ታላቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ

“ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ፤ ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኵሎሙ መጻሕፍት ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ”። ትርጉም፦ የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ አገርን በጥዑም ማሕሌትና በማያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ለቅዱስ ያሬድ ሰላምታ ይገባል።”ሊቁ አባ ጊዮጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።


ያሬድ ማለት ርደት፣ ወሪድ፣ ማለትም መውረድ ማለት ነው። ከአዳም ስድስተኛ በሆነው በመላልኤል ልጅ በያሬድ ጊዜ ደቂቅ ሴት ከደብር ቅዱስ ወደ ደቂቀ ቃየን ወደ ምድረ ፍዳ ስለወረዱ ያንን ለማስታወስ አባቱ መላልኤል ያሬድ ብሎታል። ኩፍ5፥21-22 በኢትዮጵያም ዳግማዊ ያሬድ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተነስቶ ሰማያዊውን ልዩ ጣዕመ ዜማ ወደ ኢትዮጵያ የሚያወርድ ነውና ይህንን ለመግለጽ እግዚአብሔር አምላክ በእናቱ እና በአባቱ ላይ አድሮ ያሬድ እንዲባል አድርጓል። ምስጢሩ ልዩ ጣዕመ ዜማን ከሰማይ የሚወርድ መሆኑን ያሳያል።


አንድም ያሬድ፦ ማለት ንብ ማለት ነው። ንብ የማይቀስመው አበባ እንደሌለ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ከቅዱሳት መጻሕፍት የማይጠቅሰው የለምና።


አንድም ያሬድ፦ ማለት ረአዬ ምስጢር ነጻሬ ኅቡአት “ምስጢር ተመልካች ምስጢር ገላጭ ማለት ነው። ምስጢር ገላጭ መባሉ የመላእክት ምስጢራት የነበሩትን ጸዋትወ ዜማ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯልና፤ ” ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን፤ ከቅዱሳን መላእክት በሰማይ የሰማኹት ዜማ ምን ይረቅ! ምን ይጠልቅ!” እንዲል። ምስጢር ተመልካች መባሉ ደግሞ ኅቡእ (ስውር) የኾነ የነቢያት፣ የሐዋርያትን፣የሰማዕታትና የጻድቃን ገድል አምልቶ አስፍቶ ስለሚናገር ነው።


አንድም ያሬድ፦ ማለት እንዚራ፣ በገና፣ መሰንቆ ማለት ነው። እነዚህ በስልት በስልት ሲመቱ ለሚሰማቸው ደስ እንዲያሰኙ፤ የቅዱስ ያሬድም ዜማ በንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ አደባባይ በቤተ ክርስቲያን ሲሰማ መላእክት ፣ሰውንና እንስሳትን ደስ ያሰኛልና።


ታላቁ ማኅሌታይ ካህኑ ቅዱስ ያሬድ፦ ከእናቱም ቅድስት ክርስቲና (ታውክልያ) ከአባቱ ከቅዱስ አብዩድ (ይስሐቅ) በአኵስም (አክሱም) በ505ዓ.ም ሚያዝያ5 ቀን ተወለደ። አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር። በዚያን ጊዜ የብሉያትና የሐዲሳት መምህራንና ተማሪዎች የሚገኙት አክሱም ጽዮን ነውና የአኵሱም ቤተ ቀጢን (ቤተ ጉባኤ) መምህር የነበረው የእናቱ ወንድም አጎቱ መምህር ጌዴዎን ይባል ነበር።

ቅዱስ ያሬድ የሰባት ዓመት ሕጻን በኾነ ጊዜ አባቱ ስለ ሞተ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በዚያ ዘመን አጠራር ለጌታው ዐደረ። ጌታውም የዐፄ ገብረ መስቀል ቢትወድድ አዛዥ ዜና ገብርኤል ይባላል። ያሬድን ዐቅሙ ለጉልበት ሥራ እንዳነሰ አይቶት ወደ አጎቱ ላከው።

መምህር ጌድዎንም ዐቅሙንና ዕውቀቱን በመገመት ለተማሪዎች “በሉ ፊደል አስቆጥሩት” አላቸውና ትምህርቱን ጀመረ። ኾኖም ቃለ እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለነበር አብረው የሚማሩትም ሕፃናት “ሰነፍ ያሬድ ዕንጨት ስበር ውሃ ቅዳ” እያሉ አፌዙበት፤ ቀለዱበት። አጎቱ ጌዴዎንም ከትምህርቱ ድክመት የተነሣ በጨንገር (በአለንጋ) ቢገርፈው ሕፃኑ ያሬድም በዚህ ተበሳጭቶና ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ወደ መደባይ ወለል ደረሰ። ለጥሙ ከምንጭ ውሃ ጠጥቶ ለድካሙ ከዛፋ ጥላ አረፈ። በምን ምክንያት ከጓደኞቹ በታች እንደኾነ ሲያስብና ሲያሰላስ ሳያዝንና ሲተክዝከቆየ በኋላ እግዚአብሔር አንድ የሚያጽናና ምልክት አሳየው። ይኸውም አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፋ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ ተማሪ ያሬድም ከዚህ ትል ትዕግሥትን፣ ጽናትን፣ ጥረትን፣ ስኬትን ትምህርት ወስዶ እኔም እኮ ተስፋ ሳይቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረግኹ እግዚአብሔር ያሳካልኛል ብሎ በተስፋ ተጽናንቶ እንደገና ወደ መምህሩ በመመለስ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ። ወደ መደባይ ያደረገው የነበረውን ጉዞ ሠርዞ ወደ አክሱም ከተማ ወደ መምህሩ ጌድዬን ጉባኤ ቤት ተመለሰ። በመጸጸት አጎቱን “አባቴ ስለተቆጣኸኝና ስለገረፍከኝ ተበሳጭቼ ሔጄ ነበር ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ እግዚአብሔር ስላስተማረኝ ተጸጽቼ መጥቻለኹ። ከእንግዲህስ ወዲህ እየተቆጣኽና እየገሠጽህ አስተምረኝ” ሲል አሳቡን ሳይደብቅ ገለጸለት።


አጎቱም ያሬድ ተጸጽቶ በመመለሱ በጣም ተደስቶ ዐይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ ፈጣሪውን እያለቀሰ በለመነለት ጊዜ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለያሬድ ዕውቀትን ገለጸለት። የያሬድ ኅሊናው ተከፍቶለት መዝሙረ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መሓልየ ነቢያት፣ መሐልየ ሰሎሞንን፣ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ንባባቸውን እስከ አገባባቸው አወቀ።
ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቃሉ ይዞ ሲያስተምር ሳለ የትምህርቱን ጥራት፣ የሃይማኖት ጽናት፣ ደግነቱንና ትዕግስቱን፣ ትሕትናውና ተልኮውን በመምህሩና በካህናቱ ተመስክሮለት የአክሱም ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ሢመተ ዲቁና ሾመው። ቅዱስ ያሬድ የታላቋ የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አጋልጋይ ዲያቆን ኾነ።


ትምህርቱን በስፋት ስለቀጠለበት የመጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳት፣ የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ ሊቅ ኾነ። ቅዱስ ያሬድም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋራ በቤተ ቀንጢን ጉባኤ ቤት ይውል ስለነበር ገዳማዊ ሕይወት ከእነርሱ በመማር እንደ እነ አቡነ አረጋዊ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጰንጠሌዎን በድንግልና ተወስኖ በንጽሕና ሲያገለግል ቆይቷል።

ኅዳር 5 ቀን 527 ዓ.ም እግዚአብሔር ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን (መላእክት በአዕዋፍ ተመስለው) እርሱ ወዳለበት ላከለት። እነርሱም ያሬድ ባለበት ቦታ አንጻር በአየር ላይ ረብበው በግእዝ ቋንቋ “ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ (የተመሰገንክና የተባረክ ያሬድ ሆይ፤ አንተን የተሸከመች ማሕፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው”) ብለው አወደሱት። ቅዱስ ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን አዕዋፍ አየና “እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችኹ” አላቸው። ከሦስቱ አዕዋፍ አንዷም “ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌትን ሰምተኽ እንድታዜም የተመረጥኽ መኾኑን እነግርህና እናበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልከን መጥተናል” አለችው። ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ።


በዚያም ቅዱሳን መላእክት የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ እግዚአብሔር በቅኔና በከፍተኛ ደምፅ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ኾነው ሲያመሰግኑ እንዲሁም የእንዚራ፣ የበገና የመሰንቆ ድምፅ በሰማ ጊዜ ካለበት ሥፍራ እነርሱ ወዳሉበት ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም።

በመጨረሻም እነዚያ አዕዋፍ ወደ እርሱ ተመልሰው መጡ። “ያሬድ ሆይ፤ የሰማኸውን አስተውለኸዋል?” ብለው ጠየቁት እርሱም “አላስተዋልኹም” ብሎ መለሰላቸው። እንግዲያውስ አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ጥራ፤ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ከእግዚአብሔር መዘምራን ከቅዱሳን መላእክት በየዐይነቱ ዜማ ያለውን ማሕሌት ትማራለኽ፤ ታጠናለኽ” አሉት። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ማሕሌቱን በየዓይነቱ አውጥቶ “መልካምን ነገር ልቤ ተናገረ” እያለ ከቅዱሳን መላእክት ተማረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ሌሎችን አገልጋዮች ሰዎች ይሾሟቸዋል፤ አንተን ግን እኔ ሢመተ ክህነት (ቅስና) ሾሜኻለሁ” አለው።


ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዓታቸው ዐይቶ፤ ማሕሌታቸውን አጥንቶ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል። ከዚያም ኾኖ ፊቱን ታቦተ ጽዮን ወዳለችበት ወደ ምሥራቅ አዙሮ እጆቹን ዘርግቶ እንዲህ ብሎ ሰማያዊ ዜማን ለመጀመርያ ጊዜ በአክሱም አደባባይ (ዐውደ ምሕረት) ዘመረ።


“ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብር ግብራ ለደብተራ”። ብሎ በዓራራይ ዜማ አዜመ። ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር አሁንም ላለ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው። ስለምን በዓራራይ ዜማ ጀመረ ቢሉ ቋንቋን የሚያናግር ምስጢር የሚያስተረጉም መንፈስ ቅዱስ የገለጠልኝ ዜማ ነው ሲል ነው። ምክንያቱም ዓራራይ ዜማ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነውና።


ከሰማይ እንደተመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣዕመ ዜማውን ያሰማበት ቦታ “ሙራደ ቃል” (የቃል መውረጃ) እየተባለ ይጠራል። ይኸውም ዜማው ከሰማይ የወረደ ለመኾኑ እውነተኛ ማስረጃ ነው። ይህችንም ዜማ “አርያም” አላት። ይህም ማለት ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው።


ከዚህም በኋላ ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነ አትናቴዎስ፣ ቄርሎስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ። የመጽሐፉ የድርሰቱ ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በትግርኛ ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው፤ ሙሾ የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግእዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግእዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው ፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግእዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ ፣ታዝሎ የሚነገር ማለት ነው። ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ፣ አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው። ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ.ም ሲሆን በአፄ ገብረ መስቀል መንግሥት ነው።


አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ ይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።


ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾች አስደነቀ። ለዚህም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ የብርና የወርቅ የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽላት አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ ጠገቡ።


ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተክርስቲያኑን እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ “ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ ፤ ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተ ክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ።

“ይሔውጽዋ መላእክት እንተ በሰማያት ይሔውጽዋ መላእክት እስመ ማኅደረ መለኮት ይእቲ ዖድክዋ ዖድክዋ ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምስአል ወምስጋድ ወምስተስርዬ ኃጢአት ይእቲ ቅድስት ደብተራ፤ በሰማያት ያሉ መላእክት ይጎበኟታል፤ የመለኮት ማደሪያ ናትና መላእክት ይጎበኟታል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዞርኋት፣ ዞርኋት፣ ዞርኋት የሕንፃዋን ማማር ዐየኹ፤ እርሷ መጸለያ፣ መስገጃና የኃጢያት ማስተሰረያ ቅድስት ማደርያ ናትና”። እያለ ስለዘመረ ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሎ ተጠራ። ደብረ ዳሞ የሚለው ስያሜ በኋላ የወጣ ስም እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ። ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ገዳም ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ወደ አክሱም ተመለሰ።


ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድ ጋር አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በጣና በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።


ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ አቡነ አረጋዊን “ዑድ አባ መንገለ ምሥራቅ ወዑዳ ለዛቲ ደብር፤ ዙር አባ ወደ እርስዋም ትወጣ ዘንድ በምሥራቅ በኩል ዙር” አላቸው ወደ ምስራቅ ሲዞሩ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነጭ ሐረግ ዘረጋላቸው እርሱን ይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ገዳም ምሥራቃዊ አቅጣጫ ቅዱስ ያሬድን የምትዘክር “ከርሞ አይደርቅ” የምትባል ዛፍ አለች። ቅዱስ ያሬድ በዚች ዛፍ ሥር ተቀምጦ ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መጽሐፍ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ስላስተማረበት ይህም ቦታ ገዳም እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ከአኵሱም ወደ ማይኪራህ አምርቶ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን በአካለ ነፍስ ከሶርያ አባ ሕርያቆስ ከብሕንሳ አምጥታ ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን ንባቡን እየነገሩት በዜማ እንዲደርስላት አድርጋለች። ከዚህም አያይዞ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን ንባቡ የሌሎች ሊቃውንት ድርሰት የሆኑትን ዐሥራ አራቱን ቅዳሴዎች በዜማ አዘጋጀ።


ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ጸለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን ድርሰቱን ደረሰ። ከዚህ በኋላ አገው፣ ፎገራ እና ወደ ሌሎችም ቦታዎች እየዞረ አስተማረ።


ቅዱስ ያሬድ በአኵሱም ወንበር ዘርግቶ፣ ጉባኤ አስፍቶ ደቀ መዛሙርቱን እያስተማረ ሲኖር በጾመ ፵ ሱባኤ ላይ ሳለ አንድ ቀን በምኵራብ ሰሞን ስለምናኔው እያስታወሰ በተመስጦ ሲዘምር የዜማው ጣዕም እንኳን ሌላውን ራሱን እጅግ ይመሥጠው ነበር። በጣዕመ ዝማሬው ተመሥጦ ሲያዳምጥ የነበረው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ የዐፄ ገብረ መስቀል ዐይን ዐይኑን እየተመለከተ ሳይታወቀው በመስቀል ስላጢኑ (በበትረ መንግሥቱ ዘንግ) ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው። ቅዱስ ያሬድ ግን ከሰማያት የተገኘች ቃለ ማሕሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ ሕመሙ ሳይታወቀው ቀጠለ፤ ደሙም ያለማቋረጥ ፈሰሰ።
ቅዱስ ያሬድ የጀመረውን በፈጸመ ጊዜ ንጉሡ ደንግጦ በትሩን ከቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ቢነቅለው ደሙ በኃይል ይፈስ ጀመር። ያን ጊዜ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል የቅዱስ ያሬድን ትዕግሥት ባለ ጊዜ በመደነቅ፣ በመገረምና በመደንገጥ ዝም በማለት አፉን ይዞ ቆመና ምድራዊ ዋጋ የሚፈልግ መስሎት “ካህን ያሬድ ሆይ የምትፈልገውን ዋጋ ጠይቀኝ” አለው። ቅዱስ ያሬድ መልሶ “የፈለግኹትን እንዳትከለክለኝ ቃል ኪዳን ግባልኝ” አለው። ንጉሡም የጸና ቃል ኪዳን ለቅዱስ ያሬድ ገባለት። ቅዱስ ያሬድም “ከዚህ ሐላፊ ዓለም ክብር ተለይቼ መናኝ ሆኜ እንድኖር ተወኝ አሰናብተኝ” ብሎ አሳብን ገለጸለት።


ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ያሬድ ካህን የጠየቀውን እንዳይከለክለው ከአፉ የወጣውን መሐላ አስቦ በምናኔ አሰናበተው እንጂ ሊከለክለው አልቻለም።


ቅዱስ ያሬድ ካህንም የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ወዳለችበት ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሁለት እጆቹን በታቦተ ጽዮን ላይ አኑሮ “ቅድስት ወብፅዕት፣ ስብሕት ወቡርክት፣ክብር ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዓርገ ሕይወት” ብሎ በደረሰው አንቀጸ ብርሃን ጸሎት እመቤታችንን አመሰገ። በዚህ ጊዜ እጁ በታቦተ ጽዮን ላይ ረቦ በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ ስለነበር ከመሬት አንድ ክንድ ከፍ ከፍ ብሎ ይታይ ነበር። እስከመጨረሻው በከፍተኛ ቃል በዕዝል ዜማ እየዘመረ እግዚአብሔር እና እመቤታችንን ከአመሰገነ በኋላ እመቤታችን የቀና መንገድ እንድትመራውና እስከ ፍጻሜ ገድሉ ትረዳው ዘንድ በጸሎት ለመናት። እመቤታችንም መልሳ “ሰማያዊት ጽዮን ያደረግኻት መቅደሴን፣ በመዝሙር በማሕሌት ምስጋና የኪሩቤልና የሱራፌል ወገን ሰማያውያን ያደረግኻቸው ልጆቼ ካህናትን እንዴት ትተህ ትሔዳለህ” ብላ ቃል በቃል አነጋገረችው። የመንገዱን ስንብት እስክትፈቅድለት ድረስ በለቅሶና በእንባ ዳግመኛ ለመናት እርሷም እንዲሔድ ፈቀደችለት።


የቅዱስ ያሬድ ምናኔ፦ ወደ ገዳም ሊሄድ ተዘጋጀ በዚህ ጊዜ የሚወዱት ካህናት፣ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ተከትለውት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት። ከእርሱ በሚለዩበትም ጊዜ “ሰላመ ነሳእነ ወሰላም ኃደግነ ለክሙ ወሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስለ ኩልክሙ፤ ሰላምን ከእናንተ ተቀበልን ለእናንተም ሰላምን ተውንላችሁ የእግዚአብሔር ሰላምም ከሁላችሁ ጋራ ይኹን” ብሎ በዜማ ተሰናበታቸው። ዳግመኛ “ወሰላም እግዚአብሔር እንተ ኵሉ ባቲ ተሀሉ ወትረ ምስለ ኵልክሙ፤ ፍቅርና ስምምነት ሁሉ ያለበት የእግዚአብሔር ሰላምታ ሁል ጊዜ ከሁላችሁ ጋራ ትኑር” ብሎ በጣዕ ዜማው መረቃቸው። ካህናቱም ይህን ሰምተው አለቀሱ። እርሱም ከእርሱ ጋራ አለቀሰ። በዚሁ ጣዕመ ዜማው የመጨረሻ ቡራኬውን ሰጣቸውና እርስ በእርሳቸው ተሳስመው ተነሰነባብተው ከእርሱ በመለየታቸው እያዘኑና እየተከዙ ወደ አገራቸው አኵሱም ተመለሱ። እርሱ ግን የተከዜን ወንዝ ተሻገረ። የወንዙ ፏፏቴና ጎርፍ እንሚጮህ አንበሳ ሲጮህ በሰማ ጊዜ “አኅለፍኮሙ በእግር እንተ የብስ ማእከለ ባሕር ተከዜ…፤ በተከዜ ባሕር መካከል በእግር እንደሚሻገር በደረቅ አሻገርካቸው…” እያለ በረቀቀ ምስጢር እግዚአብሔርን በማመስገን እየዘመረ ሲሒድ አንዲት ሴት ውሃ ቀድታ ወደ ቤቶ ስትመለስ ድምፁን ሰምታ ወይ ቃል! ወይ ቃል! እንዴት አንጀት ይበላል! ምንኛስ ያሳዝናል! ብላ ደጋግማ ስለተናገረች ቅዱስ ያሬድ ቆሞ የዘመረባት ቦታ “ወይ ቃል” ተብላ ተጠራች። ዛሬ ይህች ቦታ ጎንደር ክፍለ አገር ደባርቅ አካባቢ “ወይ ቃል” ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች።


ቅዱስ ያሬድ ወደ ሰሜን ተራሮች ሔዶ ጸለምት ወጥቶ ብርድ በጸናበት በረዶ በተከማቸበት ሳኔር ተብሎ በሚጠራ በሐዊ ዐምባ ጽሞና ይዞ ተቀመጠ። በዚያም በብዙ ትጋት በጾምና በጸሎት ይልቁንም በስብሐት እግዚአብሔር ብቻ ተወስኖ ጉባኤ ዘርግቶ፣ ትምህርት አስፍቶ ከሱራፌል መላእክት እንደተማረው አድርጎ ከጸለምት፣ ከስሜን፣ ከአገውና ከሌላ አገር ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ሁሉ ማሕሌተ እግዚአብሔር እያስተማረ ኖረ።
ቅዱስ ያሬድ ከትውልድ አገሩ አኵሱም መንኖ ከወጣ በኋላ ትዕግሥቱን እያዘወተረ ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ በማስተማር በገዳመ ስሜን ኖረ። ቅዱስ ቍርባን ለመቀበልና ቅዱሳት ገዳማትን ለመሳለም በፈለገ ጊዜ በሠረገላ ብርሃን ተጭኖ አኵሱም ደርሶ ቅዱስ ቍርባን ተቀብሎ ሌሎች ገዳማትንም ይሳለም ነበር።


በመጨረሻ ቅዱስ ያሬድ ካህን ዘመኑን ሁሉ በመላእክት ማኅሌት እግዚአብሔርን በማገልገልና ይህን ማኅሌት ለሚከተሉት ደቀ መዛሙርት በማስተማር ዘመኑን ፈጽሞ ለሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በምናኔ ታግሦ በገድሉና በጣዕመ ዜማው ፀላኤ ሠናያትን ድል አድርጎ ከዚህ ዓለም ድካምና መከራ የሚያርፍበት፣ የሚሰወርበት ቀንና ሰዓት መድረሱን በጸጋ በዐወቀ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ “ይቤ ጳውሎስ ኃላፊ ንብረቱ ለዝንቱ ዓለም አኃውየ አስተፋጥኑ ገቢረ ሠናየ አነሰ በድረየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሠለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየዓሥየኒ መኰንነ ጽድቅ” 2ጢሞ4፥7-8 እያለ በሚያራራ ቃል ምክሩን ሰጥቶ ተሰናበታቸው። እነርሱም ምክሩን ተቀብለው “አባ አቡነ፣ አባ መምህርነ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተኀድገነ፤ አባታችን መምህራችን ወደ የት ትሔዳለኽ? ለማንስ ትተወናለኽ? እያሉ ሲያዝኑ ሲያለቅሱ በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ግንቦት11 ቀን በ571ዓ.ም ተሰወረ።


ቅዱስ ያሬድ ከመሰወሩ በፊት በእግዚአብሔር አምነው በእርሱ ቃል ኪዳን ለተማፀኑ፣ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ላሳነጹና ላነጹ፣ መጽሐፈ ገድሉን ለጻፈና ላጻፈ፣ ዕጣን ቋጥረው ጧፋና ጥላ ገዝተው መገብሪያ ሰፍረው፣ መጋረጃና ሌሎችንም ንዋያተ ቅዱሳት ገዝተው አምጥተው በስሙ ለታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ላበረከቱት ሁሉ የማየሠልፈውን ርስት መንግሥተ ሰማያት እንደሚያወርስለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ገብቶለታል።


ንዑድ ክብር ቅዱስ ያሬድም ስውር ዋሻ ውስጥ ገብቶ ፈጣሪውን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት ለመነው “መታሰቢያዬን የመምህሬን የጌድዮንን መታሰቢያ የሁላችንንም አባት የአዳምን መታሰቢያ ያደረገው እንግዲህ ዋጋው ምንድን ነው?” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው “የክብር መቀውጫ አስቀምጠው ዘንድ በመንግሥቴ ማልኩልኽ በፍርድ ቀን ማለትም በዕለተ ምጽዋት ያለ ሐፍረት በግልጥ ከአንተ ጋራ ይለፍ” አለው። መታሰቢያህን ያደረገ የገድልኽንም መጽሐፍ የጻፈ ወይም ያጻፈ ንዑድ ምስጉን ክብር ነው፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጠዋለኹ፤ የክብር ዙፋንም አወርሰዋለኹ” አለው። ይህንንም ቃል ኪዳን ጌታችን ከሰጠው በኋላ በስሜን ከሚገኝ አንድ ገዳም በኅቡእ (በስውር) እስከ ዕለተ ምጽአት ይኖል ዕረፍቱ ይህ ነው። ከቅዱስ ያሬድ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱም ይማረን!።

ምንጭ፦ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ቅዱስ ያሬድና የቅዱስ ያሬድ ታሪክ ከሚሉት መጻሕፍት።


“ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ። እንተ አዕረገ ልቡ ሕሊና መንፈስ ረዋጼ። ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ። በብዙኅ ፃማ ዘአልቦ ሑፃፄ። መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕፄ”። ትርጉም፦ የመላእክት ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለኾነ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከኼደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለኾነ ለቅዱስ ያሬድ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የግንቦት 11።

ቅዱስ አትናቴዎስ

ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን)ን ቀብቶ የሾመላት የእስክድርያ ሃያኛው ሊቀ ጳጳስ ታላቁ አባት ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው ?

