ሰማያዊው ፈራጅ በፈራጆች ፊት

ዕለተ አርብ ለክርስቲያኖች ሁሉ የሕማም የመገረም የመደሰት እለት ናት። በዚህች ቀን ስለሰው ሁሉ ፍቅር ሰው የሆነው ክርስቶስ ሕማምን ተቀብሏልና ከእርሱ ጋር እየወደቁና እየተነሱ ከሊቀካህናቱ ጊቢ እስከ ሊጦስጥራና ቀራንዮ ድረስ አብረው ይታመማሉ።
በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለው ግን መታመም ብቻ አይደለም። መደመምም ጭምር እንጂ። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”  ዮሐ 15፥13 ብሎ ያስተማረ አምላክ የኃጢአተኛውን ሰውነት ገንዘብ ከማድረግ አልፎ ሊያድነው በመጣው ሰው ሕማምን ተቀብሎ በማዳን ስለገለጠው ፍቅር ይደነቃል። ከልበ አምላክ ዳዊት ቃል ተውሶ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጎበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? እያለ በፍፁም መገረም ይጠይቃል። ነገሩ በመገረም አያበቃም በተከፈለላቸው ዋጋ ያገኙትን ያቃሉና በፍፁም ደስታ ሆነው በመልክአ ሕማማቱ ስብሃት ለከ እያሉ ያመሰግናሉ።

በዚህ የታላቁ የፍቅር ቀን መደመማችንን ዘላለማዊው ፈራጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በአላፊ ጠፊ ፈራጆች ፊት በመቆሙ እንጀምር።

የእለተ አርብ የአይን ምስክር ወንጌላዊው ዮሐንስ እንደሚነግረን አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሊጦስጥራ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት ጲላጦስ የተሰኘው ሀገረ ገዢም ወደነሱ መጥቶ የዚህ ሰው በደሉ ምንድነው አላቸው እነርሱም “ክፉ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስ ራሳቸው በህጋቸው እንዲወስኑ የፈለገ ቢሆንም እነርሱ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም ብለው እርሱ እንዲፈርድበት ግድ አሉት። በዚህ ሰዓት ጲላጦስ ክርስቶስን “የአይሁድ ንጉስ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ክርስቶስ የጲላጦስ ጥያቄ ከራሱ ከጲላጦስ ወይም ከሌላ የመጣ መሆኑን በሚመረምር ጥያቄ መለሰለት። ጲላጦስ ጥያቄው ከአይሁድ የመጣ መሆኑን ሲነግረው ጌታችን ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስ ግን መልሶ ጠየቀው “እንግዲያስ አንተ ንጉስ ነህ” ደግሞ ጠየቀው ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ በዚህ ሰዓት ሁሉ ይጠይቀው ዘንድ የሚገባውን ጥያቄ ጠየቀው “እውነት ምንድነው?”

ይህ የጲላጦስ ጥያቄ መሠረታዊ ጥያቄ ነበር። ነገር ግን ጲላጦስ ጠይቆ መልስ እስኪያገኝ ድረስ አልታገሰም። በዚህ ሰው ላይ በደል አላገኘሁበትም ይል ዘንድ ወደ አይሁድ ሄደ እንጂ ቢታገስ ኖሮ እውነት ማለት ክርስቶስ መሆኑን ይረዳ ነበር። ጲላጦስ ግን መሰረታዊ ጥያቄ ጠይቆ መሠረታዊውን መልስ ለመስማት ጊዜ አጣ።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን የሰማው ጲላጦስ በወቅቱ በኢየሩሳሌም ወደ ነበረው የገሊላው ገዢ ወደ ሄሮድስ መላኩን ይነግረናል። በነቢዩ ኢሳያስ (ነበር53:7) እንደተተነበየው ሄሮድስም ጌታ ኢየሱስን በብዙ መንገድ ቢመረምረውም እንደሚታረድ በግ አንዳች አልመለሰለትም ነበር። በዚህም የአለሙን ሀጢአት የሚያስተሰርይ በግ ተብሎ በመጥምቁ ዮሐንስ የተነገረውን ቃል እውነተኝነት አስረገጠ።

ሄሮድስ በደል እንዳላገኘበት ገልፆ ለጲላጦስ ቢልክበትም ሚስቱ ስለእርሱ በህልም መሰቃየቷን መልዕክት በመላኳና ለሞት የሚያበቃው በደል ስላላገኘበት ሊፈታው ወዶ አብዝቶ ወንጀል ከሰራው ከበርባን ጋር ኢየሱስን ለምርጫ አቀረበው። ከዕፀ በለስና ከእፀ ሕይወት እፀ በለስን ያስመረጠው ሰይጣንም አይሁድን በሊቀ ካህናቶቻቸው አድሮ በርባንን አሰመረጣቸው።

ጲላጦስም ፀብ ክርክር እንጂ ምንም እንደሌለ አውቆ ክርስቶስን ገርፎ አሳልፎ ሰጣቸው። ከደሙ ነፃ ነኝ ብሎ እጁን ታጠበ። የይስሐቅን ምርቃትን ከወንድሙ ጋር የተሻማው የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን እርግማኑን ተሻሙ። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻቸውም ደሙን ተሻሙ። አስቀድሞ ይሁዳ ገንዘቡን ሲመልስ በኋላም ጲላጣስና ሄሮድስ የኢየሱስን ንፅህና ቢነግሯቸውም አይሁድ የተባባሪዎቻቸውን ቃል መስማትን እንኳን አሻፈረን አሉ።

ስለዚህች የፍርድ ሰዓት እንደመማለን እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ያለውን አምላክ፣ ሂጅ አልፈርድብሽም ብሎ የታፈሩትን የፈታው ክርስቶስ ተፈረደበት። በዳግም ምፅዐቱ አለም ሁሉ በፍርድ ዙፋኑ ፊት የሚቆሙለት ክርስቶስ ተፈረደበት። ያውም የተከሳሽነት ከብር ተነፍጎት እየተዳፋና እየተደበደበ በፈራጆች ፊት ቆመ። አይሁድ ከሆሳዕና ጀምሮ ይጠይቁትና እንከን ይፈልጉበት ዘንድ ባቀረቡት በአንዱም ጥፋት ያልተገኘበትን፣ በፈራጆች ፊት ንፁህ መሆኑን የገለጠውን ክርስቶስ ስለህዝብ ጩኸት ብቻ ሲሉ ፈረዱበት። እውነት በድምፅ ብልጫ፣ ንፅህናም በጩኸት ተሸጠ።

ጠላቶቹን የሚወድ ክርስቶስ ግን በሞቱ የተለያዩትን ሰውና መላዕክት አንድ ለማድረግ በመጣበት በዚህች ዕለት ስለ እርሱ የተለያዩትን ሁሉ አንድ ያደርግ ነበር። አስቀድሞ በክስ ፈሪሳውያንንና ሰዱቃውያንን አንድ ያደረገ እርሱ ለፍርድ በፊታቸው ቆሞ ተጣልተው የነበሩትን ጲላጦስንና ሄሮድስን አስታረቃቸው። በሞት ላይ ይፈርድ ዘንድ፣ በሲኦል ላይ ይበይን ዘንድ ተፈረደበት።

እስከ መቼ?፡መንፈሳዊ ወግ

ከዓመታት ወዲህ በሰሙነ ሕማማት ከቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ከማልገኝባቸው ቀናት መካከል አንደኛው ቅዳሴ የሚቀደስበት ሐሙስ ነው። ተጨባጭ የሆነ ምክንያት የለኝም፡ ግን በስራም፡ በስንፍናም እያመካኘሁ ሐሙስን አልገኝም። የሚገርመው ነገር የሕማማትን ሐሙስ ካስቀደስኩ ዘመናት እንደነጎዱ ያስተዋልኩት  ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ዛሬ ሰፈራችን በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ስላለሁ ነው። ወይ ጊዜ።

የዛሬን አያድርገውና…የዛሬን አያድርገውና …

    እኔም በዕለተ ሐሙስ የተሰራው የምስጢረ ቁርባን ስርዓት ተሳታፊ ነበርኩኝ። ነጣ ያለ ሱሪዬን አጣጥቤ፡ ነጠላዬን አጣፍቼ  “ስጋዬንም የበላ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” የሚለውን ዝማሬ በለሆሳስ እያልኩ ወደ ቤተ ክርስቲያን የማቅናት ልምድ ነበረኝ።

   አሑን አሑን ግን እንኳን ለስጋና ለደሙ ነጠላ እንኳን ለመልበስ እፈራለሁ። አንዳንድ ጊዜ አስባለሁ ፡ እኔንጃ ነውሬ የነጠላውን ነጭ ቀለም  የሚያመነችክ ይመስለኝ ይሆን፡ እንጃ ብቻ።

   ለምን ከስጋ ወደሙ ራቅክ? ለምን ንስሐ አትገባም? የዘለዓለም ሕይወትን ማግኘት አትፈልግም? ብለህ ብትጠይቀኝ ስጋ ወደሙ ለወጣቶች አልተፈቀደም የሚል ምላሽ አልሰጥህም። እንደውም በብዙ ለታመምን እኛ በብዙ የሚያድነው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደም ምን ያህል እንደሚያስፈልገን በብዙ ማስረጃ ላስረዳህ እችላለሁ።

     ታድያ ለምን ንስሐ የማልገባ ይመስልሃል? ይቅር ባይ መሆኑን አውቃለሁ። እንደ እርሱ አይነት መሐሪ ማን አለ? እኔም ሰው ተብዬ ደጁን ለመርገጥ ከመብቃቴ የበለጠ ለእርሱ መሐሪነት ማስረጃ የሚሆን ምን አለ?  የይሁዳ ትልቁ ኃጢያት የዓለምን መድኃኒት በሠላሳ ዲናር ከመሸጡ የበለጠ አምላኩ ይቅር አይለኝም ብሎ ራሱን ማጥፋቱ እንደሆነስ መች ጠፍቶኝ።

   የዘለዓለም ሕይወትን እንደሚያሰጥም አውቃለሁ። አምላኬ አማኑኤል የተናገረውን ቃል መቼ አጥፎ ያውቃል? “ስጋዬንም የበላ ደሜንም የጠጣ፡ የዘለዓለም ሕይወት አለው”ብሎ የተናገረውንስ እንዴት አላምንም። ለማስረዳት ጠይቁ ብሎ ጠይቄ ያገኘሁትን ወይስ ከልለኝ ብዬው የሰወረኝን ልዘርዝር?

