ተስፋ

ሕይወታችን ያለ ተስፋ ባዶ ነው፤ ያለ ተስፋ መኖር አንችልም፤ ተስፋ ከሌለን ማንኛውንም ዓይነት የኑሮ ገጠመኝና ችግር ማሳለፍ አይቻለንም፡፡ የሰው ልጆች ዋነኛው ብርታት ተስፋ ማግኘትና በተስፋ መኖር ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፎ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ከበላ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በምድር ላይ ሲኖር በሀዘንና በጭንቅ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪ የልቡን ጭንቀትና ሀዘን ተመልክቶ ሊምረው ስለ ወደደ ከልጅ ልጁ ተወልደ እንደ ሚያድነው ቃል ገባለት፡፡ ይህም ለአዳም ትልቅ ተስፋ ስለ ነበረ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ በተስፋ ጠብቋል፡፡ ሰዎች በምድር ላይ ልንኖር የምንችለው ተስፋ የምናደርግበት ነገር ሲኖረን ነው፡፡ አዳም ማጥፋቱን አውቆና አምኖ ምሕረትን ስለ ለመነ ወደ ቀደ መክብሩ ተመልሶ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደቻለ እኛም ተስፋ ማድረግ ያለብን ተስፋ (ርስተ መንግሥተ ሰማያትን) ነው፡፡ ይህም የምድር ሕይወታችንን በመልካሙና በእውነተኛው መንገድ እንድንኖር ይረዳናል፡፡ ለዚህም ምሳሌዎች የሆኑት የጻድቃን የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ታሪኮች ምስክሮች ናቸው፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ሀብቱንና ንብረቱን እንዲሁም ልጆቹን በሙሉ አጥቶ በዚያ ሕመምና በሽታ በተፈራረቀበት ጊዜ እንኳን በእግዚአብሔር ተስፋ ሳይቆርጥ  ‹‹ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ›› በማለት ተናገረ እንጂ አምላክን እንዳላማረረ ቅዱሱ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ (ኢዮ. ፴፥፳፮) ይህ በእውነት ለእኛ ትልቅ ትምህርት የሚሆነን ነው፡፡ በእርግጥም እንደ ኢዮብ ያለ መከራ እና ችግር ሳይደረስብን በራሳችን ችግር ተውጠን ባለንበት በዚህ ጊዜ ተስፋ ማድረግ የምንችለው አምላካችንን ሊሆን ይገባል እንጂ በሆነው ባልሆነው ነገር እግዚአብሔርን ማማረር እራስን ለባሰ ችግር ማጋለጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሕይወቱ ውስጥ የሌለ ሰው ተስፋ ሊኖረው እንደማይችል በቅዱሳን ታሪክ ብቻም ሳይሆን በራሳችን ተሞክሮም የተመለከትነውና ያወቅነው ነገር ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሳናውቅም ሆነ አውቀን ከገባንበት ችግር ለመውጣት አቅቶን ስንባዝን የከረምንና ግራ በመጋባት መፍትሔ መስሎን ወዳልሆነ ነገር የገባን ልንኖር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ: ሰዎች ችግራቸውን ለመፍታትና ከገቡበት ዕዳ ለመላቀቅ ሲሉ ወደ ባዕድ አምልኮት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ግን የባሰ ችግር እንደ ሚያመጣ በወቅቱ ላያውቁና ላያገናዝቡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሰው ለምድራዊ ሕይወት ሲል ፈጣሪውን ክዶ ለጠላት መገዛት ከጀመረ ለጊዜው ችግሩ የተፈታለትና የሥጋ ድሎት ያገኘ ቢመስለውም ወደደም ጠላ የእርጅናው ዘመን በደረሰ ጊዜና ወደ ሞት ሲቃረብ በፍርሃት መኖር ይጀምራል። ከዚህም በባሰ መልኩ ሲያመልከው የነበረው ዲያብሎስ ሞቱ በቀረ በጊዜ ተስፋ አሳጥቶ ነፍሱን ወደ ገሃነም ሊያወርዳት ይፋጠናል፤ በዚህ ጊዜ የመዳን ተስፋው ተሟጦ ንስሓ እንዳይገባ ዲያብሎስ የማያደርገው ጥረት የለም፡፡ ሰው ሲተማመንበት የነበረው ሀብቱም ሆነ ውበቱ ወይም ሥልጣኑ ከገሃነም ሊያድነው አይችልም። ይህ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው፤ የሥጋ ነገር ሁሉ ጠፊ ነውና፤ ‹‹ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁኩ ከንቱ››   እንዲል። (መክ. ፩፥፪) ይህንን ግን በጊዜው ተረድቶ ለነፍሱ መኖር የሚችል ሰው በአሁኑ ጊዜ ጥቂት ነው፤ አብዛኛው ሰው በምድራዊ ችግሮቹ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚኖርነው፡፡ ስለሆነም ከአቅማችን በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥመን እና መፍትሔ ስናጣ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ያዳግተናል፡፡ ይቅር እንደሚለንና ምሕረትን መለመን እንደምንችልም ማመን ስለሚከብደን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡

ሕይወት በውጣውረድ የተሞላች እንደመሆኗ የሚያሳዝን ነገር በኑሮአችን ሲያጋጥመን በመከፋት ተስፋ መቁረጥ የለብንም፤ ዛሬ ቢጨልምብን ብርሃን ይሆናልና፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ‹‹…በጎ ነገርን በተጠባበቅኋት ጊዜ እነሆ ክፉ ቀኖች መጡብኝ፤ ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ›› በማለት እንደተናገረው ምንም እንኳን መከራና ችግራችን የተደራረበበት ወቅት ላይ ብንሆንም እነዚህ ክፉ ቀናት አልፈው በጎ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ ይገባል፡፡አባቶቻችን “ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም” ይላሉ። በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን በሙሉ የትኛውም ዓይነት ችግር ቢገጥመንም ሆነ መከራችን በዝቶ በሥቃይ ላይ ብንሆን አምላካችን እንደማይተወን ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሔርን ተስፋ ያደረገ ሰው ወድቆ አይወድቅም፤ ከወደቀበትም ይነሣል፤ ፈጣሪ ሰውን አይረሳምና። እንደማያይና እንደማይሰማ ሆኖ ዝም የሚለን ለሁሉም ነገር ጊዜ ስላለው ነው፡፡ በትዕግሥት እርሱን ተስፋ አድርጎ ለሚጠብቀው ሰው ችግሩን ይፈታለታል፤ ከመከራና ከሥቃይም ያወጣዋል፡፡ ‹‹እንደ ማይሰጥ ይዘገያል››  እንደተበለውም ለሁላችንም የሚያስፈልገንን ከእኛ የበለጠ ለራሳችን የሚያውቅ አምላክ ስለሆነ በጊዜው የወደደውንና የፈቀደውን ያደርግልናል፡፡ (ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት)

