ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል

ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው:: ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት “ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት” ሲሉ ይገልጹታል::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-  በ፪ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር “አሮስ” የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደምግባት የሠመረላት፣ እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር:: አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል “እንስሳ ተያዘልን” ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: ሁለት ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ተይዘው ነበር። እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ፣ ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ፣ ወገባቸው እንደ ሰው፣ ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስለው:: እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና: አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው:: “ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት” አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት:: ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም “መፍቀሬ አብ – የአብ ወዳጅ” ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን : ልጁንና ሁለቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተጠመቀ::

አበው ካህናት እሱን “ኖኅ”፣ ሚስቱን “ታቦት” : ልጁን ደግሞ “መርቆሬዎስ” ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም “ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ / የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ” እንደ ማለት ነው:: ከዚያም ደስ እያላቸው፣ ክርስቶስን እያመለኩ፣ ነዳያንን እያሰቡ፣ ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ “ካላመጣሃቸው” አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ:: ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን ሁለቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል “እንቢ” በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::

በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን “ላግባሽ” ስላላት የ፭ ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው:: እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በኋላ ግን በሕፃኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ:: በዚያም ቤተ ክርስቲያን አንጾ፣ ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጎ፣ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::

ቅዱስ መርቆሬዎስ በጦርነትም እጅግ ኃያል፣ በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ፣ የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምእመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ:: ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: በማግስቱም “ምን ይሻላል?” ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ “እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻዬን እቋቋማቸዋለሁ” ቢል ሳቁበት:: እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን “ጠብ ይቅርባችሁ፤ በሰላም ሒዱ” ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ አልነበረም::

ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ “ድሉ የጣዖቶቼ የነ አጵሎን ነው” በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ:: በ፫ኛው ቀንም “ለጣዖት ሠዋ” የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው:: “ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል:: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ:: (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ እና ሀብትህ ለጥፋት ይሁንህ)” ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው:: ያም አልበቃ:: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት: “አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም:
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም:: አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም::” ያሉት::
    
ከዚያም ቅዱስ መርቆሬዎስን ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ፣ በግርፋት፣ በእሳት፣ በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::እርሱ ካረፈ በኋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኳል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፳፻ ዓ/ም እንደ ተወለደ፣ በ፳፻፳ ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፳፻፳፭ ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሐዋርያውያን አበው (ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም፣ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ቅዱስ ፖሊካርፐስ)

ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም፡ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተተካው ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም ከሊነስና አንክሌተስ ቀጥሎ ሦስተኛው የሮም ሊቀ ጳጳስ እንደነበር ቅዱስ ሄሬኔዎስ ይናገራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማንያ ወአሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚመደበው መጽሐፈ ቀለሜንጦስ ቅዱስ ቀለሜንጦስ ለሮም የላከው መልእክቱ ነበር። በመጽሐፉም ከሥነ-ፍጥረት ጀምሮ ነገረ-ሃይማኖትና ቀኖና ቤተክርስቲያን ይገኙበታል። ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥብቅና በመቆም ሐዋርያዊ ሥራውን እየሠራ ሳለ በጠራብሎሱ መሪ ከሮም ተወስዶ፣ ወታደሮች በባህር መካከል ጥለው ገድለውታል። በዓለ ዕረፍቱን ቤትክርስቲያን ኅዳር ፳፱ ታከብረዋለች።

