ዎቹ አካባቢ በተነሳው በሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ ሀቢበ ጊዮርጊስ አማካኝነት መሆኑን የቅዱሱ ዜና መዋዕል ያሳያል፡፡ ቅዱሱ በወቅቱ ከነበሩት ፓትሪያርክ አቡነ ቄርሎስ አምስተኛ ጋር በመተባበር እንደ ናዚር ጋይድ (የኋላው አቡነ ሺኖዳ) ያሉ ወጣቶችን በማሰባሰብ ሥርዓተ ትምሕርት ቀርጾ ሕጻናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች በዘመኑ እየጀመረ ለነበረው ምዕራባዊ ጠባይና የእስልምና ጭቆና የማይበገሩ በሃይማኖት፣ በሥነ ምግባርና በዓለማዊ ዕውቀት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስጠሩ ወጣቶችን ማፍራት ችሏል፡፡

ከዚህ ዘመን ዘግየት ብሎም ቢሆን በፓራሙላው ሊቀጳጳስ ቅዱስ አቡነ ጊዮርጊስ አነሳሽነት የተጀመረው የሕንድ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎትም ሌላው የሚጠቀስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ የማላንካራው ሜትሮፖሊታን የቅዱስ አቡነ ዲዮናስዮስ  ቫታሳሪ ሚና ላቅ ያለ እንደነበር እናገኛለን፡፡

ሌላው በዕድሜ ላቅ ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ነው። በእርግጥ እስከ ሰባዎቹ ድረስ የሰንበት ት/ቤት ስያሜን የያዘ ባይሆንም በተለያዩ አድባራት የተጀመሩ የወጣት ማኅበራት ምሥረታዎች ዕድሜ ወደ ሰባ የሚሻገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከንጉሣዊ ሥርዓት ወደ ኅብረተሰባዊ ሥርዓት ለመሻገር እያጣጣረች ባለችበት ወቅት የውጭ መጻሕፍትን ማንበብና እነሱን መከተል እንደ ስልጣኔ በታየበት ወጣቱ ሃይማኖቱን እንዲሁም ባሕሉን ማጥላላት በጀመረበት የ፲፱፻፶ (1950)ዎቹ ወቅቶች ፍቅር ያገበራቸው መንፈስ ቅዱስ ያነቃቸው ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበራትን መመሥረት ጀመሩ፡፡ በደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል የተመሠረተውን የእግዚአብሔር ምስሌነ የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበርን ጨምሮ ቀዳምያኑ የተምሮ ማስተማር (ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም)፣ ማኅበረ ሥላሴና ማኅበረ ክርስቶስ (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል)፣ ምክኻ ለደናግል (ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም) እንዲሁም እንደ ሃይማኖተ አበው (በተሃድሶ ትምህርቶቹ ምክንያት ተወግዘዞ የተለየ) ያሉ ማኅበራት እስከ ሰባዎቹ ድረስ በማኅበርነት ቅርጽ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴን ያከናውኑ ነበር። በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክሕነት ሥር የወጣቶች መምሪያ ተቋቁሞለት ይመራ የነበረ ሲሆን የአገልግሎት  አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርትም በወቅቱ ተዘጋጅቶ እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል፡፡

ዐብዮታዊው መንግስት ከዐብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበርና ሴቶች ማኅበር ውጪ የወጣት ማኅበራትን በመከልከሉ መንፈሳዊ ማኅበራቱ በሌላ ስም መጠራት ግድ ስላላቸው ከአኀት አብያተ ክርስቲያናት ልምድና ከመሰባሰቢያ ቀናቸው በመነሳት ሰንበት ት/ቤት በሚል ሥያሜ ተዋቅረዋል፡፡ በሰንበት ት/ቤት ዕድገት ውስጥ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች ማለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ደማቅ አስተዋጽዖ ነበራቸው፡፡

ይሕን ታሪክ በምትጋራው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት በራሷ መንበር መመራት ከጀመረች በኋላ ወዲያውኑ ነበር የሰንበት ት/ቤት እንቅስቃሴን የጀመረችው። በተለይም የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ አቡነ ፊሊጶስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በአርመንና በሶርያ የሰንበት ት/ቤት ጅማሮ ከሌሎቹ በተለየ በዲያስጶራው ማኅበረሰብ አማካኝነት የተጀመረ ነው፡፡ በውጭ ያሉ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን የማስተማር ቅርጽ ተከትለው በአሜሪካና በአውሮፓ ትምህርቱን ካስጀመሩ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሃገር ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት ማስገባት ችለዋል፡፡