አምላካችን እግዚአብሔር “ተስፋችን ነው፤ ፈጣሪያችን መመኪያችን ነው” የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ እርሱን ያመነ ሰው ማንኛውንም የመከራ ጊዜ ማለፍ እንደሚቻለው ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ በተለይም በዚህ ጊዜ ቤተክርስቲያናችን በስደትና መከራ ላይ በሆነችበት ወቅት መለስ ብለን ታሪካችንን ልንመረምር እንደሚገባ እንወቅ! በቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደምናነበው ከሆነ፣ ቅድስት የሆነችው የእግዚአብሔር ማደሪያና የክርስቲያኖች ቤት (ቤተክርስቲያን) በየዘመናቱ በተነሡ አሕዛብ ነገሥታት ስትፈርስና ስትቃጠል  ኖራለች፡፡ በካህናትና ምእመናን ላይም ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፤ በግፍ የተገደሉ፣ ቤት ንብረታቸው በቃጠሎ አልያም በዝርፊያ ያጡ ቁጥራቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ በዚህ ጊዜ የተመለከትነውና የታዘብ ነው እንዲሁም የመሰከርነው እውነት ነው፡፡ ሰዎች ያለ ጥፋታቸው ወንጀለኛ ተብለው ሲታደኑ፣ ሲታሠሩና በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ በዓይናችን አይተናል፤ “የፍርድ ያለህ” እስክንል ድረስም ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡ “ይህ ሁሉ ለምንድን ነው በእኛ ያለ የደረሰብን?’’ ብለን መጠየቅ ግን ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ፈተና ከብዙ አቅጣጫ የሚመጣነውና። አምላካችን ለጽድቅ ሲፈትነን ጠላት ደግሞ ቀንቶ ሊያጠፋን በመሆኑ ይህንን ተገንዝበን በሕጉ በመመራትና ለሥርዓቱ ተገዢ ሆነን እንኑር! ካልሆነ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በማይመለሱ ኃጢአተኞች የሚበረታ ስለሆነ ለተቃጣ መቅሠፍትና ቅጣት እንዳረጋለን፡፡ ተስፋ ከሚያሳጡን ዋነኛ ነገሮች ኃጢአት ቀዳሚ ተጠቃሽነው፤ በጎውን ትተን ክፋት ስናስብና ስንበድል ከአምላካችን ስለምንርቅ ለመዳንም ተስፋ አይኖረንም። ኃጢአት በሠራን ቁጥር ደግሞ እግዚአብሔርን እንደ በደልን ስለምናውቅ ይቅርታን እና ምሕረትን ማግኘት እንደማንችል ማሰብ እንጀምርና ከአምላካችን እየራቀን እንዲሁም የመዳን ተስፋችን እየመነመነ ይሄዳል፡፡ በኑሯችንም በጭንቅ የተዋጠና ሰላም እና ዕረፍትን ያጣን እንሆናለን፡፡ ስለዚህም መልካሙን ሕይወት ለመኖርና በጎ ቀኖችን ለማየት ተስፋችን እግዚአብሔርን በመፍራትና ለእርሱ በመገዛት መኖር ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የክርስትና ሕይወት መንገዷ ጠባብ መተላለፊያዋም ውስን እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም “ሥርዓቱን መጠበቅ ይከብደናል” በሚል ሰበብ በተሳሳተ መንገድ መጓዝና በተጣመመ ጎዳና መራመድ መጨረሻው ገደል መግባት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ››  በማለት እንደተናገረው ይህን እውነት ለተረዳ ሰው የመኖር ትርጉሙን ማወቅ ይቻለዋል፤ (ሉቃ. ፲፫፥፳፬)  ‹‹እኔ መንገድና እውነት፣ ሕይወትም ነኝ››   በማለት አምላካችን ተናግሯልና፤ (ዮሐ. ፲፬፥፮) ትክክለኛው መንገድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተው፣ መከራ መስቀሉን የምንቀበልበት፣ ለእርሱ ፍቅር ስንል ሥጋችንን የምናራቁትበት ከፍ ሲልም ሰማዕት የምንሆንበት የክርስትና ሕይወት ነውና፡፡
አምላካች ንእግዚአብሔር ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ አሜን! መልካም ሰንበት! ምንጭ፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን

የባዕድ ምድር ባለርስቶች

   እንደ ዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብ ምንጮች ቁጥሩ፣ ወደ ሁለት ተኩል ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይኖራሉ። አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ደግሞ የአብዛኞቹ ነባር መዳረሻ ሲሆኑ ቁጥሩ የማይናቅ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በአውስትራሊያ፣ በሩቅ ምሥራቅና በአፍሪካ ውስጥ ይገኛል።እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ለተሻለ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔሀብታዊ(Economic) ሕይወት በሄዱባቸው ሀገራት ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፅሙበት ቦታና ሁኔታ ማግኘት ነው። በተለይ አኀት አብያተክርስቲያናት እንኳን በማይገኙባቸው አካባቢዎች ሕፃናት ሳይጠመቁ፣ አዋቂዎች ንስሀ ገብተው ወደ መስዋዕተ ወንጌል ሳይቀርቡ፣ የቅዳሴው ድምፅ፣ የዕጣኑ መአዛ እየናፈቃቸው ይኖራሉ።

በዚህ ኑሮ ውጥረት በሆነበትና ራስን ለማሸነፍ የማይሆነውን ለመሆን በሚገደዱበት የስደት ሕይወት የልጆቿን ጥያቄዎች መሠረት አድርጋ ሐገረ ስብከቶችን መመሥረት የጀመረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአሁን ሰዓት በውጪው የዓለም ክፍል ወደ ፳፭ አኅጉረ ስብከቶች ያሏት ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የሀገረ ስብከቶች ቁጥር ሢሶውን(1/3) ይሸፍናል።በውጪው ዓለም የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ መስፋፋት የተጀመረው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ደግሞ የሥርጭት አድማሱ ተስፋፍቷል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ግሪክና የካረቢያን ሀገራት ሕጋዊ ሰውነትንም መጎናጸፍና የልዩ ልዩ ኅብረቶች አባል እስከመሆን ደርሳለች።

