ወቅቱ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ቦታውም አዲስ አበባ ነው። በንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ኅሊና ውስጥ ያደረውን ከኤፌሶኑ ጉባዔ ፲፭፻ ዓመታት በኋላ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (ኦሪየንታል) አባቶችን የሚያሰባስብ ጉባዔ ለማዘጋጀት አዲስ አበባ እየተንጎዳጎደች ነው። በዚህ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ በራሳቸው በንጉሠ ነገሥቱ በኩል የ፭ቱ አኀት አብያተክርስቲያናት ጥሪ የደረሳቸው በግንቦት ፲፱፻፶፮ ዓ.ም. ነበር። አብያተ ክርስቲያናቱ ለመገኘት ይሁንታቸውን ሲቸሩ መርሐግብሩን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎችን በመሠየም ወደ ሥራ ተገባ።
የመጀመሪያው ኮሚቴ በሐረር ሊቀጳጳስና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (በኋላ ፓትርያርክ) የሚመራ የመርሐግብር ኮሚቴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግስት ሥራ ሚኒስቴር ሚንስትር ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ የሚመራ የአቀባበል ኮሚቴ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ የጤና ሚኒስትር አቶ አበበ ረታ ዋና ጸሐፊነት የሚመራ ጽሕፈት ቤት ተቋቋመ። ኮሚቴዎቹ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ተወካዩ ከአባ ጳውሎስ ቬርጋስ ጋር በመተባበር ከጉባዔው ወራት አስቀድመው ነበር ዝግጅታቸውን የጀመሩት። በብፁዕ ወቅዱሳን ፓትርያርኮች ከሚካሄደው ዋናው ጉባዔ አስቀድሞ ከ፭ቱም አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ዐሥር የነገረ መለኮት ምሁራን ከዝግጅት ኮሚቴው ኃላፊዎች ጋር ከታኅሣሥ ፳፱/፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ጀምሮ ለ፯ ቀናት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ተካሄደ።
ጉባዔው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ጸሎትና አባታዊ መልእክት የተከፈተ ሲሆን በብፁዕነታቸው ሊቀመንበርነት እየተመራ በዝግ ባደረገው ጉባዔ ለዋናው ጉባዔ የሚያገለግሉ ፮ ርእሰ ጉዳዮችን ለየ። እነዚህ ፮ ርእሰ ጉዳዮች:
፩. ቤተክርስቲያንና ዘመናዊው ዓለም፣
፪. በነገረ መለኮት ትምህርት ላይ የሚኖር ትብብር፣
፫. በወንጌል መስፋፋት ዙሪያ የሚኖር ትብብር፣
፬. ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶች፣
፭. የአብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት ለማስቀጠል የሚያስችል ቋሚ መንገድ ማመቻቸት፣
፮. በዓለሙ ላይ ስለሚታየው ሰላም ማጣትና ፍትህ ዙሪያ አቋማቸውን ማንፀባረቅ ነበር።
ከቅድመ ጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ለዋናው ጉባዔ በእንግድነት የተጋበዙ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ተወካዮች ታጅበው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ንጉሠ ነገሥቱ ከከፍተኛ የቤተክርስቲያንና የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያና በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በጉባዔው ላይ የተገኙ አብያተክርስቲያናት አባቶችም:
፩. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ ከ፬ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፪. ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ሞር አግናጥዮስ ያዕቆብ ፫ኛ፣ ከ፭ የአንፆኪያና የመላው ምሥራቅ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣
፫. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቫኪን ቀዳማዊ በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኢታችማንዴዝና የመላው አርማንያ ፓትርያርክ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ ካቶሊኮስ አቡነ ኮራን ቀዳማዊ በአርመን ቤተክርስቲያን የኪልቅያ መንበር ፓትርያርክ ከ፱ የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፬. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ቀዳማዊ ከ8 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፭. ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ማር ባስሊዮስ አኡጉን ቀዳማዊ ከ፯ የማላንካራ ሶሪያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (ህንድ) ጋር ናቸው። ዋናው ጉባዔ ጥር ፮ በአፍሪካ ኅብረት ዋናው አዳራሽ ሲካሄድ በጥንታዊው ሥርዓት መሠረት ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው በየደረጃው የተቀመጡ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ባለ ጠረጴዛ ላይ ከፊት ለፊት በማኖር ጉባዔው ተጀመረ። ጉባዔው በንጉሠ ነገሥቱ፣ በሶሪያና አርመን ፓትርያርኮች ተከታታይ የመክፈቻ ንግግር ከተጀመረ በኋላ በቅድመ ጉባዔ በረቀቁ ዐሳቦች ዙሪያ እስከ ጥር ፲፬ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ድረስ ውይይት አካሂደዋል። ይሄኛውም ጉባዔ በዝግ የተካሄደ ሲሆን በጉባዔው ጥያቄ መሠረት አቶ አበበ ረታ በአስተባባሪነት፣ አቶ አበራ ጀምበሬ ደግሞ በዋና ጸሐፊነት ተሳትፈውበታል። ጉባዔው ሲጠናቀቅ:
✍️ቅዱሳን ፓትርያርኮች ንጉሠ ነገሥቱን ወልታ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጋሻ) ብለው የሰየሙ ሲሆን ትውፊትና ጥንታዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ለወጣቶች፣ በከተማ ለሚኖሩ ምእመናን እንዲሁም ለቤተሰብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ፣
✍️መጽሐፍ ቅዱሳዊውንና ሐዋርያዊውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ዘመኑን ለወለዱ አዳዲስ ትምህርቶችና ርእዮተ ዓለሞች ምላሽ በሚሆኑ መልክ ማዘጋጀትና ሥነጽሑፍን ማስፋፋት፣
✍️ሥርዓተ ምንኩስናን ማስፋትና ማፅናት በተለይም የቀደመውን ሥርዓት በመመለስ የሴቶችን አገልግሎት ማጠናከር፣
✍️የቤተክርስቲያን አስተዳደር በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚታየው የሰፋ ልዩነትን መልሶ በማገናዘብ ለሐዋርያዊ ሥርዓትና ለኖላዊ አገልግሎት ምቹ በሆነ መንገድ ማስተካከል እንደሚገባ ፣
✍️በነገረ መለኮት ትምህርት የጋራ ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረፅ ጀምሮ የትምህርት ዕድሎችን፣ የመማሪያ መጻሕፍትን፣ ምሁራንን ለመጋራት፣
✍️ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ ከሮማ ካቶሊክና ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች መጠናከር እንደሚገባቸው በማመን በውይይቶች ላይ ተመሳሳይ አቋምና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ፣
✍️የኦርየንታል(ተዋሕዶ) አብያተክርስቲያናት ግንኙነት ቀጣይ ሊሆን እንደሚገባ በመስማማት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁለት ሁለት ተወካዮች እንዲሰየሙ፣
✍️በዓለም ላይ ያለ፡ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ ቅኝ ግዛትን በማውገዝ በመላው ዓለም ለሚከናወኑ የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎችን እንደሚደግፉ የሚገልፁ ውሳኔዎችን በመስጠት ተጠናቋል።
ጉባዔው ከሺህ ዓመታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ቢሆንምና በቀጣይነቱ ላይ ሁሉም አብያተክርስቲያናት የተስማሙ ቢሆንም በመሪዎች ደረጃ መሠል ጉባዔ ድጋሚ ሳይካሄድ እነሆ ፷ ዓመታት አልፈዋል። ነገር ግን ጉባዔው አብያተክርስቲያናት አሁን ላይ ላላቸው የትብብር መንፈስና አንድነት፣ በልዩልዩ ጉዳዮች ላይ ላላቸው ወጥና ተመሳሳይ አቋም መነሻ በመሆኑ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ደማቅ ኵነት ሆኖ ቀጥሏል። በሰሜን አሜሪካ መቀመጫውን ላደረገው የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ስታንዲንግ ኮንፍረስ ለተሰኘው ተቋምም ምሥረታና ህልውና እንደ ጋራ ሠነድ እያገለገለ ይገኛል። ይህን አዲስ አበባን እንደ ኒቂያ ንጉሠ ነገሥቱንም እንደ ቆስጠንጢኖስ ያስቆጠረውን ጉባዔ የዳሰስንበት ሰፊ ጥንቅር የምናበቃው አምላከ ቅዱሳን ዳግም ጉባዔውን የማስጀመር መነሳሳት በፍቁራኑ ልብ እንዲያሳድርና የቤተክርስቲያንን አንድነት እንዲጠብቅ በመመኘት ነው።