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፡ ጌታችን ለሐዋርያት ሕፃኑ ቅዱስ አግናጥዮስን በመካከል ይዞ ስለ ትሕትና አስተምሯቸዋል። በኋላኛው ዘመንም በሐዋርያት በአንጾኪያ ጵጵስናን ተሾመ።  በትራጃን የንግስና ዘመን ትራጃን ምሥራቃውያንን ድል በመንሳቱ የጣኦት መሥዋዕትን ሊሰዋ ወደ አንጾኪያ ከተማ መጣ። ክርስቲያኖች ለጣዖት እንዲሰዉ ቢያስነግርም ቅዱስ አግናጥዮስ ምዕመናን ለጣዖት እንዳይሰግዱ መስዋዕትንም እንዳያቀርቡ ያስተምራቸው ነበር። በዚኽ የተበሳጨው ትራጃን ወደ ሮም እንዲወስዱት እና ለተራቡ አናብስት እንዲሰጥ አዝዟል። ስለሚደርስበት መከራና ስለክርስቶስ ፍቅር እንዲህ እያለ ይጸልይ ነበር: “ጌታ ሆይ በፍቅርህ ብዛት ታከብረኝ ዘንድ ፣ እንደ ሐዋርያህ ጳውሎስ በብረት ሰንሰለቶች እንድታሰር ስለ ፈቀድኽልኝ አመሰግንሃለሁ”። በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች ቅዱስ አግናጥዮስን ለማትረፍ ሲሞክሩ ከሚያገኘው መከራ እንዳያስቀሩት መልእክትን ላከላቸው። “በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ከመሄድ የተሻh ሌላ ዕድል የለኝም። ስለዚህ እለምናችኋለሁ! ለ እኔ የተዘጋጀ መሠዊያ አለና። ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኜ እቀርብ ዘንድ አሰቃዩኝ፤ ከዚህ ዓለም ወደ እግዚአብሔር የምትጠልቅ ፀሐይ መሆን አንዴት ዓይነት ክብር ነው። እርሱ ባለበት እወጣለሁና፣ እኔ ለእግዚአብሔር የመገበሪያ ስንዴ ነኝ። የክርስቶስ ንጹሕ የመሥዋዕት ኅብስት እሆን ዘንድ በአናብስቱ ጥርስ ክፈጥ ይገባኛል”። ቅዱስ አግናጥዮስ በሮም በፍላቪያን አንፊ ቴያትር ፩፻፰ ዓ.ም. በተራቡ አናብስት ተበልቶ ሰማዕት ሆኗል። በዓለ ዕረፍቱም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ይታሰባል።

ቅዱስ ፖሊካርፐስ፡ በሐውርያው ቅዱስ ዮሐንስ የተሾመው ቅዱስ ፖሊካርፐስ ትውልዱም እድገቱም ጵጵስና በተሾመበት በዚህች በሰርምኔስ ከተማ ነበር። የቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዝሙር የነበረው የሰርምኔሱ ሊቀ ጳጳስ ቡኩሎስ አስተምሮ ዲቁና ሾመው። ኋላም ቡኩሎስን በመተካት የሰርምኔስ ሊቀ ጳጳስ ሆነ። መናፍቃንን ይቃወማቸው፣ አብዝቶም ለኑፋቄያቸው መልስ ይስጥ ነበር። በተለይ በዘመኑ የነበሩት ከሀድያን መርቅያንና ቀሪንጦስን ስለ ክህደታቸው ለምዕመናን በማስተማር የእረኝነቱን ሥራ ይሠራ ነበር። በሮማውያን ወታደሮች ተይዞ፣ ስለ ክርስቶስ ክፉ እንዲናገር ቢያስገድዱትም ለቀናች ሃይማኖቱ ይጋደል ዘንድ ቤዛ ለሆነው አምላኩ መስክሮ፣ በሚነድ እሳት ተጨምሮ ሰማዕትነትን ተቀብሏል።

በቅዱሳን ሐዋርያት እግር ሥር የተተኩ በጽሑፎቻቸው፣ በሥራቸውና በተጋድሏቸው የሚታወቁት ሐዋርያውያን አበው(የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ በርናባስ፣ የኤዶም ሊቀ ጳጳስ ሴማዊው ሄኔሬስና ቅዱስ ዲዮናስዮስ) በጊዜው ለነበሩት ክርስቲያኖች በቃል፣ በጽሑፍና በተግባር እያስተማሩ በሃይማኖት አጽንተዋቸኋል። ሐዋርያዊት ተብላ የምትጠራውን ቅድስት እምነት በመረከብ ተላውያነ ሐዋርያነት(Apostolic succession) እንደነበረች በማስቀጠል፣ ከሐዋርያት ባልተለየ እምነታቸው አስረድተዋል። የእኒኽ የቅዱሳንን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት በሁላችን ይደርብን!!!