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በኪራይ በሚገዙ አዳራሾች፣ ከአኀት አንዳንዴም ባስ ሲልም ከምሥራቅ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ አብያተክርስቲያናት ጋር በፈረቃ ሥርዓተ አምልኮን በመፈፀም ነው። ይህ ደግሞ በሀገራቸው ከለመዱት አንጻራዊ ነጻነት የማምለክ፣ የመማማር ዕድልና በፈለጉበት ሰዓት ወደ ቤተክርስቲያን በመምጣት ብሶታቸውንም ሆነ ምስጋናቸውን ከማቅረብ ፍላጎታቸው ጋር የማይስማማ ነው። በኪራይም ሆነ በውሰት ቦታዎች ላይ ቅዳሴው አለቀ አላለቀ፣ መርሐግብር ተዘረጋ ታጠፈ፣ የአከራዮቻቸው ችግር አይደለም። በመሆኑም እንዲወጡ ወይም ኪራይ እንዲጨምሩ ይደረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ የራስ ቤተመቅደስ መገንባት ወይም መግዛት ብቻ መሆኑን በመረዳታቸው አብያተ ክርስቲያናት ፊታቸውን ወደዚህ ለማዞር ተገደዋል።በዚህ በያዝነው የታኅሣሥ ወር ውስጥ ብቻ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በአሜሪካ ግዢው ተከናውኗል። በተያያዘም በእንግሊዝ ሎንደን የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም የግዢና ዕድሳት ወጪ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል። ባሳለፍነው ኅዳር ወር ደግሞ በቻይና የደብረ ምሕረት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተባርኮ ጀምሯል። ከዚህ ቀደም በካሊፎርኒያ፣ በኳታር፣ በጀርመንና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መሰል ተግባራት ተጀምረዋል፣ እየተከናወኑም ነው።

እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት መግዛትና መገንባት የዕለት ጉርስ ፍለጋና የቤተሰቡን ሕይወት ለመቀየር ከሀገር ለወጣው ለስደተኛው ምእመን ቀላል ነገር አይደለም። የ፳፻፲፮ቱ የእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት የክብር ተሸላሚውና ለሦስት የውጭ አብያተክርስቲያናት ግንባታና ግዢ ገንዘብ ያሰባሰበው ኮሜዲያን እሸቱ ሲናገር “ኢትዮጵያውያን በየሀገራቱ በቁጥር አናሳ ናቸው። ብቻቸውን ይህን ማድረግ አይችሉም። ያሉትም ከጉድለታቸው ቀንሰው አብያተክርስቲያናትን እያነፁ ነው። ይሄ ቅንጦት አይደለም ለዛም ነው ገቢ የምናሰባስበው” ይላል። አብያተክርስቲያናቱ የሚገዙት በብድርና ዕርዳታ ነው። “ኢትዮጵያውያን በሰው ሀገር የብድር ዕይታቸውን አስተካክለዋል” የሚሉት ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ናቸው።በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን በባዕድ ምድር ባለርስት ማድረግ የቦታ ባለቤት በማድረግ ብቻ የሚወሰን አይደለም ይልቁንም ቤተክርስቲያን በባዕድ ከተሞች ልቡ ከቤተክርስቲያን የተሰደደበት ስደተኛ ልጇና ከኢትዮጵያ ውጫ በተወለደው ልጇ ልብ ላይም ባለርስት የሚያደርጋት ጭምር ነው። ካህናትና ምእመናን ያለመሳቀቅ ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚያደርሱበት፣ ሕፃናትና ወጣቶች በሥነምግባር ታንፀው ስለ ቤተክርስቲያን የሚማማሩበት፣ ደስ ሲሰኙ መዝሙር የሚዘምሩበት፣ ሲከፋቸው ከዓለም ፊት የሚሸሸጉበት ጭምር ነው። አያድርገውና እንደ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካው ኢትዮጵያውያንን  ዓላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲከሰቱም ብቸኛ መጠለያ ካምፓቸው ቤተክርስቲያን ናት። የእነዚህ ቦታዎች መኖር የምስካየ ኅዙናንነት ተልእኮዋን ያስፋፋዋል። ከራሷ አልፎ ለኤርትራውያን ወንድሞችም ጭምር የእነዚህ አብያተክርስቲያናት መኖር የተስፋ ምልክት ነው።በዚህ ሳይገደብ እነዚህ ይዞታዎች የወንጌል  ብርሃን ያልበራላቸውን የሀገሩን ነዋሪዎች ወደ ክርስቶስ አካልነት የመጥራት ምቹ ዕድልም በመስጠት በሀገሬው ልብ ውስጥም ባለ ርስት እንድትሆን ያደርጋታል። በመጣውና በሄደው ነገር ሁሉ የሚከፋፈለውን ስደተኛ ማኀበረሰብ ኅብረት አጠናካሪ ጭምር ነው። የዛሬውን በዚህ አበቃን አምላከ ቤተክርስቲያን በውስጥም በውጪም ያሉ ልጆቿን ይጠብቅ! ምርኮዋንም ያብዛ!

ከኔሮን ቄሣር እስከ ዳክዮስ መጀመሪያ

ከዘመነ ሐዋርያት አንስቶ በተለያዩ ሀገራት ላይ የሠለጠኑ አረማውያን በቤተክር ስቲያን ላይ ያደረሱት ስደት በዘመኑ የነበረውን ክርስትና ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ያሳያል። ቅድስት ቤተክርስቲያን የጸናች ናትና ሥጋቸውን እንጂ ነፍሳቸውን ማንም ሊገድል እንደማይችል እያስተማረች የማያልፈውን ዓለም እያሰቡ ከክርስቶስ ጋር መኖርን እንዲናፍቁ ታደርጋቸው ነበር። በጊዜው የነበራቸውን ቆራጥነት፣ ለሃይማኖታቸው ሲሉ የሚያሳዩትን ጭካኔ በአላውያን ወታደሮችና ነገሥታት ዓይን የሚያስደንቅ ነበር።

ክርስቲያኖቹ ከቤተ አይሁድ ይደርስባቸው የነበረው ግፍና መከራ ይልቅ ከቤተ አሕዛብ ይደርስባቸው ከነበረው በአንጻሩ የባሰ ነበር። በተለይ በሮማውያን ዘንድ የነበረው አምልኮተ ጣዖት በሀገራቸው ውስጥ ረሃብ፣ ችግርና ቸነፈር ሲነሣ በክርስቲያኖች ምክንያት አማልክቶቻቸው ስላዘኑ እንደደረሰባቸው ያስወሩና በክርስቲያኖችም ላይ ስም የማጥፋትን ዘመቻ ያሴሩ ነበር።የሕዝቡን ልብ በክርስቲያኖች ላይ ለማነሳሳት በኔሮን ቄሣር ዘመነ መንግስት በንጉሡ ኔሮን ሮም በእሳት እንድትጋይ ሆናለች። ቀድሞውን ይደርስባቸው የነበረው መከራና እንግልት በአዋጅ ጸድቆ ክርስቲያኖች በያሉበት ተሳደው እንዲገደሉ የሚል ትዕዛዝ ወጣ። ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚሁ በኔሮን ዘመነ መንግስት ነበር። የሰማዕታቱን ዜና የሰሙ ከሮም ውጭ ይኖሩ የነበሩ ማኅበረ ምእመናን ይኽንን ክብር ለመቀበል በገፍ ወደ ሮም ይተሙ ነበር ።

ኔሮን ቄሣር በ፷፰ ዓ.ም. ከሞተ ወዲህ ላሉት ሁለት ዓመታት ሁለት ቄሣሮች ነግሠዋል። በቤተክርስቲያን ታሪክ ከ፸ – ፻፷፪ ያለው ዘመን የመሸጋገሪያ ጊዜ ተብሎ ይጠራል። በእኒኽ ዓመታት ውስጥ ሐዋርያውያን አበው (በርናባስ፣ ቀለሜንጦስ ዘሮም፣ ፖሊካርፐስ፣ ሔርማ፣ ዲዮናስዮስ፣ ፓፒየስና አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ) በእግረ ሐዋርያት ተተክተው ሲያስተምሩ የነበረበት ወቅት ነው። ከኔሮን ቄሣር በኋላ የተነሣው ወንድሙ ድምጥያኖስ ምስሉን በኤፌሶን አሰርቶ እንዲሰገድለት ትዕዛዝ አወጣ። በወቅቱ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ) ሀገረ ስብከቱ ነበረችና ሐዋርያዊ ተልዕኮውን እየፈጸመ ነበር። ይኽንን የድምጥያኖስን ተግባር አውግዞ፣ ከነበሩት የኤፌሶን ክርስቲያኖች ጋር ተቃወመ። በኋላም በድምጥያኖስ ትዕዛዝ ወደሮም ፍርድ ቤት ሄዶ ወደ ፍጥሞ ደሴት እንዲጋዝ ተደርጓል።

ከድምጥያኖስ በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ ከነበረው ጭካኔ በኋላ ከ፺፰ – ፻፲፯ ዓ.ም. የነገሠው ጨካኙ ቄሣር ትራጃን ነበር። በኃይል ብቻ ሳይሆን በዘዴና በማስፈራራት ጭምር ክርስቲያኖች ወደቤተ ጣኦት ለመመለስ ይሞክር ነበር።በአገዛዝ ቀንበራቸው በታሪክ ከነበሩ ነገሥታት ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ግፍ እጅጉን የከፋ ስለነበር በተለየ መልኩ ይጠቀሳሉ። ከትራጃን በኋላ ሀድርያን የተባለ ንጉሥ ፻፲፯ – ፻፴፰ የነገሠ ሲሆን ከበፊቱ ይልቅ መጪዎቹ ፵ ዓመታት ለክርስቲያኖች በአንጻራዊነት የእፎይታ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ሀድርያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት እንዳይገደሉ ትዕዛዝ አውጥቶ ነበር። ከእርሱ በኋላ የተነሣው አንቶኒዮስ ፒየስ ፻፴፰ – ፻፷፩ አንዳንድ ሕጎችን ከማሻሻል ውጪ ቀድሞ የነበረውን የአገዛዝ ስልት ይከተል ነበር። ሕዝቡ ክርስቲያኖች ላይ መከራ ሲያደርስ ግን አይከላከልላቸው። ከሐዋርያን አበው መካከል ቅዱስ ፖሊካርፐስ በ፻፶፭ ሰማዕትነትን የተቀበለው በአንቶንዮስ የንግሥና ዘመን ነበር።ከ፻፷፩-፻፷፫ የነገሠው ፈላስፋው ንጉሥ ማርቆስ አብሪሊዮስ “ክርስቲያኖች ሞገደኞች፣ ወፈፌዎች ናቸው” ይል ነበር፡፡ከ፻፹-፻፺፪ የነገሠው ቄሣር ከሞዶስ ቀስ በቀስ በዘዴ እያደረገ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ዕቅድ ነበረው፡፡ ሌሎችም እንደእነ እስክንድሮ – ሳዊሮስ (፪፻፳፪-፪፻፴፩)፣ እንደእነ ፊልጶስ ዓረባዊ (፪፻፵፬-፪፻፵፱) ያሉ ንቀውና ተጸይፈው ክርስቲያኖችን ከምንም አይቆጥሯቸውም ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የመጨረሻውን ድል ለማግኘት ብዙ ቄሣሮች ባላቸው ኃይልና ዘዴ በሙሉ ተጠቅመዋል፡፡ የመጨረሻውና የማያዳግመው ዘዴ ግን በዳክዮስ ዘመነ መንግስት (፪፻፵፬-፪፻፶፩ ዓ.ም.)የወጣው ዐዋጅ ነው፡፡

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

        የዚህ ቅዱስ የአባት ስም እስጢፋኖስ እና የእናቱ ስም አመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጎች ናቸው። በአክሱም ምድርም ወለዱት፤ በአደገ ጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት አስተማሩት። አባቱና እናቱም በሞቱ ጊዜ ወደ ደብረ በንኰል ገዳም ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሔዶ የምንኵስና ልብስን ለብሶ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ፈጽሞ ከሻገተ ጎመን በቀር አይበላም፤ የሚጠጣውም ውኃ ነው። እህል በመፍጨትና ውኃ በመቅዳት ሥራ መነኰሳትን ይረዳቸው ነበር። ዘመዶቹም ወደርሱ እየመጡ በአስቸገሩት ጊዜ ወደሌላ ቦታ ሔደ። እግሮቹም እስኪያብጡ ድረስ በጾም በስግደት በመቆም ተጋደለ። ከዚያም ወደሌላ በረሀ ሔዶ አርባ መዓልት፣ አርባ ሌሊት ምንም ምን ሳይቀምስ ኖረ። አንበሶችና ነብሮች የሚያስፈሩም አራዊት ሁሉ ወደርሱ በመምጣት ይሰግዱለታል፤ የእግሮቹን ትቢያ ይልሱ ነበር። በአንዲት ዕለት በጎዳና ሲጓዝ ታላቅ ወንዝ ውኃው መልቶ አገኘ። መጽሐፍና እሳትም ከእርሱ ጋር ነበር፤ ጸሎትም አድርጎ ወደ ውኃው ገባ። ውኃውም ዋጠውና ወደታች አወረደው በእግዚአብሔርም ኃይል ወደማዶ በጣለው ጊዜ መጽሐፉ ሳይደመሰስ እሳቱም ሳይጠፋ አገኘው።