እንደ ጥቅል በስድስቱም አብያተ ክርስቲያናት የሰንበት ት/ቤቶች በሊቃነ ጳጳሳት በሚመሩ የሰ/ት/ቤት ወይም የወጣቶች መምሪያ ሥር የሚተዳደሩ ሲሆን ከኢትዮጵያና ኤርትራ ውጪ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ያለ በዕድሜና በትምህርት ደረጃ የተከፋፈለ (ከኬጂ እስከ 12) የሰንበት ት/ቤት የሥርዓተ ትምህርት ልምድ ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች በአንጻሩ ለማኅበር ቅርጽ ያደላ የዘመን አከፋፈል (ሕፃናት፣ ታዳጊ ወጣት፣ ጎልማሳ) የሚከተል ሲሆን ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት ሳይኖረው ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፳፻፲፬ ዓ.ም. (2014)ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርቱን በሙከራ እንዲሁም ፳፻፲፮ (2016)ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ሃገሪቱ እንዲተገበር እያደረገች ሲሆን ይሔም ከቅድመ መደበኛ እስከ ፲፪(12)ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በዕድሜያቸውና በግንዛቤያቸው ልክ በየትም ሆነ በየትም ሆነው እንዲማሩ የሚያስችላቸው ነው፡፡ ሥርዓተ ትምሕርቱ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን የመማሪያ መጻሕፍት ኅትመትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በአኀት አብያተ ክርስቲያናት ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለ ወጥ የሰ/ት/ቤት መዋቅር  ሰንበት ት/ቤቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ያደረጋቸው ሲሆን በተለይ የግብጽና የሕንድ ሰንበት ት/ቤቶች አሁን ላይ ለደረሱበት ትልቅ ስምና አቅም እንዲሁም ላፈሯቸው ልጆች በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቦታዎች ትልቅ ቦታ መድረስ ተችሏል፡፡ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያሉ ሰንበት ፣ት/ቤቶቸ ወጥና ተናባቢ ሥርዓትን ስላልገነቡ ከአጥቢያቸው አለፍ ያለ ተሸጋሪ ተጽዕኖ መፍጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህንን አስመልከቶ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤመዋቅርና ሥልታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ በለቱ የቅዱበስ ሲኖዶስ ጉባዔ ያጸደቀ ሲሆን በቀጣ ዓመት ይተገበራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 
ለወደፊት የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሰ/ት/ቤት ልምድ በመጠኑ ለመዳሰስ ቀጠሮ በመያዝ እዚህ ላይ እናብቃ፡፡ በክርስቶስ ሰላም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት

የ፳፻፲፯ (2017) ቱ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዕለተ ረቡዕ ግንቦት ፳ / ፳፻፲፯ (ግንቦት 20- 2017) ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ በዚህ ሳምንት በቅዱስ ሲናዶስ የምደባ ውሳኔ መሠረት ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተመደቡባቸው ሐገረ ስብከቶችና የአገልግሎት ክፍሎች እየሄዱ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ፣ የባህርዳር ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በዚህ ሳምንት የእንኳን ደህና መጡ መርሐግብራት ተካሂደዋል፡፡

እኛም ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ሳምንት የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ መርሐግብራችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አደረጃጀት በሥርዓተ ሐዋርያት ፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቃለ አዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መነሻነት የምንቃኝ ይሆናል፡፡ አብራችሁን ሁኑ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ጥንታዊና የዳበረ የነገረ ሃይማኖትና የሥርዓተ አምልኮ ታሪክ ቢኖራትም ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ተላቃ ራሷን የቻለችውና አስተዳደራዊ ነጻነትን የተጎናጸፈችው  የዛሬ ፷፮ (ስልሳ ስድስት) ዓመት በ፲፱፻፶፩ (1951) ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ሆነው በተሾሙበት ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ልማድና ሓዋርያዊ ትውፊት በቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራ ሲሆን ይህም ቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚሰበሰቡበት ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያስተላልፍ አካል ሲሆን በዋንኝነትም