ቅዱስ አትናቴዎስ የተወለደው በ298ዓ.ም በእስክድርያ ነው። እርሱም ከመምህር ከሚማሩ ሕፃናት ጋራ እያለ እርስ በእርሳቸው በመጫወት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየሠሩ ከእነርሱ ውስጥ ዲያቆናትን ኤጲስቆጶሳትንም ሲያደርጉ እሊያን የክርስቲያንን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው። እርሱም “አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም” ብለው ከለከሉት እርሱ ግን “ክርስቲያን እሆናለሁ” አላቸው እነርሱም ደስ ተሰኙበት። ያን ጊዜ ወስደው በሊቀ ጳጳሳት አምሳል አደረጉት ከበታቹም ወንበር አድርገው ይሰግዱለት ጀመር። በዚያ ጊዜም ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ በዚያ አለፈ የክርስቲያን ልጆች ሲጫወቱ በአያቸውም ጊዜ አብረውት ላሉት “ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው” አላቸው።


አባቱም በሞተ ጊዜ ወደ አባ እለእስክንድሮስ መጣ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው። ከዚህም በኋላ የአባቱን ገንዘብ ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሕግ ሥርዓትንም ከአባ እለእስክንድሮስ ዘንድ እየተማረ ኖረ እርሱም ተወዳጅ ልጅ አደረገው። ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾመው የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ የተመላ ሆነ።


ስለ ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ ቤተ ክርስቲያን አጠራር በተመለከተ ሩፊኖስ የተባለው የዚያ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሚከተለውን ጽፏል።

የእስክንድርያ ክርስቲያኖች የእስክንድርያ 17ኛ ፖትርያርክ የነበረውንና በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ያረፈውን የተፍጻሜ ሰማዕት የቅዱስ ጴጥሮስን በዓል በየዓመቱ በታላቅ ሁኔታ ያከብሩ ነበር። በዚያን ጊዜ ፖትርያርክ የነበረው አባት እለእስክንድሮስ ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ በድንገት ወደ ባሕሩ ሲመለከት በዚያ የነበሩ ልጆች ጳጳስ፣ አጥማቂና ተጠማቂ እየሆኑ በባሕሩ ዳርቻ ሲጫወቱ ተመለከተ። መጀመሪያ የሕፃናት ጨዋታ ነው ብሎ አሰበ። ሁኔታቸውን እየቆየ ሲያየው ግን በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመውን መንገድ የተከተለና ከልጆች ጨዋታነት ያለፈ ነገር ሆኖ ታየው። በዚህ ጊዜ በመደነቅ አብረውት የነበሩት ካህናት ጋር በመካከር ልጆቹን ሁሉንም አስጠርቶ ምን እያደረጉ እንደሆነ ጠየቃቸው እርሱም ቅዱስ አትናቴዎስ ጳጳሳቸው ሆኖ ሌሎች ልጆች ደግሞ ተጠማቂዎች ሆነው ወደ እርሱ ሲቀርቡና እርሱ እያጠመቃቸው እንደነበረ ነገሩት።


አባ እለእስክንድሮስ በጨዋታ መልክ ሲያጠምቅ የነበረው “የጨዋታው ካህን” ምን እያለና እንዴት እንዳጠመቃቸው ሲጠይቃቸው የምሥጢራቱ አፈጻጸም መንገድ በትክክል እንደተፈጸመ በመገንዘቡ አብረውት የነበሩትን ካህናት ስለ ጉዳዩ ካማከራቸው በኋላ “እነዚህን ንጹሕ ልባቸው በመለኰታዊ ጸጋ የተጠሩትንና የተጠመቁትን ልጆች እንደገና ማጥመቅ አስፈላጊ አይደለም” ብለው በመወሰን ጥምቀታቸውን በማጽደቅ አስፈላጊ የሆኑ ቀጣይ ምሥጢራትን ፈጸመላቸው።ከዚያም ሌሎችን ሕፃናት ባርኮ አሰናበታቸው። አጥማቂውን ሕፃን አትናቴዎስን ግን ከእርሱ ጋር ይሆን ዘንድ ወደ መንበረ ፖትርያርኩ ወሰደው።


አባ እለእስክንድሮስም አትናቴዎስን በመንበረ ፖትርያርኩ የቤተ ክርሰቲያንን ትምህርትና ሥርዓት እያስተማረ አሳደገው፤ እርሱም ተወዳጅ ልጅ ሆነው። ከዚህም ጋር ሰዋስው፣ ፍልስፍና፣ ክሂሎተ ነቢብና ሌሎች በዘመኑ የነበሩ ትምህርቶችንም በሚገባ ተማረ። ቆይቶም ለመዓርገ ምንኵስና በቃ። በቅድስናው፣ በሞያውና በግብረ ገብነቱ እንከን የሌለው ወጣት አትናቴዎስ በ23 ዓመቱ ሊቀ ዲያቆን ሆነ። በዚያ ዘመኑ መዓርግ “ሊቀ ዲያቆን” ማለት የሊቀ ጳጳሱ አፈ ጉባኤ፣ እንደራሴ እንደ ማለት ነበር። ብዙውን ጊዜ የሊቀ ጳጳሳት ሲያርፉ በመንበራቸው የሚተካው ሊቀ ዲያቆናቸው ነበር።


የከበረ አባት እለእስክንድሮስ በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት አትናቴዎስ በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ከዚህ አስቀድሞ ግን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ በተደረገ ጊዜ አባ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም ሳይለይ ይህም አትናቴዎስ ከእነርሱ ጋራ ተሰብስቧል። የጉባኤውም ጸሐፊ አድርገውት በኒቅያ ከተማ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከእነርሱው ጋራ ሠራ።


ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ አርዮሳዊ ልጁ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ አርዮሳውያንም በዙ ።ይህንንም አባት አርዮሳዊው ንጉሥ ከመንበረ ሢመቱ አሳደደውና በእርሱም ፈንታ ጊዮርጊስ የተባለ ከሀዲ ሰው ሾመ። ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ሲያሳድዱትና ሲመልሱት ኖረ። በስደትም በአንዲት ምዕራባዊት አገር በነበረ ጊዜ በዚያ የጣዖት ቤት ነበረች። በዚያቺም የጣዖት ቤት ብዙ ሕዝቦች በውስጧ የሚሠሩ ብዙ የሰይጣን ሥራዎች አሏት። እርሱም የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ለመነው ያቺም የጣዖት ቤት አፍርሶ የአገር ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ወደማወቅ መለሳቸው።


ይህንንም አባት አምስት ጊዜ አሳደዱት የሹመቱም ዘመን አርባ ሰባት ሲሆን ዐሥራ አምስቱን ዓመት በስደትና በእሥራት ነው ያሳለፈው። ይህም አባት ብዙ መከራና ድካም መሰደደም ስደረሰበት ሐዋርያዊ ተብሎ ተጠራ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አትናቴዎስ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የግንቦት7 ስንክሳርና ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሕይወቱና ትምህርቱ።

“ሰላም ለአትናቴዎስ ከመ ላዕሌሁ ተነበዩ። ደቂቀ ክርስቲያን ኵሎሙ እንዘ ይትዋነዩ። ሊቀ ጳጳሳት ዘኮነ ወምእመነ ክርስቶስ ዲበ ንዋዩ። ወበእንተ ዘበጽሖ ስደት እመንበረ ክብሩ ወዕበዩ። ተሰምየ ሐዋርያዌ በኵሉ አያዩ”። ትርጉም፦ የክርስቲያን ልጆች ኹሉ ሲጫዋወቱ በርሱ ላይ ትንቢትን እንደተናሩ የጳጳሳት አለቃ ኾኖ ለተሾመና በክርስቶስ ገንዘብ (ምእመን) ላይ ታማኝ ኾኖ ለተገኘ ለቅዱስ አትናቴዎስ ሰላምታ ይገባል፤ ከፍፁም ክብሩ ዙፋን ላይ ስደት ስለደረሰበትም በግብሩ ኹሉ ሐዋርያ ተብሎ ተሰየመ።(አርኬ) የግንቦት 7።

ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ

ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ


ኤርምያስ የስሙ ትርጉም ከእግዚአብሔር የተላከ ብርሃን ማለት ሲኾን፤ ትውልዱ ከነገደ ሌዊ በመኾኑ ክህነትን ከነቢይነት አስተባብሮ የተገኘ ነው። ይህም እውነተኛ ነቢይ የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ማስተማር ጀመረ። ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዐሥራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመን መንግሥቱ እስከሚፈጸም በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት ጊዜ ያስተምር ነበር።


ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ እንደ ቅዱስ ኢሳይያስ በበትር የምትመሰል የቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ በለውዝ በትር አምሳል ተመልክቷታል (ኤር1፥11)። ይኽ ብቻ ሳይኾን ከኹለት (ሁለት) ደቀ መዛሙርቱ ከባሮክና ከአቤሜሌክ የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነች ዐጽቀ በለስ በንስር አንገት የተላከለት ታላቅ ነቢይ ነው።


ስለ ራሱ እንዲህ ሲል ራሱ ተናገረ “የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ በእናትህ ማሕፀን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ ከእናትህም ማሕፀን ሳትወጣ መረጥኩህ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ” አለኝ። ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አስረዳቸው “ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ ያለዚያ የከላውዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያሥነሣዋል ይማርካችኋልም” እንደቃሉም ሆነ። ሁለተኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ። ደግሞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና ሠላሳ ብር እንደሚወስድ ተናገረ። ስለ ብዙ ሥራዎችም ተናገረ አይሁድ ግን ሊገድሉት ወደው ገርፈው አሥረው በጒድጓድ ውስጥ ጣሉት እግዚአብሔርም አዳነው። እርሱ ግን ስለእነርሱ ይለምንና ይማልድ ነበር እግዚአብሔርም “ስለ እርሳቸው ወደእኔ አትማልድ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና” አለው።


ናቡከደነጾርም ኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልማረከውም። ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት የግብጽን ሰዎች ሲያጠፋቸው የነበሩ በግብጽ ወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በእርሱ ጸሎት እግዚአብሔር አጠፋቸው።


ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲያስተምር ኖረ። የትንቢት ወራትም በተፈጸመ ጊዜ አይሁድ በደንጊያዎች ወገሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ግንቦት 5 ቀን ሰጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የግንቦት5 ስንክሳር እና መጽሐፈ ተአምኆ ቅዱሳን (የቅዱሳን ሰላምታ) ንባቡና ትርጓሜው መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ከሚለው መጽሐፍ።


“ሰላም ለኤርምያስ እምነቢያት ዐቢያን። ወልደ ኬልቅዩ ካህን። አረፍተ ብርት ተሰምየ ወዓምደ ኀፂን። እስመ በእንተ ክርሰቶስ መድኅን። እስከ ወገርዎ እስራኤል በዕብን”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የግንቦት5።


የዕለቱ ምስባክ፦ “ላዕሌከ ተገደፍኩ እማኅፀን። እምከርሠ እምየ አንተ አምላኪየ። ኢትርኀቅ እምኔየ እስመ አልጸቁ እትመንደብ”። መዝ 21፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 2፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 7፥51-55። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 21፥33-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

አቡነ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ


አቡነ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ፦ እኚህ ጻድቅ ከከበሩና ነገሥታት ከሆኑት ወገን በአገረ ጐጃም ኢናይ በምትባል ቦታ የካቲት አሥራ ስድስት ቀን ተወለዱ፡፡ ልደታቸውም እንዲህ ነበር፡፡ ንጉሥ አምደ ጽዮን ምስረነዓዳን ወለዱ፣ ምስረነዓዳም በዝራምበሳን ወለደች፣ በዝራምበሳም ፍሬጽዮንን ወለደ፣ ፍሬጽዮንም መልከ ጼዴቅን ወለደ የእናታቸውም ስም ቅድስት ዓመተ ማርያም ነው፡፡ በተወለዱም ጊዜም በአባትና በእናታቸው ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ እግዚአብሔር ለብዙዎች አባት አድርጎ መርጦአቸዋልና፡፡


