አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በረሃ ገቡ::
በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::

ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ “አጥምቀው!” አለችው:: ወደ በረሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲልም ሕጻኑ ተነስቶ፣ እጆቹንም ዘርግቶ: “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕፃኑ ወላጆች “ለልጃችን ስም አውጣልን” ቢሉት “ቡላ” ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” ተብሎ እንደተጻፈ ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

 የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገዉት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነት የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾምና ሲጸልይ ክፉ መኮንን “ለጣዖት ስገዱ!” እያለ መጣ:: በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ሰማዕት ሆኗል::

ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና “እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል!” ሲል ጌታንን ለመነ:: ጌታችን ግን “ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ!” አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ፣ ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በረሃ ውስጥ አኖረው።

 አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል፣ ፊቱን በጥፊ ይመታል፣ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፣ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል:: በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጾሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር:: የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሣ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን!” አለው::አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎይን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተነጋገረ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከዐሥር ጊዜ በላይ ሞቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::

ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ “አምላከ አቢብ ማረኝ” ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ” ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::

የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን

የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ኀምሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት በሦስት ሺ ምእመናን በሀገረ ኢየሩሳሌም በ፴፬ ዓ.ም. ተመሠረተች:: ከዚያም ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ በመከፋፈል ተዘዋውረው አስተማሩ፡፡ አምልኮ ጣዖትን አጠፉ፡፡ ርኩሳን አጋንንትን አሳደዱ፡፡ በመስቀል ዕርፍ አርሰው፣ ንጹሕ ዘር ወንጌልን ዘርተው፣ በደማቸው አተሙ:: በእየሩሳሌም የጀመረችው ቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ለዚያች ከተማና በአካባቢው ብቻ የተገደበ ይመስል ነበር። በጽዮን ተራራ ላይ ያለው የላይኛው ክፍል እና በቤተመቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ይኖሩ ነበር። ከሐዋርያት ድንቅ ተአምራትና ከስብከታቸው የተነሣ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጨመሩ።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፡ ቀድሞውን በቁጥር ብዙ ያልሆኑ ክርስቲያኖች በሐዋርያት ይተዳደሩ ነበር። ኋላ ከግሪክ በመጡ ክርስቲያን አይሁዶችና በአረማይክ ተናጋሪ አይሁዶች መካከል አለመግባባት ተከሰተ። ከግሪክ ለመጡ ደቀ መዛሙርት ባልቴቶች ምግብን ሲያካፍሉ ችላ ይሏቸው እንደነበር ስሞታ አቀረቡ። ሐዋርያትም ሲሰሙ ሕዝቡን ጠርተው እንዲህ ያሉ ነገሮችን ይፈጽሙ ዘንድ እንዳልተጠሩ ተናግረው ይልቁን አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ይሥሩ ብለው፣ መሪዎች እንዲሆኗቸው ሰባት ዲያቆናትን ሾሙሏቸው። እኒኽም ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ፊልጶስ፣ ጵሮኮሮስ፣ ኒቃሮና፣ጢሞና፣ጰርሜናና ተመልሶ ይሁዲ የሆነው ኒቆላዎስ ናቸው። የሐዋ ፮፥፩ ልዩ ሥራቸው ባል ለሞቱባቸው እና ለድሆች እርዳታ መስጠት ነበር። ፡

እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት፡ ከሰባቱ መካከል መንፈስ ቅዱስ የሞላበት እስጢፋኖስ ትልልቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን እየሠራ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገር ነበር።  ከተመረጠ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ትኩረት ሳበ። የነጻ ወጭዎች ከምትባለው ምኩራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያ፥ ከቂልቅያና ከእስያ የሆኑ ሰዎች ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። በድፍረት በሰበካቸውና ገሰጻቸው በአይሁዶች በድንጋይ ተወግሮ አረፈ፤ ስለዚህም የሰማዕታት መጀመሪያው ሆነ።

ፊልጶስ እና ተልእኮው ፡ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ካረፈ በኋላ ከኢየሩሳሌም የመጡ ክርስቲያኖች ወደ ሰማርያ ተሰደዱ። ፊልጶስ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ለሳምራውያን ወንጌልን ሰብኮ በሰማርያ ቤተ ክርስቲያን አቋቋመ። እንደ እስጢፋኖስ ሁሉ በእጆቹ ታልልቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር። ርኩሳን መናፍስትን ካደሩቧቸው ሰዎች እያስወጣ፣ አንካሳና ልምሾዎችን ይፈውስ ነበር ። የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን “ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳ ሂድ” አለው። የሐ. ሥራ ፰፥፳፮  ፊልጶስም ተነሥቶ ሄደ። የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ በሀብቷም ሁሉ በጅሮንድ የነበረውን ባኮስን አጥምቆ በኢዮጴ፣ በጋዛ እና በቂሳርያ አዲስ ጉባኤ መሥርቷል።

ጥቅምት 20 ዓመታዊ በዓሉን የምናከብረው ቅዱስ  ” ዮሐንስ ሐጺር- አጭሩ አባ ዮሐንስ” ማነው?


ሊቃውንት ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ:-
“ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ፣
ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ” ይላሉ::
“ቁመቱ እጅግ ያጠረ፣ ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ
ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን” ማለት ነው:: ቅዱሱ የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ነው:: ወላጆቹ ምንም በሥጋዊ ሀብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጎውን ሕይወት አስተምረውታል:: ወደ ምናኔ የገባው ገና በ18 ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው፣ በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን “ምን አጠፋሁ?” ብሎ እንኩዋ ሳይጠይቅ “አባቴ ሆይ! ማረኝ?” እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር:: ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው እርሱዉ ተደብድቦ እርሱዉ ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል:: አባ ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም:: አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምሕርት ስለ ነበረ ነው እንጂ። አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምህሩ ቀርቦ “አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው:: (የአካባቢው አስፈሪ አውሬ ነበር) አባ ባይሞይ ግን “ይዘህልኝ አምጣው” አለው:: ትእዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በረሃ ወርዶ፣ ጅብ (አውሬ ) አልምዶ ይዞለት መጥቷል::
ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው:: “ምን ላድርገው አባ?” አለው:: “ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው:: ከዚያ አምጥተህ አብላኝ” ሲል አዘዘው:: ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ “እሺ” ብሎ ወስዶ ተከለው::
ከዚያም ለ2 ዓመታት ሳይታክት ውኃ አጠጣው:: ውኃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር:: ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ:: በ3ኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ፤ ደግሞም አፈራ:: ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምሕሩ “አባቴ! እንካ ብላ” ብሎ ሰጠው:: አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም:: እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም:: ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት አላቸው: “ንሱ ብሉ፤ በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው::”  ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለ12 ዓመት አስታሞታል:: መምህሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው:: “ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው” ብሏቸው ዐርፏል:: ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል:: ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኳል::
በተጨማሪም ገላዋን በመሸጥ በዝሙት ሥራ የምትተዳደር አትናስያ  የተባለች በቀደመ ሕይወቷ በገዳማውያኑ ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጣት የነበራች  ብትሆንም በጠላት አሠራር ወድቃ ከዚህ ሕይወት እንዲታደጋት በገዳማውያኑ ተመርጦ አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ፤ ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
“እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም” እያለ ቀረባት:: (መዝ. ፳፪)
ፈጠን ብሎ ከጎኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ “ምነው?” አለችው:: “የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው” አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::
ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን “ግዴለሽም፤ ንስሐ ግቢ፤ ፈጣሪ ይምርሻል” ብሎ አሳመናት:: “እሺ አባቴ” ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ፣ ጫማ ሳትጫማ፣ ሌላ ልብስ ሳትደርብ፣ ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች:: ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ኋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በረሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት፣ ብርድና ፀሐይ ጎበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና “እረፊ” ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዐምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: “የማን ነፍስ ትሆን” ብሎ ወደ አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም “ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?” ብሎ አለቀሰ:: ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ: “ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ” አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: “ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና፤ 7 ጊዜ ይነሳል::” መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር:: ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጣል። አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት:: ሰማያት ተከፍተው፣ ቅዱሳን ሊቃነ-መላእክት ሚካኤል እና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ:: “እጹብ፣ እጹብ” እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ “ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?” ቢለው “እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል / ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?” ብሎታል:: ገዢውም ደንግጦ “እብድ መነኩሴ” ብሎት ሔዷል:: ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በኋላ  ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ:: ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ “አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?” አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም “ወዳጃችን! ምን ሆንክ?” አሉት::
ቅዱሱም መልሶ “ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋችኋል” አላቸው:: እነሱም “ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::”
“ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው” ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን፣ ቴዎፍሎስ ፣ ቄርሎስ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና ሌሎችም ከምእመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ:: ከዚህ በኃላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል:: ለ400 ዓመታት በዚያው ቆይቷል::
በ825 ዓ/ም ግን በአባ ዮሐንስ ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተመልሷል:: ቅዱሱ ያረፈው ጥቅምት 20 ቀን ነው። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ረድኤት በረከት ያሳትፈን።

ቅዱስ አትናስዮስ ብጹዕ

ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር:: በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል::በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ አባ ሚካኤል አርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ:: ነገርግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም:: እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ ሄዱ:: በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀጳጳሳት የሚሾመው የሁሉም አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ:: ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ዻዻስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ:: ለሃምሳ ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን  ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ ብለው ሾመውት ተለያዩ:: በ፶፩ኛው ኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ:: “እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን “ፓትርያርክ” ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን!” ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ:: ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ:: ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም:: ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል:: ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል:: ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም:: ደቀመዝሙሩን ጠራውና  ‘ልጄ! እሺ በለኝ፤ ነፍሴ ትመርቅሃለች:: እኔ ለ1 ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ፤ እሠር፤ ፍታ:! ሕዝቡ ከጠየቁህ “ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው” ‘ ብሎት ከመንበረ ጵጵስናው ወጣ:: እጅግ የነተበ የበረሃ ልብሱን ለብሶና በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ:: ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ:: “አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?” ብሎ ለመነው:: አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት:: ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ:: ውሃ ይቀዳል፣ ዳቦ ይጋግራል ፣ ቤቶችን ይጠርጋል፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል፣ የመነኮሳቱን እግር ያጥባል:: በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር:: አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት:: ጳጳሱም ጠርቶ “ዲቁና ልሹምህ!” ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ:: “ምነው?” ቢለው፣ “አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ” አለው:: አሁንም ለ7ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ “ቅስና ተሾም!” ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው:: ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ:: ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተዉት እያለቀሰ ለመናቸው:: “ለሹመቱ ትገባለህ” ብለው ግድ ሲሉት ግን “ምሥጢር ልንገራችሁ” ብሎ “ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ” አላቸው:: የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ:: እየተንከባለለም አለቀሰ:: “ወየው ለእኔ! ጌታዬን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ” እያለም ተማለለ:: በአካባቢው የነበሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትህትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ::
ሊቀጳጳሱም አዋቂነቱን አይቶ ቅስና ሊሾመው ወደደ። በእሑድ ቀንም ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጠርቶ “መንፈስ ቅዱስ ቅስና ሊሾምህ ጠርቶሃል።” አለው አባ አትናስዮስም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተወውም ማለደው። ባልተወውም  ጊዜ “አባቴ ይቅር በለኝ፤ እኔ ቄስ ነኝ።” አለ። መነኰሳቱም ሁሉ አደነቁ በእርሱም ደስ አላቸው። አባ እልመፍርያንም አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱንም ተመልክቶ ጳጳስዋ ለሞተባት ለአንዲት ሀጉረስብከት ጵጵስና ሊሾመው ወደደ። ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም በእሑድ ቀን ሰበሰበ። አባ አትናትዮስንም አቅርበው እንዲህ አሉት “ለዕገሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ልትሆን ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ጠርቶሃል” አሉት። እርሱም ሰምቶ አለቀሰ፤ እንዲተዉትም አልቅሶ አማላቸው። እንደማይተዉትም በአወቀ ጊዜ እርሱ የአንጾኪያ ሊቀጳጳሳት አትናስዮስ እንደሆነ ነገራቸው። የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጸላቸው። በዚያን ጊዜ አባ አልመፍርያን  ደነገጠ። አክሊሉንም ከራሱ ላይ አውልቆ በምድር ላይ ወደ። ለረጅም ጊዜ እንደ ሞተ ሆነ፤ በተነሣም ጊዜ እንዲህ ብሎ ጮኸ፡ “ወንድሞቼ የማደርገውን እስቲ ንገሩኝ! ዛሬ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥለኝ ምድርም አፍዋን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና፤ ጌታዬ የአንጾኪያ ሊቀጳጳሳት አትናስዮስ ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደ ባርያ ሊያገለግል አግባብ ነውን? ወዮልኝ ወዮልኝ።” ጳጳሳቱና የተሰበሰቡት ሁሉ በሰሙ ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቀው ሰገዱለት። እጆቹንና እግሮቹንም ሳሙ፤ ሊቀጳጳሱም ያማሩ የክህነት ልብሶችን ያለብሱት ዘንድ መስቀሎችንና አርዌ ብርቱን ያመጡ ዘንድ በመንበር ላይም ያስቀመጡት ዘንድ አዘዘ። ከዚያም በኋላ ጳጳሳቱ ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት ሦስት ጊዜ አክዮስ! አክዮስ! አክዮስ! አሉት። ይህም ይገባዋል ማለት ነው። ቤተክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት። ከዚህም በኋላ መቀደሻ ልብስ ለብሶ መሥዋዕቱን አክብሮ ቀድሶ አቈረባቸው፤ እነርሱንም ሀገራቸውንም ባረከ። ለዚያችም ሀገር “ምንኛ መጠን የሌለው ደስታ ሆነ?” ተባለ። በማግሥቱም አባ እልመፍርያን ተነሥቶ በቅሎ አስመጣ፣ ለጉዞ የሚያሻውን ሁሉ አዘጋጀ፣ አባ አትናስዮስንም በበቅሎ አስቀምጦ እርሱ በእግሩ ተከተለው። ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ሁሉም ከአባ እልመፍርያን ጋር አጅበው ወደ አንጾኪያ ሀገር ወሰዱት። አባት አትናስዮስም አባ እልመፍርያንን “አንተም በበቅሎ ላይ ተቀመጥና በአንድነት እንሒድ!” አለው። አባ እልመፍርያንም “ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም! አንተ በእግርህ ወደ ሀገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ ሀገርህ አደርስሃለሁ” አለው ። የአንጾኪያ ሀገር ጳጳሳትም የሊቀጳጳሳት አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝብ ሁሉ ጋር ሊቀበሉት ወጡ። በታላቅም ክብር ተቀብለው ወደ ሹመቱ መንበር አስገቡት። ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስቀመጡት። በዚያችም ቀን ፈጽሞ ደስ አላቸው። ተሰናብተዉትም ወደ ሀገራቸው በፍቅር አንድነት ተመለሱ። ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን ለሁለት ከመከፈል ታደጋት:: ቅዱሱ በተጋድሎ ኑሮ በጥቅምት ፱ በሰላም አረፈ።(ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት፣ስንክሳር ዘጥቅምት)

በዚህሳምንት የቱን መጽሐፍ አነበቡ?

“ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ፣
ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅምሃል።” ፪ኛጢሞ ፫፥፲፰
መጻሕፍትን ምን ያህል ታነባላችሁ? የምታነቡት ለምንድን ነው? የምታነቡትስ ምንድን ነው? እንዴት ባለ የንባብ ስልት? ባታነቡስ ምን የምትሆኑ ይመስላችኋል? ከዚህ የተሻለ በማስተዋል የተደገፈና ተስማሚ መጻሕፍትን ብታነቡስ ሕይወታችሁ ምንን የሚመስል ይመስላችኋል? መጻሕፍትን ማንበብ ለክርስቲያን ግዴታው ነው። ክርስቲያኖች የሚያነቡና ያነበቡትንም የሚያስተውሉ መሆናቸውን ለማወቅ ክርስትናን የኖሩትን ቅዱሳን እንመልከት። ምሳሌ፡ የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክታትን ብንመለከት የተጻፉት ሊማሩ፣ ሊጽናኑና ሊያውቁ ለተገባቸው ሰዎች ነው። ቅዱሳን ሰማዕታት አላውያን ነገሥታትን እንደዚህ ተብሎ ተጽፏልና እያሉ ሲረቷቸው እናያለን። ሲናገሩም የቀደሙ አባቶቻችንን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ እንመለከታለን። የእመቤታችን ጸሎት ላይም ቢሆን “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች።” የሚለው ጸሎት ሀና በመጽሐፈ ሳሙኤል ምዕራፍ ፪ ላይ ከጸለየችው ጋይ ያለውን መመሳሰል በማየት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ቅዱሳት መጻሕፍትን አንባቢ እንደነበረች መረዳት እንችላለን። ይሁንና ክርስቲያኖች፡ የተመረጥን፣ አምላካችንን ልንመስል የተገባን ነንና መጻሕፍትን ማንበብ ስላለብን ብለን ግን ያገኘነውን ሁሉ አናነብም። ይህ ማለት መጻሕፍት በብዙህ ዓይነት ሰዎች ሊጻፉ ይችላሉ ። አንድ እግዚአብሔርን የካደ መናፍቅ ክህደቱን ቢጽፍ፣ አንድ ፈላስፋ ቅዱስ እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርአያው የፈጠረውን ሰው ከዝንጀሮ እንዴት እንደመጣ ጥናታዊ ጽሑፍ ቢያዘጋጅ፣ ይህንን ማንበብ ለእኛ የተገባ አይደለም። ቅዱሳት መጻሕፍት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንጻፈለት “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” ፪ጢሞ. ፫፡፲፮-፲፯ እንዳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይባላሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለማችን ላይ ካሉት ዓለማውያት መጻሕፍት በእጅጉ የሚለዩ የመጻሕፍት ዓይነቶች ሲሆኑ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተጻፉ በመሆናቸው ክብራቸውና ቅድስናቸው ልዩ ነው። እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ፣ በመንፈስም በሥጋም የሚያጎለብተን ሲሆን አሁን ካለው ምድራዊ ኑሯችን ባለፈ ለዘለዓለማዊውም ሕይወታችን ስንቅ የሚሆኑ፣ ስናነባቸው የምንቀደስባቸው መጻሕፍት ናቸው።” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን መጻሕፍት እንዲያስተምሩን፣ እንዲገስጹን የተሰጡን ናቸው። አንድ ሰው በአጠገቡ ለሌለ ወዳጁ ደብዳቤ እንደሚጽፍለት ኹሉ፥ እግዚአብሔርም ፣ ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ከእርሱ ለራቀው ለሰው ልጅ የላካቸው ደብዳቤዎች ናቸው። ቅዱሳት መጻሕፍት የተሰጡት በኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንደኾነ ቅዱስ ዮሐንስ ያብራራል፡
የመጀመሪያው: በጊዜ ሒደት አንዳንዶች ከመሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ፈቀቅ እያሉ ስለ ኼዱ ሲሆን
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ: በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ማለትም በምግባራቸው ንጽህናቸውን እያቆሸሹ ስለ ኼዱ (ጥፋታቸው እየበዛ፣ ከሥርዓት እየራቁ ስለመጡ) ነው፡፡
በመኾኑም መጻሕፍት እነዚህ በሃይማኖትም በምግባርም ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከጠባቢቱ ወደ ሰፊዋ መንገድ ፈቀቅ ያሉትን ለመመለስና ሌሎችም ወደዚያ እንዳይሔዱ ለማስታወስ የተሰጡ ናቸው። ሉቃ.፩፡፩-፬ በመሆኑም መጻሕፍትን ማንበብ የሕይወት (የድኅነት) ጉዳይ እንጂ የአማራጭ ጉዳይ እንዳልኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ መጻሕፍትን ስለ ማንበብ፡ “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ፤ በማንበብ ተወስነህ ኑር” ካለው በኋላ ምክንያቱን ሲነግረውም፡ “ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ. ፬፡፲፮) በቀጣይ ሳምንትስ ምን አሰቡ?
መልካም ዕለተ ሰንበት!

የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ስለሆነው ባህረ ሀሳብ ያውቃሉ ❓

    ባህረ ሀሳብ የግእዝ ቃል ሲሆን ከሁለት ቃላት የተወሰደ ነው። ባህር ማለት ዘመን፤ሀሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ባህረ ሀሳብ ማለት የዘመን አቆጣጠር ነው። ባህረ ሀሳብን “የጻፈው ማን ነው?” ቢሉ የመንበረ እስክንድርያ ፲፪ኛ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው። ይህ ቅዱስ አባት ቤተክርስቲያን በዘመነ ሐዲስ የምትመራበትን የአጽዋማትና የበዓላትን ቀመር ባህረ ሀሳብን የሠራ ነው።

ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው፡፡ ድሜጥሮስ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ትምህርት ባይኖረው ሕገ እግዚአብሔርን አክብሮ የሚኖር ስለነበር በዚህ ቅድስናው ምክንያት መልአከ እግዚአብሔር ለ፲፩ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዩልያኖስ ተገልጦ በነገረው መሰረት ድሜጥሮስ ፲፪ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ በመንበረ ማርቆስ ተሾሟል፡፡

   ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖራት ያደርገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት።ይህ ባህረ ሀሳብ ያለፉትን ዓመታት፣ አሁን ያሉበትን፣ወደፊት እስከ ምጽአት የሚመጡትን አጽዋማት እና በዓላት ለማወቅ ይረዳል።

  ቅዱስ ድሜጥሮስ (ከ፻፹ – ፪፻፳፪ ዓ.ም.) በመንበረ እስክንድርያ ላይ ቆይቷል፡፡ ይህም ቅዱስ አባት ቤተክርስቲያን በዘመነ ሐዲስ የምትመራበትን የአጽዋማትና የበዓላትን ቀመር ባህረ ሀሳብን የሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም በዘመኑ ብዙ ድርሰቶችን መጽሐፎችን ጽፏል፡፡

     በዚህ የዘመን አቆጣጠር ውስጥ የዘመነ ብሉይና የዘመነ ሐዲስ ድምር በጠቅላላው ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡

አዕዋድ:
አዕዋድ የሚለው ቃል ኦደ ከሚል ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ዞረ ማለት ነው፡፡ አዕዋድ ማለት ደግሞ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዞሮ የሚመጣ ማለት ነው፡፡ አዕዋድያት የሚባሉት ሰባት ናቸው፡፡ እነርሱም

       ዓውደ ዕለት፡- ከሰኞ እስከ እሑድ ያሉ ቀናት ሲሆኑ እነዚህ ቀናት በየሳምንቱ ተመላልሰው የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሳምንታት እየተመላለሱ ወራትን ያዋቅራሉ፡፡

        ዓውደ ወርኀ፡-ይህ በሠላሳ ቀን በየወሩ እየተመላለሰ ዓውደ ዓመትን ይሰራል፡፡

        ዓውደ ዓመት፡- በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀናት በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ነው።

         ዓውደ አበቅቴ (ንኡስ ቀመር)፡- ዐሥራ ዘጠኝ ሲሆን በየ፲፱ ዓመቱ ዞሮ የሚመጣ ነው፡፡ ፀሐይና ጨረቃ ተራክቦ የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡

  ዓውደ ፀሐይ፡- ሃያ ስምንት ዓመት ሲሆን በየ፳፰ ዓመቱ ተመላልሶ የሚመጣ ነው፡፡

  ዓውደ ማኅተም (ማዕከላዊ ቀመር)፡- ሰባ ስድስት ዓመት ነው፡፡ በ፸፮ ዓመት አንድ ጊዜ አበቅቴው እና ወንጌላዊው ይገናኙበታል፡፡

   ዓውደ ዐበይ ቀመር (ዐቢይ ቀመር)፡- አምስት መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ዕለት፣ ወንጌላዊ እና አበቅቴ ይገናኙበታል፡፡

  በዚህም መሠረት የ2017 ዓ.ም. አጽዋማት መቼ እንደሚውሉ እንግለፅ:-
# ጾመ ነነዌ : የካቲት ፫
# ዐቢይ ጾም: የካቲት ፲፯
# ደብረ ዘይት ፦መጋቢት ፲፬
# ሆሳዕና ፦ሚያዝያ ፭
# ስቅለት ፦ሚያዚያ ፲
# ትንሣኤ ፦ሚያዝያ ፲፪
# ርክበ ካህናት ፦ግንቦት ፮
# ዕርገት ፦ግንቦት ፳፩
# ጰራቅሊጦስ ፦ሰኔ ፩
# ጾመ ሐዋርያት ፦ሰኔ ፪
# ጾመ ድኅነት ፦ሰኔ ፬

http://youtube.com/@EMislene

ቅዱስ ድሜጥሮስ

ይህም አባት አስቀድሞ መጻሕፍትን ያልተማረ ሕዝባዊ ገበሬ ነው። በወላጆቹ የወይን አታክልት ቦታዎች ውስጥ የሚሠራ ሆነ። ከታናሽነቱም ሚስት አጋብተውት ከእርሷ ጋር ዐርባ ስምንት ዓመት ኖረ። ድንግልናቸውን በንጽሕና የጠበቁ ናቸው። የተሠወረውን ከሚያውቅ እግዚአብሔር በቀር ይህን የሚያውቅ የለም ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ዮልያኖስ ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት።ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆነውን በምልክት ገለጠለት እንዲህም አለው ። “ነገ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ አንተ የሚገባ ሰው አለ ከአንተ በኋላ ሊቀጳጳሳት የሚሆን እርሱ ነውና ያዘው አትተወው።” በዚያችም ቀን ድሜጥሮስ ወደ አታክልቱ ቦታ ገባ። ያለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ አገኘ ያንንም የወይን ዘለላ በረከት ሊቀበልበት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮልያኖስ ይዞት ሔደ።በዚያንም ጊዜ አባ ዮልያኖስ ድሜጥሮስን በእጁ ይዞ ለሕዝቡ ሁሉና ለኤጲስ ቆጶሳት አሳልፎ ሰጠው ። “ከእኔ በኋላ ሊቀጳጳሳት የሚሆናችሁ ይህ ነው ስለ’ርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ነግሮኛልና ይዛችሁ ሹሙት” አላቸው ።ከዚህም በኋላ አባ ዮልያኖስ በአረፈ ጊዜ የጸሎቱን ሥርዓት ፈጽመዉለት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መላበት። የቤተክርስቲያን የሆኑ የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍትን አንብቦ ተረጐማቸው። ብዙዎች ምሥጢራትም ተገለጡለት። ከዚህም በኋላ ባሕረ ሐሳብ የተባለውን የዘመን መቊጠሪያ ሠራ። ከእርሱ በፊት የነበሩ የክርስቲያን ወገኖች የመድኃኒታችን የጥምቀቱን በዓል ጥር ዐሥራ አንድ ቀን አክብረው በማግስቱ የከበረች ዐርባ ጾምን ጀምረው እስከ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ድረስ ይጾማሉ።ከዚያም በኋላ መጋቢት ሃያ ሁለት ቀን የሆሣዕናን በዓል አክብረው በማግስቱ የሕማማትን ሰሞን ጾም ጀምረው ይጾማሉ።ከሐዋርያትም ዘመን ጀምሮ እስከ ‘ርሱ ዘመን እንዲህ እያደረጉ ኖሩ።እርሱም እንዲህ ሠራ። የከበረች የጌታችን ጾም መግቢያዋ ከሰኞ ቀን እንዳይፋለስ ፍጻሜውም በዐርብ ቀን። ከዚህም የሆሣዕናን በዓል አያይዞ ሠራ ። በሚቀጥለው ሰኞ ቀን የሕማማት ጾም ተጀምሮ እንዲጾም የስቅለቱም በዓል ከዐርብ ቀን እንዳይፋለስ የከበረች የትንሣኤውና የጰራቅሊጦስም በዓል ከእሑድ ቀን የዕርገቱም በዓል ከሐሙስ እንዳይፋለስ። እንዲሁም አዘጋጅቶ ለኢየሩሳሌም ሀገር፣ ለሮሜ ፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሀገር ሊቃነጳጳሳት ለየአንዳንዳቸው ላከላቸው።እነርሱም በደስታ ተቀብለው ሠሩበት እስከዚችም ቀን ጸንቶ ኖረ።በቊርባን ቅዳሴ ጊዜም ዘወትር ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያየው ሆነ።የሕዝቡ ኃጢአታቸው በፊቱ ግልጥ ሆነ ። ስለዚህም የማይገባቸውን ሥጋውንና ደሙን ከመቀበል ይመልሳቸዋል ።እንዲህም ይላቸዋል ፣ “ሒዱ ንስሐ ግቡ ከዚያም በኋላ መጥታችሁ ሥጋውና ደሙን ተቀበሉ።” ስለዚህም ነገር ብዙ ሕዝቦች ኃጢአት ከመሥራት የሚጠበቁ ሆኑ። ልባቸው የደነደነ ሌሎች ግን ጠሉት። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ።”ይህ ሰው ሚስት አግብቶ ሚስቱም ከእርሱ ጋር ትኖራለች። ሳይገባውም በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ተቀምጠ። ከንጹሕ ድንግል በቀር አይሾምበትም ነበርና እኛንም ኃጢአተኞች ናችሁ ብሎ ይገሥጸናል።” በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ “ድሜጥሮስ ሆይ ራስህን ብቻ ማዳንን አትሻ ወገኖችህም ይጠፉ ዘንድ አትተው። ነፍሱን ስለመንጋዎቹ አሳልፎ ለሞት የሚሰጥ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደ ሆነ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል የተናገረውን አስብ” አለው። ድሜጥሮስም መልአኩን “ጌታዬ የምትለኝ ምንድን ነው?” አለው መልአኩም “በአንተና በሚስትህ መካከል ተሰውሮ ያለውን ምሥጢር ለወገኖችህ ግለጽ!” ብሎ መለሰለት። ከዚህም በኋላ ሕዝቡን አሰባሰባቸው። ሊቀ ዲያቆኑንም “ወጥተው ወደቤታቸው እንዳይገቡ ሕዝቡን ንገራቸው !” አለው። ራሱም ቅዳሴውን ቀደሰ ሁለተኛም ዕንጨቶችን ሰብስበው እሳትን እንዲያነዱ አዘዛቸው ። እንዳዘዛቸውም አደረጉ። ያን ጊዜ ይህ አባት ተነሥቶ ከሚነደው እሳት መካከል ገብቶ ለረጅም ጊዜቁሞ ጸለየ ከእሳቱም ፍህም አንሥቶ በሚከናነብበት ቀጸላ አደረገ ፤ ሚስቱንም ጠርቶ “መጎናጸፊያሽን ዘርጊ!” አላት። በዚያም የእሳቱን ፍህም ጨመረ፤ በእሳቱም መካከል በአንድነት እየጸለዩ ቆሙ ፤ሕዝቡም እጅግ ያደንቁ ነበር።ከዚህም በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ እንዲህ ብለው ለመኑት። “አባታችን ሆይ ይህን የሠራኸውን ሥራ ታስረዳን ዘንድ ከቅድስናህ እንሻለን ።” እርሱም “ይህን ሥራ የሠራሁት ከንቱ ውዳሴን ሽቼ አይደለም። እናንተ እኔን አምታችሁ ስለ እኔ እንዳትጐዱ እንድትድኑ ከዚች ሴት ጋር በመካከላችን ተሠውሮ ያለውን ምሥጢር እገልጽላችሁ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ አዘዘኝ ነው እንጂ!” አላቸው ።እርሷ የአባቴ የወንድሙ ልጅ ናት፤ በሕፃንነቷም አባቷ ሞተ፤ በአባቴም ቤት ከእኔ ጋር አደገች፤ አካለ መጠንም በአደረሰን ጊዜ አባቴ እርሷን አጋባኝ። ወደጫጉላ ቤትም በገባን ጊዜ “እኔ እኅትህ ስሆን ለአንተ እንዴት አጋቡኝ?” አለችኝ።እኔም “የምትፈቅጂ ከሆነ ድንግልናችንን ጠብቀን በአንድነት እንኑር። ይህንንም በመካከላችን ያለውን ምሥጢር የሚያውቅ አይኑር !”አልኋት በዚህም ተስማምተን በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ዐልጋ እየተኛን አንድ መጐናጸፊያንም እየተጐናጸፍን ዐርባ ስምንት ዓመት ያህል ኖርን። ይህን ሥራችንንም ያለ እግዚአብሔር የሚያውቅ የለም። እኔም እርሷ ሴት እንደሆነች አላወቅኋትም፤ እርሷም እኔን ወንድ እንደሆንኩ አታውቅም፤ በየሌሊቱም ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ በንስር አምሳል ወደ መኝታችን እየገባ ክንፎቹን አልብሶን ያድራል ሲነጋም ከእኛ ይሠወራል አላቸው ። በዚያንም ጊዜ በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቀው ለመኑት፤ እርሱም ይቅር አላቸው፤ አጽናናቸውም ።ይህንንም ድንቅ ሥራ ያዩ ሁሉ ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
በዚህ አባት ዘመንም ስማቸው ቀሌምንጦስ፣ አርጌንስ የሚባሉ ሌሎችም መናፍቃን ሰዎች ተነሥተው ታዩ። ሌሎችም በአንድነት ሁነው ስለሃይማኖት የፈጠራ መጽሐፍን ጻፉ፤ እርሱም አውግዞ ከምእመናን ለያቸው እርሱም ሁል ጊዜ ያለ ዕረፍት ከጠዋት እስከ ማታ ምእመናንን የሚያስተምራቸው ሆነ።ሸምግሎ በደከመም ጊዜ በአልጋ ላይ አስቀምጠው፣ ተሸክመው ወደ ቤተክርስቲያን ያደርሱታል፤ እስከ ማታድረስም ያስተምራቸዋል። ሰዎችም ሁሉ ትምህርቱን ይሰሙ ዘንድ ይጨናነቃሉ መላ የሕይወቱ ዘመንም መቶ ሰባት ነው። በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ። ከቅዱስ ድሜጥሮስ ረድኤት በረከት ያሳትፈን። (ዋቢ፡ ስንክሳር ዘወርኃ ጥቅምት)

ወጥመድ

“ዘወትር በወጥመዶች መካከል እንደምትኼድ በገደልም መካከል እንደምትመላለስ ዕወቅ”(ሲራ9:13)
ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ድረስ ወርኅ ጽጌ ብለን በምንጠራው ይህ ወቅት ቅድስት በቤተክርስቲያናችን የአምላክ እናት የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያምንና የልጇ ክርስቶስን ስደት እያሰበች በአበባ ታጅባ ሌሊቱን በሙሉ በማኅሌት ታመሰግናለች።
ታድያ እናንተስ እንዴት አደራችሁ? ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ነጠላችሁን አጣፍታችሁ አጥቢያችሁ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ለማኅሌት ተፋጠናችሁ? አበባ ይዛችሁ “ልጅሽን ታቅፈሽ እመቤቴ ሆይ ነይ ማርያም”እያላችሁ ከሊቃውንቱ ጋር ወረባችሁ? ሌሊቱን ሙሉ ነጫጭ ለብሰው “አክሊለ ጽጌማርያም”ከሚሉምዕመናን መካከልበእጣኑ ልዩመዓዛታውዳችሁ፡የከበሮድምጽእየሰማችሁየቅዱሳን መላእክትን ምግብተመገባችሁ? ኪዳንአደረሳችሁ? ታላቁን የቤተክርስቲያን ጸሎት ቅዳሴን አስቀደሳችሁ? ለምን? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው በወጥመድ እንዳይያዙ ነው። ሰዎችም የማሰቡ ኃይልን የተሰጣቸው ኃጢአትን እንዲያስወግዱ ነው በማለት ይነግረናል። ሊቁ ይህንን የሚነግረን እንሰሳት በወጥመድ መያዝ እንደማይፈልጉ ሊያስረዳን አይደለም።ይልቁኑ የማሰብ ኃይል ተሰጥቶን ሳለ ይባስ ብለን ከምድር አራዊት በታች የማናስተውልከኾንን ሊደረግልን የሚችል ምሕረት ወይም ይቅርታ እንደምን ያለ ምሕረት እንደምንስ ያለ ይቅርታ ነው? ብሎ በተግሳጽ ከተያዝንበት ሊመልሰን ነው። የሚደንቀው ነገር ደግሞ እንሰሳት ሲሆኑ፡ የያዛቸው ወጥመድ ተመልሶ የማይ’ዛቸው መኾኑነው።
እንደምታውቁት ወጥመድ እንሰሳትን ለመግደል፡ ወይንም ደግሞ ለመያዝ የምንጠቀመው መሳሪያ ነው። ወጥመድ ስናጠምድ ፡ የሚወዱትንና አይተውት ሊያጓጓቸው የሚችሉ ነገሮችን ከፊት በማስገባት ነው። በወጥመድ የተያዘ እንሰሳ መጨረሻው የሚሆነው ወይ መሞት ወይንም ደግሞ የተጠመደበትን አላማ ሲፈጽሙ መኖር ነው። ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስየሰውን ልጅ ዓለም እንደፈለገ ለማድረግ የሚጠበቅበት አንዱንና ዋነኛውን የሰውነት ክፍል ብቻ መያዝ፡ ማዘናጋትና መቆጣጠር ነው። አእምሮን። ለሰው ልጅ “እንደ ባለአእምሮ ተመላለሱ”የሚል ትእዛዝ እስኪሰጠው ድረስ አእምሮው ኃያልና ለሚሰራቸው ነገሮች ሁሉ ዋና ክፍል ነው።ታድያ ይህ ክፍል በወጥመድ በተያዘ ጊዜ መላ ሰውነት አይንቀሳቀስም።ውጤታማ አይሆንም።
አብዛኞቻችን ከስልኮቻችን ጋር ያለን ቁርኝት የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ከተቀመጥን እንዳንነሳ፡ ከምንም በላይ ደግሞ አምሽተን ተኝተን ጠዋት ላለማስቀደሳችን፡ ማጠናቀቅ የሚገቡንን ስራዎች ጨርሰን ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንሄድ ምክንያቶቻችን ናቸው።አንድ ደቂቃ ብቻ ውሰዱና አስቡት በአንድቀን ምን ያህል መንፈሳዊ መጻሕፍትን ታነባላችሁ? ምን ያህል ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ትማራላችሁ? በቀን ለምን ያህል ደቂቃ ጸሎት ታደርሳላችሁ? ምን ያህል የእግዚአብሔርን ፍቅር ታስባላችሁ? በሌላ በኩልስ በእጃችሁ የምትይዙት ስልክ ይህንን አእምሮዋችሁ ምን ያህል ተቆጣጠረው? ምን ያህል ሰዓታትን በስልክ ታጠፋላችሁ? በስልክ ላይስ ለተመለከታችሁት አሉታዊ፡የማይጠቅም ከእናንተ ጋር የማይገናኝና
የማይመለከታችሁ ነገር ምን ያህል ታወራላችሁ? ምን ያህል ስልካችሁ አእምሮዋችሁን ፡ ሰዓታችሁን ጉልበታችሁን ይመጠዋል? ያደርቀዋል? ይቆጣጠረዋል? መልሱን ለእናንተ ትተነዋል!!!

ማኅሌተ ጽጌ በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል።

🌷🌹🥀🌺🌸🌷🌹🥀🪷🌺

   እንደሚታወቀው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ያለው ጊዜ ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ ተብሎ ይጠራል፡፡ በእነዚህ ቀናት በየቤተክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩት መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከቶች፣ የሚቆመው ማኅሌት በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋክብት ምድር በጽጌያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡

         በወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው መልአኩ  “ሕፃኑንና እናቱን ወደ ግብፅ ይዘሃቸው ሽሽ፣ የሕፃኑን ነፍስ ሊገድሉት ይፈልጋሉና።” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሠረት ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ራእይ. ፲፪፥፮  ፣ ማቴ. ፪፥፲፫-፳፫ ፣ ት.ኢሳ.፲፱፥፩፣ እንባቆም ፫፥፮-፯፣ መዝ.፹፫፥፫፡፡

        ታድያ  “ሰቆቃወ ድንግል” የሚለው ድርሰት “ፀሐይን የምትለብሺ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉው ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሸሽ ጊዜ የደረሰብሽን ችግሮች ፣ ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንደ ጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።” እንዳሉት እኛም እርሷንና የልጇን ስደት እያሰብን ወቅቱን በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር እናከብረዋለን።

      እናም የምንችል ሁሉ በአጥቢያችን ባሉ ገዳማትና አድባራት በመገኘት በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡትን ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌተ ጽጌና ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣውን ዝማሬ ከሊቃውንቱ ጋር እየዘመርን በረከትን ልናገኝ ይገባል።

ይሁን እንጂ በተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት በዚህ በምንወደውና የምንናፍቀው ወቅት በቤተ መቅደስ መገኘት ካልቻልን ባለንበት ሆነን አብረን እንዘምር ዘንድ የእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት ሥርዓተ ማኅሌቱን ከደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል  በቀጥታ ስለምታስተላልፍ ከ3 ሰዓት ጀምሮ ከታች በተቀመጠው የዩቲዩብ ገጽ ይከታተሉ።

የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene

👆subscribe ያድርጉ።

ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ
(መሰባሰባችን እግዚአብሔር ምስሌነን  አንተው!)
🌷🌹🥀🌺🌸🌷🌹🥀🪷🌺

የቤተክርስቲያን ምሳሌያት (ክፍል 2)

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ ትመሰላለች (ዘፍ 22፡12)፡እግዚአብሔር  አበ ብዙኀን አብርሃምን አንድ ልጅህን  ሠዋልኝ  ባለው ጊዜ የዋሁ ይስሐቅ ሊሠዋበት ያለው የሞርያም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በሞሪያም ተራራው ላይ ይስሐቅ  ያይደለ በጉ እንደተሰዋ በቤተክርስቲያንም የሩቅ ብዕሲ ደም ሳይሆን መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ይፈተታል፡፡ ለዚህም ነው ይህች እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሞሪያም ተራራ የምትመሰለው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች (ዘፍ 35፡13-15)፡ ቤቴል (ቤት-ኤል) ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ያቺ ሀውልት እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር የተነጋገረባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ ተገለፀለት፡፡ በቤተክርስቲያንም አምኖ ለቀረበ እግዚአብሔር በረድኤት ይገለፅለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ያዕቆብን ባርኮታል፡፡ በቤተክርቲያንም ተግቶ የጸለየ እግዚአብሔር በረከትን ያበዛለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎታል፡፡ ሰውም ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተቀብሎ አዲስ ማንነትን (ክርስትናን) ይዞ በአዲስ ስም (በክርስትና ስም) ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር በቤቴል ያደረገው ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ለሚደረገው ምሳሌ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቤተል እግዚአብሔር እስራኤል ለተባለው ያዕቆብ ‹‹ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።›› ሲል የዘላለም ኪዳንን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ኪዳን ቤቴል በተባለችው ቤተክርስቲያንም ጸንተው ለኖሩት ለቅዱሳን የተሰጠ ኪዳን ነውና ያቺ እግዚአብሔር ለያዕቆብ የተገለፀባት ስፍራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኗ በተረዳ ነገር ላይ የተመሠረተ እንጂ በአጋጣሚ የተወሰደ አይደለም፡፡ልክ እንደ ቤቴል ሰውና እግዚአብሔር የሚነጋገሩባት ስፍራ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያች ስፍራ ያዕቆብ የድንጋይ ሐውልትን መትከሉ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበትን ጽኑዕ መሠረት ያሳያል፡፡ ያዕቆብ በሐውልቱ ላይ ዘይትን አፈሰሰ፡፡ ይህም ዛሬም አዲስ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚከብር ያሳያል፡፡ በዚያች ቦታ ላይ ያዕቆብ የመጠጥን መስዋዕት እንዳቀረበ በቤተክርስቲያንም አማናዊው የክርስቶስ ደም ለመስዋዕትነት ይቀርባል፡፡ በቤቴል ያዕቆብ የተከላት ሐውልት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ስንል እነዚህ ሁሉ ትንታኔዎችን በማስተዋል ነው፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች (ዘፀ 34፡1)፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ በቤተክርስቲያንም ክርስቲያኖች በጾምና በጸሎት ተግተው ሰማያዊ ክብርን (ቃል ኪዳንን) ያገኛሉና ቤተክርስቲያን በደብረ ሲና ተራራ ተመስላለች፡፡ በደብረ ሲና ተራራ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ በቤተክርስቲያንም በጾምና በጸሎት የተጉ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉና ምሳሌነቱ ትክክለኛና ተገቢም ነው፡፡ ሙሴ ከደብረ ሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እያበራ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን የኖረ ሰው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ሲሄድ በመላእክት ታጅቦ እንደዚህ እያበራ ነውና ምሳሌነቱ ጽኑዕ ነው፡፡

ይቆዩን።