ሰይጣንም በሚያስፈሩ አራዊት እየተመሰለ ይፈታተነው ነበር። እርሱ ግን ፈጣሪውን በመታመን ልቡ የታሠረና የጸና ስለሆነ አይፈራም። እርሱም ሲጸልይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ። በምራቁም መላ ሕዋሳቱን ቀብቶ ኃይልን አሳደረበት፤ ከዚያችም ዕለት ጀምሮ እግሮቹን የሚያሥር ሆነ። ማቅንም ለብሶ በየሌሊቱ ሁሉ ከውኃ ውስጥ በመግባት የዳዊትን መዝሙር አምስት ጊዜ ያደርሳል። ቊጥር በሌለውም ግርፋት ጀርባውን ይገርፍ ነበር።አንበሶችም በበዓቱ አጠገቡ ይሰማራሉ፤ እርሱም አካላቸውን ይሰፍራል፣ ይለካል፣ ቊስላቸውንም በጥቶ እሾህና አሜከላ ያወጣላቸዋል። ከዚህም በኋላ ብዙ ደቀ መዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ፥ በተጋድሎም ተጠመዱ። ከእነርሱም የመጀመሪያው አባ ዘሩፋኤል ነው። በአንዲትም ዕለት በገዳመ ለጋስ የሚኖር ከአባ ገብረ መስቀል ጋር ተገናኘ። ከዚህም በፊት አልተያዩም ነበ፤ የእግዚአብሔርንም ገናናነት ሲጨዋወቱ ዋሉ። በራት ጊዜም ጸሎትን ሲያደርጉ የተዘጋጀ ማእድ ወርዶላቸው ተመግበው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት ከአንድ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ። እግዚአብሔርም ያደረገላቸውን ምሥጢር በሚነጋገሩ ጊዜ አባታችን አባ ሳሙኤል እንዲህ አለ “እነሆ እኔ በአርያም ቁሜ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የአምላክን መንበር ሳጥን ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነኝ።” ለመቀደስም በሚገባ ጊዜ ኅብስትና ወይንን የተመላ ጽዋ ይወርድለታል። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ውዳሴዋን ሲያነብ ክንድ ያህል ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ ይላል። እመቤታችን ማርያምም ወደ እርሱ መጥታ የሚያበራ ዕንቊንና ንጹሕ ዕጣንን ሰጠችው።ፍልሰቱም ሲቀርብ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በክንፎቹ ተሸክሞ አወጣው። ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ተድላዋን ሁሉ አሳየው፤ ወደ ልዑል እግዚአብሔርም ዙፋን ፊት አቅርቦት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ተቀበለ። ወደ በዓቱም ሲመለስ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ ታኅሣሥ ፲፪ ቀን በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን! እኛንም በአባ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን! በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር! ለዘለዓሙ አሜን።

ምንጭ፦ የታኅሣሥ ፲፪ ስንክሳር

ፍቅር

በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር የወሰነ ሰው ሰውን ሁሉ ሊወድ ይገባል፡፡ ፍቅር ሲባል ፍትወታዊ የጾታ ፍቅር ሳይሆን ሁሉንም ሰው ሳይለያዩ መውደድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግጋት ሁሉ ፍቅርን ያስበለጠው፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲጠቅስ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ  ናስ ወይም እንደ ሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፤ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና ዕውቀትን  ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈርስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፤ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል፣ አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም…(፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፩) በማለት አስረድቷል፡፡

በክርስቲያናዊ ሕይወታችን በእምነት መነጽርነት እግዚአብሔርን ማየት የምንችለው ፍቅርን መሠረት ያደረገ ሕይወት ሲኖረን መሆኑን «እግዚአብሔር ፍቅርነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል» በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፮) ሀብተ ወልድ እና ስመ ክርስትና አግኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓ ሜሮን ተቀብቶ የከበረ ክርስቲያን ሁሉ ፍቅር ማለት እግዚአብሔርን የምናይበት የኅሊና መስታውት መሆኑን ተገንዝቦ በፍቅር ሊኖር ይገባዋል፡፡

ያለ ፍቅር ምንም ዓይነት ሥራ ቢሠራ ዋጋ የለውምና ፍቅርን ገንዘብ እናድርግ፡፡ ያለ ፍቅር ከሚሆን ብዙ ሥራ ይልቅ በፍቅር የሚሆን ትንሽ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነውና ፍቅርን እናስብ፣ በፍቅር እንኑር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነውና እርሱን እንምሰል፡፡ ስለ ፍቅር ሰው ሆኖ የተሰቀለልንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን እኛም ለወንድሞቻችን ፍቅርን እንስጥ፡፡ በፍቅር እየኖርን የምናደርገው መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ፍሬ አፍርቶ የምናየው በፍቅር መኖር ስንችል ነው፡፡ አባቶቻችንን እናስብ፡፡ ገድል የፈጸሙት፣ ተኣምር ያደረጉት፣ ታሪክ የሠሩት፣ ስማቸውን በሰማይ መዝገብ ያሰጻፉት በፍቅር መኖር በመቻላቸው ነው፡፡ በፍቅር ስለ ፍቅር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ መልካም ሰንበትምንጭ ፦  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ (በመምህር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ)

ክርስትና በሶሪያ: መፈንቅለ መንግስት የወለደው ሥጋትና ተስፋ

ከጦርነት በፊት ከጠቅላላ ሕዝቧ ዐሥር ከመቶው ክርስቲያን እንደነበረ የሚነገርላት ሶሪያ የዛሬ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነበር። በዓረብ የፀደይ ዐብዮት ነበር ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት የገባቺው። ከኃምሳ ዓመታት በላይ ሶሪያን የመራው የበሽር አላሳድ ቤተሰብ ለውጥ በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች፣ በአይ. ኤስ. አይ. ኤስ. እና መሠል አክራሪ ሙስሊሞች የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ቢቆይም በኅዳር ወር መጨረሻ ሳምንታት የደረሰበትን ምት መቋቋም ባለመቻሉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትና ቤተሰቦቻቸው ስልጣንና ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሩሲያ ከኮበለሉ አስር ቀናትን ተሻግረዋል። የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድን ከሀገር መኮብለል ተከትሎ ሀገሪቱን ኢስላማዊ ተዋጊ ሃይሎች ተቆጣጥረዋታል። በተለይም ሀያት ታህሪር አል-ሻም ዌም (HTS) ተብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ደማስቆን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን የመቆጣጠር እድል አግኝቷል። የአላሳድ ውድቀትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ይገኛል።

በበሽር አላሳድ ከስልጣን መነሳትና የእስላማዊ ቡድኖች መተካት ከደስታ ይልቅ ስጋት ያረበባቸው ክርስቲያኖች ናቸው። ባለፉት ዐሥራ ሦስት የእርስ በእርስ ጦርነት ዓመታት እኒህ ክርስቲያኖች በልዩነት የጥቃት ሰለባዎች በመሆናቸው ከጦርነቱ በፊት ከነበራቸው የዐሥር በመቶ ሀገራዊ የሥነ ሕዝብ ድርሻ ወደ ሁለት በመቶ ወርደዋል። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ምእመናን በጅምላና በነጠላ ተገድለዋል። ብዙዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ይህ ታሪክ ከመፈጠሩ ከሺህ ዘመናት በፊት ግን ሦርያ የክርስቲያኖች መናኸሪያ ነበረች። በአንፆኪያና በደማስቆ ታላላቆቹ ሀዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ አስተምረዋል። ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ መናብርትና ከሁለቱ ጥንታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሚገኙት በሶሪያዋ አንፆኪያ ነበር።

ሶሪያ በኒቂያ ከተሰበሰቡ ሠለስቱ ምዕት የሃያው ሀገር ናት። በዚህች ምድር አግናጢዮስ ምጥው ለአንበሳና ቅዱስ ኤፍሬም በቅለውባታል። ነገር ግን የዐረብ ወረራና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የኦቶማን እንቅስቃሴ ሶሪያውያን ክርስቲያኖች አንፃራዊ የእምነት ነፃነት ወደሚያገኙባቸው ሀገራት እንዲሸሹ አልያም በሀገራቸው ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ አስገድዷቸዋል። በዐሥራ ስምንት መቶዎቹ እንኳን በተካሄደ የኦቶማን ጭፍጨፋ ከ፺ ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ተገድለዋል።ዛሬ ላይ የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ የሶሪያ ክርስቲያኖች በከባድ ውጥረት ላይ ናቸው። በተለይ ከአል አሳድ ሽሽት በፊት ክርስቲያኖች በስፋት በሚኖሩባት በአሌፖ የአማፂው ቡድንና ደጋፊዎቻቸው የጥቃት ኢላማ መሆናቸው መጪውን ጊዜ በፍርሃት እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።vከሦርያ ክርስቲያኖች ውስጥ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሦስተኛውን ይይዛሉ። የተቀሩት በክርስቲያን ምድብ የሚካተቱት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የአሲርያንና የመናፍቃን ቡድኖች ናቸው።የመንግስት ግልበጣው ሲካሄድ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ህንድ የነበሩት የሶሪያ (ያዕቆባዊት) ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ሞር አግናጢዮስ ኤፍሬም ፪ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ከወገኖቻቸው ጋር የሚመጣውን ለመጋፈጥ ወደ ሶሪያ ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሶሪያ መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ በሶሪያ መንበረ ፓትርያርክና በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና አገልጋዮች ጋር የተወያዩ ሲሆን ከሀገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች ጋር በመገናኘትም ክርስቲያኖች የሀገሪቱ ጠቃሚ አካል እንደመሆናቸው ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅ ከመንግስት ቃል እንደተገባላቸው ከውይይቶቻቸው በኋላ በመንበረ ፓትርያሪካቸው በኩል በወጣው መግለጫ አንስተዋል።

ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አዕምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና ዐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊል ፬÷፮-፯ በሚል ርእስ ባወጡት መግለጫ ምእመናንና አገልጋዮች ከመቼውም ይልቅ በፆምና በጸሎት እንዲሁም የሀገሪቱን ሁኔታ በንቃት በመከታተል እንዲያሳልፉ፣ መንግስት የአናሳዎችን መብት እንዲያስጠብቅ፣ ፓሊሶችና የጦር ኃይሎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በውጭ ያሉ ሀገረስብከቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል። ፓትርያሪኩ “የሰላምና የተስፋ ምንጭ የሆነውን የጌታችን የልደት በዓል ከፊት እየጠበቅን ሰላምና ብልፅግናን ለሀገራችን እንዲያመጣልን እንመኛለን” ብለዋል። ብፁዕ አቡነ ሞር ቡትሮስ (ጴጥሮስ) ቀሲስም ሶሪያውያን ክርስቲያኖች እውነታውን በመረዳት፣ በንቃትና በእምነት ሆነው እንዲጋፈጡ ምእመናንን እያበረታቱ ይገኛሉ።የሦርያ ክርስቲያኖች ከአል አሳድ መነሳት በኋላ የመንግስትን ቃል አምነው ያሳለፍነው እሑድ ቤተ መቅደሶቻቸውን ቢከፍቱም አክራሪዎችን ማመን የሚያስከፍለውን ዋጋ ያውቃሉና ዛሬም በስጋት ልብ ውስጥ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ።በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሶሪያ አሌፖ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማጋር አሽካሪን “ፍጹም የሚባል ደኅንነት የለም፤ ነገር ግን እንደ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። እንደ ዐሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ እናምናለን። ብለዋል።እግዚአብሔር በምድረ ሶሪያ መረጋጋትን ለቤተክርስቲያን ደግሞ ሰላምና ፍፁም አንድነትን እንዲሰጣት እንድንጸልይ እያሳሰብን የዛሬን በዚህ አሳረግን።

እንዴት ንስሐ እንግባ???

ንስሐ :- ነስሐ ከሚል የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ሐዘን፣ ፀፀት፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ንስሐ ገባ ሲባልም ዐዘነ፣ ተፀፀተ፣ ተመለሰ፣ ክፉ አመሉን ተወ ማለት ነው፡፡ ንስሐ አንድ ሰው በሠራው ጥፋት፣ ባደረገው ስህተት፣ በፈፀመው ኃጢአት ማዘኑንና መፀፀቱን ዳግመኛም ያንን የመሰለ ኃጢአት ላለማድረግ የሚወስነው ውሣኔ ነው፡፡

እንዴት ንስሐ ይገባል?  ፩. ከራስ ጋር መሆን:- ንስሐ መግባት የራስ ፈቃድ ይጠይቃል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ንስሐ እንዲገባ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ሊድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ እንደሚወዱም ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ጢሞ.፪፥፫ ላይ ነግሮናል።

፪. ምክንያትንና ለራስ ይቅርታ ማድረግን ማስወገድ:–  በንስሐ ሕይወት ለመኖር የምንሻ ከሆነ ለወደቅንበት ኃጢአት ምክንያት መደርደርና ለራሳችን ይቅርታን ለመስጠት መሞከር የለብንም። ኃጢአትን ከፈፀሙና ከሠሩ በኋላ ለኃጢአት ያበቃ ሌላ ምክንያት ማቅረብና በዚያም አንፃር ለመጽናናት መሞከር በራሱ ኃጢአት ነው። በዚህ ዓይነት ለኃጢአቱ ምክንያት እየደረደረ የሚጽናና ሰው ኃጢአትን እየለመደ ወደ ባሰ አዘቅት ከመውረድ በቀር ንስሐ ለመግባት አይችልም። ምንም ምክንያት ቢደረደር ኃጢአት ምንጊዜም ኃጢአት ነውና ለሠራነው ኃጢአት የተለያዩ ምክንያቶችን በማበጀት ራሳችንን እያጽናናን ነፃ ለመሆን መጣር የለብንም፣

፫. ንስሐ ለመግባት አለመዘግየት (አጋጣሚውን መጠቀም) :-  አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ለመግባት የገጠማቸውን የተመቻቸ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት በመቅረት ዕድሉ አምልጧቸዋል። እግዚአብሔር ሰው ሁሉ ኃጢአቱን መርምሮ ወደ ንስሐ እንዲመለስ፣ የተቀደሰ ጸጋውን ሊያድለውና በልቡናውም አድሮ ለመሥራት አብዝቶ ይሻል። ሰው በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ንስሐ ሊገባይችላል። ለምሳሌ:- በመጻሕፍት ፣ በዝማሬ ፣ በበሽታ፣ በአደጋ፣ በሞት ወዘተ. ተመክሮ ንስሐ ሊገባ ይችላል። በእነዚህ አጋጣሚዎች የሚጠቀምባቸው ሰውም አስተዋይ ነው። የጠፋው ልጅ “ተነስቼ ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ” ሲል እንደተናገረና ከአባቱ እንደታረቀ ወደ ቤቱም እንደ ተመለሰ። ሉቃ. ፲፭፥፲፰ የማያስተውል ሰው ደግሞ ኤሳውን ይመስላል። ኤሳው ብኩርናውንና በረከቱን ሁሉ ከአጣ በኋላ ወደ አባቱ ገብቶ በረከቱን ታናሽ ወንድሙ እንደ ወሰደበት ባወቀ ጊዜ “ታላቅ፣ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ። ቃሉንም አንሥቶ አለቀሰ።” ዘፍ. ፳፯፥፴፬-፴፰ ፬. ልብን አለማደንደን፣
፭. መሰናክሎችና የኃጢአት ምንጮችን ማስወገድ፣
፮. ለኃጢአት ጊዜ አለመስጠት፣
፯. ጠባይን መመርመር:- ከድብቅ ኃጥያቶች መጠንቀቅ፣
፰. ከሚወዱት ኃጢአት በመሸሽ ደካማ ጎንን ማረም፣
፱, ዘለዓለማዊውን ሕይወትና የሚጠበቅብንን ማሰብ፣
፲. የኃጢአትን ፍቅር ለማስወገድ ፍቅረ እግዚአብሔርን ማጽናት፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ወደ ንስሐ በሚወስደው የሕይወት ጎዳና ላይ ማንኛውም ሰው ሊከተላቸው የሚገቡ መርሖዎች ናቸው። ዋቢ መጽሐፍ:- የንስሐ ሕይወት (ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ወንድምአገኘሁ)

ቅድስት አርሴማ ድንግል

እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና “የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ  ይታያል:: ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት:: ቅድስት አርሴማ “ይሕ ቀረሽ” የማይሏት ውብ ናት:: ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት:: ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት:: ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት።

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:- አበው በትውፊት እንደነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ታላቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1)ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት፣
2)ትምህርተ ቤተክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት፣
3)የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር:: ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ)ን ጻድቃን የምንላቸው:: በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ 127 ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለመኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ:: በዚያም በድርጣድስ ቤተመንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው:: ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ “ካላገባሁሽ” አላት:: ድንግሊቱ ግን “እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም” አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው:: አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት:: ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን አደረገ:: የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራዕይ “ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን።” “ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም” አላቸው:: ወዲያውም  ቆፍረው አወጡት:: ቅዱሱ እንደወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን
አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሔዶ ፈወሳቸው::
የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ሃገራችን እንደመጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ / ኩላማሶ/ስባ/ውስጥ የሚገኘው) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና:: ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት “በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::”

የኤርትራው አዲሱ የፓትርያርክ ምርጫና ፈተናዎቹ

ከፍተኛ የሃይማኖት ነፃነት ችግር አለባት ተብላ በምትታማው ኤርትራ ውስጥ ፈቃድ ከተሰጣቸው አራት የእምነት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነችው የኤርትራ ቤተክርስቲያን በኅዳር ፴/፳፻፲፯ ዓ. ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን ፮ኛው ፓትርያርክ አድርጋ መርጣለች።

በዚህ ምርጫ ላይ 85 የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ጨምሮ የየገዳማቱ ተወካዮች፣ የአኅጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የነገረ መለኮት ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል። በምርጫው ላይ በብፁዕ አቡነ ዳንኤል የማዲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሚመራ 5 የግብፅ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተገኙ ሲሆን በምርጫው ላይ ከቀረቡት ዕጩ ፓትርያርኮች ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ: ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ: የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ: የደቡብ መንደፍራ ሊቀጳጳስ መካከል ብፁዕ አቡነ ባስሎዮስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመርጠዋል።

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ጀምሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠልና በሁለቱ ሀገራት መካል በተከሰተ ግንኙነት መሻከር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተነጥላ እስከ ፲፱፻፺፩ በግብፅ ቤተክርስቲያን ሥር የነበረች ሲሆን ከ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዕውቅና በአፍሪካ ምድር ሦስተኛዋ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንበረ ፓትርያርክ ሆናለች። የቤተክርስቲያኒቱ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ፊሊጶስ ከ፲፱፻፺፩ ጀምሮ ለሁለት ዓመት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ለ 2 ዓመት በፓትርያርክነት መርተው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ ሲሆን ሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ከተሾሙ ሁለት ዓመት በኋላ በሀገሪቱ መንግስት ጫና ከፕትርክና እንዲነሱ ተደርገዋል።
የኤርትራ ቅዱስ ሲኖዶስ ዘግየት ብሎም በቅዱስነታቸው ላይ ያስተላለፈው ውግዘት ቤተክርስቲያንን ለሁለት የከፈለ ሲሆን በርካታ በአሜሪካ፣ አውሮፓና፣ አውስትራሊያ የሚገኙ ጳጳሳት፣ ማኀበረ ካህናትና ምዕ
እመናን ውግዘቱን በመቃወም ከእርሳቸው በኋላ የተነሱትን ሁለት ፓትርያርኮች ማለትም ለ፯ ዓመታት ቤተክርስቲያኗን ለመሯት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና በተሾሙ በዓመታቸው ላረፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ዕውቅና ሳይሰጡ ቀርተዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ውግዘት፣ የ፰ ዓመታት ግዞትና ፖለቲካዊ የቁም እስር የኤርትራ ቤተክርስቲያንን ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ መገለልና ጫና በማምጣቱ ምክንያት ቤተክርስቲያኒቷ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለ ፓትርያርክ በዓቃቤ መንበር እየተመራች ግንኙነቷን ማደስ ላይ ትኩረቷን ስታደርግ ቆይታለች።

እኒሁ በዲያስፖራው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አኅጉረ ስብከቶች ከ፮ኛው የፓትርያርክ ምርጫ ቀደም ብሎ ባወጡት መግለጫ በ፳፻፲፭ ዓ.ም. ያረፉት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ውግዘት ባልተነሳበትና ዕርቀ ሰላም ባልተከናወነበት የሚካሄደውን ምርጫ እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል። የ፮ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሲመት በጥር ፲፰/፳፻፲፯ በታላቁ የአስመራ ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ይካሄዳል። የብጹዕ አቡነ ባስሊዮስን መመረጥ በታህሳስ ፪ ሳምንታዊ የረቡዕ ትምህርት ታላቅ ስኬት ብለው የጠሩት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ታዎድሮስ የኤርትራ ቤተክርስቲያን ለተልዕኮዋ፣ ለአንድነቷና ለክርስቶስ ክብር እንድትተጋ ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክም ለመላው የኤርትራ የካህናትና ምእመናን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላፈዋል።

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት፡

ኢያቄምና ሐና ቃል ኪዳናቸውን ለመፈጸም ዘመዶቻቸውን ባልንጀሮቻቸውን ከነልጆቻቸው በመጥራት፣ ሕፃን ልጃቸውን እመቤታችንን ልዩና ንጹሕ ልብስን አልብሰው በመንፈሳዊ ዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ መብራትን በእጆቻቸው ይዘው እያበሩ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ወሰዷት። ያን ጊዜም ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ በካህናቱ ታጅቦ የምስጋና ዝማሬን ከልኡካኑ ጋር እያሰማ እነርሱን ለመገናኘት ከመቅደስ ወጣ።በዚያም ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወደሚገባበት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚያስወጡ ፲፭ ደረጃዎች ሲኖሩ በየደረጃዎቹም መዝሙረ ዳዊት ተደጋግሞ ሲደረስባቸው ከሚጸለዩት የዳዊት መዝሙራት መካከል መዝ ፻፲፰(፻፲፱)፣ ፻፴፪ (፻፴፫) የሚገኙ ሲኾኑ እነዚኽንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አጥኚዎች “Psalms of Ascent” (የመውጣት መዝሙራት) ይሏቸዋል::

እናትና አባቷም ሊቀ ካህናቱን ካለበት ቅዱስ ቦታ ወደነርሱ እስኪመጣ ለመቆየት ልጃቸው ማርያምን ከአንደኛው ደረጃ ላይ ቢያኖሯትም እርሷ ግን በድንቅ አምላካዊ ሥራ መንፈሳዊ ኀይልን ተመልታ የሦስት ዓመቷ እመቤታችን ያለምንም ረዳት ብቻዋን ደረጃዎቹን በመውጣት በእጅጉን ወደተቀደሰው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወዳለበት ስፍራ ኼደች ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ባረካት።

ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሊቀ ካህናቱ የሰው ዘርን በመላ ወደ ገነት የሚያስገባ፣ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የእግዚአብሔር ልጅን የምትወልደው እርሷ እንደኾነች ገለጸለት። ቦታዋም በጣም የተቀደሰውና እርሱ መሥዋዕት ለማቅረብ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገባበ፣ ከእርሱ በቀር ማንም ሰው የማይገባበት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መኾኑን ገልጾለታል ፡፡ እርሱም ይኽንን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራን በማድነቅ፣ ይኽቺን የመሰለች ልጅ ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምንስ እናጠጣታለን? ምን እናነጥፍላታለን? ብሎ ሲጨነቅ ለእስራኤል ደመና ጋርዶ መናን አውርዶ የመገበ፣ ለኤልያስም በመልአኩ እጅ በመሶበ ወርቅ ኅብስት የመገበ፣ ለእዝራ ሱቱኤልም በመልአኩ በቅዱስ ዑራኤል እጅ መልኩ እሳት የሚመስል ጽዋዐ ልቡና ያጠጣው ልዑል እግዚአብሔር ለእናትነት ወደ መረጣት ወደ እናቱ መልአኩ ፋኑኤልን ላከላት። (ዘፀ ፲፮፥፴፩፣ ፩ ነገ ፲፱፥፮፣ ዕዝ. ሱቱ. ፲፫፥፴፰-፵፩)

ከዚያም “ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሀባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይ” ይላል።”  /  “በዚያን ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊን በብርሃን ጽዋዕ፣ ስቴ ሕይወትን ይዞ ረብቦ በመውረድ አንድ ክንፉን አንጥፎ፣ አንዱን ክንፉን አጎናጽፎ፣ ከመሬት የሰው ቁመት ያኽል ከፍ አድርጓት፣ ኅብስቱን መግቧት፣ ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ስላዩትና ስለተደረገው ነገር ኹሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አማናዊት የአምላክ መቅደስ፣ የአካላዊ ቃል ታቦት እመቤታችንን ምሳሌዋ ወደሚኾነው ቤተ መቅደስ ታኅሣሥ ፫ በሦስት ዓመቷ አስገብተዋታል። ከዚያም ኢያቄምና ሐና ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡የቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ መቅደስ ሕይወት በእጅጉ አስደናቂ ሲኾን የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ትውፊት (Holy Tradition) እንደሚያስረዳን ቤተ መቅደስ በኖረችባቸው ፲፪ ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለቤተ መቅደስ የሚያስፈልገውን ነገር በእጆቿ እየሠራች በፍጹም ንጽሕና እና ቅድስና ኾና እግዚአብሔርን በማመስገን መላእክት እያገለገሏት ኖራለች፡፡ ይኽነን በቤተ መቅደስ የነበራትን ቆይታ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በጥልቀት ጽፈዋል። እነሆ የሊቃውንቱ ቃል፦አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማኅሌተ ጽጌ
“ማርያም የሐናን ወተት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ብቸኝነት ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚመላለስ ደመናን የሚረግጥ የእሳት አበባ ፋኑኤል ከጓደኞቹ መላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በንጽሕና የማደግሽ ተአምር ደስ ያሰኘኛል።”

“በዐረብና በተርሴስ ወርቅ እንዳጌጠች ታቦት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ያጌጥሽ ማርያም ቀንሞስ፣ ቀናንሞስ የሚባሉ ሽቱዎች ኢያቄምና ሐና ለጳጦስ ምሳሌ የኾንሽ አንቺን ከአስገኙሽ ዘንድ በሦስት ዓመት በቤተ መቅደስ የመኖር ተአምርን አሳየሽ።”
      ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ። ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም፤ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፤ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ።”
         በ፭፻፭ (505) ዓ.ም. የተወለደው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን: “ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የኾንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ፣ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በኾነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲኽ ኾነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጐበኙሽ እንዲኽ ዐሥራ ኹለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር።” “መላእክት እመቤታችንን እኅታችን ይሏታል። በክንፋቸው ይጋርዷታል፤ በማር ወለላ የተመሰለ የእግዚአብሔር ቃል ከከንፈሮቿ ይፈስሳል፤ ጒንጮቿ እንደ ሮማን ቅርፍት ናቸው። ልዑል ወደዳት፣ ዳዊት በመዝሙሩ አመሰገናት፣ በቤተ መቅደስ ተቀበሏት።” ቅዱስ ያሬድ (መጽሐፈ ድጓ) ጌታ የመረጠሽ ማርያም ሆይ ለምኚልን። ዕፀ ጳጦስ ተብላ የተጠራችውን እመቤታችን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ተቀበላት። ኹላቸውም ቅዱሳን ዐዲሲቱ እንቦሳ ይሏታል።በዓሉን የረድኤት የበረከት ያድርግልን!

፩. ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣
፪. ነገረ ማርያም በሊቃውንት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ። ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ!