እንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን

የእንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን አተካከል ጥንተ ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ቤተ መንግስታቸው ወደ ፍልውሃ እና ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ የመንበረ ንግሥት ቊስቋም ቤተክርስቲያን በታነፀችበት ስፍራ ድንኳናቸውን ተክለው ዕረፍት ያደረጉበት ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን ዕረፍት አድርገው ሳለ እንቅልፍ ያሸልባቸውና በህልማቸው አንዲት እጅግ የተዋበች ሴት ልጅ አዝላ በእቴጌ ጣይቱ አምሳል “ይህንን ቦታ ልቀቁልኝ ቤቴን ልስራበት ” ስትላቸው ያያሉ። ንጉሡም ከእንቅልፋቸው ደንግጠው በመነሳት የሆነውን ሁሉ ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ብጡል ይነግሯቸዋል። በመቀጠልም በእቴጌ ጣይቱ አምሳል ስለታየቻቸው “በስምሽ ሆስፒታል ትሰሪበት ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ” ብለው ቦታውን ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ይሰጧቸዋል።

ከጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ስለታመሙ እቴጌ ጣይቱ ባለቤታቸውን ማስታመም ይጀምራሉ፡፡ የእንጀራ ልጃቸውም ወ/ሮ ዘውዲቱ አብረዋቸው ያስታመሙ ስለነበር እቴጌ ንጉሡ ያዩትን ራዕይ እና ሀኪም ቤት መስራት አለመቻላቸውን ጭምር በትካዜ ይነግሯቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በኃላ ንጉሡም በሞት ጎዳና ይሸኛሉ። እቴጌም እንጦጦ ተቀምጠው ያለፈውን አዱኛ እያስታወሱና አዲስ አበባን እየተመለከቱ “ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ወይ” አሉ ይባላል። ብዙ ዓመትም ሳይቆዩ እሳቸውም ባላቸውን ተከትለው አረፉ። ልጅ ኢያሱ መሪነቱን ይዘው በነበሩበት ጊዜ፤ ራስ ተፈሪ አልጋወራሽ ሲሆኑ፤ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ነገሡ።

ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው በትረ መንግሥትነቱን ከተረከቡ በኃላ፤ እቴጌ ጣይቱ የነገሯቸውን አስታውሰው፤ ሃሳባቸውን ለመፈጸም በመነሳት፤ ዛሬ መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ከተተከለችበት ቦታ ላይ ሆስፒታል ይገነቡ ዘንድ ዝግጅቱ ይጠናቀቅና የመሰረት ቁፋሮ ይጀመራል። በቁፋሮ ወቅት አስደናቂ ነገር ይከሰታል፤ ይኸውም “ታቦት ቊስቋም ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የንግሥት ዕሌኒ የመዳብ ወንበር እና የብረት መስቀል ይገኛል። ንግሥት እሌኒ ማለት የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ እኅት ሲሆኑ በ፲፬ኛው (14ኛው) መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ንግሥናቸውም በ፲፱፻፳፮ እንደነበር የኢትዮጵያ የታሪክ መጻሕፍት ያስረዳል። ፬፻፺፪ (492) ዓመት እድሜ ያለው ንብረት በመሬት ተቀብሮ በጥበበ እግዚአብሔር ተጠብቆ ምንም ሳይበላሽ ይኖር ነበር ማለት ነው ። በዚህም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተደንቀው ንዋየ ቅድሳቱን ፣መስቀል እና ሌሎችም የተገኙትን በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም እንዲቀመጥ ያደርጋሉ።

በቁፋሮ ጊዜ በተገኘ ንዋየ ቅድሳት ምክንያት ሥራው ወደተቋረጠው የሆስፒታል ቦታ በመሄድ ቤተክርስቲያን ይሰራ ዘንድ ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ.ም (ህዳር 6 ቀን 1918 ዓ.ም) የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ። መቃኞውም አስቸኳይ ይሰራ ዘንድ ለራስ ደስታ ዳምጠው ትእዛዝ ተሰጠ። በበጎ ስራቸው እና ካህናትን በመውደዳቸው ምክንያት ዘመነ ካህናት ተብሎ በሚጠራበት ጊዜ፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒሊክ ዘመነ ንግሥና፤ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ፍጻሜ ዘመን፤ በሰሜን አዲስ አበባ ልዩ ስሙ እንጦጦ በተባለ ስፍራ፤ በራስጌ ርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ጸሐይ ቅድስት ማርያምና ደብረ ኀይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ፤ በግርጌ ሀመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት እና ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተክርስቲያንን አዋሳኝ አድርጋ፤ በመኀል ባለ ልዩ ጉብታ (መሶብ) በምትመስል፤ በግማሽ አዲስ አበባን ሊያሳይ በሚችል ቦታ ላይ፤ መቅደስና ቅኔ ማኅሌት ያለው መቃኞ ቤተክርስቲያን ሰርተው በትዕዛዙ መሰረት አሰርተው ታቦተ ቊስቋም ማርያምንና ታቦተ ኢየሱስ ሌሎችንም ንዋየ ቅድሳት በእጨጌ ተድላና በዐቃቤ ሰዓት መምሬ አበበ ትዕዛዝ፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና ታላላቅ ሹማምንት ምዕመናን በተገኙበት፤ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ባራኪነት፤ ታቦቷ ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፱ ዓ.ም (ህዳር 6 ቀን 1919 ዓ.ም) ገባች። ንግሥቲቱም ፲፭ (15) ጋሻ መሬት ከአርሲ አገር ለአገልጋዮች ካህናት መተዳደሪያ ሰጥተዋል።

ስያሜዋንም መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ብለዋታል። መኳንንቱም የተለያየ ስጦታ አበርክተውላታል። በዚህ ወቅት ታቦቷን ይዘው የመጡ በመቃኞዋ ጊዜ አስተዳዳሪ የነበሩት መምሬ ብስራት ሃብተማርያም ናቸው። መምሬ ብስራት ሃብተማርያም እኚህ ታላቅ አባት የመንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን ከመመረቋ አስቀድሞ፤ በስዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ያገለግሉ ነበር። ንግሥተ ንግሥታት ዘውዲቱም የቊስቋም ማርያም ቤተክርስቲያንን በ፲፱፻፲፱ ዓ.ም አሰርተው በመጠናቀቅ ላይ ስለነበር ታቦቷ ወደ መቃኞ ቤተ ክርስቲያን የምትገባበት ዕለት ህዳር ፮ ቀን ፲፱፻፲፱ ዓ.ም እንዲሆን በመወሰኑ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ በእጨጌ ተድላ እና በአቃቤ ሰዓት አበበ አማካኝነት አገልጋይ ካህናት ሲመርጡ መምሬ ብስራት ሃብተማርያም አስተዳዳሪነቱን ግብዝናውን ተሹመው ታቦተ ቊስቋም ከበዓታ ለማርያም ገዳም ይዘው እንዲሄዱ ታዘዙ። ፲፱፻፲፱ ዓ.ም ኅዳር ፮ ቀን ጀምሮ አዲሱ ቤተክርስቲያን በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ተሰርቶ እስከ ተመረቀበት ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ.ም ለሰባት ዓመታት ያኽል ግብዝናን ከእልቅና በመያዝ ቤተክርስቲያኒቱን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። በኋላም የደብሩን አስተዳዳሪነት ለአለቃ መርሻ ያስረከቡ ሲሆን የውስጥ ግብዝናን ይዘው ቆይተው በህመም ምክንያት ለመምሬ ዘውዴ ሰረጸ ድንግል አስረክበው ታህሣሥ ፴ ቀን ፲፱፶፭ ዓ.ም በ፹፬ ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ ስትመሠረት የነበሩት የመጀመሪያዎቹ አገልጋዮች አባ ወልደ ሰማያት፣ መምሬ መንግሥቱ፣ ዲያቆን ጥሩወርቅ ያብዛ፣ ዲያቆን ደግፌ፣ ዲያቆን ተስፋ፣ ደብተራ ሙሉነህ አየለ፣ ደብተራ ግዛው ተክለጊዮርጊስ፣ ደብተራ በላይነህ፣ አለቃ አልታዬ ወልደዮሐንስ፣ አለቃ ኃይለጊዮርጊስ ጀማነህ፣ መሪጌታ ተክለ ሃይማኖት በላይነህ፣ እና መምሬ አስፋው ወልደ ኢየሱስ ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የተተከለችው መንበረ ንግሥት ቊስቋም ማርያም ስብሐተ እግዚአብሔር በሰፊው እየተከናወነ እና መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ በመቀጠሉና በታቦቷ ሰሚነት ብዙ ሰዎች ከከተማ እየመጡ ይፈወሱባታል። በ፲፱፻፳ ዓ.ም ግንባታው የተፈጸመው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤትም ከቊስቋም ማርያም ጋር ተቀራራቢ ስለነበር የበዓታው መምህር ሊቀ ሊቃውንት የሚል ማዕረግ ሲሰጠው የቊስቋም ካህናትና ንዋየ ቅድሳት ባለ አደራም ስለነበር የቊስቋም ካህናት ጉዳይ በእርሱ ባልደረባነት ለመንግስት እንዲያቀርብ ንግሥቲቱ ፈቅደዋል። ከቤተክርስቲያን ወረድ ብሎ ባለው መሬት ላይም የቊስቋም መንፈሳዊ ት/ቤት በሚል መሰረት ጥለው መስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፳ ዓ.ም ተመርቋል።

ይህ መቃኞ ቤተ መቅደስ ወደ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንደ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና የካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ይሰራ ዘንድ ንግሥቲቱ ትዕዛዝ ሰጥተው ሳለ ባደረባቸው ህመም ምክኒያት ሳይሰራ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም አርፈዋል። ስለ ውለታቸው ቤተክርስቲያንም ዘወትር በጸሎት ታስባቸዋለች ስራቸውንም ለትውልድ ስትዘክር ትኖራለች። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፤ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ተብለው መንግሥቱን ሲረከቡ፤ በራስ ደስታ ዳምጠው አማካይነት አሁን ያለውን ቤተክርስቲያን በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃ/ሥላሴ ዘመን ተሰርቶ ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ.ም የበዓተ ግብጽ ዕለት ታቦተ ሕጉ ከመቃኞ ወደ ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት በመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል። ብጹዕነታቸውም የተለያዩ አልባሳትን አበርክተዋል ።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ

ወንጌላዊው ቅዱስ_ሉቃስ፦ ይህም ቅዱስ የከበረ ወንጌል ከመዘገባቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው። እርሱም ወንጌልን ስለማስተማር በሥራው ሀሉ ሐዋርያት ጴጥሮስንና ጳውሎስን የሚያገለግላቸው ሆነ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈ ሉቃስ ነው።

ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስም ከተገደሉ በኋላ በሮሜ ሀገር የሚያስተምር ሆነ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር። ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት አንድ ግምባር ፈጠሩ። በንጉሥ ኔሮን ፊት ቁመው ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ጮኹ “ይህ ሉቃስ ብዙዎች ሰዎችን በሥራው ወደ ትምህርቱ አስገባቸው”። ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ አደባባይ ሉቃስን እንዲይቀርቡት አዘዘ።

ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስም ከዚህ ዓለም መውጫው እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ። በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘ። መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎቹን ሰጠው “ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሃልና” እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው አለው።

በንጉሥ ኔሮንም ፊት ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ “በሥራህ ሕዝቡን የምታስት እስከመቼ ነው” አለው ቅዱስ ሉቃስም ” እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም” ብሎ መለሰለት።

ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው “እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይቺን እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ” ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡ አዘዘ በቆረጡትም ጊዜ “ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ እወቅ ነገር ግን የጌታዬንና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ”። ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት። ከዚህም በኋላ ለያት በዚያም የነበሩ አደነቁ የሠራዊት አለቃውና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ቁጥራቸውም አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሉቃስን ሥጋ በማቅ አይበት አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ። ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት በአማረ ቦታም አኖሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የጥቅምት 22 ስንክሳር

የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ይኩን ሰላም በኃይልከ። ወትፍሥሕት ውስተ ማኅደረ ክበዲከ። በእንተ አኀውየ ወቢጽየ። መዝ 121፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-።

የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ”። መዝ 18፥3-4።

የሚነበቡት መልዕክታት የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቈላ 4፥12-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 1፥4-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥1-6። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰውም የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው።

መልካም የወንጌላዊው የቅዱስ ሉቃስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

ትሑትና ትዕግስተኛው አባት፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር


አባ ዮሐንስ ሐፂር፦ የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ከላይኛው ግብጽ ናቸው እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው ግን ከእርሱ በቀር ልጅ የላቸውም የዚህ ዓለምም ብልጽግና ቢሆን የላቸውም ነገር ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው። ይህንንም ቅዱስ እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት።


የዚህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥታው የመላእክት የሆነ አስኬማን ይለብስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ይኸውም የምንኵስና ልብስ ነው። ከዚያም በደረሰ ጊዜ አባ ባይሞይ የሚባለውን አንዱን አረጋዊ አባት ተገናኘው ዮሐንስም ሰገደለትና ወደ እርሱ እንዲቀበለው ለመነው ሽማግሌውም አባት “ልጄ ሆይ ያንተ በዚህ መኖር ልክ አይደለም በዚች ገዳም የሚኖሩ በእጆቻቸው ይሠራሉ በቀንና በሌሊት ይጾማሉ ይጸልያሉ በሚተኙም ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ ይተኛሉ አንተ ወጣት ጎልማሳ ስለሆንክ ይህን ሁሉ ችግር አትችልም። ነገር ግን ወደ ዓለም ተመልሰህ እንደ ሰው ሁሉ በጎ አኗኗርን ትኖር ዘንድ ይሻልሃል የዚች ገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና” አለው።
አባ ዮሐንስም እንዲህ አለው እኔ በጥላህ ሥር ልኖር መጥቼአለሁና ስለ እግዚአብሔር ብለህ ተቀበለኝ እንጂ አትመልሰኝ ይህም አባ ባይሞይ እግዚአብሔርን ሳይጠይቅ ምንም ሥራ አይሠራምና በዚያን ጊዜ ሥራውን ይገልጥለት ዘንድ ስለ ዮሐንስ ሐፂር እግዚአብሔርን ለመነው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት “እርሱ የተመረጠ መሳሪያ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል” አለው።


ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ሐፂርን ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባው የምንኵስና ልብሶችንም አምጥቶ በላያቸው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጸለየ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ በመስቀል ምልክት በልብሶቹ ላይ አማተበ ሽማግሌውም እነዚያን ልብሶች ለአባ ዮሐንስ አለበሰው።


ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ተጋድሎንና አገልግሎትን ጀመረ አባ ባይሞይም ሊፈትነው ወደደ በአንዲትም ቀን ደብድቦ “ከአንተ ጋር መኖር አልሻም” ብሎ ከበዓቱ አስወጥቶ አባረረው የከበረ አባ ዮሐንስም ከሜዳ መካከል በውጭ ቆመ በየቀኑም በጥዋት እየወጣ “ከእዚህ ላይህ አልሻም” እያለ ይመታዋል እርሱ ግን “አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ” ብሎ ከእግሩ በታች ይሰግዳል። በሰባተኛዪቱም ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሔድ ሽማግሌው አባ ባይሞይ ወጣ አባ ዮሐንስንም ሰባት መላእክት ከበው አክሊላትን ሲያቀዳጁት አያቸው ከዚያንም ጊዜ ወዲህ መፈተኑን ተወው ወደ መኖሪያውም አስገባው።


ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ ዕንጨት አግኝቶ ወስዶ ለአባ ዮሐንስ ሰጠውና “ይህን ዕንጨት ትከለው እስከሚበቅልና እስከሚያፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው” አለው። አባ ዮሐንስም ለአባቱ ታዛዥ በመሆን ተቀብሎ ወስዶ ተከለው በየቀኑም ሁለት ሁለት ጊዜ ያጠጣዋል ውኃውም ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል የራቀ ነው። ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ ታላቅም ዛፍ ሁኖ አብቦ ጣፋጭ ፍሬን አፈራ። አባ ባይሞይም ከፍሬው ለቅዱሳን አረጋውያን ወሰደላቸውና “የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ” አላቸው እነርሱም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው አደነቁ ለመምህሮቻቸው ለሚታዘዙ እንዲህ ያለ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።


አባ ባይሞይም ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል በጽኑዕ ደዌ ውስጥ ተይዞ ኖረ አባ ዮሐንስም ያገለግለው ነበር አባ ዮሐንስን እንደፈተነው የተመረጠ መሥዋዕትን ይሆን ዘንድ በዚህ ደዌ እንዲፈተን እግዚአብሔር ፈቅዷልና። በሚሞትበትም ጊዜ አባ ባይሞይ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትን ሰበሰባቸውና አባ ዮሐንስንም እጁን ይዞ “እርሱ ሰው ያይደለ መልአክ ነውና ተቀብላችሁ ጠብቁት” ብሎ ሰጣቸው። እርሱንም ደግሞ እንዲህ አለው “ከዕረፍቴ በኋላ ያን ዕንጨት ወደ ተከልክበት ቦታ ሂድና በዚያ ኑር እግዚአብሔር ላንተ ያዘጋጀልህ ነውና ብዙዎችም በአንተ እጅ ይድናሉ መታሰቢያህም በዚያ ጸንቶ ይኖራል ዜናህም በዓለም ሁሉ ይወጣል” ይህንንም ተናግሮ ዐረፈ አክብረውም ቀበሩት።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባ ዮሐንስ አረጋዊ አባቱ አባ ባይሞይ እንደነገረው ወደዚያ ቦታ ሔዶ ኖረ ዜናውም በዓለም ሁሉ እጅግ እስከ ተሰማ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። በራሱ ቤተ ክርስቲያንም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ በሹመቱም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ እጆቹን በራሱ ላይ ሲጭን “አክዮስ አክዮስ አክዮስ” የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ ይህም “ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል” ማለት ነው። የቊርባን ቅዳሴን በሚቀድስ ጊዜ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል የማይገባቸውን ይለያቸዋል “ዛሬስ ሔዳችሁ ንስሓ ግቡ ከዚያም በኋላ ተመልሳችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ” ይላቸዋል።


ይህን አባ ዮሐንስንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲያመጣለት ወደ ባቢሎን ልኮታል ይህም በግንቦት ወር በዐሥረኛው ቀን ተጽፎአል።


በአንዲትም ዕለት አንድ መነኰስ ሊጎበኘው ወደ በዓቱ ቢመጣ አባ ዮሐንስን ተኝቶ አገኘው የእግዚአብሔርም መላእክት በላዩ ይጋፉ ክንፎቻቸውንም ያርገበግቡ ነበር አንዱም ሌላውን “ተወኝ ክንፌን በላዩ ላኑር ይለዋል” ይህንንም አይቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ።
ከዚህም በኋላ የመነኰሳቱን መንደር ሊበረብሩ የበርበር አረማውያን ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ አባ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሔደ በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም በጎኑ ባለ ቦታ ተቀመጠ እስከ ሚያርፍባትም ቀን ድረስ የሚያገለግለው አንድ የታመነ ሰውን እግዚአብሔር አመጣለት።


ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊያሳርፈው በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱሳን ጻድቃኖቹን አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኵሚስን ከእርሳቸውም ጋር መንፈሳዊ አባቱ አባ ባይሞይን ያረጋጉትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መለየቱን ይነግሩት ዘንድ ወደርሱ ላካቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው አረጋጉት “ደስ ይበልህ እግዚአብሔር የማያልቅ ተድላ ደስታን አዘጋጅቶልሃልና” ክብር ይግባውና ጌታችንም እንዳዘዘ “በእሑድ ቀን ሁለተኛ ወዳንተ መጥተን ወደ ዘላለም ሕይወት እንወስድሀለን” አሉት። ባርከውትም ከእርሱ ዘንድ ተመለሱ።


በዐርብ ቀንም አገልጋዩን ወደ አንድ ቦታ ላከው ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ በእሑድም ቀን ሌሊት ዶሮ ሲጮህ እነዚያ ቅዱሳን ከሁሉም ቅዱሳን ማኅበር ጋር መጡ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ ወደርሱ መጡ ባያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ መላእክትም እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳረጓት በዚያንም ጊዜ ረድኡ መጣ ነፍሱንም ከበው እያመሰገኑ ሲያሳርጓት የጻድቃንና የመላእክትን ማኅበር አይቶ እያደነቀ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ። ከመላእክትም አንዱ ወደርሱ መጥቶ የቅዱሳንን ስማቸውን በመጥራት በጣቱ እያመለከተ ይህ አባ ዕገሌ ነው ብሎ አስረዳው ረድኡም መልአኩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው “ይህ በፊታቸው ያለ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚበራ ማን?” ነው መልአኩም “የመነኰሳቱ ሁሉ አባት አባ እንጦንስ ነው” ብሎ መለሰለት።


ወደ በዓቱም ያ ረድእ በገባ ጊዜ በምድር ላይ ሰግዶ እንዳረፈ አባ ዮሐንስን አገኘውና ታላቅ ልቅሶን በላዩ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወደ መነኰሳቱ መንደር ፈጥኖ በመሔድ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐፂር እንደ ዐረፈ ነገራቸው። እነዚያም መነኰሳት አክብረው ገንዘው ሥጋውን ተሸክመው ወስደው በቦታቸው አኖሩት። የደረቀ ዕንጨት ተክሎ በአበቀለበት ላይ በሠራት የራሱ በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልጆቹ ከዚህ አፍልሰው ወስደው እስከ አኖሩት ድረስ በዚያ ኖረ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


