ዕረፍቱ ለአቡነ ሀብተማርያም

📚ኅዳር 26

በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡

የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ ሀገሩ የራውዕይ በምትባል በስተምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው። በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበር። ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚህች ሀገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ እጅግ ሀብታም ነበር፤ ብዙ ንብረትም አለው። በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ፤ ይህችም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት፡፡

ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋኅነትን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ትዕግስትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን፡፡

አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያምም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል፤ በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግንባሩ አሸዋ እስኪነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል። ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር። ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ፡፡

ዓርባ ዓርባ፣ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ። ባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል፤ ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡

ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም ባስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱም ተገልጦ መጣ። ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያው ሁነው እያመሰገኑት ነበር። “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፡፡ በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ። ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና “ጽና ኃይልህን ላድሳት እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና። ተጋድሎህና ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ፡፡

  እነሆ አኔ በጎ ዋጋህን በዚህ ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ፤ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ። ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀምጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሄድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ” አለው፡፡

ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ “ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ ዕረፍት ልወስድህ ነው። እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና፤ አንዱ ስለ ድንግልናህ፣ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ፣ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኵስናህ፣ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ፣ አምስተኛው ስለ እኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥህ፣ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ፣ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ሰጠሁህ። እነዚህ ሰባቱ አክሊላትም ለእያንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው።

መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማጸኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ ዐምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ። ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሃን ልብስን ሥውር የሆነ መናን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡

  መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው “ወዳጃችን ሰላም ለአንተ ይሁን! ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን” አሉት፡፡ አባታችን  ሀብተ ማርያምም “በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ፤ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው” አለ፡፡

ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና “የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ” አለው፡፡

“መታሰቢያህን የሚያደርገውን፣ በስምህ ለቤተክርስቲያን መባዕ የሚሰጠውን፣ ስምህን የጠራውን ወደዚህች ሀገር አገባዋለሁ፤ ዓራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን እንደ አንድ ሺህ አደረግሁልህ፤ ይኸውም ከአንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆች መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃልኪዳን ሰጥቼሃለሁ፡፡

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋዋ ተለየች፤ ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት፡፡ በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር፤ 

ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ።

ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት



❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ በግእዝ ልሳን በእንግልጣር Mercurius በጽርዕ Ἅγιος Μερκούριος, በቅብጥ Ⲫⲓⲗⲟⲡⲁⲧⲏⲣ Ⲙⲉⲣⲕⲟⲩⲣⲓⲟⲥ; በሲርያክ: ܡܳܪܩܘ̇ܪܝܘ̇ܣ; ተብሎ ይጠራል። የተወለደው በምሥራቅ ታሕታይ እስያ በቀጶዶቅያ በአኹኗ ቱርከሰ በ224 ዓ.ም. ሲኾን ወላጆቹ ክርስቲያኖች ሲኾኑ ስሙን ፒሉፓዴር Philopater ብለውታል ትርጓሜውም በግሪክኛ “የአብ ወዳጅ” ማለት ነው። በመንፈሳዊ ትምህርት አጠንክረው አሳድገውታል።

❖ በ17 ዓመቱ የሮማን ሰራዊት ተቀላቀለ “ወተውህቦ ኀይል ዐቢይ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ወተሰምዐ ዜናሁ በኲሉ ወተለዐለ እምሰብአ ቤተ መንግሥት” ይላል። ታላቅ የድል አድራጊነት ኀይል እንደ ዳዊት ተሰጥቶት ዜናው በኹሉ ቦታ ሲሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችን ይልቅ ከፍ ከፍ ብሏል፤ በዚኽ ምክንያት ከ249-251 የሮማ መሪ በነበረው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘንድ በ17 ዓመቱ ባለሟልነት አግኝቷል፡፡

❖ ከዚያም በሮም ላይ የበርበር ሰዎች ተነሥተው የዳኬዎስን መንግሥት ሊወጉት መጡ፤ እጅግ ብዙዎችም ነበሩና ንጉሡ እጅግ ፈራ፤ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን በክርስቶስ ላይ ያለው እምነት የጸና ነበርና ንጉሡን “እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ አለውና አትፍራ” አለው፡፡

❖ “ወእምዝ ርእዮ ቅዱስ መርቆሬዎስ ለመልአከ እግዚአብሔር በውስተ ቀትል ወሰይፍ በሊኅ ውስተ እዴሁ” ይላል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በውጊያው ውስጥ የተሳለ የሚያበራ ሰይፍ በእጁ ይዞ ተገልጦለት ሰይፉን በመስጠት “ጠላቶችኽን ድል ባደረግኽ ጊዜ ፈጣሪኽ እግዚአብሔርን ዐስበው” ብሎ ሰጥቶታል፤ አንዱ ራሱ ለውጊያ የያዘው ሰይፍ ኹለተኛም ከመልአኩ የተቀበለው ሰይፍ ነበርና በዚኽ ምክንያት “አበ አስይፍት” (የሰይፎች አባት፤ Abu-Seifein) በዐረብኛ Abu-Sayfain, Abu-Sifin ወይም أبو سيفين, በቅብጥ ⲁⲃⲩⲥⲉⲫⲁⲓⲛ ሲኾን በኹሉም ፍቺው ተመሳሳይ ነው።

❖ ከዚኽ በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ ለጣዖታት ዕጣን ሊያቀርብና በዓልን ሊያደርግ ወደዶ በዓልን ባደረገ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን ከርሱ ጋር አልወጣም፤ በዚኽ ምክንያት ንጉሡ አስጠርቶት “ለአማልክት ዕጣን ለማሳረግ ከእኔ ጋር ያልወጣኽ የእኔንስ ፍቅር ለምን ተውኽ?” ብሎ ጠየቀው፤ በዚኽ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ በንጉሡ ፊት ትጥቁንና ልብሱን ወርውሮ “እኔ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም” በማለት መለሰለት፡፡

❖ ንጉሡም እጅግ ተቈጥቶ ርጥብ በኾኑ የሽመል በትሮችና እንዲደበደብና ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ እንዲገረፍ አዘዘ፡፡ ይህንን ሁሉ በክርስቶስ ስም ተቀበለ።

❖ ከመሬት ከፍ ከፍ ያሉ ሁለት ምሰሶ ላይ እንዲታሰር አደረጉት። በችንካር ቸንክረው ገላውን በስል ምላጮች ቆራርጠውታል። ከዚያም ወደ እስር ቤት ቢከቱትም በወኅኒ ቤት ሳለ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾ ሰውነቱን በዳሰሰው ጊዜ ተፈውሷል።

❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ ካለው ተወዳጅነት የተነሣ ሰዎች እንዳይነሡበት በመፍራት የቀጶዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ኾነች ወደ ቂሳርያ በብረት ማሠሪያ ታሥሮ እንዲላክ አድርጎ በዚያም ብዙዎች ሥቃያትን አደረሱበት።

❖ ከዚያም አንገቱ እንዲቆረጥ ሲወሰን እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቶ መጸለይ ጀመረ። አምላካችን ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በታላቅ ግርማ ተገለጸለትና “የተወደድክ ልጄ መርቆሬዎስ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍትህ ከቅዱሳን ጋር ና፤ ጸሎትህ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን ወደ እኔ ዐረገ፤ የአንተን ስም በያዘ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ተአምር ይደረጋል፤ በአንተ ምልጃ የሚማጸኑኝን እጠብቃቸዋለሁ፤ የአንተን ዜና ገድል የሚጽፉትን የሚያነቡትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እጽፈዋለሁ” ብሎ ቃል ኪዳንን ገባለት።

❖ ከዚህ በኋላ ጌታችን ቅዱስ መርቆሬዎስን ባረከው፤ ያን ጊዜ በጣም ተደሰተና አንገቱን እንዲቆርጡ የታዘዙት ጋር በፍጥነት ሄዶ ከንጉሡ የታዘዙትን ፈጥነው እንዲፈጽሙ ለመናቸው። ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጸለየላቸው። ከዚያም በተወለደ በ25 ዓመቱ በኅዳር 25 ቀን በ250 ዓ.ም. ራሱን በተሳለ ሰይፍ ቈርጠውት በክርስቶስ ስም የሰማዕትነትን የክብር አክሊል ተቀዳጀ፤ የሰማዕታት ዘመን ካለፈም በኋላ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውለታልና፡፡

❖ ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈጣን ተራዳኢነቱ የሚታወቅ ሲኾን ከሓዲው ዑልያኖስ ታላላቆች ሊቃውንት የነበሩትን ቅዱስ ባስልዮስንና ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሊገድላቸው በመጣ ጊዜ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ቆመው ቢማፀኑ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያና ሰጲራን በሞት እንደቀጣ፤ ቅዱስ ጳውሎስ የበርያሱስን ዐይን እንዳጨለመ፤ ዳዊት ጎልያድን በእግዚአብሔር ስም እንደጣለው ቅዱስ መርቆሬዎስም በተራዳኢነቱ እንደ ጎልያድ የታበየውን ክርስቶስን የካደው ከ361 – 363 ድረስ የመራውን ዑልያኖስን (Julian the Apostate) በረቀቀ ጦር ወግቶታል።

❖ በደብረ ምጥማቅ እመቤታችን ትገለጥ በነበረ ጊዜ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከቅዱስ ቴዎድሮስ በመቀጠል ይመጣ የነበረው ቅዱስ መርቆሬዎስ ነበር።

❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አርከ ሥሉስም የቅዱስ መርቆሬዎስን ተጋድሎ በማዘከር፡-
“ሰላም ለከ መርቆሬዎስ ዘሮም
መስተጽዕነ ፈረስ ጸሊም
አመ አንደዱ ታሕቴከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍሕም”

(በጥቊር ፈረስ ላይ የተቀመጥኽ የሮም ሰው ለኾንኸው ለመርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባኻል፤ የመርገም ልጆች ከሥርኽ እሳትን ባነደዱ ጊዜ ከተገረፈው ሰውነትኽ በብዙ ዝናብ አምሳል የፈሰሰው ደም ፍሙን አጠፋው) እያለ መስክሮለታል፡፡

❖ ሊቁም በአድናቆት በመሆን፦
“ሮማዊ ግሩም
በመንፈስ ቅዱስ ሕቱም
መዐዛ ቅዳሴከ ጥዑም ከመ ጽጌ ገዳም
ነዓ ነዓ ማዕከሌነ ቁም
በበዓልከ ትባርከነ ዮም”
(ግሩም ሮማዊ በመንፈስ ቅዱስ የታተምክ፤ እንደ ምድረበዳ አበባ የምስጋናህ መዐዛ የጣፈጠ መርቆሬዎስ በበዓልህ ዛሬ ትባርከን ዘንድ ና ና በመካከላችንም ቁም) ይለዋል።

❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፦

“ሰላም ለመርቆሬዎስ ሰማዕት ንጹሕ ድንግል
ፈጻሜ ቃለ ወንጌል”፡፡
(የወንጌል ቃል የፈጸመ ለኾነ ለንጹሕ ድንግል ሰማዕት መርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሶታል፨

[የቅዱስ መርቆሬዎስ በረከት ይደርብን፤ እናንተም በአስተያየት መስጫው ላይ በረከቱ እንዲያድርባችሁ ቅዱስ መርቆሬዎስን አወድሱት]


✍ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ኅዳር 12- የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ የንግሥ በዓል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባሉ በየትኞቹ ገዳማትና አድባራት ይከበራል?

1) ኮልፌ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ

ልዩ ስም፡-ኮ/ቀ/ክ/ከ ዊንጌት ጠሮ አራት መንታ

2)የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ገዳም

ልዩ ስም፡-ኮ/ቀ/ክ/ከ ልኳንዳ ፈጥኖ ደራሸ ካምፕ

3)ማኅደረ መለኮት ወይብላ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፡-ኮ/ቀ/ክ/ከ የሺ ደበሌ

4)በደብረ መድኃኒት አቡነ ሃብተማርያም ወቅድስት ልደት ወቅድስት አርሴማ ገዳም

ልዩ ስም፦ኮ/ቅ/ክ/ከ አስኮ ካኦጄጄ ዱቄት ፋብሪካ ከፍ ብሎ ቃሌ ተራራ ላይ ነው፡፡

5)ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦አዲስ ከተማ/ክ/ከ አውቶብስ ተራ

6)ቤተል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ኮ/ቅ/ክ/ከ ቤተል

7)የካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ሾላ መገናኛ

8)ጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትና ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ልደታ ክ/ከ ጎላ

9)ኮተቤ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ሉቄ

10)ደብረሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቂርቆስ /ክ/ከ መስቀል አደባባይ

11)ምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤልና 24ቱ ካህናተ ሰማያት ወቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ አባዶ

12)የረር በር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እና ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ጎሮ

13)ቦሌ ኆህተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ቦሌ ክ/ከ ገርጂ

14)ኮተቤ ደብረ ልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ቅድስት ኪዳነምህረት እና አቡነ ሀብተማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ኮተቤ ካራ

15)ሲኤምሲ ደብረ ጽባህ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ሲኤምሲ

16)አንቀፀ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ራስ ካሳ

17)መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ወቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ 6ኪሎ

18)ጉራራ ምስራቀ ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦የካ ክ/ከ ፈረንሳይ ጉራራ

19)መንበረ ክብር ቅዱስ ሚካኤል፤ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ቅድስት አርሴማ ገዳም

ልዩ ስም፦ጉለሌ /ክ/ከ ቀጨኔ

20)ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና መካነ ጎልጎታ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አራዳ ክ/ከ አረበኞች መንገድ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል

21)ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጎፋ

22)አፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ልዩ ስም፦ቂርቆስ ክ/ከ አፍሪካ ኅብረት

23)ረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ካቴድራል

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 2 ካራ ቆሬ

24)ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ልደታ /ክ/ከ ልደታ

25)ፉሪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ጋራ ኦዳ

26)መካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መካኒሳ
27)ላፍቶ ደብረ ትጉሃን ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ላፍቶ

28)ሐመረወርቅ ቅድስት ማርያም እና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ወረዳ 5 ወርቁ ሰፈር

29)ደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ቤተል

30)ቶታል ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ

ልዩ ስም፦ኮ/ቀ/ክ/ከ ሰፈረ ገነት

31)ፉሪ መካነ ቅዱሳን አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ እና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 1 ለቡ(ፉሪ)

32)አቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከ ጋራው መድኃኔዓለም

33)ቃሊቲ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል እና ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ/ክ/ከ ሰፈረ ገነት

34)ቂሊንጦ መካነፍስሐ ቅዱስ ሚካኤል እና በዓታ ለማርያም ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ/ክ/ከ ቂሊንጦ አደባባይ

35)ቱሉ ዲምቱ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ

ልዩ ስም፦ አቃቂ ቃሊቲ/ክ/ከ አቃቂ ኬላ ዝቅ ብሎ

36)ሣሎ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

ልዩ ስም፦አቃቂ ቃሊቲ /ክ/ከሣሎ

37) ቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል እና ፃድቁ አቡነ ጎርጎርዮስ ቤተክርስቲያን

ልዩ ስም:- ቦሌ ሚካኤል

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ

ወንጌላዊው ቅዱስ_ሉቃስ፦ ይህም ቅዱስ የከበረ ወንጌል ከመዘገባቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው። እርሱም ወንጌልን ስለማስተማር በሥራው ሀሉ ሐዋርያት ጴጥሮስንና ጳውሎስን የሚያገለግላቸው ሆነ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈ ሉቃስ ነው።

ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስም ከተገደሉ በኋላ በሮሜ ሀገር የሚያስተምር ሆነ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር። ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት አንድ ግምባር ፈጠሩ። በንጉሥ ኔሮን ፊት ቁመው ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ጮኹ “ይህ ሉቃስ ብዙዎች ሰዎችን በሥራው ወደ ትምህርቱ አስገባቸው”። ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ አደባባይ ሉቃስን እንዲይቀርቡት አዘዘ።

ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስም ከዚህ ዓለም መውጫው እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ። በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘ። መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎቹን ሰጠው “ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሃልና” እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው አለው።

በንጉሥ ኔሮንም ፊት ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ “በሥራህ ሕዝቡን የምታስት እስከመቼ ነው” አለው ቅዱስ ሉቃስም ” እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም” ብሎ መለሰለት።

ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው “እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይቺን እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ” ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡ አዘዘ በቆረጡትም ጊዜ “ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ እወቅ ነገር ግን የጌታዬንና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ”። ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት። ከዚህም በኋላ ለያት በዚያም የነበሩ አደነቁ የሠራዊት አለቃውና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ቁጥራቸውም አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሉቃስን ሥጋ በማቅ አይበት አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ። ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት በአማረ ቦታም አኖሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የጥቅምት 22 ስንክሳር

የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ “ይኩን ሰላም በኃይልከ። ወትፍሥሕት ውስተ ማኅደረ ክበዲከ። በእንተ አኀውየ ወቢጽየ። መዝ 121፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-።

የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ “አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ”። መዝ 18፥3-4።

የሚነበቡት መልዕክታት የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቈላ 4፥12-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 1፥4-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥1-6። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥1-5። የሚቀደሰውም የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው።

መልካም የወንጌላዊው የቅዱስ ሉቃስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

ትሑትና ትዕግስተኛው አባት፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር


አባ ዮሐንስ ሐፂር፦ የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ከላይኛው ግብጽ ናቸው እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው ግን ከእርሱ በቀር ልጅ የላቸውም የዚህ ዓለምም ብልጽግና ቢሆን የላቸውም ነገር ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው። ይህንንም ቅዱስ እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት።


የዚህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥታው የመላእክት የሆነ አስኬማን ይለብስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ይኸውም የምንኵስና ልብስ ነው። ከዚያም በደረሰ ጊዜ አባ ባይሞይ የሚባለውን አንዱን አረጋዊ አባት ተገናኘው ዮሐንስም ሰገደለትና ወደ እርሱ እንዲቀበለው ለመነው ሽማግሌውም አባት “ልጄ ሆይ ያንተ በዚህ መኖር ልክ አይደለም በዚች ገዳም የሚኖሩ በእጆቻቸው ይሠራሉ በቀንና በሌሊት ይጾማሉ ይጸልያሉ በሚተኙም ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ ይተኛሉ አንተ ወጣት ጎልማሳ ስለሆንክ ይህን ሁሉ ችግር አትችልም። ነገር ግን ወደ ዓለም ተመልሰህ እንደ ሰው ሁሉ በጎ አኗኗርን ትኖር ዘንድ ይሻልሃል የዚች ገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና” አለው።
አባ ዮሐንስም እንዲህ አለው እኔ በጥላህ ሥር ልኖር መጥቼአለሁና ስለ እግዚአብሔር ብለህ ተቀበለኝ እንጂ አትመልሰኝ ይህም አባ ባይሞይ እግዚአብሔርን ሳይጠይቅ ምንም ሥራ አይሠራምና በዚያን ጊዜ ሥራውን ይገልጥለት ዘንድ ስለ ዮሐንስ ሐፂር እግዚአብሔርን ለመነው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት “እርሱ የተመረጠ መሳሪያ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል” አለው።


ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ሐፂርን ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባው የምንኵስና ልብሶችንም አምጥቶ በላያቸው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጸለየ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ በመስቀል ምልክት በልብሶቹ ላይ አማተበ ሽማግሌውም እነዚያን ልብሶች ለአባ ዮሐንስ አለበሰው።


ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ተጋድሎንና አገልግሎትን ጀመረ አባ ባይሞይም ሊፈትነው ወደደ በአንዲትም ቀን ደብድቦ “ከአንተ ጋር መኖር አልሻም” ብሎ ከበዓቱ አስወጥቶ አባረረው የከበረ አባ ዮሐንስም ከሜዳ መካከል በውጭ ቆመ በየቀኑም በጥዋት እየወጣ “ከእዚህ ላይህ አልሻም” እያለ ይመታዋል እርሱ ግን “አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ” ብሎ ከእግሩ በታች ይሰግዳል። በሰባተኛዪቱም ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሔድ ሽማግሌው አባ ባይሞይ ወጣ አባ ዮሐንስንም ሰባት መላእክት ከበው አክሊላትን ሲያቀዳጁት አያቸው ከዚያንም ጊዜ ወዲህ መፈተኑን ተወው ወደ መኖሪያውም አስገባው።


ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ ዕንጨት አግኝቶ ወስዶ ለአባ ዮሐንስ ሰጠውና “ይህን ዕንጨት ትከለው እስከሚበቅልና እስከሚያፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው” አለው። አባ ዮሐንስም ለአባቱ ታዛዥ በመሆን ተቀብሎ ወስዶ ተከለው በየቀኑም ሁለት ሁለት ጊዜ ያጠጣዋል ውኃውም ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል የራቀ ነው። ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ ታላቅም ዛፍ ሁኖ አብቦ ጣፋጭ ፍሬን አፈራ። አባ ባይሞይም ከፍሬው ለቅዱሳን አረጋውያን ወሰደላቸውና “የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ” አላቸው እነርሱም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው አደነቁ ለመምህሮቻቸው ለሚታዘዙ እንዲህ ያለ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።


አባ ባይሞይም ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል በጽኑዕ ደዌ ውስጥ ተይዞ ኖረ አባ ዮሐንስም ያገለግለው ነበር አባ ዮሐንስን እንደፈተነው የተመረጠ መሥዋዕትን ይሆን ዘንድ በዚህ ደዌ እንዲፈተን እግዚአብሔር ፈቅዷልና። በሚሞትበትም ጊዜ አባ ባይሞይ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትን ሰበሰባቸውና አባ ዮሐንስንም እጁን ይዞ “እርሱ ሰው ያይደለ መልአክ ነውና ተቀብላችሁ ጠብቁት” ብሎ ሰጣቸው። እርሱንም ደግሞ እንዲህ አለው “ከዕረፍቴ በኋላ ያን ዕንጨት ወደ ተከልክበት ቦታ ሂድና በዚያ ኑር እግዚአብሔር ላንተ ያዘጋጀልህ ነውና ብዙዎችም በአንተ እጅ ይድናሉ መታሰቢያህም በዚያ ጸንቶ ይኖራል ዜናህም በዓለም ሁሉ ይወጣል” ይህንንም ተናግሮ ዐረፈ አክብረውም ቀበሩት።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባ ዮሐንስ አረጋዊ አባቱ አባ ባይሞይ እንደነገረው ወደዚያ ቦታ ሔዶ ኖረ ዜናውም በዓለም ሁሉ እጅግ እስከ ተሰማ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። በራሱ ቤተ ክርስቲያንም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ በሹመቱም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ እጆቹን በራሱ ላይ ሲጭን “አክዮስ አክዮስ አክዮስ” የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ ይህም “ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል” ማለት ነው። የቊርባን ቅዳሴን በሚቀድስ ጊዜ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል የማይገባቸውን ይለያቸዋል “ዛሬስ ሔዳችሁ ንስሓ ግቡ ከዚያም በኋላ ተመልሳችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ” ይላቸዋል።


ይህን አባ ዮሐንስንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲያመጣለት ወደ ባቢሎን ልኮታል ይህም በግንቦት ወር በዐሥረኛው ቀን ተጽፎአል።


በአንዲትም ዕለት አንድ መነኰስ ሊጎበኘው ወደ በዓቱ ቢመጣ አባ ዮሐንስን ተኝቶ አገኘው የእግዚአብሔርም መላእክት በላዩ ይጋፉ ክንፎቻቸውንም ያርገበግቡ ነበር አንዱም ሌላውን “ተወኝ ክንፌን በላዩ ላኑር ይለዋል” ይህንንም አይቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ።
ከዚህም በኋላ የመነኰሳቱን መንደር ሊበረብሩ የበርበር አረማውያን ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ አባ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሔደ በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም በጎኑ ባለ ቦታ ተቀመጠ እስከ ሚያርፍባትም ቀን ድረስ የሚያገለግለው አንድ የታመነ ሰውን እግዚአብሔር አመጣለት።


ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊያሳርፈው በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱሳን ጻድቃኖቹን አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኵሚስን ከእርሳቸውም ጋር መንፈሳዊ አባቱ አባ ባይሞይን ያረጋጉትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መለየቱን ይነግሩት ዘንድ ወደርሱ ላካቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው አረጋጉት “ደስ ይበልህ እግዚአብሔር የማያልቅ ተድላ ደስታን አዘጋጅቶልሃልና” ክብር ይግባውና ጌታችንም እንዳዘዘ “በእሑድ ቀን ሁለተኛ ወዳንተ መጥተን ወደ ዘላለም ሕይወት እንወስድሀለን” አሉት። ባርከውትም ከእርሱ ዘንድ ተመለሱ።


በዐርብ ቀንም አገልጋዩን ወደ አንድ ቦታ ላከው ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ በእሑድም ቀን ሌሊት ዶሮ ሲጮህ እነዚያ ቅዱሳን ከሁሉም ቅዱሳን ማኅበር ጋር መጡ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ ወደርሱ መጡ ባያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ መላእክትም እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳረጓት በዚያንም ጊዜ ረድኡ መጣ ነፍሱንም ከበው እያመሰገኑ ሲያሳርጓት የጻድቃንና የመላእክትን ማኅበር አይቶ እያደነቀ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ። ከመላእክትም አንዱ ወደርሱ መጥቶ የቅዱሳንን ስማቸውን በመጥራት በጣቱ እያመለከተ ይህ አባ ዕገሌ ነው ብሎ አስረዳው ረድኡም መልአኩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው “ይህ በፊታቸው ያለ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚበራ ማን?” ነው መልአኩም “የመነኰሳቱ ሁሉ አባት አባ እንጦንስ ነው” ብሎ መለሰለት።


ወደ በዓቱም ያ ረድእ በገባ ጊዜ በምድር ላይ ሰግዶ እንዳረፈ አባ ዮሐንስን አገኘውና ታላቅ ልቅሶን በላዩ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወደ መነኰሳቱ መንደር ፈጥኖ በመሔድ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐፂር እንደ ዐረፈ ነገራቸው። እነዚያም መነኰሳት አክብረው ገንዘው ሥጋውን ተሸክመው ወስደው በቦታቸው አኖሩት። የደረቀ ዕንጨት ተክሎ በአበቀለበት ላይ በሠራት የራሱ በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልጆቹ ከዚህ አፍልሰው ወስደው እስከ አኖሩት ድረስ በዚያ ኖረ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


“ሰላም ለዮሐንስ ሐጺር ትሩፈ ምግባር፤ ዘአጥረየ ትሕትና ወወረሰ ልዕልና”። ትርጉም፦ ትሕትናን ገንዘብ አድርጎ ልዕልናን የወረሰ መልካም ሥራው የበዛ ለኾነ ለዮሐንስ ሐጺር ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ

እስጢፋኖስ ማለት “መደብ” ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ “አክሊል” ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከነቢያትና ከጻድቃን ወገን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ወንድ ልጆችን ወለዱ፡፡ አንዱ ይሁዳ ሲባል ሁለተኛውም ቅዱስ እስጢፋኖስ (አስተፓኖስ) ነው፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወለደው ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለች ቦታ ነው፡፡ የተወለደውም በስዕለት ነው፡፡ እርሱም ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመሄድ ይላላካቸውና ያገለግላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙት ከ7ቱ ዲያቆናት አንዱ ሲሆን የዲያቆናት አለቃ እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማስተማሩና ብዙዎችን ክርስቶስን ወደማመን ስለመለሳቸው ክፉዎች አይሁድ በጠላትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ከጌታችን ቀጥሎ ከምእመናን ወገን የመከራውን ገፈት ስለተቀበለ (በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ስላረፈ) “ቀዳሜ ሰማዕት” ተሰኘ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ” እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ የተሰጠው ስያሜ ነው።


የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የአማኞች ቊጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሄደ ጊዜ የማኅበራዊው ኑሮ አስተዳደር ማለትም የምግብንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች (ገንዘብም ጭምሮ) በትክክልና በእኩልነት የማከፋፈሉ ሥራ በሐዋርያት ዘንድ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ እነርሱም ደግሞ ዋና ተግባር አድርገው በትጋት ለመያዝ የፈለጉት ማስተማርን ነበር፡፡ ስለዚህም አማኞችን ሁሉ ሰብስበው ከመካከላቸው በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን እንዲመርጡ አሳስቧቸው፡፡ አማኞችንም ነገሩ አስደስቷቸው ሰባት ሰዎችን መረጡ፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ (ዕረፍቱ ጥር 1)፣ ቅዱስ ጵሮኮሮስ (ሰኔ 8)፣ ቅዱስ ጢሞና (ሚያዝያ 16)፣ ቅዱስ ፊልጶስ (ጥቅምት 14)፣ ቅዱስ ጰርሜና (መስከረም 1)፣ ቅዱስ ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሣ)፣ ቅዱስ ኒቆላዎስ (ሚያዝያ 15) ናቸው፡፡ ሐዋ 6፡5፡፡


እነዚህንም ቅዱሳን በከበሩ ሐዋርያት ፊት ባቆሟቸው ጊዜ ጸልየው እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው ከባድ ሸክም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ደሀ አደጎች በመርዳት ችግሮቻቸውን አቃለሉላቸው፡፡በከበሩ ሐዋርያት ከተመረጡት ሰባቱ ዲያቆናት መካከል ሊቀ ዲያቆናት ተደረጎ የተመረጠው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ሌሎቹም ዲያቆናት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወንጌልን በማስተማርና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በማስተዳደር በጽናት ተጋድለዋል፡፡ እነዚህም ሰባቱ ዲያቆናት ከአባቶቻቸው ከከበሩ ሐዋርያት አይተው የእነርሱንም መንፈስ ተቀብለው ያልተማሩ አህዛብን ልቡናቸውን ለመስበርና የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡

ከእነርሱም ውስጥ በዋነኛነት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ “ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ ነገሩ ሐሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ” በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡

ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትእምርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡


የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በትምህርቱና በተአምራቱ ብዙዎችን ወደቀናች ሃይማኖት ስለመለሰ ክፉዎች አይሁድ ቀኑበትና የሐሰት ምስክር አዘጋጁበት፡፡ “በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው በሐሰት ከሰሱትና በሸንጎአቸው አቆሙት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ያለውን ሁሉንም እየጠቀሰ የሃይማኖትን ነገር አስተማራቸው፡፡ ነቢያትን ስለማሳደዳቸውና ስለመግደላቸው እየወቀሰ ሲናገራቸው በትምህርቱ ተናደው ጆሮአቸውን ይዘው በመጮህ በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ዘንድ እየጎተቱ ከከተማው ውጭ አወጡት፡፡


ቅዱሱም በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ከጌታችን የተማረውን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እያለ ስለ ገዳዮቹ ምሕረትን ይለምን ነበር፡፡ ሰማይም ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ክብር ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይኸውም የቀድሞው ሳውል ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅና ድንጋይ ያቀብል ነበር፡፡ “የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ” ብሎ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ሐዋ 22፥20፡፡


የቅዱስ እስጢፋኖስ መምህር የነበረው ምሑረ ኦሪቱ ገማልያልና ልጁ አቢብ በእስጢፋኖስ ትምህርትና የሞቱ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት አይተው ከይሁዲነት ተመልሰው በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ የነፃ አውጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡ በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት”፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥8-15፡፡

የአይሁድ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ያቀረቡት የክሳቸው ምክንያት ጌታችንን ከከሰሱት ክስ ጋር በሁለት ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው “የሙሴን ሕግ ሽሯል” የሚል ነው፡፡ “የሙሴን ሕግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም አታድንም፤ ሐዲስ ኪዳን (ወንጌል) ግን ትመግባለች ታድናለች” ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ የሐዋ ሥራ 6፥13፡፡ ሁለተኛው ክሳቸው “እግዚአብሔርንም ይሰድባል” የሚል ነው፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥50፡፡ አይሁድም የቅዱስ እስጢፋኖስን የወንጌል ቃል ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡ የኦሪት የካህናት አለቃውም ቅዱስ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ ዘንድ ሲጠይቀው እርሱ ግን ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በዝርዝር በሚገባ ተረከላቸው።
ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲህ አላቸው፡- “ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፏጩበት፡፡መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፡፡ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እስጢፋኖስም “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ይህንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ የሐዋ ሥራ 7፥52-60፡፡


ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለንጽሕናው ስለድንግልናው፣ ስለሰማዕትነቱ ስለተጋድሎው እና ስለስብከቱ ስለተአምራቱ ሦስቱ አክሊላት ተቀዳጅቷል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ አምላኩን ክርስቶስን በብዙ ነገር መስሏል፡፡ በመጨረሻዋ የመሞቻው ሰዓት ላይ እንኳን ሆኖ አምላኩን አብነት አድርጎ ተገኝቷል፡፡ ጌታችን “ነፍሴን ተቀበላት” እንዳለ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም “አቤቱ ጌታ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት” ብሏል፡፡ ጌታችን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ እስጢፋኖስም “ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና” በማለት ለገዳዩቹ ምሕረትን ለምኗል፡፡ በጌታችን ጸሎት እነ ፊያታዊ ዘየማንን ጨምሮ እልፍ ነፍሳት ወደ ንስሐ ተመልሰው ገነት መንግስተ ሰማያትን እንደወረሱ ሁሉ በቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት ብዙ ነፍሳት ድነው ገነት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡
የጌታችን ቅዱስ መስቀል እልፍ ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ እንደነበር ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስም ዐፅም ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡

የቅዱስ እስጢፋኖስ ልደቱና ዕረፍቱ ጥር 1 ቀን ነው፡፡ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በክብር ቀበሩት፡፡ ጥቅምት 17 የተሾመበት ነው፡፡ መስከረም 15 ቀን ፍልሰተ ሥጋው ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቅዱስ ዐፅሙ ሙትን ያስነሣ ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ በቅናት ተነሥተው እንደ ጌታችን ቅዱስ መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስን ዐፅም አርቀው በመቆፈር ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ኖሮ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ መስቀሉ ተቆፍሮ በመውጣት መስከረም 15 ቀን ቅዱስ ዐፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፡፡

ከቅዱስ እስጢፋኖስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!።

ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱስ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደና ከገድላት አንደበት።


“ሰላም ለእስጢፋኖስ እንተ ነጸረ በዐይኑ። እንዘ ወልድ ይነብር ለአብ ውስተ የማኑ። ከመ ኖትያዊ ጠቢብ ኃዳፌ ሐመር በኪኑ። ባሕረ መጻሕፍት አመ ጸበተት ልሳኑ። ተቃውሞቶ መዋግድ ስእኑ”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የጥቅምት 17።

ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ፦

እንኳን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአንዱ ለወንጌላዊ ለቅዱስ ማቴዎስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።


“ሰአሉ ለነ አርባዕቱ ወንጌላውያን መምህራን ሥዩማን አዕማዲሃ ለቤተ ክርስቲያን ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ”። ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያን ምሶሶዎች የምትኾኑ ሹማምንት መምህራን የምትኾኑ አራቱ ወንጌላውያን ለምኑልን ማልዱልን። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታቱ ላይ።


ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ፦ ይህም እንዲህ ነው በብዙ አገሮች ውስጥ አስተምሮ ብዙዎች ሰዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ከመለሰ በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድ አዘዘው። ተጒዞም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንድ ወጣት ብላቴና አገኘ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም እንዲህ ብሎ መለሰለት “አንተ ግን ራስህንና ጽሕምህን ካልተላጨህ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም”። ይህም ነገር ለሐዋርያ ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግመኛ በስሙ ጠራው። ሐዋርያውም “ወዴት ታውቀኛለህ” አለው እርሱም “እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ ከአንተም አልርቅም” አለው።


ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ ለአማልክት ካህናት አለቃቸው ከሆነ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው እንዲህም አላቸው። “ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ” በዚያንም ጊዜ ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አምነው አጠመቃቸው ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መገባቸው።
የሀገሩም ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት ጨመረው ጌታችንም አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ በሚያሠቃያቸው ነገር ሲያስብ እነሆ ልጁ እንደ ሞተ ነገሩት እጅግም አዘነ። ሐዋርያ ማቴዎስም “ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም” አለው ንጉሡም “የሞተ ማንሣት እንዴት አማልክት ይችላሉ” ብሎ መለሰ። ቅዱስ ማቴዎስም “ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅህን ማሥነሣት ይችላል” አለው። ንጉሡም “ልጄ ከተነሣ እኔ አምናለሁ” አለ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይገባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡን ልጅ ከሞት አስነሣው። ንጉሡም ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ የአገር ሰዎች ሁሉም አመኑ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ካህናትንም ሾመላቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ወንጌልን አስተማረ።

ከዚህም አስቀድሞ በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስን ሁል ጊዜ በየበዓላቸው ወደ እነርሱ ሲመጣ አየው ከእርሱም ጋር መቶ አርባ ሽህ ሕፃናት አሉ መላእክትም ሁሉ በዙሪያው ቁመው ያመሰግኑታል። በብሔረ ብፁዓን ስለ ሚኖሩ ወገኖችም ድንቅ ስለሆነ ሥራቸው ሁሉ ከሐዋርያው በኋላ ወደርሳቸው የገባ ዘሲማስ ቀሲስ ምስክር ሆነ።


ከዚህም በኋላ የሐዋርያው የተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቀርብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳመነ አገረ ገዢውም ይዞ ከወህኒ ቤት ጨመረው። በዚያም አንድ እጅግ የሚያዝን እሥረኛ አይቶ ስለኀዘኑ ጠየቀው እርሱም ብዙ የሆነ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሠጠመበት ነገረው ሐዋርያ ማቴዎስም “ወደ ዕገሌ ባሕር ዳርቻ ሒድ ወርቅን የተመላ ከረጢትንም ታገኛለህ ያንንም ወርቅ ወስደህ ለጌታህ ስጥ” አለው።


ስለዚህም ድንቅ ተአምር ብዙዎች ክብር ይግባወና በጌታችን አመኑ። መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ቅዱስ ማቴዎስንም ራሱን እንዲቆርጡ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው ቈረጡት ምእመናንም በሥውር መጥተው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የጥቅምት 12 ስንክሳር።

መስከረም ፳፩ (21)

እንኳን ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም (ለብዙኃን ማርያም)፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በግሸን በመስቀለኛው ተራራ ላይ ገብቶ ለተቀመጠበት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለመወሰን፤ በኒቅያ ጉባኤ አርዮስን ለማውገዝ ከሩቅ ለተሰባሰቡበት ቀን በሰላም አደረሰን።
የዕለቱ አንገርጋሪ ግእዝ፦ ሃሌ ሉያ “ዓይ ይእቲ ዛቲ መድኃኒት እንተ ኀሠሥዋ ወዖድዋ ነቢያት ወይቤሎ ለኖህ አመ አይህ ግበር ታቦተ በዘትድኅን እትአመን ባቲ እስመ አርአያ መስቀል ይእቲ አክሊለ ተቀጺላ ታንሶሱ። ትርጉም፦ ያች መድኃኒት ማን ናት ነቢያት የፈለጓት የዞርዋት በጥፋት ጊዜ ለኖህ አለው የምትድንበት ታቦት ሥራ በእርሷ አርአያ መስቀል ናትና እክሊል ተቀዳጅታ ትመላለሳለች።


የዕለቱ ዓራራይ ዜማ፦ “ሠለስቱ ምዕት ወሠርቱ ወሰመንቱ ኤጲስ ቆጶሳት ርቱዓነ ሃይማኖት እለ መሀሩ በስሙ በዕፀ መስቀሉ በውስተ ማኅበሮሙ ለቅዱሳን”። ትርጉም፦ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ኤጲስ ቆጶሳት ሃይማኖታቸው የቀና በስሙ በዕፀ መስቀሉ በቅዱሳን ማኅበር ያስተምሩ። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ።


ብዙኃን ማርያም፦ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል “ብዙኃን ማርያም” በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ለጉባኤ ኒቅያ ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤
ጉባዔ ኒቅያ፦ በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጥሯል፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ “አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!” የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡


በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለ ነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ ይገኙበታል፡፡


ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን “ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ” ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ (2348) መካከል ፫፻፲፰ (318) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው “ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው” ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም “ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን” ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡


፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት “ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን” የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት “ብዙኃን_ማርያም” እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡


ዕፀ መስቀል፦ በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤ ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው “የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል” አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር “የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ” የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡
ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡
መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ” የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ” ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ምየጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡ “መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!” ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


ምንጭ፦ ከማኅበረ ቅዱሳን ጽረ ገጽ የተወሰደ።

የአቡነ ሀብተ ማርያም ጽንሰት፦

አቡነ ሀብተ ማርያም

የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች። ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትዕግሥትና በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን። እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ “ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል ፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና”፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል” እንዳለ። ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል” የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣማዎች፣ ከጦጣዎችና ከዝንጆሮዎች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር። በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስላየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ። መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። “አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ” አላት። “ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን?። “ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም” አለችው። “ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር” አለችው።

ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ “በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ” ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም “ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ” አለችው። ጌታ “በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም” እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም” አለችው።


ያም ባሕታዊ “ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል”።


ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ “የፈጣሪዬ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ” አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለንተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሆኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ …ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው።

ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።

ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለሃይማኖት

አቡነ ተክለሃይማኖት


ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፦ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እኚህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ካበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ። በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ እቁባቶች ያደርጋቸዋል።


በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእነርሱም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ። ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደ መኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።


እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ “ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት” አለ። የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዚእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።


ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።


ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመንፈስ ቅዱስ ጸና።


ከዚህም በኋላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ “ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል” ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።


ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው “ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታስነሳ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ”። ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ “ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል” እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።


ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣዖት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።


ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።


ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር። ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።


ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጠምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።


በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።


በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው ።በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኰረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ስለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።


በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በኋላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስኪሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።


ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።


መድኃኒታችንም እንዲህ አለው “ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ”። አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ። ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።


ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና ነሐሴ 24 ቀን ዐረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።