ዕረፍታ ለማርያም

ልቡናዋ በይኩነኒ የጸና ንጽሐ ሥጋ ፣ ንጽሐ ነፍስ ፣ ንጽሐ ልቡና አስተባብራ የያዘች ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተንሥኢ ወንዒ”  “የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ውድ እናቴ ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ” (መኃ ፪፥፲) ብሏታል። ቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር” መዝ.፹፮፥፫  “እግዚአብሔር ማኅፀንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው” እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል።

ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፤ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ” /  “ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፤ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል”  በማለት ገልጾታል። የቤተክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደሆነ ያስረዳል። የመጀመሪያው  “ለመለኮት ማደርያ ለመሆን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትሆን ነው እንጂ ምድራዊት ሴትማ እንደ ምን ሰማይና ምድር የማይችሉትን ልትሸከመው ይቻላታል?”  የሚሉ ወገኖች ነበሩና በርግጥም እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ እንጂ የመላእክትን አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው ፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸው ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” አለ፡፡ (ዕብ.፪፥፲፬-፲፭) በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መሆኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው ቅዱስ ያሬድ እንዳለው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በለበሰው ሥጋ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

ከዕረፍቷ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን።መልካም ዕለተ ሰንበት

አዲስ አበባን እንደ ኒቂያ(የጉባዔ አዲስ አበባ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ)

ወቅቱ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ቦታውም አዲስ አበባ ነው። በንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ኅሊና ውስጥ ያደረውን ከኤፌሶኑ ጉባዔ ፲፭፻ ዓመታት በኋላ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (ኦሪየንታል) አባቶችን የሚያሰባስብ ጉባዔ ለማዘጋጀት አዲስ አበባ እየተንጎዳጎደች ነው። በዚህ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ በራሳቸው በንጉሠ ነገሥቱ በኩል የ፭ቱ አኀት አብያተክርስቲያናት ጥሪ የደረሳቸው በግንቦት ፲፱፻፶፮ ዓ.ም. ነበር። አብያተ ክርስቲያናቱ ለመገኘት ይሁንታቸውን ሲቸሩ መርሐግብሩን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎችን በመሠየም ወደ ሥራ ተገባ።

የመጀመሪያው ኮሚቴ በሐረር ሊቀጳጳስና በፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (በኋላ ፓትርያርክ) የሚመራ የመርሐግብር ኮሚቴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግስት ሥራ ሚኒስቴር ሚንስትር ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ የሚመራ የአቀባበል ኮሚቴ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ የጤና ሚኒስትር አቶ አበበ ረታ ዋና ጸሐፊነት የሚመራ ጽሕፈት ቤት ተቋቋመ። ኮሚቴዎቹ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ተወካዩ ከአባ ጳውሎስ ቬርጋስ ጋር በመተባበር ከጉባዔው ወራት አስቀድመው ነበር ዝግጅታቸውን የጀመሩት። በብፁዕ ወቅዱሳን ፓትርያርኮች ከሚካሄደው ዋናው ጉባዔ አስቀድሞ ከ፭ቱም አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ዐሥር የነገረ መለኮት ምሁራን ከዝግጅት ኮሚቴው ኃላፊዎች ጋር ከታኅሣሥ ፳፱/፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ጀምሮ ለ፯ ቀናት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ተካሄደ።

ጉባዔው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ጸሎትና አባታዊ መልእክት የተከፈተ ሲሆን በብፁዕነታቸው ሊቀመንበርነት እየተመራ በዝግ ባደረገው ጉባዔ ለዋናው ጉባዔ የሚያገለግሉ ፮ ርእሰ ጉዳዮችን ለየ። እነዚህ ፮ ርእሰ ጉዳዮች:
፩. ቤተክርስቲያንና ዘመናዊው ዓለም፣
፪. በነገረ መለኮት ትምህርት ላይ የሚኖር ትብብር፣
፫. በወንጌል መስፋፋት ዙሪያ የሚኖር ትብብር፣
፬. ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ጋር የሚኖሩ ግንኙነቶች፣
፭. የአብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት ለማስቀጠል የሚያስችል ቋሚ መንገድ ማመቻቸት፣
፮. በዓለሙ ላይ ስለሚታየው ሰላም ማጣትና ፍትህ ዙሪያ አቋማቸውን ማንፀባረቅ ነበር።

ከቅድመ ጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ለዋናው ጉባዔ በእንግድነት የተጋበዙ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ተወካዮች ታጅበው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ንጉሠ ነገሥቱ ከከፍተኛ የቤተክርስቲያንና የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያና በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቀባበል ተደርጎላቸዋል።  በጉባዔው ላይ የተገኙ አብያተክርስቲያናት አባቶችም:

፩. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ ከ፬ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፪. ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ሞር አግናጥዮስ ያዕቆብ ፫ኛ፣ ከ፭ የአንፆኪያና የመላው ምሥራቅ የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣
፫. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቫኪን ቀዳማዊ በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኢታችማንዴዝና የመላው አርማንያ ፓትርያርክ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ ካቶሊኮስ አቡነ ኮራን ቀዳማዊ በአርመን ቤተክርስቲያን የኪልቅያ መንበር ፓትርያርክ ከ፱ የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፬. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ቀዳማዊ ከ8 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልኡካን ጋር፣
፭. ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ማር ባስሊዮስ አኡጉን ቀዳማዊ ከ፯ የማላንካራ ሶሪያዊት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (ህንድ) ጋር ናቸው። ዋናው ጉባዔ ጥር ፮ በአፍሪካ ኅብረት ዋናው አዳራሽ ሲካሄድ በጥንታዊው ሥርዓት መሠረት ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው በየደረጃው የተቀመጡ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ባለ ጠረጴዛ ላይ ከፊት ለፊት በማኖር ጉባዔው ተጀመረ። ጉባዔው በንጉሠ ነገሥቱ፣ በሶሪያና አርመን ፓትርያርኮች ተከታታይ የመክፈቻ ንግግር ከተጀመረ በኋላ በቅድመ ጉባዔ በረቀቁ ዐሳቦች ዙሪያ እስከ ጥር ፲፬ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ድረስ ውይይት አካሂደዋል። ይሄኛውም ጉባዔ በዝግ የተካሄደ ሲሆን በጉባዔው ጥያቄ መሠረት አቶ አበበ ረታ በአስተባባሪነት፣ አቶ አበራ ጀምበሬ ደግሞ በዋና ጸሐፊነት ተሳትፈውበታል። ጉባዔው ሲጠናቀቅ:
✍️ቅዱሳን ፓትርያርኮች ንጉሠ ነገሥቱን  ወልታ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጋሻ) ብለው የሰየሙ ሲሆን ትውፊትና ጥንታዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ለወጣቶች፣ በከተማ ለሚኖሩ ምእመናን እንዲሁም ለቤተሰብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ፣

✍️መጽሐፍ ቅዱሳዊውንና ሐዋርያዊውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ዘመኑን ለወለዱ አዳዲስ ትምህርቶችና ርእዮተ ዓለሞች ምላሽ በሚሆኑ መልክ ማዘጋጀትና ሥነጽሑፍን ማስፋፋት፣

✍️ሥርዓተ ምንኩስናን ማስፋትና ማፅናት በተለይም የቀደመውን ሥርዓት በመመለስ የሴቶችን አገልግሎት ማጠናከር፣

✍️የቤተክርስቲያን አስተዳደር በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚታየው የሰፋ ልዩነትን መልሶ በማገናዘብ ለሐዋርያዊ ሥርዓትና ለኖላዊ አገልግሎት ምቹ በሆነ መንገድ ማስተካከል እንደሚገባ ፣

✍️በነገረ መለኮት ትምህርት የጋራ ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረፅ ጀምሮ የትምህርት ዕድሎችን፣ የመማሪያ መጻሕፍትን፣ ምሁራንን ለመጋራት፣

✍️ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ ከሮማ ካቶሊክና ከሌሎች አብያተክርስቲያናት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች መጠናከር እንደሚገባቸው በማመን በውይይቶች ላይ ተመሳሳይ አቋምና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ፣

✍️የኦርየንታል(ተዋሕዶ) አብያተክርስቲያናት ግንኙነት ቀጣይ ሊሆን እንደሚገባ በመስማማት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁለት ሁለት ተወካዮች እንዲሰየሙ፣

✍️በዓለም ላይ ያለ፡ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ ቅኝ ግዛትን በማውገዝ በመላው ዓለም ለሚከናወኑ የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎችን እንደሚደግፉ የሚገልፁ ውሳኔዎችን በመስጠት ተጠናቋል።

ጉባዔው ከሺህ ዓመታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ቢሆንምና በቀጣይነቱ ላይ ሁሉም አብያተክርስቲያናት የተስማሙ ቢሆንም በመሪዎች ደረጃ መሠል ጉባዔ ድጋሚ ሳይካሄድ እነሆ ፷ ዓመታት አልፈዋል። ነገር ግን ጉባዔው አብያተክርስቲያናት አሁን ላይ ላላቸው የትብብር መንፈስና አንድነት፣ በልዩልዩ ጉዳዮች ላይ ላላቸው ወጥና ተመሳሳይ አቋም መነሻ በመሆኑ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ደማቅ ኵነት ሆኖ ቀጥሏል። በሰሜን አሜሪካ መቀመጫውን ላደረገው የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ስታንዲንግ ኮንፍረስ ለተሰኘው ተቋምም ምሥረታና ህልውና እንደ ጋራ ሠነድ እያገለገለ ይገኛል። ይህን አዲስ አበባን እንደ ኒቂያ ንጉሠ ነገሥቱንም እንደ ቆስጠንጢኖስ ያስቆጠረውን ጉባዔ የዳሰስንበት ሰፊ ጥንቅር የምናበቃው አምላከ ቅዱሳን ዳግም ጉባዔውን የማስጀመር መነሳሳት በፍቁራኑ ልብ እንዲያሳድርና የቤተክርስቲያንን አንድነት እንዲጠብቅ በመመኘት ነው።

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ 

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ አርእስተ ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ (ባስልዮስ የሚሉ አሉ)፣ እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው ፭ ወንድ እና ፩ ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ ( ቅድስት ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን ፭ቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው:: የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው ። ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ፣ ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ፣ የብዙ ምእመናን አባት፣ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት፣
ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ፬ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው:: እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::

በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውዬውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ:: እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን “ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ” አለው:: ያ ከንቱ ሰው “እሺ” አለ:: መተተኛው ቀጠለ “በል! ሌሊት ፮ ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል” ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ፣ ነጥቆ ወደ ጥልቁ የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- “አንተ የፈለግኸው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ” አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው:: በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው “ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ” አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ:: እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተዉት አልወደዱምና ጾሙ፣ ጸለዩ፣ ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::

አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ   ” ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ፣ ቆርበህ፣ ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ፣ አማትበህስ ታውቃለህ?” አለችው:: እርሱም “በጭራሽ አላውቅም” አላት:: “ለምን?” ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት:: ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በኅሊናዋ አንድ ዐሳብ መጣላት:: “ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል” አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች:: እርሱም “ልጄ ሆይ! አይዞሽ! በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሽን አምጪው” አላት:: ሔዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው “መዳን ትፈልጋለህ?” አለው:: ሰውየው መልሶ “ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር” አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን “ሒጂና ጸልዪ! ከ፵ ቀን በኋላ ትመጫለሽ” ብሎ አሰናበታት:: በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ፬ አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት “ከ፫ ቀን በኋላ እመጣለሁ” ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ፫ኛው ቀን መጥቶ “እንዴት ነህ?” አለው:: “አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ” አለው:: “አይዞህ!” ብሎት ወጣ::
በ፮ኛው ቀን መጥቶ “አሁንስ?” አለው:: “አባ! ስቃዩ ቀረልኝ፤ ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል” አለው:: “በርታ” ብሎት ሔደ:: በ፱ኛው ቀን ተመልሶ “ደግሞ አሁንሳ?” አለው:: “አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው” አለው:: እንዲህ በ፫ ፣ በ፫ ቀናት እየተመላለሰ ለ፲፫ ጊዜ ጠየቀው:: በ፴፱ኛው ቀን መጥቶ “ዛሬ ምን አየህ” ቢለው “አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ” አለው::

ቅዱስ ባስልዮስ በ፵ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናንን ሰብስቦ፣ ያንን ሰው ከመሃል አቁሞ፣ “እግዚኦ በሉ” አላቸው:: ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ፵ ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ፤ የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር ፮ ቀን ዐርፏል::አምላከ ቅዱሳን ከረድኤት በረከቱ ያሳትፈን።

የሰላሙ ንጉሥ ልደት በጦርነት(ከቤተልሔም እስከ ላሊበላ)

አስቀድሞ በትንቢት “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ኢሳ ፱÷፮ የተባለለትን ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ትዕምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ” “የሰላማችን ምልክት ወልድ ተወለደልን” ብሎ የተናገረለት የሰላሙ አለቃ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተከበረና ለመከበርም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።ምዕራባውያንን ጨምሮ የህንድና የሶሪያ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት በጎርጎርዮሳውያን ዘመን ቀመር መሠረት ባሳለፍነው ሣምንት ታህሣሥ ፲፯ በዓሉን አክብረዋል። በኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት የዘመን ቀመር ሥር የሚገኙት የኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊያን በታኅሣሥ ፳፱ በዓለ ልደትን ለማክበር በልዩ ጉጉት ውስጥ ሆነው እየጠበቁ ይገኛሉ።በዓለ ልደት ሲነሳ በክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ ስላገኘነው ታላቅ ሠላም “ወሰላም ለምድር፤ ስምረቱ ለሰብእ” እያልን የምንዘምርበት ዕለት ቢሆንም ዘንድሮ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በዩክሬንና ሩሲያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሰላም እጦት ውስጥ ሆነው ለማክበር ተገደዋል። በዚህ ሳምንት ዘገባችንም የገና በዓል በድምቀት የሚከበርባቸው አካባቢዎች የዘንድሮን የበዓል አከባበር እንመለከታለን።

ላሊበላ – ኢትዮጵያ፡ ከአንድ አለት የተፈለፈሉ አሥራ አንድ አብያተክርስቲያናት የሚገኙባት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም የተሰኘችዋ ደብረ ሮሃ በዓለም ላይ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል አንዷ ናት። ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ አውጪዎች ለገና በዓል ከቅድስት ቤተልሔም ቀጥሎ በ፪ኛ ወይም በ፫ኛ ደረጃ የሚያስቀምጧት ላሊበላ ልብን በሚመሥጠው “የቤዛ ኩሉ” ዝማሬዋ ልቦናን ወደ ክርስቶስ የልደት ምሽት በመውሰዷ በብዙኀኑ ምእመናንና ቱሪስቶች ዘንድ በየዓመቱ ትናፈቃለች።ይህች የምስጋና ደሴት ግን ድኅረ ኮቪድ ሀገራችን ባስተናገደቻቸው አራት የጦርነት ዓመታት ምክንያት የደኅንነት ሥጋት ተጋርጦባታል። በዚህም ከሩቅና ቅርብ የሚመጡ የተሳላሚዎች መጠን በመቀነሱ አብያተ ክርስቲያናቱና በጎብኚዎች ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል። ማግሰኞ ለሚከበረው በዓለ ልደት እየተዘጋጀች የምትገኘው ላሊበላ ዘንድሮም በተስፋና ሥጋት ውስጥ ሆና እንግዶቿን እየጠበቀች ነው።በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም እየተካሄዱ ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ባስከተሏቸው ጫናዎች ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያዊያን በዓለ ልደቱን በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ገና በሩሲያና ዩክሬን፡ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝቦችን የያዙት ሩሲያና ዩክሬን በዓለ ልደትን ለዘመናት በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት በታኅሣሥ ፳፱ ያከብሩ የነበረ ቢሆንም ዩክሬን ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የሩሲያን ተፅዕኖ ከዩክሬን ለማጥፋት በሚል ስበብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግስት ውሳኔ ከምዕራባውያን ጋር በታኅሣሥ ፲፯ ለማክበር ተገዳለች። ከሩሲያና ከሩሲያ ቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ከምድረ ገጿ እያጠፋች የምትገኘዋ ዩክሬን ለኦርቶዶክሳዊያን ሲኦል ሆና እየተሠራች እንደምትገኝ በርካቶች ይናገራሉ።ዩክሬን የዘንድሮ የገና በዓልን እንደ ከዚህ ቀደም በሚያማምሩ ርችቶች ሳይሆን በእስካሁኑ ጦርነት ታይቶ በማይታወቅ የባለስቲክ ሚሳኤል ናዳ ነበር ያከበረችው። ለአንድ ሰው ሞትና ለአስራ አምስት ሰዎች መቁሰል ምክንያት የሆነው ይህ ጥቃት ከፍተኛ የኀይል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ በማድረጉ ዩክሬናውያን በዓሉን በጨለማ ለማሳለፍ ተገደዋል።

ልደት በመካከለኛው ምሥራቅ፡የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በሶሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአዲሱ ወታደራዊ መንግስት ስር ሆነው የልደት በዓልን ታኅሣሥ ዐሥራ ሰባት አክብረዋል።የልደት በዓል አከባበሩ በደማስቆ መንበረ ፓትርያርክ በሰላም የተካሄደ ቢሆንም እንደ አሌፖና አልዋ ባሉ አካባቢዎች ክርስቲያኖች የተፈናቀሉበት የልደት በዓል መታሰቢያዎች የተቃጠሉበትና ግጭቶች የተነሱበት ሆኖ አልፏል።

በዓለ ልደት በሊባኖስና ኢራቅ፡ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኪልቂያ መንበር መቀመጫ በሆነችው ሊባኖስ የገና በዓልን ከእስራኤል ጋር ባለው ጦርነት ሥጋት ውስጥ ሆና በቀዘቀዘ የሀዘን ድባብ ውስጥ አክብራለች።በኢራቋ ነነዌ ደግሞ በዓሉን በሥጋት ውስጥ ሆነው ቢጀምሩትም ኢስላማዊው የሺሃይት ብርጌድ ባደረገው ጥበቃ ያለምንም ችግር በዓሉን አከናውነዋል። ይሄንን ተከትሎ በርካታ የኢራቅ ክርስቲያኖች ለብርጌዱ ያላቸውን አክብሮት ሲገልፁ ተስተውለዋል።

ባለ ፪ በዓሏ ቤተልሔም፡ከእስራኤል ጋር አመትን የተሻገረ ግጭት ውስጥ በምትገኘው ፍልስጤም የዌስት ባንክ አስተዳደር ስር ያለችውና የክርስቶስ ኢየሱስ የልደት ቦታ የሆነችው ቤተልሔም በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የገናን በዓል ሁለት ጊዜ ታከብራለች። ታኅሣሥ  ፲፯ እና ፳፱። እነዚህ ቀናት በክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን በእስልምና ተከታዮች ዘንድ የሚናፈቅና በየዓመቱ በሚልየን የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚገኙበት የነበረ ቢሆንም ቤተልሔም ዘንድሮ ያን ተናፋቂ በዓል ለማክበር አልታደለችም። በከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር ክርስቲያኖች ሥርዓተ አምልኳቸውን በአብያተክርስቲያናታቸው አክብረው እንዲመለሱ ከመንግስት ባለሥልጣናት በተላለፈላቸው መመሪያ መሠረት የታኅሣሥ ፲፯ቱን በዓል ዝም ባለ ድባብ ያከበሩ ሲሆን የታኅሣሥ ፳፱ኙም ተመሳሳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው በዓለ ልደትን የሚያከብሩ የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪያቸውን እያሰሙ ሲሆን ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመትና ተያይዞ ለሚከበረው የልደት በዓል ለመላው ዓለም መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው። ዓለም በዚህ ትብታብ የመከራ አዙሪት መውጣት የምትችለው በይስሙላ የሰላም ስብሰባ አለመሆኑን ጠቅሰው “ስለዚህ በዚህ የልደተ ክርስቶስ መታሰቢያና የ2025 ዓ.ም. መቀበያ ላይ ቆመን ይቅር መባባል፣ ለጋራ ቤታችን መሥራትና በሰዎች አለመግባባት የታወከችውን ዓለም በሰዎች ቁርጥ ውሳኔ እንድትረጋጋ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ።” ሲሉ ጥሪያቸውን በመላው ዓለም ላሉ ሁሉ አቅርበዋል።እኛም የቅዱስ አባታችንን ጥሪ፣ ጥሪ አድርገን የልደቱ ባለቤት መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእርሱ የሚገኘውን ሰላም እንዲሰጠን እየተመኘን የዛሬውን በዚህ ቋጨን።መልካም ገና፣ መልካም ሰሞነ አስተርዕዮ!

ፍቅር

በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር የወሰነ ሰው ሰውን ሁሉ ሊወድ ይገባል፡፡ ፍቅር ሲባል ፍትወታዊ የጾታ ፍቅር ሳይሆን ሁሉንም ሰው ሳይለያዩ መውደድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግጋት ሁሉ ፍቅርን ያስበለጠው፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲጠቅስ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ  ናስ ወይም እንደ ሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፤ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና ዕውቀትን  ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈርስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፤ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል፣ አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም…(፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፩) በማለት አስረድቷል፡፡

በክርስቲያናዊ ሕይወታችን በእምነት መነጽርነት እግዚአብሔርን ማየት የምንችለው ፍቅርን መሠረት ያደረገ ሕይወት ሲኖረን መሆኑን «እግዚአብሔር ፍቅርነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል» በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፮) ሀብተ ወልድ እና ስመ ክርስትና አግኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓ ሜሮን ተቀብቶ የከበረ ክርስቲያን ሁሉ ፍቅር ማለት እግዚአብሔርን የምናይበት የኅሊና መስታውት መሆኑን ተገንዝቦ በፍቅር ሊኖር ይገባዋል፡፡

ያለ ፍቅር ምንም ዓይነት ሥራ ቢሠራ ዋጋ የለውምና ፍቅርን ገንዘብ እናድርግ፡፡ ያለ ፍቅር ከሚሆን ብዙ ሥራ ይልቅ በፍቅር የሚሆን ትንሽ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነውና ፍቅርን እናስብ፣ በፍቅር እንኑር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነውና እርሱን እንምሰል፡፡ ስለ ፍቅር ሰው ሆኖ የተሰቀለልንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን እኛም ለወንድሞቻችን ፍቅርን እንስጥ፡፡ በፍቅር እየኖርን የምናደርገው መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ፍሬ አፍርቶ የምናየው በፍቅር መኖር ስንችል ነው፡፡ አባቶቻችንን እናስብ፡፡ ገድል የፈጸሙት፣ ተኣምር ያደረጉት፣ ታሪክ የሠሩት፣ ስማቸውን በሰማይ መዝገብ ያሰጻፉት በፍቅር መኖር በመቻላቸው ነው፡፡ በፍቅር ስለ ፍቅር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ መልካም ሰንበትምንጭ ፦  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ (በመምህር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ)

ክርስትና በሶሪያ: መፈንቅለ መንግስት የወለደው ሥጋትና ተስፋ

ከጦርነት በፊት ከጠቅላላ ሕዝቧ ዐሥር ከመቶው ክርስቲያን እንደነበረ የሚነገርላት ሶሪያ የዛሬ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነበር። በዓረብ የፀደይ ዐብዮት ነበር ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት የገባቺው። ከኃምሳ ዓመታት በላይ ሶሪያን የመራው የበሽር አላሳድ ቤተሰብ ለውጥ በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች፣ በአይ. ኤስ. አይ. ኤስ. እና መሠል አክራሪ ሙስሊሞች የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ቢቆይም በኅዳር ወር መጨረሻ ሳምንታት የደረሰበትን ምት መቋቋም ባለመቻሉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትና ቤተሰቦቻቸው ስልጣንና ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሩሲያ ከኮበለሉ አስር ቀናትን ተሻግረዋል። የፕሬዝዳንት በሽር አላሳድን ከሀገር መኮብለል ተከትሎ ሀገሪቱን ኢስላማዊ ተዋጊ ሃይሎች ተቆጣጥረዋታል። በተለይም ሀያት ታህሪር አል-ሻም ዌም (HTS) ተብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ደማስቆን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን የመቆጣጠር እድል አግኝቷል። የአላሳድ ውድቀትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ይገኛል።

በበሽር አላሳድ ከስልጣን መነሳትና የእስላማዊ ቡድኖች መተካት ከደስታ ይልቅ ስጋት ያረበባቸው ክርስቲያኖች ናቸው። ባለፉት ዐሥራ ሦስት የእርስ በእርስ ጦርነት ዓመታት እኒህ ክርስቲያኖች በልዩነት የጥቃት ሰለባዎች በመሆናቸው ከጦርነቱ በፊት ከነበራቸው የዐሥር በመቶ ሀገራዊ የሥነ ሕዝብ ድርሻ ወደ ሁለት በመቶ ወርደዋል። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ምእመናን በጅምላና በነጠላ ተገድለዋል። ብዙዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ይህ ታሪክ ከመፈጠሩ ከሺህ ዘመናት በፊት ግን ሦርያ የክርስቲያኖች መናኸሪያ ነበረች። በአንፆኪያና በደማስቆ ታላላቆቹ ሀዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ አስተምረዋል። ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ መናብርትና ከሁለቱ ጥንታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የሚገኙት በሶሪያዋ አንፆኪያ ነበር።

ሶሪያ በኒቂያ ከተሰበሰቡ ሠለስቱ ምዕት የሃያው ሀገር ናት። በዚህች ምድር አግናጢዮስ ምጥው ለአንበሳና ቅዱስ ኤፍሬም በቅለውባታል። ነገር ግን የዐረብ ወረራና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የኦቶማን እንቅስቃሴ ሶሪያውያን ክርስቲያኖች አንፃራዊ የእምነት ነፃነት ወደሚያገኙባቸው ሀገራት እንዲሸሹ አልያም በሀገራቸው ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ አስገድዷቸዋል። በዐሥራ ስምንት መቶዎቹ እንኳን በተካሄደ የኦቶማን ጭፍጨፋ ከ፺ ሺህ በላይ ክርስቲያኖች ተገድለዋል።ዛሬ ላይ የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ የሶሪያ ክርስቲያኖች በከባድ ውጥረት ላይ ናቸው። በተለይ ከአል አሳድ ሽሽት በፊት ክርስቲያኖች በስፋት በሚኖሩባት በአሌፖ የአማፂው ቡድንና ደጋፊዎቻቸው የጥቃት ኢላማ መሆናቸው መጪውን ጊዜ በፍርሃት እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።vከሦርያ ክርስቲያኖች ውስጥ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የሶሪያና የአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሦስተኛውን ይይዛሉ። የተቀሩት በክርስቲያን ምድብ የሚካተቱት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የአሲርያንና የመናፍቃን ቡድኖች ናቸው።የመንግስት ግልበጣው ሲካሄድ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ህንድ የነበሩት የሶሪያ (ያዕቆባዊት) ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ሞራን ሞር አግናጢዮስ ኤፍሬም ፪ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ከወገኖቻቸው ጋር የሚመጣውን ለመጋፈጥ ወደ ሶሪያ ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሶሪያ መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ በሶሪያ መንበረ ፓትርያርክና በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና አገልጋዮች ጋር የተወያዩ ሲሆን ከሀገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች ጋር በመገናኘትም ክርስቲያኖች የሀገሪቱ ጠቃሚ አካል እንደመሆናቸው ደኅንነታቸው እንደሚጠበቅ ከመንግስት ቃል እንደተገባላቸው ከውይይቶቻቸው በኋላ በመንበረ ፓትርያሪካቸው በኩል በወጣው መግለጫ አንስተዋል።

ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አዕምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና ዐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊል ፬÷፮-፯ በሚል ርእስ ባወጡት መግለጫ ምእመናንና አገልጋዮች ከመቼውም ይልቅ በፆምና በጸሎት እንዲሁም የሀገሪቱን ሁኔታ በንቃት በመከታተል እንዲያሳልፉ፣ መንግስት የአናሳዎችን መብት እንዲያስጠብቅ፣ ፓሊሶችና የጦር ኃይሎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በውጭ ያሉ ሀገረስብከቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል። ፓትርያሪኩ “የሰላምና የተስፋ ምንጭ የሆነውን የጌታችን የልደት በዓል ከፊት እየጠበቅን ሰላምና ብልፅግናን ለሀገራችን እንዲያመጣልን እንመኛለን” ብለዋል። ብፁዕ አቡነ ሞር ቡትሮስ (ጴጥሮስ) ቀሲስም ሶሪያውያን ክርስቲያኖች እውነታውን በመረዳት፣ በንቃትና በእምነት ሆነው እንዲጋፈጡ ምእመናንን እያበረታቱ ይገኛሉ።የሦርያ ክርስቲያኖች ከአል አሳድ መነሳት በኋላ የመንግስትን ቃል አምነው ያሳለፍነው እሑድ ቤተ መቅደሶቻቸውን ቢከፍቱም አክራሪዎችን ማመን የሚያስከፍለውን ዋጋ ያውቃሉና ዛሬም በስጋት ልብ ውስጥ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ።በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሶሪያ አሌፖ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማጋር አሽካሪን “ፍጹም የሚባል ደኅንነት የለም፤ ነገር ግን እንደ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። እንደ ዐሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ እናምናለን። ብለዋል።እግዚአብሔር በምድረ ሶሪያ መረጋጋትን ለቤተክርስቲያን ደግሞ ሰላምና ፍፁም አንድነትን እንዲሰጣት እንድንጸልይ እያሳሰብን የዛሬን በዚህ አሳረግን።

እንዴት ንስሐ እንግባ???

ንስሐ :- ነስሐ ከሚል የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ሐዘን፣ ፀፀት፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ንስሐ ገባ ሲባልም ዐዘነ፣ ተፀፀተ፣ ተመለሰ፣ ክፉ አመሉን ተወ ማለት ነው፡፡ ንስሐ አንድ ሰው በሠራው ጥፋት፣ ባደረገው ስህተት፣ በፈፀመው ኃጢአት ማዘኑንና መፀፀቱን ዳግመኛም ያንን የመሰለ ኃጢአት ላለማድረግ የሚወስነው ውሣኔ ነው፡፡

እንዴት ንስሐ ይገባል?  ፩. ከራስ ጋር መሆን:- ንስሐ መግባት የራስ ፈቃድ ይጠይቃል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ንስሐ እንዲገባ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ሊድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ እንደሚወዱም ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ጢሞ.፪፥፫ ላይ ነግሮናል።

፪. ምክንያትንና ለራስ ይቅርታ ማድረግን ማስወገድ:–  በንስሐ ሕይወት ለመኖር የምንሻ ከሆነ ለወደቅንበት ኃጢአት ምክንያት መደርደርና ለራሳችን ይቅርታን ለመስጠት መሞከር የለብንም። ኃጢአትን ከፈፀሙና ከሠሩ በኋላ ለኃጢአት ያበቃ ሌላ ምክንያት ማቅረብና በዚያም አንፃር ለመጽናናት መሞከር በራሱ ኃጢአት ነው። በዚህ ዓይነት ለኃጢአቱ ምክንያት እየደረደረ የሚጽናና ሰው ኃጢአትን እየለመደ ወደ ባሰ አዘቅት ከመውረድ በቀር ንስሐ ለመግባት አይችልም። ምንም ምክንያት ቢደረደር ኃጢአት ምንጊዜም ኃጢአት ነውና ለሠራነው ኃጢአት የተለያዩ ምክንያቶችን በማበጀት ራሳችንን እያጽናናን ነፃ ለመሆን መጣር የለብንም፣

፫. ንስሐ ለመግባት አለመዘግየት (አጋጣሚውን መጠቀም) :-  አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ለመግባት የገጠማቸውን የተመቻቸ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት በመቅረት ዕድሉ አምልጧቸዋል። እግዚአብሔር ሰው ሁሉ ኃጢአቱን መርምሮ ወደ ንስሐ እንዲመለስ፣ የተቀደሰ ጸጋውን ሊያድለውና በልቡናውም አድሮ ለመሥራት አብዝቶ ይሻል። ሰው በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ንስሐ ሊገባይችላል። ለምሳሌ:- በመጻሕፍት ፣ በዝማሬ ፣ በበሽታ፣ በአደጋ፣ በሞት ወዘተ. ተመክሮ ንስሐ ሊገባ ይችላል። በእነዚህ አጋጣሚዎች የሚጠቀምባቸው ሰውም አስተዋይ ነው። የጠፋው ልጅ “ተነስቼ ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ” ሲል እንደተናገረና ከአባቱ እንደታረቀ ወደ ቤቱም እንደ ተመለሰ። ሉቃ. ፲፭፥፲፰ የማያስተውል ሰው ደግሞ ኤሳውን ይመስላል። ኤሳው ብኩርናውንና በረከቱን ሁሉ ከአጣ በኋላ ወደ አባቱ ገብቶ በረከቱን ታናሽ ወንድሙ እንደ ወሰደበት ባወቀ ጊዜ “ታላቅ፣ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ። ቃሉንም አንሥቶ አለቀሰ።” ዘፍ. ፳፯፥፴፬-፴፰ ፬. ልብን አለማደንደን፣
፭. መሰናክሎችና የኃጢአት ምንጮችን ማስወገድ፣
፮. ለኃጢአት ጊዜ አለመስጠት፣
፯. ጠባይን መመርመር:- ከድብቅ ኃጥያቶች መጠንቀቅ፣
፰. ከሚወዱት ኃጢአት በመሸሽ ደካማ ጎንን ማረም፣
፱, ዘለዓለማዊውን ሕይወትና የሚጠበቅብንን ማሰብ፣
፲. የኃጢአትን ፍቅር ለማስወገድ ፍቅረ እግዚአብሔርን ማጽናት፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ወደ ንስሐ በሚወስደው የሕይወት ጎዳና ላይ ማንኛውም ሰው ሊከተላቸው የሚገቡ መርሖዎች ናቸው። ዋቢ መጽሐፍ:- የንስሐ ሕይወት (ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ወንድምአገኘሁ)

ቅድስት አርሴማ ድንግል

እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና “የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ  ይታያል:: ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት:: ቅድስት አርሴማ “ይሕ ቀረሽ” የማይሏት ውብ ናት:: ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት:: ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት:: ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት።

ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:- አበው በትውፊት እንደነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ታላቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1)ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት፣
2)ትምህርተ ቤተክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት፣
3)የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር:: ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ)ን ጻድቃን የምንላቸው:: በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ 127 ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለመኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ (ዘአርመንያ) ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ:: በዚያም በድርጣድስ ቤተመንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው:: ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ “ካላገባሁሽ” አላት:: ድንግሊቱ ግን “እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም” አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው:: አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት:: ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን አደረገ:: የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራዕይ “ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን።” “ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም” አላቸው:: ወዲያውም  ቆፍረው አወጡት:: ቅዱሱ እንደወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን
አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሔዶ ፈወሳቸው::
የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ሃገራችን እንደመጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ / ኩላማሶ/ስባ/ውስጥ የሚገኘው) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና:: ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት “በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::”

የኤርትራው አዲሱ የፓትርያርክ ምርጫና ፈተናዎቹ

ከፍተኛ የሃይማኖት ነፃነት ችግር አለባት ተብላ በምትታማው ኤርትራ ውስጥ ፈቃድ ከተሰጣቸው አራት የእምነት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነችው የኤርትራ ቤተክርስቲያን በኅዳር ፴/፳፻፲፯ ዓ. ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን ፮ኛው ፓትርያርክ አድርጋ መርጣለች።

በዚህ ምርጫ ላይ 85 የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ጨምሮ የየገዳማቱ ተወካዮች፣ የአኅጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የነገረ መለኮት ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል። በምርጫው ላይ በብፁዕ አቡነ ዳንኤል የማዲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሚመራ 5 የግብፅ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተገኙ ሲሆን በምርጫው ላይ ከቀረቡት ዕጩ ፓትርያርኮች ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ: ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ: የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ: የደቡብ መንደፍራ ሊቀጳጳስ መካከል ብፁዕ አቡነ ባስሎዮስ ፮ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመርጠዋል።

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ጀምሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠልና በሁለቱ ሀገራት መካል በተከሰተ ግንኙነት መሻከር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተነጥላ እስከ ፲፱፻፺፩ በግብፅ ቤተክርስቲያን ሥር የነበረች ሲሆን ከ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዕውቅና በአፍሪካ ምድር ሦስተኛዋ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንበረ ፓትርያርክ ሆናለች። የቤተክርስቲያኒቱ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ፊሊጶስ ከ፲፱፻፺፩ ጀምሮ ለሁለት ዓመት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ለ 2 ዓመት በፓትርያርክነት መርተው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ ሲሆን ሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ከተሾሙ ሁለት ዓመት በኋላ በሀገሪቱ መንግስት ጫና ከፕትርክና እንዲነሱ ተደርገዋል።
የኤርትራ ቅዱስ ሲኖዶስ ዘግየት ብሎም በቅዱስነታቸው ላይ ያስተላለፈው ውግዘት ቤተክርስቲያንን ለሁለት የከፈለ ሲሆን በርካታ በአሜሪካ፣ አውሮፓና፣ አውስትራሊያ የሚገኙ ጳጳሳት፣ ማኀበረ ካህናትና ምዕ
እመናን ውግዘቱን በመቃወም ከእርሳቸው በኋላ የተነሱትን ሁለት ፓትርያርኮች ማለትም ለ፯ ዓመታት ቤተክርስቲያኗን ለመሯት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና በተሾሙ በዓመታቸው ላረፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ዕውቅና ሳይሰጡ ቀርተዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ውግዘት፣ የ፰ ዓመታት ግዞትና ፖለቲካዊ የቁም እስር የኤርትራ ቤተክርስቲያንን ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ መገለልና ጫና በማምጣቱ ምክንያት ቤተክርስቲያኒቷ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለ ፓትርያርክ በዓቃቤ መንበር እየተመራች ግንኙነቷን ማደስ ላይ ትኩረቷን ስታደርግ ቆይታለች።

እኒሁ በዲያስፖራው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አኅጉረ ስብከቶች ከ፮ኛው የፓትርያርክ ምርጫ ቀደም ብሎ ባወጡት መግለጫ በ፳፻፲፭ ዓ.ም. ያረፉት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አትናቴዎስ ውግዘት ባልተነሳበትና ዕርቀ ሰላም ባልተከናወነበት የሚካሄደውን ምርጫ እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል። የ፮ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሲመት በጥር ፲፰/፳፻፲፯ በታላቁ የአስመራ ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ይካሄዳል። የብጹዕ አቡነ ባስሊዮስን መመረጥ በታህሳስ ፪ ሳምንታዊ የረቡዕ ትምህርት ታላቅ ስኬት ብለው የጠሩት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ታዎድሮስ የኤርትራ ቤተክርስቲያን ለተልዕኮዋ፣ ለአንድነቷና ለክርስቶስ ክብር እንድትተጋ ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክም ለመላው የኤርትራ የካህናትና ምእመናን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላፈዋል።

ምጽዋትን መስጠት

ምጽዋት ማለት ስጦታ፣ችሮታ፣ ልግስና ማለት ነው፡፡ ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያዩትን ችግር በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት ከፍጹም ፈቃድና ርኅራኄ የሚያደርጉት ስጦታ ምጽዋት ይባላል፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ ፻፳፭-፻፳፯ እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ ከተቀባዮች ጋር ሆኖ የሚቀበል በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር፣ ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው “ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው። ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው። (ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)፡ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም “ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” ይላል። (ምሳ፲፱÷፲፯) ምጽዋት ብልሆች ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ ያልተማሩትን በዕውቀት የሞያ እርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሞያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ፣ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡ ”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ድሀ፣ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ” (ዘዳ ፲፭÷፲፩) “ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው፤ እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ ካንተ ጋር ይኑር” (ዘሌ፳፭÷፴፭)

ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡ “……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፣ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን? (ኢሳ፶፯÷፯) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ“ ይላል (ሉቃ፫÷፲፩)፡፡ ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው (ሉቃ፳፩÷፩-፬) ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው፣ ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡

ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል፣ በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ በችግራቸው በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ እሱ በተቸገረ ጊዜ በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዐቅቦ፣ ወያሐይዎ፣ ወያበፅዖ ዲበ ምድር። / ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል” ብሎ ጽፏል። (መዝ፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ። /  እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና” (መክ ፲፩÷፩) ብሏል። “እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል?” ልንል እንችላለን። “እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው!” ማለት ምጽዋትህን ለተቸገሩት፣ ለድሆች ስጥ ማለት ነው፡፡ “ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ” ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት፣ በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ፤ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል ምግብህን በከርሠ ርኁባን ፣ መጠጥህን በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው (ዘዳ፲፭፥፯)

ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡ በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ፣ ተግሣጽ፣ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡ “እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ፣ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ። /  ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም፤ ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና“ይላል። (መዝ፻፰÷፲፭)

“ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡ ለሰው ማዘን፣ መራራት፣ ገንዘብ መስጠት፣ ከአምላክ ባሕርይ የሚገኝ ነውና። /  ወበምጽዋት ይትሜሰሎ ሰብእ ለፈጣሪሁ፤ እስመ ውሂበ ምፅዋት ወተሣህሎ እምነ ጠባይዕ አምላካዊ”።
“ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር ነው፡፡ከአምላክ ጋር የሚነግዷት ንግድ ናት፡፡ /  ወምጽዋትሰ ልቃሕ አምላካዊት ወይእቲ ካዕበ ተናግዶ አምላካዊት ማእምንት ርብሕት“። “ዳግመኛም ቍርባን ና፤ በከርሠ ነዳያን የምትቀርብ ናት። /  ወይእቲ ካዕበ ቍርባን ውክፍት በኀበ መቅደስ ነባቢት“ እንዳሉ። (፫ቱ፻)

ራሱን መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል፤ ወጥቶ ወርዶ ራሱን ይርዳ።
ቅዱሳን ሐዋርያትም “ገንዘብ እያለው ምጽዋት የሚቀበል ወዮለት” ብለዋል፡፡

“ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች። / ለእሳት ዘትነድድ ያጠፍኣ ማይ፤ ወከማሁ ምጽዋትኒ ታኀድግ ኃጢአተ” እንዳለደ። ሲራክ ፫÷፳፰
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ ብዙኀ ጊዜ፤ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ።  ብዙ ጊዜ ሰጠሁህ፤ ይበቃሃል አትበል፤ አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን? እንደራስህ አታየውምን?” ይላል፡፡

ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፡፡ ”ስጡ ይሰጣችኋል“ተብሏልና (ማቴ.፲፥፰፣ ፪ኛቆሮ. ፱፥፯—፲፪) በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር። የጌታን ትእዛዝ፣ ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል። (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭) ምጽዋትን በፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡ አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ“ እንዲሉ፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው“ (ያዕ፬÷፲፯) ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንድንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ፤ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም (፪ኛቆሮ፱÷፲፭)