“ሰላም ለዮሐንስ ሐጺር ትሩፈ ምግባር፤ ዘአጥረየ ትሕትና ወወረሰ ልዕልና”። ትርጉም፦ ትሕትናን ገንዘብ አድርጎ ልዕልናን የወረሰ መልካም ሥራው የበዛ ለኾነ ለዮሐንስ ሐጺር ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ

እስጢፋኖስ ማለት “መደብ” ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ “አክሊል” ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከነቢያትና ከጻድቃን ወገን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ወንድ ልጆችን ወለዱ፡፡ አንዱ ይሁዳ ሲባል ሁለተኛውም ቅዱስ እስጢፋኖስ (አስተፓኖስ) ነው፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወለደው ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለች ቦታ ነው፡፡ የተወለደውም በስዕለት ነው፡፡ እርሱም ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመሄድ ይላላካቸውና ያገለግላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙት ከ7ቱ ዲያቆናት አንዱ ሲሆን የዲያቆናት አለቃ እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማስተማሩና ብዙዎችን ክርስቶስን ወደማመን ስለመለሳቸው ክፉዎች አይሁድ በጠላትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ከጌታችን ቀጥሎ ከምእመናን ወገን የመከራውን ገፈት ስለተቀበለ (በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ስላረፈ) “ቀዳሜ ሰማዕት” ተሰኘ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ” እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ የተሰጠው ስያሜ ነው።


የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የአማኞች ቊጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሄደ ጊዜ የማኅበራዊው ኑሮ አስተዳደር ማለትም የምግብንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች (ገንዘብም ጭምሮ) በትክክልና በእኩልነት የማከፋፈሉ ሥራ በሐዋርያት ዘንድ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ እነርሱም ደግሞ ዋና ተግባር አድርገው በትጋት ለመያዝ የፈለጉት ማስተማርን ነበር፡፡ ስለዚህም አማኞችን ሁሉ ሰብስበው ከመካከላቸው በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን እንዲመርጡ አሳስቧቸው፡፡ አማኞችንም ነገሩ አስደስቷቸው ሰባት ሰዎችን መረጡ፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ (ዕረፍቱ ጥር 1)፣ ቅዱስ ጵሮኮሮስ (ሰኔ 8)፣ ቅዱስ ጢሞና (ሚያዝያ 16)፣ ቅዱስ ፊልጶስ (ጥቅምት 14)፣ ቅዱስ ጰርሜና (መስከረም 1)፣ ቅዱስ ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሣ)፣ ቅዱስ ኒቆላዎስ (ሚያዝያ 15) ናቸው፡፡ ሐዋ 6፡5፡፡


እነዚህንም ቅዱሳን በከበሩ ሐዋርያት ፊት ባቆሟቸው ጊዜ ጸልየው እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው ከባድ ሸክም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ደሀ አደጎች በመርዳት ችግሮቻቸውን አቃለሉላቸው፡፡በከበሩ ሐዋርያት ከተመረጡት ሰባቱ ዲያቆናት መካከል ሊቀ ዲያቆናት ተደረጎ የተመረጠው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ሌሎቹም ዲያቆናት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወንጌልን በማስተማርና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በማስተዳደር በጽናት ተጋድለዋል፡፡ እነዚህም ሰባቱ ዲያቆናት ከአባቶቻቸው ከከበሩ ሐዋርያት አይተው የእነርሱንም መንፈስ ተቀብለው ያልተማሩ አህዛብን ልቡናቸውን ለመስበርና የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡

ከእነርሱም ውስጥ በዋነኛነት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ “ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ ነገሩ ሐሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ” በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡

ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በትምህርቱና በተአምራቱ ብዙዎችን ወደቀናች ሃይማኖት ስለመለሰ ክፉዎች አይሁድ ቀኑበትና የሐሰት ምስክር አዘጋጁበት፡፡ “በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው በሐሰት ከሰሱትና በሸንጎአቸው አቆሙት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ያለውን ሁሉንም እየጠቀሰ የሃይማኖትን ነገር አስተማራቸው፡፡ ነቢያትን ስለማሳደዳቸውና ስለመግደላቸው እየወቀሰ ሲናገራቸው በትምህርቱ ተናደው ጆሮአቸውን ይዘው በመጮህ በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ዘንድ እየጎተቱ ከከተማው ውጭ አወጡት፡፡


ቅዱሱም በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ከጌታችን የተማረውን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እያለ ስለ ገዳዮቹ ምሕረትን ይለምን ነበር፡፡ ሰማይም ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ክብር ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይኸውም የቀድሞው ሳውል ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅና ድንጋይ ያቀብል ነበር፡፡ “የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ” ብሎ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ሐዋ 22፥20፡፡


የቅዱስ እስጢፋኖስ መምህር የነበረው ምሑረ ኦሪቱ ገማልያልና ልጁ አቢብ በእስጢፋኖስ ትምህርትና የሞቱ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት አይተው ከይሁዲነት ተመልሰው በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ የነፃ አውጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡ በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት”፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥8-15፡፡

የአይሁድ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ያቀረቡት የክሳቸው ምክንያት ጌታችንን ከከሰሱት ክስ ጋር በሁለት ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው “የሙሴን ሕግ ሽሯል” የሚል ነው፡፡ “የሙሴን ሕግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም አታድንም፤ ሐዲስ ኪዳን (ወንጌል) ግን ትመግባለች ታድናለች” ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥13፡፡ ሁለተኛው ክሳቸው “እግዚአብሔርንም ይሰድባል” የሚል ነው፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥50፡፡ አይሁድም የቅዱስ እስጢፋኖስን የወንጌል ቃል ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡ የኦሪት የካህናት አለቃውም ቅዱስ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ ዘንድ ሲጠይቀው እርሱ ግን ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በዝርዝር በሚገባ ተረከላቸው።
ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲህ አላቸው፡- “ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፏጩበት፡፡መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፡፡ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እስጢፋኖስም “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ይህንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥52-60፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለንጽሕናው ስለድንግልናው፣ ስለሰማዕትነቱ ስለተጋድሎው እና ስለስብከቱ ስለተአምራቱ ሦስቱ አክሊላት ተቀዳጅቷል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ አምላኩን ክርስቶስን በብዙ ነገር መስሏል፡፡ በመጨረሻዋ የመሞቻው ሰዓት ላይ እንኳን ሆኖ አምላኩን አብነት አድርጎ ተገኝቷል፡፡ ጌታችን “ነፍሴን ተቀበላት” እንዳለ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም “አቤቱ ጌታ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት” ብሏል፡፡ ጌታችን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ እስጢፋኖስም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና” በማለት ለገዳዩቹ ምሕረትን ለምኗል፡፡ በጌታችን ጸሎት እነ ፊያታዊ ዘየማንን ጨምሮ እልፍ ነፍሳት ወደ ንስሐ ተመልሰው ገነት መንግስተ ሰማያትን እንደወረሱ ሁሉ በቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት ብዙ ነፍሳት ድነው ገነት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡
የጌታችን ቅዱስ መስቀል እልፍ ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ እንደነበር ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስም ዐፅም ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡

የቅዱስ እስጢፋኖስ ልደቱና ዕረፍቱ ጥር 1 ቀን ነው፡፡ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በክብር ቀበሩት፡፡ ጥቅምት 17 የተሾመበት ነው፡፡ መስከረም 15 ቀን ፍልሰተ ሥጋው ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቅዱስ ዐፅሙ ሙትን ያስነሣ ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ በቅናት ተነሥተው እንደ ጌታችን ቅዱስ መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስን ዐፅም አርቀው በመቆፈር ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ኖሮ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ መስቀሉ ተቆፍሮ በመውጣት መስከረም 15 ቀን ቅዱስ ዐፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፡፡

ከቅዱስ እስጢፋኖስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱስ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደና ከገድላት አንደበት።


“ሰላም ለእስጢፋኖስ እንተ ነጸረ በዐይኑ። እንዘ ወልድ ይነብር ለአብ ውስተ የማኑ። ከመ ኖትያዊ ጠቢብ ኃዳፌ ሐመር በኪኑ። ባሕረ መጻሕፍት አመ ጸበተት ልሳኑ። ተቃውሞቶ መዋግድ ስእኑ”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የጥቅምት 17።

የጥቅምት 14 ዓመታዊ የንግሥ በዓላት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየትኞቹ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ይከበራሉ?

እናስተዋውቃችሁ፡

የጥቅምት 14 በዓለ ንግሥ በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት በእነዚህ አብያተ ክርስትያናት ይከበራል። የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላትን ምንነትና ምክንያትን በዚህና በሌሎች ማኅበራዊ ገጾቻችን ላይ ማግኘት ይችላሉ።

1) ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል

2) ጽርሃ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

3) መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤ/ክ
ልዩ ስም፦የካ ኮተቤ

4)የረር ጎሮ ደብረምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ጎሮ

5)ቀበና ቤዛዊተ አለም ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤ/ክ
ልዩ ስም፦የካ ቀበና

6) ጽርሃ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ቦሌ ሰፈራ

7)ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ወደብረ ትጉሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቀጨኔ መድኃኔዓለም

8) ቀበና መካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ፈረንሳይ ለጋስዮን

9) መንበረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ ሽሮ ሜዳ

10) መናገሻ ገነት ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አራዳ ጊዮርጊስ

11) አፍሪካ ህብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቂርቆስ አፍሪካ ህብረት

12) ጎፋ ቤዛ ብዙኃን ቅድስት ኪዳነምሕረት ካቴድራል

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጎፋ ካምፕ

13)ፈለገ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሳሪስ 58

14) ፉሪ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 1 ኮንዶሚንየም

15) ምዕራፈ ቅዱሳን ፈለገ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ አረጋዊ ገዳም

ልዩ ስም፦አቃቂ ክ/ከ ሳሪስ

16) ደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊ ወ ገብረ ክርስቶስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ኮ/ቅ/ክ/ከ ወረዳ 1 ዘነበ ወርቅ

17) ፈጬ ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ ፈጬ

18) ጃቴ መካነ ሕይወት ቅድስት ኪዳነምህረት ካቴድራል

ልዩ ስም፦አቃቂ ክ/ከ 08

19) ቃሊቲ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና አቡነ አረጋዊ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 12 ሰሪቲ

20) ደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል።

ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ፦

እንኳን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአንዱ ለወንጌላዊ ለቅዱስ ማቴዎስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።


“ሰአሉ ለነ አርባዕቱ ወንጌላውያን መምህራን ሥዩማን አዕማዲሃ ለቤተ ክርስቲያን ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ”። ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያን ምሶሶዎች የምትኾኑ ሹማምንት መምህራን የምትኾኑ አራቱ ወንጌላውያን ለምኑልን ማልዱልን። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታቱ ላይ።


ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ፦ ይህም እንዲህ ነው በብዙ አገሮች ውስጥ አስተምሮ ብዙዎች ሰዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ከመለሰ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድ አዘዘው። ተጒዞም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንድ ወጣት ብላቴና አገኘ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም እንዲህ ብሎ መለሰለት “አንተ ግን ራስህንና ጽሕምህን ካልተላጨህ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም”። ይህም ነገር ለሐዋርያ ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግመኛ በስሙ ጠራው። ሐዋርያውም “ወዴት ታውቀኛለህ” አለው እርሱም “እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ ከአንተም አልርቅም” አለው።


ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ ለአማልክት ካህናት አለቃቸው ከሆነ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው እንዲህም አላቸው። “ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ” በዚያንም ጊዜ ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መገባቸው።
የሀገሩም ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት ጨመረው ጌታችንም አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ በሚያሠቃያቸው ነገር ሲያስብ እነሆ ልጁ እንደ ሞተ ነገሩት እጅግም አዘነ። ሐዋርያ ማቴዎስም “ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም” አለው ንጉሡም “የሞተ ማንሣት እንዴት አማልክት ይችላሉ” ብሎ መለሰ። ቅዱስ ማቴዎስም “ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅህን ማሥነሣት ይችላል” አለው። ንጉሡም “ልጄ ከተነሣ እኔ አምናለሁ” አለ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይገባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡን ልጅ ከሞት አስነሣው። ንጉሡም ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ የአገር ሰዎች ሁሉም አመኑ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ካህናትንም ሾመላቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ወንጌልን አስተማረ።

ከዚህም አስቀድሞ በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስን ሁል ጊዜ በየበዓላቸው ወደ እነርሱ ሲመጣ አየው ከእርሱም ጋር መቶ አርባ ሽህ ሕፃናት አሉ መላእክትም ሁሉ በዙሪያው ቁመው ያመሰግኑታል። በብሔረ ብፁዓን ስለ ሚኖሩ ወገኖችም ድንቅ ስለሆነ ሥራቸው ሁሉ ከሐዋርያው በኋላ ወደርሳቸው የገባ ዘሲማስ ቀሲስ ምስክር ሆነ።


ከዚህም በኋላ የሐዋርያው የተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቀርብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳመነ አገረ ገዢውም ይዞ ከወህኒ ቤት ጨመረው። በዚያም አንድ እጅግ የሚያዝን እሥረኛ አይቶ ስለኀዘኑ ጠየቀው እርሱም ብዙ የሆነ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሠጠመበት ነገረው ሐዋርያ ማቴዎስም “ወደ ዕገሌ ባሕር ዳርቻ ሒድ ወርቅን የተመላ ከረጢትንም ታገኛለህ ያንንም ወርቅ ወስደህ ለጌታህ ስጥ” አለው።


ስለዚህም ድንቅ ተአምር ብዙዎች ክብር ይግባወና በጌታችን አመኑ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ቅዱስ ማቴዎስንም ራሱን እንዲቆርጡ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው ቈረጡት ምእመናንም በሥውር መጥተው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የጥቅምት 12 ስንክሳር።

«በቤተክርስቲያን የጽጌ ማኅሌት እንጂ የጽጌ ጾም የሚባል ነገር የለምን❓❓❓»

የእመቤታችን ስደት

የዛሬ ዓመት ነው፤  እጅ ለመንሳትና  ደጅ ለመጥናት የ«ተክልዬ»  የክብር ማረፊያ ወደሆነችው የምድር ጌጥ ደብረ ሊባኖስ አቀናሁ። “ተክልዬ”ን በውሥጣቸው እንዳይ ተስፋም እንዳልቆርጥ  ለተሠጡኝ አባ ጌታዬ (የመጋቢ ምትክ) እንግዳ ልጃቸው ነኝ።

         ወደ እርሳቸው ማልደን እንወጣና ከወንድሞች ጋር ገብተን ቅድመ ቅዳሴ ተምረን፣ ተመክረንና አድምጠን እንወጣለን።

       በዚያ ቀን በተለየ መልክ በመጪው “የጽጌ ጾም” ስለሚገኘው በረከት እየነገሩን  አባቶች በልዩ ፍቅር ተጠብቀው እንዴት እንደተጠቀሙባት እየነገሩን እንድንዘጋጅ  ይመክሩን ጀመር ። በቸኮለ ማቅኛ (ድፍረት በነዳው አንደበት) ድንገት ማረም አማረኝና  «በቤተክርስቲያን ወርኃ ጽጌ ፣ ዘመነ ጽጌ ፣ ማኅሌተ ጽጌ  እንጂ የጽጌ ጾም የሚባል ነገርኮ የለም አባታችን!» አልኳቸው።

     አልተናደዱም ግን አዘኑ። በትካዜ እጅጉን ዝግ ባለ ድምጽ “እንዲያ እያላችሁ ነው ምታስተምሩት? ” አሉኝ። “ለምን መሰልዎት አባታችን… ” ብዬ ለማስረዳት እኔ የጽጌን ጾም ንቄና አጥቅቼ ሳይሆን የፈቃድ ጾም ስለሆነ እያልኩ ላብራራ ስንደረደር በከንቱ መውተርተሬን ገትተው እንዲህ አሉ “ተወው የኔ ልጅ አባቴ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ብሎሃል «ጾም ታጸምም ኵሎ ፍትወታት ዘሥጋ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና»
#ጾም_የሚባል_የሌለው_በዓለ_ሃምሳ_ብቻ_ነው። ቀንበር አለዘብን ብላችሁ ሸክም አታክብዱ፤ መብል ሥጋን ያገዝፋል ጾም ግን ሰውነትን ያቀላል …  ዛሬማ ፍቅር በራቀበት፣ ተስፋ በመነመነበት፤ ትውልድ እያለቀ ፣ እምነት እየደረቀ  ያለጊዜዋ ምድርን   ልታሳልፉ  ጾም የለም እያላችሁ መስበክ ጀምራችኋላ? ”

            ተግሳጹ ከጅራፍ በላይ የሚያም ነበር!  ያኔ  ኅሊናውን ዋሻ ፣ አንደበቱን ጋሻ አድርጎ ራሱን የሚከላከል «ሰው» በተፈለገው ልክና በተገቢው መንገድ መጥፋቱ እያስጨነቃቸው   «ምላሱ የሰላ አእምሮው የላላ» ከልክ በላይ የሚፈነጭ የኔቢጤው በየቦታው “ጾመ ጽጌን” ማውገዙ  እጅጉን ሕመም እንደሆነባቸው አስረድተው በአላዋቂነት ስለሰጠሁት ማቅኛ ይቅርታዬን ተቀብለው አለፉኝ።

         ከቅዱስ ያሬድ የነገሩኝን እያሰላሰልኩ
ጾመ … ጻመወ …  ጸመወ … (ጾመ፣ መከራ ተቀበለ፣ ዝምአለ) የሚለውን ዘር እየቆጠርኩና እያዛመድኩ   ጿሚ፣ ጸማዊ፣ ጽምው ለመሆን በመጣር ከጽሙና መንደር ደርሶ መቆጠብ ያለውን ዋጋ እየመዘንኩ ተመለስኩ።

          ባለ ብዙ መልእክት ሆኖ “«ጾም ታጸምም ኵሎ ፍትወታት ዘሥጋ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና» አለ አባቴ ቅዱስ ያሬድ” ያሉት በውስጤ ተመላለሰ።

          ጾም የሥጋን ፍላጎቶች ሁሉ ጸጥ ታደርጋለች። ለወጣቶችም ዝምታን ታስተምራቸዋለች።  (እውነት ነው እርጋታ፣ ዝምታ ፣ ጽሙና…  የጾም ውጤት ነው)

         በቤተክርስቲያናችን የበዙ የጾም ቀናት አሉን ፤ በዓመት ውስጥ በአጠቃላይ ወደ ፪፻፷ ገደማ ይደርሳሉ   ከእነዚህ ውስጥ ወደ ፩፻፹ የሚጠጉ ቀናት ለሁሉም አማንያን እንደ ግዴታ በአዋጅ አጽዋማት ውስጥ ተካትተዋል።   ቀሪዎቹ ደግሞ በካህናቱ እና ሌሎች  ምዕመናን በቀኖና ፣ በፈቃድ…  የሚጾሟቸው ናቸው። መናንያኑ ግን ከዓመት እስከ ዓመት የዱር ዕፀው ቅጠላ ቅጠል ከውኃ ጋር ሰንበትና በዓለ ፶ እየቀመሱ ከዓመት እስከ ዓመት ይጾማሉ።

✧ ቅዱስ ያሬድ ሌላ ምክርም አለው ፦

⇨ “በፍኖተ ጽድቅ ፍትሑ ለእጓለ ማውታ ወአነሂ እትመየጥ ኀቤክሙ ለሣህል ከመ ፈለገ ሰላም ዛቲ ጾም በቍዔት  ባቲ ትፈሪ ጽድቅ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ወታበጽሕ ውስተ አዕምሮ ዚአሁ”

➺ በእውነት መንገድ ለድሃ-አደግ ፍረዱ (የተቸገረውን እርዱ)  እኔም ወደእናንተ ለይቅርታ እንደ ሰላም ወንዝ እመለሳለሁ፤  ጥቅም የሚገኝባት  ይህች ጾም ጽድቅን የምናፈራባት ለወጣቶች እርጋታን የምታስተምር እርሱን ወደማወቅ የምታደርስ ናት ።

✧ የተዋህዶ ዓይን የኢትዮጵያ ብርሃን ቅዱስ ያሬድ ሌላም ምዕዳን ይጨምራል

⇨ ጾም ቅድስት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ተመጠወ ሙሴ ሕገ እግዚአብሔር ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ኤልያስ ዓርገ ውስተ ሰማያት ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ዳንኤል ድኅነ እምአፈ አናብስት ጾም ቅድስት ሶስና ድኅነት እምዕደ ረበናት ጾም ቅድስት ዓቀመ ኢያሱ ፀሐየ በገባዖን ጾም ቅድስት ጳውሎስኒ ይቤ ትግሁ እንከ አኃውየ በጾም ወበጸሎት ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ጾም ቅድስት ትሚህሮሙ ለወራዙት ጽሙና።

➺ ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች።  ጾም የተለየችና  የተቀደሰች ናት። በዚህች በተቀደሰችዋ ጾም  ሙሴ የአምላኩን ሕግ ተቀበለባት፤  ጾም የተለየችና  የተቀደሰች ናት። በዚህች ቅድስት ጾም ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገባት ፤  ጾም የተለየችና  የተቀደሰች ናት። በዚህች ቅድስት ጾም ዳንኤል ከአንበሶች አፍ ዳነባት በዚህች ቅድስት ጾም ሶስና ከመምህራኑ ክስ ተርፋለች በዚህች ቅድስት ጾም ኢያሱ በገባዖን ፀሐይን አቆመ ። ጾም የተለየችና  የተቀደሰች ናት! ጳውሎስ እንዲህ አለ ‘ እንግዲህ ወንደረሞቼ በጾምና በጸሎት ትጉ’ ጾም የተለየችና  የተቀደሰች ናት። በዚህች በተቀደሰችዋ ጾም … ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች።

✧ ደራሲውም እንዲህ ሲል መክሮናል

… ማርያም ታቦት ጽላተ ኪዳን ሐዲስ፣
ቅብዕኒ ርጢነ ጾም እስከ ሰኮና እግር ወርእስ፣
እስመ ጾም ትፌውስ ሕማማ ለነፍስ።

➺ ለሐዲስ ኪዳን ጽላት ታቦቱ ፡ ማርያም አንቺ ነሽና
የጾም መድኃኒቱን ቀቢኝ ፡ ከራስጠጉር እስከ እግር ሰኮና
የነፍስ ሕመም የሚፈወስ ፡ በጾም «በጸሎት» ነውና።

እንግዲህ ከአባቴ ይኼን ያዝኩላቸው በቤተክርስቲያናችን ጾም የሌለው ለበዓለ ሃምሳ ብቻ ነው። ይልቅ ሰውን በማንጠቅምበት አልፎም ለማያድንም ምክንያት  ጾመ ጽጌን አንንቀፋት።

“ወዝኬ ዘሰ ዘይሜህር ዘእንበለ ይኅሥሡ እምኔሁ ወዘእንበለ ምክንያተ ድልወት ለበቁዔተ ሰማእያን ውእቱኬ አብድ ወአኮ ጠቢብ ➺ ይኸውም አስተምረን ሳይሉት እና ሰሚዎቹን የሚጠቅምበት ምክንያት ሳይኖረው ላስተምራችሁ የሚል ሰው አላዋቂ ነው እንጂ አዋቂ አይባልም፡፡ ሰነፍ እንጂ ጠቢብ አይባልም” (ፊልክስዩስ)

      ✨እንኳን ለጽጌ ጾም አደረሰን አደረሳችሁ። በማኅሌት የታጀበውን ተወዳጁን ዘመነ ጽጌ ወርኃ ጾም ተደርቦበት  የበረከት ዋጋና በጎ ምላሽ የሚያሰጠን ያድርግልን።

✍ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ

መስከረም ፳፩ (21)

እንኳን ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም (ለብዙኃን ማርያም)፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በግሸን በመስቀለኛው ተራራ ላይ ገብቶ ለተቀመጠበት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለመወሰን፤ በኒቅያ ጉባኤ አርዮስን ለማውገዝ ከሩቅ ለተሰባሰቡበት ቀን በሰላም አደረሰን።
የዕለቱ አንገርጋሪ ግእዝ፦ ሃሌ ሉያ “ዓይ ይእቲ ዛቲ መድኃኒት እንተ ኀሠሥዋ ወዖድዋ ነቢያት ወይቤሎ ለኖህ አመ አይህ ግበር ታቦተ በዘትድኅን እትአመን ባቲ እስመ አርአያ መስቀል ይእቲ አክሊለ ተቀጺላ ታንሶሱ። ትርጉም፦ ያች መድኃኒት ማን ናት ነቢያት የፈለጓት የዞርዋት በጥፋት ጊዜ ለኖህ አለው የምትድንበት ታቦት ሥራ በእርሷ አርአያ መስቀል ናትና እክሊል ተቀዳጅታ ትመላለሳለች።


የዕለቱ ዓራራይ ዜማ፦ “ሠለስቱ ምዕት ወሠርቱ ወሰመንቱ ኤጲስ ቆጶሳት ርቱዓነ ሃይማኖት እለ መሀሩ በስሙ በዕፀ መስቀሉ በውስተ ማኅበሮሙ ለቅዱሳን”። ትርጉም፦ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ኤጲስ ቆጶሳት ሃይማኖታቸው የቀና በስሙ በዕፀ መስቀሉ በቅዱሳን ማኅበር ያስተምሩ። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ።


ብዙኃን ማርያም፦ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል “ብዙኃን ማርያም” በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ለጉባኤ ኒቅያ ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤
ጉባዔ ኒቅያ፦ በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጥሯል፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ “አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!” የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡


በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለ ነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ ይገኙበታል፡፡


ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን “ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ” ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ (2348) መካከል ፫፻፲፰ (318) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው “ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው” ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም “ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን” ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡


፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት “ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን” የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት “ብዙኃን_ማርያም” እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡


ዕፀ መስቀል፦ በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤ ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው “የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል” አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር “የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ” የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡
ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡
መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ” የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ” ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ምየጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡ “መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!” ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


ምንጭ፦ ከማኅበረ ቅዱሳን ጽረ ገጽ የተወሰደ።

የ2016 ዓ.ም የአጽዋማትና የበዓላት አወጣጥ ( በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ )

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ንዌጥን በረድኤተ እግዚአብሔር ጽሒፈ ቀመረ ባሕረ ሐሳብ ዘድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ጸሎቱ ወበረከቱ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን ።


መጽሐፉ መርሐ ዕውራን፤ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፤ መርሐ ዕውራን አለው አላዋቂዎችን መርቶ ወደ ዕውቀት የሚያደርስ ስለኾነ፤ ሐሳብ ቊጥር ነው ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኀጢአቶሙ ወእለ ኢኃሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ እንዲል፤ ባሕረ ሐሳብ አለው ባሕር እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል፤ ከለመዱት በኋላ በልብ ተኝቶ ይውሏል ይኽም መጽሐፍ እስኪለምዱት ድረስ ያስፈራል ይገርማል ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር አስታውቆ ደስ ያሰኛልና፤ አንድም ባሕር ከለመዱት በኋላ ከመሠረቱ ወርዶ አሸዋ ይዞ ይወጧል ይኽም መጽሐፍ ከለመዱት በኋላ ብዙ ምስጢር ያስታውቃል ያስመርምራል፤ አንድም የባሕር አዟሪቱ መንገዱ ብዙ ነው የዚኽም መጽሐፍ መንገዱ ስልቱ ብዙ ነውና፤ አንድም ሐሳበ ባሕር ይላል ባሕር ዘመን ነው ሠፈራ ለባሕር በመሥፈርት ወደለዋ ለዓለም በመዳልው መኑ ዘአእመረ ስፍሐ ሰማይ ወዕመቀ ቀላይ እንዲል በባሕር ውስጥ ያለውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው እንዳያውቀው በዘመንም ኹሉ የሚደረገውን እግዚአብሔር እንጂ ሰው አያውቀውምና፤ ኢኮነ ለክሙ ታእምሩ መዋዕለ ወአዝማነ ዘሠርዐ አብ እንዲል፡፡ 

👉 ድሜጥሮስ ማለት መጽሔት ማለት ነው፤ አንድም ፀሓይ ማለት ነው ሰውን በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና የድሜጥሮስ ትውልዱ ነገዱ ከአዝማደ እስክንድርያ ነው ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ ያባቱ ወንድም ያጐቱ ሴት ልጅ ነበረችው አባቷ ሲሞት ልጄን ከልጅኽ አትለይብኝ አደራ ብሎት ሞተ፤ አብረው አደጉ አካለ መጠን አደረሱ ዘመኑ ሐሳውያን የበዙበት ነበርና ርሱንም ከሌላ ብናጋባው ርሷንም ለሌላ ብንድራት ከሃይማኖት ይወጣሉ ከምግባር ያድጻሉ ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ ርስ በርሳቸው እናጋባቸው ብለው መከሩ መክረው አልቀረ ሠርግ አደረጉ፤ ሥርዓተ ከብካቡ ሲፈጸም ሥርዓተ መርዓዊና ሥርዓተ መርዓት ያድርሱ ብለው ከጫጉላው ቤት አግብተዋቸው ኼዱ፤ ርሷን አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶ ድሜጥሮስ ያንት ወንድምነት ለኔ የኔ እኅትነት ላንተ አልበቃ ብሎ የባዕድ ሥራ እንሥራ አልኽን አለችው፤ እኔስ የናት ያባቴን ፈቃድ ማፍረስ ይኾንብኛል ብዬ ነው እንጂ ፈቃዴም አይደል ፈቃድሽ ካልኾነ አንተወውምን አላት እንተወው አለችው፤ እንኪያስ የተለያየን እንደኾነ አንችን ለሌላ ወንድ እኔንም ለሌላ ሴት ያጋቡናልና መስለን እንኑር አላት እንኑር አለችው፤ በአንድ ቤት በአንድ አልጋ እየተኙ 48 ዘመን ኖሩ፤ ርሱን መልአኩ ቀኝ ክንፉን ርሷን ግራ ክንፉን እያለበሳቸው ያድራል፤ ሲነጋ በመስኮቱ በአምሳለ ርግብ ወጥቶ ሲኼድ ያዩታል ስለምን ቢሉ በቅተዋልና አንድም በንጽሕናቸው ይትጉበት ብሎ፤ በዘመኑ የተሾመው ሊቀ ጳጳስ ሉክዮስ ሉክያኖስ ይባላል አረጀ ደከመ፤ ሕዝቡ ተሰብስበው አባታችን አንተ አረጀኽ ደከምኽ ካንተ ቀጥሎ የሚሾመውን ንገረን አሉት፤ እናንተም ወደ እግዚአብሔር አመልክቱ እኔም ወደ እግዚአብሔር አመለክታለኊ ብሎ ቀን ቀጥሮ ሰደዳቸው ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጣ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ካንተ ሊባረክ ይመጣል ካንተ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው አለው፤ ሕዝቡም በቀጠራቸው ቀን መጡ አገኛችኹት አላቸው እኛስ አላገኘንም አሉት እኔ አገኘኹላችኊ አላቸው፤ ስሙ ድሜጥሮስ የሚባል ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ሊባረክ ይመጣል ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ርሱ ነው ለጊዜው እንቢ ይላችኋል ግድ ብላችኊ ሹሙት አላቸው፡፡

👉 ይኽም ድሜጥሮስ ተክል አጽድቆ ዕርፍ አርቆ የሚኖር ገበሬ ነበር ይላሉ፤ ከዕለታት በአንድ ቀን ተክል ለመጐብኘት ከተክል ቦታ ገብቶ ሳለ ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ ይኽንስ ከሊቀ ጳጳሱ ወስዶ ሊባረኩበት ይገባል ብሎ በንጹሕ ዕቃ አድርጎ ይዞ ኺዶ ንገሩልኝ አለ፤ እንዲኽ ያል ይዞ የመጣ ሰው ከደጅ ቁሟል ብለው ነገሩት እንዲኽ ያል ይዞ የመጣውን ከደጅ ያቆሙታልን ያገቡታልን እንጂ ግባ በለው አለው፤ ገብቶ ተባርኳል፤ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው ይኽ ነው ብሏቸው ወዲያው ዐረፈ፤ ቀብረው ሲመለሱ ሕዝቡ ተሾምልን አሉት በማርቆስ ወንበር የሚቀመጥ የተማረ ነው ደግሞም ንጹሕ ድንግል ነው፤ እኔ እንደምታውቁኝ ሕዝባዊ ነኝ ደግሞም ሥጋዊ ነኝ እንደምን አድርጎ ይኾናል አላቸው፤ እኛስ አባታችን ያዘዘንን ትተን ሌላ አንሾምም አሉት፤ ርሱም እንደማይተውት ዐውቆ ሊቀ ጳጳሱ ሲሾም ምን ያደርግላችኊ ነበር አላቸው አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ይተረጒምልን ነበር አሉት ወንጌል አምጡልኝ አለ፤ አመጡለት እንኳን ትርጓሜውን ንባቡን አያውቀው የነበረ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ተርጒሞላቸዋል፤ ይኽም ብቻ አይደለም ብሉይና ሐዲስ ተርጒሟል፡፡

👉 ከዚኽ በኋላ ከደጀ ሰላም ቆሞ አንተ በቅተኻል ተቀበል አንተ አልበቃኽም ቆይ እያለ ከልክሏቸዋል፤ ሕዝቡም ቆንጆ ሚስቱን ከቤቱ አስቀምጦ እኛን ይከለክለናል ብለው አምተውታል፤ መልአኩም ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ ወብእሲትከ አላ አላ አድኅኖ ሕዝብከ አለው፤ ርሱም ዕንጨት እየያዛችኊ ተሰብሰቡ ብሎ ዐዋጅ ነገረ ምእመናኑም ዕንጨት እየያዙ ተሰበሰቡ ደመራ አሠርቶ በእሳት አቃጥሎ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ ሊቀድስ ገባ ጸሎተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ በእሳቱ መኻከል እየተመላለሰ ያጥን ጀመር፤ ሚስቱም ከዚያ ነበረችና ስፍሒ አጽፈኪ ልብስሽን ዘርጊ አላት ዘረጋች እሳቱን እየታፈነ ከልብሷ ላይ አደረገላት ልብሷ ሳይቃጠል ቀርቷል ሕዝቡም አባታችን ይኽን ተአምራት ያደረግኸው ስለምን ነው አሉት፤ አምታችኹኝ አላቸው፤ አላበጀንም በድለናል ይቅር በለን አሉት፤ ይፍታሕ ወይኅድግ ያንጽሕ ወይስረይ ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜ ከዚያ ወዲኽ ተጀምሯል፡፡

👉 ድሜጥሮስ በተሸመ በ27 ጌታ ባረገ በ207 ዘመን ይኽን መጽሐፍ ተናግሮታል፤ ስለምን ቢሉ ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ርሱ የነበሩ ምእመናን ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ሳኒታ ጀምረው በየካቲት 21 ይፈጽሙ ነበር፤ ሕማማትንም ወአጐንድዮሙ መዋዕለ ይላል በመጋቢት ያደርጉ ነበር እንዲኽ ማድረጋቸው ተጠምቆ ጹሟል ሕማሙም በመጋቢት ነው ሲሉ፤ አጽዋማትን በዓላትን እንዳገኙ ያደርጉ ነበር፤ ርሱ ግን በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ይላል ሰኞ የሚኾነውን ከሰኞ ረቡዕ የሚኾነውን ከረቡዕ ኀሙስ የሚኾነውን ከኀሙስ ዐርብ የሚኾነውን ከዐርብ እሑድ የሚኾነውን ከእሑድ እንዳይወጣ ኢየዐርግ ኢይወርድ እየሰጠ ወስኖታል፤ አይወጣም አይናወጥም ቢናወጥስ አጽዋማት በዓላትም እንደቀድሞ በኾኑ ነበር፤ ርሱም በዘአለበዎ መንፈስ ቅዱስ ባልተባለም ነበር፡፡

👉 ድሜጥሮስ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ ርክብ፣ ምሕላ ድኅነት ከረቡዕ፤ ዕርገት ከኀሙስ፤ ስቅለት ከዐርብ እንዳይወጣ ግለጽልኝ ብሎ ግብር ገባ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከሌቱ በ23 በ23 እስከ 7 ሱባኤ ቈጥረኽ 161 ይኾናል፤ 150ውን ገድፈኽ 11 ይተርፋል፤ አበቅቴ በለው ብሎታል፤ መልአኩም ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ከመዓልቱም እስከ 7ት ሱባኤ ቈጥረኽ 49 ዕለት ይኾናል 30ውን ገድፈኽ 19ኝን መጥቅዕ በለው ብሎታል፤ የድሜጥስ ጥንተ አበቅቴና መጥቅዕ ይኽ ነው፤ የሌሊቱን አብዝቶ የቀኑን ስለምን አሳነሰው ቢሉ የሌሊት ልቡና ክት የቀን ልቡና ባካና ነውና፤ አንድም ቀን ሲፈርድ ሲተች ጉባኤ ሲያደርግ ይውላልና፤ ሕማማትን ያስቀድማል ትንሣኤን ያስከትላል ሐዘኑ ለደስታው እንዲመች፤ ካላዘኑ ደስታ ካልጾሙ ፋሲካ የለምና፤ የሐዲሱን ያስቀድማል ዘመኑ ነውና የብሉዩን ወደኋላ ያደርጋል፤ አልቦ መጥቅዕ ወአበቅቴ አንድ ወገን ያደርጋል፤ ታሪክ፣ መቅድም፣ አርዕስት እየሰጠ ወስኖታል፤ ታሪኩ ይኽ ነው፤ መቅድሙን ያመጣዋል።

👉 በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካለት ሦስት ስላልነ በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ጸሎቱ ልመናው በረከቱ ክብሩ ይደርብንና የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ የተናገረውን የባሕረ ሐሳብ ቊጥር መጽሐፍን በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡ እግዚአብሔር እንደዛሬው ኹሉ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት ሳለ ክብሩ በብቻው እንደቀረ ዐውቆ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፤ አስቦም አልቀረ ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የቀረውን ፍጥረት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጠረ “ወኲሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ፤ ወእንዘ ኢየኀድግ ርእሶ ዘእንበለ ሰማዕት፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘንተ እምአፍአ ብከ ሰማዕት ወመምህር ዘይመርሐከ ኀበ ዝንቱ፤ ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ” እንዲል፤ እግዚአብሔርስ የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቈጠር ፍጡር ተናግሮ ባልፈጸመውም ነበር፤ እየወገን እየወገኑ ግን ብዙውን አንድ ብዙውን አንድ እያሉ ቢቈጥሩ ከእሑድ እስከ ዐርብ የፈጠረው ሥነ ፍጥረት 22 ነው፡፡ እስከዚኽ አርዕስት ነው፤ ይኽንንም በሥነ ፍጥረት ይመለከቷል።

👉 የፀሓይ ጥንታት ሦስት የጨረቃን ዐምስት የሚል ነውና፤ ይኽ ዓለም የተፈጠረበት ዕለተ እሑድ ጥንተ ዕለት፤ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፀዋት የተፈጠሩበት ዕለተ ሠሉስ ጥንተ ቀመር፤ ብርሃናት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕ ጥንተ ዮን ይባላል፤ “እሑድ ወሠሉስ ወረቡዕ ዘውእቶሙ ሠለስቱ ጥንታት” እንዲል።

👉 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ቢቈጠር በፀሓይ 7516 ዘመን፤ በጨረቃ 7746 ዘመን ከ8 ወር ከ14 ዕለት ይኾናል። ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ የነበረው በፀሓይ 5500 ዘመን፤ በጨረቃ 5668 ዘመን ከ10 ወር ከ9 ዕለት፤ ይኽ ዓመተ ኩነኔ፣ ዓመተ ፍዳ ይባላል፡፡

👉 ከልደተ ክርስቶስ ወዲኽ ያለው ግን በፀሓይ 2016 ዘመን ነው፤ በጨረቃ 2077 ዘመን ከ10 ወር ከ5 ዕለት ይኽ ዓመተ ሥጋዌ፣ ዓመተ ምሕረት ይባላል፤ መላው ዓመተ ዓለም ነው፤ ዓመተ ዓለም ባለው ዓመተ ምሕረት የሚል ይገኛል፤ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድም ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል፤ ስለምን ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት አለው ቢሉ? ሰው በዚኽ ዓለም ሳለ ኀጢአት ሠርቶ ንስሓ ቢገባ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት የሚያገኝበት ስለኾነ ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል “በዕለት ኅሪት እሰምዐከ ወበዕለተ መድኀኒት እረድአከ ወናሁ ይእዜ ዕለት ኅሪት ወናሁ ዮም ዕለተ አድኅኖት” እንዲል፡፡

👉 ለዚኹም መሥፈሪያ ሰባት አዕዋዳት አሉት፤ ምንና ምን ቢሉ? ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ከሊኹም ሦስቱ በዕለት አራቱ በዓመት ይቈጠራሉ፤ በዕለት የሚቈጠሩት ሦስቱ ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት ናቸው፤ በዓመት የሚቈጠሩ አራቱ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡

👉 ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቀዳሚት ያሉ ሰባት ዕለታት ናቸው፤ እሊኽም አውራኅን ለማስገኘት በሰባት በሰባት ሲመላለሱ ይኖራሉ “እስመ ኊልቊ ሰብአቱ በኀበ ዕብራውያን ፍጹም ውእቱ” እንዲል

👉 ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር ፴ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29፤ አንድ ጊዜ ፴ ይኾናል፤ እሊኽም ዓመታትን ለማግኘት በ፴ በ፴ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡

👉 ዐውደ ዓመት በፀሓይ 365 ዕለት በጨረቃ 354 ዕለት ነው፤ በፀሓይማ ምነው 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት፤ በጨረቃ 354 ዕለት ከ22 ኬክሮስ ከ1 ካልዒት ከ37 ሣልሲት ከ52 ራብዒት ከ48 ኀምሲት አይደለውም ቢሉ “ወበውስተ ውሁድኒ ንብል አልቦ ወኢአሐዱ” እንዲል መጽሐፍ ትርፍ ትቶ ጐደሎ መልቶ መቊጠር ልማድ ነውና ፷ ካልመላ ብሎ እንዲኽ አለ እንጂ ቊጥሩስ አለ “እስመ ልማደ መጽሐፍ ይነግር ኊልቈ ምሉዓ ወፍጹመ ወየኀድግ ዘተርፈ ወይዌስክ ዲበ ሕፀፅ ካልዐ” እንዲል፤ ዕለታትን አዕዋድ አላቸው አውራኅን የሚያስገኙ ስለኾነ፤ አውራኅን አዕዋድ አላቸው ዓመታትን የሚያስገኙ ስለኾነ “ወበከመ ይትወለዳ አውራኅ እምዕለታት ወዓመታት እምአውራኅ ከማሁ ይትወለዳ አዕምሮታት እመከራት ወእምግባራት እንዲል፡፡

👉 ዐውደ አበቅቴ 19 ዓመት ነው በዚኽ ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ይገናኙበታል፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ መምህራነ ወንጌል ሐዋርያት፣ ሊቀ ጳጳሳት ዲሜጥሮስ ከ፳ው አንድ ቀመር አንድ ተረፈ ቀመር፤ ከ፵ው ኹለት ቀመር ኹለት ተረፈ ቀመር፤ ከ፷ው 3 ቀመር 3ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፹ው 4 ቀመር 4ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፻ው 5ቀመር 5ት ተረፈ ቀመር እያላችኊ ቊጠሩ ማለታቸው ከዚኽ የተነሣ ነው “ወእምዘተርፈከ እምዐሠርቱ ወተሰዓቱ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ እስመ ለዛቲኒ ዐሠርቱ ወተሰዓቱ ሙሴ ገብራ በጥበበ እግዚአብሔር ዘይገብሩ ባቲ ፍስሐ አይሁድኒ ወክርስቲያንኒ” እንዲል

👉 ዐውደ ፀሓይ 28 ዓመት ነው፤ በዚኽ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ረቡዕ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ረቡዕ ማቴዎስ እንዲል፤ ዕለትን ፀሓይ አለው “ወበትእዛዝከ ይቀውም ዕለት” እንዲል፤ ወንጌላዊዉን ፀሓይ አለው “አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም” ካለው አንዱ ርሱ ነውና፤ በሰንጠረዥ ፀ፣ ደ ይላል፤ ዐውደ ፀሓይ ማለት ነው፡፡

👉 ዐውደ ማኅተም 76 ዘመን ነው፤ በዚኽ አበቅቴ ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ አበቅቴው 18 ወንጌላዊዉ ዮሐንስ ነው፤ ማኅተም አለው አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉ ለወንጌላዊው ፍጻሜ ነውና፡፡

👉 ዐውደ ቀመር 532 ዘመን ነው፤ በዚኽ ዕለት፣ ወንጌላዊ፣ አበቅቴ እሊኽ 3ቱ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ሠሉስ ማቴዎስ እንዲል አበቅቴው አልቦ ነው “ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊ ዮሐንስ” እንዲል፤ በዐውደ ፀሓይ ቦታ ዐውደ ማኅተም፤ በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሓይ የሚል ይገኛል፤ ከኹለቱ አንዱ ቢታጣ አንዱ ከቀመር ገብቶ ይቈጠራል፤ ቀመርን ለሦስቱ ስም በሰጡ ጊዜ ዐውደ ቀመር ዐቢይ ቀመር፤ ዐውደ

ማኅተም ማዕከላዊ ቀመር፤ ዐውደ አበቅቴ ንዑስ ቀመር ይባላል፤ ዐቢይ ቀመር መደቡ 14 ቊጥሩ 532፣532፤ ማዕከላዊ ቀመር መደቡ 6 ቊጥሩ 76፣76፤ ንዑስ ቀመር መደቡ 3 ቊጥሩ 19፣19 ነው፡፡

👉 ከዚኽም ዓመተ አበቅቴን ለማግኘት 7516 ዘመን በዐቢይ ቀመር ቢቀምሩ 532፤ 532 የተፈጸመለት 14 ዐቢይ ቀመር፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 11 ዓመት ይተርፋል።

👉 መላውንም በማእከላዊ ቀመርም ቢቀምሩ 76፤ 76 የተፈጸመለት 98 ማእከላዊ ቀመር 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 11 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 በዐውደ ፀሓይም ቢቀምሩ 28፤ ኻያ ስምንት የተፈጸመለት 266 ዐውደ ፀሓይ፤  19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 11 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 መላውንም በንዑስ ቀመር ቢቀምሩ 19፤ 19 የተፈጸመለት 395 ንዑስ ቀመር
ኹኖ 11 ዓመት ይተርፋል፡፡

👉 7516ቱን ዘመን በቀመረ ዐረብም ቢቀምሩ 228፤ 228 የተፈጸመለት 32 ቀመረ ዐረብ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 11 ንዑስ ቀመር ኹኖ 11 ዓመት ይተርፋል።

👉 ስመ አቅማር ብዙ ነው አይቶ መተው ነው፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተጀመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ11ዱ አንዱን ቢያትቱ 10 ይተርፋል፤ 10 ዓመተ አበቅቴ ወጣ ገጠር ወንበር ይላል፡፡

👉 አበቅቴን ለማግኘት ከ10ሩ ዓመተ አበቅቴ 11፤ 11 ዕለት ቢነሡ 110 ይኾናል፤ ከ110ሩ 90ውን በ3፤ ፴ ቢገድፉት 20 ይተርፋል፤ 20 አበቅቴ ወጣ በዘመነ ዮሐንስ፡፡

👉 መጥቅዕንም ለማግኘት ከ10ሩ ዓመተ አበቅቴ 19 ዕለት ቢነሡ 190 ይኾናል፤ 190ውን በ6፤ ፴ ቢገድፉት 10 ይቀራል፤ 10 መጥቅዕ ወጣ በዘመነ ዮሐንስ፤ 20 መጥቅዕና 10 አበቅቴ ፴ ይኾናሉ እንጂ ከ፴ አይወጡም ከ፴ አይወርዱም፤ “ዓዲ መጥቅዕ ወአበቅቴ ክልኤሆሙ እመ ይበዝኁ ወእመ ይውኅዱ ኢየዐርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወባሕቱ ወትረ ይከውኑ ፴” እንዲል።

(ከዚኽ በኋላ አበቅቴ ከመጠነ ሠርቀ መዓልትና ከሚለው ዠምሮ…ኢየዐርግ ኢይወርድ ኹሉ እንደ ታሪኩ አስገባ)     
 
❤ መጥቅዕ 10 መጥቅዕ ሲያንስ በጥቅምት ይውላልና ጥቅምት ኀሙስ ይብታል፤ ኀሙስ – ኀሙስ 8፤ ዐርብ 9፤ ቅዳሜ 10፤ በዐለ መጥቅዕ ጥቅምት 10 ቅዳሜ ቀን ይውላል፤ የቅዳሜ ተውሳክ 8፤ 8 እና 10= 18 መባጃ ሐመር ይገኛል፤ በጥቅምት ሳኒታ የካቲት ዐርብ ይብታል፡፡ ዐርብ – ዐርብ 8፤ ዐርብ – ዐርብ 15፤ ቅዳሜ 16፤ እሑድ 17፤ ሰኞ 18 የካቲት 18 ነነዌ
♦ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ 14 ና 18=32፤ ፴ ውን ገድፎ 2 ይተርፋል።  መጋቢት እሑድ ይብታል እሑድ 1 ሰኞ 2
መጋቢት 2 ቀን ዐቢይ ጾም፡፡
♦ የደብረ ዘይት ተውሳክ 11፤ 11 እና 18=29፤ እሑድ እስከ እሑድ 8/ .. 15/ … 22/ … 29 መጋቢት 29 ደብረ ዘይት፡፡
♦ የሆሣዕና ተውሳክ 2፤ 2 እና 18=20፤ መጋቢት እሑድ ብቷል ሚያዝያ ማግሰኞ ይብታል፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 8/ …15/ ረቡዕ 16፤ ኀሙስ 17፤ ዐርብ 18፤ ቅዳሜ 19፤ እሑድ 20 ሚያዝያ 20 ሆሣዕና
♦ ከዚኽም በዓለ ፍሥሕን (የአይሁድ ፋሲካን) ይናገሯል፤ ፍሥሕን 4 ነገር ይጠብቃታል፤ ገቦ መጥቅዕ፤ ሰሙነ ሕማማት፤ 190 ዕለት፤ 14 ሌሊት፤ ፍሥሕ የዕለት ተውሳክ አትሻም በደረቅ መጥቅዕ ነው የምትወጣው መጥቅዑ 10 የፍሥሕ ተውሳክ 10= 20
በዓሉን አናከብረውም ስለምን እናወጣዋለን ቢሉ ሐዋርያት ፍሥሕን ከትንሣኤ ጋራ አንድ አድርጎ ያዋለ ካህን ቢኾን ከክህነቱ ይሻር፤ ምእመን ቢኾን ከምእመናን ይለይ ብለው አውግዘዋልና ስለዚኽ ለይተን እናወጣዋለን፡፡
♦ የስቅለት ተውሳክ 7፤ 7 እና 18=25፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 8/ …15/ …22 ረቡዕ 23/ ኀሙስ 24/ ዐርብ 25 ሚያዝያ 25 ስቅለት
♦ የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ 9 እና 18=27፤ ዐርብ 25 ቅዳሜ 26 እሑድ 27 ሚያዝያ 27 ትንሣኤ
♦ የርክብ ተውሳክ 3፤ 3 እና 18=21፤ ሚያዝያ ማግሰኞ ብቷል ግንቦት ኀሙስ ይብታል፤ ኀሙስ – ኀሙስ 8/ …15/ …22/ አንዷን ታግሦ ግንቦት 21 ርክብ
♦ የዕርገት ተውሳክ 18፤ 18 እና 18= 36፤ ፴ውን ቢገድፉ 6 ይተርፋል። ሠኔ ቅዳሜ ይብታል። ቅዳሜ 1፤ እሑድ 2፤ ሰኞ 3፤ ማግሰኞ 4፤ ረቡዕ 5፤ ኀሙስ 6 ግንቦት 6 ዕርገት፡፡
♦ የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28፤ 28 እና 18=46፤ ፴ውን ገድፎ 16 ይቀራል፤ ቅዳሜ – ቅዳሜ 8/ …15/ እሑድ 16 በዓለ ጰራቅሊጦስ ሠኔ 16፡፡ 
♦ የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29፤ 29 እና 18=47፤ ፴ውን ገድፎ 17 ይቀራል፤ ቅዳሜ – ቅዳሜ 8/…15/ እሑድ 16፤ ሰኞ 17 ሠኔ 17 ጾመ ሐዋርያት
♦ የምሕላ ድኅነት ተውሳክ 1፤ 1 እና 18= 19፤ ቅዳሜ እስከ ቅዳሜ 8/ …15/እሑድ 16/ ሰኞ 17/ ማግሰኞ 18/ ረቡዕ 19 ሠኔ 19 ምሕላ ድኅነት።

👉 ዓመተ ወንጌላዊን ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዓመተ ወንጌላዊ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ለእመ ተርፈ አሐዱ ማቴዎስ ወክልኤቱ ማርቆስ ወሠለስቱ ሉቃስ ወለእመ ዐረየ ክፍል ዮሐንስ እንዲል፤ ዓመተ ወንጌላዊን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ አንድ ቢተርፍ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ መኾኑ፤ ኹለት ቢተርፍ ማርቆስ፤ ሦስት ቢተርፍ ሉቃስ ቢተካከል ዮሐንስ መኾኑን በዚኽ ይታወቃል፤ 7516 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1879 ደርሷቸው ይተካከላል፤ ቢተካከል ዮሐንስ ያለው ይኽ ነው፤ ዛሬ ወንጌላዊዉ ዮሐንስ መኾኑ በዚኽ ታውቋል፡፡

👉 ጥንተ ዮንንም ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ጥንተ ዮን ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት ወትገድፎ በበሱባኤ ወዘተርፈከ እምሱባኤ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ ወእምዝ ይከውን ጥንተ ዮን እንዲል፤ ጥንተ ዮንንም ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ 5ኛ መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን አትቶ 1 ቢተርፍ ጥንተ ዮን ረቡዕ መኾኑን መስከረም ረቡዕ መባቱን፤ 2ት ቢተርፍ ኀሙስ፤ 3 ቢተርፍ ዐርብ፤ 4 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 5 ቢተርፍ እሑድ፤ 6 ቢተርፍ ሰኞ፤ 7 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡ 
አከፋፈል እንዳለፈው 7516 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1879 ደርሷቸው ይተካከላል፤ ይኽን በሱባዔ ይገድፏል፤ ከሺው 300 ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ ከ800ው አንዱን መቶ ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ 400 ይተርል፤ ከ100ው 2፤ ከ400ው 8፤ ከ8ቱ አንድ፤ ከዚያም 1 እና 79= 80 ይኾናል፤ ከ80ው 77ቱን በ11 ሱባዔ ቢገድፉ 3 ይተርፋል፡፡
ከአንዱ ወንጌላዊ 3 ከ4ቱ ወንጌላውያን 12፤ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜን 1879 ዕለት ትኾናለች፤ ርሷ በዕለት፤ ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና ግድፈት እንዳለፈው፤ መጠነ ራብዒት  3= 15፤  ከ15ቱ 7ቱን በአንድ ሱባዔ ቢገድፉ 8 ይተርፋል፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተዠመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ8ቱ አንዱን ቢያትቱ 7 ይተርፋል፤ 7 ቢተርፍ ማግሰኞ ያለው ይኽ ነው፤ የማግሰኞ ጥንተ ዮን 7 ነውና፡፡ ጥንተ ዮንም ማለት ጥንተ ፀሓይ፤ ጥንተ ጨረቃ፤ ጥንተ ከዋክብት ማለት ነው፤ ጥንተ ዮን ብሂል ጥንተ ተፈጥሮቶሙ ለፀሓይ፤ ወወርኅ ወከዋክብት እንዲል፡፡

👉 ዕለተ ቀመርንም ለማወቅ ለጥንተ ዮን ከወጣው አንዱን ሳያትቱ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 3 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 4 ቢተርፍ ዐርብ፤ 5 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 6 ቢተርፍ እሑድ፤ 7 ቢተርፍ ሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፤ ለጥንተ ዮን የወጣው 8 ነው፤ በሱባኤ ቢገድፉ 1 አንድ ቢተርፍ ማግሰኞ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ቀመርም ማለት ቀመር የተዠመረበት ዕለት ማለት ነው፤ ቀመር የተዠመረው ማግሰኞ ነውና፡፡

👉 ዕለተ ዮሐንስንም ከዚኽ ይናገሩታል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዕለተ ዮሐንስ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ፤ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት፤ ወክልዔተ ዕለተ ጠቢባን ወትገድፎ በበሱባዔ ወዘተርፈከ እምሱባዔ ኢተአትት አሐደ ዓመተ፤ ወእምዝ ይከውን ዕለተ ዮሐንስ እንዲል ዕለተ ዮሐንስን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ፤ 5ኛ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ 7ኛ 2ት ዕለተ ጠቢባንን ጨምሮ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን ሳያትቱ አንድ ቢተርፍ ዕለተ ዮሐንስ እሑድ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡

👉 ለጥንተ ዮን የወጣ 8 እና 2 ዕለተ ጠቢባን= 10 ይተርፋል፤ በሱባኤ ቢገድፉ 3 ይተርፋል። 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ዮሐንስም ማለት አሻቅቦ ወደ ላይ እስከ ፍጥረተ ዓለም፤ አቈልቊሎ ወደ ታች እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ቢቈጥሩ ለወንጌላዊዉ ዮሐንስ የሚደርሰው ቀን ማለት ነው፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘኀለፈ ይመርሐከ ዝንቱ እስከ ፍጥረተ ዓለም ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘይመጽእ ያበጽሐከ ዝንቱ እስከ ምጽአተ ክርስቶስ እንዲል፤ አንድም ሠርቀ ቲቶን ዕለተ ዮሐንስ ይለዋል፤ ቲቶ የተባለው መስከረም ነው፤ የመጥምቁ ዮሐንስ በዓል የሚውልበት ቀን ማለት ነው፤ ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ እንዲል፡፡

👉 ዕለተ በዓል ዘኀለፈ ዕለተ በዓል ዘይመጽእ የእሑድ አሚሩ ሰንበተ ክርስቲያንን ለማወቅ በዘመኑ የወጣውን ጥንተ ዮን፤ ሠርቀ መዓልት፤ 2 ዕለተ ጠቢባን በየወሩ የሚገኘውን አጽፈ ወርኅ እሊኽን 4ቱን አንድ አድርጎ ቈጥሮ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ እሑድ አሚሩ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ ሰኑዩ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ሠሉሱ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ ረቡዑ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ ኀሙሱ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ሰዱሱ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት ሰቡዑ፤ 8 ቢተርፍ በሱባዔ ገድፎ እሑድ አሚሩ የሚያሰኘው ይኽ ነው፡፡

👉 አጽፈ ወርኅም ማለት የወርኁ ከወርኅ የሚደረብ ማለት ነው፤ ይኽስ ከምን ይገኛል ቢሉ? ወሩን በሱባዔ ቢገድፉ 4 ሱባዔ ኾኖ 2 ይተርፋል፤ የወርኁ 2 የዓመቱ 24፤ እንዲኽ ግን ስለኾነ ለመስከረም አጽፈ ወርኅ የለውም በጥንተ ዮን፤ በሠርቀ መዐልት በኹለት ዕለተ ጠቢባን ይቈጠራል፤ በእሊኽ በ3ቱ ይቈጠራል፤ ጥንተ ዮን 7፤ ሠርቀ መዐልት 1 = 8፤ ኹለት ዕለተ ጠቢባን 2፤ 10 ይኾናል፤ በሱባኤ ቢገድፉ 3 ይተርፋል። 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ሠሉሱ ያለው ይኽ ነው።

👉 ዕለተ ጠቢባንም ማለት ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም የፈጠሩበት፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን የሚያመሰግኑበት ቀን ማለት ነው፤ (ዬ) ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም ከእሑድ እስከ ዐርብ ፈጥረዋል፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን ዘወትር ያመሰግናሉ ብሎ የቊጥር መጽሐፍን የተማሩ መምህራን ዕለተ ሰንበትን፤ 6ቱ ዕለታትን፤ ያለፉትን የሚመጡትን በዓላት የሚያውቁባቸው የሚያሳውቁባቸው ማለት ነው፤ ዕለተ ጠቢባንም የተባሉ እሑድና ሰኞ ናቸው፤ ከቀመር ገብተው አልተቈጠሩም፡፡

👉 ዕለተ ምርያ አዕዋዲትንም ለማወቅ የፀሓይ ዐውደ ዓመት 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ነው፤ ይኽነን በሱባዔ ቢገድፉት 52 ሱባዔ ኾኖ 1 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይተርፋል፤ ይኽቺውም አንድ ዕለት የተባለችው ዐምስተኛዪቱ ጳጒሜን ናት፤ ዕለተ ምርያ አዕዋዲት ይላታል፤ ዕለተ ምርያ ማለት ዕለተ መድኀኒት ማለት ነው፤ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን የምታሳውቅ ማለት ነው፤ ርሷ በዋለች ልደት ይውላልና፤ አዕዋዲትም አላት ዘመኑን የምታዘዋውር የምታለዋውጥ ማለት ነው፤ እሑድ የዋለውን ሰኞ፤ ሰኞ የዋለውን ማግሰኞ እንዲውል የምታደርግ ርሷ ናትና፡፡

👉 መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ኬክሮስ 15፤ የ2 ዓመቱ 30፤ የ4 ዓመቱ 60 ኬክሮስ ነው፤ 60ው ኬክሮስ 1 ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም በሉቃስ መጨረሻ ዮሐንስን ተጠግታ የምትውል ስድስተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ መጠነ ራብዒት፣ ሠግረ ዮሐንስ ይላታል፤ መጠነ ራብዒት አላት ርሷ በዕለት ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና፤ ሠግረ ዮሐንስም አላት ዮሐንስ ተራምዶ የሚውልባት ስለኾነ፡፡

👉 ዕሪና መዓልትና ዕሪና ሌሊትንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ካልዒት 6፤ የ5ቱ ዓመት 30፤ የ10ሩ ዓመት 60 ይኾናል፤ 60ው ካልዒት 1 ኬክሮስ ይኾናል፤ የ100ው ዓመት 10 ኬክሮስ፤ የ600 ዓመት 60 ኬክሮስ፤ 60ው ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም ሰባተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ ዓለም በተፈጠረ በ600 ዘመን ዕሪና መዓልት ዕሪና ሌሊት ኾኗል፤ ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 12 ዕሪና መዓልት 12 ዕሪና ሌሊት ኾኖ 13ኛው ከተዠመረ 316 ኾኖ በዘመነ ማቴዎስ ይኸውም ሊመላ 284 ይቀራል፡፡

(ከዚኽ በኋላ እንዲኽ ብሎ ባሕረ ሐሳብ አውጪው እንዲኽ ብሎ አሥርቆት ያውጣ፡፡)
በዘንዜከር ሐሳባተ ሕጉ ወትእዛዙ ለእግዚእነ ወአምላክነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ማቴዎስ ዜናዊ፤ ወንጌላዊ አለው ዮሐንስን ባለዘመን ነውና፤ ዜናዊ አለው ማቴዎስን የሚመጣ ነውና ወረኛ ንጉሥ እንዲሉ፡፡
👉 በሰብዐ ወኀምስቱ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ዓለም፡፡ በኀምሳ ወኀምስቱ ምዕት ዓመተ ዓለም፤ በዕሥራ ምዕት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፤ ሠረቀ ለነ ወርኀ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኀ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አሜን።

👉 አበቅቴ 20፤ ሠርቀ መዓልት 1፤ ሕጸጽ 1= 22፤ ዕሥራ ወሰኑዩ ሠርቀ ሌሊት፤ ዕሥራ ወሰዱሱ ሠርቀ ወርኅ፤ አሚሩ ሠርቀ መዓልት፤ ሰቡዑ ሠርቀ ዕለት፤ ዮም በዛቲ ዕለት ዘአቅረብነ ለከ አምኀ ስብሐት ያዐርጉ ለነ መላእክት ተወከፍ ለነ እግዚአ ስብሐት፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡            

አዘጋጅ፡- መጋቤ ሐዲስ ዶከተር ሮዳስ ታደሰ

የአቡነ ሀብተ ማርያም ጽንሰት፦

አቡነ ሀብተ ማርያም

የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች። ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትዕግሥትና በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን። እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ “ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል ፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና”፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል” እንዳለ። ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል” የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣማዎች፣ ከጦጣዎችና ከዝንጆሮዎች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር። በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስላየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ። መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። “አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ” አላት። “ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን?። “ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም” አለችው። “ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር” አለችው።

ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ “በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ” ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም “ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ” አለችው። ጌታ “በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም” እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም” አለችው።


ያም ባሕታዊ “ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል”።


ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ “የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ” አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለንተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሆኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ …ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው።

ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።