ለትምህርት በደረሱም ጊዜ መዝሙረ ዳዊት ይማሩ ዘንድ አባትና እናታቸው ለመምህር ሰጧቸው ፡፡ እርሳቸውም እምቢ ብለው ወደ አባትና እናታቸው ቤት ተመለሱ ፡፡ ፈረስ ጋላቢም ሆኑ፡፡ ደግሞ እኚህ ጻድቅ በጐለመሱ ጊዜ አባትና እናታቸው መልኳ የምታምር ሚስት አጩላቸው፡፡ የአባታቸውንም ሹመት የንጉሥ ሠራዊት አለቃ ሆነው ተሾሙ፡፡ በልባቸውም ሰሎሞን እንደተናገረው “ከፀሐይ በታች ያለው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ” አሰቡ ።”በምድር ላይ ቋሚ የፀና ሕይወት የለምና” ይህንም ብለው ከአባትና ከእናታቸው ቤት ተሰደዱ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ እየመራቸው ቅጽሮ ወደሚባል አገር ደረሱ የበሩም ጠባቂዎች አባታችን መልከ ጼዴቅን ከተሸከሟቸው ሁለት የወርቅ ልብሶች ጋር አቆሙአቸው “አትሻገር ተመለስ” አሏቸው፡፡ ያ የበር ጠባቂ የሆነ ሰውም “ለሌላው እስከምመለስ ጠብቀው” አላቸው ይህን ብሎም ይረዷቸው ዘንድ ጓደኞቹን ሊጠራ ሄደ የሚመራው መልአክም መልከ ጼዴቅ “ከወርቅህ ጋር ከዚህ ሂድ” አላቸው ልብሶቻቸውንም ተሸክመው ሄዱ፡፡ ይመራቸው የነበረ የእግዚአብሔር መልአክም እነዚህን የበርሃ ጠባቂዎች እንደ ድንጋይ የፈዘዙ እንደበድን የደነዘዙ አደረጋቸው፡፡ መናገርም ተሳናቸው፡፡
ከዚህ በኋላም የኢዮስያስ ቦታ ወደ ሆነችው ደጋ ዳሞት ደብረ ምዕራፍ ደረሱ፡፡ ከአባታችን ኢዮስያስ ቀጥሎ (በኋላ) በተሾሙት በአባታችን በአቡነ አሮን እጅ በዚያ መነኰሱ እርሳቸው አስቀድመው በስውር መንኵሰው ነበርና፡፡ አባታችን አቡነ አሮን ንዑድ ክቡር ለሚሆን መልከ ጼዴቅ የምንኩስናን ልብስ አለበሳቸው፡፡

ከዚህም በኋላ አባትና ወንድሞቹ ዘመዶቹም ኤናይ ከምትባል አገሩ እየፈለጉ መጡ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ተሰወራቸው አላገኙትም አባታችን አሮንንም ይዘው “ልጃችን አባት እናቱን እጮኛውንና ሹመቱን ትቶ ወደ አንተ መጥቷልና ስጠን” አሉት፡፡ አባታችን አሮንም ቅዱስ መልከ ጼዴቅ እንደመነኰሰ ነገራቸው፡፡ ያን ጊዜም አባትና እናቱ ወንድሞቹና ዘመዶቹ ታላቅ ለቅሶን አለቀሱ አዘኑ “ወዮልን ወዮልን ክብራችን ፈርሶአልና ኃይላችንም ተሽሮአልና ወልደን እንደ አልወለድንም ሆነናልና” አሉ፡፡ ከአባታችን ከአቡነ አሮን ጋር አስታረቋቸው አባቱም ያን ጊዜ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን” አለ አስቀድሞ ቅዱሳንን ሲጎበኝና ለነዳያን ሲራራላቸው ባየሁ ጊዜ ይህ ልጅ መነኩሴ እንደሚሆን በልቤ አስብ ነበር፡፡ ትተውትም ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላም የእግዚአብሔር መልአክ ክቡር መልከ ጼድቅን በዚያ ወስዶ ደብረ መድኃኒት አደረሳቸው፡፡ በዚያም ከቀሲስ አስጢፋኖስ የዳዊትን መዝሙርና የመጻሕፍትን ቃል እየተማሩ ተቀመጡ፡፡ ፈጥነውም ጨረሱ መንፈስ ቅዱስ በእርሳቸው ላይ ይናገራልና፡፡


ከዚህ በኋላ ከትንሽ ዋሻ ገቡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ በማሰብ በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ በየቀኑ እስከ ሦስት ሺህ ድረስ ይሰግዳሉ፡፡ ሰውነታቸውንም እንዲሁ ይገርፋሉ፡፡ የክርስቶስን መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን በብረት ቸንክረው መከራውን ያስባሉ፡፡ ጎኑ በጦር መወጋቱን አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፤ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና እንክርዳድን ይመገባሉ፤ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነባሉ፤ ብፁዕ መልከ ጼዴቅ በቀንና በሌሊት በጾምና በጸሎት ይጋደሉ ዘንድ ጀመሩ፡፡ የዳዊትን መዝሙር በየቀኑ ሦስት ጊዜ ይጸልዩ ነበር። እየተጋደሉም አርባ መዓልትን ቆዩ፤ ሌሊትም ራቁታቸውን ማቅ ብቻ ለብሰው ከባህር ውስጥ ይቆማሉ፡፡ በነጋም ጊዜ ወደ በዓታቸው ይመለሳሉ፡፡ በየዓመቱም አራት ጊዜ እንዲህ ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱም አርባ ቀን እህል ሳይበሉ ወይን ሳይጠጡ ቆዩ። ( ከቅጠልና ከእንጨት ፍሬ ከሣርም ፍሬ የጽዋው ቁመት በትንሽ ጣት ልክ ከተሰፈረ ጥቂት ውኃ በስተቀር) እንደዚህ እየተጋደሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በደብረ መድኃኒት ሰባት ዓመት ኖሩ፡፡

የእግዚአብሔርም መልአክ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን ደናግል መነኰሳትን መስለው ሁሉን እያከናወኑ እያለ ፡ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ “መገረፍህ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፤ የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፤ መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፤ ሞትህም ስለ እኔ ሞት ይሁንልህ” ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ “ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ ነፍሱ በአንተ ቃል ኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንሰሐ ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፣ መጥቶም የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም” የሚል እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን መድኃኔዓለም ሰጣቸው። እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ ሰው አይበሰብስም፡፡


የእግዚአብሔር መልአክ አባታችን መልከ ጼጼቅን “በግራሪያ አገር ወደምትገኝ የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ደብር ወደሆነች ወደ ደብረ ሊባኖስ ሂድ” አለው፡፡ አባታችን መልከ ጼዴቅም በዚህ መልአክ ትዕዛዝ ሄዱ ደብረ ሊባኖስ ደረሱና በዚያ እያሉ ቅዱሳንን እጅ ነሷቸው ከንቡረ ዕድ እንድርያስ ጋርም ተቀመጡ፡፡ ትንሽ ዋሻ በዓትን ሰጡዋቸውና “ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ እግዚአብሔር ያጽናህ የገድልህንም ፍጻሜ ይሰጥህ” አላቸው፡፡ አባታችን እንድርያስ በእሱ ላይ በባረከ ጊዜም አባታችን መልከ ጼዴቅ ወደ በዓቱ ገብቶ ምስጋና ጸሎትና ስግደት ተግቶ ያዘ፡፡ እንደ መጀመሪያውም ታስሮ እያለ በየለቱ እስከ ሦስት ሺህ ስግደት ይሰግድ ነበር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እስከሚፈስ ድረስ መንታ በሆነ የገመድ ጅራፍ ሰውነቱን ይገርፍ ነበር፡፡ እንባውም እንደክረምት ነጠብጣብ ይፈስ ነበር፤ የዓይኑ ብሌን እስኪገለበጥ ድረስ ያነባ ነበር፡፡ የሥጋውንም ቁስል እንደ መርፌ ሰርስሮ ወደ ውስጥ አካሉ እስኪገባ ድረስ በማቅ ፀጉር ይሰቀስቅና ይደመድም ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ መከራ ሲቀበልም ከእግዚአብሔር ምሥጋና ዝም አይልም ሥራውንም ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፡፡ “ጌታ ሆይ የተኛሁትን አንቃኝ የደከምሁትን አበርታኝ የጨለምሁትን እኔን አብራልኝ” ይል ነበር፡፡ ይህንንም የሚለው ለራሱ ብቻ አይደለም ስለዓለም ሁሉ ነበር እንጅ እሱስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋርና በአርያም ካሉ ከሱራፌል ጋር በክህነት የሚያገለግል ፍጹም ንጹሕና ጻድቅ ሰው ነው፡፡


ከዚህ በኋላም አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሦስት የብርሃን አክሊሎችና የወርቅ ዘውድ ተቀዳጅቶ ተገለጠለት፡፡ የብርሃን ልብሶችን ለብሶ የመስቀል ምልክት ያለው በትርም ተመርኩዞ ፊቱም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ መጣና ወደ አባታችን መልከ ጼዴቅ ቀርቦም “ልጄ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፡፡ አባታችን መልከ ጼዴቅም መልሶ “የእግዚአብሔር ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን አንተ ማነህ አለው፡፡ “እኔ ከእናቴ ማኀፀን ጀምሮ መድኃኔዓለም የመረጠኝ ተክለሃይማኖት ብሎም የሰየመኝ ፍሰሐ ጽዮን ነኝ” አለው፡፡ “ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወደቅሁ ከኔ ጋር የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ አነሣኝ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዳሞት ንጉሥ ሞተለሚ እንዴት እንዳደረገው የጣዖት ማምለኪያዎችን እንዴት እንዳጠፋ ብዙ ሰዎችን በክርስቶስ እንዴት እንደአሳመነ ያን ጊዜ ነገረኝ፡”፡
ስለዚህም “እግዚአብሔር አከበረኝ ከፍ ከፍ አደረገኝ፤ የብዙዎችም አባት አደረገኝ፤ ልጄ ሆይ አንተም ጸንተህ ተጋደል የብዙዎች አባት ትሆናለህ፤ እግዚአብሔር ለመጋደል ያበርታህ ሰላምንም ይስጥህ”፡፡ ይህንም ብሎ ከእርሱ ተሠወረ፡፡ ከርሱ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባታችን መልከ ጼዴቅ መጣና ወዳጄ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፡፡ መልከ ጼዴቅም “አንተ ማነህ” አለው፡፡ “እኔ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ” አለው፡፡ ያን ጊዜም ከእግሩ በታች ወደቀ፡፡ ጌታችንም እጁን ይዞ፡፡ አነሣውና “ጽና አትፍራ” አለው፡፡ ያን ጊዜም እናቱ ድንግል ማርያም፣ ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል፣ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር ከነቢያት፣ ከሐዋርያት ጋር፣ ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር መጣች መድኃኔዓለምም አባታችን መልከ ጼዴቅን “ከእናትህ ማኀፀን ጀምሮ በምስክር ሁሉ ፊት መረጥሁህ ካህንም አደረግሁህ ዛሬም የብዙዎቹ አባት አደርግሃለሁ፡፡ ኃጢአተኞችንም የምትመልስ ትሆናለህ፡፡ ያልጠቆረ ብሩህ አክሊልና በሰው እጅ ያልተሠሩ የብርሃን ልብሶችን እሰጥሃለሁ፡፡ ርስትህ ከአጥማቂዬ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ይሁን፤ ሹመትህም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይና ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን፣ ስምህም የኔ ምሳሌ በሆነው መልከ ጼዴቅ ይሁን” አለው፡፡


የመጀመሪያው በጥምቀት የተሰጠው ስሙ ኀሩየ ወልድ (በወልድ የተመረ) የሚል ነበርና ያን ጊዜም ቁመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ ብርሃናቸው እንደ ፀሐይ የሚያበራ፤ ሦስት የወርቅ መስቀሎችን ሰጠው” በላያቸው ላይ ውጣ” አለኝ፤ እኔም በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት ጊዜ ወጣሁ እስከ አርያምም አገቡኝ፡፡ በዚያም የእግዚአብሔርን መንበር አየሁ፡፡

በአንድነት በሦስትነት የሚኖር የዘመናት ጌታም በላይ ተቀምጧል፡፡ ይህም ነገር እጅግ ድንቅ ነው ወልድ በምድር ላይ ከእርሱ ጋራ እየተነጋገረ ሳለ በአርያም ደግሞ በሦስትነቱ ተቀምጦ አየሁ፡፡ ጌታም ሥርዓትህ እንዲሁ እንዳየኸው ይሁን፤ እስከ ዕለት ዕረፍትህም ድረስ ስለ ገድልህ ጽናት የሚሆን ሰጥቼሃለሁ” አለው፡፡ በጸሎቱ የተማጸነውን እንደሚምርለትና ሌላም ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ “እኔም ከአንተ አልለይም፣ መላአክቶቼም ይጠብቁሃል” አለው፡፡ መልከ ጼዴቅም ይህንን በሰማ ጊዜ በፊቱ ሰገደ፡፡ “አቤቱ ለእኔ ለኃጢአተኛው አገልጋይህ ይህን ሁሉ ክብር የሰጠኸኝ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይባረክ” አለው፡፡ ጌታችንም ባርኮት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡


አባታች መልከ ጼዴቅ እንደዚህ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ ዕረፍታቸው ሲደርስ ትንሽ በተቅማጥ በሽታ ታመሙ ያንጊዜም የጌታችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክቶች ጋር መጣች፡፡ መላእክትንና ቀደምት አባቶችን፣ ነቢያትንና ሐዋርያትን፣ ጻደቃን ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣ ደናግልና መነኮሳትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም ምስክሮች አድርጎ አቆመ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000 ሕፃናት ከአለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጡ፡፡

“በእኔና በአንተ መካከል እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ይሁኑ፤ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በእጅህ የተጠመቀ፣ በቃልህ የተናዘዘና በእጅህ የተሳለመ ምሬልሃለሁ፤ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውና ያጻፈውን ምሬልሃለሁ ከአንተም ጋር ርስት እሰጠዋለሁ፤ የቤትህ ልጆች መንግሥተ ሰማያትን ከአንተ ጋር ይውረሱ” አለው፡፡ ዳግመኛም “ለምህረት ያልጠራኋትን ነፍስ ለመሳለምም ሆነ ለመባረክ ወይም ለመናዘዝ ወደ አንተ አላቀርብም፤ ከኃጥአንም ወገን አንተ ስለ እነርሱ ከለመንኸኝ እምርልሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው። አባታችንም ግንቦት 4 ቀን ነፍሳቸው ከስጋቸው ተለየች።

ምንጭ፦ ገድለ መልከ ጼጼቅና መዝገበ ቅዱሳን።

ግንቦት ፩ (ልደታ ለማርያም)


እንኳን አምላክን ለወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ለጸናች ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ለልደቷ መታሰቢያ ዓመታዊ የንግሥ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።


የዕለቱ አንገርጋሪ፦ “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም እም ሐና ወኢያቄም ከመ ትቤዙ ነቢያት ወጻድቃነ አማን ተወልደት እመ ብርሃን”። ትርጉም፦ በእመቤታችን ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ ይኸውም ከሐና ከኢያቄም መወለዷ ነው ነቢያትና ጻድቃንን በልጇ ታድናቸው ዘንድ በእውነት የብርሃን እናት ተወለደች። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።


አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት፦ እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ቅዱስ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ቅድስት ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና። እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኀዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።


ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው። በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለቅድስት ሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት፡፡ ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርም አመሰገኑት።ኢያቄም ለሚስቱ ሐና እንዲህ አላት “ሰማያት ሲከፈቱ አየሁ፤ ነጭ ወፍ መጣ በራሴ ላይም አረፈ” እንደዚህም ሁሉ ሐናም “ርግብ በራሴ ላይ ስትቀመጥብኝ በማሕፀኔም ስታድር አየሁ ገባች” አለችው።


ከዕለታት በአንድ ቀን ሐና እና ኢያቄም ወጥተው ወደ ተክል ቦታ ገቡ፡፡ ቁመውም ሲጸልዩ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ልጅ ስለሌላቸው ፈጽመው አዘኑ፡፡ከሐዘናቸውም ብዛት የተነሳ አንቀላፍቷቸው ተኙ፡፡ ሐናም ተኝታ ሳለች በባሏ በኢያቄም እጅ በትር እንደተያዘች ያችም በትር አብባ አፍርታ አየች፡፡ሁለተኛም ኢያቄም በሐና እጅ ከፍሬ ሁሉ የሚመስለው የሌለ የሚጣፍጥ መልካም ፍሬ ተይዞ አየ፡፡ከእንቅልፋቸው በነቁ ጊዜ ደስ አላቸው በመኝታቸው ስላዩት ነገር እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡


ከዚህም በኋላ ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን ብለው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ከዚህም በኋላ የከበረች ሕፃን ነሐሴ ሰባት ቀን ተፀነሰች፡፡የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ በቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ተሳለች።ከስድስት ወር በኋላም የብፅዕት ሐና መፅነስ ታወቀ። ዘመዶቿም ሰሙ ወደ እርሷ መጥተውም “የምንሰማው ይህ ነገር አውነት ነውን? ዘመንሽ ካለፈ በኋላ በአንቺ ላይ የተደረገው ነገር ምንድን ነው?” አሏት። ከሐና ዘመዶች ወገን የአርሳባን ልጅ የምትሆን አንዲት ዐይኗ ማየት የተሳናት አንዲት ሴት ነበረች። “የሰማሁት እውነት ነውን?” ብላ የሐናን ማኅፀን ዳሰሰች። “እህቴ ሆይ ሽማግሌ ስትሆኚ እንዴት ፀነስሽ” አለቻት። ዳግመኛም ማየት የተሳነው ዐይኗን ዳሰሰችው ያን ጊዜም ዐይኗ ተከፈተላት ብርሃንንም አየች። “ብፅዕት ሐና ሆይ ለአንቺ ብፅዓን ይገባሻል ፅንስሽ በማኅፀንሽ እያለ ገና ሳይወለድ በሽተኞችን የፈወሰ በግልጽ ከታየ ከማሕፀንሽ ከወጣማ ምን ያህል ይፈውስ ይሆን?”አሉ፡፡እንደዚሁም ሁሉ ብዙ በሽተኞች መጥተው እየዳሰሱ ከበሽታቸው ይፈወሱ ይድኑም ነበር። ይህ ነገርም በእስራኤል ሽማግሎዎች ሁሉ ዘንድ ዕፁብ ድንቅ ሆነ።


ቅድስት ሐናም የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ በግንቦት አንድ ቀን ከፀሓይ ይልቅ ፈጽማ የምታበራ ሴት ልጅ በሊባኖስ ተራራ ላይ ወለደች፤ የመልኳም ደም ግባት ከመዓር ከሦከር ይልቅ ደስ ያሰኛል፤ የመዓዛዋም ሽታ ከሽቱ ሁሉ ይበልጣል። ዘመዶቿና ጐረቤቶቿም በሰሙ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አላቸውና ተሰብስበው ወደስዋ መጡ ወደሷም መጥተው ልጅዋን ባዩ ጊዜ ፈጽመው አደነቁ እርስ በርሳቸውም “እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም” ተባባሉ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ ላይ አድሯልና የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና። ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ ያችንም ብላቴና ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው። በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናትና ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።


የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን። በዘአዝፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት”። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት ወንጌል ማቴ 1፥1-18።
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን። ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ”። መዝ 86፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 4፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 8፥13፣ የሐዋ ሥራ 7፥44-51 ወይም የሐዋ ሥራ 1፥12-15 የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የልደታ ለማርያም በዓል፡፡ ለሁላችንም ይሁንልን።
ምንጭ፦ ተአምረ ማርያም፣ ድርሳነ ቅድስት ሐና ወኢያቄምና የግንቦት 1 ስንክሳር ።

ሐዋርያው ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ፦

የቅዱስ ማርቆስ ወላጆች ስም የአባቱ ስም ቅዱስ አርሰጡጳውሎስ ሲሆን የእናቱ ስም ቅድስት ማርያም ይባላል፡፡ አባቱ ባለጸጋና ያላገባ ነበር የአባቱ ስም ስምዖን ይባል ነበር፡፡ ስምዖንም አርስጡጳውሎስን እንዲያገባ ይገፋፋው ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በቤቷ እንግዶችን የምትቀበልና የምታስተናግድ ማርያም የተባለችውን የወንጌላዊ የቅዱስ ማርቆስ እናት አገኘ ፡፡ እሱም እሷም ሳያስቡት ባዩት ሕልምና በመፈክረ ሕልም (በሕልም ፈቺዎች) በተነገራቸው መሠረት ተገናኝተው የትዳር ሕይወትን መሠረቱ፡፡


አርስጡጳውሎስ ከከበረውና በባለጸግነቱ ከታወቀው ከአባቱ ካገኘው ሀብት ለነዳያን የሚመጸውት፣ ዐሥራት በኩራት የሚያወጣና ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር የሚጸልይ ደግ አባት ነበር፡፡ እሱም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ዘመድ የአክስት ልጅ እንደሆነና ቅዱስ ጳውሎስም በመልአክቱ የጠቀሰው እሱን እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ “አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል” ቈላስይስ 4፥10 ነገር ግን አንዳንድ የግሪክ፣ የላቲን፣ የግእዝና የኮኘት ትርጉሞች “የበርናባስ የወንድሙ ልጅ” የሚለውን ሐረግ አይጠቅሱም ይህም ምንአልባት አንዳንድ የግሪክ ቃላት ከአንድ በላይ ትርጉም ስላላቸው ይሆናል፡፡


የቅዱስ ማርቆስ እናት ማርያም ተብለው ከተጠሩት ብዙ ቅዱሳት አንስት መካከል አንዷ ናት፡፡ ቤቷ በኢየሩሳሌም እንደነበረና ምዕመናንም በቤቷ በጸሎት ይሰበሰቡ እንደነበር በሐዋ 12-12-17 በሰፊው ተገልጾአል፡፡ ይህም በጥንት ወይም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ካሉት መንፈሳውያኑ ሴቶች (ቅዱሳት አንስት) ከፈተኛ ቦታ ያላት እንደነበር ያመለክታል። በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን በአንድነት በክርስቶስ ስም ይሰባሰቡ ስለነበር ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኙትም በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ “በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ”፡፡ ሐዋ 11-26


የቅዱስ ማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ነበር፡፡ በማርቆስ እናት በማርያም ቤት በጽርሐ ጽዮን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጸላቸውና መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ እንዲህ ተጽፏል “አመ ሣልስት ዕለት ተንሥአ እሙታን ወቦአ ኀበ ሀለው አርዳኢሁ ጉቡአን ወአስተርእዮሙ በጽርሐ ጽዮን … ወበ ፶ ዕለት ፈነወሎሙ መንፈሰ ቅዱስ ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኩሉ በሐውርት … በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የተሰበሰቡ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ገባ በጽርሐ ጽዮንም ታያቸው …በ50ኛው ቀንም
በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው በአገሩ ቋንቋ ሁሉ ተናገሩ”


በኢየሩሳሌም ውስጥ የማርያም ቤት የሐዋርያት መገናኛና መሰባሰቢያ ነበር፡፡ ስለዚህም የማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኀብረት መለያ ሆኖ ይታወቃል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ የተወለደው በአባቱ ወገን ከነገደ ይሁዳ ሲሆን የተወለደበት ቦታ ከአምስቱ የምዕራብ ከተሞች አንዷ በሆነችው በሊቢያ በሲርኔ ይኸውም አብራይሮሎስ በተባለች ትንሽ መንደር ተወለደ፡፡ ትውልዱ ዕብራዊ ቤተሰቦቹም ይኖሩበት የነበረው በሰሜን አፍሪካ በጥንታዊቱ ፔንዲፓሊስ ሲሪኒካ (ቀሪና) በተባለችው በዛሬው ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ደማቅ ከተማ ስለነበር ቅዱስ ማርቆስ አፍሪካዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው የሚሉ አሉ፡፡( ሉሌ መላኩ ቤተክርስቲያንን እወቅ)


የቅዱስ ማርቆስ የስሙ ትርጓሜ ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው ንብ ከሁሉ እንዲቀስም አስቀድሞ ከክርስቶስ በኋላም ከሐዋርያት ተምሮአልና፡፡ አንድም አንበሳ ማለት ነው አንበሳ ለላሕም ጌታው እንደሆነ እንዲሰብረው እርሱም አምልኮተ ላሕምን ከግብጽ አጥፍቷልና፡፡ አንድም ካህን ልዑክ ማለት ነው፡፡ ብሥራተ ማሪ ማርቆስ ይላል የተደራረበ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ካህን ማለት ነው፡፡


የቅዱስ ማርቆስ ሁለተኛ ስሙ ዮሐንስ ይባላል። “ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለ ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ” ሐዋ12፥12


የቅዱስ ማርቆስ ተክለ ቁመናና መልክ
እንዲሁም አለባበሱን እንዲህ በማለት ተጠቅሷል፡፡ “የግብጽና የኢትዮጵያ ኮከብ ብፁዕና ቅዱስ ማርቆስ መልኩ ቀይ ቅንድቦቹም ከበድ ያሉ ዓይኖቹም እንደሰማያዊ ኀብር የጠሩ ቁመቱ ረጅም ከአንገቱም ስር ስርጉድ የሆነ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ራሰ በራህ የሆነ ቀሚስ (ልባልባውም) በወገቡ የሆነ የግብጽና የኢትዮጵያ አባት የቅዱስ ማርቆስ ምልክቱ ይኸ ነበር፡፡