፩.  በነገረ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ማለትም በእምነት፣ በቀኖና በትውፊትና በመንፈሳዊ ባህሎች ዙሪያ መልስ የመስጠት፣
፪.  የአጽዋማትና የበዓላትን ጨምሮ በሚነሱ የቀኖና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት፣
፫.  የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር የመምራት፣ ሕጎችን የማውጣት፣ ሐገረ ስብከት የማደራጀት፣ መምሪያዎችና ድርጅቶችን የመክፈትና ሹመቶችን የመስጠትና በቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ  ውሳኔ የመስጠት መብቶች አሉት፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም ጥቅምት ፲፪ (12) ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ባስተማረው በሐዋርያውና ወንጌላዊው ማቴዎስ በዓል ቀንና መንጋውን የመጠበቅ ክህነታዊ አደራ ለሐዋርያት በተሰጠበት በበዓለ ርክበ ካህናት (በትንሳኤ ፳፭/25ኛ ቀን) የሚካሄድ ሲሆን ጉባዔው ሁል ጊዜ የፓትሪያሪኩ መንበር ባለበት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በዋዜማው በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚደረግ ሥርዓተ ጸሎት መክፈቻውን ያደርጋል፡፡

ቅዱስ ፓትሪያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር ማለትም ሰብሳቢ ሲሆኑ በእርግና፣ በጤና ችግር አልያም ለረጅም ጊዜ በመንበራቸው መገኘት በማይችሉበት ጊዜ ወይም አጀንዳው እርሳቸውን የሚመለከት ካልሆነ በስተቀር ያለ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሰብሳቢነት ጉባዔውን ማካሄድ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም በሹመት ቅድምና ካላቸው ሦስት አባቶች መሐል በሚደረግ ምርጫ የሚመረጡት አባት ጉባዔውን የሚሰበስቡ ይሆናሉ፡፡

በጉባዔው ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በተመለከተ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ከምልዓተ ጉባኤው ከግማሽ በላይ ድምጽ አስፈላጊ ሲሆን ለሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የተመለከተ እንደሆነ ሙሉ ድምጽ  ያገኘ ሲሆን ብቻ ውሳኔ ይተላለፍበታል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በነገረ ሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ማድረግ የማይችሉ ሲሆን  ድምጸ ተዓቅቦ አድርጎ የተገኘ አባት ከሲኖዶስ አባልነቱ ይሰረዛል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከመደበኛ ዓመታዊው ጉባዔያቱ ባሻገር እንደ አስፈላጊነቱ አስቸኳይ ጉባዔያትን በቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ በብፁዕ ዋና ጸሐፊ ወይም በቋሚ ሲኖዶስ ጥያቄ እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከግማሽ በላዩ ስብሰባ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜ ሊጠራ ይችላል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሥልጣን ዘመን ዕድሜ ልክ ሲሆን በዕርግናና በጤና ምክንያት ጉባዔያትን መካፈል ካልቻለ ሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ተከብሮለት በማረፊያው የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሃይማኖታዊ ጉዳይ ቢከሰስ በጉባዔው ቀርቦ ራሱን የመከላከል መብት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባልነቱ ይሰረዛል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ሥራውን ለማከናወን ይረዳው ዘንድ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሚመራ ጽ/ቤት የሚኖረው ሲሆን የዋና ጸሐፊውና የምክትላቸው የሥራ ዘመን ለሦስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን ለተጨማሪ አንድ ዙር በድጋሚ መመረጥ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባሸገር ቅዱስ ፓትሪያርኩ፣ ብጹዕ ዋና ጸሐፊና ብጹዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በቋሚነት እንዲሁም ሌሎች በየሦስት ወሩ የሚመረጡ ፬ የሲኖዶስ አባላትን የያዘ ቋሚ ሲኖዶስ ሲኖር በሳምንት ሁለት ጊዜ በመሰብሰብ በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪነታቸው ለእርሱ የሆነ ስድስት አካላት ሲኖሩ እነርሱም የሊቃውንት ጉባዔ፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ የሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር ኮሚሽን፣ የቁጥጥርና ምርመራ አገልግሎት፣ የልማትና ክርሥቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንዲሁም የሕጻናትና የቤተሰብ ጉዳዮች መምሪያ ናቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስና የቋሚ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር የሆኑት ቅዱስ ፓትሪያርኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት፣ መሪና ወካይ ሲሆኑ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥማቸው በጸሎት ይታሰባል፡፡ ሙሉ ስማቸው “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዕገሌ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት” ይሆናል ይኸውም
፩.  ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ :-  በኢትዮጵያ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ራስ/ሰብሳቢ መሆናቸውን፣
፪.  ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም :-በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ አንብሮተ ዕድ በቅዱስ ፍሬሚናጦስ የተመሠረተው የአክሱም መንበር ሐዋርያዊ ወራሽ መሆናቸው፣
፫.  ዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት:- በኢትዮጵያዊው ሐዋርያ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር ከ፲፫ (13)ኛው መ.ክ.ዘ. ጀምሮ ከግብጽ ለሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት እንደ ኤጲስ ቆጶስ ያገለገሉት የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌዎች መንፈሳዊ ወራሽ መሆናቸውን ያሳያል።
በብዙዎች ዘንድ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የምትለዋ ሃረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበር “የተክለሃይማኖት መንበር ነው” የሚል የተሳሳተ መረዳት ቢኖርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግብጽና ኤርትራ አቻዎቿ ከእስክንድሪያው መነበረ ማርቆስ የተገኘች የመንበሩ ወራሽ ስትሆን  ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚወርሱት የዕጨጌነት ሥልጣኑን ነው፡፡

የቅዱስ ፓትሪያርኩ መቀመጫ በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሲሆን ፓትሪያርኩ ዕምነትና በቀኖና ጥሰት ካልተወገዙ፣ ጥፋታቸው ከታመነበት ወይም የገቡትን ቃል ሲያከብሩ ካልተገኙ በስተቀር በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡ በህመም፣ በዕርግና ሥራቸውን ለመሥራት የማይቻላቸው ሆኖ ሲገኝ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሚሾምላቸው ሲሆን ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራቸውን በማካሔድ ላይ እያሉ እሥራትና ግዞት ቢደርስባቸው ቤተክርስቲኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡

ቅዱስ ፓትሪያርኩ ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፉ አዲስ አባት እስኪመረጥ ድረስ በሹመት ቅድምና ካላቸው ጤነኛ አባቶች መሐል አንዱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ ይሾማሉ የሥራ ዘመናቸው ከዐርባ እስከ ሰማንያ ቀናት ብቻ ይሆናል፡፡ በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀመንበር ሆነው ምርጫውን ያስፈጽማሉ፤ ነገር ግን ዕጩ መሆን አይችሉም፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስና ከቅዱስ ፓትሪያርኩ በመቀጠል የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛው የአስተዳደር አካል በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ የሚመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ፲፯ (17) መምሪያዎች (የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ፣ ውጭጉዳይ መምሪያ፣ የገዳማት መምሪያ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያ እና ሌሎችም) ፣ ፮ (6) ድርጅቶች (ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ፣ ትንሣኤ አሳታሚ፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና ሌሎችም) የሚኖሩ ሲሆን ለተወሰኑ መምሪያዎችና ድርጅቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ይመደብላቸዋል፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተዋረድ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር አካል ሀገረ ስብከት ነው። ይህም በአንድ ሊቀጳጳስ ወይም ጳጳስ ሥር የሚተዳደር መንፈሳዊ የአስተዳደር ክልል ሲሆን በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከሰባ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐገረ ስብከቶች ሲኖሩ ቁጥራቸው እንደየዘመናቱና ለአስተዳደር እንዳለው ምቹነት ሊጨምርና ሊቀንስ ይችላል፡፡ ሐገረ ሰብከቱ ከሊቀ ጳጳስ/ጳጳስ በተጨማሪ የክህነት ማዕረግ ያለው ሥራ አስኪያጅ የሚመደብለት ሲሆን በውስጡ ልዩ ልዩ ጽ/ቤቶችና የአስተዳደር ጉባዔን ያካትታል፡፡

አንድ ሐገረ ስብከት የሚያስተዳድረው መንፈሳዊ የአስተዳደር ክልል በወረዳ ቤተ ክህነቶች የሚከፋፈል ሲሆን በመጨረሻም አስተዳደራዊው መዋቅር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት / ገዳማት ጋር ይደርሳል፡፡ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያዎች ለሦስት የሚከፈሉ ሲሆን
፩.  ገዳማት፡- የወንዶች፣ የሴቶችንና የአንድነት ገዳማትን የሚያጠቃልል በአበምኔት/እመምኔት የሚመራ ፣
፪.  አድባራት፡ በከተሞችና በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥባቸው በፓትርያርክ ወይም በሊቀጳጳስ የደብርነት ማዕረግ የተሰጣቸው፣ በደብር አለቃ ሰብሳቢነት በሚመራ ሰበካ ጉባዔ የሚተዳደሩ፣
፫.  ገጠር ቤተ ክርስቲያን
፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸምባቸው የደብርነት ማዕረግ ያላገኙ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

በ፳፻፲፯ (2017)ዓ.ም. የተካሄደው የርክበ ካህናት ጉባዔን መነሻ በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ቅርጽ በወፍ በረር ለመዳሰስ የሞከርንበት መሰናዶን እዚጋ በመግታት ለሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መልካም የአገልግሎተ ዘመንን እንመኛለን፡፡ ሰናይ ሳምንት።

ደብረ ሥልጣን፡ እኅታማማቾችን ባላንጣ ያደረገው ገዳም

ኢየሩሳሌም በተለይም ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት የሚጓዝ ማንኛውም ጥቁር ክርስቲያን በአውሮፓውያንና በአረቦች በተያዙ ቅዱሳት መካናት መካከል የትንሣኤው ቤተክርስቲያን ኩታ ገጠም በሆነ ቦታ ላይ ኢትዮጵያዊውን የጥቁሮች ገዳም ሲያይ ልቡ በሐሴት መሞላቱ አይቀርም፡፡

በእርግጥ ለክርስቲያን ፡ ሁሉ ሀገሩ፣ ሁሉ ወንድሙ ቢሆንም በመልኩ እንደ እንግዳ የማይታይበት እርሱም እንደ ሌሎች ሁሉ በክርስትና ቅድሚያ ጥሪ ከደረሳቸው ወገን መሆኑን ማወቅ ለደካማው ሥጋ የሚሰጠው ልዩ ዕረፍት አለ፡፡ ያ ቦታ ደግሞ ጥንታዊው በኢየሩሳሌም ካሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘጠኝ ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው ደብረ ሱልጣን ወይም በሃገሬው ቋንቋ ዴር ሱልጣን የተሰኘው ገዳም ነው፡፡ ገዳሙ በኢትዮጵያ ሥር የሚተዳደር ቢሆንም “የይገባኛል” ጥያቄ በሚያነሱት የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳትና ምእመናን ጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም በቦታው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በእምነትና ምሥጢራት አንድ በሆኗቸው ግብጻውያን አቻዎቻቸው ይደበደባሉ፣ ይዛትባቸዋል፣ ባዕታቸው ይወረራል፡፡

ሰላም የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ወዳጆች በሰሙነ ትንሤኤው ውስጥ ሆነን በትንሳኤው መካን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያን ይዞታ ለመጎብኘት የምናብ ጢያራችን ላይ ልናሳፍራችሁ ከዛሬው የእለተ አርብ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ማረፊያ ላይ ተገኝተናል መልካም ጉዞ፡፡

የዴር ሡልጣን ገዳም ከ፱፻፶ (1950) ዓመተ ዓለም ገደማ ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት ዘመን ድረስ ያለ አንዳች ባላንጣ ለኢትዮጵያውያን ማረፊያና መኖሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ኢየሩሳሌምና አካባቢው በሮማውያንና ባይዛንታውያን እየተገዛ ሲተዳደር በቆየባቸው ዘመናት ጭምር የኢትዮጵያ ሕጋዊ ንበረትነቱና ይዞታነቱ በይበልጥ ተረጋግጦ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በቦታው ላይ መኖሪያና ቤተ ጸሎት ሠርተው ለ፫፻ (300) ዓመታት ያህል ይዞታቸውን በሰላም አስጠብቀው ኖረዋል።

የመጀመሪያው እስላማዊ ንጉሥ ዑማር ኢብን አል ካታብ ኢየሩሳሌምን እንደተቆጣጠረ የዑማር ቃል ኪዳን በተሰኘው ዐዋጁ አማኝነት ኢትዮጵያውያን በዴር ሡልጣን ላይ ያላቸውን የባለቤትነትና የይዞታ ባለመብትነት በማረጋገጥ የሰጠው ይፋዊ መግለጫም የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ዴር ኤል ሡልጣንንና ሌሎችንም አያሌ ንብረቶች ከጥንት ጀምሮ በይዞታዋ ሥር አድርጋ ስትገለገልባቸው እንደነበረ ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች በየዘመኑ መዝግበውታል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ ስለ ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ጽሑፍ በ፲፫፻፸፫ (1373) ዓ.ም. እና በ፲፱፻፸፩ (1971) ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ስለ ንብረቶች ባለቤትነት የወጡ ማስታወቂያዎች ጭምር ኢትዮጵያ በከተማዋ የንብረቶች ባለቤት እንደነበረች ይጠቁማሉ፡፡

በብሪቲሽ ቤተመዘክር የሚገኝ አንድ ስለ ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ጽሑፍ ከ፲፬፻፸፫ (1473) ዓ.ም. በፊት ኢትዮጵያ በጎልጎታ መቅደስ እንደ ነበራት መዝግቦታል፡፡ በተጨማሪም ዐፄ ዘርዓያዕቆብ በ፲፬፻፴ (1430) ዓ.ም. ለዴር ሡልጣን ገዳም የላኩት ስጦታና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅድሳት መካናት ንብረቶች በኢየሩሳሌም ማስታወቂያ ተገልጾአል። ከእነዚህ መረጃዎች ኢትዮጵያ እስከ ፲፭ (15) ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የንብረቶቹ ባለቤት እንደነበረች ማስተዋል ይቻላል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ እነዚህ ሕጋዊ የታሪክ ማስረጃ ሰነዶች እያላት ግብጻውያኑ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያውያንን ያህል ቀርቶ አንዳች ቦታ ሳይኖራቸው ዴር ሡልጣን “የእኛ ነው” ለማለት እንዴት በቁ?

ታሪክ እንደሚነግረን በ፲፯፻፸፭ (1775) ዓ.ም. ኢብራሃም ጃወሀሩ የሚባል ግብጻዊ ኢየሩሳሌም ሔዶ የሚጠጋበትና የሚያስጠጋው አጣ፡፡ ግራ ሲገባው ወደ ኢትዮጵያውያኑ በመሔድ “የሃይማኖት ወገናችሁ ነኝ” ብሎ ማረፊያ ሲለምናቸው እነርሱም በደግነት አስጠጉት፡፡ ከዚያ በኋላ በገዳሙ በነበረው ቆይታ ከኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጋር በመላመዱ ቀስ በቀስ ይዞታውን እያስፋፋ ሔደና “ቀሲስ ጆርጅ” የተባለ። የሚያግዘው ግብጻዊም ከሀገሩ አስመጣ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ አስቀመጠው። ጥቂት ቆይቶ ይህ በ”አስጠጉኝ” ልመና የመጣ ግብጻዊ ተስፋፊ ያልተጠበቀ ችግር በኢትዮጵያ መነኮሳት ላይ አደረሰ፡፡

አምባሳደር ተፈራ ኃይሌ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅድሳት መካናት ንብረቶች በኢየሩሳሌም በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹትም በንብረቶቹ ላይ ተቀናቃኝ የተነሣው በ፲፱ (19)ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ መሆኑን ጠቁመው በወቅቱ በኢየሩሳሌም ገብቶ የነበረው ወረርሽኝ በሽታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያስረዳሉ። ወረርሽኙ ኢትዮጵያውያን ምእመናንን ፈጃቸው፡፡ በዚህ አሳዛኝ አደጋ ተጠቅመው የአርመንና የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በገዳሙ የነበሩትን መጻሕፍት፣ መዛግብትና ሰነዶች ወዘተ “ወረርሽኝ ያሰራጫሉ’ ” በሚል ሰበብ እንዲቃጠሉ የኢየሩሳሌም ገዢ ለነበረው ለቱርክ መንግሥት እንደራሴ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ እንደራሴውም በቀረበለት አቤቱታ መሠረት ሰነዶቹ እንዲቃጠሉ አደረገ፡፡ በዚህም እርምጃ የኢትዮጵያውያን የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ረጃዎች በእሳት ቃጠሎ ወደሙ፡፡ ግብጾቹም ያለአንዳች ስጋት የመቅደሱንና የገዳሙን ቁልፎች በእጃቸው አደረጉ፡፡ ወረርሽኙ ካለፈም በኋላ ግብጾቹ ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱትን ኢትዮጵያውያን ምእመናን መጸለያና መጠለያ ነፈጓቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ምእመናንና መነኮሳቱም ንብረታቸውን መነጠቃቸውንና የደረሰባቸውን ግፍ በመዘርዘር ንብረቶቹ እንዲመለሱላቸው ለቱርክ መንግሥት እንደራሴ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡

እ.ኤ.አ በ፲፱፻፸ (1970) ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል አከባባር ወቅት ግብጻውያኑ ለጸሎት በሔዱበት በእስራኤላውያን የፀጥታ ኃይሎች ተከላካይነት ኢትዮጵያውያኑ የሁሉቱን አብያተ መቅደስ ቁልፎች በመለወጥ በእጃቸው አስቡ፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያውያኑ ፍላጎት ወረራን በኃይል ማስመለስ ሳይሆን ሁለቱ ወገኖች ያላቸው ማስረጃ ከሥር ጀምሮ ታይቶ በገዳሙ የባለቤትነትና የይዞታ ጭብጥ ላይ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበት ነበረ። በእስራኤል መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔና “ገዳሙን አጥተን ከምንቆይ ቁልፉን በእጃችን አስገበተን እንዲከበር እንከራከር” በሚለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፈቃድ ቁልፎቹ ተቀየሩ፡፡ ኮፕቶቹም ከ፲፱፻፶፩ (1951) ዓ.ም. እስከ ፲፱፻፹፩ (1981)ዓ.ም. እኤአ ሊታዩልን የሚገቡ ቀሪ ሰነዶች በሚልና አስተዳደሩን ያወኩትን ይዞታን የማስፋፋት ግድያዎችን ለመግታት የኦቶማን ቱርክ አዝ እኤአ በ፲፰፻፴፭ (1835)ዓ.ም. ያወጣውን የ “ባለህበት ዕርጋ” ሥርዐተ እግድ (irman of Zlcede) ወይም ‘Status Quo Are’ በመጥቀስ የአብያተ መቅደሱን ቁልፎች በኃይል መቀየር ተቃውመው ለኢየሩሳሌም ጠቅላይ ፍ/ቤት ከሰሱ፡፡ ጠቅላይ ፍ/ቤቱም መንግሥት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የመሸጋገሪያ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል ብሎ ስለነበር የእስራኤል መንግሥት በ፲፱፻፹፩ (1981)ዓ.ም. እኤአ የሚኒስትሮች ኮሚቴን አቋቋመ፡፡ ሁለቱም ወገኖች ኮሚቴው ድረስ መረጃቸውን አቅርበው የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ኢትዮጵያውያኑ ቁልፎቹን ይዘው እንዲቆዩ የሚል ውሳኔ ቀረበ፡፡

አሁን ላይ የባለቤትነት ጥያቄው በፍርድ ቤት እየተካሄደ ቢሆንም የግብጽ ቤተክርስቲያን ሀገሪቱ ያላትን የመካከለኛው ምሥራቅ ተቀባይነት እንዲሁም ተጽዕኖ በመጠቀም ባገኘችው አጋጣሚ የባለቤትነት ጥያቄዋን እያጎላች ትገኛለች፡፡ የዛሬ ሳምንት ባነሳነው ርእስ ላይ እንደተመለከትነው ሁለቱን የመካከለኛው ምሥራቅ ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናትን በማሳመን ፍትህ የራቀው መግለጫ እስከ ማውጣት ደርሳለች፡፡ ምንም እንኳን የባለቤትነት ክርክሩን የመርታት አቅም እንዳላት የምትታመን ብትሆንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩ ላይ ያላት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑ ገዳሙን የመነጠቅ ዕድሏን እንደሚያሰፋው ይታመናል፡፡

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በሰላምና በፍቅር ይጠብቅ! ለዘገባው በዋነኝነት የሚያዚያ ፳፻፭ (2005) ዓ.ም. አዲስ ጉዳይ መጽሔትን እና የተዋሕዶ ሚደያ ማዕከል ዘገባዎችን ተጠቅመናል፡፡

የጻድቃኔ ማርያም ገዳምን ያውቁት ኖሯል?