ታዲያ ለምን አልቆርብም? ስንፍና፡ ትዕቢት፡ መሞትን መርሳት ፡ በድጋሚ እንጃ ብቻ።

አላውቅም።

   ተጠየቅ –  አምላክህ በመስቀል ተሰቅሎ በፍቅር አይኑ እያየ ስጋዬን ብሉና የዘለዓለም ሕይወትን አግኙ ሲል ፡ ከእርሱ መሸሽ ምን ይባላል? በትሕትና የሐዋርያቱን እግር ያጠበው አምላክ ንስሐ ብንገባ ከክፉ ስራችን ሁሉ ሊያነጻን፡ ሊያጥበን  እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት በደላችንን ሊረሳ ፡ አስበኝ እንዳለው ፊያታዊው ዘየማን ከእርሱ ጋር በገነት ሊያኖረን የሚወድድን አምላክ ስለምን ይሆን የምሸሸው ? የእናንተን አላውቅም።  እኔ ግን ምን ሆኛለሁ? እስከመቼስ እንደዚህ እቀጥላለሁ?  ራሴን እጠይቃለሁ?

ለምን… እስከ መቼ?

https://t.me/EMislene

ምክረ ረሲአን

በአንድ አጀንዳ ዙሪያ መመካከር የተለመደ ነው። ሰዎች በአንድ ግለሰብ ብቻ መወሰን በማይችሉ ጉዳዮች ላይ ይመለከታቸዋል ከሚሏቸው ሰዎች ጋር ይወያያሉ፣ ይወስናሉ። እነዚህ መሰባሰቦች ጉባኤ፣ ሸንጎ፣ ምክር ተብለው ይጠራሉ። በመዝሙረኛው ዳዊትም በሕብረት መቀመጥ ተብሎ ተጠርቷል።


ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ነውና ምንም እንኳን በጉባኤ ተሰባስቦ መነጋገር ጠቃሚና ዘመን የጠገበ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልማድ ቢሆንም ጉባኤዎች ሁሉ ንጹሐንና ጠቃሚዎች አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስና የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል።

የምክር ምልከታችንን ንጹሑን ዮሴፍን ለማጥፋት በመከረው የአስራ አንዱ ወንድሞች ታሪክ እንጀምር። የዘፍጥረት ጸሐፊው ሙሴ በ37ኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ስለዛች ምክር እንዲህ ብሎ ይጀምራል “እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ።”— ዘፍጥረት 37፥18 ለምክራቸው መነሻ የሆነው ዮሴፍ ያየው ህልም ነበር። ህልሙ የፈጠረባቸውን ቅናት መቆጣጠር ስላልቻሉ
በምክራቸው ላይ አንደኛው ወንድሙ እንግደለው ብሎ ሲነሳ ሌላኛው አይ በሕይወት ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው ሲል እናደምጣለን። የጉባኤው ሀሳብም የመጨረሻ ውጤት የዮሴፍ መሸጥና የያዕቆብ እንባ ነበር።

የዚሁ ምክር ተመሳሳዩን በሐዲስ ኪዳንም እናገኛለን። መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ የሰራቸውን ድንቆችና ተዓምራት የሰሙ አይሁድ ክርስቶስን ሊያስወግዱ ጉባኤ ሰሩ።

የብሉይ ኪዳኑ ምክረ ውሉደ ያዕቆብና የሐዲስ ኪዳኑ ምክረ አይሁድ መሐል የበዛ መመሳሰል እናያለን። በብሉይ ኪዳኑ ጉባኤ ዮሴፍ ላይ የተነሱበት ወገኖቹ ነበሩ። በሐዲስ ኪዳኑ ምክርም ላይ አይሁድ የተነሱት ለሙሴ ከወንድሞች መሐል እንዳንተ ያለን አስነሳለው ተብሎ በተነገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር።

የብሉይ ኪዳኑ ምክር መነሻው ቅናት ነበር። እኛን ሊገዛና የበላያችን ሊሆን ይወዳል ብለው ነበር ለመግደል በኋላም ሀሳቡን አሻሽለው በባርነት ለመሸጥ የተስማሙት። የሐዲሱም ምክር ምንም እንኳን የሮማን የበላይነት ለማጽናትና የአይሁድን እምነትና ባህል ለመጠበቅ የሚል ሽፋን ቢኖረውም ትክክለኛው ምክንያቱ ግን ቅናት ነበር። ይሄም በጲላጦስ ዘንድ ጭምር የታወቀ እንደነበር ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ያነሳዋል። “በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።” ማቴዎስ 27፥18

የምክራቸው ሀሳብም ተመሳሳይ ነበር የተመቀኙትን ሰው እንዴት ማስወገድ እንዳለባቸው። በዮሴፍ ላይ የመከሩት ይገደል አይገደል በሚለው ሃሳብ ተከፋፍለው እንደነበረው ሁሉ በአይሁድም መካከል ይህ አይነት ክርክር እንደነበረና ሦስት ቀን እንደፈጀባቸው ዕለተ ረቡዕም የተስማሙበት ቀን መሆኑን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያነሱታል። ኢየሱስን የመሸጥ ሀሳብ በይሁዳ የቀረበውም ልክ እንደ ዮሴፍ መሸጥ ዘግየት ብሎ ነበር። ዮሴፍ ከጉባኤ ውጪ ላሉ ነጋዴዎች ሲሸጥ ኢየሱስ ግን ከጉባኤው ውጭ ባለ ሰው ለጉባኤተኞች ለድርድር ቀረበ። የዮሴፍ መሸጥ ከወንድሞቹ ምክር በኋላ እንደ መጣ ሁሉ ይሁዳም የመጣው ጉባኤው ከተበተነ ከሰዓታት በኋላ ነበር። ከእንግዲህ ባሮች አይደላችሁም ወንድሞች እንጂ ተብሎ የተነገረለት ይሁዳ ወንድሙ ይሆን ዘንድ በትህትና ራሱን ዝቅ ያደረገውን ክርስቶስ ሊሸጠው ከአይሁድ ጉባኤ መልስ ተገኘ።

ከደቀመዛሙርቱ መካከል አሳልፎ የሚሰጣቸው ሰው ይኖራል ብለው ለማይገምቱት አይሁድ የይሁዳ መምጣት ያልተጠበቀ ሆኖላቸው ነበር። “ሁከት እንዳይፈጠር በበዓል አንያዘው” ማቴ 26:5 ብለው ያሉት በስውር አሳልፎ የሚሰጣቸው ደቀ መዝሙር እንዳለ ስላላወቁ ነበር። “ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት” የሚለውም ቃል የይሁዳ መምጣት በአይሁድ ጉባኤ ያልተጠበቀ መሆኑን አመላካች ነበር።

የክፉዎች ምክር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ መሸጥ የሚያበቃ ብቻ አይደለም። “ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል።” ዮሐ 15፥20 ብሎ እንደተናገረው በክርስቶስ ላይ የመከሩ ጠላቶች በሐዋርያቱና በአርድእቱም ላይ ለመነሳት ከመምከር ወደ ኋላ አላሉም። ሐዋ 4:17፣ ሐዋ 9:23

የክፉዎች ምክር በዘመነ ሰማዕታትም ብዙ ሰማዕታትን በመከራ ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስክር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሄ የአይሁድና የአህዛብ በክፉ የመዶለት ጠባይ ታዲያ በኋላ ዘመን በተነሱና የኢየሱስ ክርስቶስ ስምን በሚጠሩ ነገር ግን የእርሱን የማይመስል ወንጌል በሚሰብኩ መናፍቃንም ጭምር መታየት ጀመረ። ይህንንም ከታሪክ ሁሉ ጎልቶ በሚታየውና ቅዱስ አባት ዲዮስቆሮስን ስለእውነት በብቸኝነት ባቆመው የኬልቄዶን ጉባኤም ላይ እንመለከተዋለን። አስቀድመው የቅዱሱ አባት ዲዮስቆሮስ ወንድም የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቶስን የተዋሕዶ ስግው ቃልነት በመሰከረ ወንድማቸው ላይ ተነሱበት። በሀሰት ጉባኤያቸው አውግዘው ለዩት። ነገር ግን በዚህ ቁጣቸው ያልበረደላቸው መለካውያኑ ግን በዲዮስቆሮስ ላይ እጃቸውን አነሱበት ጥርሱን አርግፈው ጽሕሙን ሲነጩት እንኳን ለቀናኢ እምነቱ ለእርጅና ክብሩ እንኳን አልተጨነቁም ነበር።

እኒህንና ሌሎች መሰል ምክሮችን ለታሪክ እንተወውና ፈጣሪ አለማት ክርስቶስን ለማስወገድ ወደተመከረባት ወደዚህች ቀን እንመለስ። ይህች ቀን የክርስቶስን መሲሕነት የተገለጠባት ስለመሆኑ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ከቁጥር 49-52 እንዲህ ያነሳልናል
“በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው “እናንተስ ምንም አታውቁም። ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ህዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል”

ይሄ ምንኛ የሚደንቅ ምስክርነት ነው? የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው እንዲሉ ለመግደል ከተሰበሰበ ጉባኤ ያውም ከሊቀ ካህኑ ይሄንን መስማት እንደምን ያስደምም። ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለዚህ ምስክርነት እንዲህ ይለናል


“…ይህንም ከልቡ የተነገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ህዝቡ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ። ስለ ህዝቡ ብቻ አልነበረም የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ”

የመንፈስ ቅዱስን ስራ እዚህ ጋር እንመልከት ስምዖን ጴጥሮስ አንተ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ያስመሰከረ መንፈስ ቅዱስ የካህናት አለቃው ቀያፋንም ልቡን አንቅቶ ፊቱን ፀፍቶ የእውነትን ቃል እንዲናገር አደረገው። ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመስቀል ላይ መስዋዕትነቱን እስኪፈጽም ድረስ ኦሪት አላለፈችም ነበርና በክፉ ተንኮል ሥራ ተጠምዶ በነበረው በቀያፋም አንደበት እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የትንቢት ቃልን አኖረ። ይሄም ዛሬም ያሉ ካህናት ምንም እንኳን ኃጥእ ቢሆኑ ክህነታቸው እስኪሻር ድረስ እግዚአብሔር በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሥራውን የማያቋርጥ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

“የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።” መዝ 2:2-4

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሁኖ መከራን ተቀበለ። በመከራውም አዳነን።

የግብረ ሕማማትን መጽሐፍ ምን ያህል ታውቁታላችሁ?

በቤተክርስቲያን የጸሎት ሕይወት ውስጥ ታላቅ ቦታ ካላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ‹መጽሐፈ ግብረ ሕማማት› ነው፡፡ ሊቃውንቱ ‹ግብር› የሚለውን ‹አገልግሎት› ብለው ይተረጉሙትና ‹ግብረ ሕማማት› ማለት ‹በሕማማት ወቅት የሚፈጸም አገልግሎት› ማለት ነው ይላሉ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹እርሱ ሕመማችንን ተሸከመ› (ኢሳ 53÷4) በማለት የገለጠው ኃይለ ቃል ለሰሙኑም ሆነ ለመጽሐፉ ስያሜ መነሻ መሆኑንን ሊቃውንቱ ይገልጣሉ፡፡ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው ‹ወአንት ሙሰ ተዐቀቡ ወግበሩ ተዝካረ ሕማማቲሁ – እናንተ ግን ተጠበቁ፣ የሕማማቱንም መታሰቢያ አድርጉ› ብለው ደንግገዋል (ግብረ ሕማማት፣ 1996፣9) ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም <ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሐተ – የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና ብሎ የጠራ እግዚአብሔር ይመስገን› ብሎ ገልጦ ነበር፡፡

ግብረ ሕማማት ከበዓለ ሆሳዕና እስከ በዓለ ፋሲካ የሚከናወነውን ሥርዓት የያዘ ትልቅ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉ የተወሰነ ክፍልና ሥርዓቱ ከ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ ጀምሮ በግብጽ ቤተክርስቲያን ነበረ፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ አሁን በምናየው መልኩ የሰሙነ ሕማማት ምንባባትን ያዘጋጁት የገዳመ መቃርስ መነኮሳት መሆናቸውን ግብረ ሕማማት ይገልጥልናል፡፡ በእነዚህ የገዳመ መቃርስ አባቶች በመታገዝ የእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ገብርኤል 2ኛ (1131-1145) (የኛ ግብረ ሕማማት “ጸሐፊ የነበረው የታሪክ ልጅ አባታችን አባ ቅብርያል” ይለዋል፡፡ ኢብንቱርያክ የሚለውን ተርጉሞ ሳይሆን አይቀርም፡፡) የሰሙነ ሕማማት መጽሐፍ (ፓሻ) በእርሱ አስተባባሪነት ሊቃውንቱ ለየቀኑ እና ለየሰዓቱ የሚሆኑትን ምንባባት ከብሉይ እና ከሐዲስ እያውጣጡ አዘጋጇቸው፡፡

ፓትርያርክ ገብርኤል አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስና የሊቃውንት ትርጓሜ ዕውቀት ያላቸው ሊቃውንት በማሰባሰብ ለየሰዓቱና ለየኩነቱ የሚነበበውን ሥርዓትና ንባብ አዘጋጁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በሰላማ መተርጉም ጊዜ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ከጎንደር መድኃኔዓለም ተወስዶ በብሪቲሽ ሙዝየም በሚገኘው ግብረ ሕማማት ላይ ከአባ ሕርያቆስ ድርሳን መጨረሻ ላይ <<ዘንተ መጽሐፈ ዘተርጎመ ብፁዕ ወርቱዕ ሃይማኖት አቡነ አባ ሰላማ ይጽሕፍ ስሞ እግዚአብሔር ውስተ መጽሐፈ ሕይወት› ይላል፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ የብሕንሳው ጳጳስ አቡነ ቡትሮስ ምንባባቱን ለየሰዓታቱ በተመጣጣኝ ሁኔታ በማካፈል ሁሉም ቀናት ተመጣኝ የሆኑ ሁሉም ዓይነት ምንባባት እንዲኖሯቸው አድርገዋል፡፡ ግብረ ሕማማታችንም «ከኦሪት እና ከነቢያት፣ ከነዌ ልጅ ከኢያሱ፣ ከንጉሥ ሰሎሞን መጽሐፍ ወስዶ ሁላቸው ትክክል እስከ ሆኑ ድረስ በየሰዓቱ ሁሉ የሚገባውን አደረገ፡፡ አባቶች ከተናገሩት ሁለት ሁለት ተግሣፅ እና ምክር አንዱ በነግህ አንዱም በማታ እንዲነበብ አደረገ» ይላል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደሚሉት ከሆነ ግብረ ሕማማትን አሁን ባለው መልክ ያዘጋጁት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ እስከ 14ኛው መክዘ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለሰሙነ ሕማማት የሚሆኑ የጸሎት ሥርዓት ሳይኖሯት ቆየች ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አቡነ ሰላማ መተርጉም የተወሰነውን የመጽሐፈ ግብረ ሕማማት ድርሳናት በመተርጎም ቀድሞ በነበረው የሰሙነ ሕማማት የጸሎት ሥርዓት ውስጥ መጨመራቸውን ይገልጣሉ ። አሁን ባሉን የግብረ ሕማማት ቅጅዎች የአቡነ ሰላማን ስም የሚያነሣው ከሊቃውንቱ ድርሳናት መጨረሻ ላይ የሆነውም ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ አቡነ ሰላማ መተርጉም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን አሰባስበው የትርጉም ሥራ ይሠሩ የነበሩት በደቡብ ጎንደር ስማዳ በምትገኘው ደብረ ዕንቁ ማርያም ነበር፡፡ አቡነ ሰላማ የግብጹን ግብረ ሕማማት ይዘውት የመጡ ይመስላል፡፡ በደብረ ዕንቁ የነበሩ ሊቃውንት መጽሐፉን መነሻ በማድረግና ከቀደመው የቤተክርስቲያን ጸሎት ጋር በማስማት አሁን የምናውቀውን ግብረ ሕማማት አዘጋጅተውልናል፡፡

እስካሁን ባሉን መረጃዎች ረጅም እድሜ ያስቆጠሩት የግብረ ሕማማት ቅጅዎች በ15ኛው መክዘ የተጻፉት ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ በኢትዮጵያ ማይክሮ ፊልም ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ (EMML 1765, 4434, 4752) EMML 1765 የሐይቅ እስጢፋኖስ ቅጅ ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ላይ ልዩ ልዩ ድርሳናትን የተረጎሙት አባ ሰላማ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ EMML 4434 የእንዳ ፍሬ ማርያም (ሞረት) ሲሆን EMML 4752 ደግሞ ሰሜን ሸዋ የሚገኘው የሙሽ ዜና ማርቆስ ንብረት ነው፡፡

በግብረ ሕማማት ውስጥ ከጾመ ድጓና ምዕራፍ የተወሰዱ ጸሎቶች መኖራቸው ፤ በግብጹ መጽሐፍ ላይ የሌሉ ከተአምረ ማርያምና ከተአምረ ኢየሱስ የሚነበቡ ምንባባት መገኘታቸው ፤ እንዲሁም የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቅርጽ ካልሆነ በቀር በብዛትና በዓይነት የተለዩ መሆናቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የመጽሐፉን መነሻ ከግብጽ ወስደው ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንዲሆን አድርገው ማዘጋጀታቸውን እንደሚያሳይ የሚገልጡ አሉ፡፡ ለብዙ ዘመናት ግብረ ሕማማት በግእዝ ብቻ የሚገኝ መጽሐፍ ነበር፡፡ በሊቀ መዘምራን ላዕከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ (ዘአሰላ) ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ታትሟል፡፡

√ በግብረ ሕማማት ውስጥ ሦስት ነገሮች አሉ፡-

የመጀመሪያው ጸሎት ሲሆን ‹ዐማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም› እየተባለ የሚጸለየውና ካህናትና ምእመናን በየመካከሉ የሚደግሙት ዳዊት የዚሁ መገለጫ ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ ስግደት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሰዓት፣ በሦስት፣ በስድስት፣ በዘጠኝና በ11 ሰዓት ከጸሎት ጋር የሚደረግ ስግደት አለ፡፡ በዕለተ ዓርብ ደግሞ የ12 ሰዓት ጸሎትና ስግደት አለው፡፡ ከግብረ ሕማማት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሦስተኛው ክፍል ንባቡ ነው፡፡

በሰሙነ ሕማማት በመጽሐፈ ግብረ ሕማማት መሠረት የሚነበቡ ብዙ ምንባባት አሉ፡፡ እነዚህንም በአራት መድበን መመልከት እንችላለን፡፡

  1. መጽሐፍ ቅዱስ፡- በተለይም በዋናነት ከብሉይ ኪዳን ከኦሪት፣ ከጥበብ መጻሕፍት (ምሳሌ ፣ መኃልየ መኃልይ፣ ጥበበ ሰሎሞን፣ ሲራክ፣ ኢዮብ፣ ከመጽሐፈ ኢያሱ፣ ከመጽሐፈ ሩትና ከሌሎችም የሚቀርቡ ከሰሞኑ ጋር የሚሄዱ ምንባባት አሉ፡፡
  2. ትርጓሜ፡- የልዩ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትርጓሜ ይነበባል፡፡ በተለይ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያን ትርጓሜ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ከእርሱም ጋር የኤጲፋንዮስ፣ የአትናቴዎስ፣ የቄርሎስና የያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜያት ይሰማሉ፡፡
  3. ምዕዳን፡- በግብረ ሕማማት የክርስቲያንን ልዩ እሴቶች የሚመለከቱ ምክሮች ይቀርባሉ፡፡ ስለ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ወገንን መርዳት የተመለከቱ ምንባባት አሉ፡፡
  4. መጻሕፍተ ሊቃውንት፡- በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከተዘጋጁና እምብዛም ከማናገኛቸው ድርሳናት መካከል በግብረ ሕማማት ውስጥ የምንሰማቸው አሉ፡፡ መጽሐፈ ዶርሖ፣ ላሃ ማርያም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ከተለመዱት ምንባባት ደግሞ ስንክሳር ፣ተአምረ ኢየሱስና ተአምረ ማርያም ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ መጽሐፉ በአማርኛ የሚነበብ በመሆኑ ምእመናን ሁላችን በማስተዋል ብናዳምጥ በሌላ ጊዜ የማናገኛቸውን የቤተክርስቲያን ታሪኮች ፣ ምሥጢራትና ምንባባትን የምናዳምጥበት ዕድል ይሆናል፡

በቀሲስ ኢዩኤል ሰለሞን።

ድንግል ማርያም ስለ ልጇ ስላለቀሰችው ለቅሶ


ወዳጆቼ ሆይ የአባቶቼ አለቃ የያዕቆብ ለቅሶ ዛሬ ታደሰ አለ። በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ለወለደችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? መከራ ስለተቀበለችበት ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? የድንግልና ጡቷን ላጠባችው ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በቤተልሔም በበረት ለወለደችው ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በማሕጸኗ ዘጠኝ ወር ለተሸከመችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? ከሃገር ሃገር አዝላው ለተሰደደችበት ልጇ ድንግል ማርያም ስለምን አታለቅስ? ከቶ መቃብራቸውን ስላላየችው ልጆቿ ራሄል የምታለቅስ ከሆነ በአንድ ልጇ መቃብር ደጃፍ ላይ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስ?


የባለ መልካም ስም ሽማግሌ የያዕቆብ ልቅሶ በብላቴናይቱ ድንግል ዛሬ ታደሰ። ወንድሞቹ ባሰሩት ጊዜ ያዕቆብ ወደ ዮሴፍ አልተመለከተም። ድንግል ግን ልጇ በእንጨት መስቀል ላይ ተቸንክሮ አየችው። ዮሴፍ በሰዲ ጉድጓድ ውስጥ ሳለ ያዕቆብ በላዩ እንዲያለቅስ ወደ ዮሴፍ አላየም። ድንግል ግን በአይሁድ ጉባኤ መካከል ተሰቅሎ ልጇን አየችው። ዮሴፍን ወንድሞቹ ልብሱን ሲያራቁቱት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን በጎ ምክር በሌላቸው በአይሁድ መካከል ልብሱን ተገፎ ራቁቱን ሆኖ አየችው። ወንድሞቹ ዮሴፍን በሃያ ብር ሲሸጡት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን ይሁዳ ልጇን በሰላሳ ብር ሲሸጠው አየች።አራዊት ባልቀደዱት ልብስና በሌላ ደም ላይ ያዕቆብ አለቀሰ። አምላካዊ ደም ግን ድንግል ማርያም ስለእርሱ በላዩ የምታለቅስበት በቀራንዮ አለት ላይ የፈሰሰው ነው። ድንግል ግን ዛሬ ያየችው ለልጇ ያለበሱትን ሌላ ልብስ ነበር የራሱን ልብስ ግን እርስ፡በእርሳቸው ተካፈሉት። የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸው ዮሴፍን በሸሩት ጊዜ አለቀሱ ተጸጸቱ። የእስራኤል ልጆች ግን ጌታቸውን በሰቀሉት ጊዜ አላለቀሱም አልተጸጸቱም። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው በነገሠ ጊዜ ተደሰቱ። አይሁድ ግን ጌታቸው ከሙታን ተለይቶ በተነሳ ጊዜ ደስ አላላቸውም።


ድንግል ሆይ በእውነት በልጅሽ መቃብር ላይ ልቅሶሽ ጣዕም ያለው አሳዛኝ ነበር።ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል? ምን ታደርጊያለሽ ብለው የልጅሽን መሰቀሉን በነገሩሽ ጊዜ በመላእክት መካከል ቃልሽ ያማረ ነበር። እነሆ ልጅሽን በመኮንኑ ፊት አቁመውታል። የአይሑድ ሊቃነ ካህናትም ያሰቃዩታል። ያቃልሉታል። ማርያም ሆይ ምን ታደርጊያለሽ? እነሆ ልጅሽን በፍርድ አደባባይ መካከል ልብሱን ገፍፈው እያራቆቱት ነው።የኢያቄም ልጅ ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል ምንስ ታደርጊያለሽ?እነሆ በኢየሩሳሌም ሜዳ የሚሰቀልበትን ግንድ ብቻውን ተሸክሟል። አንድስ እንኳን ወደ እርሱ የሚቀርብ የለም። የሃና ርግብ ሆይ ለምን ተቀመጥሽ? የምትሰሪውስ ምንድን ነው? እነሆ ልጅሽን ሰቅለውት በቀራንዮ ቦታ ቆሟል።የዳዊት ዘር ሆይ ልጅሽን በመስቀል ላይ ለምን ከፍ ከፍ አደረጉት?እመቤቴ ድንግል ሆይ በዮሐንስ ቤት ዛሬ ልቅሶሽ በእውነት ጣዕም ያለው ነበረ። እንዲህ ስትዪ ወዮ ለዚህ መራራ ወሬ ነጋሪ ለኢዮብና እስራኤል ለተባለ ያእቆብ ካረዷቸው መርዶ የመረረ ነው።ዛሬ ወደ እኔ ለሚመጣ ለዚህ ለክፉ ወሬ ወዮ ልጄ ሆይ ሃገሩን ባቃጠሉት ጊዜ ለሎጥ ካረዱት መርዶ ያስጨንቃል። በእኔ ላይ ለደረስው ለዚህ አስጨናቂ ነገር ወዮ ። ልጄ ሆይ ስለ ኃያላን እስራኤል ሞት ለዳዊት ካረዱት መርዶ ይበልጣል። በዚህ በክፉ ወሬ ወደ እኔ በመጣው ለዚህ ወሬ ነጋሪ ወዮ። ልጄ ሆይ እነሆ ስታረጋጋኝ ሠላሳ ዓመት ይሆናል።ልገስጽሕም አልተቻለኝም ዛሬ ወደእኔ ወሬህ እስከመጣ ድረስ ወጥተህ እስክትገባ አንዲትስ ሰዓት እንኳን አላመንኩም ።


ልጄ ሆይ ለሐዘኔ ሁሉ ምስክሬ ሰሎሜ ናት እኔ ዳኛውን አየው ዘንድ ከቤቴ አልወጣም፡ በፈራጁም ፊት አልቆምም ሌባውን ሲቆርጡት ሽፍታውንም ይገድሉት ዘንድ ሲፈርዱበት አላየሁም። ከቶ ቀራንዮን አላየሁትም። የጎልጎታን ቦታ አላውቀውም ሁልጊዜ በሚጣሉበት ቦታ አልቆምኩም። ልጄ ሆይ ክፉ የሆነ ፍርድ አላየሁም። በፍርድ አደባባይም ከቶ ለዘለዓለም አልቆምኩም ልጄ ሆይ ያደረግኩብህን ግፍ አላውቅም።

እኔም በዮሐንስ ቤት ነበርኩ። ወዳጄ ሆይ በሊቀ ካህናቱ በሃና ጊቢ የተቀበልከው ግፍ ወሬው መራራ ነው።ልጄ ወዳጄ ሆይ ዛሬ ከእኔ ላይ ነጻነቴን አስወገድኩ። ስለልደትህ በናዝሬት መልካም የምስራች ነገሩኝ ፡ ዛሬ ግን በኢየሩሳሌም ይህችን ክፉ መርዶ አረዱኝ ። በዮሴፍ ቤት መልካም ዜና ደረሰኝ፡ በዮሐንስ ቤት ግን የሞት ዜና መጣብኝ። ልጄ ወዳጄ ግን እኔ በልቤ ደስ እያለኝ ተቀምጬ ነበር ። በየዕለቱ ፋሲካ ደርሷል። በዓሉን እናከብር ዘንድ ወደ ቤታችን እንመለሳለን እያልኩ ነበር ። የዚህ አይነቱ አሽካም ደረሰኝ ። ልጄ ወዳጄ ሆይ በእንባና በሐዘን በዓሌ ወደ ለቅሶ ተመለስ። ፋሲካዬም ወደ ልብ ሐዘን።

ድንግልንም ልጇን ስላላየችው ፍጹም ሐዘንና ለቅሶ አገኛት። በዮሐንስ ቤትም ሳለች እንደገና ወደ ለቅሶዋ ተመልሳ ዮሐንስ ሆይ ወደ ቀራንዮ ትመራኝ ዘንድ እማጸንሃለሁ አለችው። ዮሐንስ ሆይ ከእኔ ጋር ወደ ጎልጎታ ትትሄድ እማጽንሐለሁ።ሌባውን ሲሰቅሉት ወንበዴን ቸብቸቦውን ሲቆርጡ አላየሁም እንደ ወንበዴ ልጄን ወዳጄን በውስጡ የሰቀሉበትን ቦታ አይ ዘንድ ሃገሬን ክብሬን ትቼ በእግሬ እሄዳለሁ።

ልጄ ሆይ ከወንድሞችህ አንድስ እንኳን አብሮ የቆመ የለም። ወይም ስላንተ አንድም ቃል የሚናገር የለም። ልጄ ሆይ በልጇ ላይ የእናት ሐዘን ሌላ ነው። ወዳጅም ስለ ወዳጁ የሚያዝነው ሌላ ነው። እናትም በተወዳጅ ልጇ ላይ ከልብ የምታዝነው ሐዘን ልዩ ነው። ወዳጅም በወዳጁ ልዩ ሐዘን አዝኖ ያለቅሳል ሐዘኔም በኢየሩሳሌም ካሉ ሰዎች ሁሉ ይጸናል።
ልጄ ወዳጄ ሆይ ልቅሶዬ በእኔ ዘንድ ከተሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ ልቅሶ ይበልጣል። ዮሐንስም ከልቅሶና ከሐዘን መጽናናትን እንደማትችል፡ እርሱም ሊያረጋጋት እንደማይችል ባየ ጊዜ እርሷም ካላየሁት መጽናናት አልችልም እያለች ስለሆነ ዮሐንስም እኔ ካንቺ ጋር ወደ ቀራንዮ እሔዳለሁ ታዪው ዘንድ ተነሺ እንሒድ አላት። ድንግልም ከዮሐንስ ቤት ወጥታ በኢየሩሳሌም ሜዳዎች ውስጥ በእግሯ ተጓዘች። ድንግልንም ፈጥና ስትራመድ የሚያዩዋት ሰዎች እንዲህ የምታለቅስ ይህች ማናት አሉ። እርስ በእርሳቸውም ይነጋገሩ ነበር። ሌሎችም ከገበያ የምትሻውን ስትገዛ ከቶ ይህችን አላየናትም ይሉ ነበር። ሌሎችም እርስ በእርሳቸው ይህች እንግዳ ናት በሃገር ውስጥ ያለማስተዋል ትሄዳለችና ይሉ ነበር። የጌታ ኢየሱስ ደቀመዝሙር እንደሆነ ዮሐንስን የሚያውቁት እንጃ ይህችስ እናቱ ትሆናለች ። በመስቀል ተሰቅሎ ታየው ዘንድ ትሮጣለች ይሉ ነበር፡ ሌሎችም ይህች የዮሴፍ ሚስት ትሆናለች ስለልጇ ወሬ ነግረዋት ይሆናል ይሉ ነበር። ሌሎችም መልኳ ደም ግባቷ እንዴት ያምራል እዩ ይሉ ነበር።ሌሎችም በዚህ ሃገር ከቶ እንደዚህች አላየንም መልኳ የልጇን መልክ ይሉ ነበር። በገበያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለእርሷ ይነጋገሩ ነበር። ነገሩም በገበያ ሁሉ ተሰማ። ሰሎሜም በኋላዋ ትከተላት ነበር፡ ሌሎችም ሴቶች ራሳቸውን ተከናንበው ይከተሏት ነበር፡ በልብ ከማዘንም ምንም ወደቀኝም ወደግራ መለስ ቀለስ አትልም ነበርና።

ልመናዋ በረከቷ በሀገራችን በኢትዮጵያ በሕዝበ ክርስቲያኑም ላይ ለዘለዓለሙ አድሮ ይኑር። አሜን።

ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት

‹‹ወአንትሙሰ ተዐቀቡ፤ ወግበሩ ተዝከረ ሕማማቲሁ፤ እናንተስ ተጠበቁ፤ የሕማሙን መታሰቢያ አድርጉ››፤/ትእዛዝ ፴፩/

ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ማግስት ጀምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችን የምሥጢረ ሕማማቱን ነገር መንፈስ ቅዱስ ሲገልጽለት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማታችንንም ተሸከመ››ማቴ. ፰፥፲፯/ኢሳ ፶፫፥፬/ ሲል ተናገረ፤ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፍቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግስት በመሸከም መከራ መስቀሉ ስለተፈጸመበት፤ እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ተባለ፤ ኢሳ. ፶፫፥፬፡፡

ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም የነበረው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንዑስ፤ በማዕከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትንና በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ታዲያ ሰሙነ ሕማማትን ጌታችን ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገው ትድግናን ቅዱሳን መጻሕፍት በየበኩላቸው ቢዘረዝሩትም ቸርነቱ፤ ርህራሄውና በጠቅላላው በአምላካዊ ጥበቡ የሰራቸው ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ሥራዎች ጸሐፊ፣ አንባቢና ሰሚ ሊደርስባቸውና ዝርዝራቸውን ሊከተላቸው ሲፈልግ፤ ገና በሀሳቡ ውጥን ላይ ድካም እንዲሰማውና ፍጡርነቱ ፈጣሪን እንዳይመረምር ያስገድደዋል፡፡

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በቃሉ ብቻ ዳን በማለት ሊያድነው ሲቻለው የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ በፈቃዱ ሰው የሆነበትን፤ ሰውም ከሆነ በኋላ የተቀበላቸው ልዩ ልዩ መከራ የተቀበለበት ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማትን የምናከብረው አባቶች ሐዋርያት የጌታን ጾም ለብቻው እንድናስበው እንዳደረጉን ሁሉ የጌታ ሕማማትም እንዲሁ በተለየ ለብቻው እንድናስበው የሰሩልን ሥርዓት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሳምንት ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተ ኩነኔ (፶፻፭፻ ዘመን) እና የጌታችን ሕማም መከራ እንግልት የሚታሰቡበት ነው ብለው ያስቡታል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሁለት ነገሮች ምክንያት በማድረግ በሰሙነ ሕማማት የሚተገበሩ ሥርዓቶች አሉ፤ እነርሱም፡-

ጥቁር ልብስ መልበስ

በሰሙነ ሕማማት ወቅት በተለይ በዕለተ ዐርብ ካህናቱ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ የኃዘንና የመከራ መገለጫ በመሆኑ በዚህ ወቅትም የጌታን ኃዘን መከራ ለማሰብና ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ባይገኝ ደግሞ የተገኘውን ልብስ ገልብጠው ይለብሱታል፡፡

በጸሎተ ሐሙስ ቃጭሉ ተቀይሮ ጸናጽል ይሆናል

በጸሎተ ሐሙስ በቅዳሴው ወቅት ቃጭሉ ተለውጦ ጸናጽል ይሆናል፤ ምክንያቱም በዘመነ ኦሪት የነበሩ አበው ጸሎታቸው ፍጽም ሥርዓት እንዳላሰጣቸው ለማጠይቅ ነው፡፡ ከቃጭል የጸናጽሉ ድምጽ ከርቀት እንደማይሰማ ሁሉ የአበው ጩኸት አናሳ መሆኑን ለማጠየቅ፤ የይሁዳን ግብር ለመግለጥና ይሁዳ ጌታን ለማስያዝ በድብቅ ያደባ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡

እርስ በእርሳችን አንሳሳምም፤ መስቀል አንሳለምም

እርስ በእርሳችን አለመሳሳማችን ይሁዳ በመሳም አሳልፎ መስጠቱን ለማሰብና ለማስረዳት ሲሆን መስቀልን ያለመሳለማችን ምክንያቱ ደግሞ፤ መስቀል በዘመነ ኦሪት የኃጥአን መቅጫ እንጂ የሰላም ምልክት እንዳልነበረ ለማጠየቅ ነው፡፡ መጻሕፍትም በመስቀሉ ሰላምን አደረገ እንዲሉ መስቀል አዳኝ የሆነ ጌታ ከተሰቀለ በኋላ መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡

አብዝተን መጾም አለብን

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አብዝተን እንድንጾምና እንድንጸልይ ያዙናል፤ ለምሳሌ በሰሙነ ሕማማት የሚችል በሁለት ቀን ውኃና ጨው ያለበት ምግብ እየተመገበ እንዲጾም ሲያዙን ያልቻለ ግን ፲፫ ሰዓት እየጾመ እየጸለየ ውኃንና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲመገብ አዘዋል፡፡

ለሙታን ፍትሐት አይደረግም

በሰሙነ ሕማማት ወቅት ለሞቱ ሰዎች ፍትሐት አይደረግላቸውም፤ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔን የምናስብበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ የነበሩ ሰዎች ፍትሐት እንደማይደረግላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ተስፋ ላለውና ለአማኝ እንጂ ለማያምን ትንሣኤ ዘለክብር፤ ለማይነሣ ቢሆን ፍትሐት አይደረግለትም፡፡

