ግንቦት ፩ (ልደታ ለማርያም)


እንኳን አምላክን ለወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ለጸናች ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ለልደቷ መታሰቢያ ዓመታዊ የንግሥ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።


የዕለቱ አንገርጋሪ፦ “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም እም ሐና ወኢያቄም ከመ ትቤዙ ነቢያት ወጻድቃነ አማን ተወልደት እመ ብርሃን”። ትርጉም፦ በእመቤታችን ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ ይኸውም ከሐና ከኢያቄም መወለዷ ነው ነቢያትና ጻድቃንን በልጇ ታድናቸው ዘንድ በእውነት የብርሃን እናት ተወለደች። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።


አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት፦ እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ቅዱስ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ቅድስት ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና። እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኀዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።


ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው። በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለቅድስት ሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት፡፡ ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርም አመሰገኑት።ኢያቄም ለሚስቱ ሐና እንዲህ አላት “ሰማያት ሲከፈቱ አየሁ፤ ነጭ ወፍ መጣ በራሴ ላይም አረፈ” እንደዚህም ሁሉ ሐናም “ርግብ በራሴ ላይ ስትቀመጥብኝ በማሕፀኔም ስታድር አየሁ ገባች” አለችው።


ከዕለታት በአንድ ቀን ሐና እና ኢያቄም ወጥተው ወደ ተክል ቦታ ገቡ፡፡ ቁመውም ሲጸልዩ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ልጅ ስለሌላቸው ፈጽመው አዘኑ፡፡ከሐዘናቸውም ብዛት የተነሳ አንቀላፍቷቸው ተኙ፡፡ ሐናም ተኝታ ሳለች በባሏ በኢያቄም እጅ በትር እንደተያዘች ያችም በትር አብባ አፍርታ አየች፡፡ሁለተኛም ኢያቄም በሐና እጅ ከፍሬ ሁሉ የሚመስለው የሌለ የሚጣፍጥ መልካም ፍሬ ተይዞ አየ፡፡ከእንቅልፋቸው በነቁ ጊዜ ደስ አላቸው በመኝታቸው ስላዩት ነገር እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡


ከዚህም በኋላ ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን ብለው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ከዚህም በኋላ የከበረች ሕፃን ነሐሴ ሰባት ቀን ተፀነሰች፡፡የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ በቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ተሳለች።ከስድስት ወር በኋላም የብፅዕት ሐና መፅነስ ታወቀ። ዘመዶቿም ሰሙ ወደ እርሷ መጥተውም “የምንሰማው ይህ ነገር አውነት ነውን? ዘመንሽ ካለፈ በኋላ በአንቺ ላይ የተደረገው ነገር ምንድን ነው?” አሏት። ከሐና ዘመዶች ወገን የአርሳባን ልጅ የምትሆን አንዲት ዐይኗ ማየት የተሳናት አንዲት ሴት ነበረች። “የሰማሁት እውነት ነውን?” ብላ የሐናን ማኅፀን ዳሰሰች። “እህቴ ሆይ ሽማግሌ ስትሆኚ እንዴት ፀነስሽ” አለቻት። ዳግመኛም ማየት የተሳነው ዐይኗን ዳሰሰችው ያን ጊዜም ዐይኗ ተከፈተላት ብርሃንንም አየች። “ብፅዕት ሐና ሆይ ለአንቺ ብፅዓን ይገባሻል ፅንስሽ በማኅፀንሽ እያለ ገና ሳይወለድ በሽተኞችን የፈወሰ በግልጽ ከታየ ከማሕፀንሽ ከወጣማ ምን ያህል ይፈውስ ይሆን?”አሉ፡፡እንደዚሁም ሁሉ ብዙ በሽተኞች መጥተው እየዳሰሱ ከበሽታቸው ይፈወሱ ይድኑም ነበር። ይህ ነገርም በእስራኤል ሽማግሎዎች ሁሉ ዘንድ ዕፁብ ድንቅ ሆነ።


ቅድስት ሐናም የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ በግንቦት አንድ ቀን ከፀሓይ ይልቅ ፈጽማ የምታበራ ሴት ልጅ በሊባኖስ ተራራ ላይ ወለደች፤ የመልኳም ደም ግባት ከመዓር ከሦከር ይልቅ ደስ ያሰኛል፤ የመዓዛዋም ሽታ ከሽቱ ሁሉ ይበልጣል። ዘመዶቿና ጐረቤቶቿም በሰሙ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አላቸውና ተሰብስበው ወደስዋ መጡ ወደሷም መጥተው ልጅዋን ባዩ ጊዜ ፈጽመው አደነቁ እርስ በርሳቸውም “እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም” ተባባሉ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ ላይ አድሯልና የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና። ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ ያችንም ብላቴና ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው። በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናትና ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።


የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን። በዘአዝፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት”። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት ወንጌል ማቴ 1፥1-18።
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን። ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ”። መዝ 86፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 4፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 8፥13፣ የሐዋ ሥራ 7፥44-51 ወይም የሐዋ ሥራ 1፥12-15 የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የልደታ ለማርያም በዓል፡፡ ለሁላችንም ይሁንልን።
ምንጭ፦ ተአምረ ማርያም፣ ድርሳነ ቅድስት ሐና ወኢያቄምና የግንቦት 1 ስንክሳር ።

ሐዋርያው ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ፦

የቅዱስ ማርቆስ ወላጆች ስም የአባቱ ስም ቅዱስ አርሰጡጳውሎስ ሲሆን የእናቱ ስም ቅድስት ማርያም ይባላል፡፡ አባቱ ባለጸጋና ያላገባ ነበር የአባቱ ስም ስምዖን ይባል ነበር፡፡ ስምዖንም አርስጡጳውሎስን እንዲያገባ ይገፋፋው ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በቤቷ እንግዶችን የምትቀበልና የምታስተናግድ ማርያም የተባለችውን የወንጌላዊ የቅዱስ ማርቆስ እናት አገኘ ፡፡ እሱም እሷም ሳያስቡት ባዩት ሕልምና በመፈክረ ሕልም (በሕልም ፈቺዎች) በተነገራቸው መሠረት ተገናኝተው የትዳር ሕይወትን መሠረቱ፡፡


አርስጡጳውሎስ ከከበረውና በባለጸግነቱ ከታወቀው ከአባቱ ካገኘው ሀብት ለነዳያን የሚመጸውት፣ ዐሥራት በኩራት የሚያወጣና ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር የሚጸልይ ደግ አባት ነበር፡፡ እሱም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ዘመድ የአክስት ልጅ እንደሆነና ቅዱስ ጳውሎስም በመልአክቱ የጠቀሰው እሱን እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ “አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል” ቈላስይስ 4፥10 ነገር ግን አንዳንድ የግሪክ፣ የላቲን፣ የግእዝና የኮኘት ትርጉሞች “የበርናባስ የወንድሙ ልጅ” የሚለውን ሐረግ አይጠቅሱም ይህም ምንአልባት አንዳንድ የግሪክ ቃላት ከአንድ በላይ ትርጉም ስላላቸው ይሆናል፡፡


የቅዱስ ማርቆስ እናት ማርያም ተብለው ከተጠሩት ብዙ ቅዱሳት አንስት መካከል አንዷ ናት፡፡ ቤቷ በኢየሩሳሌም እንደነበረና ምዕመናንም በቤቷ በጸሎት ይሰበሰቡ እንደነበር በሐዋ 12-12-17 በሰፊው ተገልጾአል፡፡ ይህም በጥንት ወይም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ካሉት መንፈሳውያኑ ሴቶች (ቅዱሳት አንስት) ከፈተኛ ቦታ ያላት እንደነበር ያመለክታል። በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን በአንድነት በክርስቶስ ስም ይሰባሰቡ ስለነበር ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኙትም በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ “በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ”፡፡ ሐዋ 11-26


የቅዱስ ማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ነበር፡፡ በማርቆስ እናት በማርያም ቤት በጽርሐ ጽዮን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጸላቸውና መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ እንዲህ ተጽፏል “አመ ሣልስት ዕለት ተንሥአ እሙታን ወቦአ ኀበ ሀለው አርዳኢሁ ጉቡአን ወአስተርእዮሙ በጽርሐ ጽዮን … ወበ ፶ ዕለት ፈነወሎሙ መንፈሰ ቅዱስ ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኩሉ በሐውርት … በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የተሰበሰቡ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ገባ በጽርሐ ጽዮንም ታያቸው …በ50ኛው ቀንም
በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው በአገሩ ቋንቋ ሁሉ ተናገሩ”


በኢየሩሳሌም ውስጥ የማርያም ቤት የሐዋርያት መገናኛና መሰባሰቢያ ነበር፡፡ ስለዚህም የማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኀብረት መለያ ሆኖ ይታወቃል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ የተወለደው በአባቱ ወገን ከነገደ ይሁዳ ሲሆን የተወለደበት ቦታ ከአምስቱ የምዕራብ ከተሞች አንዷ በሆነችው በሊቢያ በሲርኔ ይኸውም አብራይሮሎስ በተባለች ትንሽ መንደር ተወለደ፡፡ ትውልዱ ዕብራዊ ቤተሰቦቹም ይኖሩበት የነበረው በሰሜን አፍሪካ በጥንታዊቱ ፔንዲፓሊስ ሲሪኒካ (ቀሪና) በተባለችው በዛሬው ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ደማቅ ከተማ ስለነበር ቅዱስ ማርቆስ አፍሪካዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው የሚሉ አሉ፡፡( ሉሌ መላኩ ቤተክርስቲያንን እወቅ)


የቅዱስ ማርቆስ የስሙ ትርጓሜ ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው ንብ ከሁሉ እንዲቀስም አስቀድሞ ከክርስቶስ በኋላም ከሐዋርያት ተምሮአልና፡፡ አንድም አንበሳ ማለት ነው አንበሳ ለላሕም ጌታው እንደሆነ እንዲሰብረው እርሱም አምልኮተ ላሕምን ከግብጽ አጥፍቷልና፡፡ አንድም ካህን ልዑክ ማለት ነው፡፡ ብሥራተ ማሪ ማርቆስ ይላል የተደራረበ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ካህን ማለት ነው፡፡


የቅዱስ ማርቆስ ሁለተኛ ስሙ ዮሐንስ ይባላል። “ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለ ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ” ሐዋ12፥12


የቅዱስ ማርቆስ ተክለ ቁመናና መልክ
እንዲሁም አለባበሱን እንዲህ በማለት ተጠቅሷል፡፡ “የግብጽና የኢትዮጵያ ኮከብ ብፁዕና ቅዱስ ማርቆስ መልኩ ቀይ ቅንድቦቹም ከበድ ያሉ ዓይኖቹም እንደሰማያዊ ኀብር የጠሩ ቁመቱ ረጅም ከአንገቱም ስር ስርጉድ የሆነ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ራሰ በራህ የሆነ ቀሚስ (ልባልባውም) በወገቡ የሆነ የግብጽና የኢትዮጵያ አባት የቅዱስ ማርቆስ ምልክቱ ይኸ ነበር፡፡


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዊ በሚሰብክበት ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ ወጣት ነበር፡፡ ልቦናው የቀና እንደሆነም አውቆ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የመጀመሪያ አድርጐ መረጠው ከዚህ በኋላ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኖ ጌታ ወንጌልን ሲያስተምር፤ ተአምራት ሲያደርግ ያስተውል ነበር ፡፡ በምሴተ ሐሙስ በአይሁድ ሲያዝና መከራን ሲቀበል ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም መንገድ ላይ ሆኖ በርቀት ድርጊቱን ይከታተል ነበር፡፡ በወንጌሉም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ስለ አርሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ “ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጐበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ”፡፡ ማር14-51-52
ቅዱስ ማርቆስ በቤቱ መጻፊያ ይዞ የጌታን ተአምራት ይጽፍ ነበር፡፡ የግሞ ሊናሮስ የሚባል አገልጋዩን ጌታን እንዲከተልና የሚያደርገውንም ተአምራት እንዲጽፍ ያደርግ ነበር ፡፡

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዓለ ፋሲካን ሲያከብር ተከተሉት” የተባለውም ቅዱስ ማርቆስን እንደሆነ እንዲህ ተጽፍል፤ “ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እነዲህም አላቸው ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውሃ የተሸከመ ሰውም ያገኛችኋል ተከተሉት የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ፣ ከደቀመዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት፡፡ እርሱም በደርብ ላይ ያለውና የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፣ በዚህም አሰናዱልን፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ ፋሲካም አሰናዱ” ማር 14፥13-15፤ ሉቃ 22፥10-12።


ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም የእናቱ የማርያም ቤት የደቀ መዛሙርቱ መገናኛና መሰባሰቢያ ስለነበር ደቀመዛሙርቱን የበለጠ እንዲያውቃቸውና እንዲቀርባቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ በተለይም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ባለው የጠበቀ ዝምድናና ቀረቤታ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት ልጅ በመሆንና ለአገለግሎቱም ፍጹም መንፈሳዊና እውነተኛ የክርስቶስ ምስክር ለመሆን በቅቷል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በልጅነቱ በኢየሩሳሌም ለመኖር በመታደሉ በዚያም ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት የማግኘት ዕድል ገጥሞት ነበርና የዕብራይስጥ፣ የላቲንና የግሪክ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌልን መስበክ የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ያስተምር ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት አንደተገለጸው ቅዱስ ማርቆስ ከቅድስ ጳውሎስና ከቅድስ በርናባስ ጋር ይሰበክ ነበር፡፡ ከዚያም በፊት ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አስተምሮአል፡፡


ቅዱስ ማርቆስ ንጹሕና ድንግል መሆኑን መልካምነቱንና ትምህርቱን ተመልክቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ለግብጽና ለአካባቢዋ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ ሾመው፡፡ በግብጽ አገሮች በሎኒያ፣ በመርቅያ፣ በጣውንቄ፣ በበርቃ ለመጀመሪያ አስተማረ እርሱ ነው፡፡ ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ አዳኝ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንንም አስተማራቸው፡፡ ሁሉም የዚያች አገር ሰዎች ልቡናቸው የደነደነ ነበሩ በርኵሰት ሁሉ የተሞሉ አማልክትንም ያመልኩ ነበር፡፡ ሰይጣንን በማምለክም ይኖሩ ነበር፡፡ በየቦታው በየመንገዱም ሁሉ ምኩራቦችን የአማልክትን ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ መድኃኒትን፣ ዝሙትንም ያደርጉ ሕጻናትን ይገድሉ በደማቸው መድኃኒትን ያደርጉ ነበር፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሐዋርያት በሄደ ጊዜ አስቀድሞ ብርቃ ደረሰ፡፡ ዘመዶቹ ከእነርሱ ወገን ናቸውና፡፡ እግዚአብሔርን ቃልም አስተማራቸው በመካከላቸው ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ በሽተኞችን ፈወሳቸው ለምጻሞችንም አነጻቸው፤ በእርሱ ላይ በአደረው ጸጋም አጋንንትን አስወጣ፤ ብዙዎችም በትምህርቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ አምላኮቻቸውንም (ጣዖቶቻቸውንም) ሰባበሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጠመቃቸው፡፡


በዚያ ቦታም ወደ እስክንድርያ ይሄድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተገለጠለት፡፡ በዚያም መልካም ተዘራባት ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ወንጌላዊው ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ለጦርነት እንደተዘጋጀ ጎልማሳ ሆነ ወንድሞቹንም ሰላም አላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ቦታ ቅዱስ ወንጌልን አስተምር ዘንድ ወደ እስክንድርያ እንድሄድ አዝዞኛል” አላቸው፡፡ እነርሱም ሸኙት በመርከብም ተሳፍሮ ወደ እስክንድርያ ሄደ በደረሰ ጊዜም ወደ ከተማው በር ገባ የጫማው ማሠሪያም ተቆረጠ “በቅንነትም መንገድ ፈጠነች” አለ በዚያም ከከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበር፡፡ ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዩናኒም ቋንቋ “ኢታስታያስ” አለ ትርጓሜው አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን” አለው “እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም” አለ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በጣቶቹ ላይ መራቅ ጨመረና አፈር ወሰደ ያን ጫማ ሰፊ ቀባው “በሕያው አግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ስም አጅህ ትፈወስ” አለው፡፡ ስለዚህም ተፈወሰች ጫማ ሰፊውም በሥልጣኑ በቃሉ ያደረገውን ድንቅ ተአምር በተመለከተ ጊዜ “የቸሩ አምላክ አገልጋይ ሆይ እለምንሃለሁ ዛሬ ውጣና በቤቴ ዕረፍ በአንድነትም እንመገብ መልካም ነገርን አድርገህልኛልና” አለው፡፡ ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ተደሰተ፡፡

“እግዚአብሔር ሰማያዊት የምትሆን ሕይወት ኀብስትን ይስጥህም” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ አስገባው፡፡ ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ ገባለት። “የእግዚአብሔር በረከት በዚህ ቤት ይኑር” አለ፡፡ ወንድሞች በአንድነት ጸለዩ ከጸሎት በኋላም ተቀመጡና ደስ እያላቸው ተመገቡ፡፡ ጫማ ሰፊውም ቅዱስ ማርቆስን “አባት ሆይ እለምንሃለሁ ይህንን የምትለው እንዴት ነው፤ ይህ ስምስ ምንድን ነው ይህ እንደዚህ የሚቻለው ነው” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ ላየው እሻለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ አሳይሃለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ ነው እያለ የወንጌሉን መጀመሪያ አስተማረው፡፡ በትንቢት ስለ እርሱ የተናገሩትንም ከመጻሕፍት ተናገረ፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ የምትለውን ይህን መጽሐፍ እለምንሃለሁ ከረጅም ዘመን ጀምሮ የግብጻውያን ልጆች እንደማይማሩበት አልሰማህምን” አለው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔርን ነገር ይነግረው ዘንድ አስቀደመ “የዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ናት” አለው ጫማ ሰፊውም የቅዱስን ነገር በሰማ ጊዜ በእግዚአብሔር አመነ ለእርሱም አመለከተው ከእርሱም ኃይላትን ተአምራትን አየ እርሱ ቤተሰቡ፣ ከአገሩ ሰዎችም ብዙዎቹ ተጠመቁ፡፡ የጫማ ሰፊው ስምም አንያኖስ ይባላል፡፡ ያን ጊዜም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምዕመናን በዙ፡፡ የአገሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜም “ይህ የገሊላ ሰው ከዚህ አገር ደርሷል፤ የአማልክትን እጅ መንሻ ለውጧል፤ እንዳይመለኩ ከልክሏል” አሉ ሊገሉትም ፈለጉት ይጥሉት ዘንድም በእርሱ ላይ ፍለጋን አበዙ ብፁዕ ማርቆስ ይህን በተረዳ ጊዜ አስተማራቸውና አንኖስንም ኤጲስ ቆጾስነት ሾመላቸው ሦስት ካህናትንም ሾመላቸው ስማቸውም ወልዮስ፣ መሪደስና በሪሞስ ይባላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ሰባት ዲያቆናትን አንድ ላይ አሥራ አንድ ሰዎችን ሾመላቸው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ብርቃ ወጣ ለዓመታትም በእርሷ ተቀመጠ፡፡ በሁሉም አገራት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትን ሾሞላቸው ወደ እስክንድርያም ተመለሰ፡፡ በእግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ጸጋና ማመን በዛባት የላም ቦታ በሚባለው በባሕሩ ዳር ካለው ቦታም ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከዚያ ቦታ ከዓለቱ ሥርም ታላቅ ድንጋይ ቁራጭ ነበር፡፡ ጻድቁም ስለ ምዕመናን መልካም ሃይማኖት እግዚአብሔርን አመሰገነ ብዙ ዘመን በቆየ ጊዜም ክርስቲያኖች በዙ አማልክትንም ተዘባበቱባቸው፤ አረማውያንንም ናቋቸው፡፡

አረማውያንም ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ወደ አገራቸው እንደ ደረሰ ተረዱ፡፡ ከሰሙት ተአምራት ብዛት የተነሳ ልቡናቸው በቁጣ ተሞላ እርሱ ሕመምተኞችን ይፈውስ፣ ለምጻሞችንም ያነጻ፣ ደንቆሮዎችንም እንዲሰሙ፣ እውራንንም እንዲያዩ ያደርጋል መልካም ተስፋንም ያስተምራቸው ነበር ይይዙት ዘንድም ፈለጉት፤ በየቤታቸውም ጥርሳቸውን ያፋጩ ነበር፤ በአማልክቱ ምኵራብም “እኛ ለዚህ ጠንቋይ ተሸነፍን” እያሉ ጮኹ፡፡ ምዕመናን የሚያከብሩት ዕለት ሰንበት የተባረከው የፋሲካ በዓልም በሰንበት ቀን ሆነ፤ ይህም ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን ነው፡፡


በዚያች ዕለትም በእነርሱ ዘንድ የሰራቢስ የልደቱ ቀን ነበር፡፡ ያማረች ዕለትን አገኙ ሰላዮችን ላኩና ያዙት፡፡ እርሱን የቅዳሴ ጸሎት ሳይፈጽምም በሰንሰለት አሠሩት በላሞች ቦታ እንጐትተው እያሉም እንደ አውራ ፍየል በየመንገዱ ጐተቱት፡፡ ቅዱስ ማርቆስም በጐተቱት ጊዜ አግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በተቀደሰው ስምህ መከራን እንድቀበለ አዘጋጅተኸኛልና አመሰግንሃለሁ” አለ፡፡ ሥጋውም በየመሬቱ ተቆራረጠ ደሙም በየዐለቱ ፈሰሰ፡፡


ሌሊት ሲሆንም ይገድሉት ዘንድ እስከሚሰበሰቡ ድረስ ወደ እስር ቤት አስገቡት፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲሆንም በሮች ተዘግተው ጠባቂዎችም ተኝተው ሳሉ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክም “የግብጽን አገራት ሁሉ የምታረጋጋ የእግዚአብሔር አገልጋይ ማርቆስ ሆይ ስምህ በሰማይ ባለ የሕይወት መጽሐፍ ተጽፏል ከሐዋርያት ቁጥርም ተቆጥሮአል፤ መታሰቢያህም አይረሳም፤ በምድርም ስፍር ቁጥር የሌላትን ሥልጣን፣ ጸጋ ኃይል እነሆ ሰጥቶሃልና፤ ነፍስህ በሰማይ ይሆናል ሥጋህም በመሬት አይጠፋም” አለው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ይህን ምሳሌ በተመለከተ ጊዜ እጆቹን ወደ ሰማይ አነሣ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከፊትህ አልጣልኸኝም፣ ከቅዱሳን ማኀበርም ደምረኸኛልና አመሰግንሃለሁ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ ነፍሴን በሰማይ ተቀበላት፤ ከፊትህም አትተወኝ” አለ፡፡ ይህን በተናገረ ጊዜ ጌታችን አዳኝ ከሆነው ከሕማሙ በፊት በመቃብርም ከመጨመሩ አስቀድሞ በሐዋርያት መካከል እንደነበረ ሆኖ ታየው፡፡ “የመረጥሁህ ማርቆስ ሆየ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሁን፤ በወንጌል አስተማርሁህ፤ እነሆ መከራን ከመቀበሌ አስቀድሞ ከጓደኞችህ ከሐዋርያት ጋር አንደሆንሁት በአርአያ ተገለጥኩልህ፤ ከእነርሱ ምንም ጉድለት እንዳይኖርብህ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከጸጋህ ታላቅነት የተነሣ አመሰግንሃለሁ፤ በሥጋህ አንደነበርህ ሆነህ አንዳይህ የተገባኝ አድርገኸኛልና” አለው “ስለተቀደሰው ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ ትዕግሥትን አድለኸኛልና” ጌታችንም ሰላምን ሰጠውና በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማይ አረገ ፡፡ ሲነጋም የአገሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከእስር ቤትም አወጡት በሰንሰለትም አሰሩት፤ ዳግመኛም በላሞች ቦታ እንደፍየል እንጐትተው እያሉ በከተማው ጐተቱት፡፡


ብፁዕ ማርቆስም ምስጋናን አቀረበ በሰማይ ተገለጠ፡፡ በየአገሩ ከጎተቱት በኋላም ደሙ በየመንገዱና በየአደባባይዋ ሞላ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን በእጅህ ሰጠሁ” አለ፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላም ሚያዝያ 30 ቀን ዐረፈ፡፡ ሁሉም አረማውያን ቅዱስ ማርቆስ አንዳረፈ በተመለከቱ ጊዜም ሥጋውን በእሳት ያቃጥሉት ዘንድ አውበካልዮን በምትባል ቦታ ጽኑ እሳትን አነደዱ፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድም ጨለማና ቀዝቃዛ ነፋስ ሆነ፤ ፀሐይም ብርሃኑን ሰወረ፡፡ በዚች ዕለትም እስከ ምሽት ድረስ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ዝናምና ብርድም ሆነ፤ ከአገሩ ሰዎች ከሽማግሌዎች ብዙዎች ወደቁ ከእነርሱም ብዙዎቹ ሞቱ ያን ጊዜ ፈሩ ሂደወም ከአገሩ ሰዎች የቅዱሱን ሥጋ አኖሩት፤ የተዘባበቱበትም አሉ “ ታላቁ አምላክ ሆይ የዚህን ሰው ነፍስ ተቀበላት በዚች ዕለት የልደቱ ዕለት ናትና” አሉ፡፡ ምዕመናን ወንዶች ደረሱና የቅዱሱን ሥጋ ከእሳቱ ወሰዱት ጸሎት ወደሚጸለይበት ቦተም አደረሱት በእርሱ ላይም ተሳሉ፣ ምስጋናንም አቀረቡ እንደ ሥርዓታቸውም እንደ አገሩ ሰዎች ገነዙት በቆፈሩለት መቃብርም ቀበሩት፡፡ መታሰቢያውንም በደስታ፣ በምሥጋና አብዝተው አደረጉ፣ አበዙ በአገሩ መሠረታዊ ቦታም አስቀመጡት፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ በግብጽ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰ የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ ዕረፍቱ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በ30 ሠላሳኛው ቀን በታላቋ አገር በእስክንድርያ ሆነ ፡፡ ከሐዋርያውና ከወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡ በጸሎቱ ይማረን!፡


፡ ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያት ፤ ስንክሳር ፤ ክብረ ቅዱስ ማርቆስ ከሚለው መጽሐፍ።


“ሰላም ለማርቆስ ለማርያም ዕጓላ። ዘሰሐብዎ በአህባል ውስተ ዐፀደ ላሕም ከመ ዳቤላ። አመ አውዕዮቶ ፈቃዱ ለእሳት በነበልባላ። ዝናም ወአስሐትያ አጥፍኡ ማዕበላ። መብረቅኒ ለሥጋሁ ከለላ”። ትርጉም፦ በላም በረት ውስጥ እንደ ወይፈን በገመድ የሳቡት ለኾነ ለማርያም ልጅ ለቅዱስ ማርቆስ ሰላምታ ይገባል፤ ርሱን በእሳቲቱ ላንቃ (ወላፈን) ለማቃጠል በወደዱ ጊዜ ውርጭ እና ዝናብ ማዕበሏን አጠፋ፤ መብረቅም ሥጋውን ጋረዳት። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 30።

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር ማነው?


የእዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ኅርማኖስ ነው እርሱም ለዲዮቅልጥያኖስ የአማካሪዎቹና የሠራዊቱ አለቃ ነው ስለ አምልኮ ጣዖት ሥራ ምክሩና ንግግሩ ሁሉ ከእርሱ ጋራ ነበር የእናቱም ስም ማርታ ይባላል በክርስትናዋ የጸናች ብፅዕት ናት።


ቅዱስ ፊቅጦርም በአደገ ጊዜ አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበው ንጉሡም በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕርግ አድርጎ ሾመው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ። እርሱም የዚህን ዓለም ክብር ናቀ ሥጋ አይባላም ወይን አይጠጣም ዘወትርም ይጾማል ጸሎትንም ባለማቋረጥ በቀንና በሌሊት ይጸልያል። በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጐበኛቸዋል ለድኆችና ለምስኪኖችም ይመጸውታል።


የቅዱስ ቆዝሞስና ድምያኖስ እናት ቅድስት ቴዎዳዳን በገደሉዋት ጊዜ ንጉሡም ስለ መፍራት ሊቀብራት ማንም አልደፈረም። ይህ ቅዱስ ፊቅጦርም መጥቶ ሥጋዋን ወሰደ ከንጉሥ ስለሚመጣው ቅጣት ሳይፈራ ቀበራት። ጣዖት ስለ ማምለኩ አባቱን ዘወትር የሚገሥጸውና ብዙ ጊዜም የሚመክረው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም። ተከሶም ወደ ንጉሥ በአቀረቡት ጊዜ “አማልክት ያልሆኑ ርኲሳን ጣዖታትን ለሚያመልክ ሰነፍ ዝንጉ ልብ የለሽ ለሆነ ንጉሥ አላገለግልም። ከዛሬ ጀምሮ ለሕያው ንጉሥ ክርስቶስ እገዛለሁ የሰጠኸኝንም ገንዘብህን ንሣ” ብሎ በፊቱ ትጥቁን ፈትቶ ጣለለት።


አባቱ ኅርማኖስም ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና በኄርሜኔዎስ መኰንን ዘንድ በዚያ ፊቅጦር እንዲቀጣ ንጉሡን መከረው። በዚያን ጊዜም ከአደባባይ አወጡት እናቱም በብዙ ልቅሶ ልትሸኘው መጣች። እርሱም ሲመግባቸው ስለ ነበረ የታሠሩ ምዕመናን ስለ ድኆችና ምስኪኖች ስለ ሙት ልጆችና ስለ ባልቴቶች የሚሹትን በመስጠት እንድትጐበኛቸው አዘዛት ከዚያም አፉን ለጉመው ወሰዱት።


በእስክንድርያ አገር ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ሰማያት አውጥቶ ስለ ክብራቸው ለመናገር የሚያስጨንቁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳይቶ ወደ መኖሪያው መለሰው። መኰንኑም በእሳት በአፈሉት በዝፍት፣ በዲን ደግሞ አሠቃየው ከዚያም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ደግመው ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና ከሥቃዩ ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ከቊስሉ ይፈውሰው ነበር።


ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱን ቆረጡ። በእሳት ያጋሉዋቸውን ችንካሮች በጐኖቹ ውስጥ ጨመሩ እግዚአብሔር ግን አጽንቶ አስታግሦ ያለ ጉዳት በደኅና ያነሣዋል። ከዚህም በኋላ በዚያ በረኃብ እንዲሞት ከዱር ባለ ግምብ ውስጥ አሠሩት። እርሱ ግን መጥረብ የሚያውቅ ስለሆነ ላይዳዎችን በመጥረብና በመሸጥ በየጥቂቱ እየተመገበ የቀረውን ለድኆች እየሰጠ ኖረ። አንድ መኰንንም መጥቶ በዚያ ግምብ አቅራቢያ አደረ ስለ ቅዱስ ፊቅጦርም እርሱ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነ የኅርማኖስ ልጅ እንደሆነ ነገሩት። መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ጅማቶቹን መዘዙ አፋን መቱት ቊልቊል ሰቀሉት በእጆቹ ላይ ከባድ ደንጊያ አንጠልጠሉ። ከዚያም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ፣ አደሮ፣ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዩ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾለት አጸናው አረጋጋው። ሥሮቹንም ሕዋሳቶቹን በቦታቸው መለሰለትና አዳነው።


አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ነበረች ቅዱስ ፊቅጦርን ሲያሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር። መላእክትም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ዐረፉ። ያቺም ብላቴና በጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም ያመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ሚያዝያ 27 ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊል ተቀበለ። ምዕመናን ሰዎችም ሥጋውን ወስደው በከበሩ ልብሶች በድርብ በፍታ ገነዙት። እናቱ ማርታም ከአንጾኪያ እስክትመጣ በንጹሕ ቦታ አኖሩት በመጣችም ጊዜ ከዚያ ወሰደችው። ውብ ቤተ ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረች ከእርሱም ታላላቅ
ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ፊቅጦር በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ27 ስንክሳር።


“ሰላም ለፊቅጦር ተአምራቲሁ ዘአርአየ። ድኅረ በሰይፍ ተወቅየ። ልብሱ ዘወርቅ አመ ተኀድገ በዝየ። ያሠርጉ ጣዖታቲሁ ሶበ ልበ ንጉሥ ሐለየ። ኀበ ህላዌሁ ተመሥጠ ሰማየ”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 27።

በጡቶቿ ደም ልጆቿን ያጠመቀችው ቅድስት ሣራ


ቅድስት ሣራና ሁለት ልጆቿ፦ ይቺም ቅድስት ከአንጾኪያ አገር ናት እርስዋም ከዲዮቅልጥያኖስ መኳንንት ለአንዱ ስሙ ስቅራጥስ ለሚባል ሚስቱ ናት እርሱም በፊት ክርስቲያን ነበረ በኋላ ንጉሡን በመፍራት ካደ እርስዋ ግን በክርስትናዋ ጸንታ ኖረች። ባልዋ ስቅራጥስም “እኔ የክርስቲያንን ሃይማኖት እወዳለሁ የንጉሡን ሥቃይ ከመፍራት በቀር ክርስቶስን በልቤ አልካድኩትም” ይላት ነበር። እንደዚህም ስትኖር ሁለት ልጆችንም ወለደች በአንጾኪያም አገር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልተቻላትም። አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋልና ጠፍተዋልምና ሰውን ወዳድ ክርስቶስን ብዙ ስለመውደዷ ልጆቿን ታስጠምቃቸው ዘንድ ታላቅ ተጋድ አደረች ወደ እስክንድርያ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልትሔድ ወዳ አሽከሮቿን አስከትላ ሁለቱን ልጆቿን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።


የክብር ባለቤት ጌታችንም የሃይማኖቷን ልዕልና ለመጪው ትውልድ ሊገልጥ ወዶ ያቺ መርከብ ለመሥጠም እስከምትደርስ በባሕር መካከል ጥልቅ ነፋስን አስነሣ። ይቺ ቅድስትም ልጆቿ ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ ፈራች ተነሥታም ጸለየች ከዚያም ምላጭ አንሥታ ጡቷን የቀኙን በጣች ከደሟም ወስዳ ፊታቸውን በመስቀል ምልክት ቀባች በደረታቸውና በጀርባቸውም ላይ እንዲሁ አደረገች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም በባሕሩ ውስጥ አጠመቀቻቸው ያን ጊዜም ታላቅ ጸጥታ ሆነ።


ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰች ጊዜ ከአገር ልጆች ጋራ ያጠምቃቸው ዘንድ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልጆቿን አቀረበች በዚያን ጊዜም ከአገር ልጆች አጠመቀ። ወደልጆቿም ደርሶ ሊአጠምቃቸው ወሰዳቸው ያን ጊዜ ውኃው ረጋ እነርሱን ትቶ ከአገር ልጆች አጠመቀ ውኃውም ተፈትቶ ወረደ ደግሞ ሊአጠምቃቸው ወደ ልጆቿ ተመለሰ አሁንም እንደቀድሞው ውኃው ረጋ እንዲሁም ሦስት ጊዜ አደረገ ውኃውም ይረጋል አደነቀ። እናታቸውን አቅርቦ ጠየቃት እርሷም የሆነውን “በባሕር መካከል ዐውሎ ነፋስ እንደተነሣባት ጡቷን በጥታ ደሟን እንደ ቀባቻቸውና በባሕር ውስጥ እንዳጠመቀቻቸው ነገረችው ስለ አደረገችውም በድፍረት በፊቱ ሰግዳ ይቅር ይላት ዘንድ ለመነችው”። አባ ጴጥሮስም ” ሴትዮ አትፍሪ ሃይማኖትሽ ፍጹም ነው አንቺ በባሕር ውስጥ በአጠመቅሻቸው ጊዜ በመለኮታዊት እጁ ያጠመቃቸው ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና አይዞሽ” አላት። ማጥመቁን በፈጸመ ጊዜ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው።


ይቺም ቅድስት ወደ አንጾኪያ ቤቷ ተመለሰች። ባሏም በአያት ጊዜ ይህን በማድረጓ ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ሒዶ ከሰሳት ያደረገችውንም ነገረው። ንጉሡም ወደርሱ ያቀርቧት ዘንድ አዘዘ ስትቀርብም ወደ “እስክንድርያ ለምን ሔድሽ ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ልታመነዝሪ ነውን” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት “ክርስቲያኖች አያመነዝሩም እንደናንተ የረከሰ ጣዖትን አያመልኩም ከእንግዲህ ደግሞ ከእኔ ቃልን አትሰማም የወደድከውን አድርግ” ሁለተኛም “በእስክንድርያ ካንቺ የሆነውን ንገሪኝ ብሎ ጠየቃት ምንም ምን አልመለሰችለትም።


ንጉሥ ከዲዮቅልጥያኖስም እጆቿን የኋሊት አሥረው ሁለቱን ልጆቿን በሆድዋ ላይ አድርገው ሦስቱንም በእሳት ያቃጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ። ፊቷንም ወደ ምሥራቅ መልሳ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ጸለየች ከዚያም ከልጆቿ ጋራ ሚያዝያ25 አቃጠሉዋት የድልና የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ለዘላለም ይማረን አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 25 ስንክሳር።


“ሰላም ለሣራ እምሥርወ ክርስቲያን ሙላዳ። ብእሲሃ ዕልው ሶበ ዐውደ ምኵናን ወሰዳ። እምሰሚዐ ቃሉ ርኵስ ሶበ ኢትሠጥወቶ ለአግሪጳዳ። አዘዘ ያውዕይዋ ለእቶነ እሳት በነዳ። አንቢሮሙ በከርሣ ፪ተ ውሉዳ”። አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 25።


የዕለቱ ምስባክ፦ “ወአምላክነሂ መስተሣህል። የዐቅብ ሕፃናት እግዚአብሔር። ተመንደብኩሂ ወአያድኃነኒ”። መዝ 114፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 10፥12-22፣ 1ኛ ዮሐ 4፥4-18፣ የሐዋ ሥራ 8፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥1-8። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ


ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል ከቀጰዶቅያ አገር ነው የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍስጥዓዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ። ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ። ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው። ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው።


ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም። ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቊስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደ ሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርነት አክሊል እንደሚቀበል ነገረው። ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው።


ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ ሞልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር። ቅዱሱም ያንን ጽዋ በመስቀል መልክት አማትቦ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ። ከእርሱ ጋራ ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቊጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው።


ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ። ቅዱሱንም “እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን” አሉት። በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቊጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ።


ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት። አቃጥለው አሳርረው ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ይድራስ ከተባለ ተራራላይ በተኑት። ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው። ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ። ቊጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታስነሳ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን በእርሱም እናምናለን” አሉት። ቅዱሱም ጸለየ ከመቃብር ጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ። ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ። ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት። የዚያች መበለትም ቤቷ ምሰሶ ቅርጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ። ያቺም መበለት በተመሰለች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ “የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደእኔ መጣ” አለች። ቅዱሱም “እኔ አምላክ አይደለሁም የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው “የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ። ዕውር፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምህሃለሁ”። ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያንጊዜም አየ። ቅዱስም “በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ” አላት። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት። ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው በመንኰራኵር አበራዩት ሙቶም በከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለሰ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ።


ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት “ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ” አለው። ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው። ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለእስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እንደሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀምረ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች።


በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአያት ጊዜ ፈገግ አለ “ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው” አላት ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ “ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እዘዘው” አለው። ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው። በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ “እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም” ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ። ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ከወገኖቹ ጋራ ዐፈረ። ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ። እርሷም “አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖች አትጣላቸው አላልኩህምን” አለችው። ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።


በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት። ያን ጊዜም የክብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ድል አድራጊ ቅዱስ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥታትን ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው። ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋራ ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ፣ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወታደሮቹ የቅዱሳን የከበረች ራሱን ቈረጡት ደም፣ ውኃና ወተት ፈሰሰው፤ ጌታም ቅዱስ ሚካኤልን በብርሃን ልብስ ደሙን እንዲቀበለው አዘዘ። ጌታችንም የኃያሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ነፍስ በእጁ ተቀብሎ ሳማት፤ በሰማያዊ ልብስም አጐናጥፎ ከእርሱ ጋራ ወደ ሰማይ አሳረጋት። አየር በሙሉ ቅዱሳን መላእክትን ተሞላ። ለቸር አባቱና ለመንፈስ ቅዱስ ቊርባን አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ ቅዱሳን ሁሉ በየወገናቸው ያመሰግኑ ነበር። የብርሃን ልብስ አለበሰው። በዕንቈ ባሕርይ ያጌጠ ከጽሩ ወርቅ የተሠሩ መከራ በተቀበለባቸው ሰባት ዓመታት ልክ ከዕፀ ሕይወት አበቦች የተሠሩ አክሊሎች ያሉበትን ዘውድ አቀዳጀው ለዘላለም ከማኅበረ በኵር ጋራ ስሙን ጻፈው። ሰማያውያን መላእክትና ቅዱሳንንም ሁሉ በየወገናቸው በመንበሩ ላይ እንዲአስቀምጡት፤ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በዓል እንዲ ያደርጉለት አዘዛቸው።


ከዚህም በኋላ ከመብረቁ፣ ከነጐድጓድ፣ ከንውጽውጽታው ጽናት፣ ከዝናሙ ብዛት የተነሳ በምድር ላይ ትልቅ ድንጋፄ ሆነ። ምድርም ሦስት ጊዜ ተናወጸች ከዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሸሹ ወደ ከተማም ሔዱ ጭፍሮችም ይህንን በአዩ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አመኑ። ነፍሱም ወደ ሰማይ በዐረገች ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሰገደች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምን ነፍስ ከሥጋዋ በተለየች ጊዜ አስቀድሞ ለሥሉስ ቅዱስ ትስገድ ከዚህ በኋላ ወደ ወዳጄ ወደ ጊዮርጊስ ይወሰዷት እና ለርሱ እጅ ትንሣ ብሎ አዘዘ፤ በዚህ ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስክርነቱ ሚያዝያ በባተ በሃያ ሦስት ቀን በዕተ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጸመ። አገልጋዮቹም ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደ ሀገሩ ልዳም ወስደው ቤተክርስቲያን ሰርተው በውስጡ አኖሩት፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችንን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ ገድለ ጊዮርጊስ እና የሚያዚያ 23 ስንክሳር።

📖ቅዱስ ጴጥሮስ ከዕንባው በኋላ





ጴጥሮስ መራራ ልቅሶን ካለቀሰና ከተመለሰ በኋላ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ የተሞላበትን ሕይወት ኖሯል፡፡ ጌታችን ለሦስት ጊዜ እንደሚክደው በነገረው ሰዓት ‹‹አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና››ብሎት ነበር፡፡ሉቃ 22-32 ቅዱስ ጴጥሮስ በመራራ ለቅሶ ወደ ጌታው በጸጸት ከተመለሰ በኋላ ጌታችን ንስሓውን እንደተቀበለለት ያሳየው ከሞት እንደተነሳ ነበር፡፡ ጌታችን ወደ መቃብሩ ለመጡት ሴቶች በመላእክቱ በኩል በተናገረው መልእክት‹‹ሒዱና ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም ጌታ በገሊላ የቀድማችኋል ብላችሁ ንገሯቸው››በማለት በትንሳኤው ደስታ ላይ ክጄዋለሁ ብሎ ተስፋ ቆርጦ ከደቀ መዛሙርቱ እንዳይለይ ጴጥሮስን በስም ጠቅሶ ጠርቶታል፡፡ማር 17-7

በገሊላ ባህር ጌታችን በተገለጠላቸው ጊዜም ‹‹የዮና ልጅ ስምዕን ሆይ ከሁሉ ይልቅ ትወደኛለህ››ብሎ ከወቀሳ ይልቅ ርኅራኄን በተሞላ ቃል በማነጋገር ሦስቴ የካደው ጰጥሮስ ሦስት ጊዜ አሳምኖታል፡፡ዮሐ 21 15-17 ልቡ በጸጸት የተሰበረው ጰጥሮስም እንኳን እንደበፊቱ ‹‹ከወንድሞቼ እበልጣለሁ››ሊል ቀርቶ ‹‹ጌታ ሆይ እወድሃለሁ›› ለማለት እንኳን ድፍረት አጥቶ‹‹እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ››ብሏል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በንስሓ ከተመለሰ በኋላ ‹‹ከሁሉ ይልቅ እኔ›› ማለቱን ትቶ‹‹እርስ በእሳቸው እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ›› የሚል የትሕትና መምህር ሆነ፡፡1ኛጴጥ 5-5 በአንዲት አይሁዳዊት ገረድ ፊት ፈርቶ ስ ካደው ጌታው በብዙ ሕዝብ ፊት መስክሮ በአንድ ቀን ሦስት ሺ ሰዎች ክርስትያን አደረገ፡፡ሐዋ 2 14-41 ጌታችን ከወደቀበት ጭቃ ላይ አንስቶ እንደ እንቁ ወልውሎ አክብሮ በበጎቹ ላይ የሾመው ጴጥሮስ እስከ ሽምግልናው ድረስ ያለ መታከት አደራውን በመወጣት ሐሙስ ምሽት ለበደለው በደል ብዙ ትጋት ካሰ፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‹‹ከፊትህ አትጣለኝ ቅዱስ መንፈስህ ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ›› ብሎ በጸጸት ከጸለየ በኋላ ‹‹ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ›› እንዳለ ጴጥሮስም ከንስሓው በኋላ ‹‹ወንድምህ አጽና›› የተባለውን ያለመታከት ጠብቆ ብዙ ኃጢአተኞችን ወደ እግዚአብሔር መለሰ፡፡

ቅዱስ ጰጥሮስ የአገልግሎቱ ፍጻሜ ያደረገው በሮም አደባባይ በሮማውያን ወታደሮች ተከብቦ ነበር፡፤ጌታችን‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደ ምትወደው ትሔድ ነበር ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደ ማትወደው ይወስድሃል›› ብሎ ነግሮ ነበር፡፡ስለዚህ የቄሳር ወታደሮች ሽማግሌውን ጴጥሮስ እጆቹን አስዘረጉት ሰንሰለትን አስታጥቀው እየጎተቱ ወደ ሮም አደባባይ ወሰዱት፡፡ በዚያች ቀን ጰጥሮስ የሮምን ወታደሮች አልፈራም እሳት ለመሞቅ ወደ ማንም አልተጠጋም፡፡ ሐሙስ ማታ ያየውን የጌታውን ፊት ወደ ሰማዓትነት ሲመጣም ያየውን የጌታን ፊት በዓይነ ሕሊናው እያየ ‹‹ጌታዬ ሆይ ዛሬስ አልክድህም››ብሎ ተነሳ፡፡

ወደ አደባባዩ እንደደረሱሮማውያን እንደ ለመዱት በመስቀል ሊሰቅሉት መስቀል አዘጋጅተው ተመለከተ፡፡ጰጥሮስ ግን ‹‹አይሆንም ጌታዬ በተሰቀለበት መስቀል ላይ እኔ ልሰቀል አይገባኝም››አለ፡፡ ለሮማውያን መስቀሉ ባዶ እንጨት ቢሆንም እንደ ጰጥሮስ ላለ ክርስትያን ግን አሁንም ክርስቶስ በዚያ መስቀል ላይ‹‹እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሏል›› ስለዚህ በጌታው ዙፋን ላይ ይቀመጥ ዘንድ ጰጥሮስ ሕሊናው አልፈቀደለትም፡፡

ስለዚህ በዚያው መስቀል ላይ ጭንቅላቱን ወደ ታች ዘቅዝቀው ይሰቅሉት ዘንድ ለመናቸው፡፡እነርሱም የፈቃዱን አደረጉለት፡፡ሽማግሌው ቅዱስ ጰጥሮስ በሮም ቫቲካን አደባባይ ላይ ተዘቅዝቆ እርቃኑን ተሰቀለ፡፡‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህ››ለሚለው የጌታው ጥያቄም በዚያች ዕለት መልስ ሰጠ በረከቱ ይደርብን! አሜን

✍ሕማማት
ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ገጽ 155

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

📖አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

የአባታቸው ስም ስምዖን ፣የእናታቸው ደግሞ አቅሌስያ ይባላሉ። በደቡባዊ ግብፅ ይኖሩ ነበር።በትዳር ሲኖሩ ልጅ ባለመውለዳቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር ።

ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” ይላል (ማቴ ፯÷፯-፰) አቅሌስያ እግዚአብሔን የሚፈራ ልጅ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚሆን ልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን የማያውቅ ከሆነ ግን ማኅፀኗን እንዲዘጋው ትለምን ነበር።ልጅ እንደምትወልድ ተነግሯትም ወደ ቤቷ ተመለሰች።

በእግዚአብሔር ኃይል የተዘራው ፍሬም አፍርቶ ለክርስቲያን ተስፋ የሚሆን ልጅ ተወለደ።ወዲያው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስሙን ገብረ መንፈስ ቅዱስ አለው።እንደ ተወለዱ ስብሐት ለአብ ፣ ስብሐት ለወልድ ፣ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣቸውን ፈጣሪ አመስግነዋል። የእናታቸውንም ጡት ሳይቀምሱ በእግዚአብሔር ተአምር. እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይኖሩ ጀመሩ። ስምዖን እና አቅሌስያም ባዩት ነገር ተደነቁ።በዚህም ሁኔታ ፫ ዓመታት ተቆጠሩ።ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ታዞ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀብለህ ገዳማውያን ወዳሉበት ውሰደውና ከአበምኔቱ በር አስቀምጠው ስለምግቡ እንዳይጨነቁ ፣ምግቡም ቃለ እግዚአብሔር ነው ብለህ ንገር አለው።

ቅዱስ ገብርኤልም ሕፃኑን አቅፎ ወደ ፯ኛው ሰማያት ወስዶ ከእግዚአብሔር ጋር አገናኘው።

እግዚአብሔርም ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳኑ ጋር እንዲገናኙ መልአኩን አዘዘው።መልአኩም መልሶ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወሰደው ።ሕፃኑን አባ ዘመደ ብርሃን በር ላይ አገኙት፣ደስ ብሏቸውም ተቀበሉት።አስተምረው መዓርገ ዲቁና አቡነ አብርሃም ከተባሉ ጳጳስ እንዲቀበሉ አደረጓቸው። 60 አንበሶችና 60 ነብሮችም አብረዋቸው ይኖሩ ነበር። እነዚህን ምን አበላቸዋለሁ? አሉጻድቁ “የረገጥከውን እየላሱ ይጠግባሉ፣ወደ እኔም እስክትመጣ አብረውህ ይኖራሉ” አላቸው።

ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸውም ፩ ክንድ ከስንዝር የሚሆን ፀጉር በቀለላቸው።ከሰው ተለይተው ጻድቁ በጫካ ከአናብርትና ከአናብስት ጋር ይኖሩ ጀመር።

በግብፅ ለ፫ መቶ ዓመታት ሲጋደሉ ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ለመሔድ ተነሡ። ምድረ ከብድ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ እግራቸውን የኢትዮጵያን አፈር ነካ።ከዚያም መልእክ ወደ ደብር ቅዱስ ዝቋላ ወሰዳቸው። ከባሕር ዳር ቁመው የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአት ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፣ ወደ ባሕር ተወርውረው በመዘቅዘቅ ይጸልዩ ነበር።መልአከ እግዚአብሔር ውጣ ሲላቸው መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ካልማርክልኝ አልወጣም ብለው ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ። መቶ ዓመታት ያህል በባሕር ወድቀው ከጸለዩ በኋላ ጌታችን ወደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሄዶ መላውን ሕዝብ ምሬልሃለሁ ውጣ አላቸው።

ሰይጣን ሲፀልዩ በቊራ ተመስሎ ፪ቱንም ዐይኖቻቸውን አጠፋቸው።ሳያቋርጡ ፀለዩ ። ቅዱስ ጳውሎስ ” ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” እንዲል (፩ ተሰ ፭÷፲፰) በሱባኤም ቆዩ ። ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ወርደው ዐይናቸውን እፍፍ ቢሉባቸው ከቀድሞው የላቀ ብርሃን አገኙ።ወደ ዝቋላ ሔደው መቶ ዓመት ሲዋጓቸው የነበሩትን አጋንንትን አጠፏቸው።

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ100 ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው። ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ብዙ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት።

ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት 5 ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል። ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። “ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ: ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ: ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ: ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ: ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።” እንዲል::

ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍቱ መጋቢት 5 ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 15 ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ የመጋቢት 27 ስቅለት ጥቅምት 27 ቀን እንደሚከበረው ሁሉ ወደ ጥቅምት 5 ቀን ተዛውሮ እንዲከበር ተደረገ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፣ ገድለ መንፈስ ቅዱስና ስንክሳር

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
https://youtu.be/qprpfEqVSG4
የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

📖 የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የከበረች ራሱ መገኘት

ይህም እንዲህ ነው ከሐዲ ኄሮድስ የከበረ ዮሐንስን ራሱን ይቆርጡት ዘንድ ባዘዘ ጊዜ በእሥር ቤት ራሱን ቆርጠው ወደ ኄሮድስ አቀረቧት እርሱም ለወገኖቹ በማሳየት በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ስለ አደረገው ሥራ እንደሚያዝን ገለጠላቸው የክብር ዮሐንስንም ራስ በቤቱ ውስጥ አስቀራት። የፊተኛዪቱ ሚስቱ የንጉሥ አርጣ ልጅ ግን በአባረራት ጊዜ ወደ አባቷ መጥታ በፊቱ አለቀሰች ኄሮድስ በእርሷ ላይ ያደረገውን ሁሉ እርሷን አሳዶ የወንድሙን ሚስት ኄሮድያዳን እንዳገባ ነገረችው። በዚያንም ጊዜ ንጉሥ አርጣ ተቆጥቶ ተነሣ ሠራዊቱንም ሰብስቦ ወደ ገሊላ ዘመተ የገሊላንም አገሮች ሁሉ አጠፋ በእሳትም አቃጠለ። ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ኄሮድስ በአባረራት በልጁ ምክንያት ንጉሥ አርጣ ይህን እንዳደረገም በአስረዱት ጊዜ ስለዚህ ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ተቆጣ ኄሮድስንም ወደ ሮሜ ከተማ ወደርሱ አስቀረበው በእርሱም ምክንያት የአገሮች ጥፋት በመደረጉና ታላቁን ነቢይም ስለ መግደሉ ከሹመቱ ሻረውና ወደሌላ አገር አስጓዘው በዚያም በክፉ አሟሟት ሞተ። የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ግን በኄሮድስ ቤት ተቀብራ ትኖር ነበር ከዚህም በኋላ ንጉሥ ጢባርዮስ ጭፍሮቹን ልኮ የኄሮድስን ቤት አስፈረሰ ጥሪቱን ሁሉ ወሰዶ ለሚያየውም ሁሉ አርአያና ተረት ሆነ ያለ ጣሪያና ያለ ደጃፍ ቀርቷልና ነጋዴዎችም መናኸሪያ አድርገው ያድሩበት ነበር።

በዚያንም ወራት በገንዘብ ድኆች በሃይማኖት ባለጸጎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ እነርሱም ሊሰግዱ የከበረች የአርባ ቀን ጾምንም ሊጾሙ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ ነው። ምሽትም በሆነ ጊዜ ምድረ በዳ በሆነ በኄሮድስ ቤት ውስጥ አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሳቸው ለአንዱ በሕልም ተገለጠለትና የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ አስረዳው ወደቤቱም ተሸክሞ ይወስዳት ዘንድ አዘዘው በነቃም ጊዜ ራእይን እንዳየ ለባልንጀራው ነገረው። ቅዱስ ዮሐንስም ወደአመለከተው ወደዚያ ቦታ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ በቆፈሩም ጊዜ የሸክላ ዕቃ አግኝተው ከፈቷት ያን ጊዜ እጅግ የሚመስጥ በጎ መዓዛ ወጣ የቅዱስ ዮሐንስንም ራስ አገኙዋት ከእርሷም ተባረኩ ወደ ሸክላው ዕቃ መለሱዋትና በፊቱ እንደ ነበረ አፉን ዘጉ ያም ሰው ከእርሱ ጋር ወደ ቤቱ ወሰዳት ታላቅ ክብርንም አከበራት ሁል ጊዜም የሚያበሩ መብራቶችን በፊቷ አኖረ።

የዚያም ሰው ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ ለእኅቱ ነገራት እርሷ ቅድስና ስለአላት እርሱ ሲሠራው እንደነበረ ትሠራ ዘንድ አዘዛት እርሷም የምታከብራትና ሁል ጊዜ መብራትንም የምታበራ ሆነች። የቅዱስ ዮሐንስም ራስ ወደ አርዮሳዊ ሰው እስከ ደረሰች ድረስ ከአንዱ ሰው ወደ አንዱ ሰው የምትፋለስ ሆነች ይህም ሰው በከሀዲው አርዮስ እምነት ውስጥ እያለ የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ድንቆች ተአምራቶችን እንደምታደርግ ያስብ ነበር።

የከበረ ዮሐንስም ከእርሱ የሚበልጥ ሰው በላዩ አስነሣበትና በዚያ ቦታ አሳደደው ያም ቦታ አባ ቄርሎስ በኢየሩሳሌም አገር አባ አንያኖስ በአገረ ኀምዳ ኤጲስ ቆጶስነት እስከ ተሾሙ ድረስ ፈጽሞ ሰው የማይኖርበት ምድረ በዳ ሆነ። ቅዱስ ዮሐንስም ለአባ አንያኖስ በሕልም ተገልጦ የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ ነግሮ አመለከተው አባ አንያኖስም ሒዶ እንደ ዛሬው ግንቦት ሠላሳ ከዚያ አወጣት ይህም የካቲት ሠላሳ ቀን ከአገኙዋት በኋላ ዳግመኛ ያገኙበት ነው።

👉 እንዲህም የሚል አለ የከበረ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ተናገረ ይህም ኄሮድስ በአዘዘ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በእሥር ቤት ሳለ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው በጻሕል አድርገው ወደ ኄሮድስ አመጡለት እርሱም ለኄሮድያዳ ልጅ ሰጣት እርሷም ለእናቷ ወስዳ ሰጠቻት። ይቺም የረከሰች አመንዝራ ልትዳስሣት በወደደች ጊዜ በወጭቱ ውስጥ ጠጒሩዋ ተዘርግቶ ወደ አየር በረረች በአየርም ሆና “የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም” እያለች የምትጮኸ ሆነች እንዲህም እያለች ዐሥራ አምስት ዓመተት ኑራ በዓረቢያ ምድር ዐርፋ በዚያ ተቀበረች።

ነጋድያንም በዚያ ቦታ የሚያድሩ ሆነ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሁለት አማንያን ነጋዴዎች ወደዚያ ቦታ ደርሰው አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም በሕልም ተገለጠላቸውና የከበረች ራሱን ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም አወጡዋት ከእርሳቸውም ጋር ቤታቸው ወስደው ታላቅ ክብር አከበሩዋት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም መለኮትን በአጠመቀ በከበረ ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን ልዩ የሆነች በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 30 ስንክሳር።

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org

ጻድቅ ወሰማዕት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ)

እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ በአጤ (ዐፄ) ሱሱንዮስ አንገቷን ተሰይፋ ሰማዕት ለሆነችና ታላቁን ገዳም ራማ ኪዳነ ምሕረትን ላቀናች ለታላቋ ለጻድቅ ወሰማዕት ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ለዕረፍቷ በዓል በሰላም አደረሰን (የካቲት 29) ።

በጎንደር ክፍለ አገር ደራ ፎገራ አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አጠገብ ኮክታ ማርያም ተብሎ በሚጠራው ቦታ ውስጥ ተወለደች፡፡ዛሬም ይህ አካባቢ እመ ምዑዝ መንደር ይባላል፡፡የአባቷ ስም ቅዱስ ላባ የእናትዋ ስም ቅድስት ወንጌላዊት ይባላል፡፡ እነዚህም ወላጆቿ እጅግ ደጋግ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለተራበ፣ ለተጠማ የሚያዝኑና የሚራሩ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ በጎ ምግባር ያላቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በረከት ሁሉ በሥራ ላይ የሚያውሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ ስላልወለዱ ወደፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ ቸር አምላክ ስለሆነ እንደ ቅድስት ሐና እመ ሳሙኤል ጸሎታቸውን ሰምቶ የተመረጠች ደግ ሴት ልጅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በሚያዚያ 4 ቀን ተፀንሳ ታኀሣሥ29 ቀን ከእነሱ ተወለደች፡፡ ስመ ጥምቀቷ ማርያም ጸዳላ የዓለም ስሟ ሙዑዚት ሲሆን ሙዑዚት ማለት ጣፋጭ ማለት ነው፡፡ (ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ደግሞ የቆብ ስሟ ነው።)

በተወለደችም ጊዜ በእግርዋ ቆማ “በማኀየዊ ቸርነትህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኸኝ ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል” ብላ አመሰገነች ከእግዚአብሔር የተላከ መነኵሴም ወደ እርሷ በመሄድ የዳዊትን መዝሙር፣ መጻሕፍትንና የቤተክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ አስተምሯታል፡፡

ቅድስት እናታችን አምላኳን አስከ መጨረሻው በድንግልና ማገልገል ብትፈልግም ዕድሜዋ ከፍ ሲል ቤተሰቦቿ ዘርዐ ክርስቶስ ከሚባል አገረ ገዥ ጋር በቤተክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል አጋቧት ፡፡ እርሷ ግን በጫጉላ ቤት ሳሉ በእኩለ ሌሊት ባሏን “ወንድሜ ሆይ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ድንግልናችንን እንጠብቅ” አለችው፡፡ እርሱም “እሺ” ብሏት ይህንን ተመካክረው በጸሎት ሲተጉ አደሩ፡፡ ለእግዚአብሔር እየተገዙ በጾም በጸሎት በንጽሕናና በድንግልና ኖሩ በሌሊትም ወደ፡ባሕር ውስጥ እየገቡ ጸሎት ያደርጉ ጀመር፡፡ በመጨረሻም እርሷ በጳጳሱ በአባ ማርቆስ እጅ ስትመለኵስ ባሏም ድንግልናውን እንደጠበቀ በሰማዕትነት አንገቱን ተሰይፎ አርፏል፡፡ እርሷ በነበረችበት ዘመን ንጉሥ ሱስንዮስ “ሁለት ባሕርይ” የሚለውን የረከሰ የሮማውያንን ሃይማኖት ሕዝቡ ሁሉ እንዲያምን በማወጁ ምክንያት በአገራችን ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት ግጭት ስለተነሣና ከ8ሺህ በላይ ክርስቲያኖች በግፍ ተጨፍጭፈው ሲያልቁ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከእነ አቡነ ስምዖንና ከሌሎችም ቅዱሳንና ቅዱሳት ጋር ተሰልፋ ሰማዕትነትን ተቀብላ ለሃይማኖትዋ ምስክር ሆናለች፡፡ ባለቤቷ ዘርዐ ክርስቶስም በሰማዕትነት ዐርፎ ሰባት አክሊላት ወርደውለታል፡፡

እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሱስንዮስ በአደባባይ ሲያስገርፋቸው ሥጋቸው እየተቆራረጠ መሬት ላይ የወደቀውን የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ሰብስባ “ይህን ለንጉሡ እጅ መንሻ ስጡልኝ” ብላ ላከችለት፡፡ “ይህ የየሃይማኖት ፍሬ ነው፡፡ እኛስ አስከአሁን በሃይማኖታችን አለን፣ አንተ ብትገለን መከራም ብታደርስብን ሃይማኖታችንን አልካድንም፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ከሞት አስነሣን ይህን የሥጋዬን ቁራጭና የእህቶቼን የደናግላንን ሥጋ ብላው ፣ ደማችንን ጠጣ ሃይማኖትህ የከፋ፣ ሰነፍ፣ የረከስህ ነህ” ብላ ልካለታለች፡፡ መልእክተኞቹም ለንጉሡ ወስደው ሰጥተውታል፡፡

ሱስንዮስ አዋጁን እንዳወጀ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖንም ካህናትንና ክርስቲያን ልጆቻቸውን አነሳስተው እያስተማሩና እያጠነከሩ እያለ በጦር ተወግተው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡


ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት ግን እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስን፣ ቅድስት አካለ ክርስቶስን፣ ቅድስት እመ፡ወተትን … ወዘተ አነሳስተው ንጉሡን መክረውታል፣ ገሥጸውታል፣ ንጉሡ ግን ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የሃይማኖቷን ጽናት ስላየ ሥጋዋ እየተቆረሰ መሬት ላይ እስኪወድቅ ድረስ በብረት በትር አጥብቆ ያስገርፋት ጀመር፡፡
በመጨረሻም ምድር እየሰወረቻት ለመግረፍ የማይመቻቸው ቢሆን ከሌሉቹ ሰማዕታት ጋር አንገቷን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡ በዚህም ጊዜ ፍጹም ጨለማ ሆኖ ምድርም ተነዋወጠች፡፡ ስምንት ሺህ ዐሥር ቅዱሳንም በሰማዕትነት ዐረፉ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን አንገቷን በሰይፍ ቢቆርጧትም ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ገነትንና ሲኦልን አሳይቶ 14ቀን በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተቀመጠች በኋላ እንደገና እንደተኛ ወይም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ከሞት አስነሥቶ ወደ ቦታዋ መለሳት፡፡

እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤልም ከሞት ካስነሣት በኋላ መናኝ ሆና በየገዳሙና በየአድባራቱ እየሄደች ዓለምን ስትዞር ያቀናቻቸው ብዙ ገዳማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአባ ጉባ ተመሥርታ በግራኝ ወረራ ጠፍታ የነበረችውን ራማ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምን አቅንታ የወንድና ሴቶች መነኰሳት በጋራ አብረው ይኖሩ የነበረ ቢሆንም የበጎ ሥራ ጠላት የሆነው ሰይጣን በማኀበረ መነኰሳቱ መካከል ሊፈጥር ያለውን ክፉ ፈተና ለእናታችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጾላት በገዳሟ ውስጥ የወንዶችና የሴቶች መነኰሳት መኖሪያ የተለያየ እንዲሆን አድርጋለች፡፡

ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምም በመሄድ ላይ ሳለች በመንገድ ሰውን የሚበሉ ፍጡሮች ወደሚኖሩበት አካባቢ ስትደርስ 60 የሚሆኑ አገልጋዮቿን ለመብላት ይዘው ሳር ቅጠል እንዲበሉ በማድረግ ዓይናቸውን በጉጠት በማውጣት ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ዘጉባቸው ሰይጣንንም ያመልኩ ነበርና ከ4 ወራት በኋላም በዓል አድርገው ለመብላት ከእሳት ውስጥ ጨመሩአቸው፡፡ እነርሱ ግን ምንም አልሆኑም፡፡ ያን ጊዜም “እናንተ ሰዎች ምንድን ናችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡ ቅድስት እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስም ክርስቲያን መሆናቸውንና እነርሱ የሥላሴ ሕንጻ የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው ብትመክራቸው “ምን እንበላለን?” አሏት፡፡ እርሷም ከራማ ኪዳነ ምሕረት ስትነሳ የእህል ዘርን ለአገልጋዮቿ አስይዛ ስለነበር ከዚያ ስንዴ ወስዳ ዘራችው፡፡ስንዴውም በአንድ ቀን ተዘርቶ በቅሎ፣ ታጭዶ፣ ደርቆ፣ ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡


ቅድስት እናታችንም ቀምሳ ስታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም እንደዚህ እያደረጉ እየሠሩ እንዲበሉ አስተምራ አስጠምቃቸው ስድስት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታላቸዋለች፡፡ወንጌልን፣ ስንክሳርን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ግንዘትን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ አርጋኖንን ሁሉ በእጅዋ ጽፋ አስቀመጠችላቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጣላት በልጅዋ ምክንያት ስለ ደረሰባት ሀዘኖች አውርታላታለች፡፡ የፈለገችውንም እንድታደርግበት በእጅዋ ያለውን መስቀል ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሰጥታታለች፡፡ በዚህም መስቀል ባሕር ከፍላ ደቀ መዛሙርቶቿን አሻግራለች፡፡

እናታችን የአባታችን የአባ ኤዎስጣቴዎስን ገድል በማንበብና በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እርዳታ ባሕሩን በአጽፏ ተሻግራ ወደ አገረ ናግራን ሄዳለች፡፡ እንዲሁም በበትረ መስቀል እንደ ዘርዐ ቡሩክ ከባሕር ውስጥ የሰጠሙ የደቀ መዛሙርቶቿን መጻሕፍት ምንም ሳይሆኑ ማውጣት ችላለች፡፡ በሁሉም አገር እየዞረች ቅዱሳት መካናትን ትሳለም ነበር፡፡ ደብረ ደሞ ሄዳ “ሴቶች መውጣት አይችሉም” ቢሏት በሀዘን ስታለቅስ ቅዱስ ሚካኤል በሥውር ወስዶ አድርሷታል፣ አቡነ አረጋዊም ተገልጸውላት ባርከዋታል በዚያም ሥጋ ወደሙን ተቀብላለች፡፡


እናታችን ወደ ኢየሩሳሌምም ሄዳ ቅዱሳት መካናትን እየተሳለመች ለ7 ዓመታት ቆይታለች ቅዱስ ሚካኤልም በዓምደ ብርሃን እየመራት ተመልሳ ወደ አገራችን መጥታ በድጋሚ ከሱስንዮስ ጋር ተሟግታለች፡፡ ሙታንንም እያስነሳች እንዲመሰክሩላት ብታደርግም እርሱ ግን ከጥፋቱና ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም ነበር፡፡ የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ መልእክቷንም በንስር አሞራ አድርጋ እየላከች ትመክረው ነበር ፡፡

በአንድ ወቅትም በአገራችን እህል መታጣት ሆነና ቅድስት እናታችን ዝክር የምታደርግበት እህል አጣች፡፡ደናግል ልጆቿንም ጠርታ ትንሽ ዱቄት እንዲያመጡላት ነግራቸው በእርሱ ጸሎት አድርጋበት “ወደ ቦታው መልሱት” አለቻቸው፡፡ በማግስቱም እንሥራው ጋኑ ሁሉ በዱቄት ተሞልቶ አግኝተውታል፡፡ የካቲት ኪዳነ ምሕረትንም በዓል በደስታ አክብረዋል፡፡ መልአኩም ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ካመጣት በኋላ ዛሬ ገዳሟ ካለበት ቦታ ስትደርስ ከቦታዋ ላይ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ በቀስተ ደመና ተከቦ አይታ “ይህች ቦታ ምንታምር” ብላ ጠራቻት፡፡

በቦታውም ላይ በመድኃኔዓለም ትእዛዝ የቅድስት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀን ታህሣሥ14 ቀን በዕለተ ዓርብ ጧት በሰንሰል (በስሚዛ) እንጨት ጀምራ ማታ እንደተፈጸመ በ3ኛው ቀን እሁድ ታህሣሥ16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር በድርገት (በቁርባን) ጊዜ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አእላፋት መላእክት ጋር ወርዶ መቅደሱን ሲባርክ መቅደሱ በ4ቱ ማዕዘን ለጌታ ሰገደ። ለጌታ እንደ ሰገደ ዛሬም ድረስ ይታያል ጌታችንም “ይህ መቅደስሽ ሳይፈርስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ይቆይልሻል፡፡ በዚህ ቦታ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡ በምድርም ስምሽን የጠራ፣ መታሰቢያሽን ያደረገ፣ የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ የተረጐመ ሁሉ ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና ያልታሰበውን ለነዚህ ሁሉ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፡፡ ከሩቅም ከቅርብም ከቀኝም ከግራም መጥቶ መቅደስሽን ለተሳለመ ሁሉ እስከ 12ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ፡፡ላልምረው ቦታችን አላስረግጠውም፡፡ በረከቴም በእሱ ላይ በልጆቹም በንብረቱ ላይ ለዘለዓለሙ ይኖራል፡፡ ስለጾምሽ፣ ስለጸሎትሽ፣ ስለተጋድሎሽ፣ ስለ ስግደትሽ ሰባት አክሊል ሰጠሁሽ” አላት፡፡

ፃድቋ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ብዙ ገድል በሠራችበት ብዙ መነኰሳይያትን በአቋቋመችበት ገዳሟ በእመ ምዑዝ ኪዳነ ምሕረት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም የካቲት29 ቀን ዐረፈች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር መጥቶ ነፍሷን ተቀብሎ ወደ ገነት ወስዶ አኖራት፡፡ ባረፈች ጊዜ በሥጋዋ ላይ ታላቅ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ የታየ ሲሆን እንደ ፀሓይም ከጠዋት እስከ ማታ ያበራ ነበር፡፡ በመካነ መቃብሩዋም ላይ እስከ አርባ ቀን ድረስ ብርሃን ተተክሉ ታይቷል፡፡

ምንጭ፦ገድለ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ። ከእናታችን ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። በጸሎቷም ይማረን!።

📖 አስታውስ

👉ደካማነትህን አስታውስ፦ ያን ጊዜ በጣም ጠንቃቃ ትሆናለህ፣ ሊጎዱህ በሚችሉ በትምክህትና በውዳሴ ከንቱም አትሸነፍም።

👉የተሰጠህን በፍቅር የተሞላ የእግዚአብሔርን ቸርነት አስታውስ፦ ይህም በምስጋና የተሞላ ሕይወት እንድትመራ ያደርግሃል።

👉በእግዚአብሔር ፍቅርና ሥራ ላይ ስትታመን ፍጹም የሆነ እምነት በልብህ እያደገ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያሳለፍከው ጊዜ ደግሞ በእምነት እንድትኖር ያበረታታሃል።

👉የሰዎችን ፍቅርና ካንተ ጋር ያሳለፉትን መልካም ጊዜ አስታውስ፦ የሰዎችን ቀናነት ትጠራጠር ዘንድ ወይም ያደረጉብህን ክፉ ነገር ታስብ ዘንድ ይገባሃልን? የቀደመ ፍቅራቸው ስለ እነርሱ ይማልዳል ያንተንም ቁጣ ያበርዳል።

👉ሞት እንዳለ አስታውስ፦ እንዲሁ በዓለም ያለ ፈተናም እንደሚያልፍ። “ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” መክብብ 1፡14 ማለትን ትረዳለህ።

👉በእግዚአብሔር ፊት መቆምህንና እርሱም እንደሚመለከትህ አስታውስ፦ ያኔ ኃጢአት አትሰራም እግዚአብሔርን ታየዋለህና።

👉ስለ አንተ የፈሰሰውን የክርስቶስን ክቡር ደም አስታውስ፦ በዚህም ሕይወትህ ያለውን ዋጋ በእርግጥ ታውቃለህ፤ በዓይኖችህ ፊት የከበረ ይሆናል፣ ስለዚህም በከንቱ በመኖር አታጠፋውም “በዋጋ ተገዝታችኋልና” 1ኛ ቆሮ. 6፥20 እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ።

👉በወላጆችህ እምነት በተጠመቅህባት ቦታ ለእግዚአብሔር የገባኸውን ቃል አስታውስ፦ ዲያብሎስን፣ ሥራዎቹን ሁሉ፣ ሐሳቦቹንና ጥበቡን፣ ኃይሉንም ትክድ ዘንድ ኃይል ታገኛለሕና።

👉በዚህ ዓለም እንግዳ መሆንህንና ወደ ሰማያዊው ቤትህ እንደምትመለስ ዘወትር አስታውስ፦ ያን ጊዜ በዚህ ዓለምና በደስታው ተስፋ ማድረግን ትተዋለህ።

👉በጠባቡ በር መጓዝ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚያደርስህ አስታውስ፦ ሰፊው ደጅ ፊት ለፊትህ ተከፍቶ ብታየው፣ አልፈኸው ሂድ ከእሱም ራቅ፣ በእርሱ የሄዱ እንዳሉ አልቀዋልና።

👉ዘላለማዊውን ሕይወትህን አስታውስ፦ ሁልጊዜም ስለዚህ ትጋ።

👉የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህንና እርሱን መምሰል እንዳለብህ አስታውስ፦ እውነተኞች ከሆኑት ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር አካሄድህን አስተካክል።

👉የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆንህን አስታውስ፦ በውስጥህ ያለውንም ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝን። ዘወትርም ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሁን።

✍አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org