የያዕቆብ ሌሊት ይሁንልን ሲባል?

ቅዱስ ያዕቆብ የይስሐቅ ልጅ ማለትም የአባታችን የአብርሃም የልጅ ልጅ ነው። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ርብቃን አገባ፤ ርብቃም መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራትም። አባታችን ይስሐቅ ስለ ይስሐቅ ሚስት እግዚአብሔርን ለመነ፤  እግዚአብሔርም ተለመነው ርብቃም ፀነሰች። ትወልድ ዘንድ ዘመኗ በተፈፀመ ጊዜም። እነሆ በማሕፀኗ መንታ ነበሩ።
በፊትም የመጣው ቀይ ነበረ፤ ሁለተኛውም ጠጉር ለብሶ ነበር ስሙም ዔሳውተባለ። ከዚህም  በኋላ ወንድሙ ወጣ በእጁም የዔሳው ተረከዝ ይዞ ነበር ስሙም ያዕቆብ ተባለ። አባታቸው ይስሐቅ ኤሳውን ይወድ ነበር፤ እናታቸው ርብቃ ግን ያዕቆብን አስበልጣ ትወደው ነበር።

አባታቸው ይስሐቅ በሸመገለ ጊዜ በጣም አርጅቶ ነበርና ለሚወደዉ ልጁ ሊባርከው አሰበ። ነገር ግን እናታቸው ርብቃ የዔሳውን ምርቃት ለያዕቆብ በመምከር የዔሳው በረከት ተወሰደበት። ዔሳውም በጣም ተናዶ ወንድሙን ያዕቆብን ለመግደል ወሰነ፤ በረከቱን ወስዷል እና ርብቃም ታላቁ ልጇ የዔሳው ቃል ደረሳት። ታናሹም ልጇን ያዕቆብን ጠርታ “እነሆ ዔሳው ወንድምህ ሊገድልህ ፈልጓል፤ ቃሌን ስማ ተነስና ወደ ካራን ምድር፣ ወደ ወንድሜ ላባ ሂድ፤ የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድለት ጥቂት ቀናት በዛው ተቀመጥ” ብላ አሳመነችው። ዘፍ ፳፯፥፵፬-፵፭ ያዕቆብም ” እሺ “ብሎ” መንገዱን ጀመረ።

ያዕቆብም ከቤርሳቤ ወደ ካራን ሄደ፤ ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፤ ፀሐይ ጠልቃ ነበርና ከዛ አደረ። በዛም ስፍራ ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፤ ህልምንም አለመ። እነሆ መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፣ ራሱም ወደ ሰማይ ደረሰ፤ የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት፣ ይወርዱበት ነበረና እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። እንዲህም አለ : “የአብርሐም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጥሃለው፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል። እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ፣ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ። የምድርም አህዛብ ሁሉ ባንተ በዘርህም ይባረካሉ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በመትሄድበት መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለው፣ የነገርኹህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነስቶ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም  ነበር” አለ። ፈራ እንዲህም አለ “ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።” ያዕቆብም ማልዶ ተነሳ፤ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው። በበላዩም ዘይት አፈሰሰበት፤ ያዕቆብም ይንን ስፍራ “ቤቴል” ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዞያች ቦታ ስም ሎዛ ነበር። ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስዕለት ተሳለ “እግዚአብሔር ከኔ ጋራ ቢሆን፣ የምሄድበትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ ፣ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ ቤት በጤና ብመለስ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል። ለሐውልት የተከልኩትም ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል። ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለው ብሎ ቃል ገባ።” ዘፍ ፳፰
እኛም እግዚአብሔር አምላክ ከቅዱሳን መላእክቱ ከኛ ጋር እንዲያድርና ጥሩ የሰላም እንቅልፍ እንዲያስተኛን፣ ቅዱሳንንና  መላእክትን እንዲያሳየን፣ ከመጥፎ ህልም እንዲጠብቀን፣ እግዚአብሔር ከኛ ጋር እንዲሆን፣ ከመጥፎ አጋንንት እንዲጠብቀን፣ የያዕቆብ ሌሊት ይሁንልን! እንላለን። የያዕቆብ ሌሊት ይሁንልን።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ

ቤተክርስቲያናችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን
አፈ በረከት
አፈ መዐር (ማር)
አፈ ሶከር (ስኩዋር)
አፈ አፈው (ሽቱ)
ልሳነ ወርቅ
የዓለም ሁሉ መምህር
ርእሰ ሊቃውንት
ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
የሐዲስ ዳንኤል
ሊቀ ጳጳሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
መምህር፣ ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
ጥዑመ ቃል … እያለች ብዙ ታከብረዋለች ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ነገዱ ከሶርያ፣ የተወለደው በ፫፻፵፯ ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ፣ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምህርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕፃንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመኑ አስኳላም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ፲፭ ዓመቱ ነበር:: በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው:: ቅዱሱ ገና በ1፲፮ ዓመቱ ሀብት፣ ንብረት፣ ውበት፣ ክብርና ዕውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በረሀ ገባ::

ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበረሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት:: ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጓሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱሱ ኅሊናው ሳይታክት፣ ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት፣ መልእክታትና ትርጓሜያት ቢቆጠሩ ዐሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሠራ ዕድሜው ገና ለጋ፣ ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

በኋላም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው ቅዱሱ አፈ ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልአከ ሞትን ገስፆ ለዐሥር ዓመታት አቁሞታል::

     ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ድሃ፣ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: በዚህም ምክንያት የወቅቱ ንግሥት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ሁለት ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሀገር ፍሬ አፍርቶ፣ አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ፷ ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::

አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ (ግብዣ አዘጋጀ)። በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ፣ አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ፲፪ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ:: ደንግጦ “ወዴት ናችሁ ጌቶቼ” ቢላቸው “ቁስጥንጥንያ፣ ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና” አሉት:: “እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ” አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀዉት ጎዳናቸውን ቀጠሉ:: በማግስቱ በቤተ መንግሥት ውስጥ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን “ጥያቄ አለኝ” ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው::
     ‘ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ “ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ / የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?’ ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::
     “ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ኅብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::
   ‘ “እርሷ ማን ናት? በማሕፀኗ ያለውስ ማን ነው?” እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ኅብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም:: አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ፣ ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኑን አወቀ ማለት ነው’ እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ፣ በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ “አፈ። ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!” ስትል ተናገረች:: ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ “እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . .” ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል::

ሊቁ ባረፈ በ፴፭ ዓመቱ በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን፣ በግንቦት ፲፪ ቀን ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኳል:: የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን።

ፍቅርን መስጠት

ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል አለው፡፡ የክርስቲያኖች የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና፡፡ ”ነገር ግን በእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው። (፩ኛጴጥ፭÷፰) ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የመጀመሪያው ፍቅር ነው። (ገላ፭÷፳፪) በዘመናችን ግን ይህ የመንፈስ ፍሬ ከሰው ልጆች ልቡና እየጠፋ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ -መዛሙርቱ በደብረ ዘይት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ ምልክቱን ሲነግራቸው ከሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ገልጾላቸዋል፡፡ ”ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት (ማቴ ፳፬÷፲፪) የፍቅር ሸማ ከሰው ልጆች ልቡና ውስጥ ተገፍፎ እንደሚወድቅ ተነግሮናል።