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዊ በሚሰብክበት ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ ወጣት ነበር፡፡ ልቦናው የቀና እንደሆነም አውቆ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የመጀመሪያ አድርጐ መረጠው ከዚህ በኋላ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኖ ጌታ ወንጌልን ሲያስተምር፤ ተአምራት ሲያደርግ ያስተውል ነበር ፡፡ በምሴተ ሐሙስ በአይሁድ ሲያዝና መከራን ሲቀበል ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም መንገድ ላይ ሆኖ በርቀት ድርጊቱን ይከታተል ነበር፡፡ በወንጌሉም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ስለ አርሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ “ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጐበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ”፡፡ ማር14-51-52
ቅዱስ ማርቆስ በቤቱ መጻፊያ ይዞ የጌታን ተአምራት ይጽፍ ነበር፡፡ የግሞ ሊናሮስ የሚባል አገልጋዩን ጌታን እንዲከተልና የሚያደርገውንም ተአምራት እንዲጽፍ ያደርግ ነበር ፡፡

“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዓለ ፋሲካን ሲያከብር ተከተሉት” የተባለውም ቅዱስ ማርቆስን እንደሆነ እንዲህ ተጽፍል፤ “ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እነዲህም አላቸው ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውሃ የተሸከመ ሰውም ያገኛችኋል ተከተሉት የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ፣ ከደቀመዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት፡፡ እርሱም በደርብ ላይ ያለውና የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፣ በዚህም አሰናዱልን፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ ፋሲካም አሰናዱ” ማር 14፥13-15፤ ሉቃ 22፥10-12።


ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም የእናቱ የማርያም ቤት የደቀ መዛሙርቱ መገናኛና መሰባሰቢያ ስለነበር ደቀመዛሙርቱን የበለጠ እንዲያውቃቸውና እንዲቀርባቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ በተለይም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ባለው የጠበቀ ዝምድናና ቀረቤታ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት ልጅ በመሆንና ለአገለግሎቱም ፍጹም መንፈሳዊና እውነተኛ የክርስቶስ ምስክር ለመሆን በቅቷል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በልጅነቱ በኢየሩሳሌም ለመኖር በመታደሉ በዚያም ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት የማግኘት ዕድል ገጥሞት ነበርና የዕብራይስጥ፣ የላቲንና የግሪክ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌልን መስበክ የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ያስተምር ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት አንደተገለጸው ቅዱስ ማርቆስ ከቅድስ ጳውሎስና ከቅድስ በርናባስ ጋር ይሰበክ ነበር፡፡ ከዚያም በፊት ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አስተምሮአል፡፡


ቅዱስ ማርቆስ ንጹሕና ድንግል መሆኑን መልካምነቱንና ትምህርቱን ተመልክቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ለግብጽና ለአካባቢዋ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ ሾመው፡፡ በግብጽ አገሮች በሎኒያ፣ በመርቅያ፣ በጣውንቄ፣ በበርቃ ለመጀመሪያ አስተማረ እርሱ ነው፡፡ ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ አዳኝ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንንም አስተማራቸው፡፡ ሁሉም የዚያች አገር ሰዎች ልቡናቸው የደነደነ ነበሩ በርኵሰት ሁሉ የተሞሉ አማልክትንም ያመልኩ ነበር፡፡ ሰይጣንን በማምለክም ይኖሩ ነበር፡፡ በየቦታው በየመንገዱም ሁሉ ምኩራቦችን የአማልክትን ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ መድኃኒትን፣ ዝሙትንም ያደርጉ ሕጻናትን ይገድሉ በደማቸው መድኃኒትን ያደርጉ ነበር፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሐዋርያት በሄደ ጊዜ አስቀድሞ ብርቃ ደረሰ፡፡ ዘመዶቹ ከእነርሱ ወገን ናቸውና፡፡ እግዚአብሔርን ቃልም አስተማራቸው በመካከላቸው ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ በሽተኞችን ፈወሳቸው ለምጻሞችንም አነጻቸው፤ በእርሱ ላይ በአደረው ጸጋም አጋንንትን አስወጣ፤ ብዙዎችም በትምህርቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ አምላኮቻቸውንም (ጣዖቶቻቸውንም) ሰባበሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጠመቃቸው፡፡


በዚያ ቦታም ወደ እስክንድርያ ይሄድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተገለጠለት፡፡ በዚያም መልካም ተዘራባት ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ወንጌላዊው ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ለጦርነት እንደተዘጋጀ ጎልማሳ ሆነ ወንድሞቹንም ሰላም አላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ቦታ ቅዱስ ወንጌልን አስተምር ዘንድ ወደ እስክንድርያ እንድሄድ አዝዞኛል” አላቸው፡፡ እነርሱም ሸኙት በመርከብም ተሳፍሮ ወደ እስክንድርያ ሄደ በደረሰ ጊዜም ወደ ከተማው በር ገባ የጫማው ማሠሪያም ተቆረጠ “በቅንነትም መንገድ ፈጠነች” አለ በዚያም ከከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበር፡፡ ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዩናኒም ቋንቋ “ኢታስታያስ” አለ ትርጓሜው አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን” አለው “እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም” አለ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በጣቶቹ ላይ መራቅ ጨመረና አፈር ወሰደ ያን ጫማ ሰፊ ቀባው “በሕያው አግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ስም አጅህ ትፈወስ” አለው፡፡ ስለዚህም ተፈወሰች ጫማ ሰፊውም በሥልጣኑ በቃሉ ያደረገውን ድንቅ ተአምር በተመለከተ ጊዜ “የቸሩ አምላክ አገልጋይ ሆይ እለምንሃለሁ ዛሬ ውጣና በቤቴ ዕረፍ በአንድነትም እንመገብ መልካም ነገርን አድርገህልኛልና” አለው፡፡ ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ተደሰተ፡፡

“እግዚአብሔር ሰማያዊት የምትሆን ሕይወት ኀብስትን ይስጥህም” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ አስገባው፡፡ ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ ገባለት። “የእግዚአብሔር በረከት በዚህ ቤት ይኑር” አለ፡፡ ወንድሞች በአንድነት ጸለዩ ከጸሎት በኋላም ተቀመጡና ደስ እያላቸው ተመገቡ፡፡ ጫማ ሰፊውም ቅዱስ ማርቆስን “አባት ሆይ እለምንሃለሁ ይህንን የምትለው እንዴት ነው፤ ይህ ስምስ ምንድን ነው ይህ እንደዚህ የሚቻለው ነው” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ” አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ ላየው እሻለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “እኔ አሳይሃለሁ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ ነው እያለ የወንጌሉን መጀመሪያ አስተማረው፡፡ በትንቢት ስለ እርሱ የተናገሩትንም ከመጻሕፍት ተናገረ፡፡ ጫማ ሰፊውም “እኔ የምትለውን ይህን መጽሐፍ እለምንሃለሁ ከረጅም ዘመን ጀምሮ የግብጻውያን ልጆች እንደማይማሩበት አልሰማህምን” አለው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔርን ነገር ይነግረው ዘንድ አስቀደመ “የዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ናት” አለው ጫማ ሰፊውም የቅዱስን ነገር በሰማ ጊዜ በእግዚአብሔር አመነ ለእርሱም አመለከተው ከእርሱም ኃይላትን ተአምራትን አየ እርሱ ቤተሰቡ፣ ከአገሩ ሰዎችም ብዙዎቹ ተጠመቁ፡፡ የጫማ ሰፊው ስምም አንያኖስ ይባላል፡፡ ያን ጊዜም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምዕመናን በዙ፡፡ የአገሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜም “ይህ የገሊላ ሰው ከዚህ አገር ደርሷል፤ የአማልክትን እጅ መንሻ ለውጧል፤ እንዳይመለኩ ከልክሏል” አሉ ሊገሉትም ፈለጉት ይጥሉት ዘንድም በእርሱ ላይ ፍለጋን አበዙ ብፁዕ ማርቆስ ይህን በተረዳ ጊዜ አስተማራቸውና አንኖስንም ኤጲስ ቆጾስነት ሾመላቸው ሦስት ካህናትንም ሾመላቸው ስማቸውም ወልዮስ፣ መሪደስና በሪሞስ ይባላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ሰባት ዲያቆናትን አንድ ላይ አሥራ አንድ ሰዎችን ሾመላቸው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ወደ ብርቃ ወጣ ለዓመታትም በእርሷ ተቀመጠ፡፡ በሁሉም አገራት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትን ሾሞላቸው ወደ እስክንድርያም ተመለሰ፡፡ በእግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ጸጋና ማመን በዛባት የላም ቦታ በሚባለው በባሕሩ ዳር ካለው ቦታም ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከዚያ ቦታ ከዓለቱ ሥርም ታላቅ ድንጋይ ቁራጭ ነበር፡፡ ጻድቁም ስለ ምዕመናን መልካም ሃይማኖት እግዚአብሔርን አመሰገነ ብዙ ዘመን በቆየ ጊዜም ክርስቲያኖች በዙ አማልክትንም ተዘባበቱባቸው፤ አረማውያንንም ናቋቸው፡፡

አረማውያንም ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ወደ አገራቸው እንደ ደረሰ ተረዱ፡፡ ከሰሙት ተአምራት ብዛት የተነሳ ልቡናቸው በቁጣ ተሞላ እርሱ ሕመምተኞችን ይፈውስ፣ ለምጻሞችንም ያነጻ፣ ደንቆሮዎችንም እንዲሰሙ፣ እውራንንም እንዲያዩ ያደርጋል መልካም ተስፋንም ያስተምራቸው ነበር ይይዙት ዘንድም ፈለጉት፤ በየቤታቸውም ጥርሳቸውን ያፋጩ ነበር፤ በአማልክቱ ምኵራብም “እኛ ለዚህ ጠንቋይ ተሸነፍን” እያሉ ጮኹ፡፡ ምዕመናን የሚያከብሩት ዕለት ሰንበት የተባረከው የፋሲካ በዓልም በሰንበት ቀን ሆነ፤ ይህም ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን ነው፡፡


በዚያች ዕለትም በእነርሱ ዘንድ የሰራቢስ የልደቱ ቀን ነበር፡፡ ያማረች ዕለትን አገኙ ሰላዮችን ላኩና ያዙት፡፡ እርሱን የቅዳሴ ጸሎት ሳይፈጽምም በሰንሰለት አሠሩት በላሞች ቦታ እንጐትተው እያሉም እንደ አውራ ፍየል በየመንገዱ ጐተቱት፡፡ ቅዱስ ማርቆስም በጐተቱት ጊዜ አግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በተቀደሰው ስምህ መከራን እንድቀበለ አዘጋጅተኸኛልና አመሰግንሃለሁ” አለ፡፡ ሥጋውም በየመሬቱ ተቆራረጠ ደሙም በየዐለቱ ፈሰሰ፡፡


ሌሊት ሲሆንም ይገድሉት ዘንድ እስከሚሰበሰቡ ድረስ ወደ እስር ቤት አስገቡት፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲሆንም በሮች ተዘግተው ጠባቂዎችም ተኝተው ሳሉ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክም “የግብጽን አገራት ሁሉ የምታረጋጋ የእግዚአብሔር አገልጋይ ማርቆስ ሆይ ስምህ በሰማይ ባለ የሕይወት መጽሐፍ ተጽፏል ከሐዋርያት ቁጥርም ተቆጥሮአል፤ መታሰቢያህም አይረሳም፤ በምድርም ስፍር ቁጥር የሌላትን ሥልጣን፣ ጸጋ ኃይል እነሆ ሰጥቶሃልና፤ ነፍስህ በሰማይ ይሆናል ሥጋህም በመሬት አይጠፋም” አለው፡፡


ቅዱስ ማርቆስም ይህን ምሳሌ በተመለከተ ጊዜ እጆቹን ወደ ሰማይ አነሣ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከፊትህ አልጣልኸኝም፣ ከቅዱሳን ማኀበርም ደምረኸኛልና አመሰግንሃለሁ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ ነፍሴን በሰማይ ተቀበላት፤ ከፊትህም አትተወኝ” አለ፡፡ ይህን በተናገረ ጊዜ ጌታችን አዳኝ ከሆነው ከሕማሙ በፊት በመቃብርም ከመጨመሩ አስቀድሞ በሐዋርያት መካከል እንደነበረ ሆኖ ታየው፡፡ “የመረጥሁህ ማርቆስ ሆየ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሁን፤ በወንጌል አስተማርሁህ፤ እነሆ መከራን ከመቀበሌ አስቀድሞ ከጓደኞችህ ከሐዋርያት ጋር አንደሆንሁት በአርአያ ተገለጥኩልህ፤ ከእነርሱ ምንም ጉድለት እንዳይኖርብህ” አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከጸጋህ ታላቅነት የተነሣ አመሰግንሃለሁ፤ በሥጋህ አንደነበርህ ሆነህ አንዳይህ የተገባኝ አድርገኸኛልና” አለው “ስለተቀደሰው ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ ትዕግሥትን አድለኸኛልና” ጌታችንም ሰላምን ሰጠውና በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማይ አረገ ፡፡ ሲነጋም የአገሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከእስር ቤትም አወጡት በሰንሰለትም አሰሩት፤ ዳግመኛም በላሞች ቦታ እንደፍየል እንጐትተው እያሉ በከተማው ጐተቱት፡፡


ብፁዕ ማርቆስም ምስጋናን አቀረበ በሰማይ ተገለጠ፡፡ በየአገሩ ከጎተቱት በኋላም ደሙ በየመንገዱና በየአደባባይዋ ሞላ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን በእጅህ ሰጠሁ” አለ፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላም ሚያዝያ 30 ቀን ዐረፈ፡፡ ሁሉም አረማውያን ቅዱስ ማርቆስ አንዳረፈ በተመለከቱ ጊዜም ሥጋውን በእሳት ያቃጥሉት ዘንድ አውበካልዮን በምትባል ቦታ ጽኑ እሳትን አነደዱ፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድም ጨለማና ቀዝቃዛ ነፋስ ሆነ፤ ፀሐይም ብርሃኑን ሰወረ፡፡ በዚች ዕለትም እስከ ምሽት ድረስ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ዝናምና ብርድም ሆነ፤ ከአገሩ ሰዎች ከሽማግሌዎች ብዙዎች ወደቁ ከእነርሱም ብዙዎቹ ሞቱ ያን ጊዜ ፈሩ ሂደወም ከአገሩ ሰዎች የቅዱሱን ሥጋ አኖሩት፤ የተዘባበቱበትም አሉ “ ታላቁ አምላክ ሆይ የዚህን ሰው ነፍስ ተቀበላት በዚች ዕለት የልደቱ ዕለት ናትና” አሉ፡፡ ምዕመናን ወንዶች ደረሱና የቅዱሱን ሥጋ ከእሳቱ ወሰዱት ጸሎት ወደሚጸለይበት ቦተም አደረሱት በእርሱ ላይም ተሳሉ፣ ምስጋናንም አቀረቡ እንደ ሥርዓታቸውም እንደ አገሩ ሰዎች ገነዙት በቆፈሩለት መቃብርም ቀበሩት፡፡ መታሰቢያውንም በደስታ፣ በምሥጋና አብዝተው አደረጉ፣ አበዙ በአገሩ መሠረታዊ ቦታም አስቀመጡት፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ በግብጽ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰ የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ ዕረፍቱ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በ30 ሠላሳኛው ቀን በታላቋ አገር በእስክንድርያ ሆነ ፡፡ ከሐዋርያውና ከወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡ በጸሎቱ ይማረን!፡


፡ ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያት ፤ ስንክሳር ፤ ክብረ ቅዱስ ማርቆስ ከሚለው መጽሐፍ።


“ሰላም ለማርቆስ ለማርያም ዕጓላ። ዘሰሐብዎ በአህባል ውስተ ዐፀደ ላሕም ከመ ዳቤላ። አመ አውዕዮቶ ፈቃዱ ለእሳት በነበልባላ። ዝናም ወአስሐትያ አጥፍኡ ማዕበላ። መብረቅኒ ለሥጋሁ ከለላ”። ትርጉም፦ በላም በረት ውስጥ እንደ ወይፈን በገመድ የሳቡት ለኾነ ለማርያም ልጅ ለቅዱስ ማርቆስ ሰላምታ ይገባል፤ ርሱን በእሳቲቱ ላንቃ (ወላፈን) ለማቃጠል በወደዱ ጊዜ ውርጭ እና ዝናብ ማዕበሏን አጠፋ፤ መብረቅም ሥጋውን ጋረዳት። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 30።

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር ማነው?


የእዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ኅርማኖስ ነው እርሱም ለዲዮቅልጥያኖስ የአማካሪዎቹና የሠራዊቱ አለቃ ነው ስለ አምልኮ ጣዖት ሥራ ምክሩና ንግግሩ ሁሉ ከእርሱ ጋራ ነበር የእናቱም ስም ማርታ ይባላል በክርስትናዋ የጸናች ብፅዕት ናት።


ቅዱስ ፊቅጦርም በአደገ ጊዜ አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበው ንጉሡም በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕርግ አድርጎ ሾመው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ። እርሱም የዚህን ዓለም ክብር ናቀ ሥጋ አይባላም ወይን አይጠጣም ዘወትርም ይጾማል ጸሎትንም ባለማቋረጥ በቀንና በሌሊት ይጸልያል። በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጐበኛቸዋል ለድኆችና ለምስኪኖችም ይመጸውታል።


የቅዱስ ቆዝሞስና ድምያኖስ እናት ቅድስት ቴዎዳዳን በገደሉዋት ጊዜ ንጉሡም ስለ መፍራት ሊቀብራት ማንም አልደፈረም። ይህ ቅዱስ ፊቅጦርም መጥቶ ሥጋዋን ወሰደ ከንጉሥ ስለሚመጣው ቅጣት ሳይፈራ ቀበራት። ጣዖት ስለ ማምለኩ አባቱን ዘወትር የሚገሥጸውና ብዙ ጊዜም የሚመክረው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም። ተከሶም ወደ ንጉሥ በአቀረቡት ጊዜ “አማልክት ያልሆኑ ርኲሳን ጣዖታትን ለሚያመልክ ሰነፍ ዝንጉ ልብ የለሽ ለሆነ ንጉሥ አላገለግልም። ከዛሬ ጀምሮ ለሕያው ንጉሥ ክርስቶስ እገዛለሁ የሰጠኸኝንም ገንዘብህን ንሣ” ብሎ በፊቱ ትጥቁን ፈትቶ ጣለለት።


አባቱ ኅርማኖስም ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና በኄርሜኔዎስ መኰንን ዘንድ በዚያ ፊቅጦር እንዲቀጣ ንጉሡን መከረው። በዚያን ጊዜም ከአደባባይ አወጡት እናቱም በብዙ ልቅሶ ልትሸኘው መጣች። እርሱም ሲመግባቸው ስለ ነበረ የታሠሩ ምዕመናን ስለ ድኆችና ምስኪኖች ስለ ሙት ልጆችና ስለ ባልቴቶች የሚሹትን በመስጠት እንድትጐበኛቸው አዘዛት ከዚያም አፉን ለጉመው ወሰዱት።


በእስክንድርያ አገር ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ሰማያት አውጥቶ ስለ ክብራቸው ለመናገር የሚያስጨንቁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳይቶ ወደ መኖሪያው መለሰው። መኰንኑም በእሳት በአፈሉት በዝፍት፣ በዲን ደግሞ አሠቃየው ከዚያም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ደግመው ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና ከሥቃዩ ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ከቊስሉ ይፈውሰው ነበር።


ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱን ቆረጡ። በእሳት ያጋሉዋቸውን ችንካሮች በጐኖቹ ውስጥ ጨመሩ እግዚአብሔር ግን አጽንቶ አስታግሦ ያለ ጉዳት በደኅና ያነሣዋል። ከዚህም በኋላ በዚያ በረኃብ እንዲሞት ከዱር ባለ ግምብ ውስጥ አሠሩት። እርሱ ግን መጥረብ የሚያውቅ ስለሆነ ላይዳዎችን በመጥረብና በመሸጥ በየጥቂቱ እየተመገበ የቀረውን ለድኆች እየሰጠ ኖረ። አንድ መኰንንም መጥቶ በዚያ ግምብ አቅራቢያ አደረ ስለ ቅዱስ ፊቅጦርም እርሱ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነ የኅርማኖስ ልጅ እንደሆነ ነገሩት። መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ጅማቶቹን መዘዙ አፋን መቱት ቊልቊል ሰቀሉት በእጆቹ ላይ ከባድ ደንጊያ አንጠልጠሉ። ከዚያም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ፣ አደሮ፣ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዩ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾለት አጸናው አረጋጋው። ሥሮቹንም ሕዋሳቶቹን በቦታቸው መለሰለትና አዳነው።


አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ነበረች ቅዱስ ፊቅጦርን ሲያሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር። መላእክትም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ዐረፉ። ያቺም ብላቴና በጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም ያመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ሚያዝያ 27 ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊል ተቀበለ። ምዕመናን ሰዎችም ሥጋውን ወስደው በከበሩ ልብሶች በድርብ በፍታ ገነዙት። እናቱ ማርታም ከአንጾኪያ እስክትመጣ በንጹሕ ቦታ አኖሩት በመጣችም ጊዜ ከዚያ ወሰደችው። ውብ ቤተ ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረች ከእርሱም ታላላቅ
ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ፊቅጦር በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ27 ስንክሳር።


“ሰላም ለፊቅጦር ተአምራቲሁ ዘአርአየ። ድኅረ በሰይፍ ተወቅየ። ልብሱ ዘወርቅ አመ ተኀድገ በዝየ። ያሠርጉ ጣዖታቲሁ ሶበ ልበ ንጉሥ ሐለየ። ኀበ ህላዌሁ ተመሥጠ ሰማየ”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 27።

በጡቶቿ ደም ልጆቿን ያጠመቀችው ቅድስት ሣራ


ቅድስት ሣራና ሁለት ልጆቿ፦ ይቺም ቅድስት ከአንጾኪያ አገር ናት እርስዋም ከዲዮቅልጥያኖስ መኳንንት ለአንዱ ስሙ ስቅራጥስ ለሚባል ሚስቱ ናት እርሱም በፊት ክርስቲያን ነበረ በኋላ ንጉሡን በመፍራት ካደ እርስዋ ግን በክርስትናዋ ጸንታ ኖረች። ባልዋ ስቅራጥስም “እኔ የክርስቲያንን ሃይማኖት እወዳለሁ የንጉሡን ሥቃይ ከመፍራት በቀር ክርስቶስን በልቤ አልካድኩትም” ይላት ነበር። እንደዚህም ስትኖር ሁለት ልጆችንም ወለደች በአንጾኪያም አገር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልተቻላትም። አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋልና ጠፍተዋልምና ሰውን ወዳድ ክርስቶስን ብዙ ስለመውደዷ ልጆቿን ታስጠምቃቸው ዘንድ ታላቅ ተጋድ አደረች ወደ እስክንድርያ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልትሔድ ወዳ አሽከሮቿን አስከትላ ሁለቱን ልጆቿን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።


የክብር ባለቤት ጌታችንም የሃይማኖቷን ልዕልና ለመጪው ትውልድ ሊገልጥ ወዶ ያቺ መርከብ ለመሥጠም እስከምትደርስ በባሕር መካከል ጥልቅ ነፋስን አስነሣ። ይቺ ቅድስትም ልጆቿ ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ ፈራች ተነሥታም ጸለየች ከዚያም ምላጭ አንሥታ ጡቷን የቀኙን በጣች ከደሟም ወስዳ ፊታቸውን በመስቀል ምልክት ቀባች በደረታቸውና በጀርባቸውም ላይ እንዲሁ አደረገች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም በባሕሩ ውስጥ አጠመቀቻቸው ያን ጊዜም ታላቅ ጸጥታ ሆነ።


ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰች ጊዜ ከአገር ልጆች ጋራ ያጠምቃቸው ዘንድ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልጆቿን አቀረበች በዚያን ጊዜም ከአገር ልጆች አጠመቀ። ወደልጆቿም ደርሶ ሊአጠምቃቸው ወሰዳቸው ያን ጊዜ ውኃው ረጋ እነርሱን ትቶ ከአገር ልጆች አጠመቀ ውኃውም ተፈትቶ ወረደ ደግሞ ሊአጠምቃቸው ወደ ልጆቿ ተመለሰ አሁንም እንደቀድሞው ውኃው ረጋ እንዲሁም ሦስት ጊዜ አደረገ ውኃውም ይረጋል አደነቀ። እናታቸውን አቅርቦ ጠየቃት እርሷም የሆነውን “በባሕር መካከል ዐውሎ ነፋስ እንደተነሣባት ጡቷን በጥታ ደሟን እንደ ቀባቻቸውና በባሕር ውስጥ እንዳጠመቀቻቸው ነገረችው ስለ አደረገችውም በድፍረት በፊቱ ሰግዳ ይቅር ይላት ዘንድ ለመነችው”። አባ ጴጥሮስም ” ሴትዮ አትፍሪ ሃይማኖትሽ ፍጹም ነው አንቺ በባሕር ውስጥ በአጠመቅሻቸው ጊዜ በመለኮታዊት እጁ ያጠመቃቸው ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና አይዞሽ” አላት። ማጥመቁን በፈጸመ ጊዜ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው።


ይቺም ቅድስት ወደ አንጾኪያ ቤቷ ተመለሰች። ባሏም በአያት ጊዜ ይህን በማድረጓ ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ሒዶ ከሰሳት ያደረገችውንም ነገረው። ንጉሡም ወደርሱ ያቀርቧት ዘንድ አዘዘ ስትቀርብም ወደ “እስክንድርያ ለምን ሔድሽ ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ልታመነዝሪ ነውን” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት “ክርስቲያኖች አያመነዝሩም እንደናንተ የረከሰ ጣዖትን አያመልኩም ከእንግዲህ ደግሞ ከእኔ ቃልን አትሰማም የወደድከውን አድርግ” ሁለተኛም “በእስክንድርያ ካንቺ የሆነውን ንገሪኝ ብሎ ጠየቃት ምንም ምን አልመለሰችለትም።


ንጉሥ ከዲዮቅልጥያኖስም እጆቿን የኋሊት አሥረው ሁለቱን ልጆቿን በሆድዋ ላይ አድርገው ሦስቱንም በእሳት ያቃጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ። ፊቷንም ወደ ምሥራቅ መልሳ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ጸለየች ከዚያም ከልጆቿ ጋራ ሚያዝያ25 አቃጠሉዋት የድልና የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ለዘላለም ይማረን አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 25 ስንክሳር።


“ሰላም ለሣራ እምሥርወ ክርስቲያን ሙላዳ። ብእሲሃ ዕልው ሶበ ዐውደ ምኵናን ወሰዳ። እምሰሚዐ ቃሉ ርኵስ ሶበ ኢትሠጥወቶ ለአግሪጳዳ። አዘዘ ያውዕይዋ ለእቶነ እሳት በነዳ። አንቢሮሙ በከርሣ ፪ተ ውሉዳ”። አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሚያዝያ 25።


የዕለቱ ምስባክ፦ “ወአምላክነሂ መስተሣህል። የዐቅብ ሕፃናት እግዚአብሔር። ተመንደብኩሂ ወአያድኃነኒ”። መዝ 114፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 10፥12-22፣ 1ኛ ዮሐ 4፥4-18፣ የሐዋ ሥራ 8፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥1-8። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ


ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል ከቀጰዶቅያ አገር ነው የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍስጥዓዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ። ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ። ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው። ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው።


ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም። ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቊስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደ ሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርነት አክሊል እንደሚቀበል ነገረው። ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው።


ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ ሞልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር። ቅዱሱም ያንን ጽዋ በመስቀል መልክት አማትቦ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ። ከእርሱ ጋራ ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቊጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው።


ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ። ቅዱሱንም “እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን” አሉት። በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቊጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ።


ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት። አቃጥለው አሳርረው ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ይድራስ ከተባለ ተራራላይ በተኑት። ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው። ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ። ቊጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታስነሳ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን በእርሱም እናምናለን” አሉት። ቅዱሱም ጸለየ ከመቃብር ጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ። ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ። ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት። የዚያች መበለትም ቤቷ ምሰሶ ቅርጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ። ያቺም መበለት በተመሰለች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ “የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደእኔ መጣ” አለች። ቅዱሱም “እኔ አምላክ አይደለሁም የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው “የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ። ዕውር፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምህሃለሁ”። ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያንጊዜም አየ። ቅዱስም “በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ” አላት። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት። ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው በመንኰራኵር አበራዩት ሙቶም በከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለሰ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ።


ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት “ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ” አለው። ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው። ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለእስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እንደሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀምረ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች።


በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአያት ጊዜ ፈገግ አለ “ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው” አላት ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ “ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እዘዘው” አለው። ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው። በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ “እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም” ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ። ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ከወገኖቹ ጋራ ዐፈረ። ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ። እርሷም “አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖች አትጣላቸው አላልኩህምን” አለችው። ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።


በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት። ያን ጊዜም የክብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ድል አድራጊ ቅዱስ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥታትን ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው። ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋራ ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ፣ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወታደሮቹ የቅዱሳን የከበረች ራሱን ቈረጡት ደም፣ ውኃና ወተት ፈሰሰው፤ ጌታም ቅዱስ ሚካኤልን በብርሃን ልብስ ደሙን እንዲቀበለው አዘዘ። ጌታችንም የኃያሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ነፍስ በእጁ ተቀብሎ ሳማት፤ በሰማያዊ ልብስም አጐናጥፎ ከእርሱ ጋራ ወደ ሰማይ አሳረጋት። አየር በሙሉ ቅዱሳን መላእክትን ተሞላ። ለቸር አባቱና ለመንፈስ ቅዱስ ቊርባን አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ ቅዱሳን ሁሉ በየወገናቸው ያመሰግኑ ነበር። የብርሃን ልብስ አለበሰው። በዕንቈ ባሕርይ ያጌጠ ከጽሩ ወርቅ የተሠሩ መከራ በተቀበለባቸው ሰባት ዓመታት ልክ ከዕፀ ሕይወት አበቦች የተሠሩ አክሊሎች ያሉበትን ዘውድ አቀዳጀው ለዘላለም ከማኅበረ በኵር ጋራ ስሙን ጻፈው። ሰማያውያን መላእክትና ቅዱሳንንም ሁሉ በየወገናቸው በመንበሩ ላይ እንዲአስቀምጡት፤ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በዓል እንዲ ያደርጉለት አዘዛቸው።


ከዚህም በኋላ ከመብረቁ፣ ከነጐድጓድ፣ ከንውጽውጽታው ጽናት፣ ከዝናሙ ብዛት የተነሳ በምድር ላይ ትልቅ ድንጋፄ ሆነ። ምድርም ሦስት ጊዜ ተናወጸች ከዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሸሹ ወደ ከተማም ሔዱ ጭፍሮችም ይህንን በአዩ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አመኑ። ነፍሱም ወደ ሰማይ በዐረገች ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሰገደች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምን ነፍስ ከሥጋዋ በተለየች ጊዜ አስቀድሞ ለሥሉስ ቅዱስ ትስገድ ከዚህ በኋላ ወደ ወዳጄ ወደ ጊዮርጊስ ይወሰዷት እና ለርሱ እጅ ትንሣ ብሎ አዘዘ፤ በዚህ ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስክርነቱ ሚያዝያ በባተ በሃያ ሦስት ቀን በዕተ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጸመ። አገልጋዮቹም ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደ ሀገሩ ልዳም ወስደው ቤተክርስቲያን ሰርተው በውስጡ አኖሩት፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችንን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ ገድለ ጊዮርጊስ እና የሚያዚያ 23 ስንክሳር።

📖ቅዱስ ጴጥሮስ ከዕንባው በኋላ





ጴጥሮስ መራራ ልቅሶን ካለቀሰና ከተመለሰ በኋላ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ የተሞላበትን ሕይወት ኖሯል፡፡ ጌታችን ለሦስት ጊዜ እንደሚክደው በነገረው ሰዓት ‹‹አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና››ብሎት ነበር፡፡ሉቃ 22-32 ቅዱስ ጴጥሮስ በመራራ ለቅሶ ወደ ጌታው በጸጸት ከተመለሰ በኋላ ጌታችን ንስሓውን እንደተቀበለለት ያሳየው ከሞት እንደተነሳ ነበር፡፡ ጌታችን ወደ መቃብሩ ለመጡት ሴቶች በመላእክቱ በኩል በተናገረው መልእክት‹‹ሒዱና ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም ጌታ በገሊላ የቀድማችኋል ብላችሁ ንገሯቸው››በማለት በትንሳኤው ደስታ ላይ ክጄዋለሁ ብሎ ተስፋ ቆርጦ ከደቀ መዛሙርቱ እንዳይለይ ጴጥሮስን በስም ጠቅሶ ጠርቶታል፡፡ማር 17-7

በገሊላ ባህር ጌታችን በተገለጠላቸው ጊዜም ‹‹የዮና ልጅ ስምዕን ሆይ ከሁሉ ይልቅ ትወደኛለህ››ብሎ ከወቀሳ ይልቅ ርኅራኄን በተሞላ ቃል በማነጋገር ሦስቴ የካደው ጰጥሮስ ሦስት ጊዜ አሳምኖታል፡፡ዮሐ 21 15-17 ልቡ በጸጸት የተሰበረው ጰጥሮስም እንኳን እንደበፊቱ ‹‹ከወንድሞቼ እበልጣለሁ››ሊል ቀርቶ ‹‹ጌታ ሆይ እወድሃለሁ›› ለማለት እንኳን ድፍረት አጥቶ‹‹እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ››ብሏል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በንስሓ ከተመለሰ በኋላ ‹‹ከሁሉ ይልቅ እኔ›› ማለቱን ትቶ‹‹እርስ በእሳቸው እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ›› የሚል የትሕትና መምህር ሆነ፡፡1ኛጴጥ 5-5 በአንዲት አይሁዳዊት ገረድ ፊት ፈርቶ ስ ካደው ጌታው በብዙ ሕዝብ ፊት መስክሮ በአንድ ቀን ሦስት ሺ ሰዎች ክርስትያን አደረገ፡፡ሐዋ 2 14-41 ጌታችን ከወደቀበት ጭቃ ላይ አንስቶ እንደ እንቁ ወልውሎ አክብሮ በበጎቹ ላይ የሾመው ጴጥሮስ እስከ ሽምግልናው ድረስ ያለ መታከት አደራውን በመወጣት ሐሙስ ምሽት ለበደለው በደል ብዙ ትጋት ካሰ፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‹‹ከፊትህ አትጣለኝ ቅዱስ መንፈስህ ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ›› ብሎ በጸጸት ከጸለየ በኋላ ‹‹ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ›› እንዳለ ጴጥሮስም ከንስሓው በኋላ ‹‹ወንድምህ አጽና›› የተባለውን ያለመታከት ጠብቆ ብዙ ኃጢአተኞችን ወደ እግዚአብሔር መለሰ፡፡

ቅዱስ ጰጥሮስ የአገልግሎቱ ፍጻሜ ያደረገው በሮም አደባባይ በሮማውያን ወታደሮች ተከብቦ ነበር፡፤ጌታችን‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደ ምትወደው ትሔድ ነበር ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደ ማትወደው ይወስድሃል›› ብሎ ነግሮ ነበር፡፡ስለዚህ የቄሳር ወታደሮች ሽማግሌውን ጴጥሮስ እጆቹን አስዘረጉት ሰንሰለትን አስታጥቀው እየጎተቱ ወደ ሮም አደባባይ ወሰዱት፡፡ በዚያች ቀን ጰጥሮስ የሮምን ወታደሮች አልፈራም እሳት ለመሞቅ ወደ ማንም አልተጠጋም፡፡ ሐሙስ ማታ ያየውን የጌታውን ፊት ወደ ሰማዓትነት ሲመጣም ያየውን የጌታን ፊት በዓይነ ሕሊናው እያየ ‹‹ጌታዬ ሆይ ዛሬስ አልክድህም››ብሎ ተነሳ፡፡

ወደ አደባባዩ እንደደረሱሮማውያን እንደ ለመዱት በመስቀል ሊሰቅሉት መስቀል አዘጋጅተው ተመለከተ፡፡ጰጥሮስ ግን ‹‹አይሆንም ጌታዬ በተሰቀለበት መስቀል ላይ እኔ ልሰቀል አይገባኝም››አለ፡፡ ለሮማውያን መስቀሉ ባዶ እንጨት ቢሆንም እንደ ጰጥሮስ ላለ ክርስትያን ግን አሁንም ክርስቶስ በዚያ መስቀል ላይ‹‹እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሏል›› ስለዚህ በጌታው ዙፋን ላይ ይቀመጥ ዘንድ ጰጥሮስ ሕሊናው አልፈቀደለትም፡፡

ስለዚህ በዚያው መስቀል ላይ ጭንቅላቱን ወደ ታች ዘቅዝቀው ይሰቅሉት ዘንድ ለመናቸው፡፡እነርሱም የፈቃዱን አደረጉለት፡፡ሽማግሌው ቅዱስ ጰጥሮስ በሮም ቫቲካን አደባባይ ላይ ተዘቅዝቆ እርቃኑን ተሰቀለ፡፡‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህ››ለሚለው የጌታው ጥያቄም በዚያች ዕለት መልስ ሰጠ በረከቱ ይደርብን! አሜን

✍ሕማማት
ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ገጽ 155

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org