ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለሃይማኖት

አቡነ ተክለሃይማኖት


ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፦ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እኚህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ካበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ። በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ እቁባቶች ያደርጋቸዋል።


በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእነርሱም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ። ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደ መኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።


እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ “ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት” አለ። የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዚእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።


ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።


ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመንፈስ ቅዱስ ጸና።


ከዚህም በኋላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ “ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል” ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።


ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው “ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታስነሳ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ”። ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ “ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል” እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።


ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣዖት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።


ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።


ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር። ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።


ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጠምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።


በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።


በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው ።በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኰረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ስለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።


በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በኋላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስኪሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።


ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።


መድኃኒታችንም እንዲህ አለው “ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ”። አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ። ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።


ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና ነሐሴ 24 ቀን ዐረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ሐይቅ እንደጸለየች።

በሸዋ ከፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች ሀገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ ሀገሯ ናት። በዚህም ሀገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ግንቦት 12 ቀን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና “በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች” በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።


በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን አፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነገሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማዊ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።


ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በጣም ተበሳጨችና በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት። ያም እሳት ትንታግ በአገልጋይዋ ጉረሮ ድረስ ዘለቀና ገደላት። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦችዋ መጥተው የአገልጋይቱን አስከሬን ወደሌላ ክፍል ወሰዱት። ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ “ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ” እያለች አለቀሰች።


ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለእግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች “አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ”። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በሐዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እሷ ወዳለችበት ክፍል መጥተው “እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ” አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ “ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን” ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔር አመሰገነች።


ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም “እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው” አሏት። እርሷም “ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው” አለቻቸው።

ከዚህም በኋላ ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ “በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየነሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር “ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈውን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መጽውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦

ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ፡ ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት “ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል” ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም “ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ… ” አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መጻተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደ እርስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች ከእግሩ ሥርም ወደቀች።

ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆኑ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ” አላት። እርስዋም “አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?” አለችው። “አዎን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ” አላት። “እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው” አለችው። “አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና ። የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም” በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና በአደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና “እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል” አላት።


ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ” አላት። በዚህን ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና” አለችው። “የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብዬ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋዬ እንደመሆኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና” አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ” አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ” ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዟት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ “እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ” እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህ አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።


ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው” አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ “ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል” በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም “ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ” እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ “ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን” አላት። እርሷም “ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ” አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ሁካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ “አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?” እያለች አደነቀች። ጌታም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን” አላት። እስዋም “አዎ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ” አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ “እነዚህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው” አለው። በዚህ ጊዜ “አቤቱ ፈጣሪዬ የእኔ መኖሪያዬ ወዴት ነው?” አለችው። ጌታም “መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች።

በየአንዳንዳቸው አክሊል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉባቸው የእነዚህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከርስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ “እነዚህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና” አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?” አላት። እርስዋም “አዎን ጌታዬ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው” አላት። “በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ” አለችው። “ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው” አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች።

ስለ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዕረፍት፦

ከዚህ በኋላ በአዲስ ተጋድሎ ጀመረች። ደናግሉን ልጆቿን ሰበሰበችና “ከእግዲህ እርስ በራሳችሁ በመፈቃቀር ኑሩ እግዚአብሔርም በመፍራት ተቀመጡ” አለቻቸው። ይህንንም ከአለች በኋላ ለ1079 ደናግል ወይም መነኰሳት አስተዳዳሪ እመ ምኔት ሾመችላቸው። “ከወሰንኩላችሁ ሕግ ወይም ከሰራሁላችሁ ሥርዓት አትተላለፉ ከእግዲህ ከዛሬ በስተቀር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንገናኝም እና” አለቻቸው። ይህንንም ተናግራ ከእነርሱ ስትለይ አንዲት መነኵሲት ወይም መበለት ጠርታ ሹል የሆኑ ብረቶች አምጭልኝ” ብላ አዘዘቻትና አመጣችላት።


ከዚያም በእናታችን ክርስቶስ ሠምራ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፈረችና በውስጡ ዕፀ ከርካዕ ወይም የሎሚ እንጨት አስተከለችበት። ዳግመኛ “ከእግዲህ እግዚአብሔር ይቅር እስኪለኝ ድረስ ከዚህ አልወጣም” ብላ ከጉድጓዱ ውስጥ ገባች። ሦስት የተሳሉ ጦርች በፊቷ ሦስት ጦር በኋላዋ፣ ሦስት ጦር በቀኝ ጎኗ፣ ሦስት ጦር በግራዋ ጎን ተከለች። መበለቲቱም የፊጢኝ ወይም የኋሊት በገመድ አሰረቻት። ከዚህም በኋላ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕዝብ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ሰዎች አጥብቃ ትጸልይና ታዝን ጀመር።


በዚህ አይነት ተጋድሎ ሰውነቷን ወይም ሥጋዋን በልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ ስትፈትን ኖረች። ፈጥና በክንፈ ረድኤት ወደ በዓቷ የምትመለስበት ጊዜ አለ። በዚህ አይነት ግብር ለብዙ ዘመን ኖረች። በምትሰግድበት ጊዜ ወደፊት ስትል ደረቷን ወደኋላ ስትል ጀርባዋን ወደቀኝ ስትል ቀን ጎኗን ወደግራ ስተል ግራ ጎኗን ጦሩ እየወጋት ከቊስሉ የተነሣ ጦሩ የወጋት ገመዱ የከረከራት መላ ሰውነቷ ሸቶ ተልቶ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ተጋድሎ አደረገች።


እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን እግዚአብሔር ኃይል ጸንታለችና ከጉድጓድ ወጥታ በጣና ባሕር ውስጥ ገብታ እንድትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ አዘዛት ከዚያም በባሕሩ ውስጥ እየጸለየች ሦስት ዓመት ተቀመጠች።


ከሦስት ዓመት በኋላ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በጣና ባሕር ውስጥ ሳለች ለጌትነቱ ክብር መሰገድ የሚገባው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእስዋ መጣ። እርሱም ጋር ቅዱሳን ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል እናቱ ማርያም መጡ። ዐሥራ አምስቱ ነቢያት ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰባ ሁለቱ አርድእት ጻድቃን ሰማዕታት ደናግልና መነኰሳት ሌሎች ሁሉም በየሥርዓታቸውና በየማዕረጋቸው በየነገዳቸው መጡ። ኄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት አለቃቸውን ሕፃኑ ቂርቆስን ተከትለው እደዚሁም ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በየነገዳቸውና በየወገናቸው መጡ።


ከነዚህ ሁሉ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት መጥቶ “ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ይወዳል እርሱ ጌታሽ ነውና” እያለ በገናውን ይደረድር ነበር። እንዲህም እያለ በሚዘምርበት ጊዜ በዚያ ያሉ ቅዱሳኖች በሙሉ “የእግዚአብሔር ባለሟል ወይም ወዳጅ ይህች ክርስቶስ ሠምራ በእውነት ብፅዕት ነች” እያሉ ዘመሩ።


በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዛሬ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ላስተላልፍሽ መጥቻለሁ” አላት። “ድካምሽ ወደዕረፍት ኃዘንሽ ወደ ደስታ ችግርሽ ወደ ብልጽግና ተለውጦልሻል። እውነት በእውነት እልሻለሁ ወይም እነግርሻለሁ በፍጹም ደስታ መታሰቢያሽን ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት አስደስተዋለሁ። በችግሩ ወይም በጭንቁ ጊዜ በመታመን ስምሽን ቢጠራ እኔ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድነዋለሁ።


የገድልሽን ዜና የሚናገረውን መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፍላቸዋለሁ። ቤተ ክርስቲያንሽን የሠራ ወይም ያሠራ ያሣነፀ ወይም ያነፀ እኔ በመንግሥተ ሰማያት ንጹሕ አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ። በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ በዕለተ አርብ ከተቆረሰው ሥጋዬ አበላዋለሁ። በስምሽ ለተጠማው እፍኝ ውሃ ያጠጣ እኔ በዕለተ አርብ ከጎኔ በፈሰሰው ደሜ አረካዋለሁ። በዓልሽ በሚከበርበት ዕለት ጧፍ፣ ዕጣን፣ ወይም ዘይት ንጹሕ ስንዴ የመሰለውንም ሁሉ መባ ያገባ መሥዋዕቱን እንደ አብርሃምና እንደ መልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አድርጌ እቀበልለታለሁ” አላት።


በዚህ ጊዜ “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባርያህ ባለሟልነትን በፊትህ ካገኘሁስ አንድ ጊዜ እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም “ትናገሪ ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ” አላት። ” አቤቱ ሥጋዬ የሚቀበርበትን ወይም የሚያርፍበት ቦታ ወዴት ታዝዛለህ” አለችው። መቃብርሽ በዚች ጓንጒት በምትባል ደሴት ውስጥ ነው” አላት። “ነገር ግን ሥጋሽ በመሬት ውስጥ ይቀበራል ስላልኩሽ ኀዘን አይግባሽ በኋለኛው ዕለት እኔ አስነሣዋለሁና” አላት።


“አቤቱ እንዲህ ከሆነ መታሰቢያዬን እያደረገ ስሜን እየጠራ በስሜ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ የሚቀበረውን እስከ ስንት ትውልድ ድረስ ትምርልኛለህ” አለችው። “እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ” አላት። ይህንም ቃል ኪዳን በሰጣት ጊዜ ፈጽማ ተደሰተች።
ዳግመኛም “ይህች ደሴት እንደ ደብረ ታቦርና ደብረ ዘይት ስሟ የተጠራ ይሁን” አላት። “እንደዚሁ ይህችን ሥጋሽ የምታርፍበትን ቦታ ቀደስኳት አከበርኳት። መጽሐፍ የተናገረውን አልሰማሽምን ቦታ ሰውን የሚያከብረው አይደለም ሰው ቦታን ያስከብረዋል እንጂ። ስለዚህ ነገር ስላንቺ ይቺን መካነ መቃብርሽን ቀደስኳት አከበርኳት። ስሟም ደብረ ፍቅር ደብረ ምሕረት ተብሎ ይሰየም ወይም ይጠራል። እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርልታል። እውነት እውነት እልሻለሁ አንቺን ያከበረ ሁሉ እኔ በሰማያዊ መንግሥቴ አከብረዋለሁ። አንቺን የወደደ ወይም ያፈቀረሽን እኔ አፈቅረዋለሉ።


ዳግመኛም “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ይህ የዛሬው በዓልሽ የደስታና የተድላ ቀን ነው” አላት። ይህንንም ብሎ በብዙ ወገን ወይም ሠራዊት ላይ ሾማት። “ክብርሽ ከአሮንና ከሙሴ፣ ከጴጥሮስና ከጳውሎስ፣ ሰይጣንን ድል ከአደረገው ከሕፃኑ ቂርቆስ፣ ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከፀሐየ ልዳ እየተባለ ከሚጠራ ከጊዮርጊስ ጋር ክብር ጋር ትክክል ነው” አላት።


በደብረ ጽዮን ከሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ጋር ትዘምሪ ዘንድ በክብር ተካከልሽ። በእውነት አንቺን የሚያፈቅሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው” አላት። ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ እግዚአብሔርን ከሚያከብሩ ወይም ከሚፈሩ በስተቀር በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውስ ተራራ ላይ ማን ይኖራል” ብሎ ተናግሯልና። ስለዚህም አንቺን የሚያከብሩ ሁሉ አንቺን ከአለሽበት ቦታ ገብተው ከአንቺ ጋር ይደሰታሉ”።
ከዚህም አምላካዊ ቃል ጋራ በነሐሴ 24 ቀን የአባታችን ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ዕለት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች። በዚህ ጊዜ የነጎድጓድ ብልጭልጭታ ሆነ ነቢዩ ዳዊት “በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ” ብሎ እንደተናገረ የመላእክት ሠራዊትና ጻድቃን ሰማዕታትም ሁሉ እልል እያሉ አመሰገኑ። እርሷም ከነርሱ ጋር እየተደሰተች አመሰገነች። ከዚያም መላእክት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አድርሰዋት ወይም አሳርገዋት በአሸናፊው በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሰገደች።


ከዚህ በኋላ ጌታ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን እናቴ ማርያምን ወደ ምትኖርበት ውሰዳት” አለው። ቅዱስ ሚካኤልም “ጌታ ወደ አዘዘልሽ ቦታ እንሒድ” አላት። ቅዱስ ሚካኤልም ይዟት ሲሔድ እጅግ የሚያስደነግጥና ከፀሐይ ከጨረቃ ከዋክብት ብርሃን ይልቅ ብርሃኑ የሚያበራ መንበር አየች። ይህን መንበር በአየችውም ጊዜ በጣም አድርጋ ወደደችው።


የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም “ክርስቶስ ሠምራ ምን ትመለከቻለሽ” አላት። “ያን ቡሩህ የሆነ መንበር እመለከታለሁ” አለችው። “ይህ መንበር ለአንቺ ቢሆን ትወጃለሽን” አላት። “አዎን ጌታዬ ለእኔ ቢሆን እወዳለሁ” አለችው። “እንግዲያውስ ለአንቺ የተዘጋጀ ነው” አላት። በዚያ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል “ጌታዬ መኖርያሽ እናቴ ከማርያም ጋር ነው ብሎኝ አልነበረምን”። ታዲያ እንዴት ይህ መንበር ለአንቺ የተዘጋጀ ነው ትለኛለህ” አለችው። መላአኩም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ለምን ቸኮልሽ” አላት። ይህን ካለ በኋላ ወደ እመቤታችን ወደ ድንግል ማርያም መኖርያ ወስዶ አደረሳትና። “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እግዲህ ተመልከች” አላት። በተመለከተቻት ወይም ባየቻት ጊዜም ማርያም ወይም ሰው አልነበረችም ነገር ግን ከፍታዋ ወይም ቁመቷ የላቀ ተራራ ነበረች እንጂ።


ቅዱስ ሚካኤልም “ማርያም ነች ብኸኝ አልበረምን ታዲያ እንዴት ተራራ ልትሆን ቻለች” አለችው። ያን ጊዜ ምሥጢሯ እስኪገለጽልሽ ድረስ ትንሽ ታገሽ” አላት። ከዚያም ቀና ብላ ብትመለከት እመቤታችን ድንግል ማርያምን አየቻትና እንደአሞራ በራ አንገቷን አቅፋ ሳመቻት። እመቤታችንም “ክርስቶስ ሠምራ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ አንቺንም የሚያፈቅር የገድልሽን ዜና የሚሰሙ ሁሉ የተባርኩ የተመሰገኑ ናቸው” በማለት ሳመቻት። ይህንም ከአለቻት በኋላ በቀኟ አስቀመጠቻት…።


ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ አባ ይስሐቅ የሚባል መነኵሴ ከእናታችን ከክርስቶስ ሠምራ ዘንድ ቢሄድ ሥጋዋ ብቻ ወይም አስከሬኗ በጉድጓድ ውስጥ እንደተተከለ ምሰሶ ወይም ዓምድ ቆሞ አገኘው። ነፍስዋ ከሥጋዋ ያልተለየች ወይም በሕይወት ያለች መስሎት ነበርና “እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ባርኪኝ” አላት። የሚመልስለት ቢያጣ ወደ እርስዋ ቀረበና ሥጋዋን ዳሰሰው። እንዳረፈችም ባወቀ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ ከመሬት ላይ እየወደቀ እየተነሣ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።


መነኰሳቱን ሁሉ ያለቅሱላት ዘንድ ጠራቸው። መነኰሳቱም እየተሽቀዳደሙና እየተሯሯጡ መጥተው አርፋ አገኟት። በዚህ ጊዜ “አንቺን የተሸከመች ማኅፀን የተባረከች ነች አንቺንም ያጠቡ ጡቶች የተመሰገኑ ናቸው” እያሉ ጽዕኑና መራራ ልቅሶን አለቀሱ።
ከዚህ በኋላ አባ ይስሐቅ ሥጋዋን ወይም አስከሬኗን በንጹሕ በፍታ ገንዞ በሳጥን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቀበራት። መነኰስ ይስሐቅም ወደ በዓቱ መመለሱ ቀርቶ በዚያው ቤተ ክርስቲያን በስተ ምሥራቅ በኩል በቁመቱ ልክ ጎድጓድ አስቆፍሮ በውስጧ ገባ።
ከዚያም ከጎድጓዱ ውስጥ ገብቶ “ከእንግዲህ እስክሞት ድረስ እንደ እናቴ ክርስቶስ ሠምራ ከዚህ ጎድጓድ አልወጣም” በማለት ወሰነ። ይህንንም ካለ በኋላ መሪር እንባ እያለቀሰ እህል ሳይቀምስ እስከ 40 ቀን ተቀመጠ። ከ 40 ቀን በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየችና በእናታችን በክርስቶስ ሠምራ አማላጅነትና ልመና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ።


እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ የኖረችው ሦስት መቶ ሰባ አምስት (375) ዓመታትን ነው። ከእናታችን ከቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ።

ደብረ ታቦር ✍ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ደብረ ታቦር

የሞተውን ሙሴን ከ1644 ዓመታት በኋላ አምጥቶ፤ የተሰወረውን ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ የሕያዋን አምላክና የሙታን አሥነሺያቸው እርሱ መኾኑን የገለጸበት፡ታላቅ ምስጢር የተከናወነበት ነው፡፡ (ማቴ 17፡1-9)።

ይኽ በዓል ከጌታችን 9ኙ ዐበይት በዓላት አንደኛው ነው። ታሪኩ በ3ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲኾን ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎቹን ሐዋርያትን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ የምስጢር ደቀ መዛሙርት የሚባሉት፣ በእምነት በተስፋ በፍቅር የሚመሰሉት ሦስቱን (ጴጥሮን፣ ያዕቆብን፣ ዮሐንስን) ይዟቸው ወደ ታቦር ተራራ ወጣ።

ጌታ 8ቱን ሐዋርያት ይዟቸው ያልወጣው በይሁዳ ምክንያት ነው።ምክንያቱም ከምስጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባኹበት ባለ ነበርና ነው፤ ነገር ግን በተራራው ላይ ለ3ቱ የተገለጸው ምስጢር ከተራራው ሥር ላሉት ከይሁዳ በስተቀር ተገልጾላቸዋል፤ ለእኛም እንደ ሐዋርያት ምስጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፡፡

የታቦር ተራራን የመረጠበት ምክንያት

1)አስቀድሞ የጌትነት ክብሩ በዚያ ተራራ ላይ እንደሚገልጽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 88፡12 ላይ፦ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚኣከ ይትፌሥሑ” (ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ይደሰታሉ) በማለት ጌታ በዚያ ተራራ ላይ ብርሃኑን ሲገልጽ የብርሃኑ ነጸብራቅ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ እንደሚታይ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡

ሌላው ታቦር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ጊዜያት ሲጠቀስ በተለይ በመሳ 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ጠላት የነበረው ሲሳራን መስፍኑ ባርቅ በተራራው ላይ ድል ነሥቶበት ነቢይቱ ዲቦራም በተራራው ላይ በደስታ አመስግናበታለች ዘምራበታለች። በተመሳሳይ መልኩ የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖችን ጠላት የኾነውን ዲያብሎስን የኹላችን ፈጣሪ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ አምላክነቱን ገልጦ ድል ስለነሣው ነቢያት ሐዋርያት ምእመናን የሚያመሰግኑት ስለኾነ ለምሳሌነቱ ተስማሚነት ያለውን የታቦርን ተራራን መርጦታል፡፡

ለምን ሙሴንና ኤልያስን ከነቢያት መኻከል መረጠ? ቢሉ፦

ሀ) በማቴ 16፡13 ላይ ሐዋርያትን ስለማንነቱ እንደጠየቃቸው እንደመለሱለት ኹሉ በእውነት ጌታችን የሙሴና የኤልያስ በአጠቃላይ የነቢያት ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ሲገልጽላቸው ነው።

ለ) በዘፀ 33፡17-23 ላይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥልቅ ግንኙነት የተነሣ “እባክኽ ክብርኽን አሳየኝ” ብሎ ልመናን አቀረበ፤ እግዚአብሔርም “ወአነብረከ ውስተ ስቊረተ ኰኲሕ ወእከድን እዴየ በላዕሌከ እስከ አኃልፍ” (በሰንጣቃው ዐለት አኖርሃለኍ፤ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይኽ እጋርዳለኍ፤ ካለፍኍ በኋላ እጄን አንሥቼልኽ ጀርባዬን ታያለኽ፤ ፊቴ ግን አይታይም) ብሎታል (ዘፀ ፴፫፥፲፯-፳፫)፡፡

ይኸውም ጀርባ በስተኋላ እንደሚገኝ ኹሉ በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በታቦር ተራራ ላይ እንደሚገለጽለት ሲያመለክተው ነው። ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብም ስለ ታቦር በሚተነትነው መጽሐፉ ሙሴ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውሃ ከእስራኤል ጋር በበደለው በደል ምክንያት ምድረ ርስት ኢየሩሳሌም እንዳይገባ አይቷት ብቻ በናባው ተራራ ላይ እንዲያርፍ ኾኗል (ዘፀ ፴፪፥፶፪፤ ዘፀ ፴፬፥፩-፰)፡፡ ይኽ ለሙሴ አሳዛኝ ቢኾንም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሙሴ በፊት በሩቁ ያያት ግን ያልገባባት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ያለች ታቦር ተራራ ላይ አምጥቶት በዘመነ ብሉይ በአካለ ሥጋ ያልገባባትን ርስት እንዲገባባት አድርጎታል፤ ይኸውም አዳምና ልጆቹ በአካለ ሥጋ ያጡትን ርስታቸው ገነትን በአካለ ነፍሳቸው ዳግመኛ ሊያገባቸው እንደመጣ የሚያመለክት መኾኑን በስፋት አስተምሯል፡፡

ጌታችን በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በሐዲስ ኪዳን ከነበሩት ከሐዋርያት ሦስቱን በታቦር ተራራ ላይ ማውጣቱ፦

1) የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በመኾኗ ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንደሚነገሩ ለማመልከት

2) በተራራ በተመሰለች በጉባኤ ቤት ብሉይና ሐዲስ እንደሚነገሩ ለመግለጽ፡፡

3) ሌላው የታቦር ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ስትኾን ይኸውም ጌታ ነቢያትንና ሐዋርያትን በተራራዋ ላይ መሰብሰቡ መንግሥተ ሰማያትን ነቢያትም ሐዋርያትም እንደሚወርሷን ለማመልከት

4) ሙሴ ያገባ ሲኾን ኤልያስ ድንግል ነውና መንግሥተ ሰማያትን ደናግልም ያገቡም እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ነው፡፡

5) እንደ ያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜ ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን ሲጽፍ፦ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) እንዳለ፤ ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበር” (ዮሐ 1፡1) ብሎ እንደ ሙሴ አምላክነቱን የሚመሰክር ነውና ሙሴ አስቀድሞ የጻፈልኝ፤ አኹንም ዮሐንስ አምላክነቴን የሚጽፍልኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡

6) ሙሴና ኤልያስ ይመሳሰላሉ፤ ይኸውም በሲና ተራራ 40 ቀንና ሌሊት እንደጾመ ኤልያስም በደብረ ኮሬብ 40 ቀንና ሌሊት የጾመ ነውና፨

7) ሙሴ ንጉሡ ፈርዖንን የገሠፀ እንደነበር ኤልያስም ንጉሡ አክዐብን የገሠፀ ነውና፨

8) ሙሴ ከንጉሡ ፈርዖን ፊት ሸሽቶ እንደሄደ ኤልያስም ከንግሥቲቱ ኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ ሄዶ ነበር።

9) ዳግመኛም ሰማይኑን ዝናብ እንዳያዘንም በተሰጠው ሥልጣን ባሰረውና ከ3 ዓመት ከ6ወር ቆይታ በኋላ እንዲዘንብ በፈታው ኤልያስን እንዳመጣ ኹሉ የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሥልጣነ ተሰጥቶት “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” (ማቴ 16፡18-19) ላለው ለጴጥሮስን ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን መስጠቱን ለማመልከት አምጥቷቸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን ያለው መንፈሳዊ አከባበር ደማቅ ነው፤ ይኽ በዓል በቤተ ክርስቲያን በማሕሌት በቅዳሴ በትምህርት የሚከበር በዓል ሲኾን በሀገርኛ የቡሔ በዓል ይባላል፤ ቡሔ ማለት ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ላይ ሲገልጹት ቧ ብሎ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል የልብሱን እንደ በረዶ ነጭ መኾን ያስረዳል ስለዚኽ የብርሃን፣ ብርሃናዊ ማለት ነው፡፡ በዚህ በዓል በታቦር የታየው የብርሃኑ ምሳሌ የሚሆን ችቦ ይበራል፤ ሌላው በዚኽ በዓል ሰሞን በገጠር ከተራራ ላይ እረኞች ሕጻናት ዥራፍ እየገመዱ ማስጮኻቸው ጌታ በተራራ ላይ ብርሃኑን በገለጸ ጊዜ አብ በደመና ኾኖ “እርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ባለ ጊዜ ሐዋርያት በድምፁ ደንግጸው መውደቃቸውን ለማመለክት ነው፡፡ ጌታችን ጌትነቱን ገልጦበታል። የአብ ድምፅ ተሰምቶበታልና ታቦር ተራራ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።” በማለት ገልጦታል (2ኛ ጴጥ 1:17-18)

መልካም በዓል

“አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” ሉቃ 1 ፡28

ጾመ ፍልሰታ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የምንኖር የእግዚአብሔር ልጆች በረከትን ከምንቀበልባቸው የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 16 ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ፍቅር ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ ለእግዚአብሔር በመገዛት በተሰበረ ልቦና እና በተሰበሰበ ህሊና ከጥሉላት መባልዕት (ለሰውነት ብርታት ከሚሰጡ የእንስሳት ተዋፅኦ እና ቅባትነት ካላቸው ምግቦች) እና ከክፉ ሥራ ሁሉ ተለይተን በበረከት የምንትረፈረፍበት የጾም ወቅት ነው። ፍልሰታ የሚለው ቃል ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር፣ የነበሩበትን ስፍራ ለቆ ወደ ሌላ ስፍራ መወሰድ ወይም መፍለስ ማለት ነው። ጾም አምላካችን እግዚአብሔርን የምናስብበት፣ ነፍስና ሥጋችንንም የምናስገዛበት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ነው። በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳን አበው ጾም የጸሎት እናት፣ የእንባ ምንጭ፣ የነፍስንም ቁስል የምትፈውስ መድኃኒት መሆኗን አስተምረውናል። በመሆኑም በከበረ ጾም የለበሱት መንፈሳዊ ጸጋ ዛሬም ድረስ ስማቸው በሚጠራበት ክብራቸው በሚዘከርበት ቦታ ሁሉ አጋንንትን የሚቀጠቅጥ ኃይልና የትሩፋት ፍሬ ሆኖ ይገኛል።

ጾመ ፍልሰታን በመጀመሪያ ጊዜ የጾሙ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው። የጾሙበት ምክንያትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታ አርፋለች። ከጌታችን ዕርገት በኋላ በእርስዋ ሲጽናኑ የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በእመቤታችን እረፍት አዝነው፤ አልቅሰው የከበረ ሥጋዋን ተሸክመው በክብር ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ ሲጓዙ አይሁድ በክፋት ተነሱባቸው። ቀድሞ ‘ልጅዋ ተነሣ ዐረገ’ እያሉ ያስቸገሩን አንሶ ደግሞ እርስዋንም ‘ተነሣች ዐረገች’ እንዳይሉን ሥጋዋን እናቃጥል ብለው በኃይል መጡባቸው። ከእነዚሁ አይሁድ መካከል ጉልበታም የነበረ ታውፋንያ የተባለ ሰው በጉልበቱ ታምኖ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ጎትቼ እጥላለሁ ብሎ የአልጋውን ሸንኮር ቢይዝ የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጁን ቀጥቶታል። ወዲያውም መላኩ የከበረች የድንግልን ሥጋ ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በደመና አሳርጎታል። የቀሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ እመቤታችን ሲያዝኑ ሲተክዙ ቅዱስ ዮሐንስን አግኝተው የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ? ቢሉት በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አለች ብሎ አጽናንቷቸዋል።

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈሳዊ ፍቅር እና ቅናት ተነሣሥተው ለቅዱስ ዮሐንስ የተገለጠ ምሥጢር ለእኛም ይገለጥልን ብለው ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ፤ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሰነበቱ። ሁለተኛውን ሱባኤም ሲጨርሱ በ14ኛው ቀን እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶ የከበረ መዓዛ ያለውን የእመቤታችንን ሥጋ በመላእክት እጅ አምጥቶ ሰጥቷቸዋል። ቅዱሳን ሐዋርያትም በፍጹም ምስጋናና በታላቅ ክብር እመቤታችንን በጌቴሰማኒ ቀብረዋታል። ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጇ ሥልጣን ፍጹም ኃይል ሆኗት በክብር ተነሥታለች። ትንሣኤዋን ‘ከመ ትንሣኤ ወልዳ’ ወይም ‘እንደ ልጇ ትንሣኤ’ ነው ያሰኘውም ይሄ ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሙታን ተነሥታ፣ በውዳሴ መላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ ከቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ አግኝቷታል። ሐዋርያው ቶማስም ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ከወንድሞቼ ተለይቼ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ለማየት አልታደልኩም ብሎ በጣም አዘነ። እመቤታችንም ቶማስን ‘ከአንተ ቀድሞ ትንሣኤዬን ያየ የለም እንግዲህ ሄደህ ለወንድሞችህ ሐዋርያት ተነሣች ዐረገች ብለህ የምሥራች ንገራቸው፣ ምልክትም ይሆን ዘንድ እነሆ መግነዜን (ሰበኔን) ውሰድ ፣ አንተ ዕርገቴን እንዳየህ እነርሱም ይህን ዐይተው እንዲያምኑ’ ብላው ወደ ሰማይ ዐረገች። የሐዋርያው ቶማስ ሐዘንም ወደ ደስታ ተለወጠ። ይህ ሐዋርያ ኢየሩሳሌም ደርሶ ሌሎቹ ሐዋርያትን አገኛቸው ‘የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ?’ ብሎም ጠየቃቸው። እነርሱም እንደቀበሯት ነገሩት። ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ይህ እንዴት ይሆናል? አላቸው። እነርሱም መጠራጠር ልማድህ ነው እያሉ መቃብሯን ሊያሳዩ ወሰዱት።

ሲደርሱም መቃብሯ ባዶ ሆኖ አገኙት ፣ እጅግም ደነገጡ። ቶማስም አትደንግጡ እመቤታችን ከሙታን ተነሥታ በውዳሴ መላእክት፣ በክብር ስታርግ አግኝቻታለሁ። እንዲያውም የተከፈነችበትን ሰበን ሰጥታኛለች ሲል ከእመቤታችን እጅ የተቀበለውን ሰበን አሳያቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም በሆነው ሁሉ ተደነቁ። በቶማስ እጅ ያለውንም የእመቤታችንን ሰበንዋን ለበረከት ተከፋፈሉት። በሰበኑም ሙት ያስነሱበት፣ ድውይ ይፈውሱበት፣ አጋንንትን ያርቁበት ነበር።ካህናት አባቶቻችን በእጅ መስቀላቸው ላይ የሚያደርጓት ጨርቅ የዚህ ሐዋርያት የተከፋፈሏት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሰበን ምሳሌ ናት። ዛሬም ድረስ ያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ አርፎበት የነበረው መቃብር በምዕመናን ይጎበኛል። ቅዱሳን ሐዋርያት ሐዋርያው ቶማስ ያየውን የእመቤታችንን የትንሣኤዋንና ዕርገቷን ክብር ያዩ ዘንድ በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ደግመው ሱባኤ ገቡ። በ16ኛው ቀን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረች እናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ተገለጠላቸው። እመቤታችንን መንበር፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ዋና ዲያቆን አድርጎ እርሱም ገባሬ ሰናይ ካህን ሆኖ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። የቅዱሳን ሐዋርያቱም ሱባኤ ሰምሮላቸዋል።

በዚሁ መሠረት የከበረች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምዕመናን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አብነት በማድረግ እነርሱ በዚህ ታላቅ ሱባኤ እመቤታችንን እንዳገኙ፣ የማያልቅ የእናትነት በረከቷን ለማግኘት፣ በተወደደ አማላጅነትዋም የልጇን ይቅርታና ምሕረት ለማግኘት፣ በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን። ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅዱሳን ሐዋርያት ተባርኮ በተሰጠን በዚህ ጾመ ፍልሰታ ሌሊቱን በሰዓታት፣ ነግሁን በኪዳን እና በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ከቅዱስ ኤፍሬምና ከአባ ሕርያቆስ በፈቃደ እግዚአብሔር የተገኙትን የእመቤታችንን ምስጋናዎች የውዳሴዋን እና የቅዳሴዋን ትርጓሜ በማሰማት ቅዱስ ወንጌሉ ተሰብኮ በከበረ ቅዳሴ የመድኃኔዓለምን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ታቀብላለች።

ይህ ምሥጢር የተረዳቸው በርካታ ምዕመናን ሱባኤውን በታላላቅ ገዳማት ተወስነው ሲያሳልፉ እጅግ ብዙዎች ደግሞ በያሉበት ደብር ሥርዓተ ቅዳሴውን እያስቀደሱና በጸሎት እየተማጸኑ ይጠቀሙበታል። እንግዲህ በያለንበት ቦታ በዚህ ሱባኤ በንስሐ በታጠበ ሕይወት በረከተ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማግኘት እንድንተጋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታሰማለች። የእግዚአብሔር አብ ጸጋ ፣የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችንም ጋር ይሁን።

ምንጭ
1 የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
2 ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ

እጨጌ (እጨ) አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ

በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 ዓመት ለኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩት ጻድቅ ።

እጨጌ (እጨ) አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ፦ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ “በምን አውቀኸኝ ነው?” ብላ አቅፋ ሳመችውና “ከእንግዲህ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ዓመት ትኖራለህ…” ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኋላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጣ። ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኵስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖረዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዮሐንስ ወደ ተዘጋጀላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡


ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡


አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚህም በኋላ “ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?” ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም “አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?” አሏት እርሷም “አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?” አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው “በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ” ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ “የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ” ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለሃይማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዮሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምህረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡


አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበስ በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዮሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኋላ ዕረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋርያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ “ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኵሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…” የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡


ቅዱስ አባታችንም በ 500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው “በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም” አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ 134 ዓመት በኋላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡


ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምህረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምህረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡


ከአባታችን ከእጨጌ አቡነ ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።

ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ

በሰማዕትነት እንደሚያርፉ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡ “አለቃ ተጠምቀ” የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው “ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ” ብለዋቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት ናቸው። አቡነ ጴጥሮስ ። የተወለዱት በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ነው፡፡

ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መምህር ኃይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ሁሉንም በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አወቁ፡፡ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሐ አባት ሆኑ፡፡
ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡

ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለሀገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡

በወቅቱ በነበረው ጦርነት የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም “ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ” በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያንቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን “የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል” ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኃይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡ እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡

ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር።

“ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው “ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም” ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡ወደ ምሥራቅ አፍሪካው ዜና መዋዕል አዘጋጁ ወደ ፖጃሌ ዘገባ እንመለስና የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- “ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞች ሦሰት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው፤ መካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡

የቀረበባቸውም ወንጀል “ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል” የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም “ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፡- “አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡ ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ፡- “አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፤ እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን” ብለው አወገዙ፡፡

ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍጥነት ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ፡፡ ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡ የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኚያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ “ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ “ይህ ያንተ ሥራ ነው” ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡ ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ “ተኩስ!” በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡

ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው” በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?” ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውን ተናረዋል፡- “አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡
ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት “በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል” አለኝ፡፡ “እንዴት?” ብለው “አላየህም ሲያጨበጭብ?” አለኝ፡፡ “ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባህል ሲናደድም ያጨበጭባል” አልኩት፡፡ “እንዴት?” ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡ “ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ” ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል” ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል ሙስሊም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ። በዚያው እርሷም “የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ” ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ ቀብራቸው በምሥጢር መፈጸሙን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምሥጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም “ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምሥጢር ቀበሯቸው” ከሚል ከመላምት ያለፈ ነገር ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ “ፉሪ ለቡ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው “ሙኒሳ ጉብታ” ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡

እንዲሁም የአቡነ ጴጥሮስን ሥጋ በተመለከተ ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአ.አ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር መደረጉ በትንሣኤ መጽሔት ቁ.58 1978 ዓ.ም ላይ የተገለጠ ቢሆንም ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ቅዱሳን መላእክት የጻድቃንን በድን እያመጡ ወደሚያስቀምጡበትና በውስጡ የሚቀመጥ አስክሬን ወደማይፈርስበት አቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ገዳም መላእክት ወስደው እንዳስቀመጡትና በዚያም እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ውስጥ የቅዳሱኑ አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ የአንገት ክራቸው ራሱ ሳይበጠስ እንደዛው እንደነበሩ ስለሚገኝ ቦታውም እጅግ ትልቅ የቃልኪዳን ቦታ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በዚህ በጨረሻው ሀሳብ ይስማማል፡፡

ሰማያዊ ክብርን የሚያስገኝ አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተክርስቲያን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) አቡነ ዼጥሮስን “የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት” ወይም በፈረንጅኛው አፍ (MARTYR OF THE MILLENIUM) በሚል መጠሪያ ሰይሟቸዋል።
ላልተነገረላቸውና ላልተዘመረላቸው ለእኚህ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያናችን ድንቅ አባት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 12 ቀን 1998 ዓ.ም እኚህን ሰማዕት “አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ” ተብለው እንዲጠሩ ወስኗል፡፡ በስማቸውም መቅደስ እንዲታነጽ ፈቅዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት (ኢሳ 56፡4) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቁ በተወለዱበት ሥፍራ መታሰቢያ አቁማላቸዋለች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው የተሰየመው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና መታሰቢያ ሐውልታቸው ሲሠራ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ለግንባታ የሚሆን አሸዋ ከመርዳት አንስቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ድንኳን እስከመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረዋል፡፡ ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የአባታችንን እጅግ አኩሪ ታሪክ ሲያዘክራቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአ.አ መሐል ከተማ ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።

📖የቤተክርስቲያን ፈተና

የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከዓለመ መላእክት ነው፡፡ ታዲያ ፈተና ሁሌ አብሯት የሚኖር ቤተክርስቲያን መፈተን የጀመረችው በዚሁ በዓለመ መላእክት ነበር፡፡ ዲያብሎስ ትዕቢትንና ሐሰት ከራሱ አንቅቶ መላእክትን «እኔ ፈጠርኋችሁ» በማለት ባሰማው የሐሰት አዋጅ ከሰው ልጅ ወደዚህ ምድር መምጣት ጀምሮ በብሉይ ኪዳንም በርካታ ፈተናዎች ተፈራርቀዋል፡፡

የቤተክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ለቤተክርስቲያን የመፈተን ምክንያት የሚሆኑ አካላትንና ድርጊቶችን ቆጥሮና ወስኖ ማስቀመጥ ወይም መገደብ ባይቻልም ጐልተው የሚታዩትን መዘርዘር ግን ይቻላል፡፡ ከእነዚህ የፈተና ምንጮች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

«የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች በጌታ አነጋገር «ጸራዊ» በሐዋርያት አነጋገር «ቢጽ ሐሳውያን» በሊቃውንት አነጋገር «መናፍቃን» ይባላሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው ወይም ከቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተወሰነውን የተማሩ ፤የተወሰነውንም ተምረው ያልያዙ ጐደሎዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እንክርዳድ ስንዴ መስሎ እንደሚያድግ በክርስቶስ ዐጸደ ወይን በቤተክርስቲያን ውስጥ የበቀሉ አሳሳቾች ናቸው፡፡

ስልታቸውን በየስፍራውና በየዘመኑ እየለዋወጡ ሐመረ ኖኅ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ማዕበላቸው እያንገላቷትና እያማቷት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ወዳልተሰበኩት ሕዝብ ደርሳ ትምህርቷን እንዳታስተምር ልዩ ልዩ የክህደት ትምህርት በመፍጠር አባቶችን ሥራ ያስፈቱ ናቸው፡፡ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በክህደት ትምህርታቸው ብቻ ሳይቆጠቡ ቤተክርስቲያን ላይ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ የተቸገሩ ምእመናንን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ እንሰጣለን በማለት፣ የቤተክርስቲያኒቱን የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት እንረዳለን በማለት፣ እንዲሁም ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን በመጠቀም የቤተክርስቲያን ዋነኛ የፈተና ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ ከጌታ ትንሣኤ እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ዘመነ ሐዋርያት ከ70 ዓ.ም እስከ 160 ዓ.ም ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዋርያነ አበው እንዲሁም ከ16ዐ ዓ.ም እስከ 312 ዓ.ም ያለው ዘመነ ሰማዕታት በመባል ይታወቃል፡፡በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍላተ ዘመናት የነበረው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከአይሁድ ጋር የተደረገ ተጋድሎ ነው፡፡ ይኸውም ምንም እንኳን የአይሁድ ማኅበረሰብ ቃል ኪዳን የተገባለት፣ ትንቢት የተነገረለት፣ በአንድ አምላክ አማኝ ቢሆንም የክርስቶስን አዳኝነትና አምላክነት ላለመቀበል በአመጽ በመግፋቱ፣ እነርሱን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስና ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ነበር፡፡

ሦስተኛው ክፍል ግን ቅዱሳን አበው ከአላውያን ነገሥታት ጋር ባደረጉት ተጋድሎ የሚዘከር ዘመነ ሰማዕታት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና በመምህራኑ አማናዊ ምሳሌነት በመላው ሮም የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ለባሮች የነጻነት ትምህርት የተሰበከላቸው ሲሆን ባለጸጋዎችም ቢያምኑ የክርስቶስ አገልጋዮች ለመሆን እንደሚበቁ ተነገራቸው፡፡ /1ቆሮ 7፥22/ የአሕዛብን የቀደመ ትዕቢትና ኩራት የእግዚአብሔር ቃል ሲያፈራርሰው፤ የአሕዛብን የአመንዝራነት ሕይወት የክርስቲያኖች ቅድሰና አሸነፈው፡፡ በአሕዛብ ልማድ በወንዶች መካከል ሴቶች የክብር ቦታ ያልነበራቸው ሲሆን በክርስትና እኩልነትና መከባበር ታወጀ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ክፉዎች በክርስቲያኖች ላይ የሰውን ሥጋ ይበላሉ፤ ለቄሳር አይታዘዙም፤ ግብር አይከፍሉም፤ የሚሉ ተራና ክፉ ወሬዎችን አወሩ ፡፡ በዚህ የተነሳ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ያሉ ኢአማኒያን/ከሃድያን/ ነገሥታት ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት እንዲያልፉ ያደረጉበት እኩይ ተግባር ፈጸሙ፡፡ ይህም ደጉ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መንበረ ሥልጣኑን ይዞ ለክርስቲያኖች ሠላም እስኪያወርድላቸው ድረስ የቀጠለ ጉዳይ ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን ለምድራዊ ኑሮ ሲባል በተለያየ ሥርዓተ መንግሥት ሥር የሚኖሩ ሰዎችን ነው በሥርዓቷና እና በትውፊቷ እንዲኖሩ የምትጥረው፤ የእርሷ ድርጊት ሁሉ ከአመራራቸው ጋር የማይሄድ የሚመስላቸው ሁሉ እንደየዘመናቸው ሁኔታ መከራን አጽንተውባቸዋል፡፡ ይህም የሁል ጊዜ የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡

«የክርስቶስ ፍቅር ገብቷቸው ክርስትናንና ከዚያ የሚከተሉትን ኃላፊነቶችን፣ ክህነትን እስከ ጵጵስና ድረስ «አውቃለሁ፤ እበቃለሁ» ብለው ወይም « ይገባኛል» ብለው ሹመት ፈልገውና ተካሰው ሳይሆን «እኛ አንበቃም ተውን» እያሉ፣ ነገር ግን ለመንጋው የግድ መሪ ስለሚያስፈልገው «እናንተ ለዚህ ሓላፊነት ትበቃላችሁ መንጋውን ጠብቁ» እየተባሉ አደራ ሲጣልባቸው የተሰጣቸውን ከባድ ሓላፊነት የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የተወጡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች ቤተክርስቲያናችን አሏት፡፡

በሦስቱ ጉባኤያት /ኒቅያ ቁስጥንጥንያና ኤፌሶን/ ዶግማዋን አጽንታ፣ ክፉዎችን ለይታ፣ ጥርት ያለውን እምነት ይዛ፣ አንድነቷን ጠብቃ የተጓዘችው አንዲት ዓለም አቀፋዊት ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የሕንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን የአሳዛኝ ታሪክ ምሳሌ ያደረጋት የመናፍቃን ደባ ነው፡፡ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክሳውያኑ ጐራ ተለይታ የኖረችው እዚህ ግባ በማይባል ፖለቲካዊ / ምድራዊ ሥልጣን/ ምክንያት በተጀመረ ጠብ ነው፡፡

«ሰውን ብትታገል ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በመጥቀስ የጻፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ነው / የቤ.ተ. ገጽ 48/።

ፈተና የቤተክርስቲያን የመኖሯ መገለጫ ነው፡፡ነገር ግን ቤተክርስቲያን ፈተና በሚገጥማት ወቅት በሚነሳው ማዕበል ተከፍተን ከመርከቧ ወደ ባሕር እንዳንወርድ ምን ማድረግ ይገባናል❓

ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን፡፡የ አበው አባቶቻችን የተጋድሎ ገድል ስናነብ የምንረዳው ምንም እንኳን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ቢኖራቸውም ከባድ ፈተና በገጠማቸው ጊዜያት ግን የበለጠ ይበረታሉ። በርካታ ቃል ኪዳናትን የተቀበሉት በርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍትን የጻፉት የብዙ ጸጋ ባለቤት የሆኑት በፈተና ውስጥ ነው፡፡

የምንማረው ከአባቶቻችን ነውና ቤተክርስቲያን ፈተና ላይ በምትሆን ጊዜ በጋዜጣ በሚጻፈው፣ በድረገጽ በሚለቀቀው «እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ» ወሬ ተገፍቶ እርሱን ብቻ በማውራት የራስ ሕይወትን መዘንጋት አይገባም፡፡ የሚሰሙት ዜናዎች፤ የሚፈጸሙት ድርጊቶች የግል መንፈሳዊ ሕይወትን የመሸርሸር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የቀደመ መንፈሳዊ ሕይወታችን መጠበቅ ማጽናት እግዚአብሔር አምላክ በፈተና ውስጥ ለቤተክርስቲያን በጐ የሆነውን ሁሉ እንዲያደርግ ጉዳዩን በጸሎት መያዝ መሆን አለበት፡፡

ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነታዊ /ዶግማዊ/ በሆነ ችግር የተፈተነች እንደሆነ የቤተክርስቲያን ቋሚ ምስክር የሆኑ መጻሕፍትን፣ ትውፊተ አበውን፣ የቀድሞ የቤተክርስቲያን ድንጋጌዎችን መጠየቅ፣ ማንበብ በእርሱም መመራት ተገቢ ነው፡፡

ከመ አድኃኖሙ መልአከ እግዚአብሔር ለሕጻን ወእሙ


በዘመነ ሰማእታት ከሐድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቲያኖች ላይ መከራ አጽንተውባቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሰማእትነትን ሲቀበሉ የተቀሩት አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ እየሉጣም የሦስት ዓመት ህፃን የነበረውን ቅዱስ ቂርቆስን ይዛ ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኮንን አገኘችው ሰዎችም ነገር አሰሩባት ወደእርሷ አስቀረባት እና ስለ ጣዖት አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኮንን ሆይ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ህፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እሱን ጠይቅ አለችው፡፡

ህፃኑም ወዳለበት ጭፍራውን ልኮ ወደእርሱ አስመጣው ህፃኑም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ህፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው፡፡ ህፃኑም መልሶ አዎ ለኔ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፡፡ መጻሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏል እና አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስካስደነገጣቸው ድረስ ንጉሱን መኳንንቱንና ጣኦታቱን ረገማቸው፡፡ ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ፡፡ መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በያይነቱ በሆነ ስቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው እናቱንም ከእርሱ ጋር አሰቃያት፡፡ እግዚአብሔርም ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር፡፡ ብዙዎች አህዛብም ይኸንን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማእትነት ሞቱ፡፡ የሰማእትነትንም አክሊል ተቀበሉ፡፡

በህፃኑም ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት፡፡ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው፡፡ መስፍኑም በውስጡ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ፣ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምራችሁ ታላቅ የብረት ጋን አምጡልኝ ብሎ ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም እንዳዘዛቸው ካደረጉ በኋላ ያዘዝከንን ሁሉ ፈጽመን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፡፡ ድምፁ እንደነጐድጓድ ይጮኸል ወላፈኑም እንደጸሐይ ነጸብራቅ በሩቁ ይጋረፋል፡፡ የፍላቱም ኃይል በ14 ክንድ ያኽል ከፍታ ወደ ላይ ይዘላል፡፡ እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት በዚህ ጊዜ ህፃን ቂርቆስና እናቱ እየሉጣ በክርስቶስ ሥም ስለሚያምኑ አስረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ሊጨምሯቸው ከእስር ቤት አወጧቸው፡፡ በዚያም ፍላቱ ወደላይ በሚዘል ብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው የእነዚህን ቅዱሳን አሟሟት ያዩ ዘንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ቅድስት እየሉጣ የፍላቱን ጩኸት
በሰማችና ባየች ጊዜ ተሸበረች፡፡ ተዘጋጅቶላት ከነበረው ክብር ልታፈገፍግ ሞከረች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናት ሆይ ከዚህ የብረት ጋን ግርማ የተነሳ አትፍሪ ድንጋጼም አይደርብሽ አናንያንና አዛርያን ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከእቶነ እሳት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ፡፡ እናት ሆይ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለመዳን ስትይ በማያልፈው ዘላለማዊ እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሽን ይኽስ አይሆንም ይቅርብሽ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናት ሆይ ሶስናን ከእደ ረበናት /መምህደራነ አይሁድ/ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ እርሱ እኛንም ከጋን ፍላት ያወጣናል፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን ልጆቹንና ሚስቱን በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባሳጣው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ እግዚአብሐር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ እግዚአብሔርም እንደወደደ አደረገ ከማለት በስተቀር ምንም የተናገረው ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም የሱን ዓላማ በመከተል ይኽንን መከራ ልንታገስ ይገባናል፡፡ ነገር ግን እናቱ በዚህ ምክር ልትጽናና ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዐይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ አምላክ ሆይ ይችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለህ ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን ይኽን እንዳታደርግ ግን ቸርነትህ ትከለክልኸለች፡፡ አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ አንድዱት ቅጠሉን ግን ጠብቁት ብለኽ ልታዝ መለኮታዊ ባሕሪህ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም በአንድ ጠብቁት ብለኽ ታዝዛለኽ እንጂ፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይኽንን ያየ ሁሉ ማዳን የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡ አቤቱ ዲያብሎስም ከባለስልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ ቅዱሳኖቹንም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማው በማለት እንዳይደነፋ
ለእናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ስጣት ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከእየሉጣ አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ በሰማያዊ መንግሥት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታኽ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ እነሆ በብረት ጋን ውስጥ የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም /በምንጭ/ ላይ እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቸዋለሁና አለችው፡፡ እኒኽም ቅዱሳን ይኽንን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን የሚቆለምም ልብንም የሚያቀልጥ ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርን የሚበጣጥስ መሳሪያ ካለበት የብረት ጋን ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፡፡ ከቅዱሳኑም አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱ ጋር ማቃጠሉና መፍላቱ ጸጥ አለ፡፡

ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ
በጭንቃቸው ጊዜ ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ይህ መልአክ ከሰማእታትና ከጻድቃን ጐን እንደማይለይ እወቁ ለኃጥአንም ኃጢአታቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላቸዋል፡፡ እኛም የዚህ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓሉን እያከበርን አማላጅና ወዳጅ እናድርገው፡፡ በዚህም በሚመጣውም ዓለም ሊረዳን ይችላልና፡፡


ዳግመኛም መስፍኑ ሐሳቡ ሳይሳካለት ስለቀረ 14 የሾሉና የጋሉ የብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ በኢየሉጣ አካል ሰባቱን በራሱ በቂርቆስ አካል ማለት ሁለቱን በጆሮዎቹ ሁለቱን በዐይኖቹ ሁለቱን በአፍንጫዎቹ አንዱን በልቡ ይቸነክራቸው ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡ ዳግመኛም የህፃኑን የእራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ ይጨምሩ ዘንድ አዘዘ፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህንን መከራ ከእርሱ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው በገመድ እንዲገትቱት አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ መልአኩ አዳነው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ሁሉ ተአምር ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑት ቅዱስ ገብርኤልንም አከበሩት፡፡


የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ፣ ቅዱስ ቂርቆስ እና የእናቱ የቅድስት እየሉጣ ተራዳኢነት ጸሎት አይለየን።


“ አልቦ እም ሰብእ ዘከማየ ዘይቴክዝ ነግሀ ወሠርከ
ወአልቦ እመላእክት ናዛዜ ሕዙናን ዘከማከ
ወበእንተዝ ኀሠሥኩ አእሚርየ ኪያከ
ኦ ገብርኤል ናዝዘኒ ወአስምዓኒ ቃልከ
ዕሴተ ጸሎትየ ዝንቱ ዘአቅረብኩ ለከ”

ሶርያዊው ሊቅ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በግእዝ “ማር ኤፍሬም ሶርያዊ” ሲባል፤ በሶርያ (ܡܪܝ ܐܦܪܝܡ ܣܘܪܝܝܐ (Mār Aprêm Sûryāyâ))፤ በግሪክ (Ἐφραίμ ὁ Σῦρος)፤ ሲባል ይህ አባት የነበረበት ዘመን ከ፫፻፮-፫፻፸፫ (306-373) ዓ.ም ነው፡፡ሀገሩ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች ሀገር ሲሆን አባቱ የጣዖት ካህን እንደነበር ስንክሳር ይነግረናል። ቅዱስ ኤፍሬም የንጽቢን ጳጳስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ የሔደው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሳስቶት ነበር። ከእርሱም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ የክርስትና ጥምቀትን በመጠመቅ በእርሱ ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ።


የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ያደረበት ይህ ቅዱስ አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር። ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ላይ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋር ወደ ቅዱሳን ጉባኤ ሔዷል። ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራዕይ የተነሳ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ “ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው” የሚል ቃልም ከሰማይ ወደርሱ መጣ።


ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወደደ። ወደ ቂሣርያ አገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማዕዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው። ሦስት ምልክቶችን እስኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እነዚህ ናቸው። ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምዕመናን ላይ ያድር ነበር።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ። በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመር። የየራሳቸውን ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስ ለመነው። በጸለየም ጊዜ ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራት በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎም ሁሉ ተጋደለ።


አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች እራሷንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበርና ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችው ኃጢአቷን ሁሉ ጽፋ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች። “አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢአቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱ እንዳልሽው ይሁንልሽ” አላት። እርሷ ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢአቷ በቀር ኃጢያቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበርና በአየችም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም “ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሂጂ እርሱ ይቺን የቀረች ኃጢአትሽ ያስተሠርይልሻል” ይላታል። ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሄዳ እርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። እርሱም እንዲህ አላት “ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሂጂ ግን ሞቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኚዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይቺን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመስስልሻል።”


ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሞቶ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው። ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑ ተደመሰሰላት።አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑ ዲዳን የሚባል አንድ ከሃዲ በተነሳ ጊዜም ከሃዲውን ተከራክሮ ረትቶታል።
እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሺህ ድርሳናትና ተግሣጻትን ደርሷል። ከእነርሱም ውስጥ አምላክ የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያው ውዳሴዋ አንዱ ነው። “አቤቱ የፀጋህን ማዕበል ግታልኝ” እስከሚል ደረስ ጸጋ ተትረፍርፎለት ነበር።

ቅዱስ ኤፍሬም በዓለም ባሉ ክርስቲያኖች የሚከበር ታላቅ ቅዱስ ሊቅ አባት ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት የሚያውቅና እጅግ በጣም አስደናቂ የሆኑ የሃይማኖት መጻሕፍትን የጻፈ ሊቅ ሲሆን ካለው ጥልቅ ዕውቀት የተነሣ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ በሶርያ (ܟܢܪܐ ܕܪܘܚܐ, Kenārâ d-Rûḥâ)፤ የኤዴሳ ዲያቆን (Deacon of Edessa)፤ የሶርያዎች ፀሐይ (the Sun of the Syrians)፤ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ (a Pillar of the Church) ተብሏል።

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ከጻፋቸው በርካቶች የሃይማኖት መጻሕፍት ውስጥ አራት መቶው እስካሁን ድረስ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሓፊው ሶዘመን ባደረገው ጥናት ቅዱስ ኤፍሬም የጻፋቸው በመስመር ቢቈጠሩ ሦስት ሚሊየን እንደሚመሉ አረጋግጧል፡፡
የጻፋቸው መጻሕፍት ለአራት ክፍል የሚከፈሉ ሲሆኑ እኩሌቶቹ በስድ ንባብ እኩሌቶቹ በግጥም መልክ ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ይኸውም መጻሕፍቱ በዝርዝር ሲታዩ፡-
ሀ) በመዝሙራት መልክ የተዘጋጁ
☞ስለ እምነት (ባለ ፹፯ (87) ክፍል መዝሙራት)፤
☞መናፍቃንን በመቃወም (ባለ ፶፮ (56) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ገነት (፲፭ (15) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ጁሊያንን በመቃወም (፭ ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ክርስቶስ ልደት (፶፱ (59) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ቤተ ክርስቲያን (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ንጽቢን (፸፯ (77) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ድንግልና (፶፪ (52) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ጾም (፷፯ (67) ክፍል መዝሙራት)፤
☞ስለ ኅብስት፤ ስለ ጥምቀት፤ ስለ ስቅለት፤
☞ስለ ትንሣኤ (፴፭ (35) ክፍል ያላቸው መዝሙራት) ወዘተርፈ ጽፏል፡፡

ለ) በድርሳናት መልክ የተዘጋጁ
☞ስድስት የሃይማኖት ድርሳናት፤
☞በ፫፻፶፰ (358) ዓ.ም በመሬት ንውጽውጽውታ ስለ ኒኮሜድያ ጥፋት ድርሳን፤
☞ስለ ሰሙነ ሕማማት፤ ሌሎች በርካቶች ድርሳናት ወዘተርፈ. ጽፏል፡፡

ሐ) ጥበባዊ፤ ግጥማዊም፤ ስድ ንባባዊም ይዘት ከሆኑት፡-
☞ስለ ጌታችን ንግግር፤ ☞ስለ ዕለተ ምጽአት የሚናገር ወዘተርፈ
መ) ሙሉ በሙሉ ስድ ንባብ የሆኑ
☞የኦሪት ዘፍጥረትና ዘጸአት ትርጓሜ፤
☞የአራቱ ወንጌላት ትርጓሜ፤
☞የግብረ ሐዋርያት ትርጓሜ፤
☞የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜ፤
☞ለባርዳይሰን፤ ለማኒ፤ ለመርቅያን ክሕደቶች መልስ ወዘተርፈ ጽፏል፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ዕረፍቱም በ373 ዓ.ም ሐምሌ15 ሲሆን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህነን ሊቅ ሲያወድሰው፡-
“ሰላም ለኤፍሬም ደራሲ ዘጽሩይ ልሳኑ፤
አብያተ ክርስቲያናት ይሠረጉ በድርሳኑ”፡፡
(በድርሳኑ አብያተ ክርስቲያናት የሚሸለሙ (የሚያጌጡ) አንደበቱ የጠራ ለደራሲው ለኤፍሬም ሰላምታ ይገባል) ብሎታል፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም እነዚህን ድርሰቶቹን በሶርያ ቋንቋ የጻፋቸው ሲሆኑ ወደ በርካቶች ቋንቋዎች የተወሰኑ ሥራዎቹ ሲተረጐሙ ከነዚህ ውስጥ በአርማንያ፤ በኮፕቲክ፤ በግእዝ፤ በሕንድ፤ በአረብኛ፤ በጆርጂያ፤ በግሪክና በሌሎች ተተርጒመዋል፡፡

በእጅጉ የሚገርመው በእኛ ቋንቋ በግእዝ ከተተረጎሙት ውዳሴ ማርያምን ጨምሮ በጥንታዊ ብራና መጻሕፍታችን ውስጥ ዐሥራ ሰባት የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍት ሲገኙ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ በሃይማኖተ አበው ላይና በግብረ ሕማማት ላይ ብቻ ለሕትመት ሲበቁ ሌሎቹ ግን በዘረፋ ብራናዎቹ ከሀገር በመውጣታቸው ምክንያት ሊገኙልን አልቻሉም፡፡

በግእዝ ተተርጉመው የነበሩ የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍትን ዝርዝር “Mariological themes in the writings of St. Ephrem the Syrian” በሚል ርእስ በጻፍሁት የመመረቂያ ጽሑፌ ላይ ከገጽ ፯-፰ ድረስ ስላሰፈርሁት በዚያ ላይ ተመልከቱ (Rodas Tadese, Mariological Themes in the writings of St. Ephrem the Syrian, Un published essay pp 7-8)፡፡

ይህ ታላቅ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን በእጅጉ ይወዳት የነበረ ሊቅ ሲሆን፤ ርሷንም ከመውደዱ የተነሣ ከሉቃስ ወንጌል ወበሳድስን ጸሎተ ማርያምን አውጥቶ በዕድሜዋ ልክ 64 ጊዜያት ድረስ እየጸለየ የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው እንደ ልብስ ለብሼው ተጎናጽፌው እያለ ይመኝ ነበር ።

የአምላክ እናትም ለርሷ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አይታ ከልጇ አማልዳው “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ) እስኪል ድረስ እጅግ በርካቶች መጻሕፍትን እንዲጽፍ ሆኗል፡፡ ለዚህ ፍጹም አባትም ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰባት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ክብር ሆና እየተገለጸችለት ውዳሴዋን ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፤ በዚህም የአምላክ እናት “የቅዱስ ኤፍሬም እመቤት” ተብላ ትወደሳለች፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በመዋሥዕት መጽሐፉ ላይ ስለ ቅዱስ ኤፍሬም ክብር ሲመሰክር፦“ሖረት ማርያም ኀበ ኤፍሬም ወትቤሎ ትወድሰኒ ሊተ ኀቤከ መጻእኩ ወይቤላ ኤፍሬም ለማርያም አንሰ ኢይክል ወድሶተኪ እስመ ላዕላዕ ወልቱት አነ፤ ካዕበ ትቤሎ ማርያም እሞሙ ለሰማዕት ወድሰኒ ሊተ በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ፤ ቆመ ኤፍሬም ወጸለየ ኀበ እግዚአብሔር ወይቤ ፈኑ ሊተ መንፈስ ቅዱስ ውዳሴ ማርያም ዘእነብብ” (እመቤታችን ማርያም ወደ ኤፍሬም ሄደች፤ እንዲህ አለችው ታመሰግነኝ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ፤ ኤፍሬም እመቤታችን ማርያምን አንቺን ማመስገን አልችልም አላት፤ እኔ ፍጹም አንደበተ ኮልታፋ ምላሰ ጎልዳፋ ነኝና፤ ዳግመኛ የሰማዕታት እናታቸው ማርያም ተናገረችው፤ መንፈስ ቅዱስ ባስገዘበህ መጠን አመስግነኝ፤ ኤፍሬም ቆመና ወደ እግዚአብሔር አመልክቶ የማርያምን ምስጋና በምናገር ገንዘብ መንፈስ ቅዱስን ላክልኝ አለ) በማለት ገልጿል፡፡

ይህ ሊቅም በተቀበለው ሰፊ በረከት እጅግ ጥልቅና ብዙ የነገረ ማርያም አስተምህሮ ይኸውም የንጽሕናዋን፣ የቅድስናዋን፣ የዘላለማዊ ድንግልናዋን፣ የአምላክ እናትነቷን፣ የክብሯን ነገር አምልቶ አስፍቶ የጻፈላት ቅዱስ አባት ነው፡፡
መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር በሐምሌ 15 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በብፁዕ ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 15 ስንክሳርና መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ያጋጀው ጽሑፍ

አባ ባውማ ስለ አቡነ ኪሮስ

በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ ባየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ የወጣ፡ ጌታቸንም መርቶ ወደ ምዕራባዊቷ በረሀ ያደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ለብቻውን የኖረ ሰውም ሆነ የዱር አራዊት ቢሆኑ ያላዩት ይህ ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር። ቅዱስ አባታችን ኪሮስ። በሐምሌ 8 በዓለ ዕረፍቱን ስለምናከብረው አባታችን በአስቄጥስ ገዳም የነበረው ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ እንዲህ አለ ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለሁ “አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ”። ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” ብዬ ጠየቅሁት “አዎን” አለኝ። ሁለተኛም “ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት” “ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው” አለኝ።
ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና “በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?” አልሁት “አዎን አለ” አለኝ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ “ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ” እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ “አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው” ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ። “እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ” አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር።ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ “እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ” ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ “እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው” አልሁት።


እርሱም “ልጄ ሆይ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም” አለኝ። “በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም “ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል አለኝ። በሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ “በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው” አለ።


ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ። አባ ኪሮስም መድኃኒታችንን “ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው ባርከው” አለው መድኃኒታችንም “የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ” አለኝ።


ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው “እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ሥጋዬንና ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም። አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ” መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። “ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር የሠራት ናት” እያለ አመሰገነባት።


መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን “እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር” አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን “በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው” አለው። ቅዱስ አባ “ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ” አለ። ያን ጊዜ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ “የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” አለ ዳግመኛም “ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም” አለ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤልም ሰጣት።


እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ መስቀሉን አኑሮ ዘጋት። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከመድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች።


እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስሁ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው። መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ኪሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።