ገዳሟ ከወረዳው ከተማ ሠላድንጋይ በስተምሥራቅ አቅጣጫ በእግር ጉዞ የዐሥር ደቂቃ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት የተመሠረተች ገዳም ናት፡፡ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስሥት ቱርኮች ግብፅን ወረው ክርስቲያኑን ፈጅተው በዚያው የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናትን ባቃጠሉና በፈጁት ጊዜ በወቅቱ ከተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የደብረ ምጥማቅ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡

ከወረራውና ከቃጠሎው በፊት አስቀድመው ቀሳውስቱ ጽላቷን አውጥተውና ሸሽገው አስቀምጠዋት ስለነበር በጊዜው አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የሚባሉ መነኩሳት ከብዙ ተከታዮቻቸው ጋር በሱዳን በኩል አድረገው ወደ ሀገራችን አምጥተው ጽላቷን ለአጼ ዘርዓያዕቆብ እንዳስረከቡ ከገዳሟ የተገኙት ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ንጉሡም ጽላቷን ተቀብለው ጅባት፣ ከዚያም አንጦጦ፣ በበረህ ተራራ ላይ፣ ደብረ-ብርሃንና በሌላም ስፍራ በማዘዋወር አስቀምጠዋታል፡፡ ከዚያ በኋላ አፄ ዘርዓያዕቆብ በተገለፀላቸው ራእይ መሠረት አሁን ደብረ ምጥማቅ እየተባለ በሚጠረው ስፍራ ቤተ ክርስቲያን አሳንጸው የቤተክርስቲያኒቱም ስም ግብጽ ባለው መጠሪያዋ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ደብረ ምጥማቅ ተብላለች፡፡

ከብዙ ዘመን በኋላ ግራኝ አህመድ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ሲያቃጥል ከተቃጠሉት መካከል አንዷ ይህች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ሆኖም ከወረራው በፊት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ በራይዕ በተገለፀላቸው መሠረት የቤተ ክርስቲያኑን ቅርስና ንብረት አሁን ፃድቃኔ ማርያም መካነ ቅዱሳን ገዳም በሚባለው ዋሻ ውስጥ ሰውረውታል፡፡

በኋላም በተቃጠለችው ቤተክርስቲያን ሌላ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በእርጅና ምክንያት ፈርሶ ስለነበር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንድ ኢጣሊያዊ መሃንዲስ ልከው በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም. ቤተከርስቲያኑን አሠርተዉት ነበር፡፡ በአሁኑም ሰዓት ከቆይታዋ የተነሳ በማርጀቷ ሌላ ቤተክርስቲያን ለማሠራት የግንባታ ፕላን ተዘጋጅቶ ቤተክርስቲያኗን ለመሥራት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ይህች ቤተክርስቲያን / ገዳም ብዙ ዕድሜ ያስቆጠረች ብትሆንም ታላቅ ዕውቅና ያገኘችው ከ፲፱፻፺ዎቹ ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ከ፴ ሰዎች በማይበልጡ የተጀመርው የጉብኝት ጉዞ በአሁኑ ጊዜ በዓመት ከ፻፶ ሺህ- ፮፻ ሺህ ሕዝብ በላይ ወደ ገዳሟ እንደሚመጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የፃድቃኔ ማርያም መካነ ቅዱሳን ገዳም ዓመታዊ በዓላት መስከረም ፳፩፣ ኅዳር ፳፩፣ ጥር ፳፩፣ ግንቦት ፳፩ እና ነሐሴ ፲፮ ናቸው፡፡ በተለይም በግንቦትና በነሐሴ በሚከበረው በዓሏ ላይ የሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በዚህ ቅዱስ ስፍራ በተለያዩ ደዌ የተያዙ ሰዎች ሲፈወሱ ማየትና መስማት ቦታውን እጅግ ታላቅ ያደርገዋል፡፡