የቤተክርስቲያን ምሳሌያት

ምንም እንኳን ቀጥሎ የምናያቸው ቦታዎች የቤተክርስቲያን ምሳሌያት ቢሆኑም አንዳቸውም በሁለንተናቸው ሙሉ ለሙሉ አይመስሏትም ምክንያቱም እርሷ የክርስቶስ አካሉና የሙላቱ ተካፋይ ናትና ፡፡ ኤፌ 1፥23

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች (ዘፍ 7)

ሊቁ አውግስጢኖስ በማየ አይኅ/በጥፋት ውሃ/ ጊዜ ነፍሳት ከሞተ ሥጋ የዳኑባት ያቺ የኖኅ መርከብ የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት ይለናል፡፡ ያቺ የኖኅ መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት፡፡ ቤተክርስቲያንም ቅድስት ፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት  የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡ የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ኖኅ መርከብን እንዲሠራ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመሠረታት ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኖኅ ወደ መርከቡ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ያስተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የሰው ልጅ ሁሉ አምኖ ይድን ዘንድ የድኅነት ጥሪዋን ለሁሉም ነው የምታስተላልፈው፡፡ የኖኅ መርከብ ፈቃደኛ ሆኖ ለመጣ ሁሉ (ለእንስሳትም ጭምር) በቅታለች፡፡ ቤተክርስቲያንም አምኖ ለመጣ ሁሉ የሚበቃ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላት ናት፡፡ በተጨማሪም የጥፋት ውኃው እየሞላ ሲሄድ የኖኅ መርከብ ከምድር ከፍ ከፍ እያለች ትሄድ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፈተና ሲበዛባት በውስጥዋ የሚኖሩት (በፈተና የሚፀኑት) የሚያገኙት ክብር እንደዚሁ ከፍ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ኖኅን አሰበ፣ የጥፋት ነፋስን አሳለፈ፣ ውኃውም ጎደለ፡፡ በቤተክርስቲያን ላይም የሚመጣውን ፈተና እንደዚሁ እግዚአብሔር ያሳልፋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኖህ መርከብ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ምሳሌ ቢሆንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ወደ ኖኅ መርከብ ተኩላ ገብቶ ሲወጣም ተኩላ ሆኖ ይወጣል:: ወደ ቤተክርስቲያን ግን ተኩላ ሆነው ገብተው በግ ሆነው የወጡ ብዙዎች ናቸው” ብሎአል:: ይህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ንግግር በሂሳብ ትምህርት የምናገኘውን የፍጹምነት መጠን /Absolute Value/ ያስታውሰናል፡፡ የትኛውም አሉታዊ አኃዝ /Negative intiger በዚህ የፍጹምነት መጠን ││ ውስጥ ሲገባ ወደ አዎንታዊነት አኃዝ /positive intiger እንደሚቀየረውና አወንታዊ አኃዝ ሳይለወጥ እንደሚቀረው በልብ መሻት ወደ ቤተክርስቲያን የሚገባ ኃጥእ ታድሶ ይወጣባታል፡፡

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ 18፡1)

አብርሃም ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለባት ያቺ የአብርሀም ድንኳን (ኀይመተ አብርሃም) የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ምሳሌ  ናት፡፡ ሥላሴ በእንግድነት በአብርሀም በቤቱ ድንኳን ስር እንደተገኙ በቤተክርስቲያን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድራሉ፡፡ በአብርሃም ድንኳን ውስጥ አብርሃም ምሥጢረ ሥላሴን እንደተማረ በቤተክርስቲያንም ምሥጢረ ሥላሴ ይነገራልና፡፡
በአብርሃም ድንኳን ድሀ ሀብታም፣ ነጭ ጥቁር፣ የተማረ ያልተማረ፣ ኃጥእ ጻድቅ ሳትል እንግዳ እንደተቀበለች ቤተክርስቲያንም ያለ አድሎ ሁሉን በእኩል አይን ትቀበላለች፡፡ በአብርሃም ድንኳን ምግበ ሥጋ ይመገቡባት እንደነበር በቤተክርስቲያንም ሥጋ ወደሙና ቃለ እግዚአብሔር እንመገባለን፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቤተክርስቲያን በአብርሀም ድንኳን ትመሰላለች፡፡
በአብርሀም ድንኳን ውስጥ የነበሩት ሁሉ የየራሳቸው ምሳሌ አላቸው፡፡ አብርሀም የካህናት ምሳሌ ነው፡፡ መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ሲሰዋ የነበረ ነውና፡፡ በአብርሀም ቤት ይስተናገዱ የነበሩት እንግዶች የክርስቲያኖች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ ሲኖር እንግዳ ነውና፡፡ ምግበ ነፍስንም (የእግዚአብሔር ቃልንና የክርስቶስን ሥጋና ደም) ወደ ቤተክርስቲያን ቀርቦ ይመገባል፡፡ አብርሀም ቤት ሳይሠራ በድንኳን ውስጥ እድሜውን ሁሉ ኖሯል፡፡ ፍፁማን አገልጋዮችም እንደ አብርሀም ዓለምንና ጣዕሟን ሁሉ ንቀው ቤተክርስቲያንን ተጠግተው ይኖራሉና አብርሀም የእነዚህ አርአያ ነው፡፡ ሥሉስ ቅዱስ በአብርሀም ቤት ተገኝተው ቤቱን በበረከት ሞልተውታል፡፡ ዛሬም እንደዚሁ በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ላመኑትና ለታመኑት ሁሉ ድኅነትን ያድላሉ፡፡
ከዚህ ሌላ ሰይጣን እንግዶች ወደ አብርሃም ድንኳን እንዳይሄዱ ይከለክል እንደነበር በትርጓሜ መጻሕፍት ሊቃውንት አስተምረዋል፡፡ ይህም ምሳሌው ክርስቲያኖች ወደ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ የተለያዩ ፈተናዎች እያቀረበ ሊያስቀራቸው እንደሚሞክር የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዶች ቢቀሩም ሥሉስ ቅዱስ ተገኝተዋል፡፡ በቤተክርስቲያንም ሰዎች በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያን ሳይሄዱ ቢቀሩ እንኳን እግዚአብሔር ሁሌም እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ምሳሌ ነው፡፡ …. ይቀጥላል።

ባህርያተ ቤተክርስቲያን

ንዑድ መምህር ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” 1ቆሮ 2፥15 እንዲል ባህርዩ ለማይመረመር ጌታ አካል የሆነች ቤተክርስቲያን ምሉዕ ባህርይዋን መመርመር ለሰው ልጆች የሚቻል አይደለም። ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍትና እውነት ላይ ተመሥርተው ሃይማኖታቸው የቀናች 318ቱ ሊቃውንት፡ አዘውትረን በምንጸልየው የሃይማኖት ጸሎት ላይ ስለ ባህርይዋ እንዲህ ይሉናል:-

” ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኲሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት – ሐዋርያት በሰበሰቧት ከሁሉ በላይ በምትሆን በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን” ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት 17:12

በዚህ ከኒቂያ እስከ ቁስጥንጥንያ ባሉ ጉባኤያት የረቀቀው ዓለምአቀፋዊ ጸሎተ ሃይማኖት (Creed) ላይ የቤተክርስቲያን ክብር እንደ መሠረተ እምነት መጠቀሱ ቤተክርስቲያን ምን ያህል በክርስትና እምነት ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ወደ ርዕሳችን ስንመለስ በዚህ ጸሎተ ሃይማኖት ወይም የእምነት ድንጋጌ አንቀፅ ላይ 4 የቤተክርስቲያንን ባህርያትን እንመለከታለን። አንዲት፣ ቅድስት፣ ዓለም አቀፋዊት፣ ሐዋርያዊት … እስቲ በየተራ እነዚህን ባህርያት እንመልከት

ቅድስት /Holy/

ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት ራሷ ቅዱስ ነውና አካሉ ቅድስት ነች። “ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” 1ጴጥ 1:15-16 እንዲል ቅዱስ ጴጥሮስ በእርሱ በክርስቶስ አካልነት ውስጥ ያሉ የቤተክርስቲያን አካላት ሁሉ ከቅድስናው ተካፋይ ናቸውና ቤተክርስቲያን ቅድስት ነች፣ አንድም በጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ እንደተነሳው ከጉባኤ አይሁድ፣ ከጉባኤ አህዛብ ተመርጣ የተለየች በክርስቶስ ደም የተዋጀች ስለሆነች ቤተክርስቲያን የተመረጠች፣ የተቀደሰች ነች። ሐዋ 20:28

አንዲት /One/

ቤተክርስቲያን በተለያዩ ቦታዎች እንደመገኘቷና በተለያዩ አስተዳደራዊ ክልሎች በመከፋፈሏ አብያተ ክርስቲያናት ተብሎ በብዙ ቁጥር ልትጠራ ብትችልም መነሻዋ እርሱ አንድ እግዚአብሔር እንደሆነ መዳረሻዋም እሱ እንደመሆኑ ልጆቿም በአንድ መንፈስ ቅዱስ እንደመጠመቃቸው የአንዱ ክርስቶስ አካል ናቸውና አንድ ናት። “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።” ሮሜ 12፥5 ዳግመኛም “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤” ኤፌሶን 4፥5

ከሁሉ በላይ የምትሆን /በሁሉ የሞላች (Catholic)

ቤተክርስቲያን የአምላኳ አካል እንደመሆኗ መጠን እርሱ በዓለም የሞላ እንደመሆኑ ሁሉ እርሷም በሁሉ ቦታዎች አለች። በዚህ የለችም የምትባልባት ቦታ የለም እያንዳንዱ አማኝ ቤተክርስቲያን እንደ መሆኑ፣ እያንዳንዱ በእርሱ ስም የተሰበሰቡ በስሙ ያመኑት ሰዎች ስብስብ ቤተክርስቲያን እንደመባሉ እርሷ በዓለሙ ሁሉ የመላች የአንዱ የክርስቶስ መንግስቱ ነች። በሰማይም በምድርም እርሷ አለች።
“እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።” ኤፌ 1፥23

ሐዋርያዊት (Apostolic)

እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ ያሉ የቀደሙ አባቶች በመልእክታቸው የቤተክርስቲያን ስም ከመጥራታቸው በፊት ሐዋርያት በሰበሰቧት የምትል ቅፅል በብዛት ይጠቀማሉ። ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት ስንል ማቴዎስ በወንጌሉ የመጨረሻው ምዕራፍ እንደዘገበው ጌታችን ለሐዋርያት ያዘዘውን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴ 28:19-20 ቃል መሠረት በማድረግ ነው።  በመሆኑም ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ አብሮ የሚሆነው ለሐዋርያዊው ትምህርት ለምትታመን ቤተክርስቲያን ነው። ቅዱስ ጳውሎስም የቤተክርስቲያን እምነት በሐዋርያት ት/ት እንደታነፀ ይናገራል። ኤፌ 2:20 መምህር ጳውሎስ ከዚህም ሻገር ብሎ ወንድሞቹ የሚሆኑትን የመጀመሪያው ጳጳሳት ሐዋርያትን ወክሎ ይሄንን ግዝት ይናገራል:-

“ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” ገላ 1:8-9

ይቆየን

/እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ በቀጣዩ ሳምንት የቤተክርስቲያን ምሳሌያትን እንዳስሳለን/

ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም: 1ቆሮ 11:15

ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም: 1ቆሮ 11:15

ነገረ ድኅነታዊውን የዓለምን ታሪክ ለሁለት እንክፈል ካልን የምንከፍለው በሁለት ነው። የመጀመሪያው ዓለም አስቀድሞ የተፈጠረበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዓለም የታደሰበትና እንደገና የተወለደበት ዘመን ነው።

ዓለም የተፈጠረው በስድስት ቀናት ሲሆን ይሄም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የጠበቃቸው የስድስት ሺህ አመታት (5500 ዘመን) ምሳሌ መሆናቸውን ቤተክርስቲያን ታስተምራለች። በእነዚህ ስድስት ቀናት የተፈጠሩ ፍጥረታት የነገረ ድኅነት ማሳያ መሆናቸውን በወፍ በረር ለመመልከት እንሞክራለን።

እሑድ

የብሉይ ኪዳን መፅሐፍ የሚጀምረው በሥነ ፍጥረት ትረካ ነው። መጽሐፉ የሥነ ፍጥረት ትረካውን ለመጀመር የሚጠቀማት ዓረፍተ ነገር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” የምትል ናት። ይህች ዓረፍተ ነገር የእግዚአብሔርን አምላክነት፣ ከሃሊነትና ፈጣሪነት የምታውጅ አዋጅ ናት። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሊቀ ነብያት ሙሴ መጽሐፉን በጻፈበት ቋንቋ ልዩ ምሥጢር እንዳለው ይነግሩናል እንመልከተው:-
בְּרֵאשִׁית בָּרָא אֱלֹהִים אֵת הַשָּׁמַיִם וְאֵת הָאָרֶץ‎ 
(ቤሬሺት ባራ ኤሎሂም ኤት ሃሽማይም ቬት ሃ’ርትዝ)

እንደ ሊቁ ጠርጡለስ ያሉ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ የሚለው ቃል ከጊዜ ገላጭነቱ ባሻገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የፍጥረት መጀመሪያ ብሎ የጠራውን መነሻ በማድረግ መጀመሪያ የሚለው ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ነው ይላሉ። በዮሐንስ ወንጌል ላይም ሥጋን የተዋሐደ ቃል እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ሲያጠይቅ በመጀመሪያም ቃል ነበረ ብሎ የቃል (የክርስቶስ)ን መጀመሪያነት ይናገራል። “ባራ/ፈጠረ” የሚለውም ቃል በእብራይስጥ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚነገር አምላካዊ የመፍጠር ችሎታን የሚናገር ቃል ነው።

የዕብራይስጡ ኤሎሒም የሚለው ቃል ደግሞ በሐዲስ ኪዳን በገሃድ ስለተነገረው ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ይናገራል ምክንያቱም ኤሎሂም የኤል (አምላክ) ብዙ ቁጥር አመልካች / Plural/ ሲሆን ፈጠረ የተባለበት ቃል ባራ ግን ነጠላ ቁጥር /singular/ መሆኑ የእግዚአብሔርን ልዩ ሦስትነት አመልካች ነው። ለአያያዥነት የምትገባው “ኤት” ከፊደል አፃፃፏ ባሻገር ባላት የዕብራይስጥ ሥዕላዊ መግለጫ ደግሞ እጅግ ድንቅ ምስልን ይሰጠናል። ኤት የአሌፍና የታው ፊደላት ድምር ሲሆን አሌፍ በሥዕላዊ መግለጫ የበሬ አንገት አይነት ምልክት ሲኖረው ታው ደግሞ የመስቀል ምልክት አለው። ይሄም የኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል የመሰዋት ምስጢር የያዘ ነው። በቃሉ ላይ ያሉት አሌፍና ታው የዕብራይስጥ የመጀመሪያና የመጨረሻ ቃላት መሆናቸው ደግሞ አልፋና ኦሜጋ (ራዕ 21:6) ያለውን ያመላክታል።

እንግዲህ በአንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ነገረ ሥላሴና ነገረ ክርስቶስ በዚህ መልክ በምሳሌያት ተጠቅሶ ይገኛል።

ሰኞ
በዕለተ ሰኞ የተሰራው ታላቅ ሥራ ከአራቱ ባህርያተ ሥጋ አንዱ የሆነውን ውሃን መከፈል ነበር። የውሃ መከፈልን ቅዱስ ባስሊዮስ በሰማይ የሚያመሰግኑና በምድር የሚራዱ የመላእክትን ሕብረት ይወክላሉ ሲል ምሳሌነቱን የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት (ከአይሁድና ከአህዛብ የመጡ ክርስቲያኖች) እንዲሁም በሰማይና በምድር የሚገኙ የቅድስት ቤተክርስቲያን አካላትም ይተረጎማል።

ማክሰኞ

የማክሰኞ ሥነ ፍጥረት ውስጥ በጉልህ የምናየው የምድር ማብቀል ዘወትር ማክሰኞ የምንደግመውን ውዳሴ ማርያም ያስታውሰናል። በውዳሴ ማርያሙ አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ንፅህት ድንግል የሆነች እመቤታችንን ዘር ያልተዘራባት እርሻ አንቺ ነሽ የሕይወት ፍሬ ካንቺ ወጣ ይላታል። ብሉይ ኪዳን በኢሳያስ ትንቢትና (ኢሳ 7:14) በሉቃስ ወንጌል ላይም (ሉቃ 1:34-35) ተፅፎ እንደምናነበው ክርስቶስ የተወለደው ህቱም ድንግል ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ያለወንድ ዘር ነው። የመጀመሪያዋ ምድር ያለ ገበሬ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳበቀለች ሁሉ እመቤታችንም በእግዚአብሔር ፈቃድ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኝታለች።

ረቡዕ

በዚህ ቀን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተፈጠሩ። ፀሐይ የፀሐየ ጽድቅ የክርስቶስ ምሳሌ ናት እርሱ በባህሪው ብሩህ የሆነ ነው ( ዮሐ 8:12) ጨረቃና  ከዋክብት ከፀሐይ የሚካፈሉ ሲሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እናንተ የክርስቶስ ተካፋዮች ናችሁ (ዕብ 3:14) እንዲል የቀደመ እምነታቸውን ጠብቀው የሚገኙ ሁሉ እነርሱም በጸጋ የዓለም ብርሃን ይሆናሉና (ማቴ 5:14) ጨረቃና ከዋክብት የቅዱሳን ምሳሌ ናቸው። ይሄውም በመስቀል በተከፈለ ዋጋ የተገኘ ክብር ነው።

ሐሙስ

ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም የሚለው ነገረ ድኅነታዊ ጥሪ ለኒቆዲሞስና ለብዙ ሰማዕያን እንግዳ ነገር ነው። ዮሐ 3:1-10 ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ግን በዕለተ ሐሙስ ነፍሳትን (እንስሳትን፣ አራዊትን፣ አዕዋፋትን) ያስገኘችውን ውሃ እንድንመለከት ይነግረናል። በውሃው ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ ሰፎ ነበር የሚለውን አብነት አድርጎ ዶሮ እንቁላሎቿን ሸፍና በሙቀት እንደምተፈለፍል ሁሉ ይህችም የቀደመችው ውሃ ሕያዋንን አስገኝታለች። የቀደመችው ውሃ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ለምታስገኘው ውሃ ምሳሌ ናት። የቀደመችው ፍጥረታዊ ውሃ የሚባሉና የሚያስፈሩ እንስሳትን አስገኝታለች ዳግማዊቷ የድኅነት ውሃ ግን በእረኛቸው ክርስቶስ ፊት የሚሰበሰቡ በጎች ምዕመናን ታስገኛለች።

አርብ

በክርስቶስ ደም  የሰው ልጅ ዳግም የተወለደባት ዕለተ አርብ ጥላ በሆነችው ቀዳሚቷ አርብ የሰው ልጅ ተፈጠረ። የተፈጠረው በእግዚአብሔር መልክ ነው። የእግዚአብሔር መልክ ከሚተረጎምባቸው ትርጓሜዎች ብዙ ናቸው ከእነርሱም አንዱ በዮሐ 1:18፣ቆላ 1:15 ላይ በተጠቀሰው መነሻ ያ መልክ ከአዳም የልጅ ልጅ ተወልዶ የሰውን መልክ ገንዘብ የሚያደርገው የክርስቶስ መልክ መሆኑን ነው።

ቅዱስ አትናቴዎስ ነገረ ሥጋዌን በገለፀበት ድርሳን እንዳለው የአዳም ከሥጋና ከነፍስ መሰራትም የክርስቶስ የሥጋና የመለኮት ፍጹም ተዋሕዶ ማሳያ ነው። ፍፁም ተቃራኒዎቹ ስጋና ነፍስ ያለመቀላቀል፣ ያለመጠፋፋት አንድ እንደሆኑ በክርስቶስም መለኮትና ሥጋ ከሁለት አካልና ባህሪ ያለመከፈል አንድ እንደሆኑ ማሳያ ነው።

ይቆየን

ቤተክርስቲያን ማን ናት?

ቤተክርስቲያን የሰማያዊያንና የምድራውያን ኅብረት ናት።

የዓለማችን እጅግ ጥንታዊና አካታች ኅብረት ቤተክርስቲያን ናት። ከሰማያዊያን መላእክት ጀምሮ እስከ ዕለት አማኝ ድረስ በአሚነ ሥላሴ ሥር ያሉትን ሁሉ ታጠቃልላለች። በመሆኑም በእያንዳንዱ ምድራዊ ኅጥእ መመለስ በሰማይ መላእክት ዘንድ ደስታ ይደረጋል። /ሉቃ 15:7, ሉቃ 15:10/ በዚህ አለም በፀናች በቀናች ሃይማኖት ውስጥ ሆነው ያንቀላፉትም ቢሆኑ በእርሱ እንደማመናቸው ቢሞቱ እንኳን ሕያው ናቸውና (ዮሐ 11:25) የሞት ኃይል ከቤተክርስቲያን ኅብረት አይነጥላቸውም። እንደውም እንደደመና በዙሪያችን ከበውን ምሳሌነታቸውን ያሳዩናል ይማልዱልናልም። (ዕብ 12:1፣ ራዕ 6:10)

የቤተክርስቲያን አንድነት የሚመነጨው ትንሳኤና ሕይወት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ግንድነት ላይ ነው። በስሙ የሚያምኑ ሁሉ ቅርንጫፎቹ ናቸው። ፍሬ ማፍራትን እንቢ ካላሉ በስተቀር የትኛውም ኃይል ከግንዱ ክርስቶስ ሊያላቅቃቸው አይችልም። (ዮሐ 15:1-5)  በዕለተ ሐሙስ ጸሎቱ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያኖች አንድነት የዘለዓለማዊው የቅድስት ሥላሴ አንድነት (የፈቃድ፣ የሀሳብ፣ የስልጣን) መልክ መሆኑን ይነግረናል:- “..ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።.…እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።…” ዮሐ 17:11-23 ። ለዛም ነው ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር በማስገዛት በሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው በስሙ ያመኑ ሁሉ በአንድ ልብ ነበሩ የተባለው።  ሐዋ 1:14፣ 2:1፣ 4:24፣ 5:12፣ 15:26። ያም ልብ የክርስቶስ ልብ ነው። 1ቆሮ 2:16።

ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተች ናት። ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትን በሚገልፅ መሠረተ እምነት ላይ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ፡ ጴጥሮስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ሲመሰክር አንተ አለት (በግሪኩ Πέτρος – ጴጥሮስ) ትባላለህ ካለው በኋላ ምስክርነቱን በሴት አንቀጽ በዚህችም አለት (በግሪኩ πέτρα – ጴጥራ ) ቤተክርስቲያኔን እመሰርታለሁ ብሎ ተናግሯል  ። የመመስረቻው አለት ጴጥሮስን ከሰየመበት አለት ተለይቶ በሴት አንቀጽ መነገሩ ሐዋርያው በተናገራት የእግዚአብሔር ቃል እንጂ በራሱ  በሐዋርያው ላይ የተመሠረተች አለመሆኑን ይነግረናል (ማቴ 16: 15-18)። ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ተመስርታለች ስንል ምን ማለታችን ነው የሚል ካለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚናገሩ የነቢያትና የሐዋርያት፡ የመጻሕፍትም ሆነ የትውፊት ትምህርቶች የቤተክርስቲያን መሠረቶች ናቸው።

ራሷ ክርስቶስ ነው እሷም አካሉ ናት። የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ግንኙነት በዘመናት ውስጥ ለአይን ጥቅሻ እንኳን የተቋረጠ አይደለም። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ  “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴዎስ 28፥20 ብሎ እንደተናገረው ለቅፅበት እንኳን እርሱ ቤተክርስቲያንን ሊተዋት አይችልም። ከክርስቶስ የተለየች ቤተክርስቲያን ትሞታለች ምክንያቱም ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራሷ እርሷም አካሉ ናትና። አንዳንዶች ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው ስንል ምሳሌ (Metaphor) አድርገው ይወስዱታል ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም። ብርሃነ አለም ጳውሎስ በኤፌሶን የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ስለ ክርስቶስ ሕማም ከተናገረ በኋላ  “ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” ኤፌሶን 1፥22 ብሎ ራስነቱ የምሳሌ ሳይሆን የእውነት መሆኑን ያስረዳናል። ለአካሉ ራስ እንደመሆኑ መጠን በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርስን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ እንደደረሰ ይቆጥረዋል።  ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በቀደመ ዘመኑ አስተውሎታል። ከክርስቶስ እርገት በኋላ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሲፋጠን የነበረው ሳውል (በቀድሞ ስሙ) በታላቅ ብርሃን ውስጥ የገጠመው አምላካዊ ወቀሳ “ለምን ቤተክርስቲያንን ታሳድዳለህ” ሳይሆን “ለምን ታሳድደኛለህ” የሚል ነበር ምክንያቱም የቀድሞው ሳውል ያሳደደው ክርስቶስ ራሱ የሆነላትን ቤተክርስቲያንን ነውና። (ሐዋ 9:1-6) ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ራስነትን በፍፁም ልቧ የምትቀበለው በመሆኑ  የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የፖፕ የበላይነት (ራስነት) ትቃወማለች። ቤተክርስቲያን አካባቢያዊ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት (የኢትዮጵያ፣ የህንድ፣ የግብፅ፣ የሶሪያ፣ የአርመን፣ የኤርትራ ፓትሪያርክ) እንጂ ሁሉ አቀፍ ምድራዊ ራስ/አባት የላትም ምክንያቱም አለማቀፋዊ አባቷ፣ ሊቀካህኗና ራሷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና።

ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራናት። ቤተክርስቲያንን የሚያመለክቱ ቃላት የሚገለፁት በሴት ፆታ ነው። ይሄም በክርስቶስ አባትነትና ሙሽራነት ትይዩ ያለችው ቤተክርስቲያን የምዕመናን እናትና ሙሽራ ስለሆነች ነው። ሙሽራው ክርስቶስ ከእርሷ ጋር ነውና ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ ናት /ዮሐ 3:29/ በመሆኑም ሙሽራ ለሙሽሪት ባለው ፍቅር መጠን ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ተወዳለች እርሱም ነፍስን አሳልፎ እስከመስጠት ያለ ነው። (2ቆሮ 11፣ ኤፌ 5) የቤተክርስቲያን ሙሽርነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን በኋላም በሐዲስ ኪዳን የተገለጠ መለኮታዊ ሀሳብ ነው። ባለ ራዕዩ ዮሐንስም በዮሐንስ ራዕይ ለታረደው በግ ሙሽራ ትሆን ዘንድ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም እንደወረደችና ይህችም የቅዱሳን ህብረት መሆኗን ይናገራል። (ራዕ 19-21)

ቤተክርስቲያን የምሥጢራት መፈፀሚያ ናት። ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየውና አማናዊነቱ የሚገለጠው በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ በሚገኝባቸው የጥምቀት፣ የሜሮን፣ የቁርባን፣ የንስሐ፣ የክህነት፣ የተክሊልና የቀንዲል ምሥጢራት ነው። እነዚህ ምሥጢራት አንድን ሰው አስቀድሞ ክርስቲያን በማድረግ በቤተክርስቲያን በኩል ከክርስቶስ ጋር አንድ ያደርጉታል። ይኸውም መንግስቱን መውረስ ነው። ነገር ግን ከእነዚህ ምሥጢራት አንዳቸውም በነጠላ ቁጥር ሊፈፀሙ አይችሉም። የግድ የአማንያንን ኅብረት ይጠይቃሉ በመሆኑም በአካለ ሥጋም ሆነ በአካለ ነፍስ ያሉ ምዕመናን ሊገኙ ይገባል። ከዛም ባሻገር ምሥጢራቱን የሚመራው አካል በክርስቶስ ለቤተክርስቲያን በተሰጠ ስልጣነ ክህነት ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ የተሾመ መሆን ይኖርበታል። ለዛም ነው ሐዋርያት መሰባሰብን ቁልፍ አድርገው የሚያስተምሩት (ሐዋ 15:6፣ 1ቆሮ 11) የመሰባሰቡ አስፈላጊነት “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” ማቴ 18፥20 የሚለው የማይሻር አምላካዊ ቃል ነው በመሆኑም ምሥጢራቱን የሚፈጽሙ ሁሉ በመሰባሰብ የሚታየውን አገልግሎት አማናዊ ያደርገው ዘንድ በመሐላቸው ያለውን ክርስቶስ ይጠይቁታል።

ይቆየን

አባ ሙሴ ጸሊም

አንድ በግ በአንድ ጊዜ ጨርሶ እንደሚበላና አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ እንደ ሚጠጣ ስለ እርሱ እራሱ ተነግሯል። እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ በሥራውም ኃይለኛ የነበረ ይበላና ይጠጣ፣ ይቀማና ያመነዝር ነበር ይገድልም የነበረ ማንም ሊቋቋመውም የማይችለው ነበርና ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል። እርሱ ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ የነበረ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ “ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ” በልቡም “የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ” የሚል ነበር። አባ ሙሴ ጸሊም።
ከዚህም በኋላ በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማና ተነሣ ። ሰይፉንም ታጥቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ።በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው። አባ ኤስድሮስም ፈራው። ሙሴ ጸሊምም “እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ” ሲለው አባ ኤስድሮስ ወደ አባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው። እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረውና “ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ።” ብሎ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኰሰው ። ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ። ሰይጣንም ቀድሞ ሲሠራው በነበረ በመብሉና በመጠጡ በዝሙቱም ይዋጋው እርሱም በራሱ ላይ የሚደርስበትን ሁሉ ለአባ ኤስድሮስ ይነግረው ነበር። በዚህም ጊዜ አባ ኤስድሮስ አጽናንቶ ሊሠራው የሚገባውን ያስተምረው ነበር።
ከገድሉ ብዛትም የተነሣ አረጋውያን መነኰሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ ከሩቅ ቦታ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር። እንዲህ እያደረገ በመጋደል በብዙ ዘመናት ኖረ። ታዲያም ሰይጣን በእርሱ ቀንቶ በእግሩ ውስጥ አስጨናቂ የሆነ አመታት መታው ተኝቶም እየተጨነቀ ብዙ ቀን ታመመ።
ከዚህም በኋላ የመታውና የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐውቆ ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቀ ዕንጨት እስኪሆን ድረስ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን አበዛ። እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አይቶ ከደዌው ፈወሰው የሰይጣንንም ጦር ከእርሱ አራቀለት የመንፈስም ጸጋ አደረበት ወደ እርሱም አምስት መቶ ወንድሞች መነኰሳት ተሰበሰቡ በእነርሱም ላይ አበ ምኔት ሆነ።
ከዚህም በኋላ ቅስና ሊሾሙት መረጡት በቤተ መቅደስም ሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ በአቆሙት ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱም አልፈቀደም ነበርና አረጋውያኑን “ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት ከዚህ አውጡት” አላቸው እነርሱም “መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ” በማለት ራሱን እየገሠጸ ወጣ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሳቱ ጠራውና እጁን በላዩ ጭኖ ቅስና ሾመው እንዲህም አለው “ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ”።
ከእለታት በአንዲት ዕለት ቅዱሳን አረጋውያን ወደርሱ መጡ ። ውኃ አልነበረውምና ከበዓቱ ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ይል ነበር ከዚህም በኋላም ብዙ ዝናም ዘንሞ ጒድጓዶችን ሁሉ ሞላ። አረጋውያንም ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ትል ነበር ብለው ሲጠየቁት “እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን” ነበር ያላቸው።
አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ ሔደ አባ መቃርስም የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ” አላቸው አባ ሙሴም “አባቴ ሆይ ምናልባት እኔ እሆናለሁ በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው የሚል ጽሑፍ አለና” ብሎ መለሰ።
ከዚህም በኋላ የበርበር ሰዎች መጡ አባ ሙሴም ከእርሱ ጋራ ያሉትን መነኰሳት “እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ” አላቸው እነርሱም “አባታችን አንተስ አትሸሽምን” ሲሉት “በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል ስለ ሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ” እንዳለም ወዲያውኑም የበርበር ሰዎች ገብተው በሰይፍ ገደሉት መሸሽ ስላልፈለጉ ከእርሱ ጋር ሰባት መነኰሳትም ተገደሉ። አንዱ መነኮስ ግን ከምንጣፍ ውስጥ ተሠወረ ። የእግዚአብሔር መልአክ በእጁ አክሊል ይዞ ባየ ጊዜ ግን ከተሠወረበት ወጣና በበርበር ሰዎች ተገደለ። የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበለ።
ወንድሞች ሆይ ከሀዲና ነፍሰ ገዳይ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ለውጣ ደግ አባት መምህርና የሚያጽናና ለመነኰሳትም ሥርዓትን የሠራ ካህንና በሁሉም አብያተ ክርስቲያን ስሙ እንዲጠራ እንዳደረገችው የንስሐን ኃይሏን ተመልከቱ።ሥጋው በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ ለዘላለም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ይታያሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የሰኔ 24 ስንክሳር።

ገሪማ ገረምከኒ


የሮም ንጉሠ ነገሥት ከነበሩት ወላጆቹ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም አማላጅነት ተወልዶ ይስሐቅ የተባለው ፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ተምሮም ዲቁናን የተሾመውና በአባቱም ዙፋን ላይ በንግሥና በቅንነት እየገዛ ሰባት ዓመት የኖረው ቅዱስ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወጥቶ ወደ ምንኩስና የሄደው በዋሻ በሚኖረው አባ ጰንጠሌዎን መልእክት ነበር። የሚገርመው በመንገዱ ላይ ጌታችን የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጦለት ብርሃናውያን በሆኑ ክንፎቹም ተሸክሞ የዐሥር ወር የሚሆነውን መንገድ በሦስት ሰዓት አስፈጽሞ በአባ ጰንጠሌዎንም ደጅ አቁሞታል።አባ ጰንጠሌዎንም ቅዱስ ይስሐቅን ተቀብሎ በበዓቱም አስገብቶ የምንኲስና ልብስን ካለበሰው በኋላ፡ ይስሐቅ በጾም በጸሎትና በስግደት ተጠምዶ ቆዳው ከዐፅሙ እስከሚጣበቅ ተጋድሏል።


ወደ መደራ ሄዶም በእግዚአብሔር ኃይል ድንቅና ተአምር እያደረገ በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማስወጣት ብዙ ዘመን ኖሯል። በአንዲት ዕለትም በጥዋት ሥንዴ ዘራ በሠርክም መሥዋትን አሳረገ። በማግሥቱም በግራር ዛፍ ላይ በሮችን አውጥቶ የሥንዴውን ነዶ አበራ የሰባ ሰባት የእንቅብ መስፈሪያም ሆነ። ሁለተኛም የወይን ሀረግ በአለት ላይ ተከለ ወዲያውም በቀለች አበበችና አፈራች በእርሷም መሥዋዕትን አሳረገ። አንዲት ቀንም ሲጽፍ መሸና ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ በቦታውም እንዲቆም በማዘዝ ጽሕፈቱንም እስኪጨርስ አቆመው። ምራቁንም ትፍ ባለበት ዘንድ ጠበል ፈልቆ እስከ ዛሬ ለበሽተኞች ፈውስ ሆኖ ይኖራል።
ታዲያ በአንዲት ዕለት ሰዎች ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው “ቀሲስ ይስሐቅ እኮ ከበላ በኋላ የቁርባን ቅዳሴ ቀደሰ” ብለው ነገሩት አባ ጰንጠሌዎንም ወደርሱ ሄዶ “ልጄ ይስሐቅ ሆይ ምሥጢር ስለ አለኝ ከአጠገባችን ሰዎችን አስገልል” አለው ይስሐቅም “ሰዎችን ተውና ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ይገለሉ” አለ። ወዲያውኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ሸሹ። አባ ጰንጠሌዎንም “ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ” አለ ስለዚህም ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ገሪማ ተባለ።


መልካም ተጋድሎንና የቀና አካሔዱን በፈፀመ ጊዜ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት “ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያው ለሚያደርግ፣ ገድሉንም ለሚጽፍና ለሚያጽፍ፣ ለሚያነበውና ለሚተረጉመው ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ዳግመኛም “የተራበውን ላበላ፣ የተጠማውንም ላጠጣ እኔ የሕይወት እንጀራን እመግበዋለሁ የድኅነት ጽዋንም አጠጣዋለሁ” አለው። በቤተ ክርስቲያንህም በማኅሌት ያመሰገነውንና የጸለየውን እኔ የመላእክትን ምስጋና አሰማዋለሁ የተራቆተውንም ለሚያለብስ የብልህ እጅ ያልሠራው የብርሃን ግምጃን አለብሰዋለሁ ነፍሱም ከሥጋው በምትለይ ጊዜ የጨለማ መላእክት አይቀርቡትም። የብርሃን መላእክትም በዙሪያው አቆማቸዋለሁ። በስምህም ቤተ ክርስቲያን ለሠራ በሰማያት አርባ ሰባት የብርሃን ቦታዎችን እኔ እሰጠዋለሁ፣ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ የሚሰጠውንም እኔ በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ፣ ቦታህን የሚያከብረውንም እኔ በመንግሥቴ አከብረዋለሁ፣ ጠላቶች አጋንንትን ረግጦ የሚገዛበትንም እሰጠዋለሁ”። ብሎ ቃልኪዳን ገብቶለታል።
አባ ገሪማም “ይህን ታላቅ ሀብት በቸርነትህ ብዛት የሰጠኸኝ አቤቱ ስምህ ይክበር ይመስገን ግን ጌታዬ ሆይ መታሰቢያዬን ላደረገ፣ ገድሌንም ለጻፈ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ” አለ። መድኃኒታችንም “እስከ ዐሥራ ሁለት ትውልድ እምርረዋለሁ” ብሎታል። አባ ገሪማም መድኃኒታችንን “ልጆች ባይኖሩትስ ምን ታደርግለታለህ” ባለው ጊዜ መድኃኒታችንም “ዐሥራ ሁለት ዕጽፍ ክብር እሰጠዋለሁ” ብሎ መልሶለታል።
ዳግመኛም “የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለሁ” አለውና ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኝቶ ሰኔ 17 ቀንም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቆ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል።


ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም አባ ገሪማ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አቤቱ በቅዱስ መንፈስህ አንጻኝ

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

ጌታ ሆይ በበዓለ ሀምሳ ቅዱስ መንፈስህን ልከህ ሐዋርያትን አጽንተህ አንጽተህ ሰባ ሁለት ቋንቋዎችን ገልጸህ ከዓለም የተሰበሰቡ በጸሎት የተጉ ሦስት ሺሕ ሰዎችን ለራስህ መረጥክበት፡፡ በብሉይ ኪዳኑ በዓለ ኀምሳ ቀድሞ ከደረሰው እሸቱን መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡልህ እንደምትቀበልበት ሥርዓት ዛሬም የሐዲስ ኪዳኗን ቤተ ክርስቲያን ሦስት ሺሕ ምእመናን ለራስህ እሸት አድርገህ ተቀበልክ፡፡

እነዚያ ሰዎች በእውነት ምንኛ የታደሉ ናቸው፡፡ ከእነርሱ ቀጥሎ የሰማዕታትን አዝመራ ልታጭድ፤ የጻድቃንንም ሰብል በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ ባልከው ቦታ ልትሰበስብ፣ የሊቃውንትንም ነዶ በዐውደ ምሕረት አደባባይህ ልታከማች፣ የንጹሐን ምእመናንን ክምርም በዐውድማሕ ልትከምር መሆኑን ዛሬ በተቀበልካቸው ቀድመው በደረሱ እሸቶችህ አሳወቅኸን፡፡ ገና ሳይሰበክ ያመኑ፣ ገዳማት ሳይመሠረቱ በጸሎት የተጉ፣ ሐዋርያት ወደ እንኳን ወደ ዐለም ወደ እሥራኤል ቤት ሳይወጡ እነዚህ ከዓለም ሁሉ መጥተው ቀድመው የተሰበሰቡ ምንኛ የተመረጡ ናቸው፡፡ በሐዋርያት የወረደውን መንፈስህን አይተው ያደነቁ፣ አይሁድ ሐዋርያትን በጉሽ የወይን ጠጅ ሰክረዋል ሲሉ ሰምተው ያልደነገጡ፣ ቋንቋቻቸውን ሰምተው ጸጋህን የተረዱ፣ በዚች ቀን ተጠምቀው የመጀመሪያዋን ቅድስት ጉባኤ የመሠረቱት እነዚህ አማንያን በእውነት ምንኛ የተመረጡ ናቸው፡፡ በርግጥም ከሐዋርያት ስብከት በፊት የደረሱ እውነተኛ የመንፈስ ቅዱስ እሸቶች፡፡

ጌታ ሆይ እኔ ግን እንኳን ከሰው ከዓለም ቀድሜ ለፍሬ ለእሸትነት መሥዋዕት ልደርስ ከአዝመራውም የምገኝ አይመሰለኝም፡፡ ነገር ግን ቸርነትህን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በቃርሚያ ለቃሚ እንኳ ሰብሰብህ ለትንሽ ዐውድማህ እንድታበቃኝ እለምንሃለሁ፡፡ አዎን እኔ ለጽድቅ አዝመራ አጫጆች ለእጃቸው የማልጨበጥ፣ ለዐይናቸው የማልገባ ቃርሚያ እንኳን ከሆንኩ ትልቅ እድል ነው፤ ሩትን ልክህ እንደምትሰበስበን አውቃለሁና፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ ገበሬዎች ሐዋርያት በአንድ ቀን እንዳደረሷቸው ለእሸት መሥዋዕት ዛሬ እንደቀረቡልህ ሦስት ሺሕ ትጉኃን ምእመናን አድርገህ ተቀበለኝ አልልህም፤ ነገር ግን ገበሬዎች ባይሰበስቧቸውም እንደ ሩት ያሉ የተናቁ ግፉዓን ከሚለቅሟቸው ቃርሚያዎች አንዱ መሆንን ግን አትንፈገኝ፡፡

ጌታ ሆይ በዕለተ በዓለ ኀምሳ ትጓሃኑ ምእመናን እያዩት የወረደውን በእሳት ላንቃ አምሳል የሚወርድ ስጦታህን አልጠይቅህም፤ በእኔ ላይ የሰለጠነውን የዓለምን መንፈስ እንድታርቅልኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ በሰባ ሁለት ወይም በርከት ያሉ ቋንቋዎችን መናገርን እንድትሰጠኝም እኔ አልጠይቅህም፣ በምሰማቸው ቋንቋዎች መልካሙን መስማትና ማስተዋልን እንድትሰጠኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ በቋንቋ ዐለምን ለማገልግል አልጠይቅህም፣ በቋንቋ ምክንያት እንዳልጠፋና ሌሎችንም እንዳላጠፋ፤ የሌሎችን ቋንቋ እንዳልጠላ፣ ቋንቋዬን ጠሉ ብዬም ሰዎችን እንዳልጠላ ትረዳኝና ልቡናዬንም ትጠብቅልኝ ዘንድ ግን በእውነት እለምንሃለሁ፡፡ አቤቱ ባለብዙ ቋንቋዎችን አንድ ማድረገን ባልችል በቋንቋቸው ምክንያት መከፋፈልና መለያየትን ማምጣትን ግን ከእኔ ፈጽመህ አስወግድልኝ፡፡

አምላኬ ሆይ ዛሬ እንደ ሐዋርያትህ በመንፈስ ቅዱስ ልሞላ አልልህም፤ ለእኔ በውስጤ የሞላውን ቆሻሻ ካስወገድክልኝ በእጅጉ ይበቃኛል፡፡ የእሳት ላንቃዎች ይውረዱብኝ አልልህም፤ ከውስጤ እየጨሰ የሚወጣውን የንዴት፣ የብስጭትና የስድብ እሳት ካበረድክልኝ ይበቃኛል፡፡ በቅዱስ ያዕቆብ አድረህ “እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል” /ያዕ 3 ፤ 5 – 6/ ስትል የገለጽከውን የሚያቃጥለኝን ጎጅ እሳቴን ካጠፋህልኝ ነፍሴ ትልቅ ዕረፍት ታገኛለች። እንደ ሐዋርያት በመንፈስ ሆኖ ጥበብን መናገርንም ዛሬ አልተይቅህም፡፡ ሳላውቀው መንፈስ ቅዱስን ከመስደብ እንድትጠብቀኝ፤ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ ኃጢአትን ሊያስተሠርዩ በተሾሙ ላይ አፌን ከመክፈት በእነርሱ ያደረ መንፈስ ቅዱስንም ከመስደብ እንድትጠብቀኝ ግን እለምሃለሁ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልሰከር አልልህም፤ በነገር ከመስከር፣ በስሜት ከመናጥ አውጥተህ በመንፈስና በእውነት ከሚያመልኩህ እንድትደምረኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ ነቢይ ኤልሣዕ በሰማርያ ሆኖ በሶርያ የሚመከረውን ያውቅ እንደነበረ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታህ በዓለም ያለውን የተሰወረውን ሁሉ ልወቅ አልልህም፡፡ “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” / ዮሐ 16 ፤ 13/ ባልከው ቃል ኪዳን መሠረት በስምህ ከሚያጨበረብሩት ጠብቀህ ወደ እውነት ብቻ እንድትመራኝ ግን እለምነሃለሁ፡፡

ጌታ ሆይ ከጥፋት ጎዳና ከመልሰከኝ ለእኔ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ እንደ አይሁድ ካለ ሥጋዊ ቅንዓት አውጥተህ እንደ ዳዊት ወዳለ መንፈሳዊ ቅንዓት አድርሰኝ፡፡ ከሐዋርያትህ ጋር ቆሜ እንደ ሲሞን መሠርይ ባለ የስህተት መንገድ መንፈስህንና ጸጋህን ከመመኘትና በዚያም ከሚመጣ ርግማን ጠብቀኝ /ሐዋ 5፣/፡፡ ይልቁንም ቤተ መቅደስ ተጠርተው መገኘት ባይችሉም በቤታቸው ሳሉ ልባቸውን አይተህ ጸጋህን እንደ ሰጠሃቸው እንደ ኤልዳድንና እንደ ሞዳድ /ዘኍ 11 ፤ 26/ የመሆንን የትሕትና መንፈስ አድለኝ፡፡ ጌታ ሆይ እንደ ይሁዳ ኖሬ ኖሬ መጨረሻ ላይ ከመውጣት ጠብቀኝ፡፡ ይልቁንም እንደ ፈያታዊ ዘየማን ባለቀች የጭነቅ ሰዓት እንኳ ልቤን ለንስሐ አንቃልኝ ፡፡ ጌታዬ ሆይ ለአገልግሎትህና ለተልእኮ በወጣሁበት እንደ ዴማስ መንገድ ላይ ከመጥፋት አድነኝ፣ ይልቁንም እንደ ጳውሎስ ለጥፋት ከምፈጥንበት ጎዳና መልሰህ ከመንጋህ ደርበኝ እንጂ፡፡ በታላቅ ነቢይ ቀብተህ አክብረኸው ሳለ ለሥጋውና ለጠቅሙ ቀንቶ እንደናቅኸው እንደ ሳዖል ከመሆን ጠብቀኝ፤ ይልቁንም ሚስቱ ሜልኮል እስክትስቅበት ድረስ ራሱን ጥሎ ለክብርህ ብሎ በተራው ሕዝብ ፊት እንደ ዘፈነው እንደ ዳዊት የማስተዋልን መንፈስ አድለኝ፡፡

ጌታ ሆይ እኔ በመንፈስ ሆኜ መናገርን ዛሬ አልጠይቅህም፤ በመንፈስ ሆኜ ስለኃጢአቴ ማዘንን እንድትሰጠኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ ጌታ ሆይ እንደ ሕዝቅኤል እንደ ነቢያትም ሁሉ መንፈስህ መጥቶ ይዳስሰኝ፣ ቀጥ አድርጎም ያቁመኝ አልልህም /ሕዝ 3 ፤ 12/፡፡ የዳዊትን ቃል ተውሼ ግን አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ” እልሃለሁ /መዝ 50፤ 1-2/፡፡ እንደ እስጢፋኖስ አድርገህ መንፈስ ቅዱስን ሙላብኝም አልልህም፡፡ ነገር ግን በተነሳሂው በዳዊት ቃል “ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” እልሃለሁ መዝ 50 ፤ 11/።

ጌታ ሆይ ብዙ ነገር እየዘረዘርኩ ዛሬ ብዙ ስጦታ አልጠይቅህም፡፡ የምጠይቅህ አንድ ነገር ነው፤ በእውነት ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፡፡ “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። 4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ” መዝ 51 ፤ 2 – 3/። “ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ” /መዝ 19፥12/ ። “አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ” /መዝ

25 ፤ 11/። “አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና / መዝ 39፥12/። “እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ” /መዝ 69፥29/። “አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ። የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና። አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና። አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ” /መዝ 86 ፤ 3 – 6/ ። “በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ” /መዝ 51 ፤ 7 – 12/። ጌታ ሆይ በሐዋርያትህ ላይ ባወረድከው፣ በቤተ ክርሰቲያንህ አድሮ በሚኖረው፣ እስከ ዕለተ ምጽአት ከወዳጆችህ በማይለየው በቅዱስ መንፈስህ አኔን አንጻኝ፤ አሜን፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

እግዚአብሔር ምስሌነ
@EMislene

አካልና ጥላ : መግቢያ

“እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።”
ቆላ 2፥17

ሐዋርያው ቅዱስ ጳወሎስ በታናሿ እስያ ለሚገኙ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ላይ መገረዝ በጥምቀት እንደተተካ በተናገረበት አንቀፁ፡ ስለ በዓላትም ያነሳና የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች፣ ሥርዓቶች በሙሉ ሊመጣ ያለው የክርስቶስ ጥላ እንደሆኑ ያነሳል።

በእርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ እንደውሃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ ካለምንም በድንገት ብቅ ያለ አይደለም። መምህራችን ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ያስተማሯቸው ትምህርቶች አስቀድሞ  ለከበሩ አባቶች ለእነ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከተገለጠው እውነት ጋር የሚስማሙ እንጂ እንግዳ ትምህርቶች አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ከእነሱ ጋር ሊከራከሩ የወደዱ አይሁዶችን ከመጽሐፋቸው በመጥቀስ ዝም ያሰኟቸው ነበር። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው “ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።” ማቴ 22፥29 ብሎ የተናገረው ለዚሁ ነው።

በመሆኑም ኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሃይማኖት መረዳት አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚጓዝ ሳይሆን የብሉይ ኪዳን ጽሁፎችን ከሐዲስ ኪዳኑ ጋር እያስማሙ በኅሊና አበው የመጓዝ ጥበብ ነው።

የብሉይ ኪዳን አስፈላጊነት ብዙዎች እንደሚያነሱት የሥነ ፍጥረት ትረካን ለመረዳት፣ የቀደሙ አበውን ለማወቅ፣ የእግዚአብሔርን ጠብቆት ለመረዳት ብቻ አይደለም በእርግጥ ገፀ ንባቡ የሚነግረን ይሄን ቢሆንም በውስጡ እጅግ ድንቅ የሆነ የነገረ ድኅነት ሃሳቦችን ይዞ ይነሳል።

በሥነፍጥረት በአዳም አፈጣጠር ውስጥ ካለው የዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ሥጋ መሆን ጀምሮ፣ በአቤል ደም፣ በኖህ መርከብ፣ በይስሐቅ መሰዋት፣ በሙሴ መነሳት ወዘተ ሥጋዌውን በብዙ ምሳሌያት ይናገራል። በምሳሌ ብቻም ግን አይደለም በዘመናት ባናገራቸው ነብያት በኩል አይተው የጻፉት በሚመስል ልክ ይመጣ ያለውን መሲህ ክርስቶስን ይተርኩታል። ወንጌላውያኑም የክርስቶስ ኢየሱስን ሥጋዌ በዘገቡባቸው ሥፍራዎች ላይ በነቢይም / በመጽሐፍም እንደተናገረው ሲሉ የሚያነሱት ይሄንን ነው። ይሄ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መገናዘብ ግን በግላዊ መረዳት የሚደረስበት አይደለም። ይልቁንም ከቀደሙ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር በሚስማማ አንድ ልብ እንጂ።

እርሱም ሐዋርያው እንደሚለው ሁሉን አንድ            የሚያደርግ የክርስቶስ ልብ ነው (1ኛ ቆሮ 2:16) በመሆኑም ይህ የክርስቶስ ልብ (ሃሳብ) ደግሞ በብቸኝነት የሚገኘው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነውና ከቀደሙት አባቶች ጋር በትርጓሜና በጸሎት መተባበርን ይጠይቃል። ምክንያቱም አርዮስን ጨምሮ ብዙዎች የብሉይ ኪዳንን ገፀ ንባብ በገዛ ፍላጎታቸው ልክ በመተርጓማቸው ከክርስቶስ አንድነት እንዲለዩ ሆነዋል።

በመሆኑም በዚህ አምዳችን በየሳምንቱ አርብ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ሀሳቦች እንዴት ሊመጣ ላለው አካል ክርስቶስ ጥላ እንደሆኑ እንመለከታለን። የአምዱ አላማ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብቻ ባለመሆኑ በውስጡ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ድህነት፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ አበውና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ይዳሰሱበታል።

አምዱ ዘወትር አርብ የመሆኑ ምሥጢር በዕለተ አርብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ወደተናገራቸው ቃላት ይወስደናል። በዚህች ዕለት ከተናገራቸው ቃላት መካከል በዮሐንስ ወንጌል የተዘገበው የመጨረሻው ቃል “ተፈፀመ”  ነው። የቤተክርስቲያን መተርጉማን ይሄን ሲተረጉሙ ከሚያነሷቸው ትርጓሜዎች አንዱ “ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ በኦሪትና በነብያት የተነገሩት ሁሉ ተፈጽመዋልና ተፈፀመ አለ” የሚል ነው።  በመሆኑም ብሉይ ኪዳናዊው ድንግዝግዝ ጥላ ወለል ብሎ በተገለጠበት በዕለተ አርብ በማዕከለ ዘመን ላይ ቆመን ወደፊትና ወደ ኋላ እንጓዛለን።

ቀጣይ ሳምንት 👉 “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም ? 1ቆሮ 11:15 “

ይቆየን

ቤተክርስቲያን ምንድን ነው? /የቃሉ ትርጉም/

ብዙዎች ቤተክርስቲያን ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የአድባራትና የገዳማት ህንፃ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያን ማን ናት ተብሎ ለሚጠየቀው ጥያቄ እያንዳንዱ ክርስቲያን ምዕመንን ብሎ የሚመልስም አይጠፋም።  በእርግጥም ከቤተክርስቲያን ትርጓሜ ስፋት አንፃር እነዚህ ሁለቱም መልሶች ትክክል ናቸው። ነገር ግን ለህንፃውም ሆነ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንነት መሠረቱ ግን በክርስቶስ ራስነት ውስጥ ያለው የአማንያን ሕብረት፣ መሰባሰብ፣ ወገን ወይም ጉባኤን ነው።ቤተ ክርስቲያን የሚለው የግእዝ ቃል የሚነግረንም ይሄ ነው። በሀገራችን የሚኖሩ አይሁድን ቤተ አይሁድ፣ ቤተ እስራኤል እንደምንለው ቤተ ክርስቲያንም የክርስቲያን ህብረት፣ የክርስቲያን ጉባኤ፣ የክርስቲያን ወገን (ዘር) ማለት ነው።መጽሐፍ ቅዱስ በተፃፈባቸው ጥንታውያን የዕብራይስጥና የግሪክ (ጽርዕ) ቋንቋዎችም የቤተክርስቲያን አቻ ትርጉሞች የሚያሳዩት ይሄንኑ ነው።

በዕብራይስጥ ቋንቋ ሁለት ቃላት ቤተክርስቲያን የሚለውን ቃል የሚተኩ ሲሆን አንደኛው “עֵדָה” (አይ’ዳው) ሲሆን መሰባሰብ፣ ጉባኤ፣ ቤተሰብ ወይም ሕብረት ማለት ነው። ሁለተኛውም የዕብራይስጡ ቃል “קָהַל” (ቃ’ዋል) ተመሳሳይ ትርጓሜ አለው። የግሪኩ ἐκκλησία (አቅሌሲያ)ም በተመሳሳይ መሰብሰብን፣ ጉባኤንና ህብረትን አመላካች ነው።κυριακός (ኩሪ’ያኮስ) የሚለው የግሪክ ቃል ደግሞ በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ከአቅሌሲያ ጋር በትይዩ ያገለግል የነበረ ቃል ሲሆን የጌታ ቤት፣ የክርስቲያኖች ቤት የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ዛሬ ላይ ለምንጠቀመው የግእዙ ቤተ ክርስቲያን ወይም ለእንግሊዘኛው CHURCH መነሻ ቃል እንደሆነ ይታመናል።

ከላይ ለማየት እንደምንችለው የዕብራይስጡም፣ የግሪኩም፣ የግእዙም ሆነ የእንግሊዝኛው ስም በብዛት ትኩረት የሚያደርጉት ከሦስቱ የቤተክርስቲያን ትርጓሜዎች (ከህንፃው፣ ከእያንዳንዱ ምዕመንና ሕብረቱ) ላይ ነው። የዚህ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱን ማለትም የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንነትና የህንፃው ቤተክርስቲያንነት የሚመነጨው በክርስቶስ ራስነት በተሰበሰቡ የምዕመናን ህብረት በመሆኑ ነው። አንድ ምዕመን በጥምቀት በሚገኝ ልጅነት ከቤተክርስቲያን ሕብረት ጋር እስካልተዋሃደና የሕብረቱ አካል እስካልሆነ ድረስ ቤተክርስቲያን መሆን አይችልም በተመሳሳይም አንድ ህንፃ ቤተክርስቲያን ለመባል የክርስቲያኖች ሕብረት የሚሰባሰብበትና በአንድነት ቅዱስ ምሥጢራትን የሚፈጽሙበት ሊሆን ይገባል።

/እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ በቀጣዩ ሳምንት የቤተክርስቲያንን ምንነት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሊቃውንት አንፃር እንዳስሳለን/ ይቆየን።

ማንም ሲመግብህ አላየሁም አባ ኑፊር ( Abba Nufeir the Anchorite)

አንድ የስድስት ዓመት ልጅ በገዳም ከመነኮሳት ጋር እየኖረ ሳለ እንደ ልጅነቱ ቶሎ ቶሎ መመገብ ያስፈልገው ስለነበር ወደ ምግብ አብሳዩ እየሄደ ዳቦ፣ ዘይት እና ፍራፍሬ ይጠይቃል። ምግብ አብሳዩም ሁልጊዜ የሚጠይቀውን እየሰጠው ይዞ ይሄድ ነበር።
ታድያ አንድ ቀን የገዳሙ ምግብ አብሳይ ይሄ ልጅ ዳቦውን እየያዘ ወዴት ነው የሚሄደው ? ምን አልባት ዶሮ እየመገበበት ይሆን? በማለት ተገርሞ ሊመለከት ሕጻኑን ተከትሎት ሄደ ። ሕፃኑ ኑፊርም የተሰጠውን ዳቦ ይዞ ወደ ገዳሙ ቤተክርስቲያን በመግባት በሩን ሲዘጋው ምግብ አብሳዩም በመስኮት በኩል የሚሆነውን ይከታተል ጀመር። ሕፃኑም የተሰጠውን ዳቦ ወስዶ ጌታችን በእመቤታችን እቅፍ ሆኖ ወደ አለው ሥዕል ተጠግቶ ” እስካሁን ማንም ሲምግብህ አላየሁም ፤ ክርስቶስ ሆይ እኔ ግን ዛሬ ዳቦ አምጥቼልሀለሁ” ብሎ የያዘውን ዳቦ ወደ ሥዕሉ ሲዘረጋው ጌታችን ከሥዕሉ እጁን ዘርግቶ ዳቦውን ሲቀበለው ምግብ አብሳዩ ተመለከተ።
ምግብ አብሳዩ ባየው ነገር እጅግ ተደንቆና ተገርሞ ወደ አበ ምኔቱ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው። አበምኔቱም “ነገ መጥቶ ዳቦ ስጠኝ ብሎ ቢለምንህ እንዳትሰጠው ይልቁንም እስከ ትላንት ድርስ ስትመግበው የነበረው ልጅ ይስጥህ” በለው ብለው ያሰናብቱታል።ሕጻኑ ኑፊርም እንደለመደው በቀጣዩ ቀን ዳቦ ፍለጋ ወደ ምግብ አብሳዩ ሲሄድ አብሳዩም አበምኔቱ የነገሩትን ነገሮ ያሰናብተዋል ሕፃኑ ኑፊርም ወደ ገዳሙ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለው በሥዕለ አድህኖ ፊት ቆሞ ጌታችንን ” ክርስቶስ ዛሬ ዳቦ አላመጣሁልህም እንደውም እሱ ይስጥህ አሉኝ አንተ ግን ዳቦ ከየት ታመጣለህ ?” አለው ጌታችንም ከሥዕሉ እጁን ዘርግቶ እጅግ ግዙፍ የሆነና በጥዑም መአዛው ገዳሙን የሚያውድ ሰማያዊ ዳቦ ሰጠው።
ሕጻኑም ዳቦውን መሸከም ስላልተቻለው በዳቦው ጥዑም መዓዛ ከተሰበሰቡት መነኮሳት ሁሉቱ ቀርበው ያግዙት ጀምር። ይህ ድንቅ ተአምርም በገዳሙ እና በአካባቢው ሰው ሁሉ ተሰማ። የገዳሙም መነኮሳት ከዳቦው በልተው ጠገቡ። በሚበሉም ጊዜ ዳቦውም አይጎድልም ነበር። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የገዳሙ መነኮሳት ለሕፃኑ ትልቅ ክብር እና ተስፋ ኖራቸው። እያደገ ሲሄድ ቅድስናው እንደሚጨምር በማወቅ በፍቅር እና በተስፋ ይጠብቁት ነበር።
ይህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥዕለ አድህኖው በኩል ያናገረው ቅዱስ ሰው አባ ኑፊር ይባላል።ከሕጻንነታቸው ጀምሮ በግብፅ ሄርሞፖሊስ በምትባል ከተማ ውስጥ በምትገኝ ገዳም ከመነኮሳት ጋር ያደጉ ነበር።ገዳም ውስጥ ባደጉበት ጊዜ ቃለ እግዚአብሔር እና የምንኩስና ሕይወትን በሚገባ ተምረው አድገዋል። እድሜያቸው ከፍ ሲል የምነናን ሕይወት ልባቸው ስላሻተ የገዳሙን አበምኔት አስፈቅደው ወደ በረሀ ገብተው ለ60 ዓመታት ያህል የሰው ፊት ሳያዩ ከእግዚአብሔር ጋር በብሕትውና ኖረዋል።በበረሀ በሚኖሩበት ጊዜ ጢማቸው ሰውነታቸውን በመሸፈን እንደ ልብስ ሆኖ ያገለግላቸው ነበር። እረፍታቸው ሲቃረብ ልዑል እግዚአብሔር አባ በፍኖትዮስ የተባሉ አባትን ወደ አባ ኑፊር ላከ። አባ በፍኖትዮስም ከአባ ኑፊር ቅዱስ የሆነውን ተጋድሏቸውን ከሰሙ በኋላ ታሪካቸውን ጽፈው ለእኛ አስቀምጠውልናል።
አባ ኑፊር የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ በአባ በፍኖትዮስ እጅ በዛው በተጋደሉበት በረሀ ውስጥ ተቀብረዋል።
ከረድኤታቸው ያሳትፈን።
Father Stefanos Anagnostopoulos
Excerpt from [ “Explaining the Divine Liturgy” Byzantine Publishing House, 2005, pp. 251-252]