በወይራ ቅጠል ጥብጠባ ይደረጋል

በዕለተ ዐርብ ሥርዓቱን ከፈጸምን በኋላ ወደ ካህናት አባቶቻችን እየሔድን በወይራ ዝንጣፊ ጥብጠባ ተደርጎልን ቀኖና እንቀበላለን፤ በዚህ ወቅት የምንቀበለው ቀኖና የሰሙነ ሕማማትን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ወይራ ጽኑ በመሆኑ የጌታ መከራ ጽኑ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ሕጽበተ እግር ይደረጋል

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

በዚህ ወቅት በዋነኝነት ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ይነበባል

የሰሙነ ሕማማት ሥርዓተ ጸሎትና አገልግሎት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮት ጋር የተያያዘ ቢሆንም አሁን ያለውን ሥርዓት የያዘ ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጻሕፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ የዋለው ከጌታ ልደት በኋላ በ፲፬ተኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፬፻፹ ዓ.ም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ ዐዜብ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት፤ ቀደም ሲል በግዕዝ ብቻ ታትሞ በነበረው የግብረ ሕማማት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡

የመጽሐፉ ስያሜም ከጥንት ስሙ ጀምሮ ግብረ ሕማማት እንደሚባል በመጽሐፍ ውስጥ በብዙ ክፍል ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከጥንት ፍጥረት ከባሕርይ አባቱ አብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ በረቂቅ ጥበቡ ዓለማትንና ፍጥረታትን ሁሉ በየወገኑ ፈጥሮ እንደ ባሕርያቸው በቸርነቱ እየመገበና እየጠበቀ ሲገዛ ይኖራል፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ በተለየ አካሉ ዓለምን ከፈጠረበት በሚበልጥ ጥበብ ሰው ሆኖ፤ ሥጋን ለብሶ፤ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፤ አዳምን ከነዘሩ እንደገና በአዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ክብሩና ቦታው እንደመለሰው ያመለክታል፤ ፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፯/ ዕራ.፳፩፥፭/ ኢሳ. ፵፫፥፲፱/፡፡

ሆሳዕና፡ አሁን አድን

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት 8ኛው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል። ሆሣዕና ከሁለት የእብራይስጥ ቃላት יָשַׁע (ዮሻህ) እና נָא (ና) የመጣ ሲሆን ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ታሪኩም በ4ቱ ወንጌላት ላይ የተመዘገበ ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕጻናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ (ማቴ 21፡1-17፣ ማር 11፡1-10 ሉቃ 19፡29-38 ዮሐ 12፡12-16)


ጌታችንና ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ። ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት። ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ፈጣሪ የኹሉ ጌታ መኾኑን አመለከታቸው።

ፈታችሁ አምጡ የሚለው ትዕዛዝ ዓለም ሁሉ ከኃጢአት የሚፈታበት ዘመን እንደደረሰና ከእርሱም ባሻገር ካህናት በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣን የተሰጣቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡


ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ አደረጉበት፡፡ ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን ትሰውርልናለህ የሚል ምስጢርን የያዘ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ዙፋኑን በፍርሀት በረዐድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት እርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ተጓዘ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በእነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡


ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚህ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ዲዳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት ሲያመሰጥር ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡

በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አህያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡ ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡”
ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው እንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር “የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በንጹሕ አንደበታቸው አንደበታቸው ተፈቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ማመስገናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡


ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ጀርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደህ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኅን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡


ሆሳዕና የድህነት ጥሪ ስለሆነ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ሁሌም እንደ ህጻናቱ አሁን አድን ብለን ዘወትር እንጠራው ዘንድ ከ9ኙ ዓበይት በዓላት አንዱ አድርጋ በልዩ ክብር ታከብረዋለች፡፡

ከበዓለ ሆሣዕና ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡

ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም( ሳማ ሰንበት)

ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም
ሰንበትን የሰራት፣ በሰንበተ ክርስቲያን (እሑድ) መፍጠርን አሐዱ ብሎ የጀመረ፣ በሰንበተ ክርስቲያን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ፣ በሰንበተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ልኮ ቤተክርስቲያንን የመሠረታት የሰንበት ጌታዋ (እግዚእ ለሰንበት) ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበተ ክርስቲያን ይህችን ዓለም ለማሳለፍ እንደሚመጣ አምናና ተዘጋጅታ የምትጠብቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ለክርስቲያኖች ሁሉ የዘወትር ጉጉት የሆነውን የምጽአቱን ነገር ለማዘከር ከየዕለት አዋጇ ባሻገር በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት በምልዐት በዓል አድርጋ ታነሳዋለች።


ይህ በዓል ከሚከበርባቸው አብያተክርስቲያናት አንዱ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቤተክህነት የሚገኘው የሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም ነው።


ገዳሙ ከግራኝ አህመድ በፊት በ1026ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በወቅቱ ደብረ ዘይት ይሰኝ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ጠፍ ደብር ሆኖ ከቆየ በኋላ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አያት በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን በድጋሚ ሲቀና ሳማ ተሰኘ።
የገዳሙን ታሪክ የሚያትቱ መዛግብት እንደሚናገሩት ገዳሙ በግራኝ አህመድ ዘመን ከጠፋ በኋላ የገዳሙ መሥራች የሆኑት አባ ገብረ ሕይወትና ሌሎች መነኮሳት ታቦተ ተክለሃይማኖትና ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ከጎንደር ወደ ሸዋ መጡ።


ገዳማውያኑ ገለልተኛ በዐት ሲፈልጉ አሁን ሳማ ሰንበት በሚገኝበት የምንጃር ሸንኮራ አካባቢ ከሚገኝ ጠቦ ከሚሰኝ ወንዝ ሸንተረሩ ላይ በዐት ፈልፍለው ጽሙና ያዙ።


በዚህ ወቅት ሙገሬ ዛላ በተሰኘው ጫካ አንድ ተዓምር ተከሰተ። ዛፍ ሊቆርጥ ወደ ጫካው የገባ አንድ ገበሬ ዛፍ ለመቁረጥ ሲሞክር እሳት እየነደደ አላስጠጋ ይለዋል በዚህ ወቅት ካህናት ተጠርተው የምሕላ ጸሎት ሲደረግ በሥፍራው ላይ ታቦተ እግዚአ ሰንበት ተገኘና አውጥተው ሁኔታውን ለንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሳወቁ። ንጉሱም በጠቦ ወንዝ ሸንተረር ላይ ስለነበሩት መናንያን ሰምተው ስለነበረ ጽላቱ ለአባ ገብረ ሕይወት እንዲሰጥ በማዘዛቸው አባ ገብረሕይወት ተቀብለው ለረጅም ዘመን በዋሻቸው ዓመት እየቀደሱበት ቆዩ። በኋላ ላይም የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር አሑን ገዳሙ በሚገኝበት ደልዳላ መሬት ላይ ገዳሙን ገደሙ።

ገዳሙ ከዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጋር ግንኙነት እንዳለውም ይነገራል። ገዳሙ ከሰንበተ ክርስቲያን ስም ጋር በተያያዘ የተመሠረተ ብቸኛው ቤተክርስቲያን ሲሆን በውስጡ በርካታ የብራና መጻሕፍት የሚገኙበት ነው። በየዓመቱም በእኩለ ጾም በበዓለ ደብረ ዘይት የሚከብር ሲሆን በአንድ ወቅት ገዳሙ ተቃጥሎ ነበር። ከቃጠሎው በኋላ በክብና በሰቀላ መልክ ሁለት ሆኖ ተሠርቶ በክብ መልክ በተሠራው ታቦተ ተክለሃይማኖት፡ በሠቀላው ደግሞ ታቦተ እግዚአ ለ ሰንበት ገባበት ። በምርቃቱ እለት የተገኙት የወቅቱ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ገዳሟን “ብሔረ ሕያዋን” ሲሉ ሰይመዋታል።

የመጋቢት 27 በዓለ ንግሥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የት የት ይከበራል?

1 ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍና ቅዱስ ሚካኤል

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ

2)     ድልበር መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ ድልበር

3)    ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቀራንዮ

4)     ፍኖተ ሎዛ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ብርጭቆ ኮንዶሚንየም

5)     ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦አዲስ ከተማ/ክ/ከ አውቶብስ ተራ

6)    አስኮ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ አስኮ አዲስ ሰፈር
7)     ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ አባዶ

8)     አያት መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም እና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ /ክ/ከ አያት ጠበል
9)    ምስራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቀበና ካቴድራል(ቅዳሴ ቤት)

ልዩ ስም፦አራዳ ክ/ከ ቀበና

10)     ቦሌ ሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ሰሚት ወጂ

11)    ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ጉርድ ሾላ

12) ካራ አሎ ደብር ቅዱስ ደብረ ቀርሜሎስ መድኃኔዓለም እና ጻድቁ አቡነ ገሪማ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ ካራ

13)    ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል
ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ካዛንቺስ

14)     ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ወደብረ ትጉኃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ ክ/ከ ቀጨኔ መድሃኔዓለም

15) እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ማርያም ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ጉለሌ ክ/ከ እንጦጦ ቁስቋም
16)   ፈረንሳይ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ፈረንሳይ ብረት ድልድይ

17)     ቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ቦሌ ቡልቡላ
18)   ብሔረ ጽጌ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያምና መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ብሔረ ጽጌ

19)     ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጎፋ
18)     ጽርሐ ንግስት ቅድስት ሐና ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ፉሪ ሐና ማርያም

19)     ረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ
20)     ጎፋ ቤዛ ብዙሃን ቅድስት ኪዳነምሕረት ካቴድራል

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጎፋ ካምፕ
21)     ቶታል ፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለምቤ/ክ
ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቶታል 3 ቁጥር ማዞሪያ

22)  ማሕደተ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ልደታ /ክ/ከ ልደታ

23)   ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦ቂርቆስ ክ/ከ መስቀል ፍላወር

24)     ደብረ ፍስሐ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቂርቆስ /ክ/ከ ቂርቆስ

25)    ላፍቶ ደብረ ኢያሪኮ መድኃኔዓለም እና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አብያተክርስትያናት

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ(ላፍቶ)
26)     ፉሪ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 1 ኮንዶሚንየም

27)     ደብረ ሰሊሆም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ በርታ ሰፈረ ሰላም

28)  አቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ጋራው መድኃኔአለም

29)  ፈጬ ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ፈጬ


30)  ቃሊቲ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ሰፈረ ገነት

31)   ቃሊቲ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና አቡነ አረጋዊ ቤ/ክ
ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 12 ሰሪቲ

የተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ዘአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳም


በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ ብዙ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን ተከዜ ኪዳነ ምሕረት ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም አንዱ ነው። ገዳሙ የሚገኘው በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ ወረዳ  በዜሮ ሰባት ቀበሌ እና በመቄት ወረዳ ነው።  የአባቶች ገዳም ተከዜን ተሻግሮ ከወንዝ ማዶ የሚገኝ ሲሆን የእናቶች ገዳም ላስታ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ነው።  ገዳሙ የተከዜን ወንዝ በሥሩ እየጠጣ የቅዱሳን መነሀሪያ የሆነ በቆላማው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የተከዜን ወንዝ መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው። በስተ ሰሜን የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በደቡብ የአቡነ አሮን ገዳም በቅርብ ርቀት የሚያዋስኑት ገዳም ነው። ወደ ገዳሙ ለመድረስ በወልዲያ ወይ በባሕር ዳር በጋሸና አድርጎ ወደ ላሊበላ በሚወስደው መንገድ ላይ በተለምዶ ግራኝ አምባ (አዲስ አምባ) በመባል የምትታወቀው ከተማ ሲደርሱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ታጥፎ እስከ ገዳሙ ክልል ድረስ በተጠረገው መንገድ በእግር ወይም በመኪና መጓዝ ይቻላል።

በገዳሙ ውስጥ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እነሱም የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በእናቶች ገዳም፣ የመድኃኔ ዓለም በአባቶች ገዳምና የቀጭን አበባ ሥላሴ ናቸው። አመሠራረትና እስካሁን ያለው ታሪክ የገዳሙ መሥራች በጽኑዕ ተጋድሏቸው የሚታወቁት አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ሲሆኑ የተመሠረተውም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው።

የአባታችን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ትውልዳቸው ሸዋ ቡልጋ ሲሆን አባታቸው ንዋየ ጽዮን እናታቸው ፍቅርተ ክርስቶስ የሚባሉ ደጋግ  በተለይም ለምጽዋት እና እንግዳ ለመቀበል የተጉ ክርስቲያኖች ነበሩ። በዘመናቸውም እመቤታችን በእንግድነት ተገልጻላቸው ይህን ቅዱስ አባት እንደሚወልዱ አብሥራቸዋለች።  የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ዲቁና እንደ ተቀበሉ ወደ ታላቁ የአየለነ (እየላ) ሚካኤል መጥተው በዲቁና እያገለገሉ በጽኑ ተጋድሎ እየተጋደሉ ቆይተው ምንኵስናን ለመቀበል ወደ ደብረ በንኰል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄዱ። በዛም በብዙ ተጋድሎ ከቆዩ በኋላ በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኵስናን ተቀብለው በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከእመቤታችን እጅ የተቀበሏትን የቃል ኪዳን መታሰቢያዋ የሆነችውን ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ይዘው መሃል ተከዜ ወደሚገኘው ወደዚህ ገዳም መጥተዋል። ወደ ገዳሙ ሲደርሱም በአናምርትና በአናብስት ተከቦ በረድኤተ እግዚአብሔር ሲጠበቅ አግኝተውታል። ለታቦተ ኪዳነ ምሕረት ማደሪያ የሚሆን ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ሌሊት ተከዜ ወንዝ ውስጥ ሲጸልዩ እያደሩ ቀን ቀን አሜከላ አንጥፈው ሲሰግዱ በመዋል አብዝተው እየተጋደሉ መኖራቸውን ቀጠሉ። ገዳሙም የብዙ መናንያን መሰባሰቢያና ትልቅ ገዳም ሆነ። 

የተከዜ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በቅዱስ ገብረ ማርያም (ሐርቤ) ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን ገዳሙን ከምሥረታ ጀምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እስከ ማሳደግ ድረስ የደረሱት ታላቁ አባት ሐዋርያ ክርስቶስ ናቸው። እኒህ አባት በእግዚአብሔር ጥሪ የኦሪት መሥዋዕት ይሠዋበት በነበረው ከእየላ ሚካኤል ተነሥተው ወደዚህ ገዳም የተከዜን ወንዝ ተከትለው በመምጣት ዙሪያዋን አንበሶች እና ነብሮች አጥሯን ፤ ቅጥሯን እየጠበቁ አገኟት። ወደ ገዳሙ ሲገቡ ሰማይ ተከፍቶ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ ታያቸው። ጌታችን “ወዳጄ ሐዋርያ ክርስቶስ እንኳን ደኅና መጣህ፤ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ትኖራለህ” አላቸው። ከዚህ ጋር አያይዞም “ይህ ቦታ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብሎ ይጠራል” አላቸው። እርሳቸውም ከእመቤታችን በተቀበሉት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳኗ መታሰቢያ በሆነው በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ታቦት ስም የመሠረቱትን ገዳም ምዕራፈ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና መድኃኔ ዓለም አንድነት ገዳም ብለው ከጌታችን በተነገራቸው ቃል ኪዳን መሠረት መጥራት ጀመሩ። ሐዋርያ ክርስቶስም  በዚህ ገዳም እየጸለዩ እና እየሰገዱ ለዓለም ምሕረትን እየለመኑ ለሕሙማን ፈውስን እያሰጡ የምንኵስና ሕይወት በገዳሙ እንዲሰፋ እና እንዲጠናከር አድርገዋል። 

በመጨረሻም እግዚአብሔር አምላክ እስከ ዳግም ምጽአት ‘‘ሞት የለብህም’’ ብሎ  ስለ ፍቅራቸውና ስለ ጽኑ ተጋድሏቸው ዐሥራ ሁለት ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያ ክርስቶስም ቃል ኪዳን ተቀብለው በ፲፩፻፲፭ ዓ.ም. ግንቦት ፲፮ ቀን ተሠውረዋል።  አፄ ምኒልክ ለገዳሙ መገልገያ የሚሆኑ የተለያዩ ንዋየ ቅዱሳትን አበርክተዋል። ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ከባላምባራስ ጉግሳ ወሌ ጋር በየገዳማቱ እየሄዱ ይረዱና ለሕይወታቸው ይማፀኑ ነበር። ብዙ ተኣምራትንም አድርጋላቸዋለች።

ገዳሙ ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ  በሳቸው እግር በተተኩ አባቶች ፈተናዎችን እያለፈ በጽኑ ገዳማዊ ሕይወትና ሥርዓት ቢቆይም በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. በነበረው ድርቅ ምክንያት ተፈቷል። ከሦስት በማይበልጡ መነኰሳት እየተጠበቀ ያለ ምንም የውስጥ አገልግሎት እስከ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ቆይቷል። በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በአባ ኪዳነ ማርያም አማካኝነት በርካታ መናንያን ተሰባስበው ድጋሚ ተጠናክሮ በአሁኑ ሰዓት ፮፻፲፮ መናንያንና ከ፴ የሚበልጡ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙበት ገዳም ሆኗል። (ምንጭ በገዳሙ ከሚገኙ አባቶች)

ሥርዓተ ገዳም አንድነት ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጥብቅ የአንድነት ሥርዓት ያለው ነው።

በዚህ ገዳም ቁሪት፣ ዘረኝነት፣ ነገረ ሠሪነት ክልክል ከመሆኑም አልፎ ውጉዝ ነው። ማንም በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ሰው የገዳሙን የአንድነት  ሥርዓት የማክበር ግዴታ አለበት ። ምግብንም የገዳሙ መጋቢ ከቆነነው ውጭ መጠቀም ፈጽሞ ክልክል ነው። እንግዳ ወደ ገዳሙ  ለሥራ፣ ለጠበል፣ ለጸሎትና ለሱባኤ ሲመጣ ከመናንያን  በዓት ማረፍ ከተመደበለት ሊቀ አበው ውጭ ያለ ሥራና ያለ መጋቢው ፈቃድ ከሌሎች ጋር መገናኘት ክልክል ነው። ይህ እና ይህን የመሳሰሉት ሥርዓቶች በመናንያኑ ዘንድ የአንድነት ገዳማዊ መንፈሳዊ ሕይወት ቃል ኪዳን ውስጥ ተካትተው የሚታወቁ ናቸው።

ሥርዓተ ምንኵስና በገዳሙ ለምናኔ የሚመጣ ሰው ስለ መጣበት ምክንያት ተጠይቆ ያስረዳል። ቤተሰቡን ትዳሩን ልጆቹን በትኖ አለመምጣቱን፣ ወንጀል ሠርቶ ለመደበቅ አለመምጣቱን፣ ገዳሙን በማንኛውም መንገድ ሊጎዳ አለመምጣቱን፣ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ  እና መሰል ሁኔታዎችን ተጠይቆ ለ፺ ቀናት (ለሦስት ወራት) ደጅ እንዲጠና ይደረጋል። ከዚያም በሰላም ለኪ ወደ ገዳመ ማኅበሩ ገብቶ ለሦስት ዓመት የአመክሮ ጊዜ ይሰጠዋል። 

ከሌላ ገዳም ፈልሶ የመጣ እንደ ሆነ በምን ምክንያት ከነበረበት ገዳም እንደ ወጣ፣ በምግባር ችግርም ተባሮ እንደ ሆነ ይጠየቃል። ‹ነበርኩበት› ወዳለው ገዳም ተደውሎ ስለ እርሱ ይጠየቃል። ፈተና ጸንቶበት የመጣ እንደ ሆነ ይቀበሉታል። በምግባር ብልሹነትና ሁከት በማስነሣት የተባረረም ከሆነ ተለይቶ እንዲመከርና በጥንቃቄ ገዳመ ማኅበሩን በማይበጠብጥበት ሁኔታ እንዲታረም ይደረጋል። ምክንያቱም ሁከት ይፈጥራል በሚል ሥጋት ብቻ እንደ መጣ ቢባረር ወደ ዓለም ተመልሶ ይወድቃልና የመታረሚያና የጽሞና ጊዜ ይሰጠዋል። የማይመለስ ከሆነና ለገዳማዊ ሕይወት እንቅፋት የሚሆን ሆኖ የተገኘ እንደ ሆነ  ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል።

ምንፍቅናንና ሁከትን ሊዘራ የመጣ ከሆነ ግን ሳይውል ሳያድር ገዳሙን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል። በገዳሙ ውስጥ የአመክሮ ጊዜያቸውን በጥሩ ገዳማዊ ሕይወት ላሳለፉ አባቶችና እናቶች አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የልደታቸው መታሰቢያ በሚከበርበት ሐምሌ ፲፮ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም በገባችበት በኅዳር ፮ የምንኵስና ሥርዓታቸው ይፈጸማል።

ሐምሌ ፲፮ የጻድቁ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዓለ ንግሥ ሲሆን በኅዳር ፮ ደግሞ እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ደብረ ቍስቋም የገባችበት ዓመታዊ በዓል ነው። ስለዚህ ወደ መርንኵስና ሕይወት ለሚቀላቀሉ አባቶችና እናቶች ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ለመቀበል ነው።  በገዳሙ ሥርዓት መሠረት ከወላጅ አልባዎች ውጭ ለምናኔ የሚመጡ ዕድሜያቸው ከ፲፰ ዓመት በታች የሆኑትን አይቀበልም። ይልቁንም ውስጣቸው ያለው መንፈሳዊነት ልምላሜው የማይቋረጥበትን መንገድ አመላክቶና ምክር ሰጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመልሳል። ፩.፫.የአመጋገብ ሥርዓት አመጋገብን በተመለከተም ገዳሙ ሥርዓት አለው።

በበዓለ ሃምሳ በቅዳሜና እሑድ ከጧቱ  ሦስት ከሃያ እና ዘጠኝ ሰዓት ከሃያ ላይ፣ ሥራ በማይሠራባቸው በዓላትና በፍልሰታ በቀን አንድ ጊዜ ዘጠኝ ሰዓት ፣ በሰሙነ ሕማማት ከዋክብት ሲታዩ፤ በሌሎች ቀናት ለአረጋውያንና ለካህናት ዘጠኝ ሰዓት በቀን አንድ ጊዜ ሲሆን ለሚወጡት ለሚወርዱት (ሥራ ለሚሠሩ) አርድእት በሰባት ሰዓት የመቁንን ሥርዓት ተሠርቷል። በገዳሙ አንድነት በ፳፻፰ ዓ.ም. በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ዐበይት በዓላትንና ዓመታዊ የቅዱሳን መታሰቢያ በዓላትን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ በገዳሙ ውስጥ አስካሪ መጠጥ አይዘጋጅም፤ ሥጋ አይበላም፤ ከውጭም ይዞ መግባት ፈጽሞ ክልክል ነው።

በገዳሙ ሕመምተኞች የሚረዱበት በአባቶችም በእናቶችም ቤተ ሕሙማን ያለ ሲሆን እነሱን የሚንከባከቡ ትራስ ቀና የሚያደርጉ የሚያጎርሱ ልብሳቸውን የሚያጥቡ አረጋውያንንም የሚጦሩ ሊቀ አበው አሉ። በገዳሙ ውስጥ አእምሮውን ላጣ፣ ሂድ ሂድ ለሚለው ሰው ለ፫ ቀን፣ ለ፯ ቀን ጸሎተ ማርያም ይደረግለታል በሁሉም ጸሎቶች ያታሰባል፤ የንስሓ አባቱ እንዲጎበኙትና እንዲመክሩት ይደረጋል። የማይተወው ከሆነና የሚጸናበት ከሆነ እግረ ሙቅ ይደረግለታል። ከዚህም በተጨማሪ የምክርና የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት በገዳሙ አባቶችና እናቶች የሚገለገል መለስተኛ ክሊኒክም አለ። የቤተሰብ ጉብኝት ሥርዓት ዘመድ ጥየቃንም በተመለከተ ገዳሙ ሥርዓት አለው። ማንኛውም የመናኝ ቤተሰብ ዘመድ ‹በዚህ ገዳም ይገኛልና ልጠይቀው መጥቻለሁ› ካለ የገዳሙን ህልውና የሚፈታተን ሰው አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንዲሁም ስለ መናኙ ማንነትና ስም ይጠየቅና “የተባለው ሰው በገዳሙ ስለ መኖሩ እናጣራለን” ተብሎ በእንግዶች ማረፊያ እንዲያርፍ ይደረጋል። ከዚያም የተባለው ሰው በገዳሙ ያለ ከሆነ እከሌ የሚባል ሰው ያውቅ እንደ ሆነ ተጠይቆ “አውቀዋለሁ” ካለ “ሊጠይቅህ መጥቷልና ልታገኘው ትፈልጋለህ ወይ” ተብሎ ይጠየቃል። “አዎ አግኝቸው ስለ ደኅንነቴ እንዲያውቅና ስለ ሁሉም ነገር ልነግረው እፈልጋለሁ” ካለ እንዲገናኙ ይደረጋል። “አይ ላገኘው አልፈልግም ደኅና መሆኔን ነግራችሁ ሸኙት” ካለ ወይም “አይ ለምናኔ ሕይወቴ ፈተና ስለሚሆንብኝ ላገኘውም አልፈልግም እዚህ መኖሬንም አትንገሩት በጥሩ የእንግዳ አሸኛኘት አስተናግዳችሁ ሸኙት” ካለ በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ይሸኛል።

የገዳሙ አስተዳደር የአገልግሎት መዋቅር ገዳሙን የተመለከተ ማንኛውም ሕግና ሥርዓት ሲወጣና ሲወሰን ሁሉም የገዳሙ አንድነት በተገኙበት ነው። ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ቀጥሎ የገዳሙን የትኛውንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርና የገዳሙ ሥርዓተ ገዳም በትክክል እየተተገበረ መሆኑን የሚከታተል ውይይት አድርጎ ለችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የአበው መማክርት አስተዳደር ጉባኤ የሚባል ፲፫ አባላት ያሉት አበ ምኔቱ፣ እመ ምኔቷ፣ አፈ መምህሩ፣ ጸሓፊው፣ መጋቢው፣ ሊቀ አርድእቱ እና የሰባቱ ዘርፎች ተጠሪዎች ያሉበት ነው።


የሥራ ዘርፎች
የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ፦ ይህ ዘርፍ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና የአብነት ትምህርት ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ነው።


የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት ዘርፍ፦  በዚህ ዘርፍ ውስጥ የማኅበር መቁነን ዝግጅት ክፍል እና የቁሳቁስ አቅርቦት አገልግሎት ክፍል ይገኛሉ። በውስጡ እንጨት ፈላጮች፣ አህያ ጫኞች ፣ ሊቀ አበው ፣ ባለ ተስፋዎች፣ እጓል መጋቢዎች እና አረጋውያንን ያካተተ ነው።

የአገልግሎት ዘርፉ ሥያሜ (የቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት) የሚለው በገዳሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያካትት ቢሆንም  ሥያሜው ግን በዚህ ክፍል ለተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ብቻ ስተለተሰጠ እኛም ሥያሜውን እንዳለ ወስደነዋል። 


የእጅ ሥራ ዘርፍ፦  በውስጡም የጥሬ ዕቃና ምርት ማደራጃ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የጥልፍ ሥራና የኅትመት ሥራ ክፍሎችን በሥሩ የያዘ ነው። በእደ ጥበብ ሥራ ያለውን ከምርት እስከ ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር ያለው በዚሁ ዘርፍ ሥር ነው። 


የግብርና ልማት ዘርፍ፦ በውስጡም የእርሻ፣ የደንና የአትክልት ልማት እና የርባታ ክፍሎችን የያዘ ነው።


የግንባታ ልማት ዘርፍ፦  የቤቶች ግንባታ፣ የመንገድ ሥራና የውኃ ሥራ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ዘርፍ ነው።
የቴክኒክና የኢንዱስትሪ ዘርፍ፦ የተሽከርካሪ አገልግሎት፣ የወፍጮና ሌሎች የሞተር ነክ አገልግሎቶች እና የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው።

የሥነ ጽሑፍና ቅንብር ሥራዎች ዘርፍ፦ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ የድምፅና የምስል ቅንብር ሥራዎች እና የድምፅና ምስል ቀረጻ ክፍሎችን የያዘ ዘርፍ ነው። ሁሉም የገዳሙ ማኅበረሰብ ከላይ ከተጠቀሱት የሥራና የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የተካተተ ነው። የዘርፎቹም ተጠሪዎች የአበው መማክርት ጉባኤ አባላት ናቸው።

ምንጭ – ሐመር 2012