“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻው ቀርቧል፤ እንግዲህ እንደ ባለአዕምሮ ዐስቡ፤ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” ይላል። (፩ኛ ጴጥ ፬÷፯) ወጥ ማጣፈጫው ጨውና ቅመም እንደሆነ ሁሉ የሰው ማጣፈጫውም ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡የፍቅር ምንጩ ክርስቶስ ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ለተራቡ ሥጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቶናልና“ ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው (ሉቃስ ፩፥፶፫) ዘለዓለማዊ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር በቃላት ከመነገርና በልቡና ከመታሰብ በላይ የሆነውን ጥልቅ ፍቅሩን የገለጠው በመስቀል ነው፡፡ በአዳም በደል ምክንያት “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን” (ኢሳ፶፫÷፮)፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን እንዳንቀር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖርበት የእኛን በደል ተሸክሞ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ይህንኑ ሲመሰክር “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት። (ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው)” ብሏል (ቅዳሴ ማርያም)፡፡
እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጦልናል፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) በማለት እርሱ እንዲሁ እንደወደደን እኛም እንዲሁ እንዋደድ ዘንድ አዞናል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ  “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል?” (፩ኛ ዮሐ ፬÷፰-፲፪) በማለት ያስተማረን።  ስለዚህ ነገ ነፍሳችን ልብሰ ጸጋዋን ተገፋ ከክርስቶስ ፊት እራቆቷን እንዳትቆም ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅር ሸማኔ ሆነን ልብሰ ጸጋ ልንሠራላት ይገባል፡፡ ድሩን ሃይማኖት ማጉን ፍቅር አድርገን የክብር ልብስ የሠራንላት እንደሆነ ሞገስ ታገኛለች፡፡

ሰው ለፍቅር ዘወትር የጋለ ብረት ምጣድ ሆኖ ከተገኘ ዕድሉ የቀዘቀዘና የፈዘዘ አይሆንበትም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽዋ ጸናጽል ሆኜኛለሁ….” (፩ኛ ቆሮ ፲፫÷፩-፰) ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን፣ ተስፋንና ፍቅርን ከዘረዘረ በኋላ የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል፡፡ ክርስቲያኖች የሚኖረን ፍቅር እንደ ፀሐይ እንጂ እንደ ጨረቃ መሆን የለበትም፡፡ ፀሐይ ሁል ጊዜ ሙሉ ነች የእኛ ፍቅር ወጥ መሆን አለበት እንጂ ጥቅም ስለምናገኝ ብቻ ሰዎችን የምናፈቅር ከሆነ ጨረቃ ሁነናል ማለት ነው፡፡ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም፣በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን”  (፩ኛ ጤሞ ፬÷፲፩-፲፪) ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን በፍቅር የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ ፍቅር ለሌሎች በመስጠት ክፉ የሚያስቡትን በፍቅር ማሸነፍ ይገባል፡፡

ዘመነ ሐዋርያውያን አበው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ ካስተማራቸው እና ወደ ዓለም ከላካቸው ከመጀመሪያዎቹ የወንጌል ገበሬዎች ሐዋርያት በኋላ የተነሡ አባቶች ነበሩ፡፡ እነዚህም አባቶች ከጌታ ሐዋርያት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውና የእነርሱ ደቀ መዛሙርት ስለነበሩ፣ በትምህርተ ሃይማኖትና በምግባርም መሳዮቻቸው ስለሆኑ ሐዋርያውያን አበው ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነርሱም ከቅዱሳን ሐዋርያት በቃልም በሥራም የተማሩ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ፣ በመንበራቸው የተተኩ ደቀ መዛሙርታቸው ናቸው፡፡ በማንኛውም የሥራ መስክ መንፈሳዊ አደራቸውን ከቅዱሳን ሐዋርያት ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን የመሩ፣ ርቱዐነ ሃይማኖት የሐዋርያት ሁለተኛ ዙር ሐዋርያት ናቸው፡፡ ዘመናቸውም ከ70 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 160 ዓ.ም. ድረስ የዘለቀ ነው:: በእርግጥ “ሐዋርያውያን አበው” የሚለው ቃል በዚያን ጊዜ አይታወቅም ነበር፡፡ ስያሜውን በስፋት መጠቀም የተጀመረው ከዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው፡፡

ከነዚህም አበው ብዙዎቹ ብዙ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ተርጉመዋል፣ በጽሑፎቻቸውም ክርስቲያኖች በደረሱባቸው ስደቶች ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ አጽናንተዋቸዋል፡፡ እንዲሁም በየጊዜው በተነሡት መናፍቃን ትምህርት እንዳይታለሉ በማለት ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በሥርዓት ለመምራት የሚያስችሏቸውን ጽሑፎች በቅዱስ መጽሐፍ ቃል ላይ ተመሥርተው ጽፈዋል፡፡ መጽሐፈ ዲድስቅልያ፣ መልእክተ በርናባስ፣ መልእክታተ ቀሌምንጦስና ራእየ ሔርማ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም “ቀደምት የክርስትና ጸሐትት” (Early Christian Writers) ይባላሉ። (GEOFFREY PARRINDER, A CONCISE ENCYCLOPEDIA OF CHRISTIANITY, P.26; GEORGE W. GRUBE, THE COMPLETE BOOK OF ORTHODOXY, P. 37)

እነዚህ አበው ከቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ከቤተ አሕዛብም የተገኙ ናቸው፡፡ በሐዋርያት ጊዜ እነርሱን እየረዱ ኖረዋል፡፡ ባስተማሯቸውም ትምህርት ጸንተው በማጽናታቸው በዐላውያን ነገሥታት ሰይፍ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ ሐዋርያውያን አበው ከሚባሉት መካከል ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ ፖሊካርፐስ፣ ሄርማስ፣ ፓፒያስና አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ አባቶች ለቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነትን እስከ መቀበል ደርሰው ከሠሩትና ካስተማሩት ይልቅ ከሞቱ በኋላም ሕያው በሆነው ስማቸውና ትምህርታቸው እየሠሩ ያለው ሥራ ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርታቸው መናፍቃንን እያሳፈረ አጋንንትን እያስደነበረ ነውና፡፡ ሊቃውንቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በአነርሱ አስትንፋስ (ትምህርት) ነውና፡፡
እነርሱን መሆን ባይቻልም ቤተ ክርስቲያንም የእነዚህን ቅዱሳን አበው ብሔረ ሙላዳቸውን፣ ጥንተ ነገዳቸውን፣ የገድላቸውን ጽንአትና የሥነ ጽሑፋቸውን ብስለት መዝግባ አስቀምጣልናለች።

አብዛኛዎቹ የሐዋርያውያን አበው ድርሳናት የክርስቶስ ምጽአት ላይ ያተከሩ ሲሆን ከዚህም የተነሣ በመጀመሪያው እና ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የነበሩት አበው ክርስቶስ በቶሎ ይመጣል የሚል ጠንካራ አመለካከት (Eschatological attitude) ስለነበራቸው ብዙ ድርሳን የማዘጋጀት ዓላማ አልነበራቸውም፡፡ በጻፏቸው ጥቂት ድርሳኖችም ላይ ነገረ ምጽአታዊ ትምህርቶች በስፋት ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡

እነዚህ ሐዋርያውያን አበው በተለያየ አገር የኖሩ ይሁኑ እንጂ በመልእክቶቻቸው ያንጸባረቁት አስተምህሮት ግን ተመሳሳይ እና ከአንድ ምንጭ የተቀዳ ነው:: ይህም ነገር የቤተ ክርስቲያንን ኩላዊትነት (Catholicity) የሚያሳይ ቀዳማዊ ማስረጃ ነው፡፡

ምንጭ:
፩. አባቶችህን እወቅ (ዲ/ን አቤል ካሳሁን) ፳፻፲፪ ዓ.ም.
፪. ነገረ ቅዱሳን (አሉላ ጥላሁን እና ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ) 2014 ዓ.ም

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

   በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም::ስለዚህም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አባት ሊቀ ሊቃውንት፣ ርእሰ ሊቃውንት፣ የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን) ሐኪም (Doctor of the Church)፣ ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች::

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በ300 አካባቢ) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር:: ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም “ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ!” ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ:: ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት:: ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::

     ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ፣ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው:: ከዚህበኋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) ፳ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ፵፰ ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በረሃ ሲያግዙት በስደት ከ፲፭ ዓመታት በላይ አሳልፏል::

አርዮሳዊ መናፍቅ ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ)  ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም የሚያሳድድ ሆነ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር:: በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በረሃ አግዞ፣ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሾሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል፣ ቅዱሱን ለስድርት ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው::
     ሁለት አማራጮችን አቅርቦ “ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምእመናን) መልሰኝ” አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

     ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ:: ቅ. ሚካኤልና ቅ.ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፉ፣ ሌሎች መላእክት እየመገቡት  እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰዉት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል።

     በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው:: ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ፣ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ፫፻፸ዎቹ ዓ/ም አካባቢ አርፏል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የንዋየ ቅድሳት ምንነት፣ አዘገጃጀትና አጠቃቀም

ንዋየ ቅድሳት ከሁለት ቃላት የወጣ ሲሆን
ንዋይ:- ማለት ቅርስ ንብረት ጥሬ ዕቃ ማለት ነው።
ቅድሳት:- ማለት ደግሞ ቅድስና ክብር ንጹሕ ጸጋ ያላቸው መሆናቸውን ያመለክታል። ንዋየ ቅድሳት ከተመረጡ የተመረጠ ከተለዩ የተለየ ለዘለዓለሙ ስሙ የሚኖርበት ምርጥ ዕቃ ማለት ነው። ይህም ስለሆነ ነው ዕቃው ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ተባርኮና ተጸልዮበት የሚገባው። ከቡራኬ በኋላ ግን ተራ ዕቃ የነበረው ንዋየ ቅድሳት ሆኖ ለቤተመቅደስ የአምልኮ ሥርዓት መፈጸሚያ የክብር ዕቃ በመሆን ለአገልግሎት ይውላል። ንዋየ ቅድሳት በአጠቃላይ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች የሚጠሩበት ስም ነው።

የንዋየ ቅድሳት አዘገጃጀት :- ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ የመገልገያ ዕቃዎችን ለማዘጋጀት በቅድሚያ የሚሠሩበትን ነገር ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል። “ከንዋየ ቅድሳት ሁሉ የከበረ ታቦት ነው። ታቦት ደግሞ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ከማይነቅዝ እንጨት እንዲቀረጽ ታዘዘ።” ዘጸ.፳፭÷፩-፱ እንግዲ ንዋየ ቅድሳትን በምናዘጋጅ ጊዜ ከማይነቅዝና ከጠንካራ ነገር መሆን ይኖርበታል።

የንዋየ ቅድሳት አጠቃቀም:- ንዋየ ቅድሳት ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር የአምልኮት ሥርዓት በምናከናውንበት ጊዜ ሁሉ የምንገለገልባቸው የተቀደሱ ዕቃዎች ናቸው።ንዋየ ቅድሳት ለአምላካችን እግዚአብሔር የአምልኮ ሥርዓት በምናከናውንበት ጊዜ ሁሉ  ምንገለገልባቸው የተቀደሱ ዕቃዎች ናቸው፡፡ ስለሆኑም ስንጠቀምባቸው ለመንፈሳዊ አገልግሎት መሆን አለበት። 

በንዋየ ቅድሳት ላይ የሚደረግ ጸሎት:- በንዋየ ቅድሳት ላይ ሁሉ ጸሎት ማድረግ ተገቢ ነው፤ ለዚህም ካህናት “እግዚአብሔር አምላክነ ኄር ወመሐሪ ወቅዱስ …..”  የሚለውን ጸሎት ይጸልያሉ። ጸሎት ላዕለ ማሕፈዳት ፣ ጸሎት ላዕለ ጻሕል ፣ ጸሎት ላዕለ ጽዋዕ ፣ ጸሎት ላዕለ ዕርፈ መስቀል፣ ጸሎት ላዕለ መሶበ ዘወርቅ የሚባሉ ጸሎቶች አሉ እነርሱን ይጸልያሉ። ንዋያቱ በተደረገው ጸሎት ይከብራሉ።

የንዋየ ቅድሳት ምሥጢር :- ምሥጢር ማለት ሰው ሳያውቀው እግዚአብሔር ብቻ በሚያውቀው መንገድ የሚከናወን ረቂቅ መንፈሳዊ ሥራ ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በተመላለሰበት ጊዜ ሲያስተምር በምሳሌ ነበር። ይኸውም ሁሉም እንደሚገባው በሚያውቀው ነገር እየመሰለ ያስተምራል። ልክ እንደዚ ሁሉ ንዋየ ቅድሳትም በምሥጢር የከበሩ በምሳሌ የተነገሩ ናቸው።

ዋቢ መጽሐፍ :-ንዋየ ቅድሳት አዘገጃጀት፣ አጠቃቀም እና ምሥጢር (በሚሊዮን በለጠ አሰፋ)

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ

‎ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ከነገሡ ፲፩ ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ፪ኛ ነው:: እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው:: ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው::

    እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጆሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር:: ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች:: ሕፃኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ “ነአኩቶ” እያለ ሲዞር ሰማችው::  እዚያው ላይም ‘ነአኩቶ ለአብ’ (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት:: ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግሥቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በረሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕፃን ወደ አጎቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ::

     የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከእርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕፃኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ:: በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና:: ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም ዕድሜው 30 ደረሰ::

    በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ:: ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት:: ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ:: በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው:: ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር፣ ቅዳሴ ሲቀድስ፣ በጾም ይውላል:: ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቁዋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል:: ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል:: ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል:: እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል:: በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ፤ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር:: እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና::

     ከተጋድሎው ጎን ለጐጎ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር:: በተለይ በ፲፪፻፲፩ ዓ.ም.  አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት:: እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግሥቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት፣ ይቀድስባትም ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ:: እርሱም “ወገኖቼ! ከወዴት መወጣችሁ?” ቢላቸው “መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን” ሲሉ መለሱለት:: በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ “አሽተን (አሸተን) ማርያም” ስትባል ትኖራለች::

     ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠው በ፴ ዓመቱ ነው:: ለ፵ ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ ፸ ዓመት ሞላው:: በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ሰላምታንም ሰጠው::

     “ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ፵ ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም፤ ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና:: የሚያከብርህን አከብረዋለሁ:: ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ” አለው:: ቀጥሎም “ይህች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር” አለው:: እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጸበል ይንጠበጠባል:: ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን:: ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና::

     ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደዉታል:: የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ኅዳር ፩ ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ፫ ነው ይላሉ:: በዙፋኑም ላይ የአጎቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።

ይህ ቅዱስ ንጉሥ ሆኖ ሳለ ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያሳየ ንጹሕና ድንግል  ጻድቅ ነው። የጦር መሪ ሳለ በእጁ ደም ያልፈሰሰ ፍቅር ማለት ለእርሱ ክርስቶስ ብቻ የሆነ ነበር። የሃገር መሪ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደመሆኑ እጅግ ጊዜው የተጣበበ ቢሆንም  ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም::

እኛ ቤተ ክርስቲያንን “በሐኪ” ለማለት (ለመሳለም) እንኳ ‘ጊዜ የለኝም’ ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል፣ ያንጽ፣ በክህነቱ ያገለግል፣ በማዕጠንት ያጥን፣ ለረጅም ሰዓትም ይጸልይና በቀኝና በግራ  ጦር እየተከለ ይሰግድ ነበር። ታድያ ይህ ቅዱስ ለእኛ እንደምን ያለ ተሞክሮ በጎ አርአያ ነው?

አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ ንጉሥ ጸሎት ይማረን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በረሃ ገቡ::
በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::

ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ “አጥምቀው!” አለችው:: ወደ በረሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲልም ሕጻኑ ተነስቶ፣ እጆቹንም ዘርግቶ: “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕፃኑ ወላጆች “ለልጃችን ስም አውጣልን” ቢሉት “ቡላ” ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ  “ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ፣ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን” ተብሎ እንደተጻፈ ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

 የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገዉት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነት የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾምና ሲጸልይ ክፉ መኮንን “ለጣዖት ስገዱ!” እያለ መጣ:: በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ሰማዕት ሆኗል::

ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና “እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል!” ሲል ጌታንን ለመነ:: ጌታችን ግን “ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ!” አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ፣ ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በረሃ ውስጥ አኖረው።

 አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል፣ ፊቱን በጥፊ ይመታል፣ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፣ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል:: በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጾሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር:: የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሣ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን!” አለው::አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎይን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተነጋገረ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከዐሥር ጊዜ በላይ ሞቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ::

ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ “ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ “አምላከ አቢብ ማረኝ” ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኩዋ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ” ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ::